ኢየሱስን ብቻ መተማመንና የሌላ የማንንም ተስፋ አለመጠበቅ ለምን የግድ ሆነብን? ወደኢየሱስ ለመቅረብና ከኢየሱስ ለመታረቅ ሌላ መንገድ እንደሌለ ማወቅ የሚገባን ምርጫ የለሽ መሆኑን መረዳት የሚገባንስ ለምን ይሆን?
በኢየሱስ ብቻ መታመንና ወደእሱም ለመቅረብ ሌላ አድራሽ መንገድ ወይም አቋራጭ ጎዳና ላለመኖሩ አሳማኙ ምክንያት እኛ ሳንፈልገው ፈልጎን የመጣ መተኪያ የሌለው መድኃኒት እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው።
ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፈ ትንቢቱ ላይ እንደከተበው: በኋለኛው ዘመን ይህንን የእግዚአብሔርን ቃል መገለጥ እንዲህ ጽፎልናል።
"ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁት። " (ኢሳ 65: 1)
ይህ የኢየሱስ መገለጥ ለእኛ ያተረፈልን ነገር በስሙ ላልተጠራነው ለእኛ የእግዚአብሔር ልጆች መባልን አስገኝቶልናል። በሞት ጥላ ሥር ወድቀን ለነበርን የሕይወት መትረፍረፍ በዝቶልናል። በጨለማ ግዞት ተውጠን ለነበርን ዘላለማዊ ነጻነትን የሚያጎናፅፍ የምሥራቹ አዋጅ ተሰብኮልናል። ስለሆነም ወደአብ ለመቅረብ ሌላ መንገድና በር በላይ በሰማይ ይሁን በታች በምድር ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ የለም።
የኢየሱስ ክርስቶስ እኔነት ለእኛ የሕይወት እኔነት ብቁ ዋስትና የሆነው ኢየሱስ መተኪያ የሌለው ሕይወትን የመስጠት እኔነት ስላለው ነው። ይህንንም በቁና አስተማማኝ እኔነት በመዋዕለ ሥጋዌው ኢየሱስ ራሱ ብዙ ጊዜ ነግሮናል። እስኪ ጥቂቱን እንመልከት።
"እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል"(ማቴ 10: 40)
"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ"(ማቴ 11:28)
"እርሱም÷ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው" (ማቴ16: 15)
" ኢየሱስ ግን አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ"
(ሉቃ 8:46)