Tuesday, January 2, 2018

ኢየሱስ አዳነን እንጂ ከአብ ጋር እንታረቅ ዘንድ አላማለደንም ማለት ኑፋቄ ነው!!


****************
አንድ ሰው በፌስቡክ ገጹ ላይ "ኢየሱስ አዳነን እንጂ አላማለደንም" የሚል የስሕተት ትምህርት ፅፎ ስላየኹ ይቺን አጭር ፅሑፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ። ማስረጃችንም ቅዱስ መጽሐፍ ነው።

መልሴን በጥያቄ ልጀምር። " አዳነን እንጂ አላማለደንም" ማለት ምን ማለት ነው? ይህ አባባል "ኢየሱስ ይፈርዳል እንጂ አያማልድም" የሚሉ ሰዎች ለሞገት የሚያቀርቡት ክርክር እንደሆነ እረዳለሁ። ይህ የስነ ሞገት ክርክር ጥያቄ ማስከተሉ የግድ ነው። እርግጥ ነው: ኢየሱስ ፈራጅ አምላክ ነው። ታዲያ ፈራጅ አምላክ ሆኖ ሳለ እኛን የአዳም ልጆች ከዘላለማዊ ቁጣ ለማዳን ለምን ሰው መሆን ይጠበቅበታል? በሰማያዊ አምላካዊ ሥልጣኑ " ድናችኋል" የሚል ቃል ቢሰጥ የሚቃወመው ማነው? መከራና ሞት ወደሚያስከትል ደካማ ሥጋ በመምጣት ሰው መሆን ምን ያደርግለታል?
  ያዳነን በፈራጅነቱ እንጂ በምልጃ አይደለም የሚሉ ሰዎች አምላክ ሰው መሆን ሳያስፈልገው በለይኩን ቃሉ ለምን እንዳላደን ወይም ከፈራጅነቱ ምን ጎድሎበት ሰው ወደመሆን እንደወረደ ሊገልፁልን ይገባል።
ከአብ ጋር ለማማለድ ካልሆነ በስተቀር የማዳን ሥልጣን አንሶት ነው ሰው የሆነው? ብለን እንጠይቃለን። ያለምልጃውም አልዳንም: መዳንም የለም እንላለን።



