Tuesday, March 13, 2012

የሚያረክሰው የትኛው ነው?

አሜሪካ በሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ንዑስ ክፍል፣ በነዲ/ን አሐዱ አስረስ፣ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ በነቀሲስ በላቸው፣ በነሊቀ ኅሩያን ከፈለኝ ወዘተ ሰዎች የሚመራ ጉባዔ አካሂዶ ነበር። ጉባዔው በዋናነት የሚያጠነጥነው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አውግዛቸዋለች በሚሏቸው ተሃድሶአውያን ላይ እና በአሜሪካ ስደተኛው ሲኖዶስ የሚባለው አካል የምንፍቅና ደረጃው ምን እንደሚመስል ለማጋለጥ የተካሄደ ነበር።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አባ ወ/ትንሣዔ የተባሉትን አባት መናፍቅና ተሀድሶ ናቸው የሚል ዘመቻም አብሮ ተሰርቷል። ለተሃድሶነታቸው በምክንያትነት የቀረበው አባ ወ/ትንሳዔ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሰውን የሚያረክሰው አሳማ መብላት፤ አህያ መብላት ወይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የልምድ አስተምህሮ ሸኮናው ድፍን ወይም የማያመሰኳ ርኩስ ነው የሚለው ሳይሆን «ከሰው አፍ የሚወጣ ነው የሚያረክሰው» ብለው ስላስተማሩ ተሃድሶና መናፍቅ  ተብለው ተፈርጀዋል።
እስኪ ይህንን ቪዲዮ ያዳምጡ።  በጥራት ለማዳመጥ ድምጹን ይቀንሱ!




እነዚህ ሰዎች የጠሉትን ለመምታት እንዲህ ዓይነት የተቀናጀ ዘመቻ ሲሰሩ ለሚያቀርቧቸው ዘመቻዎች አስረጂ የሚሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጣቸው ምንድነው? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። በዲያቆን በጋሻው ላይ ዘመቻ የሰሩ ሰዎች ሁሉ ማኅበሩ ከጀርባ ሆኖ ግፋ በለው! ውረድ በለው! በሚል ጦረኝነት ቢነዳቸውም ከወረዱበት ዘብጥያ ሊታደጋቸው ግን አልቻለም። እንደዚሁ ሁሉ አባ ወ/ትንሳዔ መናፍቅና ተሃድሶ ናቸው ብሎ በጉባዔ ዘመቻ በመስራትና ቪዲዮ በማጠናቀር «በዩቱብ» የለቀቀባቸው እውን አሳማ ወይም አህያ የሚበላ ቢኖር የሚኮነን ሆኖ ነው? ረክሷል ማለት ነው?

እውነታው ግን እነዚህ እንስሳት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ የማይበሉት በአዲስ ኪዳን ርኩስ ናቸው የሚል ትምህርት ስላለ ያንን ለመፈጸም ሳይሆን የኦሪትን ሥርዓት ስትከተል የቆየችና በኦሪቱ የተከለከሉትን እንስሳት ሳትበላ የቆየች ስለሆነ ወደአዲሱ ኪዳን ስትገባ የቀደመው ሥርዓቷን ይዛ በመቀጠሏ ብቻ ነው።
ያልተለመደውን ነገር እንዲለመድ ለማድረግ ማስተማር የወንጌል ወግ አይደለምና ቤተክርስቲያኗ ምእመናኗን እንዲለማመድ አለማድረጓ የሚያስነቅፋት አይደለም። ደግሞም እየበሉ የቆዩ ወይም መብላት የፈለጉትን ትረክሳላችሁ ወይም ትኰነናላችሁ አትልም።
ጽድቅ በመብላት ወይም ባለመብላት አይደለምና።
የሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ሊቁ አቡነ ጎርጐርዮስ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ 180 እና 181 ላይ ከጻፉት ጽሁፍ ይህንን ለአስረጂነት አቅርበናል።


