Tuesday, May 14, 2013

ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል … !!


ጸሐፊው በፍቅር ለይኩን (ምንጭ የረቡዕ ሪፖርተር ጋዜጣ)፤ለደጀ ብርሃን በተለይ የተላከ
በቅርቡ ሙስጠፋ አል ላባድ የተባለ ሊባኖሳዊ ፖለቲከኛና ጸሐፊ Egypt is Battling Ethiopia over the Nile Water በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ አሳትሞ አውጥቷል፡፡ ይህን የአል ላባድን መጽሐፍ ‹‹አስ ሳፊር›› የተባለ የሊባኖስ ዕለታዊውና ተነባቢ የዐረብኛ ጋዜጣ የመጽሐፉን አጭር ዳሰሳ በፊት ለፊት ገጹ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ራኒ ጌሃ የተባለ ጋዜጠኛም የሊባኖሱን ‹‹አስ ሳፊር›› ጋዜጣ ዳሰሳ Egypt and Ethiopia Heading Toward a War Over Water በሚል ርዕስ በእንግሊዘኛ አሳትሞ ወሬውን ለዓለም መገናኛ ብዙኃን አድርሶታል፡፡
   ሊባኖሳዊው ጸሐፊ በመጽሐፉ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ጥንታዊና ሺሕ ዘመናትን ያስቆጠር፣ ታሪካዊና ሕጋዊ የሆነ ልዑላዊ መብቷን በመጋፋት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ግዙፍ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እየገነባች ነው በማለት የተለመደውን ውግዘትና ማስፈራራት የተንጸባረቀበት የሚመስል እሳቤውን በመጽሐፉ በሰፊው አካቶታል፡፡
    ጸሐፊው ይህ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችው ግዙፍ ግድብ ‹‹በግብፃውያን ጉሮሮ ላይ የመቆም ያህል ነው፡፡›› ሲል በቁጣና በእልኽ ስሜት ውስጥ የገባ በሚመስል ሁናቴ ነው የገለጸው፡፡ ይኽም ይላል ሙስጠፋ አል ላባድ 97.5 በመቶ በረሃማ ለሆነችው ግብፅ፣ ዓለምን እጹብ ድንቅ ላሰኘው ለግዙፍ ሥልጣኔዋ፣ ወርቃማ ለሆነው ታሪኳ፣ ክብርና ኩራቷ እንዲሁም 90 ሚሊዮን የሚሆነው የግብፅ ሕዝብ ሁለተናዊ ሕይወት ቁልፍ በሆነው በዚህ ታሪካዊ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የጀመረችው የኃይል ግንባታ ለግብፃውያን አስጊ መሆኑን ነው የገለጸው ላባድ በመጽሐፉ ውስጥ፡፡
  ይኸው ጸሐፊ ግብፅ፣ ሱዳንና ብሪታኒያ የተዋዋሉትን የ1950 ስምምነት በማንሣት ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት ማንም ሊጋፋው የማይችል ታሪካዊና ሕጋዊ መብቷን መሆኑን አስረግጦ ሊያስረዳንም ሞክሯል፡፡
   ላባድ በተጨማሪም የታችኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት የሆኑት ግብፅና ሱዳን በተናጠል ከእንግሊዝ ጋር ያደረጉትን ስምምነት ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ይደግፋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በላይኛዎቹ ተፋሰስ አገራት በኢትዮጵያ አስተባባሪነት በናይል ወንዝ ላይ ፍትሐዊ የሆነ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር ያደረጉትን የኢንተቤውን ስምምነት በማንሣት ኢትዮጵያ በላይኛዎቹ ተፋሰስ አገራት መካከል ያደረገችውን ስምምነት በተመለከተ ሲናገር ‹‹ኢትዮጵያ ግብፅን በጉልበት ለማስፈረም አትችልም፤›› ሲል ይደመድማል፡፡
  ይህ ስምምነትና ይላል ላባድ ግብፅ እስከሌለችበትና እስካልተስማማች ድረስ ዋጋ የሌለው ወረቀት ላይ ብቻ ፉከራ ነው የሚል አንድምታ የተንጸበራቀበት አቋሙን ለመግለፅ ሞክሯል በዚሁ መጽሐፉ፡፡
    ሙስጠፋ አል ላባድ ግብፅ ወይም ግብፃውያን ዘወትር የማያንቀላፉ፣ ንቁ የሆነና በተጠንቀቅ የቆሙ ሁለት ዓይኖች አሏት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትልቁና ዋንኛው ዓይኗ ሁሌም በዓባይና በዓባይ ዙሪ ላይ እንደተተከለ ነው፡፡ ሌላኛው ዓይኗ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅና በባሕረ ሰላጤው እንደሚያማትር ጽንፈኝነት የተጫነው በሚመስል አገላለጽ ሊያስረዳን ይዳደዋል፡፡
   እናም ሙስጠፋ ግብፅና ግብፃውያን በዓባይ ዙሪያ ላይ ምን ያህል ስሱና ቀልድ የማያውቁ መሆናቸውንም ሊነግረን ይሞክራል፡፡ ይኸው ሊባኖሳዊ ጸሐፊ ኢትዮጵያ ይህን ያህል ግዙፍ የሆነና በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይል ለመገንባት ያነሳሳት ምክንያቶች በማለት ስድስት ዐበይት ምክንያቶቹን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይተነትናል፡፡ ወደእነዛ የሙስጠፋ አል ላባድ ትንታኔዎች ለመግባት አልሻም፡፡
