Monday, October 5, 2015

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!


በአማን ነጸረ ፣ መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም

የታላላቅ ኦሮሞ ወንድሞቼን ቅሬታ የተጫናቸው ጽሑፎች አንብቤ ቅር አለኝ፡፡መነሻ የሆናቸውን ታሪካዊ በደል ለመረዳት አልሰነፍኩም፡፡ያም ሆኖ መስመር ያለፈና ባንድ ቦይ ብቻ የፈሰሰ በመሰለኝ ቅሬታቸው ቅር አለኝ፡፡ቅሬታዬ ቆየ፡፡ፈራሁ፡፡ከዚህ በላይ በሆዴ ከቆየ ቂም ይሆንና ይጎዳኛል ብዬ ፈራሁ፡፡ስፈራ ቅሬታዬን በረጅሙ (በፌስቡክ ስሌት ነው ርዝማኔው መጉላቱ) ጻፍኩት፡፡ሆኖም ስጽፈው ከ3 ችግሮች እንደማልነጻ አምኜ ነው፡፡አንድም በሁለንተናዬ ስላደኩበትና አሁን ድረስ በዕለት ኑሮዬ ስለሚደጉመኝ እንዲሁም የማኅበራዊ መደብ ጀርባዬ ስለሚመዘዝበት ተቋም ስናገር ንግግሬ ከሚዛናዊነት ይልቅ ወደ ተከላካይነት (advocacy?) እንደሚያጋድል ይታወቀኛል፡፡ሲቀጥል አማተር ነኝና የአጻጻፍና የማስረጃ ስደራ ችግር አያጣኝም፡፡እንዲያም ሲል ከሃይማኖት-ፖለቲካ ተዛምዶ አንጻር ያለኝ አረዳድና ንባብ ድኩም መሆኑን አልስተውም፡፡በተረፈ ‹‹አንዳንድ›› ብዬ የምጠራቸውን የኦሮሞ ጸሐፍት በስም ጠቅሻለሁ፡፡ጉዳዬ ስለክታባቸው ያውም ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን (ከአሁን በኋላ የኢኦተቤክ) በማስመልከት ስለጻፉበት ነጥብ ብቻ ነው፡፡ከዚህ ውጭ እነሱም ሆነ ሌሎች ጸሐፍያን ስለሚያነሱዋቸው ተያያዥ ጉዳዮች መጻፍ የዚች ትሑት (ታናሽ) ጽሑፍ ዐላማ ስላልሆነ ተዛማጅ ጉዳዮችን አለመንሳቴን በአትሕቶ-ርእስ እገልጻለሁ፡፡
በዚች ጽሑፍ የማተኩርባቸው ቅሬታዎች፡- (1)የኢኦተቤክ ደባትር ‹‹ጋላ›› የሚለውን ቃል ሆን ብለው ኦሮሞን ለማሳነስ ፈልስፈዋል፣(2)የኢኦተቤክ ሥርዓት እኩልነትን አይቀበልም፣(3)አቶ አጽሜ እና አለቃ ታዬ የኢኦተቤክ ደባትር ናቸው፣(4) የኢኦተቤክ ለአፋን ኦሮሞ ጽዩፍ ናት፣(5)በኢኦተቤክ እልህ የተነሳ ወለጋ ፕሮቴስታንት ሆነ፤ጅማ፣ወሎ፣አርሲ እና ሐረር ሰለሙ፣(6)የኢኦተቤክ አስተምህሮ ከኦሮሞ ባሕል ጋር ተጻራሪ ነው፣(7)የኢኦተቤክ ካሕናት በሲሶ ገዥነት በኦሮሞ ምድር የመሬት ከበርቴች ነበሩ የሚሉ ናቸው፡፡አሁን ቀጥታ ወደታመቀው ክስና ሐተታዬ….

1-- ክስ አንድ፡- ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል የኢኦተቤክ ደባትር ፈጠራ ነው!!

‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል ‹‹የአቢሲኒያ ቤተክሕነት ፈጠራ ነው›› ይላሉ እነ አባስ ሐጂ(ዶ/ር)፡፡‹‹ጋላ›› = መጻተኛ (stranger/outsider) የሚለው አገላለጽ የአቢሲኒያ ቤተክሕነት ፖለቲካዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ አመክንዮ ያለው ፈጠራ ነው-- “fabricated by an Abyssinian clergy for politico-ideological reasons” ይሉናል (Mekuria cited in Being and Becoming Oromo: Re-examining the Galla/Oromo Relationship,p.105)፡፡ይቺን አገላለጽ በክብር እቃወማታለሁ፡፡ምክንያቱም በበኩሌ ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል በዚያ መልኩ በኢኦተቤክ የሃይማኖታዊ ሥርዓት መከወኛ መጻሕፍት ተጽፎ እና ተተርጉሞ አላገኘሁትም፡፡አውቃለሁ፡፡ብዙ የኦሮሞ ጉዳይ ጸሐፍት በ1960ዎቹ በ‹‹ራዕየ-ማርያም›› የወጣውን ስርዋጽ (ሆን ተብሎ በእኩያን የተጨመረ--ስረ-ወጥ--ከስር ያልነበረ) ጽሑፍ ይጠቅሳሉ፡፡እንደማመጥ፡-
(1.1) እሱ ስርዋጽ በኢኦተቤክ ደረጃ በሊቃውንትና በቅ/ሲኖዶስ ተመክሮበት ወይም በማናቸውም ከኢኦተቤክ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ባለው አካል ፈቃድ/ትእዛዝ/ የወጣ አይደለም፡፡
(1.2) ስርዋጹ የኦሮሞን ብቻ ሳይሆን የሙስሊም፣የፈላሻ (ቤተ-እስራኤል) እና የሻንቅላ (ቤንሻንጉል-ጉሙዝ) ሕዝቦች ክብርንም እየጠቃቀሰ ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ያጎድፋል፡፡ታዲያ ያስተዋለ ሰው በግእዝ ቋንቋ ‹‹ሸ›› የሚባል ፊደል የማይታወቅ ሆኖ ሳለ በስርዋጹ ‹‹ፈላሻ እና ሻንቅላ›› የሚሉ ‹‹ሸ›› የበዛባቸው ቃላት በመታየታቸው ብቻ ተራ የእኩያን ጭማሪ (ስርዋጽ) መሆኑን መረዳት ይችላል፡፡እንዲህ ዐይነት ስርዋጽ ጽሑፎች ከዚህ በፊትም ከአንዳንድ ገድላትና ዜናመዋዕሎች ጋር ጎጃምን እንደ አገርና ሕዝብ በተለየ መልኩ ለማነወር በኵሸት ሕዝቡን ‹‹በላዕተ-ሰብእ (ቡዶች)››፤ሀገሩን‹‹ሀገረ-በላእተ-ሰብእ (የቡዶች ሀገር)›› የሚል ተቀጽላ ለመስጠት ተሞክሮ ሊቃውንቱ ታግለው ስርዋጹን ከኅትመት ከልተውታል፡፡ግብጻውያን በፍትሐ-ነገሥቱ ላይ የጨመሩት ‹‹የኢትዮጵያ አዋቂዎች ከራሳቸው ሊቅ ጳጳስ አይሹሙ›› የሚለውና በስንክሳር እስከዛሬ ለታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ‹‹ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሰው ጳጳስ ለመሾም ስላሰቡ መቅሰፍት ወረደባቸው›› የሚል ስርዋጽ በገቢር ከ1920ዎቹ ጀምሮ ቢሻርም ስርዋጹ ዛሬም አልተፋቀም፡፡እንዲህ ሲያጋጥም ለፍረጃ ከመሽቀዳደም ስርዋጹን ለማስተካከል ከመጣር በተጓዳኝ ገቢራዊነቱንም መፈተሽ፡፡
(1.3) ገቢሩ ሲፈተሸ ብዙኃን ኦሮሞ-ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ይህ ‹‹ጋላ ጋር የተኛ…›› የሚል ስርዋጽ ከመውጣቱ በፊት፣በወጣበት ጊዜ እና ከወጣም በኋላ በኢኦተቤክ ከተራ ካሕን እስከ መዓርገ-ጵጵስና ሲያገለግሉ ነበር፡፡አሁንም ያገለግላሉ፡፡ይሕም ስርዋጹ በምንም ተአምር ከኢኦተቤክ እንደማዕከላዊ ተቋም ታዝዞና ኃላፊነት ተወስዶ እንዳልገባ ገቢራዊ ማሳያ ነው፡፡ለነገሩ በ1960ዎቹ ብልጭ ብሎ የጠፋው ባለስርዋጽ መጽሐፍ አሳታሚና ማ/ቤቱም የኢኦተቤክ ንብረት አልነበሩም፡፡
(1.4) በምዕመን ደረጃ የኢኦተቤክ ብሔር ለይታ ‹‹እከሌን አግቡ፣እከሌን አታግቡ›› አትልም፡፡የመጣው ሁሉ ክርስትና ይነሳል፡፡ክርስትና ተነስቶ አቅመ-አዳም/ሔዋን የደረሰው ሁሉ ጋብቻው በሥርዓተ-ተክሊል ይፈጸምለታል፡፡ይሕ ድርጊት ብሔር አይለይም፡፡በዚህ መንገድ ቁጥራቸው አያሌ የሆነ ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን በቅድስት ቤ/ክ እርስ በርሳቸውና ከፈቀዷቸው ብሔረሰቦች ተወላጆች ጋር በሥጋ ወደሙ ተወስነው ጋብቻ ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡እየፈጸሙ ነው፡፡ስለሆነም ከ‹‹ጋላ ጋር የተኛ›› እያለ የኵነኔ ፍርድ የሚሰጠው ስርዋጽ የኢኦተቤክ ያላትን አሰራር በቃልም በተግባርም አይገልጽም፡፡ምክንያቱም ጽሑፉ--ስርዋጹ የእርሷ ስላልሆነ!!
