Wednesday, February 22, 2012

ልሳን


ልሳን ምንድን ነው

ሀ . ልሳን ምንድን ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰቸው ቦታዎችሰ
1.ልሳን ቋንቋ ማለት ነው።
ልሳን ማለት ቋንቋ ማለት ነው። በአዲስ ልሳን መናገር ማለትም በአዲስ ቋንቋ መናገር ማለት ነው። በአዲስ ቋንቋ መናገር ሲባልም ተወልደው ባላደጉበት፤ ባልተማሩት ቋንቋ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት መናገር ማለት ነው። የመጀመሪያውና ትክክለኛው ልሳን የተገለጸው በጰራቅሊጦስ እለት ነው። ታሪኩም በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ ሁለት ተገልጿል። ሐዋርያትም ሆነ በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች የተናገሩት በሚሰማና ሊተረጎም በሚችል ቋንቋ ነበር። ሐዋ 2፡ 6 ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ሐዋርያት በልሳን ሲናገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ በራሰቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋል። ሐዋርያት የሚያወቁት የራሳቸውን ቋንቋ ብቻ ነበር ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የተሰበሰቡት ከዓለም ሁሉ ነበር። ሐዋርያትም የተናገሩት የአለምን ቋንቋ ነበር።ጌታችንም በማር 16፤ 17 በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ ሲል በሚሰማ ቋንቋ ማለቱ ነው።
1ኛቆሮ 14፡ 9-11 እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል ? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና። በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤ እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል።
ብሎ ቋንቋ ሁሉ ሰሚ እንዳለውና እናንተም የምትናገሩት ቋንቋ ሰሚ ባለው ህዝብ መሐከል መሆን አለበት ብሎ ያብራራል።
2.ልሳን መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጣቸው ልዩ ልዩና ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ጸጋዎች አንዱ ነው።

Monday, February 20, 2012

«ብጹእ አቡነ አብሳዲ እኒህ ነበሩ»

 

«ብጹእ አቡነ አብሳዲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ»

ብጹእ አቡነ አብሳዲ (በቀድሞ ስማቸው አባ ገ/ማርያም) ግንቦት 12 ቀን 1912 /ም በትግራይ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በተወለዱበት ደብር  ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ንባብና እስከ ግብረ ዲቁና ያለውን ከዚያም ወደ ቀድሞው የኤርትራ ክ/ሀገር በአባ አብሳዲ ገዳም ገብተው ቅዳሴና ዜማ ቀጽለዋል። በዚያው በተማሩበት በአባ አብሳዲ ገዳም ማእረገ ምንኩስናን ተቀብለው እስከ 1942 /ም ቆይተው ሲያበቁ የግብጽን ገዳማት ለማየት ባደረባቸው ጉጉት ተነሳስተው የሱዳንን በረሃ በእግራቸው አቋርጠው ወደትልቁ የግብጽ ገዳም ገዳመ አስቄጥስ ሄደዋል። እዚያም የገዳሙ አባቶች በፈቀዱላቸው መሰረት ከገዳሙ አንድነት ገብተው እስከ 1944 /ም ቆይተዋል። እንደገና ኢየሩሳሌምን ተሳልሜ እመጣለሁ በማለት ከአንድ መንፈሳዊ ጓደኛቸው ጋር በመሆን የሲናን በረሃ በእግራቸው በማቋረጥ ወደኢየሩሳሌም አምርተው በዚያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳም ተቀላቅለዋል። ገዳሙን ያስተዳድሩ የነበሩት አቡነ ፊልጶስ ተቀብለው ከገዳሙ አንድነት ያስገቧቸው ሲሆን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት የካቲት 11/ 2004 /ም ድረስ ላለፉት 60 ዓመት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም በተለያዩ ኃላፊነቶች ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ብጹእ አቡነ አብሳዲ ከውጭ ቋንቋዎች እብራይስጥኛና አረብኛ ቋንቋዎችን በደንብ የሚያውቁ ሲሆን በዚህ የቋንቋ ችሎታቸው የኢትዮጵያ ገዳም ከግብጾች ጋር ባለው የይገባኛል ችግር እንዲያግዙና ማንኛውንም ጉዳይ መፍትሄ እንዲያመጡ ተመርጠው በገዳሙ አስተዳዳሪነት ለ27 ዓመታት አገልግለዋል። ብጹእነታቸው ለሰው አዛኝና ርኅሩህ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ተቆርቋሪና ጠበቃ ነበሩ።
ብጹእ አቡነ አብሳዲ በቀድሞ ስማቸው መጋቢ ገ/ማርያም ለኢትዮጵያ ገዳማት ያበረከቱት መንፈሳዊ ተጋድሎ ከታየ በኋላ በ1985 /ም በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኤጲስ ቆጶስነት ማእረግ ተሹመው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ረዳት ሊቀጳጳስ ተብለው ሲያገለግሉ ቆይተው የካቲት 11/2004 /ም ባደረባቸው ህመም በተወለዱ 92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የብጹእነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጋር ያሳርፍልን! አሜን
ከመንፈሳዊ ልጃቸው ኃ/ማርያም- ግሪክ አቴንስ

Saturday, February 18, 2012

የቤተክርስቲያን መታደስ!

ክፍል ፪ 


ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች

በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጥናቸው ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ የሚያምኑ ሲኖዶሱ ቀኖና ማውጣት እንደሚችል ቀኖናውን መቀበልና ማክበር እንደሚገባ የሚያምኑ ናቸው :: ሆኖም ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያን ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ አለባት በለው ለውጥ የሚናፍቁ ናቸው :: እነዚህ ቡድኖች እንዳይገለሉ የሚፈሩ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ለውጥ ብታደርግ የተሻለ ትጠናከራለች ብለው የሚያስቡ ናቸው :: ህዝቡን ለመያዝና አብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመን ንቁ ክርስቲያን ሆኖ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቀኖናዊ ለውጥ ብታደርግ ጥሩ ነው ብለው የሚናገሩ ናቸው :: በአብዛኛው ጊዜ ፍላጎታቸውን በቀጥታ ባይናገሩም በእውቀት ዳብሯል ብለው ለሚያስቡት ሰው ግን ሃሳባቸውን ይገልጻሉ ::

እነዚህ ቡድኖች እንደ ምሳሌ የሚወስዱት የእህት አብያተ ክርስቲያናትን የአምልኮ ስርአትና ነው በተለይም የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የአምልኮ ስርአት ብዙ ጊዜ ይጠቅሳሉ :: የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ ሃይማኖት ደረጃ አንድ ሊባል የሚችል እምነት ያምናሉ በጣም ጥቂት ልዩነቶች ከመኖራቸው ውጭ ዶግማችንና እንዲሁም የቅዳሴው ጸሎት ይዘትም አንድ ሊባል የሚችል ነው :: አብዛኛው ቀኖናቸውም እንዲሁ ይመሳሰላል :: ለምሳሌ የክህነት አሰጣጣቸው፡ የጳጳሳት ስልጣናቸው፡ የቤተ ክርስቲያን አስራራቸውና አከባበራቸው፡ የበአላት ቀናቸው፡ የጾም ጊዜቸው፡ የጾም አጿጿማቸው፡ የንስሃ አገባባቸው እና የመሳሰሉት የሚመሳሰሉ ናቸው ::