Friday, February 10, 2012

«ኢያሱ ወልደ ነዌ በአባቶች እግር»



«ኢያሱ ወልደ ነዌ በአባቶች እግር»

ምድራችን አንዱን በአንዱ እየተካች እዚህ ዘመን ላይ ደርሳለች። ቀድሞ የነበረው ዛሬ የለም። ዛሬ ያለው ደግሞ ነገ ላይኖር ይችላል። በለውጥ ሂደት ውስጥ እንዳለን እንገነዘባለን። ዓለም እንኳን እየተለወጠች ነው። ድሮ የሌለ እምነት ዛሬ ተፈልስፏል። የነበረውም ቢሆን ገሚሱ ረስቶታል ወይም ከልሶታል አለያም ጥሩ አድርጎ አክርሮታል። ዝናባማው ዘመን በፀሐይ ተተክቷል። የሙቀት ጨምሯል ጩኸት፣ የዕለት ከዕለት ዜና ከሆነ ውሎ አድሯል። ሉላዊነት(Globalization) የሚሉት ስልጥንና በመንፈሳዊ ሀብት የሚታይ አብሮነትና አንድነት ባይኖረውም የሳይንስ ቁስ ዓለምን አቀራርቧል። ዓለምን ለመቃኘት ማጄላንን ወይም ኢብን ባቱታን መምሰል አይጠበቅብንም። ቁርስ አዲስ አበባ፣ ምሳ አቴንስ ለመመገብ ተችሏል። ድምፀትን ለመቀበል ወይም ለመስጠት ዛሬ ሁሉ ነገር የዓይንና የጆሮ ያህል ቀርቧል። ሲሰየጥኑ ይሁን ሲሰለጥኑ «ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ» የሚለው ትረካ ዓለምን እየነዳት ይገኛል። ይህ እንግዲህ ዓለም ደርሼበታለሁ የምትለው ግኝቷ ሲሆን የተቆላለፈው ችግሯ ደግሞ የትየለሌ ሆኗል።
ኤድስ የሚሉቱ አይድኔ በሽታ ብዙዎችን ወደ መቃብር ሸኝቷል። ኢቦላና የአእዋፍ ጉንፋን(BIRD FLU) ስንቱን ፈጅቶ የታገሰ ቢመስልም ጨርሶ እንዳልጠፋ ይወቃል። ካንሰር፣ ወባ፣ ስኳር፤ ግፊትና ብዛት፣ ማነስና ድክመት ልዩ ልዩ ህመሞች በርክተዋል፣ ወይም ህመምተኞችን አበራክተዋል። ከቺሊ እስከጃፓን፣ ከግሪንላንድ እስከ አንታርክቲካ የመሬት መንቀጥቀጡና የበረዶ መደርመሱ፣ የመሬት መናዱና ጎርፉ ብዙዎችን አጥፍቷል።
ሀይቲ 230,000 ሰው ሲሞትባት፤ሱናሚ ከኢንዶኔዢያ እስከ ሶማሊያ ጠረፍ ከ280,000 በላይ ሰዎችን መጥረጉን ሰምተናል። ጃፓንም ሀገር አማን ባለችበት ሀብቷን ሳይጨምር10 ሺዎችን ዜጋ አጥታለች።
ጦርነቱ፣ ፍጅቱ፣ የስልጣን ሽኩቻው፣ የሃይማኖት ፉክክሩ፣ የአሸናፊና ተሸናፊ ግብግቡ አይሏል። ያም ሆኖ ዓለም አለሁ፣ ማለቷን አልተወችም። ያለፈውን እየረሳች፣ መጪውን ትኖር ዘንድ ትጥራለች። «ገንፎ እየሞተ፣ ይተነፍሳል» እንዲሉ መሆኑ ነው። አዎ ዓለማችን እየሞተች መተንፈሷን አላቋረጠችም። ባለውና በሚታየው ነገር ለመጽናናት ትሻለች። ቁም ነገሩ ባለውና በሚታየው ነገር ፍጹም መጽናናትን ማግኘት አለመቻሏን አለማወቋ ነው። የተነገረውን አልሰማችም ወይም አልሰምቶም ሆኖባታል።
ማቴ 243-8
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
እናም ዓለም የምትወልደውን በምትወልድበት በመጨረሻው ወር ውስጥ ነው ያለችው። እንደነፍሰ ጡር ሴት በምትወልድበት በ9ኛው ወር ውስጥ እንዳለች ልትረዳና «ወልደ አብ፣ ኢየሱስ» 9ነኛው ሰዓት ያስተማራትን ጸሎት ልታሰማ ይገባታል። «
ማቴ2746
ዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።

