በዚህ ምድር ሳለን እውቀታችን ያች ትንሿ ጭንቅላታችን በሚመጥናት መልኩ የያዘችውን ያህል ብቻ ታውቃለች። ከዚያ በላይ ልሁን ብትልም መስፋት ከምትችለው በላይ አትወጣም። ዓለም ባላት እውቀት የምታውቀው ማወቅ የቻለችውን ያህል ብቻ ነው። የሰው አእምሮ ከምታውቀው በላይ ለመሆን ብትሞክር የእውቀት መቋጠሪያዋ ይበጠስና የያዘችው ማፍሰስ ሲጀምር ሰው ለመባል ያበቃትን ማንነት ትስትና አጠቃላይ እኛነታችንን ወደ ሌላ ምዕራፍ ታሸጋግራለች። ወደ እብደት ወይም ወደ እንስሳት ጠባይዓት ማለት ነው።
አንደኛው የዓለም ጦርነትም ይሁን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻቸው ሰው ካለው እውቀት በላይ ለማምጣት በተመኘ እውቀት የተከሰተ ነው። ምናልባትም ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊመጣ የሚችለውና የከፋ የሚያደርገውም የሰው እውቀት ከማወቅ ጣሪያ በላይ ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ወዳለማወቅ ተሻግሮ የሚጎትተው እብደትና የእንስሳነት ጠባይ መገለጫ ሊሆን ይችላል።
ይህንንም ጥንታውያን አበው«እጅግም ስለት፤ ይቀዳል አፎት»ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲርቅና የተመዘዘው ሰይፍ እንዲመለስ ሲያመለክት እንዲህ ሲል ይነግረናል። «አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፥ ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ ጸጥ ብለህም ዕረፍ » ኤር 47፤6
በምድራችን ላይ የሚታየው የጦርነት፤ የእልቂት፤የእርስ በእርስ መበላላት፤ የበሽታና የረሃብ ክስተቶች ሁሉ የሰው እውቀት ያመጣው ጣጣ እንጂ የፈጣሪ ፈቃድ አይደለም። ምክንያቱም የያዝነው የዘመኑ እውቀት ስለቱ ለመኖርያ የተሰጠውን አፎት ዓለምን እየቀደደ በመገኘቱ ሰው ሰውኛነቱን ወደመካድ እብደትና እንስሳነት እውቀት እየተሸጋገረ በመገኘቱ የተነሳ ነው። እንዲሁም ይህ ሰይፍ ወደሰገባው (አፎቱ) የማይመለሰው የሰው ልጅ ያለው እውቀት እግዚአብሔር እሱን (የሰው ልጅን) እንዴት እንደሚያውቀው ለማወቅ ከመፈለግ ውጪ ስለሆነ ነው። በአጭር አገላለጽ ሰው ስለእግዚአብሔር ያለው እውቀት እሱ ማወቅ የሚችለውንና ለማወቅ የሚፈልገውን ያህል ሲሆን በአንጻሩ እግዚአብሔር ሰውን እንዴት እያወቀው እንደሆነ ለማወቅ አልቻለም ማለት ነው።