Thursday, October 31, 2013
Wednesday, October 30, 2013
የማይቀረው ለውጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘቱ አይቀርም!
ባልተዘጋጀችበትና በሚመጣው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።
(ክፍል አምስት)በክፍል አራት ጽሁፋችን በፍላጎት መጠን ማደግ፤ ለስኬት በሚደረገው ሩጫ፤ በኢንዱስትሪው ትንግርታዊ ግስጋሴና ለአእምሮ ልሽቀት የመጋለጥ አደጋ መካከል በሚኖረው ዕለታዊ የኑሮ መስተጋብር የተነሳ የአውሮፓውያን ሃይማኖቶች የማሽቆልቆል፤ የትርፍ ጊዜ ጉዳይ የማድረግ፤ ከዚያም አልፎ ተርፎ በሥራ ብቻ እንጂ በስብከት ልምምድ ምንም ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ በመቁጠር ወደ ክሂዶተ እግዚአብሔር የመሄድ ነገር መጠኑ እንደጨመረ እንደሄደና ይህም ክስተት በኢትዮጵያችንም እየታየ መገኘቱን ለማመልከት ሞክረን ነበር። ከዚህም የተነሳ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ነገር ግን ተግዳሮቶችን ለመከላከል የተወሰደ የጅማሮ ፍንጭ አለመኖሩን በማመልከት ለጉዳት የመጋለጣችንን አይቀሬነት በመጠቆም ጥቂት ለማሳየት ሞክረን ነበር። በዚህ ክፍል ደግሞ ቀጣዩን ነጥብ እንመለከታለን።
3/ የኑሮ ምቾት፤ ድሎት የተነሳ በሚከተለው ስግብግብነትና የምኞት ከፍታ በሚያስከትለው የአእምሮ ድንዛዜ የተነሳ የሚመጣው የእምነት ጉድለት፤
በመስከረም ወር ኒውዮርክ ላይ ተደርጎ በነበረው የተመድ
ጉባዔ ላይ ከዓለም የመጨረሻው ደሃ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የሚታወቁት የኡሩጓይ/Uruguay/ ፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ ባደረጉት ታሪካዊ
ንግግር እንዲህ ብለው ነበር።
«ድሃ ማነው? የሚለውን ጥያቄ በኔ አፈታት ሲተረጎም ለመኖር ሲል ብዙ የሚፈልግ አስተሳሰብ ያለው ነው» ሲሉ መናገራቸው
የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። ለምን? እንዲህ እንዳሉም በሰጡት ማብራሪያ «ብዙ የሚፈልጉ ሰዎች ያንን ለማሟላት የኅሊና እረፍት
የላቸውም፤ ከዚህም የተነሳ በሕይወታቸው ሙሉ እንደሮጡና እንደደከሙ ይኖራሉ፤ በቃኝን አያውቁም። ከእነዚህ የበለጠ የመኖር እርካታ
የሌላቸው ደሃ የትም የለም» በማለት ጉባዔውን አስደምመውት ነበር። የፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ ንግግር በኢትዮጵያውያን ምሳሌ በአጭር
ቃል ሲቀመጥ «ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ» እን,ደማለት መሆኑ ነው። የ78 ዓመቱ ጆሴ ሙጂካ የኡሩጓይ ፕሬዚዳንት ይሁኑ እንጂ የሚተዳደሩት
የገጠር መሬታቸውን በትራክተራቸው እያረሱ የሚተክሉትን ስኳር ድንችና ለውዝ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸው በዓለማችን ላይ ካሉ የሀገር
መሪዎች ልዩ ያደርጋቸዋል። በቅርቡ ለአንድ ቴሌቪዥን በሰጡት የቃለ መጠይቅ ምላሽ ላይ «የኑሮ ምቾትህ በጣም የተደላደለ ከሆነና
ከሌላው ሕዝብ የተለህ እንደሆነ ማሰብ ከጀመርህ፤ በጣም ስግብግብና ስለምትኖርበት ዓለም ማሰብ የማይችል የደነዘዘ አእምሮ ተሸካሚ
ትሆናለህ» በማለት መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ሲወጡና ሲገቡ ቀይ ምንጣፍ የሚረግጡ መሪዎች፤ ተራ ሰው የነበሩና አጋጣሚዎች
ከፍታ ላይ ያስቀመጣቸው ሰዎች በአብዛኛው ስግብግቦች ስለሆኑ ስለወጡበት ማኅበረሰብ ደንታ የላቸውም። ምክንያቱም ሰዎቹ ማሰብ ስለማይፈልጉ
ሳይሆን የሚያስቡበትን አእምሮ የኑሮው ምቾትና የአእምሮ ድንዛዜ እንዳያስቡ ዘግቶ ስለሚይዛቸው ነው» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አክለው ተናግረው
ነበር።
አባባላቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው። ይህ ሁኔታ በአውሮፓውያኑና በአጠቃላይ በምዕራባውያኑ ዘንድ ስር በመስደዱ
የተነሳ የቅንጦት/Luxury/ ኑሯቸው መጠን የለሽ ወደመሆን በመሸጋገሩ የነበረውን አዲስ ነገር አውጥቶ በመጣል ለበለጠ አዲስ ነገር
ራስን በማስገዛት አዲስ ቤት፤ አዲስ መኪና፤ አዲስ የቤት እቃ፤ አዲስ አዲስ ሁሉን አዲስ በማድረግ አባዜ አእምሮአቸው ደንዝዟል።
ስግብግብነትና በቃኝ የማለትን ገደብ የማለፉ አስተሳሰብ የሚጎትተው እንከን ለተራበ ያለማዘንን፤ ለሰዎች ችግር አለመድረስ ብቻ ሳይሆን
ደንታ ቢስ መሆንን፤ ተካፍሎ መብላት የሚለው ብሂል የሰነፎች መፈክር እንደሆነ ማሰብን የመሳሰሉ ችግሮችን ያስከትላል። ምንም እንኳን
