እግዚአብሔር ስንት ኪዳን ሰጠ?
“..........አዎ! እግዚአብሔር ልጆቹ ይጠቀሙ ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቅዱሳኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ከእነዚህም ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ኖኅ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት እንዲሁም በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ የተሰጠ ሐዲስ ኪዳን ተጠቃሾች ናቸው ….....”
( የአንድ አድርገን ብሎግ አስተምህሮ)
«.....ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር»ዕብ ፰፣፯
« ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው»ዕብ ፱፣፲፭
(መጽሐፍ ቅዱስ)
አንድ አድርገን ብሎግ የአዲስ ኪዳኑን የኢየሱስ ክርስቶስን ኪዳንና ሌሎችንም ዘርዝሮ የኪዳነ ምሕረትን ጨምሮ ብዙ፣ ብዙ ለመዳን የሚሆኑ ኪዳኖች እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እንደሰጠ ያለምንም መሸማቀቅ በኩራት ዘግቦልን ይገኛል። ስህተቱን የከፋ የሚያደርገው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው «ኪዳን» ሁለት ብቻ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረውን በመካድና በዚህ የክህደት አስተምህሮ ውስጥ ሌሎችንም ይዞ ወደጥፋት ለማምራት ማወጁ ነው።
አንድ አድርገን ብሎግ ክህደቱን ለማስፋፋት «ኪዳነ አዳም፣ኪዳነ ኖኅ፣ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ሐዲስ ኪዳን» እግዚአብሔር ለእኛ ጥቅም የሰጠን ኪዳኖች ናቸው ሲል ያለምንም ሀፍረት ጽፏል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር የሰጣቸው ኪዳኖች ሁለት ብቻ መሆናቸውን በግልጽ አስቀምጧል። «ነቀፋ የተገኘበት ፊተኛውና የዘለዓለም ርስት የሚሆን አዲስ ኪዳን » ናቸው በማለት።
«.....ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር»ዕብ ፰፣፯
« « ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው»ዕብ ፱፣፲፭
«ፊተኛው ወይም ብሉይ ኪዳን»
እግዚአብሔር ይህንን ኪዳን የሰጠው ለሰው ልጆች ሁሉ ሳይሆን እርሱ ለመረጣቸው ሕዝቦች ብቻ ነበር። ይኸውም ከጥፋት ውሃ በኋላ የአባታቸውን የኖኅን ገመና የሸፈነውና፣ የበረከት ልጅ ሆኖ የተመረቀ በምድር ቡሩክነት የተመረጠው የሴም ዘር ነበር። «እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን»፱፣፳፮ የተመረጡትና የበረከት ምርቃት የወረደላቸው ሴማውያን የእግዚአብሔር«ሕዝቦች» ሲባሉ ከነዓናውያን ግን «አሕዛብ» ተብለው መቅረታቸውንና የመጀመሪያውንም ቃልኪዳን እግዚአብሔር የሰጠው ለእነዚህ ሴማውያን እስራኤል ብቻ እንደሆነ ከቅዱሱ መጽሐፋችን ላይ እናነባለን። የሴም የትውልድ ሐረግ እስከአብርሃም ድረስ ያለውን ከዘፍጥረት ፲፩ ጀምሮ እናገኘዋለን። እንግዲህ እነዚህ ሕዝቦች ናቸው ከአሕዛብ የተለዩ ተብለው በእግዚአብሔር የተመረጡት።
«አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ»ዘጸ ፲፱፣፭
«ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል» ዘዳ ፳፯፣፱
እነዚህን ሕዝቦች እግዚአብሔር መርጧቸዋል። ከእነዚህ ምርጦቹ ጋር ለእርሱ ቅድስና በሚሆን መልኩ የመሪና የተመሪ ሕግ የሆነውን ውል በሙሴ በኩል በኮሬብ ተራራ ላይ ሰጥቷል። ይህ ህዝብ በዚህ ህግ እየተመራ ኖሯል። ህጉን ሲጥሱ እየቀጣቸው፣ ሕጉን ሲጠብቁ እየባረካቸው እንደኖሩ ሙሉ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ በሰፊው ይነግረናል። ይህ የመጀመሪያው ኪዳን መሆኑ ነው። ለሕዝብና ለአሕዛብ የሚሆን ሌላ ሕግ እስኪመጣ ድረስ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ጋር ቃል የተገባባበት የቀደመው ኪዳን ስፍራውም ኮሬብ ነው። ኪዳኑንም በ፲ ቱ ሕግጋት ሥር የሚጸና ልዩ ልዩ አፈጻጸሞችን የያዘ መተዳደሪያ ውል ነበር።