እናስ ታዲያ! አባ ወ/ትንሳዔ  አሳማ ወይም ሌላ እንስሳ የሚበላ አይረክስም፤ የሚያረክሰው ይህንን የሚባለውን ሰው አሳማ ውሻ ብለን ስንሰድበው ነው ማለታቸውን ነቅፎ ተሃድሶና መናፍቅ ናቸው የሚለው የአሜሪካው የማኅበረ ቅዱሳን ክንፍ በምን እውቀት ላይ ተመስርቶ ነው? ተሃድሶ ናቸው ተብለው ከታወጀባቸው ጋር አባ ወ/ትንሳዔ ደባልቀው  እንዲህ ዓይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ ለምን? ማነው? ማኅበረ ቅዱሳንን ከእውቀት ባዶ በሆነ  ዘመቻ እንዲሰማራ የላከው? መናፍቁ ማነው? የወንጌል ቃልን የሚቃወም ወይስ የወንጌል ቃልን የሚያስተምር?
ሊቁ አቡነ ጎርጐርዮስ ግን የቆየውን የቤተክርስቲያን ሕግ በማጣቀስ እንዲህ ሲሉ ያስተምሩናል።

 ማኅበረ ቅዱሳኖችና ተባባሪዎቻቸው ነጠላ ከመልበስ፤ ከበሮ ከመደለቅና ገንዘብ ከማግበስበስ በፊት ወንጌል ተማሩ!!
በአንድ በኩል ብጹእ አቡነ ጎርጎሪዎስ አባታችን ናቸው ትላላችሁ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ከእሳቸው የወንጌል ቃል አስተምህሮ በተጻራሪ ትቆማላችሁ። ከቶ እናንተ ምንድናችሁ?
ቻይና ሀገር የማይበላ የእንስሳ ዝርያ የለም። ታዲያ የቻይና ክርስቲያን የሰማይ ፍርዱ በሲኦል ነው ማለት ነው? ያለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይልቁንም ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት በስተቀር በዚህ ዓለም ላይ እግዚአብሔር ለጽድቅ ያኖረው ፍጥረት የለም ማለት ነው?
 ምን ዓይነት ተመጻዳቂ የተረት ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ዘመተባት? ዝምታህስ እስከመቼ ይሆን?

Monday, March 12, 2012

አቡነ ገብርኤል "የተሰደደ የለም" ያሉት የሀዋሳ ሕዝብ፣ ታላቅና ደማቅ መንፈሳዊ ጉባዔ አካሄደ

ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር የለዩት ምዕመናን አሁንም ከአሳዳጆቻቸው ጋር ተፋጠዋል

በአቡነ ገብርኤል የመልካም አስተዳደር ብልሹነት ተማረውና ተቀጥቅጠው በዱላ ኃይል ከሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣  ከደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እና ከደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቅጥር ግቢ የተባረሩት ምዕመናን የራሳቸውን ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ ማካሄዳቸው ዘጋቢዎቻችን አስታወቁ፡፡
 ዘጋቢዎቻችን በሥፍራው ተገኝተው እንዳረጋገጡት እነዚህ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት፣ ልዩ ልዩ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አገልጋዮችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አቡነ ገብርኤል ከ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አሥር ከማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች እና ኃላፊነታቸውን ከዘነጉ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ተከታታይና ኢሰብዓዊ ድብደባ፣ እሥራትና እንግልት ስላበዙባቸው ተማረው መውጣታቸው ታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የተሰደደው ሕዝብ ተበታትኖ ወደየቤቱ ከመግባት ይልቅ እየተሰባሰበ በግለሰቦች መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወንጌል በመከታተል ላይ ሲሆን በአደረጃጀት እየጠነከረ በመምጣቱ እነ አቡነ ገብርኤል እንደስጋት እንደሚያዩት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በእነ አቡነ ገብርኤል ወገን ያለው አሳዳጅ ኃይል ግፉአኑን "ተሀድሶዎች" ናቸው፣ "መናፍቃን" ናቸው በማለት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ የሐሰት ወሬ በማስተላለፍ ላይ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን አሳዳጆቹ ወደ ፍትሕና ፀጥታ አካላት እንዲሁም ወደ ክልል መስተዳድር እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዘወትር እግራቸው እስኪቀጥን ድረስ በመመላለስ እንዲያዙላቸው፣ እንዲታገዱላቸውና እንዲታሠሩላቸው በመወተወት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