Tuesday, September 15, 2015

ተከስተ ጌትነት ለተወራበት የወሲብ ቅሌት፤ ዋሽንግተን ዲሲ ለሚታተመው ዘኢትዮጵያ ጋዜጣ የሰጠው ምላሽ

እኔ ወ/ሮ ሆሳዕናን አስገድጄ አልደፈርኩም። በፍርድ ቤትም አልተከሰስኩም። ለዚህም ማስረጃ አለኝ።”
የወ/ሮ ሆሳዕና ባለቤት ባለፈው በቪ ኦ ኤ በቀረበው ፕሮግራም መግቢያ ላይ “በሚስቴ ላይ የጾታ ጥቃት ተፈጽሞባታል” ያለውና ወይዘሮ ሆሳዕናም በዚያው ፕሮግራም ላይ ቀርባ “ጉዳዩ በህግ የተያዘ ነገር ነው” ያለችው ነገር ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው። እኔ ማንንም ሰው አስገድጄ አልደፈርኩም ምንም አይነት ክስም አልቀረበብኝም። ከወንጀል ነፃ መሆኔን የሚያሳይ ህጋዊ ማስረጃ በአሜሪካን አገር ጉዳዩ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት በጠበቃዬ አማካይነት ያገኘሁት እሷ በአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ ቀርባ ከስሸው ጉዳዩ በህግ ተይዟል ብላ በተናገረች በሚቀጥለው ቀን ነው።

 ይባስ ብሎ በአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ ፓስተር ተከሰተ ባለትዳር ሴት ደፍሮ ተከሰሰ የሚለውን ዜና ውሸት እና የፈጠራ ወሬ መሆኑን የሚያሳየው እኔ እነሱ ከሚኖሩበት ሚንያፖሊስ ከተማ እኔ ወደምኖርበት ወደ ዋሽንግተን ስመለስ ወደ አውሮፕላን ጣቢያ የሸኘችኝ እራስዋ ወይዘሮ ሆሳዕና ነች። በብዙ ጭቅጭቅ የ1000 (አንድ ሺህ) ዶላር የእጅ ሰዓት በራስዋ ክሬዲት ካርድ ገዝታልኛለች። ለዚህም ሌላ ህጋዊ ማሰረጃ አለኝ። በዚያን ሰአት እንኳን ልትከስኝ ቀርቶ ለወንድ ልጅ ሰዓት መስጠት እወዳለሁ ብላ እኔ ሰአት አልፈልግም እያልኳት እሷ ግን እኔ የወንድ ልጅ ሰዓት ስለሚስደስተኝ ልግዛልህ። አንተ ብትፈልግ ወደፊት በሌላ ነገር ቀይረው በማለት ከነደረሰኙ ሰጠችኝ።

