Wednesday, January 17, 2024
“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ሐዋ 4፥12
አዳም ከአምላኩ ትዕዛዝ በወጣ ጊዜ፣ ከሔዋን ጋር ከገነት ተባሮ አሜከላና እሾህ ወደምታበቅለው ምድር መጣሉን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። ዘፍ 3:1—24
ይህ የአዳም በደል ከእሱ በተወለዱ ዘሮቹ በሙሉ በውርስ ሲተላለፍ ኖሯል። ከሰማይ ከወረደው ሁለተኛው አዳም/ ኢየሱስ/ በቀር ያለ ውርስ ኃጢአት የኖረ ማንም አልነበረም። የኢየሱስም ከሰማይ ወርዶ ሰው የመሆን ምስጢሩም የሚነሳው፣ የአዳም ዘር በሙሉ በሞት ፍርድ ሥር ያለ በመሆኑ ከሥጋ ለባሽ አንድም ሰው ዘሩን ነጻ ማድረግ ስለማይችል ነበር። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ አስረግጦ ሲያስረዳ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንደዚህ ብሎታል።
“ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ሮሜ 5፥12
ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል "ወልድ" በሥጋ ሰብእ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ከኃጢአት ብቻ በቀር አዳማዊ ባህርይን ተዋሕዶ ሰው ሆነ። አዳምንና ልጆቹን ከዘላለም ሞት ማዳን የሚችለው ከኃጢአት ነጻ መሆን የቻለ ብቻ ስለነበር ኢየሱስም የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ለኃጢአተኞች ነጻ መውጣት የአብ መስዋእት ሆኖ ቀረበ።
“በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።”ዮሐ 1፥29
ይህ የዓለምን ኃጢአትን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ካልቪኒስቶች ለዓለሙ ሁሉ አልሞተም ይላሉ) መስቀል ላይ ውሎ የኃጢአት ሥርየት እርሱ መሆኑን አምነው፣ በስሙ ለተጠመቁና እስከመጨረሻው እምነታቸውን አጽንተው ለተጠበቁ በሙሉ እንጂ ለተወሰነ ዘር፣ ነገድ፣ ጎሣ፣ ብሔር ወይም ለተወሰነ ወገን የተፈፀመ ማዳን አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሞት ወደዓለም በአንዱ አዳም በኩል ለሁሉ እንደደረሰ ሕይወት ደግሞ በአንዱ በኢየሱስ በኩል ለተቀበሉት ሁሉ ሆነ በማለት ያስረዳናል።
“በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።”
ሮሜ 5፥17
እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደዓለም የላከውና ለመስቀል ሞት የታዘዘው የአዳም ዘር በሙሉ በእርሱ አምነው እንዲድኑበት እንጂ የተወሰነ ቡድን ወይም በምርጫ ለተለየ ወገን ለይቶ ለማዳን አይደለም።
በዚህ ዘመን ጆን ካልቪን የተባለ የ17ኛው ክ/ዘመን የተነሳ የአዲስ ሃይማኖት አስተማሪ ደቀመዛሙርት ነን የሚሉ በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ክሂዶትን አጠናክረው በመቀጠል ኢየሱስ የሞተልን ለእኛ ለተመረጥን፣ አስቀድሞ ለተለየንና ለተጠራን ብቻ እንጂ ለአዳም ልጆች ሁሉ ኃጢአት አይደለም እያሉ በታላቅ ድፍረት ሲናገሩ ይደመጣሉ። ብዙዎችንም እያሳቱ ይገኛሉ።
በመጥምቁ ዮሐንስ የተመሰከረልንና "የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" ዮሐ 1:29 የሚለው ቃል በካልቪኒስቶች አስተምህሮ "ለኛ ለተመረጥነው እንጂ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም" በሚለው መቀየር አለበት
እንደማለት ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ በአዳም አለመታዘዝ ሞት ለሁሉ እንደደረሰ፣ በአንዱ በኢየሱስ መታዘዝ ሕይወት ለሁሉ እንደበዛ እንዲህ በማለት ይነግረናል።
“በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” ሮሜ 5፥19
ከእኛ ከኃጢአተኞቹ የሚጠበቀው እግዚአብሔር በልጁ ሞት እንዳዳነን፣ ሕይወትም እንደሰጠን ማመንና መቀበል ብቻ እንጂ ከእኛ በሆነ ሥራ አይደለም።
"ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም" ኤፌ 2:8—9
ነገር ግን ካልቪኒስቶች ሥራም፣ እምነትም፣ ማወቅም፣ መረዳትም፣ ማመንም ሳይጠበቅብን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተመረጥነውና የተለየነው እኛ ብቻ /predestination/ የተሰጠን ስንድን ለሲኦል የተዘጋጁት ደግሞ ያልተመረጡና አስቀድሞ
የተፈረደባቸው ናቸው በማለት አምላካዊ ምህረቱን ለግላቸው በመውሰድ በሌሎች ላይ የፍርድ ቃል በድፍረት ሲናገሩ አይሰቀጥጣቸውም። ይህ አባባላቸው ኢየሱስ የተሰቀለው አስቀድሞ ለተመረጡና ለተወሰኑ ሰዎች እንጂ በእርሱ አምነው ለሚመጡ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም ለማለት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ቦጭቀው ሲጠቀሙ ይህንን ይጠቅሳሉ።
“አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።”
ሮሜ 8፥30
ይሄንን ቃል ሲያብራሩ እኛ /ካልቪኒስቶቹ/ ራሳቸውን ማለታቸው ነው። አስቀድሞ እንድንድን የተወሰነልን ነን። ከእንግዲህ የትኛውንም ኃጢአት ብንሰራ አንጠፋም። አስቀድሞ በተሰወነልን መሠረት የጠራን አንዴ ልጆቹ አደረገን። አፅደቆም በሰማይ አከበረን ይላሉ።
ከዚህ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ክህደት ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደረጋቸው ሰይጣናዊ ትርጉም ሁለት መሰረታዊ ነገርን ከመሳት የመጣ ነው። እሱም፣
1/ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ወደሰውኛ እውቀት ማውረድና
2/ የእግዚአብሔርን ምሕረትና የይቅርታ ሚዛን አለመረዳት ናቸው።
እግዚአብሔር አምላክ የማያውቀውና የተሰወረበት ምን ምስጢር አለ? እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበትና ዓለማትን ከሚያሳልፍበት ሁሉን ቻይነቱ፣ የሉዓላዊነት ሥልጣን ውጪ የሆነና መሆን የሚቻለው አንዳችም ፍጥረት የለም። ይህም የእግዚአብሔር የሁሉን አዋቂነቱ /Omniscient/ እና የከሃሌ ኩሉነት /Omnipotent/ በራሱ አምላካዊ ባህርይው የሚገኝ ነው። ከዚህ ተነስተው እነዚህን ጥያቄዎች ብናነሳ የምናገኛቸው ትክክለኛ መልሶች ያሉት በእርሱ ዘንድ ብቻ ናቸው። የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ስንት ሰው ተወልዷል፣ በፆታ ስንቱ ወንድ ስንቱስ ሴት ነው? ስንትስ ሰው ሞቷል፣ ስንት ሰውስ በሕይወት አለ? ስንቱ ገነት ገባ? ስንቱስ ሲዖል ወረደ? የሚሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ይህንን በትክክል የማወቅ ኃይሉ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። በዚህም እግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂ አምላክ እንለዋለን።
“ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” መዝ 103፥14
“የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።”ዳን 2፥22
የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት ካልቪኒስቶቹ ራሳቸውን ከፀደቁት ጎራ ጨምረው እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የፈረደባቸውንና በሰማይ ያፀደቃቸውን ስለሚያውቅ እኛን ከፀደቁት አድርጎ አስቀድሞ ወደፅድቁ ስለጨመረን ኩነኔ የሚባለው ነገር አይመለከተንም እያሉ በአስቀድሞ መወሰን/Predestination/ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ።