(1.5) እስከማውቀው በኢኦተቤክ የኦሮሞ ሕዝብ እና ታሪክ ከሌሎች ተለይቶ በአሉታ አይታይም፡፡ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡በቅርብ ዓመታት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳውያንን በጫና የማስለምና የማጰንጠጥ ሙከራዎች ብቅ ማለት ቢጀምሩም በረጅሙ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ሕዝቡ እንደ ሕዝብም ሆነ የአስተዳደር ሥርዓቱ (ገዳ) በሌላው ሕዝብ ላይ የሃይማኖት ማንነትን በኃይል የመጫን ባሕል አልነበረውም፡፡የ16ኛው ክ/ዘ የኦሮሞ ጦርነቶችም ሃይማኖታዊ ገጽታቸው ጎልቶ ሲነገር አልሰማንም፡፡ሃይማኖት ጫና ካልተደረገበት ደግሞ ሃይማኖታዊ ሰማዕትነት የለም፡፡ስለዚህ የዮዲት፣የሱስንዮስ፣የግራኝ መሐመድ፣የደርቡሽ፣የጣሊያን፣የደርግ እና የ20ኛው ክ/ዘመን የአክራሪ እስልምና ጥቃቶች በኢኦተቤክ መዛግብት በ‹‹ዘመነ-ሰማዕታትነት›› ሲመዘገቡ የኦሮሞ ታሪክ እንደ ብሔር በዚያ መልኩ አልተካተተም፤ድሮም አሁንም፡፡ስለሆነም ያን ያህል ብሔሩን ለማሳደድና የተለየ ስም ለመስጠት የሚያበቃ ቅራኔ በኢኦተቤክ በኩል አልነበረም፤የለም፡፡
(1.6) ወደ ቤተ-መንግሥቱ ደባትር እንሂድ፡፡እውነት ነው፡፡የቀድሞ ነገሥታት ዜና-መዋዕል ጸሐፊዎች በኢኦተቤክ የተማሩ ሊቃውንት ናቸው፡፡ቅብዐ-መንግሥት ቀብተው የሚያነግሡ አንጋሾችም የኢኦተቤክ ጳጳሳት (በዜግነት ግብጻውያን ጳጳሳት) ነበሩ፡፡ነገሥታቱ ኦርቶዶክሳውያን የነበሩ መሆናቸው እውነት ነው፡፡ነገሥታቱ በአገዛዛቸው ዘይቤ ኦርቶዶክሳዊነት የተጫነው religious nationalism አዝማሚያ እንደሚያሳዩና ለኢኦተቤክ አበው የተለየ ውዴታና ከበሬታ እንደነበራቸውም አይታበልም፡፡ኦርቶዶክሳውያን አበው (ጳጳሳት) ንጉሡ በእነሱ እምነት ማደሩን እና እስከ ፍጻሜ ዘመኑም በእምነቱ እንደሚጸና ቃል አስገብተው ይቀቡት እንደነበር እሙን ነው፡፡ይሄ አሰራር ይብዛም ይነስም በሁሉም ቀደምት የነገሥታት ሥርዓት በሰፈነባቸው አህጉር ያለ ነው፡፡በኦሮሞ ጥንታዊ የገዳ ባህልም ተሞክሮው ያለ ይመስላል፡፡ለአባ ገዳነት ለመብቃት ቅብዐተ-ቃሉ (በቃሉ መቀባት) ስለማስፈለጉ ታቦር ዋሚ ብሩ ጸጋዬን ጠቅሶ ሲጽፍ ‹‹…ለአባ ገዳነት ለመብቃትም ዋነኛው መመዘኛ የዋቄፈና ሃይማኖትን አክብሮና የሕዝቡን ወግና ሥርዓቶች ተከትሎ መገኘት ሲሆን…የሉባዎች ስልጣን የሚጸድቀው በቃሉ (አባ ሙዳ) የቡራኬ፣የምርቃትና መቀባት ሥርዓት ነው›› ይላል (ታቦር ዋሚ፡ገ.248)፡፡እርግጥ የአባ ገዳ ሲመት በዘር ሳይሆን በምርጫ መሆኑ ተራማጅ ያሰኘዋል፡፡
(1.7) ወደ ሐተታዬ ስመለስ ነገሥታቱ ለኢኦተቤክ እንደሚባለው ‹‹ሲሶ መንግሥት›› ባይሆንም መጠነኛ እርዳታ ሲያደርጉ መኖራቸውም እውነት ነው፤ኦፌሴላዊ ቋንቋቸውም ለረጅም ጊዜ የኢኦተቤክ መገልገያ የሆነው ግእዝ እንደነበረም እናውቃለን፡፡ያ!ማለት ግን ዜና-መዋዕል ጸሐፊዎች በግእዝ የሚጽፉት ሁሉ የኢኦተቤክ ዶግማና ቀኖና ነው፤ወይም የኢኦተቤክ የውዳሴና ቅዳሴ ዶክመንት ነው ማለት አይደለም፡፡ግእዝ ቋንቋ ነው፡፡እምነት፣ፍልስፍና፣ኑፋቄ፣ታሪክ፣ጥንቆላ፣…ይጻፍበታል፡፡ስለዚህ ይሄን ሳያስተውሉ የኢኦተቤክ በግእዝ ቋንቋ ለተጻፈ ዶክመንት ሁሉ (በተለይ ለነገሥታ ዜና-መዋዕል) ኃላፊነት አለባት ማለት በላቲን ፊደልና ቋንቋ ለተጻፈ ሁሉ ካቶሊኮች ተጠያቂ ናቸው፤ወይም ደግሞ በዐረብኛ ለተጻፈ ሁሉ እስልምና ተጠያቂ ነው እንደማለት ይሆናል፡፡
(1.8) ‹‹ጋላ›› ወደሚለው ቃል አጠቃቀም ልምጣ፡፡ዛሬ አንዳንድ ኦሮሞ ወንድሞቻችን ሚሽነሪዎች ‹‹ጋላ›› የሚለውን ቃል ስለማይጠቀሙ ወደ ወለጋ ያቀኑ ሚሽነሪዎች ተቀባይነት አገኙ ይሉናል፡፡ሸጋ፡፡ሚሽኖችን እንስማቸው፡፡<<The Missinories referred to the Oromo as the Hamitic [non-semetic] GALLAS who spoke GALLINYA.They used this condescending term…as late as 1973, nearly ten years after working with Oromo…>>ይላሉ(GilchrristII:73) (አጽንኦቱ የኔ ነው)፡፡የሚያሳዝነው እነዚህ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ሚሽኖች ከ10 ዓመትና ከዚያ በላይ (ለምሳሌ፡- የMissio-Galla ባለቤቱ ካቶሊኩ አባ ማስያስ ከ145-1880 ዓ.ም ለ35 ዓመታት እንዲሁም የVicariatus Apostolici apud Gallas Commentarium Historicum ab erectione Vicariatus usque hodie ባለቤቱ አባ ጃሮሶ ከ1882-1938 ዓ.ም ለ46 ዓመታት) በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ቋንቋውን (አፋን ኦሮሞ) እየተናገሩ ኖረው በእንግሊዝኛና ጣሊያንኛ ተጠቃሽ መጻሕፍቶቻቸው ‹‹ጋላ›› የሚል ቃል የሚጠቀሙት ‹‹በአቢሲኒያ ቄሶች›› ተጽእኖ እንደሆነ ለማስመሰል ይሞከራል፡፡ያሳዝናል፡፡መቼም ‹‹የአቢሲኒያ ቄሶች›› ተጽእኖ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ ተጓጉዞ ለሚታተም የሚሽነሪ መጽሐፍ እንዴት ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሚሆን እነሱና ደቀ-መዛሙርቶቻቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት!!