አንተና ወይዘሮ ሆሳዕና እንዴት ተገናኛችሁ ጉዳዩስ እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሰ? ብለን ላቀረብነው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ፡ ወ/ሮ ሆሳዕናና የእኔ ባለቤት የአንድ ሰፈር ሰዎች ናቸው። ከዚያም በራስዋ በወይዘሮ ሆሳዕና ተደጋጋሚ ግፊትና ጥረት ተቀራረብን። የቤተሰባችን አካል ሆነችና አገልግሎትህን ስለምወድ እንድደግፍ ጌታ አሳሰበኝ በሚል መንፈሳዊ አካሄድ ለእኔና ለቤተሰቦቼ በተለያየ ጊዜ ስጦታ ሰጥታናለች። የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በምዕመናን በጎ ፈቃድ የፍቅር ስጦታና የአገልግሎት ድጋፍ ማግኘት የተለመደ ስለሆነ እኔም በአገልግሎት ዘመኔ እኔንና አገልግሎቴን የሚደግፉ ብዙ ደጋግ ሰዎች ስላጋጠሙኝ ወይዘሮ ሆሳዕና ያለችውንም በቅንነት ተቀበልኩት። በመጨረሻም እኔ ባለቤትህና አንተ ለምን የጋራ ቢዝነስ አንጀምርም? እኔ ገንዘብ አለኝ፣ የቤተሰብ የቢዝነስ ልምዱም ስላለኝ አንተ ደግሞ ኢትዮጵያ ታዋቂ ስለሆንክ ሦስታችን አብረን ኢትዮጵያ ቢዝነስ ብንሰራ ሊሳካልን ይችላል ብላ ጠየቀችን። እኔም ማንኛውም ዘማሪ አንደሚመኘው ከቤተክርስቲያን ምንም ነገር ሳልጠብቅ ራሴን እና ቤተሰቤን በግሌ እየሠራሁ በማስተዳደር በነፃ የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ እኔና ባለቤቴ በሀሳቡ ተስማማን። እኔ እነሱ ወደሚኖሩበት ከተማ የሄድኩት እና ሆቴል ያረፍኩት ራስዋ ወይዘሮ ሆሳዕና በአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ ቀርባ እንደተናገረችው በጋራ ስለምንጀምረው ቢዝነስ ለመነጋገር ነበር። ይህን ሀሳብ ያመጣችው እራሷ ወይዘሮ ሆሳዕና ነች።

በራሷ ገንዘብ የአውሮፕላን ትኬት ቆርጣ እራሱዋ ሆቴል ይዛ፣ (ለዚህም ማስረጃ አለኝ)። ከዚያ በኋላ አሁንም ራሷ በአሜሪካን ድምፅ ቀርባ እንደተናገረችው ያረፍኩበት ክፍል ውስጥ ገብታ ልብሷን አወለቀች። ብዙ ተፈታተነችኝ። የምሄድበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነና ሆን ተብሎ የገባሁበት ወጥመድ እንዳለ ሲገባኝ ፍላጎቱ ባይኖረኝም እሷን ሳላሳዝን ሞራልዋን ሳልነካ በሰላምና በእርጋታ ለመውጣት “በቃ አሁን እኔ መረጋጋት አልቻልኩም ፍላጎቱ የለኝም ሌላ ጊዜ ተመልሼ ልምጣና ያንቺን ፍላጐት አሟላለሁ” ብዬ ቃል ገባሁ። እሷም ተመልሼ ወደእሷ ከመጣሁና መሻቷን ከፈጸምኩ አብረን ልንሠራ ከተነጋገርንበት ቢዝነስ በተጨማሪ ለግሌ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደምትሰጠኝ ነግራኝ ተለያየን። ካረፍኩበት ሆቴል ወደ አውሮፕላን ጣቢያ ስንሄድ ለወንድ ልጅ የሰዓት ስጦታ መስጠት ያስደስተኛል ብላ ከላይ እንደጠቀስኩት የአንድ ሺህ ዶላር ሰዓት መንገድ ላይ ወደሚገኝ ሞል ኦፍ አሜሪካ የገበያ ማዕከል ውስጥ ሜሲስ የሚባል ስቶር ወስዳ ገዛችልኝ።