እግዚአብሔር ሁሉንም አዋቂ ነው ማለት ጄምስን ኮንኜዋለሁ፣ ገብረማርያምን ደግሞ አፅድቄዋለሁ ብሎ አስቀድሞ ውሳኔ የሰጠበት ሰው የለም። እንደዚያ አስቀድሞ ከተወሰነ የኢየሱስ ሰው መሆን ለምን አስፈለገ? ለምንስ ተሰቀለ? እምነትስ ምን ሊጠቅመን? እምነትንስ በሥራ መግለፅ ምን ሊጨምር? አስቀድሞ ለፅድቅ የተወሰነ ሰው ስለኃጢአት የሚከፈል ዋጋስ ለምን አስፈለገው?ቢከፈልለትም ሆነ ባይከፈልለት አስቀድሞ የተወሰነለትን ከመቀበል የሚያግደው ነገር ምን አለ?የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሳ መሆን የሚገባቸው ትእይንቶች/ ትርኢቶች/ እንጂ በመሰረታዊ የሰው ልጆች የመዳን መንገድ ላይ ትርጉም የሌላቸው ሆኖ እንዲታዩ የሚያደርግ ነው። ውሳኔው ቀድሞ ስለተሰጠ መዳኑ አይቀርበትም። ቀራንዮ ላይ የተፈፀመው ስቅለት አስቀድሞ የተነገረለትን ለማሳየት የተደረገ ትርኢት ነው ማለት ነው።
ይህ የጆን ካልቪን ትምህርት አደገኛና የእግዚአብሔርን ፍፁም የሆነ ፍቅር በመሻር ሰው የሚፈረድበት በራሱ ምርጫ ሳይሆን ለሲዖል እሳት እንደማገዶ እንጨት አስቀድሞ አዘጋጅቶት የነበረውን ሰው ወደእሳት በመወርወር የሚደረግ ድምዳሜ እንጂ በማመኑ ወይም ባለማመኑ የሚደረግ ፍፃሜ አይደለም የሚል ክህደት ነው። ይህም እግዚአብሔር ሰው በምርጫው እንዲወስን ነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ አልሰጠውም የሚል አምላክን እንደጨካኝ ገዢ የሚስል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ዮሐንስ በራእዩ የጻፈልን ቃል፣
"ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።
አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ"ራእይ 22:11—13
የሚለው ቃል አስቀድሞ በተወሰነ ነገር ላይ ዝም ብሎ የተጻፈ እንጂ ፅድቅም፣ ርኩሰትም በማድረግ እንደሥራው የሚባል ክፍያ የለም እያሉን ነው ካልቪኒስቶቹ።
የጆን ካልቪን ክሂዶተ እምነትና አስቀድሞ የመወሰን /predestination/ ስህተቶች በ5 ነጥቦች የተመደቡ ናቸው።
1/ Total Depravity/ የሰው ልጅ ከውድቀት በኋላ በጭራሽ ጻድቅ መሆን አይችልም የሚል ነው።
ይህ የስህተት ትምህርት በአዳም ስህተት የተላለፈው ውድቀት የሰውን ልጅ ከነአካቴው የክፋት ሁሉ ባለቤት ነው ብሎ በሰው ጆሮ የሚያንቃጭል የሰይጣን ውንጀላ ሲሆን ሰው ሁሉ እኔን መስሏል የሚል ሰይጣናዊ ድምፀት ያለበት ክስ ነው። ከውድቀት በኋላ ለአዳም ልጆች ሁሉ የተላለፈውን ሞት የሚያስቀር የጽድቅ ሥራና ወደወጣበት ገነት የሚመልስ ማንነት በሥራው አያገኝም ማለት፣ ሰው በጎነት፣ ደግነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር፣ የጽድቅ ሥራ መፈፀም አይችልም ማለት
አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ ተግባር የተመሰከረላቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሎጥ፣ ሳሙኤል፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ዳንኤል፣ ሠለስቱ ደቂቅ ወዘተን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም የተነሳ የካልቪኒስቶች ስሁት ትምህርት በምድር ላይ የጽድቅ ስራን መሥራት በመቻልና በሥራ በመጽደቅ መካከል ያለውን ልዩነት አቅላቅለው እውነትን ደፍጥጠው ይክዳሉ።
2/ Unconditional Election /አስቀድሞ መመረጥ/ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚድኑትን አስቀድሞ መርጧቸዋል።
ሲመርጣቸውም ምንም ዓይነት መስፈርትና መለኪያ አላደረገም። በቃ! ጻድቅ እንዲሆኑ ተፈጠሩ የሚል ነው። ኃጢአት፣ ሥርየት፣ እምነት፣ የሚባል ነገር ለፎርማሊቲ እንጂ ከተመረጡበት አያስቀራቸውም፣ አይጨምርላቸውም። የትኛውም ኃጢአት ከምርጫው አያስቀራቸውም የሚል ሲሆን እግዚአብሔር ለሲዖል መርጦ ያስቀራቸው አሉ በማለት ፍፁም ፍቅር የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ከሰው ልብ አውጥቶ የሚጥል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ሲጀመር ሲዖል ለሰይጣንና ለመላእክቱ እንጂ ለሰው ልጅ አልተፈጠረም። ማቴ 25:41
3/ Limited Atonement የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የተከናወነው ለእኛ አስቀድሞ ለተመረጥነው ብቻ ነው የሚል አስተምህሮ ነው።
