ምንጭ፤ አባ ሰላማ ብሎግ፤ Friday, February 24, 2012
እኔ መንገድ እውነት ሕይወትም ነኝ በኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም [መጽሐፍ ቅዱስ ዮሐ 14፥6]
ታምረ ማርያም የተባለው ጉደኛ መጽሐፍ ድንግል ማርያምን ያከበረ የሚመስል ነገር ግን ስድብ እና ክህደት የሞላበት መጽሐፍ መሆኑን ደጋግመን ለማሳየት ሞክረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ 1400 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ንጉሥ በዘርዓ ያዕቆብ የተደረሰ ሲሆን በወቅቱ የነበሩ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት እና ምእመናን ይህ ልዩ ወንጌል ከሐዋርያት ትምህርት የወጣ ስለሆነ አንቀበለውም በማለታቸው፣ እስከ አንገታቸው በጉድጓድ ተቀብረው በጭንቅላታቸው ላይ የፈረስና የከብት መንጋ እንደተነዳባቸው ምላሳቸውንና አፍንጫቸውን እንደተቆረጡ እራሱ ታምረ ማርያም ይመሰክራል። [ታምር 24 እና 25 ገጽ 112- 121።]ታምረ ማርያምን ቁጭ ብለን በማስተዋል ብንመረምረው መጽሐፍ ቅዱስን ለመቃወም የክርስትናን ትምህርት ለመበረዝ በጠላት ሆን ተብሎ የተቀመመ ይመስላል። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ እስራኤላዊ ነኝ ስለሚል ምን አልባት አይሁዶች መሲሐዊ እምነታችንን ለማጠፋት የፈጸሙት ሴራ ይሆን? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ዘራ ያዕቆብ አይሁዳዊ ነኝ እያለ ይመካ ነበር፤ ከዚያም አልፎ የይሁዳ ነገድ ነኝ ይል ነበር። አባ እስጢፋኖስ ግን ኢትዮጵያዊ ነህ አትዋሽ ከአይሁዳዊነት ይልቅ ክርስቲያን መሆን ይበልጣልና በዚህ አትመካ በማለት እንደተከራከረው ገድለ እስጢፋኖስ ይናገራል [በሕግ አምላክ በፕሮፌሰር ጌታቸው]
መጽሐፉን ዛሬ መመርመር ለምን አስፈለገ? የሚል ጠያቂ ሊኖር ይችላል፣ መልሳችን አብዛኛው የዋሕ ምእመን እምነቱን የመሠረተው በታምረ ማርያም ላይ ነው የሚል ሥጋት ስላለን ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ታምሯን ሰምቼ ልምጣ እንጂ ወንጌል ሰምቼ ልምጣ ብሎ አያስብም፣ እሑድ እሑድ ታምር የሚያነብ እንጂ ወንጌል ለማስተማር የሚያስብ ቄስም የለንም። 400 000 ካህናት እንዳላት የሚነገርላት ቤተ ክርስቲያናችን ታምረ ማርያም አንብቦ ከማሳለም ያላፈ አገልግሎት የሚሰጥ አይደለም። በተለይም ታምሯን ሰምቶ የሄደ ሥጋውና ደሙን እንደተቀበለ ይቆጠርለታል የሚለው ባዕድ ወንጌል ብዙ ሕዝብ ወደ ስጋውና ደሙ እንዳይደርስ ስላደረገው ይህም የስሕተት ትምህርቶች ውጤት ሆኖ ስላገኘነው፣ ሲኖዶሱ ከተኛበት እስኪነቃ ድረስ ጩኸታችንን አናቆምም። ወደ ተነሳንበት እርስ እንመለስ፥
መጽሐፉ “ቅምር” በሚባል አገር አንድ ሰው ነበር በማለት ታሪኩን ይጀምራል
“ወኢየበልዕ እክለ ወኢ ሥጋ ላሕም ወኢ ካልአ እንሥሣ አላ ይበልዕ ሥጋ ሰብእ”
ትርጉም እህል፥ የላም፥ ሥጋ የሌሎችንም እንሥሳ ሥጋ አይበላም ነበር የሰው ሥጋ ይበላ ነበር እንጂ” ቁ 68።