በዚህ ጽሁፍ ስለዓለም የዳሰስኩት ጽሁፌን በዚያ ላይ ለማንተራስ እንጂ ስለዓለም ለማስተማር ስላለሆነ ዋናው ነጥቤ ዓለም ያለችበትን ደረጃ በማሳየት የዓለም አንድ ክፍል የሆንን እያንዳንዳችን ከዚህ የዓለም ጣር ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብን «የኢያሱ ወልደ ነዌ»ን አብነታዊ መንገድ ለማሳየት ነው። ኢያሱ እንደልጅ ልጅ ሆኖ ኅሊናውን ሳያባክን፣ መንፈሳዊ ልቡናውን በጊዜው ከነበረው መሳሳቻ ጠብቆ የአባቶቹን እግር እንደተረከበ በማሳየት እኛም በዚያ መሠረትነት ላይ ቆመን ዛሬ ዓለምን ከሚንጣት ወጀብ በመዳን የኃጢአት ከተማ ኢያሪኰን አፍርሰን ርስታችንን ለመውረስ እንድንችል ለማስገንዘብ ነው። ፍየል በኃጢአተኛ የምትመሰልበት ዋናው ምክንያት፣ ግልገሎቿን አድፍጦ ወደበላባት የቀበሮ ጫካ ቅጠል ለመቀንጠስ ዳግመኛ የምትመለስ በመሆኗ ነው። እንዲሁ ሁሉ ከጎናችን ብዙዎች ንስሐ ሳይገቡ መሞታቸውን እያየን፣ በቅጽበታዊ አደጋ ዓለም ብዙዎችን እንደሸኘች እየተመለከትን፣ እኛ ዘንድ እንደማይደርስ አስበንና ለእነርሱ እያዘንን በመቆየት ሰንበትበት ሲል ሁሉን ነገር ረስተን እንደነበረው የምቀጥል መሆናችን ነው።

ይቀጥላል.............

Tuesday, February 7, 2012

ሞርሞኒዝም ምንድነው?


ካለፈው የቀጠለ
ክፍል 3
በባለፈው ጽሁፋችን ሞርሞኒዝም የብዙ አማልክት እምነት ቦታ ሆኖ የእምነቱ ተከታዮችም ወደዚህ ወደአማልክትነት ለመቀየር ብዙ መታገልና መጣር እንደሚገባው ተመልክተናል። የዚያኑ ቀጣይ ክፍል ደግሞ እነሆ አቅርበናል።
«እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው»ዘዳ6፣4
እግዚአብሔር አንድ አምላክ ሆኖ ሳለ ብዙ አማልክት አድርጎ ማቅረብን ጆሴፍ ስሚዝ ከየት አመጣው? ብለን ብንጠይቅ መልሳችን አጭር ነው። ከሔዋን ጀምሮ ሲያሳስት የኖረው ሰይጣን በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የብርሃንን መልአክ መስሎ ከሰጠው መገለጥ የተገኘ ትምህርት ነው። መሐመድ በ7ኛው ክ/ዘመን «ሂሩ»ዋሻ እየሄደ ከአላህ መልአክ ከጅብሪል አገኘሁት ባለው በሚያንዘፈዝፍና በሚያንቀጠቅጥ መገለጥ አላህ አይወርድም፣አይወለድም፣ ዒሳ(ኢየሱስ) ነብይ እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፣አልተሰቀለም፣ አልሞተም የሚል የክህደት ትምህርትን ከሰይጣን ተቀብሎ ለዓለም አስተላለፈ። እነሆ እልፍ አእላፋት ይህንኑ አምነው ይገኛሉ።
እግዚአብሔር አንድ አካል፣አንድ ገጽ ነው በማለት በመሐመድ በኩል ሲያሳስት የኖረው ሰይጣን በጆሴፍ ስሚዝ በኩል ደግሞ የለም «አምላክ ቁጥር ስፍር የለውም» ሲል መገኘቱ ሰይጣን የሰውን ልጅ ለማሳሳት መቼም ቢሆን አርፎ እንደማያውቅ ነው። እሱ ስራው ሰው የሚጠፋበት መንገድ ማዘጋጀት፣ ከእውነት ጋር የስህተት ትምህርቶችን አቀላቅሎ መስጠትና ለጥፋት ማዘጋጀትን መደበኛ ስራው አድርጎ ይንቀሳቀሳል። የሚገርመው ግን እስላሞች ይሁኑ ሞርሞኖች ያለእነርሱ ሌላው እንደማይጸድቅ፣ ሲኦል እንደሚወርድና ፈጣሪ የወደድኩት ሃይማኖት የእናንተን ነው እንዳላቸው አድርገው ራሳቸውን አሳምነው መገኘታቸው ነው።