ድነናል ግን በኢየሱስ አማላጅነት አይደለም ማለት ኑፋቄ ነው።
ኑፋቄ ደግሞ በከፊል አምኖ በከፊል መካድ ነው። ለዚህ ኑፋቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ በማቅረብ እንመርምር።
ማስታረቅ ማለት ምን ማለት ነው? በእንግሊዝኛው (Reconcliation) የሚለው ቃል ነው። (To interpose; as, to intervene to settle a quarrel; get involved, so as to alter or hinder an action)
በሰውኛ ልማድ አስታራቂ ሰው በሁለት የጥል ልዩነት ባላቸው ሰዎች መካከል ገብቶ "አንተም ተው: አንተም ተው" በማለት የሚያስማማ ሰው ማለት ነው። አስታራቂው በእድሜ: በተሞክሮና በእውቀት ተቀባይነት ያለው መሆኑ በቂ ነው:: የግድ ገለልተኛ መሆን አይጠበቅበትም።  ቅራኔ ባላቸው ሁለት ወገኖች መካከል ገብቶ ስምምነት ለመፍጠር የፀቡ ሁኔታ ያንን ያህል ጥልቅ አለመሆኑ ወይም አንደኛውን ወገን በጣም ተጎጂ ያላደረገ መሆን ለሚችል የፀብ ዓይነት የእርቅ አገልግሎት ይከናወናል። ማስታረቅ ላይ በዳይ ሆኖ የሚክስና ተበዳይ ሆኖ የሚካስ ላይኖርም ይችላል። በማቻቻልና በማግባባት ላይ ተመስርቶ የሚፈፀም ነው። የግጭቱን መንስኤና ውጤት ተመልክቶ አይወስንም።  ይልቁንም ይቅር ተባብለው: ቂም ከመያዝ ወጥተው ሰላማዊ ግንኙነት በማስቀጠል ላይ እንዲያተኩሩ ያግባባል።
****************
ማማለድ ወይም አማላጅነት ማለት ምንድነው?  በእንግሊዝኛው /to intercede ወይም  /intercession/ የሚለውን ቃል ይወክላል። (To plead on someone else's behalf.
To act as a mediator in a dispute; to arbitrate or mediate.) አማላጅ ወይም የማማለድ ተግባር ፈፃሚ መሠረታዊ የፀቡን መንስኤ መርምሮ በዳይ እንዲክስ: ተበዳይ እንዲካስ በማድረግ ወደእርቅ የሚያደርስ መካከለኛ ነው። የምልጃ ውጤት እርቅን ማምጣት ነው።  intercession ወደ reconciliation ያደርሳል። reconciliation ብቻውን ሲሆን ግን በራሱ ግብ ነው።
 የማማለድ ወይም የአማላጅነት አገልግሎት ለመፈፀም እነዚህ ሦስት ነጥቦች የግድ መሟላት አለባቸው።
ሀ/ አማላጁ በዳይን ወክሎ የሚቀርብ ነው።  ነገር ግን ከፀቡ የመንስኤ ጉዳዮች ነፃ መሆን አለበት።
ለ/ የጸቡ ነገረ መሠረት በሚያስከትለው ብያኔ ተበዳይ ተመጣጣኝ ካሳ የሚያገኝበት ይሆናል።
ሐ/ የምልጃው ፍጻሜ ጸቡን አንዴና ለመጨረሻ የሚሽር መሆን ይጠበቅበታል።
እነዚህን የትርጉም ሃሳቦች መነሻ አድርገን ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የምልጃና የእርቅ አገልግሎት እናመራለን።
***********
1/ አስታራቂነት በብሉይ ኪዳን:
*****************
የኦሪቱ ካህን የመካከለኛነት (አስታራቂነት) አገልግሎት ነበረው!
*************
1/ በኦሪቱ ዘመን ሰው ኃጢአት ሲፈፅም ኃጢአቱ ከሚያስከትለው የእግዚአብሔር ቁጣ ምህረትን ለመቀበል መስዋእት ሊያቀርብ የግድ ነበር። በዚያ ሥርዓት ውስጥ አትስራ የተባለውን የሰራውና በዳይ የሆነው ሰው ሲሆን ተበዳይ ደግሞ ሕግ ሰጥቶ ሳለ ሕጉ ያልተከበረለት እግዚአብሔር ነው። ሕጉ ባለመከበሩ ከተቀመጠው ቅጣት ለመዳን ኃጢአተኛው የሱን ሞት በምትክ ሞቶ የሚያድነው መስዋእት ያቀርባል። ሕጉ ያልተከበረለትና የተበደለው እግዚአብሔር በኃጢአተኛው ፋንታ በሚሰዋው የመስዋእት ሽታ ደስቶ ኃጥኡን ይቅር ይለዋል።
ይህንን በኃጥኡ በዳይ ሰውና በጻድቁ በእግዚአብሔር መካከል የተፈጠረውን ፀብ ለመሻር ሥርዓቱ የሚጠይቀውን መስዋዕት በማቅረብ የተወደደ መዓዛ ይሆን ዘንድ በመካከል ሆነው የሚያስታራርቁት ካህናቱ ነበሩ።

"የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ነው። "
( ዘሌ 3: 5)



እግዚአብሔር ያዘዘውን የኃጢአት መስዋእት ተቀብሎ ለማስተስረይ አቅራቢው የተሾመው ካህን ነበር። እግዚአብሔርም ስርየቱን በካህኑ በኩል ይቀበላል።
"፤ እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። "
( ዘሌ 4: 33)
 ካህኑ የስርየት አገልግሎቱን ሳይፈፅምለት ሀጢአተኛው ይቅር ሊባል አይችልም። የዚህ አገልግሎት ችግሩ መስዋእቱ ዕለት ዕለት የሚደረግ አድካሚ በመሆኑና ካህኑ ለራሱም የኃጢአት መስዋእት እንዲያቀርብ የሚገድድ ከመሆኑም ባሻገር መስዋእቱም: አገልጋዩም በሞት የሚሸነፉ ስለነበር ኃጢአተኛውን ፍፁም አድርገው የማዳን ኃይል አልነበራቸውም።
*********
(ዕብ 5 :2—3)
እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል"

*********************
2/ በሐዲስ ኪዳን የሆነው ምልጃና እርቅ÷

በወንጌል ላይ የተፈጸመው በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በደለኛውን የማዳን አገልግሎት የምልጃና የእርቅ አገልግሎት ነው። የተደረገው ምልጃ እርቅን አስከትሏል። ያለምልጃ የተፈጸመ እርቅ የለም። አንተም ተው: አንቺም ተይ  የሚል ዓይነት የማስማማትና የማቻቻል እርቅ ሳይሆን አማላጁ በበዳይ ወገን ተወክሎ: በዳይ ካሳ ከፍሎ: የነበረውን ጥሎ አፍርሶ በደም መሐላ የተፈጸመ እርቅ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
 ፍፁም ያልሆነው የሕግ መስዋእት የምልጃ አገልግሎት የሚያገለግለው ለተሰጠው የሕግ መተላለፍ ብቻ ነበር። አዳም በገነት ሳለ ለፈፀመው የመተላለፍ በደል ዋጋ የለውም። አዳምንም ሆነ ዘሮቹን ሁሉ በሞት ጠፍንጎ ለያዘው የመተላለፍ በደልም ሆነ በሕግ ከሚመጣ ኃጢአት ሁሉ ነጻ የሚያወጣ መስዋእት መኖር ነበረበት። መስዋእቱ ዕለት ዕለት በሚፈፀም ሥርዓት አድካሚ ያልሆነና መስዋዕት አቅራቢ መካከለኛው ደግሞ በሞት የማይሸነፍ÷ ለራሱ መስዋዕት ማቅረብ የማይጠበቅበት ንጹሕ መሆንም የግድ ነበረበት።  
በሰው መተላለፍ ከመጣው የእግዚአብሔር ቁጣ የሚታደግ: ከሰማይ የሆነ: ኃጢአት የሌለበት: ሞት የማያሸንፈው: ሕያዉና ዘላለማዊ መስዋእት ያለዘርዓ ብዕሲ  በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከድንግል ተፀንሶ ሰው የሆነው የእግዚአብሔር መስዋእት ኢየሱስ ተገልጿል። 
*******************
ስለ ኢየሱስ ስንናገር በምልጃ ላይ ያቀረብናቸው ሦስት ግዴታዎች ማሟላታቸውን መረጋገጥ የግድ ነው። እነሱም÷
ሀ/ አማላጁ በዳይን ወክሎ መቅረብ አለበት የሚለው ተሟልቷል?

  ✔✔✔
 ኃጢአተኛ የሆነው የሰው ልጅ ሊያቀርብ የማይችለውና  እግዚአብሔር  በኛ ምትክ ያቀረበው የመስዋዕት በግ ኢየሱስ ነው። 
" እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ " 
(ዮሐ1:25) 
በጉ ለእርቅ የሚቀርብ መስዋእት ከሆነ መስዋዕቱ የሚቀርብለት በዳይ: መስዋ ዕት አቅራቢና: መስዋዕት ተቀባይም ሊኖር የግድ ነው።
✔✔ ✔

ለ/  "የፀቡ ነገረ መሠረት በሚያስከትለው ብያኔ ተበዳይ ተመጣጣኝ ካሳ የሚያገኝበት ይሆናል" የሚለውን የአማላጅነት ሚና ኢየሱስ አሟልቷል ወይ? ብንል መልሳችን "አዎ" ነው።
,✔✔✔ ኢየሱስ በዳይ በሆነው በአዳምና በልጆቹ እንዲሁም የዐመጽ በደል በተፈፀመበት በእግዚአብሔር መካከል አማላጅ ሆኖ የቀረበ ሊቀ ካህናችን ነው።