አየር ማረፊያ አውርዳኝ ስንለያይ ለመጀመርያ ጊዜነጻነት ተሰማኝ። ዋሽንግተን ዲሲ ተመልሼ እቤቴ ስገባም የሆነውን ነገር ሁሉ ለባለቤቴ አንድም ነገር ሳልደብቅ ነገርኳት። ከዚያም እንደ አንድ ክርስቲያን እና እንደ አንድ አገልጋይ ከእኔ የማይጠበቅ ነገር አድርጌአለሁ ብዬ ያለማንም አስገዳጅነት በራሴ ፈቃድ ለቤተክርስቲያን ተናግሬ ወዲያውኑ ራሴ አገልግሎት አቆምኩ። በራሴ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአሜሪካን ክፍለግዛቶች በሚገኙ አብያተክርስቲያናት እንዳገለግል የተጋበዝኩባቸውን አገልግሎቶች በሙሉ በራሴ ፈቃድ ሰረዝኩ። እኔ ወደዋሽንግተን ከመጣሁ በኋላ ወይዘሮ ሆሳዕናም እኔን በስልክ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ አደረገች ግን አልተሳካላትም። ከዚያ በኋላ የበቀል እርምጃው ግራ በሚያጋባ መልኩ መጣ።
መጀመሪያ ለእኔ ባለቤት ለወ/ሮ የምስራች ባለቤቱዋ አቶ መላኩ ደውሎ ሚስቴ ከአንቺ ባል ጋር አብራ ስለተኛች ይቅርታ ልትጠይቅሽ ነው ብሎ ስልኩን ለወይዘሮ ሆሳዕና ሰጣት። ወይዘሮ ሆሳዕናም እኔ ከባለቤትሽ ከተከስተ ጋር ተኝቻለሁ ይቅርታ አድርጊልኝ ብላ በስልክ ለእኔ ባለቤት የድምፅ መልእክት ተወችላት (ደውለው ለባለቤቴ የተውት የእሱም የእሷም የድምፅ መልዕክት ማስረጃው አለኝ)። ከዚያ ደጋግመው ደውለው ባለቤቴን አገኟትና ባልሽ ከሚስቴ ጋር ተኛ ብሎ ነገራት። ባለቤቴም በቃ ካጠፉ ይቅር እንበላቸው እና ነገሩ ይቁም አለችው።

ባለቤቴም ሁሉንም ነገር አልቀበል ስትል ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ። አቶ መላኩ ቤተክርስቲያን ሄዶ ፓስተር ተከስተ ከሚስቴ ጋር ተኝቷል አገልግሎት ማቆም አለበት ይቅርታ መጠየቅ አለበት አለ። እኔም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው እና መንፈስ ቅዱስ እንደሚወቅሰኝ ከአንድ አገልጋይ የማይጠበቅ ጥፋት አጥፍቻለሁ። እግዚአብሔርንም በድያለሁ ለዛም እራሴን ከአገልግሎት አስቁሚያለሁ። እናንተንም ይቅርታ እጠይቃለሁ አልኩኝ። ሰዎቹ ዓላማቸው ክርስቲያናዊ ዕርቅ እንዳልሆነና አሳባቸውን በመቀየር ለሌላ ለተሻለ የበቀል እርምጃ ሊጠቀሙበት እንደሆነ አስቀድሜ ለሦስቱ ሽማግሌዎች ነግሬአቸው ነበር። ነገሩ በሰላም እንዲያልቅና ክርስቲያናዊ አካሄድ ነው ብዬ ስለማምን ሙሉ ኃላፊነት ወስጄ ይቅርታን ጠይቄአለሁ። አቶ መላኩ ግን የግብረሥጋ ግንኙነት ፈጽመሃልና እመን የሆነውንም ዝርዝር ነገር ንገረኝ ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ሙሉ ኃላፊነት ወስጄ ይቅርታንም ጠይቄ የወይዘሮ ሆሳዕናን ስሜትና ስብእና የሚነካ ዝርዝር ነገር ውስጥ ግን እንደማልገባ አሳወቅሁኝ። ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ነገር ያልተለመደ በመሆኑና አቶ መላኩ ማወቅ የሚፈልገውን መረጃ በሙሉ ከገዛ ሚስቱ ማግኘት ስለሚችል ነው። ቤተክርስቲያንም ፓሰተር ተከስተ ከአንድ አገልጋይ የማይጠበቅ ጥፋት አጥፍቻለሁ ብሎ በራሱ ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ገብቶአል አገልግሎትም አቁሞአል ፣አንተንም ይቅርታ ጠይቋል ነገሩ እዚህ ጋር ይለቅ ብለው ጠየቁት ። እነሱ ግን እኔን ለማጥፋት ቆርጠው ስለተነሱ ነገሩ እንዲቆም አልፈለጉም።

