Saturday, December 21, 2024
ታቦትም ጽላትም ዛሬ የሉም!
ታቦትና ጽላት ዛሬ የሉም!
በዚህ ርዕስ ላይ ብዙ ጊዜ ፅፈናል። አብዛኛው ሰው የሚያምነው የነገሩትን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተፃፈውን ባለመሆኑ ዛሬም ስለታቦትና ጽላት ሲከራከር ይውላል። ስለታቦትና ጽላት ምንነትና እንዴትነት ከመናገራችን በፊት አንድ ነገር በመጠየቅ ልጀምር። አንድ ሰው ናይሮቢ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነው ቢላችሁ መልሳችሁ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጠኝነት መልስ ከመስጠታችሁ በፊት ፊቱን በደንብ ታዩታላችሁ፣ ፈገግ ልትሉ ትችላላችሁ፣ ምን እያልክ ነው ብላችሁ መልሳችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ከመቼ ወዲህ? ልትሉትም ትችላላችሁ። ምክንያቱም ናይሮቢ ከኬንያ ዋና ከተማነት ተዛውሮ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆኖ የተቆጠረበትና ሊሆን የሚችልበት እድል ስለሌለ ጠያቂያችሁ እያሾፈ ወይም እየቀለደ እንደሆነ መገመታችሁ የሚጠበቅ ነው። አብዛኛው ሕዝብ የሚረዳው እውነት ናይሮቢ የኬንያ ዋና ከተማ እንጂ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አለመሆኑን ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ ይሄ የተረጋገጠ እውነት ነው።
እንደዚሁ ሁሉ ከእስራኤል ውጪ ታቦትና ጽላት ነበረኝ ወይም አለኝ የሚል ሁሉ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነው ብሎ የሚናገርን ሰው ይመስላል። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እየነገራችሁና እንደሆነ እየመሰከረላችሁ መሆኑ ነውና።
እኔ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከአህዛብ መካከል ከመረጣቸው ከእስራኤል 12ቱ ነገድ አንዱ ነኝ፣ በኮሬብ ተራራ የኪዳኑ ፅላት ሲሰጥ ነበርኩ፣ ከ40 ዓመት በኋላ ርስት ምድርን ዘመዶቼ በኢያሱ እጅ ሲወርሱ ድርሻ መሬት አግኝቻለሁ፣ ኢየሩሳሌም የንጉሡ ከተማ ከተማዬ ነበረች፣ ሥርዓተ ቤተ መቅደሱ ሲፈፀም እስከናቡከደነጾር ውድመትና ዘረፋ ድረስ እዚያው ሳከናውን ነበርኩ። ወገኖቼ ለ70 ዓመት በባርነት ባቢሎን ሲወርዱ ነበርኩ። በሄሮድስ ዘመን ቤተመቅደሱ ተሰርቶ ሥርዓተ ታቦቱ ባይፈፀምም እየሄድኩ እጸልይ ነበር። በአጭር ቃል እኔ ከተመረጡት ከእስራኤል ወገን እንጂ ከአህዛብ አይደለሁም እያላችሁ ነው። ከዚህ ሰው ጋር ስለታቦትና ጽላት አሰራርና ሥርዓት ጋር መነጋገር የምትችሉት በመጀመሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት ስትችሉ ብቻ ነው። የታቦትና የጽላት ሥርዓት እንኳን የካም ነገድ እንደሆነ በሚነገርለት በአፍሪካ ይቅርና የሴማውያን ድንኳን መገኛ በሆነችው በኢየሩሳሌምም ዛሬ የለም። ባልተመረጥክበት፣ የተለየ ኪዳን ባልተቀበልክበት፣ የመቅደሱ አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ ራስህን በራስህ ስትመርጥ ማድረግ የምንችለው ነገር ጤንነትህን በመጠራጠር ወደምታምንበት ፀበል ሂድ እንልሃለን እንጂ ላንተ ታቦትና ጽላት የምንደፋበት ምንም ምክንያት ሊኖረን አይችልም።ምክንያቱም እኛ በመንፈስ ቅዱስ የታተምን ጤነኞች ስለሆንን ለበኣል መሰዊያና ለማመለኪያ አጸድ የምናፈነድድበት ዜሮ ምክንያት የለንም። እነዚህ ሰዎች ተረፈ ምናሴ ናቸው። ምናሴ የተባለ የይሁዳ ንጉሥ እንዲሁ አድርጎ ነበር።
"ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቆመ። ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።" (2ኛ ነገ 21፣8-9)
