ዶ/ር ሽፈራው
ተ/ማርያም በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ «የኦርቶዶክሱን ክር እናስበጥሳለን» ብለዋል በማለት ማስጮሁን የጀመረው አሉላ ጥላሁን የሚባለውና የማኅበረ ቅዱሳኑ አባል የሚነዳው
«ሐራ ተዋሕዶ» መካነ ጦማር ነው። ድርጅት እንጂ እምነት የሌለው ሁሉ ያንን ተቀብሎ አስተጋባ። በእርግጥ ዶ/ር ሽፈራው ብለውታል? ወይስ አላሉትም? የሚለው ጉዳይ ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ቢሆንም «ራስ ሲመለጥና አፍ ሲያመልጥ አይታወቅም» እንዲሉ ዶ/ሩ ብለው ሊሆን
ይችላል ብለን ብንገምት እንኳን ይሄንን ያህል ማስጮህና ማጦዝ ያስፈለገው ለምንድነው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ይመስለናል።
1/ ምክንያታዊነቱ፤
አዲስ ይወጣል
በተባለው የሴኩላሪዝም ደንብ በመንግሥት የሥራ ቦታዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች ማለትም ስዕል ማድረግ፤ በጠረጴዛም ይሁን
በግድግዳ መስቀል ማንጠልጠል፤ የኮምፒውተር ስክሪን ሴቨር ማድረግ፤ መንፈሳዊ ጥቅሶችን፤ ሂጃብ፤ ኒቃብ፤ ቡርቃና ሌላ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ
ምልክቶች እንዳይኖሩ የመከልከል ደንብ እየወጣ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።
እነዚህ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደፈለጉ መጠቀም ከዚህ ቀደም ባለፉ ሥርዓታት ዘመን ያልነበሩና አዲስ የፈጠራ
ልምዶች እርግጥ ነው። ዲሞክራሲ ያሰፈናቸው ወይም ዘመን የፈጠራቸው ናቸው ወይ? ብለን አንከራከርም። ነገር ግን
ሁሉም ሃይማኖት ከማን አንሼ ሰበብ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የሚያደርግ ከሆነ ወይም «እኔን ደስ የማይለኝ ነገር በሥራ
ቦታዬ ላይ ተቀምጧል፤ ስለዚህ እንዲወገድ ይደረግልኝ» በማለት ቢቃወም ሰላማዊ የሥራ ሁኔታውን ወደሃይማኖታዊ ንትርክና ጭቅጭቅ ሊቀይር
መቻሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከዚህ በፊትም ይህ ክሰተት ተፈጽሞ «መብቴ ነው!» «መብትህ አይደለም!» ወደሚል አተካራ ማስገባቱን ያጋጣመቸው ሰዎች ሲናገሩ ተደምጧል።
ለመሆኑ ደመወዝ ሊከፈለው ውል ፈጽሞ በገባበት የሥራ ቦታ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን
ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ? ነገሩን ስንመለከተው ብዙ ጊዜ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ባልተፈቀደ ቦታም ይሁን ተገቢ ባልሆነ ሥፍራ ለማሳየት
የሚፈልጉ ሰዎች «እኔ እበልጣለሁ» ወይም «ሃይማኖቴን በጣም እወዳለሁ» በሚል ስሜት ሌላውን ለማሳነስና እነሱ በእምነታቸው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች ይመስሉናል። የዚህ ተቃራኒ ደግሞ «እኔም አላንስም» በማለት ሌላውን ለመቃወም የራሱን ምልክት
በተደራቢነት ለመጠቀም የመፈለጉ አዝማሚያ ወይም «ይነሳልኝ» ሲል ክስ
የማቅረቡ ሁኔታ ያለውን የእኔነት ውጥረት ለማርገብና
አደብ ለማስያዝ መንግሥት መፈለጉ ከተገቢነቱ አኳያ አያጠያይቅም። በየቦታው እየሄዱ በስመ ስብከት ሰበብ «ኢየሱስ
ጌታ ነው» እያሉ የግል ነጻነትን ሳያስፈቅዱ እንሰብካለን ሲሉ ከግለሰብ ጋር የሚጋጩትን ጨምሮ በሃይማኖት ሽፋን
የሌላውን መብትና ነጻነት መጋፋት ተገቢ አለመሆኑም ትክክል ነው።
«እኔ የተሻልኩ ነኝ» በሚል ራስን የማግዘፍና በፈጣሪ ፊት ያለውን ተመራጭነት ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ምልክትን መደርደር፤
አብዝቶ መናገር ወይም ራስን ለማሳየት መሞከርና የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ እንደሆንክ ማስተዋወቅ በእግዚአብሔር ፊት የበለጠ ተወዳጅ
መሆንን ሊያሳይ አይችልም። ስለዚህ የትኞቹም ምልክቶች የፊት ማሳያ እንጂ የልባችን ተግባር መግለጫዎች ስላይደሉ አስፈላጊነታቸው
ምክንያታዊ አይደሉም። የክርስትና ወይም የእስልምና ምልክት አድርጎ የሚሰርቅ ወይም የሚያመነዝር ትውልድ ምልክት ስላደረገ እንደ እውነተኛ
ሰው ሊቆጠር አይችልም።
«ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥
ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና» ሉቃ 16፤15
የሃይማኖታዊ ምልክት ፉክክር የጥፋት መጀመሪያ
ነው። አንድ ሰሞን «አንድ እምነት፤ አንዲት ጥምቀት፤ አንድ ጌታ» የሚለውን ጥቅስ በልብስ ላይ አትመው የለበሱ ሰዎችን ለመገዳደር
በሚመስል መልኩ «ኢየሱስ፤ መሐመድና ሙሴ የአላህ ነብያት» የሚል ጥቅስ ለብሰው የሚዞሩ ወጣቶችን ማየቴን አልረሳውም። ሃይማኖቱን
በተፈቀደለት ቦታና በሥፍራ እንደመጠቀም ከሌላው የተሻለ እውነተኛነት እንዳለው ለማሳወቅ በሚደረግ ሩጫ ጥፋት ለማስከተል መሞከር
የነበረውን ሰላም ከማደፍረስ በስተቀር በዚህ አድራጎት የሚታነጽ ማንም የለም።
«እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ»
1ኛ ቆሮ 14፤12
2/ የክር እናስበጥሳለን ፉከራና የተቃውሞ ዘመቻ፤
ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደጠቆምነው የፌዴራል
ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ስልጠና ላይ «ሂጃብ እንዳስወለቅን ክርም እናስበጥሳለን» ብለዋል የተባለው
ጉዳይ እውነት ነው ወይ?
«ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ከመንግሥት የሥራ ቦታዎች
ውስጥ እናስቆማለን፤ ሴኩላር የሆነ የሥራ ቦታ እንፈጥራለን» በሚለው እሳቤ ዙሪያ ከአንገት ላይ ክርም እናስበጥሳለን» የሚለውን
ፉከራ በምን መስፈርት እንደተመለከቱት ግልጽ አይደለም። እንደእውነቱ ከሆነ ክር አንገት ላይ ማሰር ሌላውን አማኝ አያውክም። ለጌጥ
ብሎ ሀብል ከሚያስር ሰው የተለየ ነገር የለውም። መንግሥት እስከዚህ ድረስ የወረደ ተግባር ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም። ተብሎ ከሆነ
መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው እንላለን።
ዶ/ር ሽፈራው ብለዋል ከተባለ በኋላ የገቡበትን አጣብቂኝ ለመከላከል እንደሆነ
ለጊዜው ባይገባንም የጉዳዩን ጡዘት በማርገብ ደረጃ በመንግሥታዊው
ሚዲያ «ፋና ብሮድ ካስቲንግ» ቀርበው አላልኩም በማለት አስተባብለዋል። «ቤን» የተባለው አፍቃሬ መንግሥት ድረ ገጽ አዘጋጅም ጥያቄ አቅርቦላቸው አለመናገራቸውን ገልጸዋል። «እንደዚህ
አላልንም» ካሉት በላይ የምንጠብቀው ምላሽ አይኖርም።
ነገር ግን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች ሁሉ
እንዳይኖሩ እናደርጋለን ተብሎ ከተዘጋጀው ደንብ ውስጥ ከተዘረዙት ሁሉ በአራጋቢዎቹ ዘንድ የዚህ የክር ጉዳይ ብቻዋን ለምን ተነጥላ
ወጣች? ነው ጥያቄያችን። ይህንን ጉዳይ አስቀድሞ ያስጮኸው የማኅበረ ቅዱሳኑ «ሐራ ተዋሕዶ» መካነ ጦማር ነው። ሐራ ደግሞ ጅራፏን
የምታስጮኸው በማኅበረ ቅዱሳኑ አሉላ ጥላሁን በኩል ነው።
ብዙ ጊዜ በአፍቃሬ ማኅበሩ ብሎጎች ስማቸው በክፉ የሚወሳው ዓባይ ፀሐዬ፤ ስብሐት ነጋና ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ናቸው። እነዚህን
የፖለቲካ ሹማምንት ማኅበሩና ደጋፊዎቹ የሚቃወሟቸው ማኅበሩ የፖለቲካ ድርጅት ስለሆነ ሳይሆን የማኅበሩን አካሄድ
በግልጽ ስለሚቃወሙ ብቻ ነው። እዚህ ላይ በአንድ ወቅት አቶ ስብሐት ነጋ «ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን
ሸክም» ማለታቸው ሳይዘነጋ ነው።
በሌላ በኩል ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማኅበር መሆኑም መታለፍ የለበትም። ማኅበሩ በፓትርያርኩ ላይ ጫና በማሳደር በወዳጆቹ ሊቃነ ጳጳሳት በኩል ማስፈጸም ያቃተውን
ቤተ ክርስቲያንን የመረከብ ዓላማ ለጊዜውም ቢሆን የተገታው በሃይማኖት ሽፋን ሀገሪቱን ወደቀውስ መውሰድ ከሚፈልጉ ተቋማት
አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ስለተባለና ስሙ ብዙ ጊዜ ብዙ ጊዜ መነሳቱም አንዱ ምክንያት ነው። በዚህ በኩል ዶ/ር ሽፈራው ብዙ ተጉዘዋል።
ማኅበሩ ከአባ እስጢፋኖስ ጀርባ ሆኖ ያረቀቀውና
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የመረከብ ሕግ ውድቅ ከሆነበት በኋላ የተወረወረበትን
ቅዝምዝም ለማሳለፍ ባለፉት ወራቶች አንገቱን ዝቅ አድርጎ ጠብቋል። መጪው ወር የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ይካሄዳል። በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ያጣውንና ለአባ እስጢፋኖስ መነሳት ምክንያት የሆነው የሕግ ማርቀቅን ጉዳይ ተከትሎ ማኅበሩን አደብ ለማስያዝ በፓትርያርኩ በኩል የቀረቡ ነጥቦች ነበሩ።
ይህንን ተከትሎ በማኅበሩ ላይ ይጸና
ዘንድ ከሚታሰበው ደንብ በፊት ጥቂት ነገር መጫር ሳያስፈልግ አልቀረም። በማኅበሩ ላይ በሴኩላሪዝም ደንብ ስዕልና ጥቅስ በመሥሪያ ቤቶች እንዳይገኙ
ከሚከለክለው ጉዳይ ውስጥ ከኦርቶዶክሳውያን አንገት ላይ የሚታሰረውን ክር ነጥሎ በማውጣት ማስጮህ የፈለገው በአማኙ ስስ ስሜት ተጠግቶ
ብዙ ተቃዋሚ በማስነሳት አቅጣጫ የማስቀየር ስልት መሆኑ ነው። በዚህም የማኅበሩ አመራር የሆነው አሉላ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶለታል። በዶ/ሩ ላይ ሁሉም ሊባል በሚችል
ደረጃ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ተቀባብለው ዘምተውባቸዋል። በዚህም ጫና ይመስላል፤ ዶ/ሩ ሳይወዱ ምላሽ ወደመስጠት
የተገደዱት። ብለውም ከሆነ «ካፈርኩ አይመልሰኝ» መሆኑ ነው። ያላሉም ከሆነ አጋጣሚውን ጠብቆ ዱላውን ያሳረፋባቸው ማኅበር ምላሽ በመስጠት
የማስገደድ አቅሙን እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ወደፊት በማኅበሩ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር እስትንፋሳቸውን የመከልከል ዘዴ መሆኑ ነው። በእርግጥ እንዲያ ከሆነ አያዋጣም።
የሚገርመው
ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ «ኦርቶዶክሶች
ክር የማይበጥሱ ከሆነ እኛም እስላሞቹ ሂጃብ አናወልቅም፤ ቆባችንንም አንጥልም» የሚል ዘመቻ መጀመሩ ነው። ነገሩ
አብረን እንጥፋ ነው። «ከኔ ኪስ መታወቂያ ከጠፋ፤ ያንተም መታወቂያ መጥፋት አለበት» ማለት ቅናት እንጂ ጤናማ
ክርክር አይደለም። ቡርቃና ኒቃብ ከክር
ጋር የሚነጻጸሩት በምን ስሌት እንደሆነ አይገባንም። ትክክልም አይመስለንም። ባለክሮች ስለክር ማሰር ሲጮሁ
ባለኒቃቦች ባለክሮችን ተጠግተው ጩኸት አስነሱ። ስለክርም፤ ስለቆብም፤ ስለኒቃብም ማንሳት የማይፈልግ ነጻው ሰው
በመንግሥት መሥሪያ ቤት ነጻ ሆኖ እንዴት ይስራ? መልሱ አጭር ነው። ሃይማኖተኞች ሃይማኖታችሁን በተፈቀደላችሁ ቦታ
ብቻ ፈጽሙ ነው። ሴኩላሪዝም ማለት ይህ ነው። መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም፤ ሃይማኖታዊ መንግሥትም የለም።
ነገር ግን ባልተጋነነ መልኩ ሥርዓት ማስያዝ የመንግሥት ድርሻ መሆኑ
እንደተጠበቀ ሆኖ ሃይማኖታዊ ነገሮችን በጥንቃቄ በመያዝና ከባለጉዳዮቹ ጋር በመነጋገር ማስተካከል እንደሚቻል ጽኑ እምነት አለን።
