Saturday, February 4, 2012

ሞርሞኒዝም!

 

በዳኒ ይትባረክ የተጻፈ( በደጀብርሃን ለብሎጉ እንዲያመች የቀረበ)
.... ክፍል ሁለት

                            ሞሮኒ ማነው?

ስለዚህ ሰው በመጽሐፍም ይሁን በታሪክ ምንም ዓይነት መረጃ አናገኝም። መዝገበ ቃላትም ቢሆን ሞሮኒ(MORONI)የኮሞሮስ ዋና ከተማ መሆኗን እንጂ ሌላ የሚሰጠን ፍንጭ የለም። ታዲያ ይህ ሞሮኒ የተባለው የጆሴፍ ስሚዝ ሰው ማነው?
በመጽሐፈ ሞርሞን (THE BOOOK OF MORMON) መግቢያ ላይ «,,አ በ421 /ም ገደማ መጨረሻ አካባቢ የኔፊ(*) ባለታሪክና ነብይ የነበረ «ሞሮኒ» በጥንታዊ ነብያት አማካይነት በእግዚአብሔር ድምጽ በኋለኛው ቀን እንደሚመጣ እንደተተነበየው ቅዱሱን መዝገብ አተመው፣ እናም በጌታ እንዲጠበቅ ደበቀው» ካለ በኋላ በጌታ ተደብቆ የተቀመጠው ሞሮኒ ከሞት ተነስቶ በ1823 /ም በቤቱ እየጸለየ ሳለ የተገለጠለትና እጅግ በሚደንቅ ግርማ እንደታየው የጆሴፍ ስሚዝ መጽሐፍ ያትታል።
እንግዲህ ሞሮኒ ማለት እንደተከታዮቹ አባባል በ421 /ም ሞቶ በ1823 /ም ትንሳዔ በማግኘት ለጆሴፍ ስሚዝ የተገለጠ መልአክ ነው ማለት ነው።
ከዚህ አባባል የምንረዳው ነገር ሰይጣን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የታየውን መለኮታዊ መልክ በሚመስል ነገር በሞሮኒ ስም ለጆሴፍ ስሚዝ በመገለጥ እንደሆነ እንረዳለን።
ሰይጣን ጆሴፍ ስሚዝን እንዳታለለው ዛሬም ቢሆን ህልም አለምኩ፣ ራዕይ አየሁ፣ መልዕክት መጣልኝ፣ እመቤታችን ታየችኝ፣ እሳት ከሰማይ ወረደ፣ በዘንዶ የሚጠበቅ ቤተክርስቲያን፣ በእባብ የታጠረ ጸበል በሚል ሰበብ በክርስትናው ውስጥ ዛሬም ብዙ ጆሴፎች አሉ።)
ሰይጣን መቼም አይተኛም። ጆሴፍ ስሚዝን እንዳጭበረበረው እኛንም ሊያጭበረብረን ይፈልጋል። ምክንያቱም ለሞርሞኖች ተስፋቸው አዲስቱ ኢየሩሳሌም ሳትሆን አሜሪካ ነች። ከድርሳናቸው አንዱ ክፍል ኔፊ እንዲህ ይላል።
«የያዕቆብ ቅሪት የሆኑትም ጌታ አምላካቸውን ወደማወቁ ይመጣሉ፣ እናም አሜሪካንን ይወርሳሉ» 3ኔፊ201
ጆሴፍን አሜሪካ የርስት ምድር እንደሆነችና አሜሪካንን የሚናፍቁ ሕዝቦች የሚፈጠሩበት ዘመን እንደሚመጡ ያኔም ሞሮኒ የተነበየላት ስለሆነ እንደሚባረኩ መዋሸቱን ስንመለከት ይህ ሰይጣን በኢትዮጵያም ውስጥ መልኩንና ማሳሳቱን ለውጦ «ደጅህን የረገጠ ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ እቆጥርለታለሁ ብሎ ቃል ገብቶለታል፣ ፍርፋሪህን የበላ የ40 ቀን ህጻን አደርግልሃለሁ ብሏል፣ በስሜ የተጠራ ዘው ብሎ ገነት ይገባል፣ የቅዳሴዬን ጸበል የቀመሰ 30 ትውልድ ሰተት አድርጌ ገነት አገባልሃለሁ ወዘተ ሞርሞናዊ ማሳሳቻዎች ከሰይጣን የወጣ ስለመሆኑ የታወቀ ነው። ሰይጣን ምን ጊዜም ክርስቶስ ያደረገልንን የሕይወት ስጦታ በመቀየር ወደሌላ የማዳኛ ምክንያቶች ለመለወጥ ሳይደክም እንደሚሰራ እንረዳለንና ነው።
ሐዋርያው እንዲህ ብሏል።« ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል»2ተሰ 211-12


               ሞርሞኖች ስለእግዚአብሔር ያላቸው አስተምህሮ

ሞርሞኖች በአጽናፈ ዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፕላኔቶች እንዳሉ፣ በነዚህም ፕላኔቶች ላይ በአንድ ወቅት ሰዎች ይኖሩበት እንደነበረና አሁን ግን አማልክት በሆኑ ኃይሎች እንደሚተዳደሩ ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔርን በተመለከተ 4 ዓይነት አስተምህሮዎች አላቸው።
1/ እግዚአብሔር ሥጋና ደም አለው ይላሉ።
2/እግዚአብሔር አምላክም ሰውም ሆኖ በሰማይ አለ ይላሉ።
3/አማልክት አባት፣ እናት፣ አያት ወዘተ ሆነው በዘር ሐረግ በየፕላኔቶቹ አሉ ብለው ያምናሉ።
4/ እያንዳንዱ ሞርሞናዊም ወደአማልክትነት ለመቀየር መጣር አለበት ይላሉ።
(Mormon doctrine, page 557 &, Doctrine & covenantes section 130. verse 22)

.....ይቀጥላል
(*) የተመለከተው «ኔፊ» የሞርሞኖች ድርሳን ነው።

Friday, February 3, 2012

ሞርሞኒዝም !

            ሞርሞኒዝም ምንድነው? 

በዳኒ ይትባረክ

ሞርሞኒዝም የሞርሞንን የእምነት ፍልስፍና መከተል ማለት ሲሆን የዚህ የእምነት ፍልስፍና መስራቹ ደግሞ ጆሴፍ ስሚዝ ይባላል።

                 ጆሴፍ ስሚዝ ማነው? 

ጆሴፍ ስሚዝ ኒዮርክ ውስጥ ሻሮን ቬርሞንት በሚባል አካባቢ ይኖር የነበረ ሰው ሲሆን የተወለደውም እ,ኤ,አ በ1805 ነው። በሚኖርበትም አካባቢም ማዕድን ለማግኘት ሲል አስማታዊ ልምምድን ያደርግ እንደነበር የብሪንግሃም ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ሚካኤል ኪውን «Early Mormonizm in the Magic World» በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ጠቁመዋል። ብሪንግሃም ዩኒቨርሲቲም የሞርሞኖች ዩኒቨርሲቲ ነው። ስለዚህ እኛ ከዚህ ፍንጭ በመነሳት ጆሴፍ ስሚዝ መተተኛ ወይም ድግምተኛ ነበር ብንል ስህተት አይሆንም።

            ሞርሞኒዝም መቼ ተጀመረ? 

ሞርሞኒዝም የተጀመረው በነጮቹ አቆጣጠር በ1830 ሲሆን የተጀመረውም ጆሴፍ ስሚዝ ተገለጠልኝ ባለው መገለጥ አማካይነት ነው። ጽሁፋቸውን ስናነብ ጆሴፍ ስሚዝ ከ14 ዓመቱ ጀምሮ «የትኛዋ ቤተክርስቲያን ትሆን ትክክል?» የሚል ጥያቄ እንደነበረውና አንድ ቀን «አብና ወልድ» ተገልጠው እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምድር ላይ እንደሌለችና በእርሱ( በጆሴፍ በኩል) እንደሚያስተካክሏት ከነገሩት በኋላ ወደየትኛዋም ቤተክርስቲያን እንዳይሄድ እንደከለከሉት «the testimony of the prophet Joseph Smith, page, 1» ላይ ተቀምጦ ይገኛል።