Saturday, February 4, 2012

ማኅበሩ አያንቀላፋም!

« ማኅበሩ አያንቀላፋም»

እንቅልፍ ለሰዎች የተሰጠ የሥጋ እረፍት ነው። «ቀን ለሰራዊት፣ሌሊት ለአራዊት»እንዲሉ! ዛሬ ግን ዓለማችን ቀንና ሌሊቱን አቀላቅላው ሰውም አራዊቱም ጉዞአቸው ባንድ ሆኗል። በሌሊት! ከነዚህ ቀኑንም ሌሊቱንም ከማያንቀላፋው ሀገርኛ ድርጅት አንዱ ራሱን በራሱ የቅዱሳን ማኅበር ነኝ የሚለው «ማኅበረ ቅዱሳን» በቁልምጫ ስሙ «ማቅ» የተባለው ድርጅት ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ ስፍራውና ድርሻው ለጊዜው ባይገባንም ረጅምና ስውር እጁ የሌለበት ቦታ የለም በሚባል ደረጃ ያለእረፍት ይንቀሳቀሳል። ለዚህም ነው የጽሁፋችንን ርእስ «ማኅበሩ አያንቀላፋም» ያልነው። አዎ! ማኅበረ ቅዱሳን አያንቀላፋም። የማያንቀላፋው ራሱን የቤተክርስቲያን ተጠሪ በማድረግና ሲኖዶሱ ባልሰጠው ውክልና በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ስውር እጁን እንደአባጨጓሬ እያርመሰመሰ በመገኘቱ ነው። ማኅበሩ በሲኖዶስ መሃል ቁጭ ብሎ በስውር እጁ ጳጳስ ሆኖ ይወስናል፣ ያስወስናል፣ይከራከራል፣ይሞግታል። ለሲኖዶሱ አጀንዳ ይቀርጻል፣ የማይስማማውን ይጥላል፣ የፓትርያርኩ የራስ ህመም እስኪነሳ ያሳብዳል። ምክንያቱም ማኅበሩ ጳጳስ ስለሆነ አያንቀላፋም። በአምሳለ ጳጳስ «ማኅበረ ቅዱሳን ባይኖር ቤተክርስቲያን ምን ተስፋ አላት» ያሰኛል። በአድባራትና ገዳማትም መካከል ሳያንቀላፋ በአለቃነት ወይም በሀገረ ስብከት ደረጃ በሥራ አስኪያጅነት ወይም በመምሪያ ኃላፊነት ውስጥም ኅቡእ መንፈስ ሆኖ ይንቀሳቀሳል። የሰባኪዎችን፣የሰንበት ት/ቤቶችን ወይም የምእመናንን ማንነት ይቆጣጠራል፣ ይመረምራል፣ ይሰልላል። ማኅበረ ቅዱሳን አያንቀላፋምና እዚህም ቦታ አለ። ንግዱ ውስጥ! ይነግዳል፣ያስነግዳል። ግብርና ታክስ የማይከፍል የንግድ ተቋም ሆኖ በሆቴሎች፣ በሱቆች፣ በንዋያተ ቅድሳት መሸጫዎች፣በኢንኮርፖሬትድ ድርጅቶች፣ በህትመት፣ በሚዲያ ውጤቶች ውስጥ ሁሉ አለ።