Monday, February 20, 2012

«ብጹእ አቡነ አብሳዲ እኒህ ነበሩ»

 

«ብጹእ አቡነ አብሳዲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ»

ብጹእ አቡነ አብሳዲ (በቀድሞ ስማቸው አባ ገ/ማርያም) ግንቦት 12 ቀን 1912 /ም በትግራይ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በተወለዱበት ደብር  ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ንባብና እስከ ግብረ ዲቁና ያለውን ከዚያም ወደ ቀድሞው የኤርትራ ክ/ሀገር በአባ አብሳዲ ገዳም ገብተው ቅዳሴና ዜማ ቀጽለዋል። በዚያው በተማሩበት በአባ አብሳዲ ገዳም ማእረገ ምንኩስናን ተቀብለው እስከ 1942 /ም ቆይተው ሲያበቁ የግብጽን ገዳማት ለማየት ባደረባቸው ጉጉት ተነሳስተው የሱዳንን በረሃ በእግራቸው አቋርጠው ወደትልቁ የግብጽ ገዳም ገዳመ አስቄጥስ ሄደዋል። እዚያም የገዳሙ አባቶች በፈቀዱላቸው መሰረት ከገዳሙ አንድነት ገብተው እስከ 1944 /ም ቆይተዋል። እንደገና ኢየሩሳሌምን ተሳልሜ እመጣለሁ በማለት ከአንድ መንፈሳዊ ጓደኛቸው ጋር በመሆን የሲናን በረሃ በእግራቸው በማቋረጥ ወደኢየሩሳሌም አምርተው በዚያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳም ተቀላቅለዋል። ገዳሙን ያስተዳድሩ የነበሩት አቡነ ፊልጶስ ተቀብለው ከገዳሙ አንድነት ያስገቧቸው ሲሆን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት የካቲት 11/ 2004 /ም ድረስ ላለፉት 60 ዓመት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም በተለያዩ ኃላፊነቶች ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ብጹእ አቡነ አብሳዲ ከውጭ ቋንቋዎች እብራይስጥኛና አረብኛ ቋንቋዎችን በደንብ የሚያውቁ ሲሆን በዚህ የቋንቋ ችሎታቸው የኢትዮጵያ ገዳም ከግብጾች ጋር ባለው የይገባኛል ችግር እንዲያግዙና ማንኛውንም ጉዳይ መፍትሄ እንዲያመጡ ተመርጠው በገዳሙ አስተዳዳሪነት ለ27 ዓመታት አገልግለዋል። ብጹእነታቸው ለሰው አዛኝና ርኅሩህ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ተቆርቋሪና ጠበቃ ነበሩ።
ብጹእ አቡነ አብሳዲ በቀድሞ ስማቸው መጋቢ ገ/ማርያም ለኢትዮጵያ ገዳማት ያበረከቱት መንፈሳዊ ተጋድሎ ከታየ በኋላ በ1985 /ም በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኤጲስ ቆጶስነት ማእረግ ተሹመው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ረዳት ሊቀጳጳስ ተብለው ሲያገለግሉ ቆይተው የካቲት 11/2004 /ም ባደረባቸው ህመም በተወለዱ 92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የብጹእነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጋር ያሳርፍልን! አሜን
ከመንፈሳዊ ልጃቸው ኃ/ማርያም- ግሪክ አቴንስ

Saturday, February 18, 2012

የቤተክርስቲያን መታደስ!

ክፍል ፪ 


ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች

በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጥናቸው ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ የሚያምኑ ሲኖዶሱ ቀኖና ማውጣት እንደሚችል ቀኖናውን መቀበልና ማክበር እንደሚገባ የሚያምኑ ናቸው :: ሆኖም ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያን ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ አለባት በለው ለውጥ የሚናፍቁ ናቸው :: እነዚህ ቡድኖች እንዳይገለሉ የሚፈሩ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ለውጥ ብታደርግ የተሻለ ትጠናከራለች ብለው የሚያስቡ ናቸው :: ህዝቡን ለመያዝና አብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመን ንቁ ክርስቲያን ሆኖ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቀኖናዊ ለውጥ ብታደርግ ጥሩ ነው ብለው የሚናገሩ ናቸው :: በአብዛኛው ጊዜ ፍላጎታቸውን በቀጥታ ባይናገሩም በእውቀት ዳብሯል ብለው ለሚያስቡት ሰው ግን ሃሳባቸውን ይገልጻሉ ::