(1.9) ወደ ቤ/ክ መጻሕፍት እንመለስ፡፡ቢያንስ ስለቅኔ ቤት እና ዜማ ቤት ምስክር መሆን እችላለሁ--ስላለፍኩባቸው፡፡በነዚህ ጉባኤያት ‹‹ጋላ›› የሚል የግእዝ ቃል አልሰማንም፡፡በሌላ በኩል በውዳሴ ማርያም የአንድምታ ትርጓሜ የ1990 እትም ላይ በገጽ-86 እንዲህ የሚል ቃል ይገኛል ‹‹…በግብፅ የሚገኙ መነኮሳት በአመት ሁለት ጊዜ ያበስላሉ፡፡…ከአኃው [መነኮሳት] አንዱ ቢታመም ትኩስ እንጀራ የሚያመጣልኝ ባገኘሁ በቀመስሁት ነበር አለ፡፡ከዚህ በኋላ አንዱ የማን ወንድም ትኩስ እንጀራ እያለ ይሞታል ብሎ በመካከሉ <በርበር የሚባል ጋላ> ያለበት ነው፤ያንን አልፎ ሄዶ አምጥቼልሀለሁ ቅመስ አለው…›› እያለ ‹‹ጋላ›› ማለትን ለሽፍታ በርበር ሰጥቶ ይተርክልናል፡፡ በቅ/ያሬድ የኅዳር 29 የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅ/ጴጥሮስ ድጓና በእለቱ ስንክሳር ‹‹ጋላት›› (በግእዙ ‹‹ላ›› ላልቶ ነው የሚነበብ) የሚል ቃል ይገኛል፡፡ቅ/ያሬድ በዐረብ ምድር በ4ኛው ክ/ዘ ስለተሰዋው ተፍጻሜተ - ሰማዕት ጴጥሮስ ሲያዜም ‹‹…አባ ጴጥሮስ ተፍጻሜ-ሰማዕት፣መጠወ ርእሶ ለ‹ጋላት›….›› ይለናል፡፡ቅ/ያሬድና የውዳሴ ማርያም መተርጉማን ቃሉን ለሰሜን አፍሪካ ኢ-ክርስቲያን የ3ኛው መቶ ክ/ዘ በርበሮች ሰጥተው ነው የሚናገሩት፡፡ከዚህ ውጭ እኔ ባጭር ዘመኔ ባነበብኳቸው የኢኦተቤክ መንፈሳዊ መጻሕፍት ‹‹ጋላ›› ስለሚለው ቃልና ስለብያኔው አላገኘሁም፤አልተማርኩም፡፡በቅኔ ቤት ‹ደብተራ› ተብለን የተማርንበት የእጅ ጽሑፍ ግስ (መዝገበ-ቃላቱን ግስ እንለዋለን) ‹‹ጋላ›› የሚል ቃል በፍጹም የለውም፡፡የእጅ ጽሑፉ ዛሬም በመጽሐፍ መደርደሪያዬ ያለ ነው፡፡
(1.10) ስለሆነም ይሕን ቃል ‹‹የኢኦተቤክ ደባትር ፈጠራ ነው›› በሚል ድምዳሜ ቤተክርስቲያኒቱንና ሊቃውንቷን በምልዐት ከሥርዓታቱ ጋር አላጥቆ ፈርጆ በጭፍን ከማሳደደድ በፊት ግራቀኙን ማየት አይከፋም፡፡ቢያንስ በተጓዳኝ የዚህን ቃል ምንጭ ዐማራን ጨምሮ በከፋ፣ሐዲያ፣ሲዳማ፣ጋሞ፣ትግራይ፣ሶማሌ….ከመሳሰሉ ብሔረሰቦች ቋንቋ ውስጥ ማሰስ፣ወደ ጎረቤት ሶማሊያና ኬንያ የታሪክ ጽሑፎች ጎራ ብሎ መጠየቅና ሰነድ ማገላበጥ፣ከሩቅ ዘመን ጀምሮ በምድረ-ኦሮሚያ ኖረው በአውሮፓ መጻሕፍትን ያሳተሙ የሚሽነሪ ጽሑፎችን በጥንቃቄ ማገላበጥ የተሻለና ሚዛናዊ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡Thomas Zitelman የተባለው ጸሐፊ በBeing and Becoming Oromo የጥናት መጽሔት Re-Examining the Galla/Oromo Relationship የተሰኘ ጽሑፉ ዘመናዊውና የታደሰው የኦሮሞ ማንነት ቅርጽ የያዘው በስዊድን ሚሽነሪዎች ነው የሚል ምልከታውን ገልጹዋል፡፡እንጥቀሰው <<During the late 19th C the Swedish Protestant missionray activities at Monkullo [Eritrea] provided a contextual frame for a modern reformation of being Oromo, by mixing Protestant zeal,romantic European nationalism and elements of Oromo past>> >>ይላል(Being and Becoming Oromo:p.108)፡፡እንጠርጥር ካልን ይቺ ጽሑፍ የሚሽነሪዎች ተጽእኖ በጎላባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ሰባክያኑ ከስብከታቸው ጋር ‹‹የአቢሲኒያዎች ቤ/ክ ለኦሮሞ ‹ጋላ› የሚል አዋራጅ ስም ስላወጣች አትሆናችሁምና አዲስ ማንነት በፕሮቴስታንታዊነት ተላበሱ የሚል ብሔር-ተኮር ቅስቀሳ በወለጋ አካባቢ ሳይካሄድ እንዳልቀረ ታመላክታለች›› ብለን መጥርጠር ይቻላል፡፡ይቺ-ይቺ ፀረ-ተዋሕዶ የሚሽኖች ስብከት ተጠራቅማ የኦሮሞ ማንነትን በአዲስ እይታ ለመቅረጽ የተጉ ምሁራነ-ኦሮሞ የሆኑ ጸሐፍት ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል--“fabricated by an Abyssinian clergy for politico-ideological reasons” እያሉ ለጥጠው እንዲጽፉ አበረታታች፡፡ጥርጣሬዬ ነው!!!የሚሽነሪዎቹ ተደጋጋሚ ጸረ-ተዋሕዶ ምዕራባዊ ጽሑፎች የወለዱት ጥርጣሬ!!

2-- ክስ-ሁለት፡-የኢኦተቤክ መዋቅር እኩልተኛ ስላልሆነ ኦሮሞዎች አይጋሩትም!!

