ጨለማ አስቸጋሪ ነገር ነው። የሰው ልጆች የሌሊቱን ጨለማ ማሸነፍ ባይችሉ ማየት የተከለከለ የዓይናቸውን ብርሃን ለማገዝ
የተለያዩ የብርሃን ምንጮችን ሰርተዋል። እንደዚያም ሆኖ የሰው ልጆች የብርሃን ምንጮች ጨለማን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አይችሉም። ይልቁንም በእንከንና በችግር የተሞሉ
በመሆናቸው በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ አንዳንዴ በጨለማው ሊሸነፉ ይችላሉ። እንኳን የሰው ልጆች የብርሃን ስሪቶች ይቅርና የሰማይ አምላክ
የፈጠራት የፀሐይ ብርሃን እንኳን ዓለሙን ሙሉ በአንድ ጊዜ እንድትሸፍን ተደርጋ አልተስራችም። ከዚህም የተነሳ በክልል ያልተወሰነ፤
ብቃቱ ምሉዕ የሆነና በጨለማ መተካት የማይችል ብርሃን እስከዛሬ ዓለማችን አልተሰራላትም። ስለዚህ ለዓይናችን
የሚታየው የብርሃን ምንጭ ውሱንነት የዚህን ያህል ግልጽ ከሆነ በሰዎች ውስጣዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን የማንነት ብርሃን ከጨለማ ማውጣት
የሚችል ማነው?
ይህንን የሕይወት ጨለማ፤ በብርሃን መሙላት የሚቻለው
ከሰው ልጆች መካከል አንድም ቅዱስና ጻድቅ የሆነ፤ ከሰማያት መላእክት መካከል ማንም የለም። ይህንን የሰው ልጆች ሕይወት በጨለማ ውስጥ ከመኖር ወደብርሃን መቀየር የግድ
ያስፈለገው ጉድለቱን መሙላት የሚችል ባለመኖሩ ነበር። እሱም ጨለማ የማያሸንፈው፤ ብርሃኑን ለተቀበሉ ሁሉ በውስጣቸው ዘላለማዊ ብርሃን
ማኖር የሚችል፤ የብርሃናት ሁሉ ጌታ ለመሆን የተገባው መገኘት ነበረበት። በጨለማ የሚሄድን ሕዝብ ወደብርሃን እንዲመጣና በሞት ጥላ
ስር የወደቁ ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወትን እንዲያገኙ፤ ነፍስና ሥጋን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር ሌላ ማን ይችላል? ፍጹም የሆነ መታመኛ እርሱ
ብቻ ነውና! ዳዊት በዝማሬው « እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው» እንዳለው መዝ ፳፯፤፩ ይህንን የሕይወት ጨለማ በብርሃን መግለጥ
የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነበር።
የሰው ልጆች ብርሃን የጨለማ ዓለምን በሙላት መግለጥ የማይችል
ከመሆኑም በላይ የነፍስን ጨለማ ደግሞ በብርሃን መሙላት ይችላል ተብሎ ስለማይታሰብ፤ መታመኛ ብርሃን የሆነው እግዚአብሔር፤ ከዘላለማዊ ብርሃኑ የወጣ ብርሃን፤ ከአምላክነቱ
የወጣ አምላክ፤ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፤ ጨለማን በመግለጥ ብርሃንን የሚሰጥ፤ በሞት ጥላ ስር ላሉ ሕይወትን የሚያድል፤ አንድያ ብርሃን ልጁን ለጨለማው
ዓለም ላከ። ይህም ብርሃን ወደዓለም መጣ።
«በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ» ዮሐ ፲፤፵፮ በማለት እውነተኛው ብርሃን እንደተናገረው።
ይህ ብርሃን ወደዓለም የመጣው ጨለማውን ዓለም በማይጠፋ ብርሃን ሊሞላ ነው። በሞት ጥላ ስር ላሉትም ሕይወትን ሊሰጥም
ጭምር ነው።«በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው» ኢሳ 9፤2 እንዳለው። የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለዓለሙ ሁሉ ሆነ።
«ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥
የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» ኢሳ ፱፤፮