ቤተክርስቲያን መጥተው ያሰቡትን ያህል እኔን የጎዱኝ እና ያዋረዱኝ ስላልመሰላችው ቪ ኦ ኤ ሄደው ፓስተር ተከስተ አስገድዶ ደፍሮኛል ጉዳዩም በህግ ተይዞአል የሚል በሽምግልናው ወቅት በጭራሽ ያልተነሳ ሌላ ተጨማሪ የውሸት ታሪክ ፈጠሩ። ይህን አላማ እንዲያስፈጽም ጋዜጠኛ አዲሱ አበበን ይዘው መጡ። አቶ አዲሱ ጋር ስንነጋገር ሆን ብሎ እኔን ለማጥቃት እንዳሰበና እውነቱን ማወቅ እንደማይፈልግ ስለገመትኩ በጉዳዪ ለይ ምንም አይነት ኢንተርቪው ላንተ አልሰጥም፣ ጉዳዪም በቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ተይዟል አልኩት። የቤተክርስቲያን መሪዎች እና ጉዳዩን የያዙትም ሽማግሌዎችም አቶ አዲሱን ይሄ የቤተክርሰቲያን ነገር ነው በዚህ ነገር ላይ ምንም አይነት ፕሮግራም በሬዲዩ ላይ መሥራት የለብህም ብለው እየነገሩትና እየተለመነ በማን አለብኝነት ጉዳዩን አጣሞ ሁላችሁም እንደሰማችሁት እኔን በሚያዋርድ ፣ስሜን በሚያጠፋ፣ ሕይወቴንና አገልግሎቴን በሚያበላሽ መልኩ ፕሮግራሙን ሰርቶ በሬድዮ አቀረበው። አሁንም የምለው እኔ የበደሉኝን ሁሉ ይቅር ብያለሁ። እንደ ክርስቲያንና እንደ አገልጋይ አጉድዬ በተገኘሁባቸው ጉዳዮች ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን ከባለቤቴና ከቤተክርስቲያኔ ደግሞ ይቅርታን አግኝቻለሁ። ዛሬ ደግሞ በእኔ ምክንያት ያዘናችሁትን ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብሏል።
አሁን እያሳየኸኝ ያለውን ማስረጃ ይዘህ ለማስተባበልና በሕግ ለመፋረድ እስከዛሬ ለምን ሙከራ አላደረግህም? ለሚለው ጥያቄም መልስ ሰጥቷል።

ሥሜንና ክብሬን በተመለከተ እኔ ሥምና የሚዋረድ ክብር የለኝም። እኔን ከጎዳና ላይ አንስቶ ሰው ያደረገኝ እግዚአብሔር ነው። ከእርሱ ውጭ በሰው የሚዋረድም የሚከብርም ማንነት የለኝም። ፍትህን በተመለከተ ደግሞ የምንኖርበት አሜሪካ የፍትህ አገር መሆኑን አውቃለሁ። የትኛውም ድርጅት፣ ባለሥልጣንም ሆነ ግለሰብ ከሕግ በታች መሆኑንም አውቃለሁ። ወንጌል አምኖ እንደዳነ ክርስቲያን ግን እግዚአብሔር ሁሉንም በጽድቅ ስለሚፈርድ ፍትህን ከእግዚአብሔር እንጂ ከማንም ሰው አልጠብቅም። ባለቤቴም ቢሆን ሁሉም ነገር በሰላምና በይቅርታ እንዲያልቅ ስለምትፈልግ ወደ ፍርድ ቤትም አልሄድንም። በዚህ አጋጣሚ ሳሚ በማያውቀውና በሌለበት ነገር በኔ ምክንያት ስለተሰቃየ ና በውሽት ስሙ ስለጠፋ በጣም ያዘንኩ መሆኔን እገልጻለሁ።