እነዚህ ቡድኖች እንደ ምሳሌ የሚወስዱት የእህት አብያተ ክርስቲያናትን የአምልኮ ስርአትና ነው በተለይም የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የአምልኮ ስርአት ብዙ ጊዜ ይጠቅሳሉ :: የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ ሃይማኖት ደረጃ አንድ ሊባል የሚችል እምነት ያምናሉ በጣም ጥቂት ልዩነቶች ከመኖራቸው ውጭ ዶግማችንና እንዲሁም የቅዳሴው ጸሎት ይዘትም አንድ ሊባል የሚችል ነው :: አብዛኛው ቀኖናቸውም እንዲሁ ይመሳሰላል :: ለምሳሌ የክህነት አሰጣጣቸው፡ የጳጳሳት ስልጣናቸው፡ የቤተ ክርስቲያን አስራራቸውና አከባበራቸው፡ የበአላት ቀናቸው፡ የጾም ጊዜቸው፡ የጾም አጿጿማቸው፡ የንስሃ አገባባቸው እና የመሳሰሉት የሚመሳሰሉ ናቸው ::

Friday, February 17, 2012

የቤተክርስቲያን መታደስ!


.............................በአሁኑ ወቅት ማንም ሰው ሊያስተውለው እንደሚችል በቤተ ከርስትያን ውስጥ ሁለት የሚጋጩና እርስ በእርሳቸው መጠፋፋት የሚፈልጉ አካላትን እናገኛለን :: አካላት ስንልም ሃሳቦች ናቸው :: ሃሳቦች ግን ሰዎችን ይዘዋል :: ሁለቱ አካላት በእየራሳቸው ለአንድ ዓላማ ይኽውም ለቤተ ክርስቲያን ለመጥቀም እንደሚሰሩ ይናገራሉ ::

ማህበረ ቅዱሳንና ማህበረ ቅዱሳናዊ አስተሳሰብ

ማህበረ ቅዱሳናዊ አስተሳሰብ የምለው ቤተ ክርስቲያን እንከን የለሽ በመሆንዋ ምንም አይነት ትችት ማቅረብ የለብንም የሚለውን እና አብዛኛው የማህበሩ አባላት እንዲሁም ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችም የሚጋሩት ነው :: ይህ ሃሳብ በመሰረተ ሃሳብነት ማነኛውም ኦርቶዶክሳዊ ሊደግፈውና ሊጋራው የሚገባው ነው :: የራስን ቤት ይልቁንም መክራና ዘክራ ያሳደገችንን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ናት እያሉ በእየ ሜዳው ስሟን ማጥፋት ክብሯን ማጉደፍ የማይገባ ስራ መሆኑ እሙን ነው :: በሌላ በኩል ደግሞ ምእመናኑ ወደ ኑፋቄ የሚነጠቁበትን እና በሃይማኖት ያሉትም ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የማይቀርቡበትን ምክነያት አጥንቶ እነዚህ እንዲህ ይደረግ ይህ ይስተካከል ማለት አግባብ ነው ::

ማህበረ ቅዱሳን በእየ ዜናው መውጣት ከጀመረ አለፈ ከረመ እንዳንዶች አይንህን ላፈረ አይነት ጽሁፍ ሲጽፉበት አንዳንዶች ደግሞ እርሱ ከሌለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አትኖርም ብለው ክርር ያለ ክርክር ያደርጋሉ :: ታዲያ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ ስለማይችሉ ትክክለኛው የቱ ይሆን ማለቱ አስፈላጊ ነው :: የዚህ ጽሁፍ ጸሓፊ ማህበሩን በሚገባ የሚያውቅ ድክመቶቹንም የማያስተባብል ስለሆነ የማህበሩን በጎ ጎኖችን ሙሉ በሙሉ ዘርዝሮ መጨረስ ባይችልም ዋና ዋና በጎ ጎኖችንና ድክመቶቹን ይጽፋል :: የጽሁፉም አላማ ሰዎች ጥሩውንና መጥፎውን ለይተው ከመልካሙ ጋር እንዲተባበሩ ከመጥፎው ደግሞ እንዲርቁ ነው ::