ሮሜ 13፣7 «ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ»
ክብር ለአንድ ነገር ዋጋ መስጠትን ይመለክታል። ዋጋው ደግሞ በዓይነት፣በገንዘብ፣በጉልበትና
በሃሳብ ወይም በመንፈስ ሊገለጥ ይችላል። የሰው ልጅ በሕይወቱ ዘመን ይህንን ዋጋ ሲከፍል ኖሯል፤ ይኖራልም። ሰው ለፈጣሪውና ለሚያመልከው፤ ለሚበልጠው፤ ለሚወደው፤ ለሚፈራው፤ ለሚመራው ክብርን ይሰጣል። ምናልባት የሚሰጥበት መንገድና የሚሰጥበት ምክንያት ይለያይ እንደሆነ እንጂ ክብርን ስለመስጠት ሃሳብ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ እንዳልሆነ እንስማማለን።
ሰው ፈጣሪው ስላደረገለትና ስለሚያደርግለት ነገር ሁሉ ክብርንና ምሥጋናን ይሰጣል። ክብርን የሚሰጠው ስለተደረገለት ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆኑ ክብር ስለሚገባውም ጭምር ነው።
ነቢዩ ሙሴና ሕዝቡ እግዚአብሔር ከጠላት እንዳዳናቸው ደስታቸውን በዝማሬ ገልጠው ክብር ሰጥተውታል።
«በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ» ዘጸ ፲፭፣፩
ክብሩ ከፍ ከፍ ያለ፣ ኃይልና ሥልጣን በእጁ የሚገኝ፣ ማድረግ የሚፈልገውን ከማድረግ የሚከለክለው ለሌለ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተገቢውን ክብር ሲሰጡ እናያለን። ስለተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን ክብሩ ፍጹማዊ በመሆኑ ለመለኰታዊነቱ ተገቢ ክብር እንደሆነም ሌላ ሥፍራም እንደዚሁ ምሥጋና ሲሰጡ እናገኛቸዋለን።
«በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ» ዘጸ ፳፬፣፲፯
ክብሩ ታላቅና ሰው ሊቀርበው የማይችል መለኮታዊ እሳት ስለሆነ ክብርና ምስጋና የተገባው ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር በቦታና በሥፍራ አይወሰንም፣ መለኮታዊ አገዛዙ ሁሉን የመላ ስለሆነም ጭምር ክብር ይገባዋል። ሁሉን በሙላት መሸፈን የሚችል ያለእሱ ማንም የለምና።