        ግን ሊባኖሳዊው ጸሐፊ ሙስጠፋ አል ላባድ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን ግዙፍ ግንባታና ይኽን ተከትሎም ከናይል ተፋሰስ አገራት በዋነኝነት ደግሞ ከግብፅ ጋር የገባችበትን ፍጥጫና የጀመረችውን ውይይት/ድርድር ፈር ለማስያዝ ግብፅ ምን ዓይነት ውሳኔ ልትወስድ እንደምትችል የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው ይለናል፡፡
     ነገር ግን ይላል ሙስጠፋ ማብራሪያውን ሲቀጥል ግብፅ ለወደፊቱ የምትወስደውን እርምጃ ምንም ይሁን ምን የምናየው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን ግብፅ ይህን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን ግዙፋ ግንባታ ለማስቆም መውሰድ ካለባት እርምጃ መከካል ብሎ በግንባር ቀደምትነት ከጠቀሳቸው ምክንያቶቹ መካከል ሲጠቅስም፡-
   ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ‹‹የማይለወጥና የማይሻር›› ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ሉዓላዊ የሆነ ጥቅሟን ለማስከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሺሕ ዘመናት እናት በሆነችው በግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በኩል ከፍተኛ የሆነ ጫና ማሳደር የምትችልበትን አማራጭ ማየት ይገባታል በማለት አበክሮ ይገልጻል፡፡
      ሙስጠፋ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን ልማት በግብፃውያን ሕልውና ላይ የመፍረድ ያህል ነው ብሎ ለሚሟገትላት ግብፅ ለዚህ የሞት ሽረት ጥያቄ ያለ ምንም ልዩነት ሁሉም ግብፃዊ ሊነሣ እንደሚገባው ይወተውታል፡፡ እናም በዚህ የሞት ሽረት ዲፕሎማሲያዊ ትግል ግብፅና ግብፃውያን ያላቸው ተስፋ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኩል ብቻ እንደሆነ ለግብፅና ለግብፃውያኑ አበክሮና አስረግጦ ገልጧል፡፡

በእርግጥ ግብፃውያን በሃይማኖት ወዳጃቸው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኩል የተቻላቸውን ያህል ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ እርግጥ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ባለፈው ወርኻ ክረምት የግብፅ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባልና አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳንት የሆኑት መሀመድ ሙርሲ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ መጥተው በነበሩበት ጊዜ ከነፍሰ ሔር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን በይፋ ከመገናኛ ብዙኃን አይተናል፣ አድምጠናል፡፡
   ይህ የመሀመድ ሙርሲ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ጉብኝትና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ እንደ አንዳንድ ተንታኞች ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ሊኖረው እንደሚችል ተገልጾ ነበር በወቅቱ፡፡
   የመጀመሪያው በሁለቱ አገራት ማለትም በግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኩል ለሺሕ ዘመናት ለዘለቀው ታሪካዊ ግንኙነት ክብርና እውቅና መስጠት ሲሆን፡፡
     በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነ የሁለቱ አገራትና አብያተ ክርስቲያናትን ግንኙነት አስታኮ በጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ዘመን በኢትዮጵያ በኩል በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው በግብጽ ኮፕቲክ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ላይ ይደረስ ለነበረው በደልና ግፍ እንደማስፈራሪያ ሆኖ በቆየውና ለግብፃውያን ሕልውና መሠረት በሆነው በዓባይ ወንዝ ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ ነው፡፡
     ምናልባትም ሌላኛው ምክንያት በዘመነ ሆስኒ ሙባረክ አንፃራዊ በሆነ መልኩ የተረጋጋ ሕይወት አላቸው የሚሉት ግብፃውያኑ ክርስቲያኖች የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ባልተጠበቀ ሁናቴ ወደ ግብፅ ፖለቲካ ማማ ላይ መውጣቱ በግብፃውያኑ ክርስቲያኖች ላይ ምንም ዓይነት የተለየ ጫና፣ ግፍና መከራ እንደማይደርስባቸው ዋስትና ወይም ማረጋገጫ የመስጠት ዓይነት እንደሆነ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡
      ይሁን እንጂ የመሀመድ ሙርሲ ጉብኝትና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር ያደረጉት ውይይት ዐቢይ አጀንዳ ግን የዓባይ ውኃ ጉዳይ መሆኑን ለመናገር ነቢይ ወይም ወልይ መሆን የሚያስፈልገው ነገር አይመስለኝም፡፡ እናም መሀመድ ሙርሲ ወደ ስልጣን በመጡ ማግሥት በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ሰበብ ይህን የግብፅንና የግብፃውያንን ቁልፍ አጀንዳ፣ የዓባይን ጉዳይ ከግብፅ ጋር ቆየና ታሪካዊ ግንኙነት ባላት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠረጴዛ ላይ ማስቀመጣቸው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የአደራ መልእክትና ትልቅ የቤት ሥራ መስጠታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
   ይህን ከላይ በአጭሩ ለመግለጽ በሞከርኩት የሙስጠፋ አል ላባድ መጽሐፍ ውስጥ ግብፅና ግብፃውያን በዓባይ ውኃ ላይ ለመደራደር ያላቸው ተስፋ ‹‹በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲየን በኩል ብቻ ነው፡፡›› የሚል አንድምታ ያለው ምክሩና ከሰሞኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባትና መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት ቃለ ቡራኬ ስለ ዓባይ ውኃ ጉዳይ ያነሡት ቁም ነገር ለዚህ አጭር መጣጥፍ መነሻ ሆነኝ፡፡
      በመላው በክርስትና ሃይማኖት አማኞች ዘንድ ባለፈው ሳምንት የተከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል አስመልክተው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚገኙ መንፈሳዊ ልጆቻቸው ቡራኬና ቃለ በረከት አስተላልፈው ነበር፡፡
      ቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት በዚህ በቃለ በረከታቸውና በቡራኬያቸውም፡- ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የዘመናት እንቆቅልሽ ሆኖ በቆየ በአንድ ወቅታዊ፣ አንገብጋቢና እጅግ ወሳኝ በሆነ አገራዊ አጀንዳ ላይ ፍጹም አዎንታዊነት፣ የድልና በእግዚአብሔር አምላካችን ኃይል ሁሉ ይቻለናል የሚል እምነትና ጽናት በተንጸባረቀበት በሚመስል፣ በትንሣኤው በዓል ‹‹የእንኳን አደረሳችሁ!›› የመልካም ምኞት መግለጫቸው ለኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ዐቢይ የሆነ መልእክትን አስተላልፈዋል፡፡
    ይኸውም ኢትዮጵያ አገራችን በእግዚአብሔር ከአምላኳ በተቸራት በጥንታዊውና በታሪካዊ ወንዟ በዓባይ ላይ የጀመረችው ታላቁ የሕዳሴው ግድብ ያለ ምንም ጥርጥር በድል ተጠናቆ፣ ለፍሬ በቅቶ፣ ‹‹ከዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው›› ተረት ወጥተን ከዓባይ በረከት ጠጥተን የምንረካበት መልካምና ብሩኅ ዘመንን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዓይናቸው እንደሚያዩት ቅዱስነታቸው ያላቸውን ጽኑና የማያወላውል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
     ቅዱስነታቸው በዚህ መልእክታቸውም ለሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለበትና በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ በአገር ፍቅር ስሜት፣ በአንድነትና ጠንካራ የሥራ መንፈስ የበኩሉን እገዛና ርብርብም እንዲያደረግም ነው ያሳሰቡት፡፡
      የቅዱስ ፓትርያርኩ ይሄ መልእክታቸው በአንዳንዶች ዘንድ እምብዛም የተወደደላቸው አይመስልም፡፡ እንደውም እነዚሁ ይህ የፓትርያርኩ መልእክት ያላስደሰታቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውን ወገኖቻችን ይህች በመንግሥት ተቀንብባ ለፓትርያርኩ አንደበት ለሕዝብ ይደርስ ዘንድ የተላላፈች ‹‹ኢህአዴጋዊ›› መልእክት ናት በማለት የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

እርሳቸው የሃይማኖት አባት ናቸው እንጂ የመንግሥት አፈ ቀላጤ አይደሉም፡፡ እናም በዚህ በትንሣኤው በዓል ላይ ማስተላለፍ የሚገባቸው መልእክት እኛ የሰው ልጆች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሥኤ ስለተጎናጸፍነው ነጻነት፣ ድል፣ በረከትና የዘላለም ሕይወት እንጂ ስለ መንግሥት የፖለቲካ አጀንዳ መሆን አልነበረበትም በማለት ቅሬታቸውን በጓዳም በይፋም ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