 የኦሪቱ ሊቀ ካህን የመስዋዕት በግ ያርዳል እንጂ ለኃጢአተኛው ራሱ አይሞትም ነበር።  የሐዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህን ግን ለኃጢአተኛው የሞተው ራሱ በግ ሆኖ ነው። የኦሪቱ ሊቀ ካህን የሚሾመው በዘር እንጂ እንደኢየሱስ "ለዘላለም ካህን ነህ" ተብሎ በመሐላ እንደተሾመው አይደለም። ኢየሱስ በማይሻር ሊቀ ካህንነቱ ዛሬም በእምነት የሚመጡትን አንዴ በፈፀመው ምልጃው ይቅር ይላል። ዘላለማዊ ሊቀ
 ካህን ወይም ክርስቶስ (ቅቡዕ) የተባለውም ለዚህ ነው። እንደኦሪቱ ካህን ሹመቱ በዚያው አብቅቶ ቢሆን ኖሮ ካለማመን ወደማመን የሚመጡትን ማን ያስታርቅ ነበር። ሐዋርያውም በማያሻማ ቃል ይህንን አረጋግጦልናል።

" እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። " 
(ዕብ 7: 24—25)

በኦሪቱ ኪዳን ለኃጢአተኛው በሚቀርበው የበጉ የመስዋዕት ጢስ ሽታ እግዚአብሔር ይቅር ይል እንደነበረው ኢየሱስ በአብ የተወደደ መልካም መዓዛችን ሆኖ ተቀባይነት አገኘን። 
"ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ " 
(ኤፌ 5: 2)

ኢየሱስ በደል በፈፀመው የሰው ልጅ ምትክ ተመጣጣኝ ካሳ በመሆን ለእግዚአብሔር የቀረበ መልካም መዓዛችን ሆኗል። የኃጢአተኛው የመስዋእት በግ ራሱ ነው። የበጉን መስዋእትነት በማይሻር ክህነት ያቀረበው ራሱ ነው።  ለኃጢአተኛው የሞተ ካህንም ራሱ ነው። ኢየሱስን ሁሉንም በራሱ ጠቅልሎ ምልጃውን ፈፀመ። አብም ምልጃውን ተቀብሎ በቀረበው አስተማማኝ ካሳ ይቅር አለን።። አስታራቂ ካሳ ከኢየሱስ በቀር የለም። እኛማ ለሥርየት የምናቀርበው ምንም የሌለን ባዶዎች ነበርን።

" ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። " 
(1ኛ ዮሐ 4: 10)
****************** 
ሐ/ የአማላጅነት አገልግሎት ሦስተኛው መስፈርት "የምልጃው ፍጻሜ ፀቡን ለአንዴና ለመጨረሻ የሚሽር መሆን ይጠበቅበታል" የሚለው ነው።  

የኢየሱስ ምልጃ ይህንን አሟልቷል ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሳችን አዎ ነው። ተደጋግሞ እንደተገለፀው በዳይ በሆንነው የሰው ልጆችና ተበዳይ በሆነው በእግዚአብሔር መካከል የነበረነውን ጥል ለማፍረስ በቀረበው የካሳ ክፍያ በኩል እርቅና ሰላም በምድር ላይ ከወረደ በኋላ ጸብ የለም።  ለጸቡ መሰረዝ ዋና ምልክቱ መስዋዕቱ መልካም መዓዛ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ በመሆኑ ነው። 
በዚህም የተወደደ መስዋዕት የተነሳ እግዚአብሔር ወስኖት የነበረውን ሞት በዘላለም ሕይወት ቀይሮልናል።
★****★*****★
"፤ እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው " 
(1ኛ ዮሐ 5: 11) 
አማኑኤል በተባለበት ስሙ ሥጋችንን ለበሰ። በመካከላችንም አደረ። ኢየሱስ: በተባለበት ስሙ በሞቱ መድኃኒት ሆነን። ክርስቶስ በተባለበት ስሙ ዘላለማዊ ካህን ሆኖ አማለደን።  ያለሞቱ አስታራቂነትና ምልጃ እኛ ልንድን አንችልም ነበርና  ስላዳነን ዘመዳችን: መድኃኒታችን: አማላጃችን እንለዋለን። በመለኮቱማ መውጣት: መውረድ: መሰቀል: መሞት የሌለበት ዘላለማዊ አምላክ ነው። 