የተስተካከለ ኑሮን መኖር ጥፋት ባይሆንም በቃኝን አለማወቅ ግን ትልቅ በደል ነው። በተለይም ደግሞ ክርስቲያኖች ኑሮዬ ይበቃኛል
ማለትን ካልተማሩ እግዚአብሔር እነሱን ለቅንጦት እንደፈጠራቸው ማሰብን መለማመዳቸው አይቀርም።
ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናል። «ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ
ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም
መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም
አደረጋችሁ» ፊልጵ 4፤10-14
የጠገቡና በዚህ ጥጋብ የተነሳ አእምሮአቸው የደነዘዘ፤
የሌሎችን ጥጋብ በማየት ለማግኘት የሚራወጡ፤ ትግላቸው ሁሉ የሥጋን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሰዎች በሌሎች ችግር የመካፈል ፍላጎት የላቸውም። እምነት እንዳላቸው ቢያስቡም የእምነታቸው ከፊል ምኞታቸውን በማሳካት ላይ የታጠረ
ነው። በአውሮፓ ይህንን መሰሉ ቅንጦትና መጠን የሌለው ምቾት በአእምሮ ላይ በመሰልጠኑ የተነሳ አብያተ ክርስቲያናቱ አማኞችን ከማስተናገድ
ተላቀው ወደመዝናኛና ሆቴልነት፤ የገበያ አዳራሽነትና ጋራዥነት ለመቀየር ተገደዋል። በክርስትና ስም ከሚጠራው ተከታይ ውስጥ ቤተ
ክርስቲያን በመሄድ በዕለተ እሁድ የጸሎት ፕሮግራም ላይ የሚገኘው ተሳታፊ ቁጥር በጣም አሽቆልቁሏል። በእንግሊዝ 1,4% ፤ በፈረንሳይ
0,9%፤ በጀርመን 1,2% ብቻ እንደሚገኙ ክርስቲያን ፖስት በ2011 ዓ/ም ባደረገው ጥናት የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት ሞክሯል።
የሥነ ምግባር ልሽቀት፤ ስግብግብነት፤ የግብረ ገብነት ድቀት መነሻው የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ምክንያት ካለማወቅና ባወቀው ላይ
ለመኖር ካለመፈለግ የሚመነጭ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊት የተነሳ የሚመጣ ነው። ምዕራባዊው ኑሮ አሁን አሁን መሥፈሪያውን የሞላ/ Saturate/
ያደረገ ይመስላል። እድገቱን የጨረሰ የወይን ግንድ እንደገና ተገርዞ
ካልታደሰ በስተቀር ፍሬ ከማፍራት መለየቱና መድረቁ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የማብቃቱ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ኢትዮጵያችንን ስንቃኝ የእድገት መሥፈሪያዋ ሞልቷን ማለት አንችልም። ይሁን እንጂ እንደሀገር ለመቀጠል መስራትና ማደግ
የግድ የማለቱን ያህል ዕለታዊ የኑሮ መስተጋብራችንን የሚሻማ የሥራና የሩጫ ሕይወት ወደመለማመዱ መግባታችን አይቀሬ ነው። ከዚህም
የተነሳ ዘመኑን የዋጀ የሃይማኖት አስተምህሮና የተግባር ተሞክሮ በአማኞቻችን ውስጥ ማሳደግ ካልቻልን ጥያቄን በሚያጭሩ፤ እምነትን
በሚሸረሽሩና ምላሽ በሚጠይቁ ዙሪያ ገባ ጥያቄዎች መወጠራችን አይቀርም። ትውልዱን አስፈራርተው፤ በማያረካ ምክንያት ውስጥ አእምሮን
በመደበቅ ማሳመን አይቻልም። ወደዚህ ምድር የመጣበትን ምክንያትና የመኖር ልኬታን የማይዘነጋ ልቡናን እንዲጨብጥ የሚያስችል መንፈሳዊ
የቃል ወተትን መጋት፤ እንደአዋቂ ማሰብ የሚችልበትን የእምነት ተስፋ እንዲጠባበቅ ካላደረግነው ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ትምህርት
ቤት ወደመሆን መቀየሯ አይቀርም። ኑሮዬ ይበቃኛልን ማሰብ የተወ ትውልድ ሌብነትን፤ ዝርፊያን፤ ሙስናን፤ ዝሙትን፤አስገድዶ መድፈርን፤
ግድያንና ልዩ ልዩ ወንጀልን መላመዱ አይቀርም። እውነተኛ እምነት ከዚህ ሁሉ አስከፊ ማንነት ይከላከላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ያለንበት መንፈስ በቆየ መልካም ባህልና ከቤተሰብእ በተወረሰ ልምድ ብዙ
የሚያሳስብ የላሸቀ የትውልድ ውድቀት ባይታይም ፍንጮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ከሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ ጉድለቶቹ የትውልዱን
ድክመት እያመላከቱ ናቸው። ገንዘብንና ጥቅምን መሠረት ያደረጉ አብያተ ክርስቲያናት መስፋፋታቸው፤ በአስነዋሪ ስነ ምግባራቸው የተነሳ
በሰማይም በምድርም ከፍ ያለው የእግዚአብሔር ስም እንዲሰደብ ምክንያት
መሆናቸውን እያየን ነው። ዝሙት፤ ስርቆት፤ ስግብግብነት፤ ዘረኝነት፤ አድልዎ፤ ፍትህ ማጣመም፤ በደልና ብቀላ እየነገሠ ነው። ጥላቻና
ቂም እየተዘራና እያደገ ይገኛል። ዘረፋና ጉቦ የብዙዎችን ዓይን አሳውሯል። «ማሰነ» ከሚለው ግእዛዊ ግስ የተጨለፈችው «ሙስና»
የተሰኘችው ዘመናዊ ቃል የሚዲያ የእርግማን ጸሎት መሆን ከጀመረችም ሰነባብታለች። በዚህ ላይ የአብያተ ክርስቲያናቱ ስፍራ የት ነው?
ብለን እንጠይቃለን።
አብያተ ክርስቲያናቱ እንኳን ለሌላው ብርሃን ሊሆኑ ቀርተው ራሳቸው በችግሩ ማስነዋል። ስግብግብነት፤ ለድሎትና ምቾት
የመራወጥ አባዜ ተበራክቷል። ገንዘብን ብቻ ማዕከል ያደረገ በእግዚአብሔር ስም የመሸቀጥ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ዝሙትና ገንዘብ
መለያቸው ሆኗል። ከወንጌላውያኑ ጀምሮ እስከ ኦርቶዶክሳውያኑ ድረስ የዚህ በሽታ ምልክት ስር ሰዷል። የዚህ ዓይነቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር የመጥፋቱ ነገር ለኑሮ ስኬት
የሚራወጠውን ህዝብ አእምሮ አይበርዘውም ማለት አይቻልም።
ከዚህም የተነሳ ሃይማኖት ለእግዚአብሔር አምልኮ የምንሰራበት የማንነታችን ቤት እንደሆነ የማሰቡ ነገር ይቀርና ክህዶተ
እግዚአብሔር የሚስፋፋበት፤ አእምሮአችንን ከተስፋ ማጣት የተነሳ ደንዝዞ ሥጋንና ሥጋን ብቻ ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች
እንዳንሆን ያስፈራል። ይህ የእምነት ጉድለት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጥበቃና ከለላ ውጭ ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ «ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለት ወደጥፋት ያደርሳል» ማለቱን ማስተዋል ተገቢ ነው።
አውሮፓውያኑንም ሲጀምራቸው እንደዚሁ በትንሽ በትንሹ ነበር። ምቾትና ምኞት የወለደው ስግብግብነት ሩጫቸውን በእጦት ቀውስ እየመታው ይገኛል። በእነሱ የደረሰ በእኛም ይህ እንዳይሆንብን
ከፈለግን መሥራት የሚገባን ዛሬ ነው። የቀነሰብንን የሰው ቁጥር ለማወቅ ስንፈልግ ያለንን እንዳናጣ እኛው ራሳችን ለመቆጠር የሚያበቃ
ማንነትን እንዳለን ቆም ብለን እናስተውል። ምድራዊው ቁጥር የሰማያዊውን መዝገብ ቁጥር አይተካምና።
ከፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ አብነታዊ ቃል ጠቅሰን ጽሁፋችንን እናጠቃልል። «እኔ የተወለድኩት ከሕዝቡ ነው። የኖርኩትና ያደኩት ሕዝቡ መሃከል ነው። ያሳደገኝ ሕዝብ ሲሾመኝ ስራልኝ እንጂ የተሻለ ኑሮ ኑርልኝ የሚል ውክልና አልሰጠኝም። የቻልኩትን ሁሉ ሕዝቡና ለምርጫው የፈቀደኝ እግዚአብሔር የሰጠኝን ችሎታ ሁሉ ሰርቼ ይበቃሃል ሲሉኝ ሕዝቡ መሐከል ተመልሼ እኖራለሁ። በሕይወቴ ሙሉ ኑሮዬ ይበቃኛልን ስለተማርኩ ወደሥልጣን ስመጣ ባዶዬን ነበርኩ፤ ስሄድም ባዶዬን ነው፤ ሳልመጣም፤ ከመጣሁም በኋላ ይሁን ስሄድ ድንች ተክዬ በላቤ ወዝ ብቻ ሰርቼ እኖራለሁ»
Friday, October 25, 2013
ኢትዮጵያውያን እንኳን በሀገራቸው በባዕድ ሀገር የነጻነትና የሃይማኖት መምህራን ነበሩ!!
በ1808 እ/ኤአ ኢትዮጵያውያን የንግድ ሰዎች ወደአሜሪካ ያቀናሉ። በቆይታቸውም ከነጮቹ ቤተ ክርስቲያን የሰማይና የምድር ገዢ ለሆነው አምላካቸው ጸሎት ለማድረስ ይገባሉ። ይሁን እንጂ የዘር፤ የቆዳ ቀለምና የነገድ ልዩነት በሌለው አምልኮተ እግዚአብሔር ኢትዮጵያውያንን በነጮቹ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠማቸው ነገር የተለየ ነው። ለጥቁሮቹ ተለይቶ ከተሰጠው ክልል ውጪ በጸሎት ቤት ውስጥ ከነጮቹ ጋር በእኩልነት መጸለይ ይከለከላሉ። ኢትዮጵያውያኑም የነጭና የጥቁር ተብሎ የተለየ አምላክ ሳይኖር በጸሎት ቤት ጥቁሮቹን የማግለል አሠራር ባለመቀበላቸው ጸሎት ቤቱን ለቀው ይወጣሉ። በዚህን ጊዜ በዚያ የነበሩ አሜሪካውያን ጥቁሮችም የመገለሉን እርምጃ ከተቃወሙት ኢትዮጵያውያን ጋር ተከትለው ይወጣሉ። በኢትዮጵያውያኑ መሪነት ጥቁሮቹ አሜሪካውያን በኒውዮርክ ከተማ አዲስ ቤተ ክርስቲያን በመመስረት ጸሎታቸውን በነጻነት ለመቀጠል ቻሉ። ጥቁር አሜሪካውያን እስከዛሬ ድረስ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን በየጊዜው በሚያዘጋጁት መንፈሳዊ ጉዞ የእምነት ነጻነትን ስላስተማረቻቸው ቤተ ክርስቲያንና ባርነት በመዋጋት ነጻ ሀገር ሆና የመዝለቋን ታሪክ በማስታወስ እናት ምድራችን የሚሏትን ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ። በተቃራኒው ደግሞ እናት ምድር ኢትዮጵያን ትተው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይሰደዳሉ። አሳዛኝ ነገር ነው። ከዚህ በፊት ይህንን በተመለከተ ያወጣነውን ዘገባ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ።
የአቢሲኒያን ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ዶ/ር ቄስ ካልቪን በትስ በየዓመቱ በሚታሰበው የጥቁር አሜሪካውያን ታሪክና ማንነት ጥናታዊ ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከነባለቤታቸው በተገኙበት ትልቅ ንግግር አድርገዋል። ፎክስ ኒውስ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ታላቅ ሀገርነት፤ ታሪክና እምነት ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። በዚህ በአፍሪካውያን ታሪክና ባህል ዓመታዊ የጥናት ጉባዔ ላይ የፕሮግራም መሪ የነበረችው በታዋቂው የቢል ኮስቢ/Bill Cosby/ ተከታታይ የቤተሰብ ፊልም ላይ መሪ ተዋናይት የነበረችው ፊሊሺያ ራሻድ ነበረች። ኢትዮጵያውያን ነጻነትን በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በባዕድ ሀገር ጭምር ሄደው ማስተማር የቻሉ ሕዝቦች ነበሩ። እንደዚህ እንደዛሬው በባርነት መልክ በዐረብ ሀገራቱና በየምዕራቡ ዓለም በስደት ጉልበታቸውን እንደሸቀጥ ከነነጻነታቸው ጭምር ከመሸጣቸው በፊት ማለት ነው። ለማንኛውም ኢትዮጵያና የጳውሎስ መልዕክት ትርጉም የተወደሰበት ዝግጅት ይህንን ይመስላል።
«አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና» ገላ 3፤28
Sunday, October 20, 2013
እውነቱ ስንናገር ጳጳሳቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዘብ አልቆሙም!!
የካህናቱና ጡረተኞች የተሰገሰጉበት የሰበካ ጉባዔ ምእመናን ተወካዮች በዓመት አንድ ጊዜ ተሰብስበው በሚመሰጋገኑበትና
የድግስ ጋጋታ በሚያስተናግዱበት የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባዔ ላይ ስለመቻቻል የቀረበውን አጀንዳ አስታከው ጳጳሳቱ ስሜታቸውን
መግለጻቸውን ሰምተን ጥቂት ተደነቅን። እንዴት ወንድ ወጣቸው? ብለንም ጥቂት አድናቆትን ቸርናቸው። ለካስ ከቀሚሳቸው ስር ሱሪ ታጥቀዋል?
ይሁን እንጂ
ሱሪ ነገረ ስር አይሆንምና ነገሩ አጋጣሚን የመጠቀም እንጂ የወንድነት አይደለም።
በዚያች የመቻቻል መድረክ ለመተንፈስ ከመፈለጋቸው በስተቀር
በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለመፍታት አንዳችም ህልምና ርእይ እንደሌላቸው የተገነዘብንበት ሁኔታ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ
እንደተቋም የት ነበረች? አሁንስ የት ነው ያለችው? ወደፊት እንዴትና የት ትራመዳለች? ለሚለው አንኳርና ቁልፍ የመንፈሳዊ ጉዞ
መልህቅ መጣያ የሚሆን የሃሳብ ወደብ አንዳችም ሳናይ በማለፉ ግንፍል ንግግራቸውን ታዘብነው። አንድም አባል ቢሆን ሲጎዳ ማየት ልብን
እንደሚሰብርና መንፈሳዊ ልማት ማካሄድ የሚቻልበትን አንድም ጋት ይዞታን ማጣቱ ቢያንገበግብም የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ ችግር በመሬት ተወሰደብኝና አንድ አባል ታሰረብኝ
በሚል አቤቱታ የሚገለጽ አልነበረም። ይሁን እንጂ ጳጳሳቱ ሲጮሁ የሰማነው ንግግር በቁራሽ መሬትና በአንድ ምእመን መጎዳት ላይ ማተኮሩ
የችግሩን ስፋት ለመመልከት አለመቻላቸውን ያመላከተ ሆኖ አልፏል።
በጳጳሳቱ ሊታይ ያልቻለውና መታየት የነበረበት የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥና የውጪ ችግር፤
1/ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል፤ ሲዘረፍ፤ ምእመናንና ምእመናት ሲሰደዱ፤ በአሸባሪና በአክራሪዎች ሲገደሉ መቆየታቸው ዓመታት
ተቆጥረዋል። ነገር ግን አንድም ጊዜ የጳጳሳቱን የድፍረት ሱሪ በንግግር አላየንም። ለምን? አንድም የፍርሃት ቆፈን ወሮአቸዋል።
አለያም የመንፈሳዊነት እንጥፍጣፊ አልቆባቸዋል። የመቻቻል ፖለቲካ ዲስኩር ሲፈነዳ አብሮ ማንዳዳት ያስተዛዝባል እንጂ አባቶች ለቤተ
ክርስቲያኒቱ ችግር ዘብ ቆሙላት አያሰኝም።
2/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንግሥታዊ ሃይማኖት ሆና ለዘመናት በመቆየቷ ብቻ ጊዜ አመጣሾች እንደጠላት
ቢመለከቷትም ዘመንና ወቅት እንደዚያ ሆና እንድታልፍ ያደረጋትን ከመቀበል ውጪ «መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው» የሚል ሕግ
ለመቅረጽ ስለማትችል ይህንን ሁሉ አስልተው እንደባላንጣ ለሚቆጥሯት ወገኖች ለመንግሥት አካላትም ሆነ ለሌሎች የሃይማኖት ተቋሟት
መናገር፤ ማስረዳትና ማሳመን የሚችል አቋም በቤተ ክህነቱ ፕሮግራም ውስጥ ባለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ የነፍጠኞችና የትምክህተኞች
መናኸሪያ ተደርጋ በሌሎች ዘንድ በተሳለው ስዕል የተነሳ አጋጣሚውን ጠብቀው ብድር የመመለስ ጨለምተኛ አካሄድ ሲታይ ያንን በመጠቆም
ብቻ ችግሩን መግፈፍ አይቻልም። ስለዚህም ጳጳሳቱ መናገር የሚገባቸውን ሰዓት ቀድሞ አሳልፈውት ዛሬ ለችግሩ ማልቀስ የቤተ ክርስቲያን ዘብ አያሰኝም።
3/ ዋናው ችግር ከውስጥ መንፈሳዊ ማንነትን መታጠቅ ያስፈልጋል። ታሪክና ዘመን የሰጣቸውን ሥልጣንና እድሜ ሊሰሩበት
እንደሚገባ የሚረዳ ውስጠት ሊኖራቸው የግድ ይላል። ውጪያዊ ተጽእኖን ለመጋፈጥና ለማሸነፍ መንፈሳዊ ትጥቅ የሌለው ሹም በጦር አውድማው
ላይ የመጠቃትና የተሸናፊነት ድምጽ ማስተጋባቱ አይቀርም። ተመሪዎቹንም ለጥቃት ያጋልጣል። አሁንም ያየነው ያንን ጩኸት ነው። ጳጳሳቱ ይህንን የመንፈሳዊ ማንነትን ትጥቅ በተዋቡባቸው አልባሳት ለመካካስ
ይፈልጋሉ። ክብሩ ግን በመንፈሳዊ ስብእና እንጂ በመልክና በቁመና ስለማይገኝ ድፍረት፤ መንፈሳዊ ቅንዓትና ጥብዓት የራቃቸውም ለዚህ
ነው።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ዘረኝነትን፤ አድመኝነትን፤ ሙስናን፤ አድልዎን፤ ብቀላን፤ ዘረፋን፤ ግለኝነትን፤ ስብእናን
የሚያጎድፍ አስነዋሪ ተግባራትን በማድረግም ይሁን የሚያደርጉትን ባለመገሰጽ፤ ይልቁንም ስር እንዲሰድና እንዲስፋፋ ምክንያት በመሆን
ግምባር ቀደሞቹ ራሳቸው ጳጳሳቱ ናቸው። ጳጳሳቱ ራሳቸውን ያውቃሉ፤ ካህናቱም በትክክል ያውቋቸዋል። ሌላው ቀርቶ ምእመናንም ጭምር። ምንም እንኳን እንዲህ ማለቱ ቢያሳፍርም እውነቱን
አለመናገር በራሱ ወደፊት ሊቀጥል በሚችለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መገፋት ላይ መፍትሄ እንዳይኖር ማድረግ ነውና ከመናገር ውጪ ሌላ
መንገድ የለንም። ሰው ድካሙን አውቆ፤ በንስሀ ተመልሶ፤ ብርታት በሚሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለመሥራት እስካልተጋ ድረስ በልብስ
ውስጣዊ ማንነትን ቢሸፍኑት ተግባር ማንነትን፤ የኃጢአት ዋጋ እዳን ሲያስከትል በግልጽ መታየቱ አይቀርም። የጥቃቱ መብዛት የኃጢአትን
ደመወዝ እየተቀበሉ የመገኘት ምልክት ነው እንጂ እግዚአብሔር በፈተና ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ስለተዋት አይደለም።
ከዚህ በፊት ስለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባወጣነው ጽሁፍ
ስንጠቁም «የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ቅጠል የሌለው ዛፍ አንድ
ናቸው» ለማለት እንደሞከርነው ጉዳዩን በሂደት ስንመለከት ዛፍነቱ ከቅጠል አልባነት በከፋ መልኩ እየበሰበሰ በመሄድ ላይ እንዳለ
በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ጭብጥ ማቅረብ የሚቻልበት ሲሆን በአጠቃላይ
ጳጳሳቱ ከውጪያዊ ተግዳሮቶች በከፋ መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን እየገፉ ወደ ገደል በመንዳት ላይ እንደሚገኙ የሚያስረዳን እውነታ ነው።
አዲስ አበባ ላይ የሚፈጸመው የቤተ ክርስቲያን የዐመጻ ተግባር ጊምቢ ላይ ዋጋ አያስከፍላትም ያለው ማነው?
ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ችግር የበሰበሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ የመነኮሳት አባቶች አመራር ከፍተኛውን ድርሻ
ይወስዳል ማለት ይቻላል። በዚህ መልኩ ከቀጠለ በወለጋ ወይም በጋሞጎፋ መሬት ተወሰደ አለያም ገበሬ ተገረፈ ከሚለው ጩኸት ይልቅ
ከውስጥ በሚመጣው የዐመጽ ተግባር የተነሳ የሚከሰተው ጥፋት የከፋ
ይሆናል።
ከሰሞነኛው የሰበካ ጉባዔው ስብሰባ ላይ የማቅ ቀኝ ክንድ አቡነ ቄርሎስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድምጽ እንደሆኑ የተደሰኮረ
ቢሆንም አቡነ ቄርሎስን የምናውቃቸው በዘመነ ሥራ አስኪያጅነታቸው ቤተ ክህነቱን ላስታ ላሊበላ ማድረጋቸውን እንጂ ዘረኝነትን ስለመዋጋታቸው
አይደለም። ሌሎቹን በስምና በቦታ መጥራት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጊዜና ቦታ የማይበቃን ስለሆነና ተግባራቱን በውል የሚያውቁ ስለሚያውቁት
ሾላ በድፍን ማለቱን መርጠነዋል። ሌሎቹ ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው!!
በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአቡነ እስጢፋኖስን የሙስና ስፋትና ጥልቀት፤ የሰው ሽያጭና ከስራ ማፈናቀል ተግባር በማስረጃ
አስደግፈን በሌላ ዓምድ እንመለስበታለን።
ስናጠቃልል ጳጳሳቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሽመድመድ ዋና ተጠያቂዎች ናቸው። የተቀበሉትን አደራ እስከሞት ድረስ የመወጣት
አለያም ካልቻሉ ደግሞ ወደበረሃቸው የመግባት ግዴታ እንዳለባቸው ስለማያውቁ አሁን ደርሶ በመቻቻል ፖለቲካዊ መድረክ ላይ ወኔ የታጠቁ
መስሎ መታየት አንድም እንደዚህ አልኩኝ ለማለት አለያም የማኅበረ ቅዱሳንን መነካት በተዘዋዋሪ መንገድ በችግሮች ሽፋን ለማካካስ
ከመፈለግ የመነጨ ከመሆን አይዘልም። ጥያቄአችንም የሚነሳው ከዚህ ነው። ይህ «መቻቻል» የሚለው መድረክ ሳይመጣ በፊት የት ነበራችሁ?
ነው ጥያቄያችን። በእነ አቡነ ገብርኤል ዓይነቶቹ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን መቼም ከችግር አትጸዳም።
እውነታውን ስንናገር ጳጳሳቱ ለቤተ ክርስቲያን ዘብ አልቆሙም ነው የምንለው!!!
Tuesday, October 15, 2013
«እስኪ በቁጣ ሳይኾን በጥሞና ነገሩን አስተውሉት!»
ZMTAOctober 10, 2013 at 6:15 AM
(ይህ ጽሁፍ በአባ ሰላማ መካነ ድር ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ያቀረበው ሲሆን ስለማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ ሁኔታ በአጭሩ ስለገለጸ ማቅረቡን ወደነዋል።)
የማኅበረ ቅዱሳንና ደጋፊዎቹ ትልቁ ችግር ይኽ ይመስለኛል፡፡
አንደኛ፣ የነገረ መለኮት ዕውቀት የላቸውም፡፡ ኹለተኛ፣ ራሳቸውን የቤተክርስቲያን ወታደሮች አድርገው ይስላሉ፡፡ እነርሱ የቤተ
ክርስቲያቱ ወታደሮች ናቸው የሚለውን ሐሳብ የተቀበለ ኹሉ ከእነርሱ ጋር የማይተባበር ኹሉ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው የሚለውን
አቀንቅኖት መቀበሉ አይቀርለትም፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ነው! የቤተ ክርስቲያኒቱ የመከላከያ ሠራዊት ነው!”
የሚለው ዐረፍተ ነገር በራሱ የጽንፈኝነት ወጥመድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ጠበቃ የምንፈልገው የተጠቂነት ፍርኀት ሲኖርብን ነውና፡፡
ምናልባት ይኽ ነገሮችን ጥቁር ወይም ነጭ ብቻ ናቸው ከሚለው ጽንፈኝነት ከሰፈነበት ባህላችን የተወለደ ይመስለኛል፡፡ አለማወቅ
ላይ ፍርኀት ሲጨመርበት ጽንፈኝነት መወለዱ አይቀርም፡፡ (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን “ምስክሮቼ ናችኹ፡፡” እንጂ
“ጠበቆቼ ናችኹ፡፡” አላለም፡፡)
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አላስተዋለው እንደኾነ እንጃ እንጂ የተናገረው ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን ጽንፈኝነት በደንብ ያሳያል፡፡ ማኅበሩንም በመንግሥት በደንብ ሊያስመታው ይችላል፡፡ እኛ የምንለውን የማይሉ፣ በእኛ ቅኝት ያላቀነቀኑ ኹሉ የቤተ ክርስቲያኒቷን ህልውና ለማጥፋት የሚታገሉ ናቸው ከማለት በላይ ጽንፈኝነት አለን? ዳንኤል ይኽን በማለቱ የማኅበሩን እውነተኛ ማንነት ዐደባባይ አውጥቶታል፡፡ ጽንፈኛ ደግሞ ከራሱ ውጪ ማንንም ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አላስተዋለው እንደኾነ እንጃ እንጂ የተናገረው ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን ጽንፈኝነት በደንብ ያሳያል፡፡ ማኅበሩንም በመንግሥት በደንብ ሊያስመታው ይችላል፡፡ እኛ የምንለውን የማይሉ፣ በእኛ ቅኝት ያላቀነቀኑ ኹሉ የቤተ ክርስቲያኒቷን ህልውና ለማጥፋት የሚታገሉ ናቸው ከማለት በላይ ጽንፈኝነት አለን? ዳንኤል ይኽን በማለቱ የማኅበሩን እውነተኛ ማንነት ዐደባባይ አውጥቶታል፡፡ ጽንፈኛ ደግሞ ከራሱ ውጪ ማንንም ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም፡፡
Friday, October 11, 2013
«የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች የሰሞኑ የአዞ እንባ የማኅበረ ቅዱሳንን ማንነት አይለውጠውም»
አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳንን ስናነሳ ለምን ተነክቶ በሚል ቁጣ ወባ እንደያዘው ሰው ይንዘፈዘፋሉ። በእርግጥ በማኅበሩ
የድንዛዜ መንፈስ የተወጉ ሰዎች እንደዚያ በመሆናቸው ከያዛቸው የወባ ዛር የሚያድን ምሕረት እንዲመጣላቸው እንመኝላቸዋለን እንጂ
አንፈርድባቸውም። ሌላው ቀርቶ ማኅበሩ ራሱ ከእውነት ጋር ታርቆና ራሱን በንስሐ ለውጦ ከስለላና ከከሳሽነት ማፊያዊ ሥራ ተላቆ ቤተ
ክርስቲያኒቱን ለራሱ አቋም ከመጠምዘዝ ቢታቀብ ሁላችንም አብረነው በቆምን ነበር። ከወንጌል እውነት ጋር እየተላተመ በተረት ዋሻ ሥር አናቱን ቀብሮ ከኔ ወዲያ
ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የለም ከሚለው ትምክህት ቢወጣ እንዴት ባማረበት ነበር። ዳሩ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ገና ከመሠረቱ የቆመበት
የህልውናው መንፈስ በደምና በማስመሰል በመሆኑ ከዚያ አቋሙ ፈቀቅ ይላል ተብሎ አይታሰብም። ጉዳዩ የታጠቀው የእልህና የበቀል መንፈስ
እስኪያጠፋው ድረስ አይለቀውምና ሄዶ ሄዶ መጨረሻው እስከዚያው ድረስ መሆኑን ደጋግመን ስንለው ቆይተናል። ያ ሰዓት የደረሰበት መሆኑን
ያሸተተው ይህ ማኅበር በቀንደኛ ሰዎቹ በኩል የአዞ እንባውን ማፍሰስ ጀምሯል።
ከማኅበሩ ቀንደኛና ተላላኪ ሰዎቹ መካከል ታደሰ ወርቁ፤
ዳንኤል ክብረት፤አባ ኃይለማርያም( የጵጵስና ተስፈኛው)፤ ሐራ ዘተዋሕዶና አንድ አድርገን ብሎጎች የመሳሰሉት ሁሉ እየተቀባበሉ የቃጠሎው
እሳት የደረሰባቸው ያህል የአድኑን ጩኸታቸውን ሲያሰሙ እያየን ነው። የሁሉም ጩኸት በአጭር ቃል ሲገለጽ በክርስትና አክራሪነት ቦታ
የለውም ወይም ለማኅበረ ቅዱሳን ይህንን የመሳሰለ ስም ሊጣበቅበት ተገቢ አይደለም የሚል ድምጸትን የያዘ ሆኖ አግኝተናል። ይሁን
እንጂ ሰዎቹ በገደል ማሚቱ ድምጻቸው እየተቀባበሉ እውነታውን ለማዳፈን ቢፈልጉም እውነቱ በማስረጃ ሊገለጥ ይገባዋልና በዚህ ዙሪያ
ጥቂት የምንለው አለን። ይከተሉን።
1/ ክርስትና፤
ክርስትና ክርስቶስ የሞተለት እምነት ስለሆነ ከሚሞቱለት በስተቀር ሌሎችን ሊገድሉለት፤ ሊደበድቡበትና ሊያሳድዱበት የተገባው
ስላይደለ በእርግጥም ክርስትና ወግ አጥባቂነት፤ አክራሪነትና፤ ጽንፈኝነትና አይመለከተውም።
Sunday, October 6, 2013
Saturday, October 5, 2013
Tuesday, October 1, 2013
“መስቀል የሚያቃጥል አይደለም”
ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ሲኖዶሱ ውሣኔ ይሰጣል - አቡነ እስጢፋኖስ
(ከደጀ ብርሃን ) ከሰማይ ወረደ ስለተባለው ሰሞነኛ ወሬ ብዙ ብዙ ተብሏል። እንደዚህ ዓይነት ደብተራዊ ቁመራ የተለመደ ሆኖ መታየቱ ለክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ፈላጊነት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ቀጥሏል። ከሰማይ ለወረደውና ወደሰማይ ለወጣው ለአብ አንድያ ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ በእምነት ልብን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ከሰማይ ወረደ ለተባለው ቁራጭ ብረት መንጋጋት አሳፋሪም አሳዛኝም ነው። በእርግጥ ይህ ትውልድ በክርስቶስ አምኖ ልቡን ከማሳረፍ ይልቅ ምልክት እንደሚሻ ዕለት ዕለት እናያለን። ለኃጢአት ሥርየት የተሰነጠቀ ድንጋይ ሲሾልክ፤ የማያየውን የተቀበረ መስቀል ፍለጋ ከወሎ ተራራ ሲንከራተት፤ ይቅርታን ለማግኘት ፍርፋሪና ዳቦ ለመብላት ሲሻማ ማየቱ በክርስቶስ ደም ሥርየትን፤ ንስሐ በመግባት ብቻ ይቅርታን በማግኘት ማረፍ እንዳልቻለ ያሳያል። እረፍት ፍለጋ ምልክት መከተል መፍትሄ አይደለም። በእውነታው ሰዎቹ እንደሚሉት እግዚአብሔር የተመሳቀለ እንጨትም፤ ብረትም ከሰማይ እርሻ ማሳ ውስጥ በመወርወር ከሰው ልጆች ጋር ይጫወታል ማለት ባህርይውን አለማወቅ ነው። ድንጋይ በመሹለክም፤ ፍርፋሪ በመብላትም፣ ተራራ በመውጣትም፤ ደረትን በመድቃትም ሆነ ጸጉርን በመንጨትም ኃጢአት አይደመሰስም። ሥርየትም አይገኝም። «በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት» እንደሆነ ወንጌል ቢናገርም (ኤፌ 1፤7) ይህንን ወደጎን ገፍቶ በሰንጥቅ ድንጋይ ለመሹለክ መሽቀዳደም ምልክት ፈላጊዎችን ከማብዛቱም በላይ ወንጌል ከስሙና ከንባቡ በስተቀር ለመታወቅ ብዙ እንደሚቀረው ነው። ከዚህ ዓይነቱ እርባና የለሽ ሰሞነኛ ወሬዎች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ እርሻ ማሳ ውስጥ ወድቆ ተገኘ ስለተባለው መስቀል ብዙ መወራቱ እንዳለ ሆኖ አንስተው፤ ወደመቅደስ አስገብተውታል የሚባሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ስለእውነታው በሲኖዶስ ውሳኔ ይሰጥበታል የሚል ዜና ስናነብ እጅጉን ገረመን። ምክንያቱም የነደብተራ ገለፈት ፈጠራ እንደቁም ነገር ሊቆጠር አይገባውም። እንዲያውም እንደዚህ ዓይነቶቹን ጸረ ወንጌል አጭበርባሪዎች ማስወገድ ይገባ ነበር። ለማንኛውም የአቡኑን የአዲስ አድማስ ዘገባ እንዲያነቡት እነሆ ብለናል።
በአቃቂ ቃሊቲ ገላን ጉራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ እስኪያስተላልፍ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ የአዲስ አበባና የጅማ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አሣሠቡ፡፡ “መስቀል ከሠማይ ወርዷል አልወረደም? ትክክለኛ ነው አይደለም?” የሚለውን ለመመለስ የግድ ቅዱስ ሲኖዶሡ ጉዳዩን መርምሮ ውሣኔ ሊያስተላልፍበት ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ይህን ለማድረግም ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቋሚ አባላት እንዳሣወቁ ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ እንደተባለው ከሠማይ የወረደ አለመሆኑ ከተረጋገጠም የቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች ይጠየቁበታል ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡
መስቀሉ ከሠማይ ወረደ በተባለ በ4ኛው ቀን ነሐሴ 27 ቀን 2005 ከሠአት በኋላ ወደ ስፍራው በማቅናት ተገቢውን የፀሎት ስርአት ከካህናቱና ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋር ካደረሡ በኋላ መስቀሉን ከወደቀበት መሬት አንስተው ወደ ቤተመቅደሡ እንዲገባ ማድረጋቸውን የገለፁት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ መስቀሉ ከሠማይ ስለመውረዱ በአይናችን አይተናል ካሉት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደማንኛውም ሠው መስማታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት መሬት ያነሱት ብፁዕነታቸው፤ “መስቀሉ ያቃጥላል፤ ብርሃናማ ነፀብራቅ አለው” የሚባለውን አለማስተዋላቸውን ጠቁመው፤ “መስቀል የሚያቃጥል ሣይሆን የድህነት ሃይል ነው ያለው፣ የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ ከመሬት ላይ ማንሣት ባልተቻለ ነበር” ብለዋል፡፡ ወረደ የተባለውን መስቀል ለመመልከት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ምዕመናን ለምን እንዳይመለከቱት ተከለከለ የሚል ጥያቄ ያነሣንላቸው ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶሡ ተጣርቶ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያጤነው በማሠብ ነው” ብለዋል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)
(ከደጀ ብርሃን ) ከሰማይ ወረደ ስለተባለው ሰሞነኛ ወሬ ብዙ ብዙ ተብሏል። እንደዚህ ዓይነት ደብተራዊ ቁመራ የተለመደ ሆኖ መታየቱ ለክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ፈላጊነት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ቀጥሏል። ከሰማይ ለወረደውና ወደሰማይ ለወጣው ለአብ አንድያ ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ በእምነት ልብን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ከሰማይ ወረደ ለተባለው ቁራጭ ብረት መንጋጋት አሳፋሪም አሳዛኝም ነው። በእርግጥ ይህ ትውልድ በክርስቶስ አምኖ ልቡን ከማሳረፍ ይልቅ ምልክት እንደሚሻ ዕለት ዕለት እናያለን። ለኃጢአት ሥርየት የተሰነጠቀ ድንጋይ ሲሾልክ፤ የማያየውን የተቀበረ መስቀል ፍለጋ ከወሎ ተራራ ሲንከራተት፤ ይቅርታን ለማግኘት ፍርፋሪና ዳቦ ለመብላት ሲሻማ ማየቱ በክርስቶስ ደም ሥርየትን፤ ንስሐ በመግባት ብቻ ይቅርታን በማግኘት ማረፍ እንዳልቻለ ያሳያል። እረፍት ፍለጋ ምልክት መከተል መፍትሄ አይደለም። በእውነታው ሰዎቹ እንደሚሉት እግዚአብሔር የተመሳቀለ እንጨትም፤ ብረትም ከሰማይ እርሻ ማሳ ውስጥ በመወርወር ከሰው ልጆች ጋር ይጫወታል ማለት ባህርይውን አለማወቅ ነው። ድንጋይ በመሹለክም፤ ፍርፋሪ በመብላትም፣ ተራራ በመውጣትም፤ ደረትን በመድቃትም ሆነ ጸጉርን በመንጨትም ኃጢአት አይደመሰስም። ሥርየትም አይገኝም። «በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት» እንደሆነ ወንጌል ቢናገርም (ኤፌ 1፤7) ይህንን ወደጎን ገፍቶ በሰንጥቅ ድንጋይ ለመሹለክ መሽቀዳደም ምልክት ፈላጊዎችን ከማብዛቱም በላይ ወንጌል ከስሙና ከንባቡ በስተቀር ለመታወቅ ብዙ እንደሚቀረው ነው። ከዚህ ዓይነቱ እርባና የለሽ ሰሞነኛ ወሬዎች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ እርሻ ማሳ ውስጥ ወድቆ ተገኘ ስለተባለው መስቀል ብዙ መወራቱ እንዳለ ሆኖ አንስተው፤ ወደመቅደስ አስገብተውታል የሚባሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ስለእውነታው በሲኖዶስ ውሳኔ ይሰጥበታል የሚል ዜና ስናነብ እጅጉን ገረመን። ምክንያቱም የነደብተራ ገለፈት ፈጠራ እንደቁም ነገር ሊቆጠር አይገባውም። እንዲያውም እንደዚህ ዓይነቶቹን ጸረ ወንጌል አጭበርባሪዎች ማስወገድ ይገባ ነበር። ለማንኛውም የአቡኑን የአዲስ አድማስ ዘገባ እንዲያነቡት እነሆ ብለናል።
መስቀሉ ከሠማይ ወረደ በተባለ በ4ኛው ቀን ነሐሴ 27 ቀን 2005 ከሠአት በኋላ ወደ ስፍራው በማቅናት ተገቢውን የፀሎት ስርአት ከካህናቱና ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋር ካደረሡ በኋላ መስቀሉን ከወደቀበት መሬት አንስተው ወደ ቤተመቅደሡ እንዲገባ ማድረጋቸውን የገለፁት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ መስቀሉ ከሠማይ ስለመውረዱ በአይናችን አይተናል ካሉት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደማንኛውም ሠው መስማታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት መሬት ያነሱት ብፁዕነታቸው፤ “መስቀሉ ያቃጥላል፤ ብርሃናማ ነፀብራቅ አለው” የሚባለውን አለማስተዋላቸውን ጠቁመው፤ “መስቀል የሚያቃጥል ሣይሆን የድህነት ሃይል ነው ያለው፣ የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ ከመሬት ላይ ማንሣት ባልተቻለ ነበር” ብለዋል፡፡ ወረደ የተባለውን መስቀል ለመመልከት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ምዕመናን ለምን እንዳይመለከቱት ተከለከለ የሚል ጥያቄ ያነሣንላቸው ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶሡ ተጣርቶ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያጤነው በማሠብ ነው” ብለዋል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)
Subscribe to:
Posts (Atom)