      በበኩሌ ግን ከትንሣኤው ኃይልና ተስፋ፣ መንፈሳዊነት ተቀዳሚና ዋና አጀንዳነት ባሻገር ይህ በዓባይ ወንዝ ላይ የተጀመረውን የታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በማስመልከት ቅዱስ ፓትርያርኩ 40 ሚሊዮን ለሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ምእመኖቻቸው ያስተላለፉት መልእክት የመንግሥት ፖለቲካዊ አጀንዳ ነው የሚያስብለው ምክንያት ብዙም አይዋጥልኝም፡፡
        አገራችን ከድህነት፣ ከልመና፣ ከራብ፣ ከስደት፣ ከተመጽዋችነት ወዘተ የምትወጣበትና እኛም ሕዝቦቿም ለጥ ብለን ከተኛንበት የስንፍና ፍራሽ ላይ አቅንቶ የሚቀሰቅሰን ሁለተናዊ የሆነ የትንሣኤው አዋጅ መለከት በብርቱ እንደሚያስፈልገን ጥያቄ የለውም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ዕለት ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ሁለተናዊ የሆነ ትንሣኤ እንደሚያሰፈልገው ማወጅ የአንድ መንፈሳዊ አባት ተግባርና ኃላፊነት እንደሆነ ነው አጥብቄ የማምነው፡፡
     ብሔራዊ ጥቅማችን፣ የአገራችንን ነፃነት፣ ልዑላዊነትና አንድነት በተመለከተ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ትላንትናው ሁሉ በቃልም በተግባርም የነበራትን ወሳኝ ሚናና ተሣትፎ በተመለከተ ዛሬም ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ማሰማቷ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ትላንትና ያደረገችው፣ ዛሬም ልታደርገው የሚገባና ወደፊትም አጽንታ ልትቀጥልበት የሚገባው መልካም የሆነ ክርስቲያናዊ ባህል ነው የሚመስለኝ፡፡
      ስለሆነም የዓባይ ጉዳይ በማንም ይነሳ በማንም አንድ የማምንበት እውነት ግን አለ፡፡ ይኸውም የዓባይ ጉዳይ ብሔራዊ አጀንዳችን፣ የሁላችንም ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ በአንድ የታሪክ ወቅት ታይተው የሚያልፉ የአንድ መንግሥት ወይም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ዓባይና የዓባይ ጉዳይ ዘርን፣ ጎሳን፣ ሃይማኖትን ሳይለይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ አንገብጋቢ ጉዳይ እንጂ፡፡

በዓባይ ጉዳይ ላይ ንጉሡ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ፣ በርካታ ኢትዮጵውያን ምሁራንና ዲፕሎማቶች ያደረጉት በርካታ የሆኑ ጥረቶችና ልፋቶች ነበሩ፡፡ የደርግ መንግሥት እንዲሁ የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፣ ለፍቷል፡፡ ዛሬ እነዚህ መንግሥታት አልፈው ታሪክ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያችን ግን ዛሬም አለች፣ ወደፊትም ትኖራለች፡፡ ዓባይ ወንዛችንም ትላንትና ነበር፣ ዛሬም አለ፣ ወደፊትም ይኖራል፡፡
      የኢህአዴግ መንግሥትም በለስ ቀንቶት ይህ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ሁሉ የዘመናት እንቆቅልሽ የሆነውን ዓባይን ጉዳይ ከወረቀት አጀንዳነት ወደ መሬት በማውረድ በታሪካችን በአፍሪካ ትልቅ የሆነውን ሕዳሴውን ግድብ እውን ለማድረግ የበኩሉን ተግባራዊ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ኢህአዴግም እንደ ትላንትናዎቹ የኃ/ሥላሴና የደርግ መንግሥታት ያልፋል፣ አንድ ቀን እንደ ሸማም ተጠቅልሎ በታሪክ ማኅፀን ውስጥ በተራው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን ግን ዛሬም፣ ሁሌም ይኖራሉ!!
       ከጥንት ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ነበረች፣ ዓባይም ነበር፡፡ ኢህአዴግ ገና ሳይታሰብ፣ ሳይጸነስና ሳይኖርም በፊት ዓባይ ይፈስ ነበር፣ ዛሬም በፊታችን እየፈሰሰ አለ፣ ወደፊትም ሲፈስ ይኖራል፡፡ መንግሥት ዓባይን በየትኛውም መልኩ ቢሆን የራሱን ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈጸሚያ፣ ዕድሜ ማራዘሚያና ጊዜያዊ የፖለቲካዊ ትርፍ ማጋበሻ አደረገውም አላደረገውም ዓባይን በማልማት ረገድ ግን ከአሁን ወዲያ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደኋላ የምንመለስበት ጉዳይ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ለምን ቢባል የዓባይ ጉዳይ በእኛ ዘመን የህልውናችን፣ የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ ሆኖ ከፊታችን ተድቅኗልና፡፡

ስለሆነም በዓባይ ወንዝ ላይ የሚካሄድ ማንኛውንም ዓይነት ልማትን በተመለከተ የሃይማኖት አባቶቻችንም ሆኑ ባለ ሥልጣኖቻችን ከሚነግሩን በላይ በተግባር አንደበት፣ በፍቅርና በአንድነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንወጣው የሚገባን ታላቅ የሆነ የቤት ሥራ ገና ከፊታችን እንዳለን ነው የሚሰማኝ፡፡
 በዚህ ረገድ ደግሞ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ታላቅ የሆነ ታሪካዊ ሚና የነበራትና ያላት ጥንታዊቷና ሐዋርያዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ መንፈሳዊ አባቶችቻንና መሪዎቻችን እንዲሁም እኛ ክርስቲያኖች ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ ምንም ልዩነት በማስተባበር ገና በተግባር ልንወጣው የሚገባ ትልቅ የቤት ሥራ በፊታቸው ተደቅኖ እንዳለ ይሰማኛል፡፡
ይህ አጭር መጣጥፍም ቤተ ክርስቲያናችን፣ መንፈሳዊ አባቶቻችንና መሪዎቻችን እንዲሁም እኛንም ጨምሮ ዓባይ ወንዛችንን በተመለከተ ከቃል ባለፈ በተግባር ልንወጣው የሚገባ ትልቅ የቤት ሥራ ከፊታችን ተዘርግቶ እንዳለ በቅንነት መንፈስ ለማሳሰብ ነው፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያናችን በቀደመ ታሪክ ዘመኗ የዓባይ ወንዝን በተመለከተ የነበራትን ወሳኝ ሚና ከታሪክ ማሕደር በመፈተሸና አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ የበኩሌንና የተሰማኝና ጥቂት ነገር ለማለት ነው ብዕሬን ያነሳሁት፡፡
      ግብፃውያኑ በመንፈሳዊነት ስም ባቀነባበሩት፣ የፈጠራ ተረት ተረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለ1600 ዘመናት በግብፃውያኑ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የባርነት ቀንበር ውስጥ ወድቃ ስትማቅቅ እንደነበር የታሪክ መዛግብቶቻችን ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ሐቅም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አጥኚዎችና የሥነ መለኮት ምሁራኖቿም ሳይቀሩ የሚመስክሩት ነው፡፡  
     እነዚህ በአፍሪካና በመላው ዓለም ባለፉት ሺሕ ዓመታቶች ባስመዘገቡት ድንቅና ኃያል ሥልጣኔያቸው የተነሣ በዓለም መድረክ እንደ ብርቅ የሚታዩ ጥንታዊ የሆኑ ሁለቱ አገራት፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ለዘመናት የሰው ዘር ታሪክ፣ ቅርስና ታላቅ ሥልጣኔ አሻራ ማሳያ የሆኑ ታላላቅ አገራት መሆናቸው በሰፊው ሲጠቀስ ቆይቷል፣ አሁንም ይጠቀሳሉ፡፡
        ለእነዚህ አገራት ታሪክ፣ ታላቅ ሥልጣኔና ዕድገት መነሻና እምብርት ደግሞ የዓባይ ወንዝ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍም፡- ‹‹ስለ ዔደን ገነት ሲያትት የዔደን ገነትን ከከበቡትና ከሚያጠጡት ወንዞች መካከል አንዱ የዓባይ ወይም የግዮን ወንዝ መሆኑን በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ የዘፍጥረት ጸሐፊ የሆነው እስራኤላዊው ነቢይ ሙሴ ይኽው የዓባይ ወንዝም ኢትዮጵያን መሬት ሁሉ እንደሚከብ ይናገራል፡፡››
        በክርስቲያኖች ቅዱስ መጽሐፍ ዘንድም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ቅዱሳን መጻሕፍት የከበረ ስምና ዝና ያላት ኢትዮጵያ ገና ከፍጥረት ማግሥት ጀምሮ የራሷን መንግስት አቋቁማ የምትኖር፣ ኃያላ፣ ባለ ታሪክና ልዑላዊት አገር እንደነበረች ይመሰክራሉ፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለማችን ታላቅ የሆኑ የአይሁድ፣ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች ማእከል እንደሆነችም ይታወቃል፡፡
         ኢትዮጵያ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የሥልጣኔ ማእከል መሆኗ ብቻ ሣይሆን ከኢትዮጵያ ምድር ፈልቆ ሱዳንና ግብፅን አቋርጦ ወደ ሜድትራኒያን ባሕር የሚገባው የዓባይ ወንዝ አያሌ ዘመናትን ላስቆጠረው ለግብፃውያኑ አፍሪካዊው ሥልጣኔ፣ መነሻና መሠረት እንደነበር የታሪክና የአንትሮፖሎጂ ምሁራን አስረግጠው ጽፈዋል፡፡
        ከእነዚህም ምሁራን መካከል አፍሪካውያኑ ስመ ጥር፣ እውቅ ምሁራንና የታሪክ ተመራማሪዎች የሆኑት ሼክ አንታዲዮፕና ኢቫን ኢቫን ሰርቲማ በጥናታቸው፡- ‹‹ግብፅ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የመንፈስ ልጅ›› እንደሆነች ባሳተሙት በዳጎስ ጥናታቸው በግልጽ ጽፈዋል፡፡
         ኢትዮጵያንና ግብፅን ከሚያስተሳስሩ ዋና ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ታሪካዊው የዓባይ ወንዝ ነው፡፡ ዛሬ ዓለም ጉድ የሚሰኝበት የግብፃውያኑ ታሪክ፣ ቅርስና ታላቅ ሥልጣኔ መሠረቱ የዓባይ ወንዝ ነው፡፡ እነዛ ዓለምን ጉድ ያሰኙና በየቀኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ቱሪስቶችን ቀልብና ዓይን የሚቆጣጠሩ የግብፅ ፒራሚዶች የተገነቡት የዓባይ ወንዝ ዳርቻን ተከትለው ነው፡፡
        ግብፅና ግብፃውያን ከዓባይ ውጪ የሚኖሩት ሕይወት፣ የሚተርኩት ታሪክ፣ ዓለም ሁሉ የሚያየው፣ የሚያደነቅውና ጉድ ጉድ የሚሉለት አንዳንችም ሥልጣኔም ሆነ ቅርስ የላቸውም፡፡ ዓባይ ለግብፅና ለግብፃውያን ሁሉን በሁሉ ነው ብንል ብዙም ከእውነታው የራቅን አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በተለምዶ ‹‹ታሪክ አባት›› ተብሎ የሚጠራው ጥንታዊው ታሪክ ጸሐፊ ግሪካዊው ሄሮዱተስ Egypt is the gift of Nile ሲል በአጭር ቃል ግብፅን የገለጻት፡፡
          እናም ኢትዮጵያና ግብፅ ለዘመናት ተሳሰረው የቆዩበት እትብት የዓባይ ወንዝ መሆኑን ማንኛችንም ብንሆን እንስተዋለን ብዬ አልገምትም፡፡ ይህ በዓባይ ወንዝ አማካኝነት የተፈጠው የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ትስስር የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ መግባት በኋላ ደግሞ ሌላ የሃይማኖትና የታሪክ የቃል ኪዳን ውልን ፈጠረ፡፡ ከ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በኋላ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ልጅ ናት ተብላ የተጠቀሰችው ግብፅ ዳግም ለኢትዮጵያውያን የመንፈስ እናት ሆና በታሪክ መድረክ ብቅ አለች፡፡
       ይህ ግብፃውያን በሃይማኖት ስም ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰሩበት የእናትነትና የልጅነት መንፈስ የፈጠረውን ወይም ያመጣውን መንፈሳዊ ፋይዳና ጥቅም፣ እንዲሁም ያሰከተለውን መንፈሳዊና አሥተዳደራዊ ቀውስና ውጥንቅጥ ለመተንተን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ እዚህ ጋር ሳይነሳ ሊታለፍ የማይገባው ነጥብ ቢኖር፡- ግብፃውያን በሃይማኖት ስም በኢትዮጵያ ላይ የጫኑት ከባድ ቀንበርና ብርቱ ክንድ ከጊዜ በኋላ መልኩን ቀይሮ ወደ ፍፁም አምባገናነዊነትና ቅኝ ግዛትነት ተቀይሮ እንደነበር ሁላችንም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡
     በወርቅ፣ በእንቁ፣ በከበሩ ስጦታዎች ጋጋታ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩት በጣት ከሚቆጠሩት ግብፃውያን ጳጳሳት በስተቀር የሚበዙት ከስምና ከምልክትነት ባለፈ (Puppet Fathers) ይሄ ነው የሚባል ሥራ እንዳልነበራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አጥኚዎች በግልጽ ይናገራሉ፡፡
        በተለይም ደግሞ ግብፅ ሙሉ በሙሉ በሙስሊም ወራሪዎች እጅ ከወደቀችበት ዘመን ጀምሮ ግብፃውያኑ ገዢዎች በጳጳሳቱ በኩል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የሆነ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም በተቀነባበረና በረቀቀ ሴራ እንዲያም ሲል በኋላኛው ዘመን በጦር ኃይል አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ወደኋላ እንዳላሉ የታሪክ ድርሳናቶቻችን በሚገባ ያስረዳሉ፡፡
          ግብፃውያኑ ኢትዮጵያ አንድ ቀን የዓባይን ወንዝ ልትገድብ ትችላለች የሚለው ስጋታቸው ቀን ከሌሊት እረፍት ስለማይሰጣቸው ዓባይን በዓይነ ቁራኛ ነበር የሚከታተሉት፡፡ እናም ኢትዮጵውያኑ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ይቃኙ ዘንድ ሁለት ሼኼዎችን ጳጳስ አድርገው በተለያዩት ጊዜያት በቃፊርነት ወደ ኢትዮጵያ ምድር ልከው እንደነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ይህን የግብፃውያኑን አሣፋሪ ቅሌት በታሪክ ድርሳናት ውስጥ አስፍረውታል፡፡

በኢትዮጵያ በኩልም የዓባይ ወንዝ ለአናሳዎቹ ግብፃውያን ክርስቲያኖች የመደረደሪያና ለግብፃውያኑ ገዢዎች ማስፈራሪያ መሣሪያም በመሆን ያገለገለበት በርካታ ጊዜያቶች ነበሩ፤ በተለይም ደግሞ በዛግዌ ስርወ መንግሥትና በመካከለኛው ዘመን ታሪካችን፡፡
      በእነዚህ ሁለት ጥንታዊ እና የታላቅ ሥልጣኔ ባለቤቶች በሆኑ ሀገራት መካከል በየጊዜው ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ይነሳ የነበረው የዓባይ ውኃ ጉዳይ ነበር፡፡ እናም በዛግዌ እና በመካከለኛው የኢትዮጵያ የታሪክ ዘመን ወደ ግብፅ የሚፈሰው የዓባይ ውኃ መጠን በቀነሰ ቁጥር ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ መነሳቱን ከታሪካችን እንረዳለን፡፡
      የግብፅ ነገሥታት አልፎ አልፎ የዓባይ ወንዝ በምንጩ አካባቢ በሚደርስ ድርቅ ምክንያት የፍሳሹ መጠን የሚቀንስ መሆኑን ባለመጠርጠር፣ የኢትዮጵያውያን ውኃን የዘጉት ወይም ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ ያደረጉት እየመሰላቸው፣ ውኃውን ለማስለቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ነገሥታት ዘንድ በየጊዜው መልእክተኛ ይልኩ ነበር፡፡