                      የጆሴፍ ስሚዝ ራዕይ

ጆሴፍ ስሚዝ በ1823 መስከረም 21 ቀን ምሽት ላይ አምላክ ነው ወደሚለው እየጸለየ ሳለ የተገለጠለትን ራዕይ እንዲህ በማለት ተናግሯል። «እግዚአብሔርን በመጥራት ላይ ሳለሁ ብርሃን በነበርኩበት ክፍል ሲመጣ አየሁ፣ ብርሃኑም ከቀትር ጸሀይ ይበልጥ ነበር፣ ወዲያውም አንድ ሰው በአልጋዬ አጠገብ እግሩ መሬት ሳይነካ በአየር ላይ ተገለጠልኝ,,» ሲል ከተናገረ በኋላ የተገለጠለት ሰው መልክና ማንነት ከመነገር በላይ እንደነበር ተርኳል። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጦችን መነሻ አድርገን ለጆሴፍ የተገለጠለት ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆን እንዴ? ብለን ብንገምት ግምታችን ግምት ሆኖ የሚቀረው ጆሴፍ ስሚዝ የተገለጠለትን ሰው ማንነት ሲነግረን ነው። እሱም «ሞሮኒ» የተባለ ነው።

               ሞሮኒ ማነው?

ይቀጥላል.................

Thursday, February 2, 2012

በጋሻውን ለማጥቃት፤ሕሙምን መበቀል?