***************;
ኢየሱስ ዘላለማዊ አምላክ በመሆኑ ካህን መሆኑ ለርሱ የሚጨምርለት አንዳች ነገር የለም። ነገር ግን ለኀጢአተኞች በእግዚአብሔር ዘንድ የዘላለማዊ እርቅና የምልጃ ሥርየት ለመሆን የሰው ፍቅር ግድ አለው።  ከኃጢአት በስተቀር በሥጋው እንደእኛ የተፈተነ የሚራራልን ሊቀካህናችን እሱ ነው። በኔ በኩል ካልሆነ ወደአብ መምጣት አትችሉም ያለውም በሰማይ ላይ መመላለሻ ጎዳና ተዘርግቷል ማለት ሳይሆን እሱ የፈፀመልንን የምልጃና የእርቅ ሥርየት አምነን በመቀበል መዳን መቻላችንን ለማስረዳት መሆኑን ማወቅ አለብን።
የኦሪቱ ሊቀካህን አማላጅና አስታራቂ መሆኑ በአዲስ ኪዳን በመሀላ የተሾመ: ኃጢአት የማያውቀው: የማይደጋገም: ሕያው የሆነ አንዴ በፈፀመው የደሙ ምልጃ ወደእሱ የሚመጡትን ሁሉ እንደምን አያድን?
 ጳውሎስም: ድካማችንን የሚያውቅ: በመከራችን የተፈተነ: የሚራራልን ሊቀ ካህን እንዳለን ገልጿል።
"፤ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። " (ዕብ 4: 15)

"፤እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። " 
(ቆላስ1: 21-22)
ያለእርቅ አገልግሎት እርቅ አልወረደም።

✔✔✔✔✔✔✔✔✔✔

ማጠቃለያ÷
እውነት ነው: ኢየሱስ አምላክ ነው። ታዲያ አምላክ ሆኖ ሳለ "ይፈርዳል" እንጂ አምላክ እንዴት "አማላጅ" ይሆናል? ወደማንስ ይማልዳል? የሚሉ ሰዎች የሳቱት  ነገር እንዳለ ግልጽ ነው።  ኢየሱስ ምልጃ መፈፀሙን ከመቃወማቸው በፊት አምላክነቱ እንዳያንስባቸው ከፈለጉ ቅድሚያ መቃወም የነበረባቸው ጉዳዮች አሉ።

ምልጃው ኢየሱስን የሚያሳንስባቸውና ከአምላክነቱ ዝቅ እንደሚያደርግባቸው ካሰቡ ትልቁ ጥያቄ መሆን የነበረበት አምላክ ሆኖ ሳለ እንዴት ሰው ይሆናል? የሚለው ነው።  አምላክስ እንዴት ይሞታል? አምላከ እንዴት በእጁ ፍጥረት ተገርፎ ይፈረድበታል? የሚሞት አምላክ እንዴት ሊኖር ይችላል? አምላክ ሞቷል ካልን አምላክ መሆን አይችልም። ምክንያቱም የሚሞት አምላክ ሌላውን አያድንም። ትልቁ ምስጢር ይኼ ነው። ኢየሱስ የክህነት ምልጃ አልፈጸመም ወይም አይፈጽም የሚሉ ሰዎች ሰው መሆን ሳይጠበቅበት በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን አይችልም ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል። በዓለም ላይ የኢየሱስ ሰው የመሆን ምስጢር ተሰውሮ ግማሹ ፍጡር ነው: ግማሹ የአምላክ ነፀብራቅ ነው: ገሚሱም የአላህ ነብይ ነው የሚያስብላቸው የእግዚአብሔር አብ ዓላማና እቅድ በኢየሱስ በኩል ምን እንደሆነ ተሰውሮባቸው ነው።ይኼንን ምስጢር ካወቅን ሥጋ የለበሰበት ምሥጢር ይገባናል። ካላወቅን ደግሞ ከአብ ጋር  ያስታረቀበት የምልጃ ምሥጢር መቼም አይገባውም። ያኔ ደግሞ ሰው የሆነበትንና በአዳም ልጆችና በእግዚብሔር መካከል የነበረውን ጥል በማሰቀረት በደሙ በኩል ያሰታረቀውንና የፈፀመውን የምልጃ አገልግሎት መረዳት እንችላለን። በአጭሩ ኢየሱስ አምላክ ሆኖ ሳለ ሰው የሆነው ከአባቱ ጋር በሞቱ በኩል ሊያማልደን ነው። አማለደ ማለት አሸማገለ: አስታረቀ ማለት ከሆነ ኢየሱስ ይኽንን አገልግሎት ፈፅሟል። የሚራብ: የሚደክም: የሚሞት ሰው የሆነበት ምክንያት ይኼው ነው። ሰው የሆነው አምላክነቱን ሸሽጎ ከሥልጣን ራሱን ባዶ አድርጎ ባሪያ ሆኖ ነው። ባሪያ ደግሞ ታዛዥ ነው። በዚህም አብ ውረድ: ተወለድ: ሙትና ሕዝብህን አድን ያለውን ቃል ተቀበሎ ፈጽሟል። ወልድ( ልጅ) የተባለውም ለዚህ ነው። በቀጥታ አምላካዊ ሥልጣን ከሆነማ አምላክ ልጅ አይወልድም: ትንሽ ሆኖም ልጅ አይሆንም። ወንጌል ይህንን በደንብ ገልጾታል። 

