Tuesday, April 22, 2025

“እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” ቆላስ 1፥13-14

"ለእኔ ኃጢአት ሥርየት ከሞተልኝ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ቤዛ የለኝም" “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” — ቆላስይስ 1፥13-14 ቤዛ የሚለውን ቃል አባ ገብርኤል የተባሉ ሊቀጳጳስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ብለው ለምን ተናገሩ? የሚል ንትርክ ተነስቶ በኦርቶዶክሶች መንደር ጩኸቱ በርክቷል። ይሄ ቤዛ በእንግሊዝኛው/ransom,redemption,deliverer/ በማለት ሲተረጉመው ግሪኩ ደግሞ (λύτρον)ሉትሮን ማለት የተከፈለ ዋጋ፣ (λύτρωσις) ሉትሮሲስ ነፃ መውጣት፣ ከእስራት፣ ከባርነት ለመፈታት የተሰጠ ክፍያ፣ ነጻነት ማለት ነው። የጌታችን፣ የመድኃኒታችንና የአምላካችን ቤዛነት ከየትኛው ምትክነት፣ ነጻ አውጪነት፣ አዳኝነትና ከሞት ታዳጊነት ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም። በዘመነ ኦሪት በባርነት የተሸጠ ሰው ለባርነቱ ዋጋ የሚከፍል ከተገኘ ነጻ ሊወጣ ይችላል። ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው። ምሳሌ13፣8 የመሳሰሉ ስለቤዛ የተነገሩ የቤዛ ቃል ንግግሮች በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ተፅፈው እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ የቤዛነት ትርጉሞች ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረገልን ቤዛነት ጋር ለክርክርም፣ ለንጽጽርም፣ ለትርጉም አቻነት የሚቀርቡ አይደለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከዘላለማዊ ድኅነት፣ ከአብ ጋር እርቅ የተደረገበት፣ መርገመ አዳም የተወገደበት፣ የገነት በር የተከፈበት ስለሆነ ከሰማይ በታች የተነገሩ፣ የተጻፉ፣ የተወሩ ስለቤዛ የተተረጎሙ ቃላት፣ ሃሳቦች ለንጽጽር ሊቀርቡ አይችሉም። በእውቀት ለመገራትና ለመመራት እምቢተኛ አእዱገ ገዳም የሆኑ የኦርቶዶክሶች ምእመናን፣ በተረት ተረት ትምህርት ሊቅ የሆኑት ዘበነ ለማ፣ አዋቂ መስሎ ለመታየት ብዙ የሚደክመው ኄኖክ ኃይሌ፣ ክንድ ከስንዘር መስቀል ጨብጠውና አንጠልጥለው ብዙ የሚያጓሩ፣ የተለሰኑ መቃብር መምህራን፣ ቀሳውስትና መነኮሳት ነን ባዮች የጌታችን፣ የመድኃኒታችንና የአምላካችንን ቤዛነትን ከሌሎች ቤዛነት ጋር ለማነጻጸር ወይም ስለቤዛነት የተነገረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይደለም ለማለት ከሰሜን ዋልታ እስከ አንታርክቲካ ሮጠው ያልቆፈሩት ጥቅስ፣ ያልዘበዘቡት ፅሑፍ፣ ያልተረተሩት ትርጉም፣ በእልህና ብስጭት መንጋጋቸው በመንጋ ያላፋጩት ጥርስ የለም። በየፌስቡኩ፣ ቲክቶኩና በየድረገጾቹ ላይ የታየው ጩኸት ተአምር የሚያስብል ነው። እነዚህ ስብስቦች ከኛ ወዲያ እውቀት ላሳር ነው ብለው የአእምሮአቸውን በር የዘጉት ድሮ ነው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተነጋግሮ መተማመን ላይ መድረስ አይቻልም። አንዳንዴማ ከእኛ በስተቀር የሚጸድቅ የለም ብለው በድፍረት ሲናገሩ መንግሥተ ሰማያት በር ላይ ቆመው አንተ ተመለስ፣ አንተ ግባ ብለው የማዘዝ ስልጣን ያላቸው ያህል ያስባሉ። መንግሥተ ሰማያት የፍትሐት ድግስ የሚበሉበት የደጀሰላም በር ይመስላቸዋል። ለነገሩ አይሁድ ፈሪሳውያን መምህራንና ጻፎችም እንደዚሁ ያደርጋቸው ነበር። እነዚህን መሰል ሰዎች ጌታ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲላቸው እናገኛለን። (ማቴ23፣27-32) እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። ብሏቸው ነበር። እነዚህኞቹ ወደመንግሥተ ሰማይ ወይ እነሱ አይገቡ፣ ወይ ተከታዮቻቸውን አያስገቡ መንገዱን በተረትና እንቆቅልሽ ስብከት ዘግተውታል። በዚያ ላይ እውቀት አለርጂክ የሆነበት ተከታያቸው ምዕመን በጩኸት ስለሚያጅባቸውና አዋቂ ነን ብለው ስለደመደሙ ከእነሱ የተለየውን ቃል እውነት ቢሆን እንኳን አይቀበሉም። ምእመኖቻቸውም ከመምህራኖቻቸው የባሱ ስለሆኑ ያንኑ የአለቆቻቸውን ትምህርት መልሰው ይጓራሉ። ይጮሃሉ። ማርያም ቤዛ ናት፣ ገብርኤል ቤዛ ነው። ገንዘብ ቤዛ ነው። ወንድምህ ቤዛ ነው፣ ጓደኛህ ቤዛ ነው የሚሉ ቃላትን ለቃቅመው በማምጣት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ጋር ለንጽጽር፣ ለትርጉምና ለማብራሪያ በማቅረብ ይንጫጫሉ። አንዳንዴ ስትመለከታቸው ክርስቲያን የሚለውን መጠሪያ አምኖ ለመቀበል እስኪከብድህ ድረስ አንደበታቸውና ጽሑፋቸው ልቅ ነው። እነዚህ ተጯጯኺዎች በዘመቻ የተነሱት የቤተክርስቲያኒቱ ጳጳስ አባ ገብርኤል የተባሉት ሰው "ተቀዳሚ፣ ተከታይ የሌለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻውን የዘላለም ቤዛ ነው" ብለው ስላስተማሩና ማርያምም የዘላለም ቤዛችን አይደለችም ስላሉ ነበር። የዚህን ትምህርት ቃል ለማፍረስና ሌሎችም ቤዛ አሉን ለማለት ያልቆፈሩት የሙግት ትርጉምና ጥቅስ የለም። ዘቤ የተረት አባት በአንድ ወቅት "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" ብሎ ሲያስተምር ነበር። ማርያም ማዳን ከቻለች የኢየሱስ ሰው ሆኖ መምጣት ሳያስፈልግ በማርያም ይፈጸም አልነበረም ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ እነዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም ማለት ስህተት ነው ብለው ለማረም ቢሞክሩም ዘቤ የተረት አባት ስህተቱን ሳያምን ዛሬም በተመሳሳይ ስህተት ላይ ይገኛል። ዘበነ ለማን ያክል ቤተክርስቲያኒቱን በአስተምህሮ ስህተት የገደለ ማንም የለም። እነኄኖክ ኃይሌ ላይገባቸው የማሉ ያህል የሚከራከሩት ስለቤዛነት የተሰጠው ትርጉም ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ማርያምን ይጨምራል፣ ሌሎችን ብዙዎችንም በተጨማሪነት ያጠቃልላል ብለው ለመከራከር ሲንደፋደፉ አይተናል። እዚህ ላይ አስረግጠን የሊቀጳጳሱን ትምህርት የተቀበልነውና ስለኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትና ቤዛነት ያስተማሩት ትክክል ነው ያልነው ጳጳሱን በተለየ ስለወደድን ሳይሆን ያስተማሩት እውነት ስለሆነ ነው። ለእውቀት አእዱገ ገዳም ለሆኑት ሰዎች የምንነግራቸው ነገር ስለቤዛ የተጻፈና የተነገረ አንድ መቶ ሺህ ጥቅስና ትርጉም ቢኖራችሁ ለንጽጽር የማይቀርብበት የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ብቸኛው ነው። የወደቀውን የሰው ልጅ ወደቀደመ ክብሩ ለመመለስ፣ ለበደለው ኃጢአት የተሰጠ ሥርየት፣ የተከፈለ የሞት ዋጋ ምትክ የሆነው ቤዛነት የኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ይሄንን የሚተካ፣ የሚያክል፣ የሚወዳደር፣ የሚቤዥ ሌላ ቤዛ ከሰማይ በታች የለም። ይሄ ቤዛነት ትልቅነቱ ዘላለማዊ፣ መድኃኒትነቱ ሕያው፣ አዳኝነቱ ሞት ያላሸነፈው ነው። ስለቤዛ በትርጉምም፣ በፍቺም በንፅፅርም ከኢየሱስ ቤዛነት ጋር ሊቀርብ የሚችል ሌላ የለም። ስለቤዛ የተነገረ ሌላ ቃል አለ ብለህ ጭንቁር የቃል ክርክር ታቀርብ ይሆናል። ያንን እያነሳህ እንደዚህ ማለት ነው፣ እንደዚያ ማለት ነው እያልክ ውሃ ወቀጣ ክርክር የማንሳት መብት ይኖርሃል። የጻፎችና የፈሪሳውያን ክርክር የወንጌል እውነት ሊቀይረው እንደማይችለው ሁሉ የትኛውም ስለቤዛ የሚሰጥ፣ የተሰጠ ትርጉምና ንጽጽር ጌታችን ካደረግልን ቤዛነት ጋር አይነጻጸርም፣ ለትርጉም ክርክር ሊቀርብ አይችልም። ለነዚህ የተለሰኑ መቃብሮች የምነግራቸው በኔ በኃጢአተኛው ምትክ ቤዛ ሆኖ የሞተ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ ቤዛ ማንም የለም ነው የምንላቸው። ቅድስት ማርያም ቤዛ ናት የሚሉ ሰዎችን ታድናለች ወይ? ተብለው ሲጠየቁ አታድንም፣ ግን መድኃኒትን ወልዳልናለች፣ ስለዚህ ቤዛ እንላታለን ይሉናል። በምትክነትና ለኃጢአት ሥርየት እንዳልሞተችልን ከታወቀ በመጽሐፍ እንደተፃፈ "የጌታ እናት" ማለታችን በቂ አይደለም ወይ፣ ባልተፃፈ የቤዛነቷ ትርጉም ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክር ለምን ያስፈልጋል? ሲባሉ ጴንጤ፣ ከሀዲ፣ ጸረ ማርያም የሚሉ ስድቦቻቸውን በእውቶማቲክ ይተኩሳሉ። እነዚህ ለእውቀት አእዱገ ገዳም የሆኑ ሊቀ ሊቃውንትና መተርጉመ መጻሕፍት ነን ባዮች በማርያምም፣ በኢየሱስም ሁለት አዳኝ እንዳላቸው ለጎጋ ምዕመኖቻቸው ያለከልካይ እየጮሁ መገኘታቸው ስናይ በነሱ ዘንድ ኢየሱስ ሌላ ብዙ ቤዛ እንዳላቸው እንረዳለን። አሁንም ደግመን እንላለን፣ ለአዳም ልጆች ቤዛ ሆኖ የሞተና ያዳነን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ቤዛ የለንም። ስለቤዛ ሚሊየን ትርጉም ቢኖርህ እሱን እያመነዠክ መኖርህ የኢየሱስን ብቸኛ ቤዛነት አይቀይረውም። የኢየሱስን ቤዛነት አምናለሁ ያለ ሰው በኢየሱስ ብቸኛ የቤዛነት ሥራ ላይ ሌላ ትርጉምና ንጽጽር ለምን ይዞ ሊመጣ አይችልም። የሚመስለው፣ የሚተካከለው፣ የዘላለም የሆነ ቤዛነት ከኢየሱስ ውጪ አለ? የለም!!! አዎ! እናውቃለን፣ የኢየሱስን ዘላለማዊ የቤዛነቱን ሥራ በፍጡራንና በምድራዊያን የትርጉም ቃላት ሸፍኖ ለማሳነስና ሰው ሁሉ ወደአንድያ ቤዛው ዓይኑን እንዳያነሳ ለመጋረድ ጠላት በስንዴው መካከል የዘራው እንክርዳድ ነው። እኛ ግን በየትኛውም የቤዛ ትርጉም ሳንወጣ፣ ሳንወርድ፣ ሳንደክም "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” እንላለን። ቆላስይስ 1፥13-14 ሊቀጳጳሱ ስለኢየሱስ ብቸኛና ዘላለማዊ ቤዛነት የተናገሩት ትክክል ነው። ከፍጡራን መካከል ሌላ የዘላለም ቤዛ የሆነልን፣ መሆን የሚችልም የለም። ከሰማይ በታች ቤዛ መሆን የሚችል ስለሌለ ነው አብ አንድያ ልጁን የላከልን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር!