Sunday, July 13, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!



( እዝራ ስነ ጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)
ክፍል አምስት

6.  የተጣረሰ  ደኅንነትና  የተቃወሰ  ክርስትና።

 በተአምረ  ማርያም  ውስጥ ተዝካር  ያድናል፤  ማርያምን  ማመን  ያድናል፤  ተዝካሯን  መደገስ  ያድናል። በምዕ. 67  እረኞች  ያጠመቁት  አይሁድ  ውኃ  በቋጫ  ስለረጩበት  ብቻ ክርስቲያን  ሆነ፤  በ94  በንጹህ  እጅ  መቁረብ  መንግሥተ  ሰማያት ያስገባል።  78  ሰዎች  ቆርጥሞ  በልቶ  በማርያም  ስም  ጥርኝ  ውኃ  ከተሰጠ  ያ  ሚዛኑን  ደፍቶ  ከገሃነም  ፍርድ  ነጻ  ያወጣል።  ምጽዋት  መስጠት መንግሥተ  ሰማያት  ያስገባል፤  ምዕ.  44፤  ወዘተ።  ክርስትና  በተአምረ ማርያም  መመነን፥  መመንኮስ፥  ያለማግባት  ወይም  ጋብቻን  መጠየፍ፥ ከተጋቡም  በኋላ  አብሮ  ከመተኛት  ያለመገናኘት፥  ወደ  ስዕል  መጸለይና  መስገድ፥ ወዘተ፥ ናቸው። በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  ግን  ደህንነትና  የክርስትና  ኑሮ  በቃልና  በሥራ ክርስቶስን  እየመሰሉ፥  እየተከተሉ  የመኖር፥  መስቀሉን  የመሸከም  የደቀ መዝሙርነት  ኑሮ  ነው።  በመጽሐፍ  ቅዱስ  መዳን  በሌላ  በማንም እንደሌለ፥  እንድንበት  ዘንድ  የተሰጠ  የኢየሱስ  ስም  ብቻ  መሆኑ፥ ክርስቶስን  የተቀበሉ  ሁሉ  የእግዚአብሔር  ልጆች  መሆናቸው፥  ለመዳን ማመን  ብቻ  እንጂ  ልፋት  እንደማያስፈልግ፥  ያመነ  የተጠመቀ እንደሚድን፥  መዳን  ደግሞ  የሚታወቅና  የሚረጋገጥ  እንደሆነ  በግልጽ  ቋንቋ  ተጽፎአል።  በተአምረ  ማርያም  ግን  ይህ  አዳኝ  እና  የማዳኑ  ደስታ  ሲሸፈንና  እንዳይታይ  ሲደበቅ  ይስተዋላል። በምዕ.  41፥13  “በእግዚአብሔር  አምነው፥  በወለደችውም  በእመቤታችን አምነው  ከቤተ  ክርስቲያን  ወጡ”  ይላል።  ቁ.  25  እምነቱን  በናቱና  በእግዚአብሔር  ላይ  ያደረገ  ሁሉ  አያፍርምና  ይላል።  53፥55  ላይ  እግዚአብሔርን  አመሰገኑ  እመቤታችንንም  አመሰገንዋት  ይላል።  እምነት ክርስቶስ  ሲደመር  ሌላ  ነገር  ሆነ  ማለት ነው! በምዕ. 56  ማርያም  አንዱን መነኩሴ፥ “ከሚያልፈው ዓለም እስክወስድህ  ድረስ  ልጄ  ካንተ  አይለይም”  አለችው። ወሳጇ  እርሷ ስትሆን እስክትወስደው  ከመነኩሴው  የማይለየው  ልጇ  ነው።  ልክ  እንደ  አገልጋይ  ማለት  ነው።  በመጽሐፉ  ማርያም  ብቻ “ከልጇ  ጎን  በፈሰሰው  ደሟ”  አዳኝ  ሆና  ቀርባለች።  ታዲያ  ይህ የሰሚዎችን  ጆሮ  እያደነቆረ  የጠፉቱ  የምሥራቹን  ወንጌሉን  እንዴት ይስሙ?

7.  የተላቀቀ  መልክዓ  ምድር።

 በተአምረ ማርያም  ውስጥ  የተናጋ  መልክዓ  ምድርም  ይታያል።  ኢየሱስ  በዋሻ  ውስጥ  ተወለደ  ይላል፤  ለምሳሌ፥  ምዕ. 10።  ግርግምና  ዋሻ  እንደምን  አንድ  ሆኑ?  በ106  በኢያሪኮ  ባህር  ዳርቻ  ገዳም  ያለባት  ደሴት  መኖሯን  ይናገራል።  ደሴት  በባህር  ውስጥ  እንጂ  በባህር  ዳርቻ  አይኖርም።  ይሁን  እዳሩጋ  ጠጋ  ብሎ  ነው  ይባል።  ግን ኢያሪኮ  እኮ  ከተማ  እንጂ  ባህር  አይደለችም።  ኢያሪኮ  የሚባል  ባህር ኖሮም  አያውቅም።  በኢያሪኮ  አቅራቢያ  የዮርዳኖስ  ወንዝ  ነው  ያለው፤ ያም ቢሆን ገዳም የተገደመበት ደሴት የለበትም። ምዕ. 9  እና  ምዕ. 118  ከእስራኤል  ወደ  ግብጽ  ወይም  ከግብጽ  እስራኤል ሲሄዱ  ባህር  ሲሻገሩ  ይታያሉ።  በሁለቱ  አገሮች  መካከል  የየብስ  መንገድ ሳለ  በባህር  የሚያስዞር  ምክንያት  የለም።  ምናልባት  ከእስራኤል  ባህረ  ኤርትራን  መሻገር  ጋር  ለማቆራኘት  ይሆናል።  ወይም  ምናልባት  ከክብረ ነገሥት  ታሪክ  ጋር  ለማመሳሰል  የተደረገ  ሙከራ  ነው።  በጉዞውም  ተጋንነው  የተጻፉት  ነገሮች  ከክብረ  ነገሥት  ጋር  መመሳሰል  ስላላቸው  ከዚያ  የተኮረጀ  ይመስላል።
በምዕ. 72  ከሄሮድስ  ሸሽታ  ወደ  ዮሳፍጥ  ሸለቆ  ሄዳ  መሸሸጓ  ተጽፏል። ሊያያት  የመጣው  ገዢ  ከሄሮድስ  ሌላ  ሲሆን  ይህ  ሰው  ከሄሮድስ  ጋር ሊዋጋ  ዘምቶ  በማርያም  አማላጅነት  ተመለሰ።  እንደ  ፀሐይ  የሚያበራ ግርማ  ኖሯት  መሸሿ ወደ  ጎን ይቅርና፥ ጫካውም  ጫካ  ሆኖ ገዳም  መሆኑ ወይም  መባሉም  ይቅርና  በዮሳፍጥ  ሸለቆ  መደበቋና  ሁለቱ  ኃያላን  ሊዋጉ  መሰላለፋቸው  ሁለት  አገሮች  ብቻ  ሳይሆኑ  የሩቅ  አገሮችም  ያስመስላቸዋል።  ግን  የዮሳፍጥ  ሸለቆ  ከኢየሩሳሌም  በ20  ኪሎ  ሜትር ርቀት  የሚገኝ  ስፍራ  ነው።  በዚህ  አጭር  ርቀት  በሄሮድስ  ግዛት  ውስጥ ሌላ ገዥ ያውም  ከሄሮድስ  ሊዋጋ  የቃጣ  አልኖረም።

8.  የተዋረደ  ጋብቻ። 

መጽሐፍ  ቅዱስ  ጋብቻ  ክቡር  መኝታውም  በሁሉ  ቅዱስ  መሆኑን  ያስተምራል።  ጋብቻ  በማኅበራዊ  ረገድ፥  ለቤተ  ሰብ  ጤናማነት፥  በቅድስና  ለመኖር፥  ዘርን  ለመጠበቅ  በሙሉ  መልኩ፥ የተከበረ  ተቋም  ነው።  በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የሚታየው  ግን  የዚህ ተቃራኒ  ነው።  ጋብቻ  የተናቀ  ነው።  ያላገቡ  ሰዎች  በተአምረ  ማርያሟ ; ማርያም  እንዳያገቡ  ይመከራሉ።  የተጋቡም  ሳይቀሩ  ትዳራቸው  ፈርሶ  እንዲመንኑ  ይደፋፈራሉ።  ምዕ.  65፥  66፥  68፥  75፥  86፥  92፥  100 እንዳያገቡ  የተከለከሉ  ሰዎች  ታሪኮች ይነበባሉ።
በምዕ. 30  ካህን  ዘራፊዎችን  ግደሉ  አባለ  ዘራቸውንም  ስለቧቸው  ብሎ  ሲያዝ  ይታያል።  ለነገሩ  ከተገደሉ  በኋላ  ብልት  ዋጋ  የለውም፤  ግን የተደረገው  ሁሉ  ተደርጎ  ይህ  ሁሉ  በማርያም  አማላጅነት  ተደረገ  ብሎ ይደመድማል።  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  አባለ  ዝርም  እንዲሰለብ  ታደርጋለች።  በምዕ. 85  ከገዛ  ሚስቱ  ጋር  መተኛቱ  እንደ  ኃጢአት  ሆኖበት  አባለ  ዘሩን  የቆረጠ  ሰው  ይገኛል።  ይህ  ሰው  ከደም  ፍሰት  የተነሣ  ሞቶ  መንግሥተ  ሰማያት  ሄዶ  በማርያም  ትእዛዝ ነፍሱ  ወደ  ሥጋዋ  ተመለሰችና  በሕይወት ኖረ።  መንግሥተ  ሰማያት  ከገባ  በኋላ  ነፍሱን  ብትመልስም  ቅሉ  ብልቱን ግን  አልቀጠለችለትም።  የሽንት  መሽኛ  ቀዳዳ  ብቻ  ተደርጎለት  መንኩሶ ኖረ።  በተአምረ  ማርያም  ትዳር  የቀለለ  ብቻ  ሳይሆን  የረከሰ  ነገር  ነው።
ከመነኮሰች  በኋላ  በፈቃደ  ሥጋ  ተሸንፋ  ከገዳም  የወጣችና  ያገባች  ሴት በመካንነት  ተቀጥታ  ወደ  ገዳሟ  ተመለሰች።  ሌሎችም  ይህም  የመሰሉ ታሪኮች ታጭቀውበታል።

9.  ያፈነገጠ  ተፈጥሮ።

 በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የበዙ  ከተፈጥሮ ሥርዓት  ጋር  የማይስማሙና  የሚቃረኑ  ነገሮች  ይነበባሉ።  በምዕ.  70  አንድ  ሰው  ሥጋ  ወደሙን  ከወሰደ  በኋላ  አውጥቶ  በንብ  ቀፎው  ውስጥ አደረገው።  በኋላ  ሥጋ  ወደሙ  ወደ  ብርሃንና  የማርያም  ስዕልነት  ተለወጠ።  በእጅግ  ብዙ  ቦታዎች  የማርያም  ስዕል  ከስዕል  ተፈጥሮ  ውጪ  ድምጽ ሲወጣው፥  ሲደማ፥  ወዝ  ሲወጣውና  ሰዎች  ያንን  እየተቀቡ  ሲፈወሱ ይታያል።  እጅ  ዘርግቶ  ከተንቀሳቀሰ  ወይም  ሌላ  ስዕል  ከሰጠ፥  የቆሰለበት  ስፍራ  ጠባሳ  ከኖረው፥  ስዕል  ሲወጉት  ከደማ  (ለምሳሌ፥  ምዕ. 31)  ስዕሉ  ሕይወት  አለው  ማለት  ነው።  ምክንያቱም  መጽሐፍ  ቅዱስ  ሕይወት በደም  ውስጥ  መኖሩን  ይመሰክራል።  ከላይ  እንደተጠቀሰው  ስዕል  በራሱ  የተፈጠረ  ካልሆነ  ስዕል  እየሠሩ፥  እየሸጡ  የሚተዳደሩ  ሰዎች  አሉና  ስዕሎቹ  በሰው  የተሠሩ  ለመሆናቸው  ጥርጥር  የለበትም።  የስዕል  አምልኮ  በመጽሐፍ  ቅዱስ  የተወገዘ  መሆኑ  እንዳለ  ሆኖ  ስዕሎቹ  ተአምራት ካደረጉ፥  ሲወጉአቸው  ከደሙ  ሕይወት  አላቸውና  ሠሪዎቹ  ምን  ሊባሉ ነው?  ፈጣሪ?  አምላክ?  በተአምረ  ማርያም  ስዕል  ብቻ  ሳይሆን  ዳቦም ሲቆርሱት ደምቷል። በተአምረ  ማርያም  ወደ  ዓሳነት  ሳይለወጡ  በባህር  ውስጥ  ሆኖ  መተንፈስም፥  መጸለይም፥  እንዲያውም  መውለድም  ይቻላል።  በተአምር 97  አንድ  መነኩሴ  የውኃ  ሙላት  አማታውና  ሰይጣን  ወስዶ  እባህር ከተተው። እዚያ ሳለ ማርያምን  ጠርቶ ሲጸልይ ማርያም  መጥታ  ሰይጣንን  ገሰጸችለት።  እሱም  ውዳሴውን  ቀጠለ፤  የሚጸልይበትን  ቦታ  አሳየችውና በዚያ  ሲጸልይ  አደረ።  ዋናተኞች  ለፍለጋ  ሲጠልቁ  ውዳሴዋን  ሲደግም  አግኝተው  አወጡት።  እዚያ  ለመቆየት  ሲል  ባትመጡብኝ  ይሻለኝ  ነበር አላቸው።  በተአምር  88  ደግሞ  አንዲት  ነፍሰ  ጡር  ከመስጠም  መዳኗ  ብቻ ሳይሆን  በባሕር  ውስጥ  ሳለች  በቤት  ውስጥ  እንዳለች  ሆና  በማርያም  ተሸፍና  ወልዳለች።  ያውም  ያለምጥ  ነው  የወለደችው።  ከተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  ሌላ  ያለምጥ  የወለደች  ሴት  ናት  ይህች  ሴት።  በ375  ዓመቷ  የሞተችው  ክርስቶስ  ሠምራ  በጣና  ባህር  ውስጥ  ሰውነቷ  ተበጣጥሶ  ዓሳዎች  በውስጧ  እየሾለኩ  12  ዓመት  ጸልያ  ወጣች  እንደሚባለው  የመሰለ  ታሪክ  ነው። 15 በምዕ. 59  አንድ  የቤተ  ክርስቲያን  ጠባቂ  አንድ  ቀን  ከራት  በኋላ  የሥጋ ድቀት  አግኝቶት  ዝሙት  ፈጸመ።  በመልአክ  ተነክቶ  የሴት  መርገም ደረሰበትና  ከዚያ  በኋላ  ማርያም  ያደረገችበትን  ይህን  ነገር  አገር  ላገር  እየተናገረ  በመዞር  ኖረ።  መልአክ  ቢነካውም  ይህን  ያደረገችው  ማርያም  ናት።  ይህች  የዚህ  መጽሐፍ  ማርያም  ምንም  ነገር  ማድረግ  ትችላለች።

ሰብዓዊ  ተፈጥሮንም  ትቀይራለች።  የወር  አበባ  ካየ  ማኅጸን  ተሠራለት ማለት  ነው።  ማመንዘሩ  ኃጢአት  ሳለ  ቅጣቱ  ሴት  መደረግ  ወይም  እንደ ሴት  መደረግ  ከሆነ  ይህች  ማርያም  ሴትነቷንም  ትጠላዋለች  ማለት ይሆን? በምዕ.  107  ብዙ  ኃጢአት  ፈጽማ  ተስፋ  የቆረጠች  ተቅበዝባዥ  የሆነች ሴት  ታሪክ  ይገኛል።  ይህች  ሴት  ወደ  በረሃ  ሂዳ  ጊንጥ  አገኘችና ዋጠችው።  መርዙ  በሰውነቷ  ተሰራጭቶ  ስትሰቃይ  የማርያም  ስዕል  መጥቶላት  በዚያ  ሆዷን  እያሸች  ማርያምን  ለመነች።  ማርያም  ወደ  ቄስ ልካት  ለዚያ  ቄስ  ተናዝዛ  አምጣ  ወለደች።  የወለደችው  ሕጻንን  ሳይሆን 40  ትልልቅና  ትንንሽ  ጊንጦችን  ነው።  ወደ  አፍ  የገባ  ወደ  እዳሪ እንደሚወጣ  ጌታ  የተናገረው  ስሕተት  ተደርጎ  ወደ  ማሕጸን  ገብቶ  በ40  ተባዝቶ ወጣ!  እንደዚህ  ትምህርት  ከሆነ  ሴቶች ላም  እንወልዳለን  ብለው  በመፍራት  ወተት  መጠጣት  ማቆም  አለባቸው።  ወይም  አስር  ዶሮ  እንወልዳለን  ብለው  እንቁላል  መብላት  መተው  ይኖርባቸዋል።  ደግሞ  ሁሉም  እንደየወገኑ  እንዲዋለድ  በፍጥረት  መጀመሪያ  የተነገረውም  ተሰረዘና  ሴት  ጊንጥ  ወለደች።  ለተአምሩ  ትክክልነት  ሲባል  መጽሐፍ ቅዱስ  መስተካከል  አለበት።
ጊንጥ ብቻ  ሳይሆን  ሌላም  የከፋ  ወሊድ ታሪክ  አለ። በምዕ. 55 የሌላ  ሴት  ባል  የቀማች  አንዲት  ሴትና  ሌላኛዋ  ሴት  በማርያም  ታቦት  ፊት  እውነተኞች  መሆናቸውን  ይማማላሉ።  የቀማችው  ሴት  ኃጢአተኛ  ኖራለችና  እርጉዝም  ነበረችና  ቆይታ  ወለደች። የወለደችው  ሕጻን  ሳይሆን  በትል  የተሞሉ  ሁለት  የላም፥  ሁለት  የበግ  ቀንዶችን  ነው።  ይህች  ሴት እብድ  ሆና  እየዞረች  ይህንኑም  ያደረገችው  ማርያም  መሆኗን  እየተናገረች  ቆይታ  ሞተች። ቀንዶቹ  ደግሞ  ከማኅጸን  እንደወጡ  እንኳ  አልተቀበሩም።
በማርያም  ቤተ  ክርስቲያን  መስኮቶች  ተሰክተው  ይኖራሉ።  የትኛዋ  ቤተ ክርስቲያን  እንደሆነች  እንኳ  ቢናገሩ  ጉዱ  ይታይ  ነበር።  አገሩ  ብሔረ አግዓዚ  ከመባሉ  ሌላ  አይታወቅም።  በቀጣዩ  ምዕራፍ  (ምዕ. 56)  የያሬድ ቅኔ  ማኅሌት  እውስጡ  ስለተጠቀሰ  ብሔረ  አግዓዚ  የኛው  አገር  መሆኑን  እንረዳለን።  ቀድሞውኑም  የሌለ  ነገር  ስለሆነና  እንዲጠየቅና  እንዲመረመርም  ስለማይፈለግ  ስፍራው  አይገለጥም።  ወይስ  ዛሬም  ቀንዶቹ  ከአገራችን  ቤተ  ክርስቲያኖች  ባንዷ  መስኮቶች  እንደተሰኩ  ይሆኑ?