የታሪከ-ኦርቶዶክስ ሊቅ ተደርጎ በነመሐመድ ሐሰን (ዶ/ር) እና በነአባስ ሐጂ (ዶ/ር) እዚህም እዚያም የሚጠቀሰው መኩሪያ ቡልቻ (ዶ/ር) <<Oromo Orthodox Christians, though they share religion with Abyssinians, do not share the political/ideological orientation of the Ethiopian Church whose main interest was the preservation [of] structural inequalities enshrined in myths and legends>>ይሉናል(Mekuria cited in Abbas Haji:106)::ታድለው!እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ <የታለ ያደረጋችሁት የመስክ ጉብኝት፣የታለ ለኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን የተደረገው ቃለ-መጠይቅ፣የታለ በየሃማኖቶቹ መካከል ለንጽጽር የሰራችሁት የዳሰሳ ጥናት?> የሚላቸው የለም፡፡የፈለጉትን ቢጽፉ ቋንቋው እንግሊዝኛ እስከሆነ ድረስ ‹‹የደብተራ ተረት›› አይባልባቸውም፡፡ታድለው!ከዚህም ከዚያም እያገጣጠሙ ለያዙት ዐላማ እና ለታደሙበት ድርጅት የሚሆን ታሪክ በልክ ይሰፋሉ፡፡ወደ ሕዝቡ ወርደው አያጠኑም፡፡ብቻ መርጠው ይተነትናሉ፡፡ታሪክ ማለት ትንታኔ፤ትንታኔ ማለት ታሪክ ይሆናል፡፡
(2.1) እስኪ የኢኦተቤክ አደረጃጀት ይታይ፡፡ጥንት ‹‹የሊቃውንት ጉባኤ/ማኅበረ-መነኮሳት/ማኅበረ-ካሕናት›› የተሰኘ የውስጥ ሃይማኖታዊ አስተዳደሩን፣ዶግማና ቀኖናውን የሚበይን አካል ነበረ፡፡ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ የኢኦተቤክ ከግብፅ መንፈሳዊ የሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥታ የራሷን ቅ/ሲኖዶስ ሰይማለች፡፡ፓትርያርኩ ከፋም ለማም ላለፉት 56 ዓመታት የሚሾመው በምርጫ ነው፡፡በአጥቢያ ደረጃ ባለው አደረጃጀት ከምዕመናንና ካሕናት የተውጣጣ ‹‹ሰበካ-ጉባኤ›› የተሰኘ አካል ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በ3ቱም ሥርዓታተ-መንግሥታት ያለማቋረጥ እየተመረጠ ቤ/ክ’ንን በማስተዳደር ላይ ይገኛል--ከፋም ለማም፡፡በደርግም አልተቋረጠም፡፡መራጩ ምዕመኑና ካሕኑ ነው፡፡እርግጥ <ዲሞክራሲ፣አሴምብሊ፣ካውንስል፣…> የሚሉ ቃላትን ባለመጠቀማችን ዲሞክራሲ ላይ በኋላቀርነታችን ለሰራነው በደል ዘመናዊ ዲሞክራት ጸሐፊዎቻችንን መጠየቅ ይኖርብናል!!
(2.2) እገምታለሁ፡፡ይሕ የ40 እና የ50 ዓመታት ተሞክሮ የሃይማኖቱን ብሉይ ታሪክ አይገልጽም ይባል ይሆናል፡፡ገዳማቱ ይመርመሯ!!!በስተሰሜኑ ማዕከላዊ ኦሮሚያ ያለውን ገዳም እንምረጥ--የሰላሌውን ደ/ሊባኖስ!!የገዳሙ መሪ ጥንት ‹እጨጌ› አሁን ‹ፀባቴ› ይባላል፡፡ብቻውን በገዳሙ ላይ የማዘዝ መብት የለውም፡፡<ምርፋቅ> በሚል ስም የሚጠራ 12 ተመራጭ መነኮሳት የሚሰየሙበት የመማክርት ጉባኤ አለ፡፡መራጮቹ የገዳሙ አባላት (መነኮሳት) ናቸው፡፡ተመራጮቹ አጠቃላዩን የገዳሙን ሕግ ከጸባቴው (አስተዳዳሪው) ጋር በመሆን ይደነግጋሉ፤ያጠፋውን ቀኖና ይሰጣሉ፤የአባላትን ቅሬታ ይፈታሉ፤ፀባቴውን ይቆጣጠራሉ፤በገዳሙ ወጣ ያለ ባሕርይ የሚያሳይ መነኮስ ካለ ጾምና ስግደት በመበየን በገዳሙ ማረሚያ ቤት እስከመላክ የሚያደርስ የውስጥ ሕግ ነበረ፡፡የገዳሙ አባል መነኮሳት በምርፋቅ አባላት ላይ ቅሬታ ካላቸው እንዲሁ ቅሬታቸውን አቅርበው ምርፋቁን አውርደው በሌላ ምርፋቅ ይተኩታል፡፡ይሕ ሥርዓት ትናንት ነበረ፤ዛሬም አለ፤ወደፊትም እስከ ምጽአተ-ክርስቶስ ይኖራል ብለን እናምናለን፤አምነን እንናገራለን!!
(2.3) ይሕን አሰራር እነ መኩሪያ ቡልቻ ከሚያወድሱት የአባ ሙዳ አሰራር ጋር እናነጻጽረው፡፡መኩሪያ ቡልቻ <<The Office of Aba Muuda was…open to the Oromo people as a whole and was visited by delegates from every ‘gosa’ and from different parts of Oromo-land, but non-Oromos were not allowed to participate in rituals>>ይላል(Being and Becoming Oromo:53)::በተጨማሪም አባ ሙዳ ወይም ቃሉ (መራሄ-ዋቄፈና) ለመሆን የሚቻለው በዘር ማለትም ከአባት ወደ ልጅ በሚተላለፍ የተወላጅነት ሰንሰለት ብቻ እና ሲመቱም እስከ እድሜ ልክ (እንደ የኢኦተቤክ የፕትርክና ቀኖና) መሆኑን ታቦር ዋሚን ጨምሮ ብዙ ጸሐፍተ-ኦሮሞ አረጋግጠዋል (ታቦር ዋሚ፡ገ.221)፡፡እንግዲህ እኩልተኛ ሥርዓት ማለት ሁሉም እንዳቅሙ እንዲወዳደር የውድድር እድል (equal opportunity) የሚከፍት ማለት ከሆነ እንደ ኦሪት ሌዋውያን ዘርና ብሔርን (ኦሮሞን ብቻ!) መሰረት አድርጎ የሃይማኖት መሪነትን የሚያወራርሰው ዋቄፈና እየተወደሰ በሌላ በኩል ላመነ፣ለተጠመቀና መንፈሳዊውን እውቀት ለጨበጠ ሁሉ እንኳንስ ብሔር ዜግነት ሳይመርጥ ለሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ክፍት ሆኖ የኖረው ቤተመቅደስ በpreservation [of] structural inequalities ሲከሰስ መስማት ግራ ያጋባል፡፡ብቻ ግን በዛሬው የUNDHR ዘመን ‹‹ዘእምነገደ-ይሑዳም ሆነ፤ዘእምነገ-ሙዳ ጊዜውን የዋጁ ሥርዓታት አይመስሉም›› ብለን እንለፍ!!

3-- ክስ-ሦስት፡- አለቃ ታዬ እና አቶ አጽሜ የኢኦተቤክ ደብተራዎች ናቸው!!

እነዚህን ሰዎች (አለቃ ታዬንና አቶ አጽሜን) መሐመድ ሀሰን፣አባስ ሐጂ፣መኩሪያ ቡልቻ፣ታቦር ዋሚ በስፋት ጠቅሰው ጽሑፋቸውን ሲመቻቸው ግብዐት አድርገውታል፡፡በጽሑፎቻቸው ‹‹የራሷ የኢኦተቤክ ጸሐፍት አለቃ ታዬና አቶ አጽሜ እንዲህ አሉ›› ለማለት ከሰዎቹ ስራ ሐሜት ሐሜቱን ነቃቅሰው እንደማጠናከሪያ ተጠቀመውበታል፡፡ሳይመቻቸው ቤተክርስቲያኗን ከነአለቃ ታዬ ጋር እየደረቡ ጭምር ጽሑፋቸውን በአያሌው አጣጥለውታል፡፡እሱ ችግር የለውም፡፡መብታቸው ነው፡፡ችግሩ ሰዎቹ የቤተክሕነት ወኪልና የኢኦተቤክ ደባትር እንደነበሩ ተደጋግሞ መጠቀሱ ነው--ያልሆኑትን!!እስኪ ባጭሩ ታሪካቸውን ከሃይማኖት አንጻር ብቻ በጨረፍታ እንይ…
(3.1) አቶ አጽመጊዮርጊስ (1825-1907 ዓ.ም) የሰሜን ሸዋ ተወላጅ (ዐማራ?) ናቸው፡፡ስለ ኦሮሞ በታሪክም በጸያፍም ሊታይ የሚችል ታሪክ ጽፈዋል፡፡እሱ የኔ ማጠንጠኛ አይደለም፡፡የኔ ማጠንጠኛ የእሳቸው ጽሑፍ የኢኦተቤክ አቋም ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ማስረገጥ ነው፡፡ምክንያቱም እሳቸው የኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ አባል አልነበሩም፡፡እንዲያውም እድል ባገኙ ቁጥር ኦርቶዶክስን የሚያጥላሉና የካቶሊክ ሚሲዮናውያን በስፋት ሀገሪቱ ላይ አለመንሰራፋት የሚያንገበግባቸው፣የነአባ ማስያስ ሚኒልክን ካቶሊክ ማድረግ አለመቻል የሚቆጫቸው፣የሱስንዮስ ዘመን የሚናፍቃቸው ሰው የነበሩ ስለመሆናቸው አንዳንድ ቃላቶቻቸው ያሳብቃሉ፡፡ጭልጥ ያሉ ካቶሊክ ነበሩ፤ያውም የኢኦተቤክ እና የካሕናቷ ከሳሽ፡፡ማስረጃ እናምጣ፡፡ፕ/ር ታምራት አማኑኤል በጻፉት ‹‹ስለኢትዮጵያ ደራሲያን›› የተሰኘ ምጥን መጽሐፍ በገጽ-14 ይኸንኑ የአቶ አጽሜን ጸረ-ኦርቶዶክስ አቋም ሲገልጹ ‹‹በካቶሊክ ሃይማኖት ያዲሱ ትውልድ ዘመን ሰው ስለነበሩ ለሃይማኖታቸው የነበረባቸው ቅንኣት በኦርቶዶክሳውያን ወገን ላይ ምክንያት ባገኙ ቁጥር ከልክ ያለፈ የተግሳጽ ቃል አስጽፉዋቸዋል፡፡አንዳንድ ጊዜም ታሪኩ መንገድ ሳይሰጣቸው በኦርቶዶክሳውያን ላይ የኃይል ቃል ለመጻፍ ምክንያቱን በግድ ፈልገው ያመጡት ይመስላል›› በሚል አስፍረዋል፡፡አቶ አጽሜ ለኦሮሞ የተቆረቆሩ መስለው የሚሽኖችን አለመምጣት በቁጭት ያነሳሉ፡፡የጦሩን መሪ ንጉሥ ምኒልክ ትተው በዐማራነት የፈረጇቸውን የኢኦተቤክ ካሕናትን ክፉኛ ይወርፋሉ፡፡የእሳቸውን የአጻጻፍ መንፈስ፣የውስጣቸውን ካቶሊካዊ ቅናትና መነሳሻ (motive) ያላጤኑ እንደነመሐመድ ሐሰን አይነት ጸሐፍት የእሳቸውን የጥላቻ ቃል እንዳለ እየወሰዱ ያጮሁታል (JOS:vol-7:p119)፡፡እነመሐመድ እና ጓዶቻቸው የካቶሊኮችን፣የሙስሊሞችንና ፕሮቴስታንቶችን ጽሑፎች ብቻ እየጠቀሱ ኦርቶዶክሳውያን ዶክመንቶችንና አማንያኑን ሳያመሳክሩ ስለኢኦተቤክ መጻፍን እንደልማድ መያዛቸውን ገና ወደፊትም በዚህ አጭር የዳሰሳ ጽሑፍ እናገኘዋለን፡፡አሁን ወደሌላው የኢኦተቤክ ደብተራ ወደተባሉት ጸሐፊ እንለፍ--ወደ አለቃ ታዬ ገብረማርያም!