ሊቁ የተረት አባት ዘበነ ለማ በአንድ ወቅት "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" ብሎ ያስተምር ነበር። ከወገኖቹ በኩል ወቀሳ ሲበዛበት እንደዚህ ብሎ የማስተማር ጩኸቱን ቢቀንስም በትምህርቱ የተበከሉት ግን ዛሬም ድረስ "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" የሚለው ስሁት ትምህርት ስር እንደሰደደ አለ። የተረት ሊቁ ዘቤ ለማ ታቦትና ጽላት የወረስነው ከሙሴ ሥርዓት ነው የሚለው ጩኸቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። የታቦት ቁመቱ፣ ርዝመቱ፣ ክብደቱ፣ አሸካከሙ፣ አቀማመጡ፣ ጽላቱ ላይ ምን ተጻፈ፣ ማን ጻፈ፣ ወዘተ የሚለው ጥያቄ ለደፋሩ ዘቤ ጉዳዩ አይደለም። የመናገር እድልና ሥፍራ ስላገኘ የስህተት መርዙን መርጨት ለሱ የተሟላ እውቀት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ በግልጽ ቋንቋ የዘበነ ለማን አስተምህሮ የሚቃወም ትምህርት ሲሰጥ ሰምቸዋለሁ። ትምህርቱ የተሟላ ባይሆንም በትክክል ያንፀባረቀው አቋም ግን ይበል የሚያሰኝ ነው። የኦሪቱ ታቦትና ጽላት ዛሬ የለንም ብሏል። ይሄ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አይደለም ብሎ ሀቁን እንደመመስከር ይቆጠራል። ነገር ግን የተጓደለው ነገር ቢኖር በቤተመቅደሱ ውስጥ መስዋእት እንሰዋበታለን በማለት የተናገረው የተሟላ መልስ አይደለም። ሲጀመር እሱ ከኦሪቱ ኪዳን ጋር በተመሳሳይ ስም ጽላት መባል የለበትም። በሌሎች አብያተክርስቲያናት እንደሚደረገው ለምሳሌ በግብጽ ኦርቶዶክስ ጠረጴዛ፣ መሰዊያ ተብሎ ይጠራል። ከዚያ ባለፈ ተሸክመውት መንደር ለመንደር አይወጡም፣ ገብርኤል ጡጦስ፣ ጣንጦስ፣ ኤፈራንጦስ እያሉ ሕዝቡን በጻድቅ ስም አያደነዝዙበትም። በእልልታና በጩኸት አያሰግዱትም፣ ይቀስፍሃል፣ ይሰነጥቅሃል እያሉ አያስፈራሩበትም። አይሸጥም፣ አይለወጥም። የኢትዮጵያው ግን ምናሴ በእግዚአብሔር ቤት ከፈፀመው አምልኮ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚህ ዘመን የተሰረቀው ታቦት በተለይም ብዙ ዘመን የቆየው ከተገኘ ብዙ ዋጋ እንደሚያወጣ ይታወቃል።
ስናጠቃልል፣
ኢትዮጵያ እስራኤል አይደለችም፣ ሆናም አታውቅም። ኪዳን አልተሰጣትም፣ ታቦትም ጽላትም የእርሷ አልነበረም። የአህዛብ ሀገር ነበረች። ክርስትና እንዴት እንደገባ ራሷ በምትተርክበት ታሪክ በፍሬምናጦስ በኩል አብርሃና አፅብሃ የመጀመሪያውን ክርስትና መንግሥታዊ ሃይማኖት አድርጋ ተቀበለች። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኦፊሴል መናገር ያለባት የኦሪቱ ታቦትና ጽላት የለኝም፣ አሁን ያለው መሰዊያ ወይም መስዋእት ማቅረቢያ ጠረጴዛ እንጂ የተለየ አምልኮ፣ ስግደትና ምስጋና የሚቀርብለት ነገር አይደለም ብላ ማወጅ አለባት። መሰዊያ የቀረበበትን ማክበር እያለች 365 ቀን በሙሉ ሕዝቡን ማሰገድ ትክክል አይደለም። ሕዝቡ መስዋእቱን ከመብላት ይልቅ የመስዋዕቱን መክተፊያ ይዞ በመውጣት ሕዝቡን በእልልታ፣ በዝማሬ፣ በቅኔና በስግደት ማሳሳት ወንጀልም፣ ኃጢአትም፣ ክህደትም ነው። ሕዝቡ የእግዚአብሔር ታቦት ይህ ነው ብሎ ያምናል። ለዚህ ታቦት ሲል ለመግደልም፣ ለመሞትም አይመለስም። እንደእውነቱ ከሆነ የሕዝቡን አእምሮ በዚህ መልኩ ቀፍድዶ በማሰር ወደሞት ከመንዳት የባሰ ከዚህ በላይ ጥፋት የለም። እውነቱ ግን እግዚአብሔር አብ ለኛ የሰጠን መዳኛችን፣ ጽላታችን፣ አምልኮና ስግደታችን በኢየሱስ በኩል እንጂ በቁሳቁስና ሰዎች ባዘጋጇቸው ምናምንቴ ሥርዓቶች በኩል አይደለም። ዓይናችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነቅለን ወደሌላ ወደማንም ለመዳን አናማትርም። ሌላ መንገድ በጭራሽ የለምና ነው።
የታቦት፣ የጽላት፣ የተክልዬ፣ የአቦዬ፣ የሳምርዬ፣ የክርስቶፎሎስ፣ የአርሳዲ፣ የፈለቀች፣ የዘነበች፣ የአርሴማ፣ የንፍሮ፣ የዳቦ፣ የአፈር፣ የአመድ የሚባል የመዳኛ ዘዴ እና 20 እና 30 ትውልድህን የሚያስምር መንገድም፣ ኪዳንም ከሰማይ በታች ሌላ ስም በጭራሽ የለም።
“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”
— ዮሐንስ 14፥6 የተባልነው ይህንን ነው። የምንድነው፣ የዳንነው በዚህ ስም ብቻ ነው።