    ለምሳሌ ታሪክ ጸሐፊው የዓረብ ተወላጅ አል ማኪን ድርጊቱ ከሆነበት ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ ሲጽፍ በፋቲሚድ ሥርወ መንግሥት በሡልጣን አቡ ታምሊን አል ሙስታንዚር የአገዛዝ ዘመን (1036-1094) ግብፅ የሚደርሰው የውኃ ብዛት በ1089-1090 አካባቢ ቀነሰ፡፡ በዚህ የተነሳ ሡልጣኑ ወዲያውኑ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አባ ሚካኤልን ከፍ ያለ ገጸ በረከት አስይዞ ኢትዮጵያውያን የተቋረጠውን የዓባይን ወንዝ እንዲለቁ ለመለመን ወደ ኢትዮጵያ እንደላካቸው አትቷል፡፡
     አል ማኪን ጉዞውም በ1092 እና በ1094 ዓ.ም ማሃል ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር በማለት፤ የኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት የነበረው ይምርሃነ ክርስቶስ አንድ ኮረብታ እንዲፈርስ ባዘዘ ጊዜ የውኃው መጠን በአንድ ሌሊት ሦስት ጫማ ከፍ ብሎ አደረ ሲል በመጽሐፉ በሰፊው ተርኮአል፡፡
      በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን የግብፅ ማምሉክ ሡልጣን አል ናሲር ሙሀመድ ኢብን ቃላኡን በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የማፍረሱና ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን በጽኑ የማሰቃየቱ ዜና ወደ ኢትዮጵያ ደርሶ ከፍ ያለ የኀዘን ስሜት መፍጠሩን አል ማቅሪዝ የተባለው የሞሮኮ ተወላጅ ታሪክ ጸሐፊ በወቅቱ ዘግቦአል፡፡
        በታሪኩ ውስጥ ስሙ ባይጠቀስም ከ1380-1409 ዓ.ም የነገሠው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዳዊት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ግብፅ ልኮ የዓባይን ወንዝ ፍሳሽ ወደ ሌላ አቅጣጫ በማዞር የግብፅን ሕዝብ በራብ ለመፍጀት እንደሚችል ለግብፁ መሪ በብርቱ ማስጠንቀቂያ ገልፆለት እንደነበር ጽፎአል፡፡

ኢብን ፋድል አል አልዑማሪ የተባለ አንድ የግብፅ ቤተ መንግሥት ባለሟልና ጸሐፊ ‹‹ማሳሊክ አል አብሳር ፊ ማምሊክ አል አምሳር›› ቀጥታ ትርጉሙ ‹‹የነገሥታት ምድር ቅኝት›› በሚል ርዕስ በዘመኑ ያስተዋለውን የተለያየ ነገር ጽፎ ነበር፡፡ በዚህ መጽሐፉ ሀበሾች (ኢትዮጵያውያን) ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ዓባይን እንደሚቆጣጠሩና ለግብፅ ሡልጣን ከበሬታ ሲሉ ብቻ ውኃው እንደተለመደው ወደዚያ እንዲፈስ የሚፈቅዱ መሆናቸውን ይናገራሉ ሲልም ገልጾአል፡፡
         የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብፃውያኑ መንፈሳዊ ባርነትና ፖለቲካዊ ሴራ ትላቀቅ ዘንድ የኢትዮጵ መንፈሳዊ አባቶችና ንጉሡ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከ1600 ዓመታት መራር የግብፃውያን ቀንበር ተላቃ የራሷን መንፈሳዊ መሪ ካገኘች አምሳ ዓመታት ያህል ተቆጥረዋል፡፡ ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግብፃውያን አገዛዝ ብትላቀቅም ሁለቱን አገራትን በሚያስተሳስራቸው በዓባይ ጉዳይ ላይ አሁንም ድረስ ግብፃውያኑ ክርትስቲያኖች ሆኑ ሙስሊሞች ያላቸው አቋም በዓባይ ላይ ለምን ሲባል ጥያቄ ታነሳላችሁ የሚል ዓይነት ጠንካራና ግትር ነው፡፡

ግብፃውያኑ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ያላትን የመጠቀም መብት በተመለከተ ሲነሳ ሁሌም ዓይናቸው ደም ነው የሚለብሰው፣ ይህ ቅናታቸውና ቅንነት የጎደለው ጭፍንነታቸው ከዓባይ አልፎም ኢየሩሳሌም ድረስ ሣይቀር እንኳን ተሻግሮ በኢትዮጵያውኑ ጥንታዊ ይዞታ በሆነው በዴር ሱልጣን ገዳም ላይ ያሳረፈውን ብርቱ ጥላቻና ክንድ አይተናል፣ ታዝበናልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምናልባት በሌላ ጊዜ ሰፋ አድርጌ እጽፍ ይሆናል፡፡
    ግብፃውያኑ እንቀድሞው ዘመን በመንፈሳዊነት ስም ኢትዮጵያንም ሆነ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ዳግም በቅኝ ገዢነት መንፈስ ይዘው ዓላማቸውን ለማስፈጸም ምንም ዓይነት ዕድል እንደሌላቸው ካወቁ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የዓባይ ውኃን በተመለከተ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብቷ ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ እንደሆነ ግብፅና ግብፃውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዱት መጥተዋል፡፡ እንደቀደመው ዘመን በማስፈራራትና በዲፕሎማሲያዊ ጫና የዓባይን ውኃ ከመጠቀም የሚከለክሉበት ምክንያት እንደሌላቸውም እርግጥ ሆኗል፡፡
