ቤተ ጳውሎስ ረቡዕ ግንቦት 29 2004 ዓ.ም.
ለብዙ ጊዜ ዱርዬ ማለት ቀጥተኛ
ትርጉሙን፣ ገላጭ ፍቺውን አላውቀውም ነበር፡፡ ዱርዬ ማለት የቆሸሸ ልብስ የለበሰ፣ ሥራ አጥቶ ድንጋይ ላይ የተቀመጠ፣ ለማኅበረሰቡ
ስጋት የሆነ ብለን እንፈታው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያማረ ልብስ የለበሱ፣ ለፕሮቶኮላቸው የሚጠነቀቁ፣ ብዙ ፋብሪካ የተከሉ፣ ብዙ
ሥልጣን የተሸከሙ፣ በጌትነት ወንበር ላይ የሚቀመጡ፣ በክብር አልባሳት የተንቆጠቆጡ፣ ወደ ስማቸው ቶሎ የማይደረስ ብዙ ቅጽል ያላቸው፣
ማኅበረሰቡ ተስፋችን ባልቴቶቹ ቀባሪያችን የሚሏቸው … ብዙ ዱርዬዎች አሉ፡፡ ትልቁ ችግራችን ሰውን በልብስ፣ ሰውን በንግግር ችሎታ፣
ሰውን በገንዘብ፣ ሰውን በመዐርግ፣ … መለካታችን ነው፡፡ ሰው በዲግሪ፣ ሰው በኒሻን አይለካም፡፡ የሰው መለኪያው የኑሮ ምርጫው
ወይም ቀጥተኛነቱ ነው፡፡ ብዙ የዓለም ክብሮች የታሪክ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ በአጋጣሚ ግን ቅን መሆን አይቻልም፡፡ ቅንነት ወይም
እውነተኛነት ምርጫ ነው፡፡
ዱርዬ ማለት ምን ማለት ነው? አሁንም ፍችውን ማሰስ አለብን፡፡
ዱርዬ ሁሉም ልብስ ልክ የሚሆነው ብዬ በራሴ መዝገበ ቃላት ፈትቼዋለሁ፡፡ ሲዘፍን እንደርሱ ሲዘምር እንደርሱ የሌለ፣ ሲጾም እንደርሱ
ሲበላ እንደርሱ የሌለ፣ ሃይማኖታዊ ልብስ ሲለብስ እንደርሱ ሲዘንጥ እንደርሱ የሌለ፣ … ሁሉም ልብስ ልክክ የሚልበት፣ ጎበዝ ተዋናይ
እርሱ ዱርዬ ይባላል፡፡ ይህን ፍቺ ያገኘሁት ተጨንቄ ሳይሆን ዓይቼ ነው፡፡ ከስድስት ወር በፊት በአንድ ሠርግ ላይ ተገኝቼ ከሚዜዎቹ
አንዱ የማውቀው ሰው ነበር፡፡ ይህ ወንድም ጠበል ሲጠጣ እንደ እርሱ ሥርዓት ያለው ዓይቼ አላውቅም፡፡ ውስኪ ሲጠጣም እንደ እርሱ
ጎዝጉዞ የሚጠጣ ያለ አይመስልም፡፡ ታዲያ እዚያ ሠርግ ላይ ትግርኛውን ሲጨፍር፣ ጉራጊኛውን ሲጨፍር ያደጉበት እንኳ እንደ እርሱ
አልተዋሐዳቸውም ብል ሐሰት አይደለም፡፡ ታዲያ ልቤ በድንገት፡- “ወይ ዱርዬነት” አለ፡፡ ወዲያው ከሠርጉ ጫጫታ በአሳብ ወጣሁና
ዱርዬ ማለት ሁሉም ነገር ልኩ የሆነ፣ ትክክለኛ ማንነቱ ግን ኃጢአት የሆነ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