(ፊልጵ 2:6—8፤ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ"
አዎ ኢየሱስ የሚፈርድ: የሚኮንን አምላክ ነው። አምላክ ሆኖ ሳለ ሰው በመሆን ራሱን ባዶ አደረገ። ፈራጁ ለአባቱ ታዘዘ። ተለማኙ ጸለየ: ለመነ። ተማላጁ ምልጃ አደረገ። የሚሾም: የሚሽር ሆኖ ሳለ በለበሰው ደካማ ሥጋ ተራበ: ተጠማ: ታሰረ: ተገረፈ: ተሰቀለ።  የማይሞተው ሞተ።
"፤ እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ " (ዕብ 5: 7)

 የሁሉ ጌታ ባዶ የሆነው እኛን ከመውደዱ ፍቅር የተነሳ ነው። ያንን ሰማያዊ ክብር ትቶ ከአባቱ ጋር ባያስታርቀን ኖሮ ከቁጣው መቅሰፍት መቼም አንድንም ነበር።
የኢየሱስን አምላክነት ለመጠበቅ "አማለደ" ካልኩ ክብሩ ያንስኛል የሚል ማንም ቢኖር ኢየሱሰ  ባዶ የሆነበትን ምስጢር የሚክድ በመሆኑ ማንም ሰው ድኛለሁ ወይም ከፍርድ አመልጣለሁ ብሎ እንዳያስብ። በአምላክነቱማ ኢየሱስ ሰው መሆን ሳያስፈልገው ማዳን ሥልጣኑ ነው።
  ሊቃውንቱ እግዚአብሔር "አምላክ ሆኖ ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ሆኖ ያዳነበት ጥበብ እንዴት ይረቅ" ያሉትም ለዚህ ነው። 
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው  “እንዘ ባዕል ዉእቱ አንደየ ርእሶ"…ባለጸጋ ሲሆን ራሱን ድሃ አደረገ ማለቱ ወልድ በሰዉነቱ ሹመትን: ትንቢትን: መንግሥትን: ክህነትን ስለተቀበለ ራሱን ድሃ አደረገ ያለዉ አይደለምን? ለመለኮት በባሕርይ ክብሩ አንጻር የክህነት: የመንግሥት: የትንቢትና ሹመት ምኑ ነው? ነዳይ ለተባለ ወልድ የተሰጠው አይደለምን? ዳግመኛም ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት በድንግል ማኅፀን በሰዉነቱ የባሕርይ ልጅ ሲሆን የሰዉን ሕግ ፈጸመ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ ፣ በአህያ ላይ ተቀመጠ ፣ የመስቀሉን ግንድ ለመሸከም እንደባሪያ ሆነ በማለት ቅዱስ ጳዉሎስ የተናገረ አይደለምን?
 ያለው ለኛ ያለውን ፍቅር የገለፀበት መንገድ ስለሆነ ነው። ( ራሱን ዝቅ አደረገ: ነፍሱንም ሰጠን) አምላክ ዝቅ አይልም: እንደሰው ነፍስም አልነበረውም። በሥጋው ይህ ሁሉ ፍቅሩ በዛልን። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለን እንዳለው ጳውሎስ ነዳይ የተባለው ኢየሱስ እሱን ለማወቅ የሚያስችል አስተዋይ ልቦና ይስጠን። እሱ ካልገለፀለት በቀር ከእግዚአብሔር የሆነለትን እውነት ማንም ሊረዳ አይችልምና። አሜን!