ለምሳሌ ፈረንሳይ ኒቃብና ቡርቃን በሕግ አግዳለች። «ኒቃብ» ዓይን ብቻ የሚታይበት ሲሆን «ቡርቃ» ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተሸፋፈነች
ሴት አለባበስ ነው። ሳርኮዚ «ለእነዚህ ሰዎች መታወቂያ መስጠት ምን ይጠቅማል?» ሲሉ ጠይቀዋል።
መታወቂያ ማን መሆኑን መለያ ነውና
አባባላቸው እውነት ነው። ስለዚህ ክርን ከቡርቃ ጋር ለማስተያየት የምትሞክሩ ጥቂት ተረጋጉ። ከጸጥታ ስጋት አንጻርም ቢያስፈራ አያስገርምም።
በ2007 ዓ/ም ያሲን ዑመር የተባለ እንግሊዛዊ አሸባሪ ፈንጂ ታጥቆ እንደሴት ቡርቃ ለብሶ እንደነበር የቢርምንግሃም ፖሊስ ሲያከሽፍበት
አይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ክር ማሰር የተጀመረው መቼ
ነው? ብለን ወደዝርዝር አንገባም። ታሪኩ ረጅም ነው። ነገር ግን «ማዕተብ» ማለት ምልክት ማለት እንደሆነ እንናገራለን። ከክርስቲያንም ኦርቶዶክስ የመሆን ምልክት!
ክር ማሰር ምልክት እንጂ ሌላ ምንም አይደለም። በአዲስ ኪዳን ስለክር ማሰር የተነገረን ነገር የለም። ማኅበሩ እንደቀድሞ ዋሾዎች
የሌለውን ጥቅስ እያቀረበ የወንጌል አስተምህሮ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ቢሞክርም ከውሸትነቱ ፈቀቅ ብሎ እውነት ሊሆን አይችልም።
ክርስትና እምነት እንጂ ምልክት አይደለም። በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት በማመን የሚኖሩበት ሕይወት ነው። የሚገርመው ደግሞ ሚሊዮኖች ክርና መስቀል
አንገታቸው ላይ እያለ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ይዘርፋሉ፤ ያመነዝራሉ፤ ይሰክራሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ይዋሻሉ። የአንገት ላይ ምልክት
እንጂ የልብ ላይ ክርስትና የላቸውምና ከዚህ ድርጊታቸው ክር ማሰራቸው በጭራሽ ሊያድናቸው አይችልም።
እንዲያውም
ሥነ ምግባር የሌላቸውን
ብዙ ጫት በሊታዎች፤ ሴትኛ አዳሪዎች፤ አመንዝራዎች፤ ሰካራሞች፤ ተሳዳቢዎች፤ ዘፋኞች ሰዎች ልብ ብላችሁ ብታዩ
አንገታቸው ላይ ክር ወይም መስቀል ታገኛላችሁ። አንገታቸውን ላይ ምንም ምልክት የሌላቸው ሰዎች በተመሳሳይ
ጥፋት ብናገኛቸው ያላዳናቸው አለማሰራቸው ነው ብንል ምልክቱን አስረው ያጠፉትንስ ለምን አልታደጋቸውም? ብለን
መጠየቁ ተገቢ ነው።
ስለዚህ ከክር ማሰር ጀርባ የራሳቸውን ዓላማ ለማራገብ የሚፈልጉ ቡድኖች ክር ስላሰራችሁ ጻድቅ አትሆኑም፤
ስላላሰራችሁም አትኮነኑም
እንላቸዋለን። ክርስትና በክርስቶስ በማመንና የሥጋ ሥራዎችን በመተው የሚጓዙበት ሕይወት እንጂ ክር በማሰር
ክርስቲያን መሆንህን ለሰዎች የምታሳይበት የጎዳና ላይ ማስታወቂያ አይደለም። ባለክሮችም እንደባለቡርቃዎቹ
ተረጋጉ።
ጥል፤ ክርክር፤ አድመኝነት፤ በወንጌል ቃል ያልሆነ
የቃላት ስንጠቃ፤ እውነትን የተቀሙ ሰዎች ተግባር ነው። አንዲቱ ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለችውም በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ስለተሞላች
ነው። የሐራ ተዋሕዶው አሉላ ያልኖረበትን ክርስትና በክር ስር ቢፈልገው አያገኘውም። እንዲያውም ጥፋት በደጁ ታደባለች።
ክርስትና ስለስዕል ስለመስቀል፤ አንገት ላይ ክር
ስለማሰር አይደለም። ክርስቶስን ስለመምሰል እንጂ።
«እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት
የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት
ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም
ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን
በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ» 1ኛ ጢሞ 6፤3-5