(3.2) አለቃ ታዬ በ1853 ዓ.ም በጌምድር (ጎንደር)ተወለዱ፡፡ከአድዋ ዘመቻ በፊት (በ1872 ዓ.ም አካባቢ) ወደ ሐማሴን (ኤርትራ) ምንኩሉ የተባለ የስዊድን ሚሲዮናውያን ማረፊያ ሄደው ፕሮቴስታንት ሆኑ፡፡እዚያ ሳሉ ከምዕራባዊው ትምህርት ይልቅ ወደ ምስራቁ አዘነበሉ፡፡የግእዝ መጻሕፍት መመርመር ጀመሩ፡፡ለዚሁ እንዲረዳቸው ወደ ጎንደር ተመልሰው በ1875 ዓ.ም ቅኔ-ቤት ገቡ፡፡በ1877 ዓ.ም ቅኔ ተቀኝተው (ቤት ሞልተው ነው የሚባለው በባሕሉ) ተመለሱ፡፡በምንኩሉ ሚሲዮን አስተማሪ ሆኑ (ደማቆቹ፡ገ.57-68)፡፡ጥሩ የንባብ ተሞክሮ በቤተ-ፕሮቴስታንት ስላዳበሩ በእነሱ እርዳታ በ1889 ዓ.ም የግእዝ ሰዋስው አሳተሙ፡፡በሚሲዮናውያኑ የተልእኮ-ድጋፍ (ስፖንሰርሺፕ) ጀርመንኛ እና ፈረንሳይኛ አጥንተው በጀርመን የግእዝ አስተማሪ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ከዚያ መልስ በጎንደር ያባታቸው (አቶ ገ/ማርያም) ርስት ተፈቅዶላቸው እስከ 1903 ዓ.ም ይኖሩ ነበር፡፡‹‹...ይሁን እንጂ በደብረ ታቦር ሳሉ ‹ጻድቃን አያማልዱም› በሚል ክርክር ከካሕናት ጋር ስለተጋጩ ብዙ ጭቅጭ አገኛቸው፡፡በመጨረሻም በዚሁ ክርክር ምክንያት ወደ አዲስአበባ ተላለፉና ከአቡነ ማቴዎስ [ግብጻዊው] ፊት ቀርበው ነገሩ ከታየ በኋላ ከኢኦተቤክ [በውግዘት] ተለይተው የሚሲዮን ማኅበር አባል ሆነው ተቀመጡ፡፡›› (መርስዔኀዘን ወልደቂርቆስ፡ገ.146)፡፡ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አለቃ ታዬ ከኢኦተቤክ ተገልለው እስከ እለተ-ሞታቸው ነሐሴ 15 ቀን 1916 ዓ.ም በመንግሥት ሠራተኛነት ታሪክ ሲጽፉ የነበረ መሆኑ አይካድም፡፡ነገር ግን ምንም እንኳ ከ19 ዓመታቸው ጀምሮ በፕሮቴስታንት እምነት በድብቅ ገብተው የኖሩ ቢሆንም የኢኦተቤክ ልጅነታቸው የታሪክ መጽሐፉን ከመጻፋቸው ከ13 ዓመታት በፊት (በኅቡዕ ፕሮቴስታንት መሆናቸው ከታወቀ ከ31 ዓመታ በኋላ) በ1903 ዓ.ም በይፋ ተቋርጡዋል፡፡ይሄው የብላታ መርስዔኀዘን መጽሐፍ በገጽ-147 ኅዳግ እንደሚተርከው አለቃ ታዬ በተወለዱ በ63 ዓመታቸው (ፕሮቴስታንት በሆኑ በ44ኛው ዓመት) በሞት ሲለዩም በኢኦተቤክ ለመቀበር ተናዝዘው ስለነበር አስከሬናቸውን ለማሳረፍ የቅ/ሥላሴ ካቴድራል ካሕናት በንግሥት ዘውዲቱ ሳይቀር ቢለመኑ ‹‹ይሕ ጸረ-ማርያም በቤተክርስቲያናችን አይቀበርብንም›› ሲሉ ተቃውሞ በማንሳታቸው የአለቃ ታዬ አስከሬን ወደ ጉለሌ ተወስዶ በፕሮቴስታንት መካነ-መቃብር ተቀብሯል፡፡እንግዲህ የኢኦተቤክ በቁም አውግዛ የለየችው፣በሞቱም ‹ሃይማኖት የለያየንን መቃብር አንድ አያደርገንም› ብላ ባመነበት አዲስ እምነት ካረፉ አዳዲስ አማንያን ወገኖቹ መቃብር ጎን እንዲያርፍ የጥምቀት ልጅነቱን ገፍፋ ቅጽሯን የዘጋችበት እና አንድም ጽሑፉን ያልተቀበለችው ዐለቃ ታዬ ነው ‹‹የኢኦተቤክ ደብተራ›› እየተባለ በየቦታው ከላይ በጠቀስኳቸው የኦሮሞ ጸሐፍት ስሟ የሚብጠለጠለው፡፡በዚህ አያያዝ ዛሬ ከኦሮሞ ብሔርተኞች ጋር ጽንፍ ረግጠው የሚወራከቡት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እና ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌም ወደፊት ‹‹የኢኦተቤክ ደባትር›› ላለመባለቸው ዋስትና የለም!!

4-- ክስ-አራት፡- ኦርቶዶክስ ኦሮሚፋን ትጸየፋለች!