ለዚህም እንዲረዳቸው ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።”ዮሐ 10፥11 ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ለእኛ ለተመረጥነው በጎቹ ብቻ ነው የሚል ነው።
ሲጀመር ካልቪኒስቶች በ/Limited Atonement/ /ለበጎቹ ብቻ/ በሚለው አስተምህሮአቸው ውስጥ ሁለት ነገር ይስታሉ። አንደኛው በማይቀየር ማዳኑ ውስጥ አስቀድሞ በጎቹ ከተመረጡ ኢየሱስ ለምን መሰቀል አስፈለገው? ዝም ብሎ እነሱን እየለየ ወደገነት ማስገባት ተገቢ በሆነ ነበር። ሲቀጥል ካልቪኒስቶች የስህተት ትምህርታቸውን ተርጉመው የኢየሱስ በጎች እኛ ነን ያሉት ራሳቸው እንጂ ካልቪኒስቶች ብቻ የተመረጡ ናቸው የሚል ማረጋገጫ በመጽሐፍም፣ በመላእክትም የተመሰከረ አይደለም። ደግሞ የተነገረን እውነት የተለየ ወንጌል የሰበከ የተረገመ ይሁን የሚል ነው። ገላ 1:8
እኛ ግን እንዲህ ብለን እናምናለን።
“በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤” ገላ 3፥26 በኢየሱስ
አዳኝነት ያመነ፣ የተጠመቀና እምነቱን በሥራ የገለፀ አማኝ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኗል ብለን እንናገራለን እንጂ ኢየሱስ የዓለም መድኃኒት የተባለበትን ሞትና ትንሣኤውን የካልቪኒስቶች ብቻ መድኃኒት ብለን ስለሁሉ የሞተበትን ምስጢር አንክድም።
4/ Irresistible Grace/ የካልቪኒስቶች ሌላው ስሁት አስተምሮአቸው አስቀድሞ በፀጋው የተጠሩት መቼም እንዳይጠፉ ሆነው የሚል ነው።
ለዚህም ደጋፊ እንዲሆናቸው ዮሐንስ በወንጌሉ የጻፈውን የራሳቸው ብቸኛ ማረጋገጫቸው አድርገው ያቀርባሉ።
“አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም”
ዮሐ 6፥37
የሚገርመው ነገር በ30 ጠገራ ብር ኢየሱስን የሸጠው ይሁዳ ከተጠሩት ሐዋርያት መካከል አልነበረም ወይ? ሲባሉ ከሐዋርያነት የተደመረው ሽያጩን እስኪፈፅም እንጂ በዘላለማዊ ጥሪ ውስጥ አልነበረም ይላሉ። ለያህዌ ስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ካልቪኒስቶች እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ላይ ቁማር ይጫወታል፣ ያለምርጫህ ብትጠፋም ላንተ መጥፋት ግድ አይሰጠውም ወደሚል የአምላክን ባህርያዊ ፍቅር
ወደማስካድ ይወርዳሉ። እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ስለሆነ የሚጠፉትንና የሚድኑትን ያውቃል ማለት የሚጠፉትና የሚድኑት እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወሰነባቸው ሳይሆን ሰዎች በሚያደርጉት የራሳቸው ውሳኔ የተነሳ መሆኑን አይቀበሉም። አዳም ከገነት ከመባረሩ በፊት ፍጻሜውን እግዚአብሔር ያውቅ ነበር ማለት አትብላ ያለውን እፀ በለስ በግድ እንዲበላ ስለወሰነበት ነበር ብሎ ማቅረብ አደገኛ ክህደት ነው። ይህም የሰው ልጅ በራሱ ማሰብና መወሰን የማይችልና አስቀድሞ በተገጠመለት የውሳኔ ሶፍትዌር የሚንቀሳቀስ ቁስ ነው እንደማለት ነው። የተወሰነብህን ትኖራለህ እንጂ በእውቀትም፣ በእምነትም የምትጨምረውና የምትቀንሰው ነገር የለም ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚነግረን አንዴ በተሰጠ ምርጫ የለሽ ውሳኔ ሳይሆን የምናምነው አምላክ አውቀን በዚሁ በእምነታችን ፀንተን ስንቆይ እንደሆነ በግልፅ ይነግረናል።
“የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤”
ዕብ 3፥14
እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ከወጡ በኋላ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ሳይገቡ በምድረ በዳ የቀሩት
እግዚአብሔር በረሃ በልቷቸው እንዲቀሩ አስቀድሞ በወሰነባቸው ውሳኔ ሳይሆን ድንቅና ተአምራትን አድርጎ ከሰማይ መና፣ ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን ዓምድ እየመራቸው በነበረው አምላካቸው ላይ በማመፃቸው ነበር።
" ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን" ዕብ3: 15—19
5/ PERSEVERANCE OF THE SAINTS ይህ ማለት አንዴ ከዳንክ ለዘላለም ድነሃል። በየትኛውም ኃጢአት ወይም በዓመጻ የሚጎድልህ ማንነት አይኖርህም ማለት ነው።
Once saved, always saved ይሉሃል። በካልቪኒስቶቹ ዘንድ በዕብራውያን 10:36 ላይ የተመለከተው በእምነት ፀንቶ፣ ፈቃዱን እያደረጉ መኖር ነገር እርባና የለውም።
“የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።”
ዕብ 10፥36
አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም የማይጠፋ ስለሆነ በካልቪኒስቶች ዘንድ የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ምንም አያስቀርበትም።
“ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥” 2ኛ ጴጥ 3፥14
የእግዚአብሔር ፈቃድ ብታደርግም፣ባታደርግም አንዴ ድነሃልና አትጠፋም፣ አትጨነቅ። ዮሐንስ በመልእክቱ የፃፈው ካልቪኒስቶችን አይመለከትም።
ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው የሚለው ቃል ቢኖርም አንዴ ስለዳንክ ችግር የለውም ይሉሃል።
“ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።”1ኛ ዮሐ 3፥8
አንዴ ስለዳንክ በኃጢአት የተነሳ ከዲያብሎስ ብትሆንም አትጨነቅ፣ አትጠፋም እያሉ ለድፍረት ኃጢአት ያበረታቱሃል። ኃጢአት መስራት፣ አለመስራትህ የሚቀንስብህ ወይም የሚጨምርልህ ነገር የለም ይሉሃል።
“ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”1ኛ ዮሐ 2፥17 ፈቃዱን ብታደርግ ጥሩ ነው። ሳትፈፅመው ብትቀርም ችግር አያስከትልብህም፣ አትጨናነቅ፣ አንተ ለዘላለም የተመረጥህ ነህና። ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ለመኖር ፈቃዱን መፈፀም ተገቢ ነው ያለው የራሱ ግምት በመሆኑ ካልቪን ያሻሻለውንና አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም ዳነ የሚለውን ትምህርት ተከተል ይሉሃል ከሃዲዎቹ!
ማጠቃለያ፣
ካልቪኒስቶቹ የሳቱት እውነት፣ የምሥራቹ ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንጂ የጆን ካልቪን ትርጉም፣ አባባል፣ አገላለፅ ወይም የአስተምህሮ አቋም አለመሆኑን አለማወቃቸው ነው። ካልቪን በአንድ ወቅት የተለየ የወንጌል አስተምህሮ ተገልጾልኛል ብሎ የራሱን ትርጉም ይዞ የመጣ ሰው እንጂ የምሥራቹ ቃል ምንጭ ስላልሆነ ካልቪኒስት ነኝ ብሎ እሱን መከተል አደገኛ ስህተት ነው። ማንም አማኝ የወንጌልን ትምህርት በብዙ መንገድ፣ ከብዙ ሰዎች ሊሰማ ወይም ሊያገኝ ይችላል።
ያ ማለት ግን የወንጌል እውነት እሱ ከሰማበት ቦታ ብቻ ይገኛል ማለት አይደለም። የየትኛውም ትምህርት ማረጋገጫና መመዘኛ መንፈስ ቅዱስና የምሥራቹ ቃል እውነት መሆኑን አለማወቃቸው ነው። ሉተር፣ ካልቪን፣ ዝዊንግሊ፣ ኤራስመስ፣ ኖክ፣ ዊክሊፍ፣ ኸስ፣ ሜላንክቶን ወይም ቲንዳል የእውነት ቃል ምንጭ ወይም የመጨረሻው የእውነት ማረጋገጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ አለመረዳታቸው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ይልቅ ግለሰቦቹ በሰጡት ትንታኔ ላይ በመመስረት ለማመን መሞከራቸው ነው ካልቪኒስት ሆነው ለመኖር የወሰኑት። እኛ ግን የተሰቀለልንና ከሞት ያዳነን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይና ደቀመዛሙርት እንጂ የአጵሎስ ወይም የጳውሎስ አይደለንም። ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም ማነው? ከሰማይ በታች ሊድኑበት ለወደዱና ወደእርሱ ለመጡ በሙሉ የሚያድነው ስም ኢየሱስ ብቻ ነው። ከሰማይ በታች የተሰጠ የካልቪን አስተምህሮ፣ ለካልቪኒስቶች ሊኖር ይችላል። እኛን ክርስቶሳውያንን አይመለከትም። የካልቪን የሚባል አስተምህሮም፣ መምህርም የለንም።