ከደጀብርሃን፤
ለልብ ሕመምተኛው የድረሱለት ጥሪ ማቅረብ ተሀድሶን መደገፍ ነው! አንድ አድርገን ብሎግ(እዚህ ላይ ይጫኑ)
በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ የቤተክርስቲያን በዓላት ሲከበሩ ከካቶሊክ ፣ ከግሪክ እና ከሌሎች ተቋማት በእንግድነት እንደሚጠሩ ይታወቃል። ምነው ያኔ በሃይማኖት የማይመስሉን ተገኝተዋል የሚል ተቃውሞ ያልቀረበ?
ጉዳዩና ቂም በቀሉ ያለው ለህመምተኛው የእርዳታ ጥሪ ለማድረግ የተንቀሳቀሱት እነትዝታው ሳሙኤል፣ እነምርትነሽ ጥላሁን በመሆናቸው ብቻ ነው። ምርትነሽ በመዝሙሯ ያስተማረችውንና ያነጸችውን የክርስትና ምግባር ዋጋ ማሳጣት ለምን?
እነምርትነሽ ካልጠፉ የልብ ህሙምም የእርዳታ በሩ ድርግም ይበልበት ክርስትና ነው? ወይስ ጸረ ክርስትና?
ያገኘነውን መረጃ እናካፍላችሁ! መልካም ንባብ!
ለእንዳለ ገብሬ የተዘጋጀው የዕርዳታ ገቢ ማሰባሰቢያ ጉባዔ በቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ የግል ውሳኔ ታገደ ዕገዳው ቀሲስ ሳሙኤል በሰው ሕይወት ላይ ያስተላለፉት ውሳኔ በመሆኑ፣ በወንጀል ሊያስጠይቃቸው ይችላል ቤተክርስቲያን የበላይ ኃላፊ ሲያዝ፣ የበታች ኃላፊ የሚሽርበት ሥርዓት አልበኝነት የነገሠባት ተቋም ሆናለች በከፍተኛ የልብ ሕመም ለሚሰቃየው እንዳለ ገብሬ ማሳከሚያ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ ጥር 20 ቀን 2004 ዓ.ም የተዘጋጀው ጉባዔ በቀሲስ ሳሙኤል የግል ውሳኔ መታገዱ ከጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡ ታማሚው አቶ እንዳለ ገብሬ ቤተክርስቲያን ድጋፍ እንድታደርግለት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ በኩል አስፈላጊው የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባዔ እንዲዘጋጅለት መርተውለታል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ መምህር አዕመረም በግል ከታማሚውና ከልዩ ልዩ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ጉባዔውን የሚያዘጋጁት መምህራን የስብከት አገልግሎት ማስረጃዎችን ከመንፈሳዊ ኮሌጆችና ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናት አቅርበው እንዲያካሂዱለት ከመወሰናቸውም በላይ አንድ የፕሮግራም መሪ እና የስብከት መምህር ከጠቅላይ ቤተክህነቱ በማከል ጉባዔው በተጠቀሰው ዕለትና ቦታ እንዲካሄድ ወስነው ወደ ባህርዳር አካባቢ መጓዛቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉባዔው ካልታገደ ተኝተን አናድርም ያሉት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት አባላት መምህር አዕመረ አለመኖራቸውን አይተው የመምሪያውን ምክትል ኃላፊ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱን በመወትወትና በማስፈራራት ጭምር አለቃው የወሰኑትን በመሻር የዕገዳ ማስታወቂያ እንዲያወጡ ያዟቸዋል፡፡ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱም ያለአንዳች ማቅማማት የአለቆችን ትዕዛዝ በመሻር ጉባዔው መታገዱን ዓርብ አመሻሽ ላይ ማስታወቂያ የለጠፉ ሲሆን፣ የአዳራሽ ቁልፍ የያዘውን አቶ በሪሁንን ቁልፉን ይዞ ከአካባቢው እንዲሰወር በመንገር ጉባዔ አለብኝ በማለት ወደ ድሬዳዋ ተጉዘዋል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ሆን ብለው ይሁን በአጋጣሚ በሥፍራው ባለመኖራቸው ጉባዔው እንዲካሄድ ማስደረግ ባለመቻሉ አስተባባሪዎች ፕሮግራሙን ለመሠረዝ መገደዳቸው ታውቋል፡፡ የዕርዳታ ጥሪውን በመስማት ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ የተመመው ሕዝብ በርካታ ሲሆን፣ ለምን ይታገዳል በሚል ብሶት ውስጥ ስለነበር ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለሌላ ቀን መተላለፉ በማስታወቂያ እንዲነገረው ተደርጓል፡፡ ታማሚው አቶ እንዳለ ታክሞ ለመዳን የቀረው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ሲሆን እስከ መጨረሻው ሰዓት ከቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ዘንድ በመሄድ "ስለ እግዚአብሔር ብለው አይጨክኑብኝ" ብሎ ቢማፀንም፣ ቀሲሱ ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" ለሚሰጣቸው ድርጎ ልባቸው ተሸንፎ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ቤተክርስቲያን የዕርዳታ እጆቿን ስትዘረጋ ዕርዳታው በአግባቡ እንዳይደርስና የታማሚው ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረግ በኃላፊነት የሚያስጠይቅ ከመሆኑም በላይ አደጋ ላይ ያለን ሰው በቸልተኝነት (ምን አገባኝ በሚል ስሜት) ተገቢውን አለማድረግ ራሱን የቻለ ወንጀል መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ተደንግጓል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ብቻም የሚታለፍ ሳይሆን ቤተክርስቲያናችን ዘርና ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ጾታ ሳትለይ ለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ዕርዳታ የምትሰጥ ከመሆኑ አንፃር የቤተክርስቲያናችንን መልካም ገጽታ የሚያጎድፍ እኩይ ተግባር ነው፡፡ የጉባዔው አስተባባሪዎችም አስፈላጊውን መረጃዎች አሟልተው በቤተክርስቲያን ልጆች አገልግሎቱ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ጉባዔው የሚታገድበት አንዳች ምክንያት አልነበረም፤ የለምም፡፡ በቤተክርስቲያናችን፣ በተለይም "ማኅበረ ቅዱሳን" እንደልብ ጣልቃ እየገባ ማተረማመስ ከጀመረ ወዲህ ሥርዓት ታውኳል፡፡ ማንም ማንንም ከማይሰማበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ቅዱስ ሲኖዶስና የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጁ የሚያስተላልፉት መመሪያና ትዕዛዝ በተራ የበታች ሠራተኞች ይሻራል፤ ይቀለበሳል፡፡ የአቶ እንዳለን ጉዳይ እንደማሳያ ብንቆጥረው የመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትና የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የሰጡት ትዕዛዝ በአንድ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ተሽሯል፡፡ በሪሁን የተባለው የአዳራሽ ቁልፍ ያዥ ቁልፉን ይዞ ተሰውሯል፡፡ ይህ በቤተክርስቲያን የተካሄደ ውንብድና እንጂ አገልግሎት ሊባል አይችልም፡፡ ዓለም በግልፀኝነትና በተጠያቂነት ዘመን ስትራመድ ቤተክርስቲያን ግን ርስ በርስ መጠላለፍ በበዛበት እና የጨለማው ዓለም ተንኮል ተተብትባ ስትታይ ይህንን ትውልድ በእጅጉ ያሰቅቀዋል፡፡ ውሳኔዎች የሚመሩት በእምነትና በሥርዓት መሆኑ ቀርቶ፣ ገንዘብ የዳኝነቱን ቦታ ሲረከብ ማየት ያለንበትን አሳዛኝ ሕይወት ያመላክታል፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረትና ጥበቃው ከእኛ አይለይ!!! አሜን!!! Posted by Dejeselaam at 1:48 AM
source' dejeselaam blog