እውቁ የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊ መሐመድ ሀሰን በJOS (Journal of Oromo Studies.volume-7) ገጽ 118 ላይ በወጣ ጽሑፉ ጆቴ የተባለ ደራሲ ጠቅሶ <<The Amhara clergy failed to capture the hearts and minds of the Oromo by their total failure to use the Oromo language for their missionary work.Infact upto 1993, the Oromo language was considered too profane to be used by the Church>> ይለናል፡፡ሸጋ፡፡በምስማማበት ተስማምቼ ልጀምር፡፡የኢኦተቤክ ኦሮሚፋን ለስብከተ-ወንጌል ድሮም ሆነ አሁን (አሁን ላይ እጅግ መሻሻል ቢኖርም) በቅጡ ተጠቅማበታለች ብዬ አልዋሽም፡፡ነገር ግን ይሕ የሆነው መሐመድ እና ጆቴ እንደሚሉት ለኦሮሚፋ በተለየ መልክ ጽዩፍ (too profane) ሆና ነው ብየ አላምንም፡፡ላስረዳ፡-
(4.1) ዐማርኛ ራሱ በሊቃውንቱ ለቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም አገልግሎት መስጠት የጀመረው በጎንደር ዘመነ-መንግሥት ወቅት ያውም ካቶሊካውያንና ፕሮቴስታንቶች የሰሜኑን ሕዝብ በአካባቢው ቋንቋው እያስተማሩ ምዕመኑን ማስኮብለላቸው ባሳደረው ጫና ነው፡፡ዐማርኛ በተደራጀ መልኩ ለመጻሕፍት ትርጓሜ የዋለበትን (የወቅቱ የትርጓሜ መንገድ በራሱ የግእዝ ተጽእኖ እጅግ ቢበረታበትም) ትክክለኛውን ጊዜ ስናስቀምጠው በአጼ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን (ከ1674-1694) ስለመሆኑ በሚሊኒየሙ የታተመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000ዓ.ም) መጽሐፍ በገጽ 187 አብራርቶ ያቀርብልናል፡፡ዐማርኛ በሥርዓተ-ቅዳሴ መካከል ለመነገር የበቃው ደግሞ ከ1913 ዓ.ም ወዲህ አባ ኪዳነማርያም በተባሉ የዋድላ (ወሎ) መነኩሴ አማካይነት ስለመሆኑ መርስዔኀዘን በገጽ 143 ተርከውልናል፡፡
(4.2) ከትርጉም ጋር በተያያዘ ጥቂት ግነት ያለበት ቢመስልም ሐቁን ያላጣውና ተስፋዬ ቶሎሳ በተባሉ አጥኚ የአፋን ኦሮሞን ጽሑፋዊ የታሪክ ሂደት የሚዳስስ የጥናት ወረቀት ገጽ-77 የተጠቀሰው የጀምስ ብሩስ አስተያየት ይታይ፡፡ብሩስ <<...there is an old law in this country (Ethiopia), handed down by tradition only, that whoever should attempt to translate the holy scripture into Amharic, or any other language his throat should be cut....>> በማለት ልማዳዊ ሕጉ ከግእዝ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ዐማርኛን ጨምሮ ይሰራ እንደነበር ይተርካል፡፡ልማዳዊ ሕጉ በአብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ አሁን ድረስ ሕያው ነው፡፡ጸሎትና ቅዳሴው ለግእዝ ያደላ ነው፡፡በትግራይ፣በጎጃም፣በጎንደር፣በወሎ እና በሸዋ ግእዝ ጠቅሶ የማይሰብክ ሰባኪ እንኳንስ በካሕናቱ በምዕመናኑም የሚሰጠው ክብር እምብዛም ነው፡፡ሕዝቡ ለግእዝ ያደላል፡፡እዚያ በአማርኛ/ትግርኛ ብቻ ብትንደቀደቅ ‹‹ስብከቱ ጥሩ ነበር፤ግና ‹ቦለቲካ› በዛው›› ይልሀል፡፡
(4.3) ተስፋዬ ቶሎሳ በጥናቱ የቀደሙ ነገሥታትን የኦሮሚፋ ቋንቋን ጨቋኝነት በስፋት ቢገልጽም እ.ኤ.አ በ1877 ዓ.ም አለቃ ዘነብ (እኒህ ሰው የአጼ ቴዎድሮስን ዜና-መዋዕል የጻፉ የሸዋ ተወላጅ ሲሆኑ የጉራጌ ሕዝብ ከምኒልክ ጋር በተዋጋ ጊዜ ተገድለዋል--አለቃ ዘነብ) ለአጼ ምኒልክ መጽሐፈ-ኢያሱን፣መጽሐፈ-መሳፍንትን፣መጽሐፈ-ሩትን እና መጽሐፈ-ሳሙኤልን ወደ ኦሮሚፋ ተርጉመውላቸው በአውሮፓ ሊያሳትሙ ሲሉ ለማሳተም ቃል የገባላቸው ሚሲዮናዊው Krapf ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ኅትመቱ እንዳልተከናወነ የፓንክረስትን የ1976 እትም መጽሐፍ ጠቅሶ አስቀምጦታል፡፡‹‹ደማቆቹ›› የተሰኘ በመፍቀርያነ-ፕሮቴስታንት ጸሐፍት የተዘጋጀ መጽሐፍም ስለ አናሲሞስ ነሲብ ሲተርክ ይህንኑ የአለቃ ዘነብን ውጥን አንስቶታል (ደማቆቹ፡ገ.29)፡፡አናሲሞስን ከአጼ ምኒልክ ያገናኙት አቡነ ማቴዎስ እንደሆኑ፣አናሲሞስም ለአጼ ምኒልክ የኦሮምኛውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳበረከተላቸው፣ንጉሡም አናሲሞስን አጃቢ ባልደረባ ሰጥተው ወደ ወለጋ እንደላኩት ይኸው መጽሐፍ (ደማቆቹ) ይገልጻል፡፡የኢኦተቤክ ያላትን አስተምህሮ ሳይቃረን እንዲያስተምር ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ (ግብጻዊ) ራሳቸው ለአናሲሞስ ነግረውት ነበር፡፡ጳጳሱ ለወለጋው የወቅቱ አስተዳዳሪ በጻፉት ደብዳቤም ይሕንኑ አሳውቀዋል፡፡እንጥቀሰው ‹‹...እጅግ ለተከበርከውና ለተወደድከው ደጃዝማች ገብረእግዚአብሔር እንዴት አለህ?እኔ የማርቆስ አምላክ ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ይሕ ከወደብ (ኤርትራ) የመጣው ኦኔሲሞስ ወደ እኛ መጥቶ እንዲያስተምር ጠይቆናል፡፡ከቤተክርስቲያናችን ትምህርትና እምነት የተለየ ጕዳይ አስተምሮ እንደሆነ እንድናውቀው አድርግ፡፡ነገር ግን ከኛ ትምህርትና እምነት ያላፈነገጠ ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ ይቀጥል፤ማንም አንዳች አይበለው›› (ደማቆቹ፡ገ.33)፡፡እርግጥ ነው በኋላ ዘመኑ አናሲሞስ ችግር አጋጥሞታል፡፡ነገር ግን ችግሩ የገጠመው ኦሮሚፋን ተጠቅሞ በመስበኩ ሳይሆን የተሰጠውን መመሪያ ጥሶ ከኢኦተቤክ ዶግማና ቀኖና የሚጋጭ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት በማስተማሩ ነው፡፡ ይሕ ደግሞ በእሱ ላይ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ባስተማሩት ጎንደሬው አለቃ ታዬ፣ካቶሊካዊ ትምህርት ባስተማሩት ጎጃሜው አባ ገብረሚካኤል (በአጼ ቴዎድሮስ ታስረው ሳለ ስላረፉ ቫቲካን እንደ ብፁዕ ሰማዕት ነው የምታያቸው)፣በልዩ ልዩ የጸጋ-ተዋሕዶ-ቅባት ክርክሮች ወቅት በዐማራና በትግራይ ሊቃውንትም ዘንድ የደረሰ ነው--መሳደዱ፡፡ስለሆነም ዛሬ ላይ ቆሜ አንድ ሰው በእምነቱ የተነሳ መሳደድ እንደሌለበት በሙሉ ልቤ ባምንም ገና ወለጋ ለምኒልክ ሳይገብር በአካባቢው በሰፈነው የባርነት ንግድ በ1854 ዓ.ም (ምኒልክ በዚህ ጊዜ በመቅደላ እስር ቤት የአጼ ቴዎድሮስ እስረኛ ነበሩ) ተሽጦ ኋላ በሚሲዮናውያን አርነት ከወጣ በኋላ ለኦሮሚፋ ቋንቋ ታላቅ ውለታን የሰራው አናሲሞስ የተሳደደው በኦሮሞነቱ እና በኦሮሚፋው ነው ብዬ አላምንም፡፡የወቅቱ የኢኦተቤክ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ቋንቋ ሳይለዩ አናሲሞስ ስለኦርቶደክስ እንዲሰብክ የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡ስብከቱን ለፕሮቴስታንታዊ ተልእኮ ሲጠቀምበት ግን ወቅቱ በፈቀደው ሕግና ሥልጣን ስብከቱን ለማገድ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ይህ እንቅስቃሴያቸው ከሃይማኖት ነጻነት ጋር እንጂ ከቋንቋ ነጻነት ጋር አይገናኝም ብዬ አምናለሁ፡፡ሌላ ዋቢ እንጥራ!
