ጽሁፉን በፒዲኤፍ ማንበብ ከፈለጉ ........>>>To read in PDF click here
ታህሣሥ 9 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው የአራዳው ምድብ ችሎት የዐቃቤ ሕግ አንደኛ ምሥክር ሆኖ የቀረበው መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ችሎቱን ፍጹም ወደ ሆነ መንፈሳዊ ድባብ ለውጦ አስተምሮ መውጣቱን የዜና ምንጮቻችን አረጋገጠዋል፡፡ ዘመድኩን በቀለ በግሉ አርማጌዶን ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ሲዲና ቪሲዲ በማሠራጨት እና የተሳሳተ መልዕክት በማስተላለፍ ምዕመናንን በማወናበዱና በወንድሞች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈቱ በአራዳው ምድብ ችሎት ላይ ክስ የተመሠረተበት ሲሆን እርሱ ራሱ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባል የሆነ ጠበቃ አቁሞ ለመከላከል ሞክሯል፡፡ በዚሁ ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 10፡25 በቆየው የክርክር ሂደት የዘመድኩን ጠበቃ የተልፈሰፈሰ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ ሞክሮ በታዳሚው ሲሳቅበት እንደዋለ እነዚሁ ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡
ጠበቃው ባቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ ቤተክርስቲያንን "አሮጊቷ ሣራ" ብለህ ተሳድበሃል፤ ታዲያ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ጥለው ከሄዱት ከእነ አባ ዮናስ በምን ትለያለህ? ብሎ የጠየቀው ሲሆን፣ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው በሰጠው ምላሽ፣ እናታችን ሣራ በዕድሜ ብታረጅም፣ እግዚአብሔር አከበራት፤ ልጆችን ሰጣት፡፡ እኔም፣ ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት በማገልገል ላይ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች አገልጋዮችን አፍርታለች ነው ያልኩት፡፡ የእኛ ሣራ ልጆችን ወልዳለች፤ የእነ አባ ዮናስ ሣራ ግን ስለመወለዷ አይታወቅም፤ በዚህ እንለያለን በማለት መመለሱ ታውቋል፡፡
መጋቤ ሀዲስ በመቀጠል የቀረበለት ጥያቄ፣ ራስህን በራስህ ሰባኪ አድርገሃል፤ የቤተክርስቲያን ትምህርት ሳይኖርህ ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ዲቁናውን ማን ሰጠህ? መጋቤ ሀዲስ የሚለውንስ ማዕረግ ከወዴት አገኘኸው? የሚል ነበር፡፡ እርሱም በበኩሉ ሲመልስ፣ ዲቁናውን የተቀበልኩት ከብፁዕ አቡነ በርተለሜዎስ የቀድሞው የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ነው፡፡ የስብከት መምህርነት ኮርስም ተከታትዬ የተሰጠኝ የምሥክር ወረቀት አለኝ፡፡ የመጋቤ ሀዲስነት ማዕረጉንም ሰባ ሺህ ያህል ሕዝብ ባለበት የሰጡኝ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በዚያን ወቅት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ናቸው፡፡
መምህር በጋሻው ሌላው የቀረበለት ጥያቄ የእኛ ጌታ ተኝቶ ይገዛል ብለሃል፡፡ ይህ አባባልህ ልክ ነው? የሚል ነበር፡፡ እርሱም ሲመልስ ታዲያ ይሄ ምን ስሕተት አለው? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሲጓዝ፣ ተኝቶ ነበርና ማዕበሉ በተነሳ ጊዜ ሲቀሰቅሱት፣ እምነት የጎደላችሁ ስለምንድርነው አላላቸውም? በከርሰ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ባደረበት ወቅት ዓለምን አልገዛም? ጌታችን፣ አምላካችን በሰው አስተሳሰብ የተኛ ፣ የሞተ ቢመስልም እርሱ ግን ሁሉንም በኃይሉ ይጠብቅ ነበር፤ በማለት መልሷል፡፡ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ሌሎችንም ተጨማሪ ማብራሪያዎችን የሰጠ ሲሆን፣ እርሱ ጥያቄዎችን በሚመልስበት ወቅት ሁሉም ከመመሰጡ የተነሳ የችሎቱ ሂደት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ እስከሚመስል ደርሶ እንደነበር በስፍራው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል፡፡