‹‹ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው›› አቡነ ጳውሎስ
ሪፖርተር ጋዜጣ፤ሰኔ 10/2012 -ትናንት በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በ‹‹ግብረሰዶምና ተያያዥ ማኅበራዊ ቀውሶች›› ላይ ለመነጋገር በተጠራው አገራዊ ኮንፈረንስ የተገኙት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፓርላማ አባላት፣ ወጣቶችና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ‹‹ግብረሰዶምንና ግብረሰዶም የሚያስፋፉ ምዕራባዊያንን›› አወገዙ፡፡ በዚሁ ታሪካዊና አንገብጋቢ በተሰኘው አገራዊ ኮንፈረንስ ላይ ከ2,000 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ አምስቱ ዋና ዋና የሃይማኖት ተቋማት የኦርቶዶክት ተዋህዶ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የወንጌላዊት መካነ ኢየሱስና የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ያወጡትን የግብረሰዶማዊነት የተቃውሞ መግለጫ በአንድ ድምፅ እንደግፋለን ብለዋል፡፡ ግብረሰዶማዊነትን ካልተቀበላችሁ በማለት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ የሚያነሱና ዕርዳታ እንከለክላለን ለሚሉ የምዕራብ አገሮችም ‹‹ዕርዳታቸው በአፍንጫችን ይውጣ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የሃይማኖት ተቋማትን በሙሉ ወክለው ጉባዔውን በፀሎት የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ሕግ ሳይጻፍ ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ትውውቅ ነበራቸው፤ የዛሬ ሳይንቲስቶችም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆንዋን ይናገራሉ፤›› በማለት በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች በሙሉ እርስ በርስ ተረጋግጠዋል፤ ብቸኛ ነፃ አገር ኢትዮጵያ ነች ብለዋል፡፡ ‹‹አሁንም የተረገጡትና የማንነት ቀውስ ያለባቸው ወገኖች ተናገሩ ብላ የምትሰማ አይደለችም፡፡ ባህላችን አልተለወጠም፣ ታሪካችን አልተቀነሰም፣ ማንነታችን አልተበረዘም፤ እንዲሁ ዝም ብለን የምንለወጥ አይደለንም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