(4.4) ከሆሮ-ጉድሩ ተማርኮ ኋላ በምድረ-ጎጃም ታላቅ ካሕን፣ጸሐፊ እና የተመሰገነ ሠዐሊ የነበረው አለቃ ተክለኢየሱስ (ነገሮ) ዋቅጅራ በ1891 ዓ.ም በኦሮሞ-ቤት (ሆሮ-ጉድሩ) ስለተካሄው የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ጉዞ (ጦርነቱ በ1871 ዓ.ም ተጠናቋልና ይሄኛው ጉዞ ለጦርነት አይደለም፤ለቤ/ክ ግንባታ እንጂ) እንዲህ ይተርካል ‹‹...የዚህ ጊዜ ንጉሥ ተክለሃይማኖት...ኦሮሞ ቤት ዲለሎ ከሚባል ቦታ ሲደርስ ቤተክርስቲያን ሲሰራ ባጀ፡፡...ኦሮሞውን ሁሉ አሳምኖ ብዙ ታቦት ተከለ፡፡ተሠሪ ሠራበት፡፡...[በ1871 ዓ.ም ከሆሮ-ጉድሩ ማርኮ] ያሳደጋቸውን ኦሮሞዎች ሁሉ ከዘመድ እያስተዋወቀ ለነሻቃ ይርባ [ሂርጳ?]፣ለነሻቃ ጉደታ፣ለነበጅሮንድ ናደው ከየአባታቸው ርስት ጉልት አድርጎ ሰጥቶ ቤት አሠራቸው፡፡...ከዲለሎ ሲመለስ አለቃ ተክለኢየሱስን ጠርቶ ዘመዶችህ እነሻቃ ይርባ [ሻቃ ሂርጳ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ሰይፍ ጃግሬ ነበር] አገራቸው ገብተው ከዘመድ ተገናኝተው ለጉልት ሲበቁ ምነው አብረኸኝ ሳትሄድ አለው፡፡...ከርሞ የቀዎ ጊዮርጊስ ጌታ አደርግሀለሁ፡፡...እዚያው [ሥዕል] እየሣልክ ታሳምንልኛለህ፡፡ነገርግን የኦሮምኛ ቋንቋ እንዳይጠፋህ ይኹን አለው፡፡›› (አለቃ ተክለኢየሱስ፡ገ.198)፡፡ይቺ የተክሌ ሐተታና ‹‹እዚያው [ሥዕል] እየሣልክ ታሳምንልኛለህ፤ነገር ግን የኦሮምኛ ቋንቋ እንዳይጠፋህ ይኹን አለው፡፡›› የምትለዋ የንጉሥ ተክለሃይማኖት አገላለጽ በወቅቱ ዛሬ እንደሚባለው በኢኦተቤክ አካባቢ ኦሮሚፋ ‹‹ጽዩፍ›› የሚባል ቋንቋ እንዳልነበረ ፍንጭ ትሰጠናለች፡፡የንጉሥ ተክለሃይማኖት ዐላማም ጎጃም ማርኮ ያቆያቸውን ኦሮሞዎች ተጠቅሞ ሆሮ-ጉድሩን እና አካባቢውን በኦሮሚፋ እያስሰበከ በኦርቶዶክሳዊነት አሳምኖ ለማጥመቅ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡
(4.5) የኢኦተቤክ በሰሜን በኩል ባሉ ብሔረሰቦች ውስጥ ሴሜቲክ በሚባሉት ዐማራና ትግራውያን (ሐማሴኖችን ጨምሮ) ብቻ ሳይሆን ሰሜናዊ ኩሽቲክ በሚባሉት አገዎች ዘመናትን የቀደመ ተጽእኖ አላት፡፡‹‹ላል-ይበላ›› የሚለው ስም አገውኛ ስለመሆኑና አገዎች ቤተመንገሥቱን 300 ዓመታት ተቆጣጥረውት እንደነበር ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ወደ ደቡብ ስንሄድ የከፋን ሕዝቦች ታሪክ የጻፈው በቀለ ወ/ማሪያም አዴሎ እንደሚነግረን የኢኦተቤክ በአካባቢው ከ600 እስከ 700 ዓመታት የቆየና የተመዘገበ ታሪክ አላት፡፡ለአብነትም በቀለ ወ/ማሪያም በ1532 ዓ.ም የተተከለው ባሃ ጊዮርጊስን ይጠቅስልናል፡፡(በቀለ ወ/ማሪያም፡ገ.122 እና 123)፡፡በወላይታም የደብረ-መንክራት ተክለሃይማኖት ቤ/ክ እድሜ ከ800 መቶ ዓመታት በላይ ይቆጠራል፡፡በ14ኛው ክ/ዘ በምድረ-ጉራጌ እነ አቡነ ዜናማርቆስ ያቋቋሙት የምሑር-ኢየሱስ ገዳም ዛሬም ከነግርማው አለ፡፡በጋሞዎች ምድር ያለችው ብርብር ማርያም ከንጉሥ ገብረመስቀልና ከንጉሥ ዘርዓያዕቆብ ጋር የተገናኘ የሺህ ዓመት ታሪክ ትቆጥራለች፡፡በሸዋ የኦሮሞ ምድር ያሉት የወንጪ(አምቦ) ቂርቆስ፣የዝቋላ/ጩቃላ አቦ፣የዝዋይ/ባቱ ደሴት ገዳማት፣የደ/ሊባኖስና የዐዳዲ ማርያም ገዳማት፣...የሚቆጥሩት እድሜ በትንሹ ከ500 ዓመታት በላይ ነው፡፡ሃይማኖቱ ከ6 ሀገራት ጋር ዶግማ ቀኖና ስለሚጋራ ከነዚህ ሀገራት የመጡ ቅዱሳን በኃላፊነት ጭምር እየተቀመጡ እስከቅርብ ጊዜ አገልግለዋል፡፡የዐረብኛ፣የሱርስት፣የግሪክ እና የእብራይስጥ ቋንቋ ሳይቀር ሊቃውንቱ እያጠኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉመዋል፡፡ላመነና ለተጠመቀ ሁሉ መድረኩ ክፍት ነበር፡፡እነ መሐመድ ሐሰን ይሄን ሳያጣሩ፣ወይም እያወቁ ሳያካትቱና ጥቂት እንኳ ለሚዛናዊነት ሳይጨነቁ ‹‹The Amhara clergy›› እያሉ ሃይማኖቱን የአንድ ብሔር በማስመሰል መጻፋቸው እጅግ ቅር ያሰኛል፡፡ሃይማኖቱ ለዐማርኛ ቋንቋ የሚባለውን ያህል ታሪካዊ የሥነ-ጽሑፍ ቦታ እንዳልነበረው እስኪ ቀ.ኃ.ሥ ይንገሩን፡፡
(4.6) ቀ.ኃ.ሥ በ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ›› የመጀመሪያ ክፍል መጽሐፋቸው ገጽ 136 በዘመናቸው ዐማርኛ የነበረበትን ዝቅተኛ የቤ/ክ አገልግሎት ሲገልጹ ‹‹...ቅዳሴው ሕዝቡ ሁሉ በማያውቀው በግእዝ ቋንቋ ስለነበር ብዙዎች የዜማውን ድምጽ ከመስማት በቀር ምስጢሩን የሚያስረዳ ቃል ሳይሰሙ በየቤታቸው ይመለሱ ነበር፡፡...›› ካሉ በኋላ በእሳቸው ዘመን ስለነበረው ጅማሮ ሲገልጹ ‹‹...አሁን ግን ጸሎተ-ቅዳሴው በአማርኛ ቋንቋ እንዲተረጎምና እንዲታተም አድርገን በየቤተክርስቲያኑ ስለታደለ ሕዝቡ መላውን እንኳ ባይሆን ዋና ዋናውን ቃል በቋንቋ ሲነበብ መስማት ጀምሯል፡፡ወንጌልና የሐዋርያት መልእክትም በአማርኛ ቋንቋ እንዲነበብላቸው ተደረገ፡፡›› ይሉናል፡፡በነገራችን ላይ መጽሐፈ-ቅዳሴ ከግእዝ ወደ አማርኛ በነጠላው የተተረጎመውና የታተመው በ1918 ዓ.