የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት
ይቻለኛል? ………ሕዝቤ እውቀት በማጣት ጠፍተዋል»
አለማወቅ የአእምሮ እውርነት ነው። የአእምሮ እውርነት
ደግሞ ከምንም በላይ ይከፋል። ሰው በአእምሮ እውርነት በሽታ ከተጠቃ ሰው ሳይሆን ለማዳ እንስሳ ይሆናል። እግዚአብሔር ደግሞ ሰው
ያለውን ጉድለት እንዲሞላ አድርጎ ፈጠረው እንጂ እንደ ለማዳ እንስሳ አንዴ በተሞላለት አእምሮ እድሜውን ሁሉ እንዲኖር አድርጎ አልሰራውም።
ህጻናት ሳለን እንደ ህጻናት እናስባለን፤ እያደግን
ስንመጣም ጤነኞች ከሆንን ከእድገታችን ጋር ተመጣጣኝ እውቀት በአእምሮአችን ይሞላል። የቅድሚያውን እውቀት ከቅርብ ወላጅ ከእናታችን
እናገኛለን። ከወላጅ አባትና ከአጠቃላይ ቤተሰቦቻችን መረዳቶቻችን ይዳብራሉ። ግንኙነቶቻችን ከቤተሰብ አልፈው ወደ ጎረቤት ሲሻገሩ
እንደዚያው እውቀቶቻችንም እየሰፉና እያደጉ ይመጣሉ።
መደበኛም ይሁን መደበኛ ባልሆኑ የእውቀት ተቋማት
ስንገባ ደግሞ እውቀታችን ከማለዳዋ ፀሐይ የብርሃን ጸዳል ይበልጥ ሰፍቶ ወጋገኑ ሁሉን እንደሚገልጠው የረፋድ ላይ ብርሃን ሆኖ ለሌላውም
መታየት ይጀምራል። እንደዚያ፤ እንደዚያ እያለ ከረፋዱ ወደ ቀትር፤ ከተሲዓት፤ ሰርክና እርበት ድረስ እውቀታችን ከሙላት ወደ ሙላት ይሻጋገራል።
ይህ ለሰው እንጂ ለለማዳ እንስሳ የተሰጠ ጸጋ አይደለም። ስለዚህ የሰው ልጅ ክቡር ነው፤ የሚያሰኘው ለማወቅ የተሰራ አእምሮ ስላለው
ነው።
ይሁን እንጂ ሰው ለማወቅ መሪ ያስፈልገዋል። ያለ መሪ ምንም ነው። እግዚአብሔር
ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ከመፍጠሩ በፊት የሚኖርበትን ቦታ አስቀድሞ አዘጋጅቶለታል። ለኑሮው ጉድለት ረዳት ሰጥቶታል። በሚኖርበት
ሥፍራ ራሱን እንዲያበዛ፤ የሚኖርበትን ቦታ ሁሉ እንዲገዛ አድርጎታል። ይህ ሁሉ የሌለውን እውቀት ምሉዕ ለማድረግ ከእግዚአብሔር
የተሰጠው ምሪት መሆኑን ያሳየናል።
ዛሬም እንደዚሁ ነን። ምሪት ያስፈልገናል። በመግቢያችን
ላይ እንዳስቀመጥነው ከቤተሰብ፤ ከማኅበረሰብ፤ መደበኛና መደበኛ ካልሆነ የእውቀት ስፍራ ወደእውቀት የሚመራን የሰው ምሪት የግድ
ይሆናል ማለት ነው። ለዚህም ይመስላል፤«ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው» የሚባለው።