ም ነበር፡፡ተርጓሚው መርስዔኀዘን ወልደቂርቆስ ነበሩ፡፡አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በነጠላ ትርጓሜ በ1832 ዓ.ም አባ አብርሃም (አባ ሮሜ) የታተመ ቢሆንም የተሟላና ሊቃውንተ-ቤተክርስቲያን የተሳተፉበት አማርኛ መጽሐፍቅዱስ የታተመው ግን በቅርቡ በ1953 ዓ.ም ነበር፡፡በዚህ ወቅት (ኧረ ቀደም ብሎ ነው!) መጽሐፍ ቅዱስን አናሲሞስ ነሲብ ወደ አፋን ኦሮሞ፤አለቃ ተወልደመድኅን ገብሩ ወደ ትግርኛ ተርጉመውት ነበር (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ-ቃላት፡ገ.95)፡፡ድጋሚ ላስታውስ!የኢኦተቤክ በቀደመው ዘመን በስብከተ-ወንጌል ረገድ በየብሔረሰቡ ቋንቋ የመስበክ ብቃት ነበራት እያልኩ አይደለም፡፡አቋሜ የኢኦተቤክ የቋንቋ አጠቃቀም ውስንነት ልክ እስልምና ለዐረብኛ፤ካቶሊክ ለላቲን ቋንቋዎች እንደሚሳሱት (ኦሪጅናል ድርሰቶችና ዜማዎች በቋንቋዎቹ ስለተቀናበሩ) እሷም ለግእዝ ስሱ በመሆን እንጂ ኦሮሚፋን በተለየ ዐይን በማየት አይደለም የሚል ነው፡፡
(4.7) ይሕ በግእዝ ብቻ የመገልገል የኢኦተቤክ ልማድ መንበረ-መንግሥቱ በአክሱማውያን (ትግራውያን)፣በዛጉዌዎች (አገዎች) እጅ እና በየጁ ኦሮሞ ወረሴህ/ወራ-ሼክ እጅ በነበረበት ጊዜ (ለምሳሌ፡- ከየጁ ኦሮሞ የሚወለዱት ታላቁ ራስ ዓሊ ደብዳቤ ሲጽፉ ‹‹ጦማር ዘእምኀበ-ርእሰ-መኳንንት ዓሊ›› በማለት በግእዝ ነው አርእስታቸውን የሚጀምሩት)፤ኋላም ዙፋኑ በአጼ ዮሐንስ ተመልሶ ወደ ትግራይ ባመራበት ዘመን በኢኦተቤክ የግእዝ የበላይነት የጸና ነበር፡፡
(4.8) የቀደመው የግራኝና ደርቡሽ ሰቆቃ (አጼ ዮሐንስ በመተማ ተሰውተው ደርቡሽ ጎንደርን በወረራ ሲያጠፋ በሃይማኖቱ እውቀት ጫፍ የደረሱ ከ20 በላይ መምሕራንን አርዶ ነበርና) በወቅቱ ሀንጎቨሩ እንዳለ ሆኖ በተለይ ደግሞ የአጼ ሱስንዮስ ዘመን ካቶሊካዊ ፍልስፍና ኋላ ፊቱን ቀይሮ ጸጋ/ሦስት ልደት/-ቅብዐት-ተዋሕዶ/ካራ/ የሚል የውስጥ ክፍፍል በመፍጠር ሃይማኖቱ በውሳጣዊ ሽኩቻ ከመዳከሙም በላይ ከሊቃውንት ማዕከላቱ ትግራይ-ጎንደር-ጎጃም-ወሎ-ሸዋ ወጥቶ ወደሌሎች ብሔረሰቦች በስፋት በስብከተ-ወንጌል እንዳይደርስ ይሄው ሽኩቻ እስከ ዘመነ-መሳፍንት ፍጻሜ ዘልቆ ጎታች የነበረ መሆኑን ማስተዋል አይከፋም፡፡ እንጂ የኦሮሚፋ ስብከት ያልተስፋፋው መሐመድ ሐሰን እና ኦቦ ጆቴ እንደሚሉት ለኦሮሚፋ too profane በመሆን አይመስልም፡፡ጥያቄ ላንሳ፡፡ዶክቶር መሐመድ ወደ ኢኦተቤክ ከማለፉ በፊት እስልምና ለቁቤ እና አፋን ኦሮሞ ያበረከተውን ጸጋ ሊተነትንልን ይችል ይሆን?የአፋን ኦሮሞ ቁራን ነበረ?ቁራን በኦሮሚፋ ይቀራ ነበር?አዛንስ?ለንጽጽር እንዲመች ጥያቄዎቹ ቢብራሩ ሸጋ ነው!ስላደገበት እስልምና-እና-ኦሮሞነት ተዛምዶ ለመተንተን የተሻለ ግንዛቤ አለው ብዬ ነው!የእሱ የተጸውኦ(መጠሪያ) ስም ‹‹መሐመድ ሐሰን›› በኦሮሚፋ አይደል!!ይተርጉምልና!!
(4.9) እግረ-መንገድ እስኪ ከ100 ዓመት በፊት በኦሮሚፋ እና በዐማርኛ ቅልቅል (ፍርንዱስ) ሆኖ የግጥም ምጣኔው ‹ሥላሴ› የምንለው ከ3ኛው መስመር ጀምሮ ቤት እየመታ የሚሄድ ባለ 8 መስመርና ባለ 6 ቤት ቅኔ እንስማ፡፡የቅኔው ባለቤት አለቃ ዘወልዴ ይባላሉ፡፡ምናልባት በፕ/ር ታምራት ‹‹ፊተኛይቱና ኃለኛይቱ ኢትዮጵያ›› የሚል መጽሐፍ በተለየ አጻጻፍ ጽፈዋል የሚባሉትና መጽሐፋቸውን ያላገኘንላቸው ዘወልዴ ይሁኑ አይሁኑ አላወቅኩም፡፡ቅኔው የተደረገው በምኒልክ ጊዜ የነበረውን አስተዳደር በመተቸት ነው፡፡የተወሰደው በ1980 ዓ.ም በደርግ ጊዜ በአ/አ/ዩ አማካይነት ከታተመው ‹የግእዝ ቅኔያት የስነ-ጥበብ ቅርስ ክፍል-2› ከተሰኘ መጽሐፍ ገጽ-389 ነው፡፡የሊቁ ቅኔ እንዲህ ይነበባል..
አርካ-ኬቲ፡ሁንዱማ-ጨብሴ፤
ሌንጫ-ጎፍታኮ፡ኢጆሌ-ሌንጫ፤
አሁንም-የእውነት፡ግሩም፡አንበሳ፡የአንበሳ-ኮርማ፡የቢያ፣
በክንድህ-ሰበርኸው፡የሁሉን፡ሶማያ፣
ዱጉማ፡ጎፍታኮ፡ዱጉማ፡አሲ-መና-ኬቲ ገበያ፣
ሀሬ-ጉደቴ፡ፈርዳን-ፉለያ፣
ማሎ፡ማሎ፡ጎፍታ-ኪያ፣
መና-ፈርዳ፡ፉደቴ፡አህያ፡፡
ትርጉም፡- ‹‹አንበሳ የአንበሳ ልጅ፤ጌታየ ክንድህ ሁሉን ሰበረች፤አሁንም የእውነት አስፈሪ አንበሳ የአገር አንበሳ ኮርማ (አንተ)፤የሁሉን በትር በክንድህ ሰበርኸው፤እውነት ጌታዬ ከዚህ ገበያ ቤትህ እንደ አይጠ መጎጥ ፈረሶች ሲርቁ አህያ ከፍ ከፍ ተደረገች፤ምነው ምነው የእኔ ጌታ የፈረስን ቤት አህያ ወሰደች›› የሚል ነው፡፡
ምስጢሩ፡- ባለቅኔው የምኒልክን በባላባቶች ላይ የተገኘ አሸናፊነት አወድሰው ነገር ግን ‹‹በባህሉ ፈረስ እያለ አህያ ቀሚስ እንደማትለብስ እየታወቀ እስዎ ታላላቆችንና ምሁራኑን ትተው ለታናናሾች እና ላልተማሩት ቦታ (ስልጣን) እየሰጡ ነው›› በማለት የምኒልክን አስተዳደር በኦሮሚፋ የሚተች ነው፡፡በውዳሴ ጀምሮ በትችት መቋጨት ከቅኔ ባሕሪያት አንዱ ነዋ!

ይቀጥላል///////