     አሁን አሁን ከግብጽ እየወጡ ያሉ መረጃዎችና ዜናዎች እንደሚያሳዩትና በቅርቡ ፕሬዝዳንት ሙርሲም እንዳረጋገጡት፡- ‹‹ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደው ልማት ግብፅንና የተቀሩት የተፋሰሱን አገሮች እስካልጎዳ ድረስ ደስተኞች ነን፡፡ ከጎናችሁም እንቆማለን ሲሉ እየተደመጡ ነው፡፡›› ይህ ከልብና ከቅንነት የመነጨ ከሆነ መልካም የሚባል እርምጃ እንደሆነም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብም እየገለጹ ናቸው፡፡

ሕዝባችን ለዘመናት ከተጣበው ድህነት፣ የመከራ፣ ሰቆቃና የስደት ሕይወት ተላቆ በአገሩና በሕዝቡ መካከል ተረጋግቶና እፎይ ብሎ መኖር እንዲችል ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ መልካም አስተዳር፣ ልማት ወዘተ በጣሙን አስፈላጊ ናቸው፡፡
       መንፈሳዊ ተቋማትና መሪዎቻቸው በአገራችን ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ መልካም አስተዳደር፣ ዕድገትና ብልጽግና እንዲሰፍን የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ድርሻና ተሣትፎ አላቸው፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ በዓባይ ወንዝ ላይ ስለተጀመረው ልማት፣ በዴር ሱልጣን ገዳማት ጉዳይና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ የተንሰራፋውን ሙሰናና ሙሰኞችን በተመለከተ ያስተላለፉት መልእክት ብዙዎችን ደስ አሰኝቷል፡፡
       የቅዱስነታቸው ይህ ቃል ከቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ብፁዓን አባቶቻች ጋር በመተባበር ተግባራዊ ሆኖ የምናይበትን ጊዜ መንፈሳዊ ልጆቻቸው በታላቅ ጉጉት እንጠብቃለን፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለተንሰራፋው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሞራል ዝቅጠትና ውድቀት፣ እንዲሁም የመንፈሳዊነት ሕይወት መታጣት ብዙ የተባለለት ያረጀና ያፈጀ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን ከማውራት በስተቀር ይህን ነው ተብሎ ሊነሣ የሚችል ተግባራዊ እርምጃ እስካሁን አልተወሰደም፡፡
      እንዲሁም ቅዱስ ፓትርያርኩ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ያጣበቡትን ነጋዴዎችና ዘራፊዎች ያለ ምንም ቅደም ሁኔታ በማስወጣት መንፈሳዊና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰዱና፣ በተጨማሪም የተሠጣቸውን መንፈሳዊ የሆነ ኃላፊነት ዘንግተው ፍጹም መንፈሳዊ ባልሆነ አካሄድ በሥጋዊና በዓለማዊ ምኞት ተጠልፈው፣ ያልደከሙበትንና ያለፉበትን ሀብትና ገንዘብ የማከማቸት ሥራ ውስጥ ተዘፈቁ የቤተ ክርስቲያኒቱን ኃላፊዎች ተገቢውን ሥርዓት እንዲይዙ እንደሚያደርጉ ያስተላለፉት መልእክት በእውነት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
       ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንፈሳዊ ቅንአትና ቆራጥነትና እንዲሁም ባላቸው ከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነትና እረኝነት በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አገልጋዮችና ተከታዮቿ መካከል ለአገርና ለወገን የሚቆረቆር፣ የተሠጠውን ግዴታውንና ኃላፊነቱን በታማኝነት የሚወጣ፣ በወንጌል የእውነት ቃል የታነጸ መልካም ዜጋና ትውልድ ለመፍጠር ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አባቶች ጋር የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ተወዳጅና ተከባሪ አባት እንዲሆኑልን እመኝላችኋለሁ፡፡
      በተጨማሪም ቅዱስ ፓትርያርኩ የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብታችንን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግብፅ ጋር የነበራትንና አሁንም ያላትን የረጅም ዘመን ግንኙነትና እንዲሁም ታሪካዊ ትስስር ከግምት ውስጥ በማስገባት የጀመሩትን እንቅስቃሴ ይቀጥሉበታል የሚል ጽኑ ተስፋ አለኝ፡፡
       ከግብፃውያን ጋር ለረጅም ጊዜያት አተካራ በገባንበትም በዴር ሱልጣን ገዳማችን ጉዳይን በተመለከተም ፓትርያርኩ በኢየሩሳሌም ለረጅም ዓመታት በመቆየታቸው ያለውን ሃይማኖታዊ ሆነ ፖለቲካዊ ችግሩን በሚገባ ያውቁታልና ቅዱስ ሲኖዶስንና መንፈሳዊ ልጆቻቸውን በማስተባበር ሰፊ የሆነ ሥራን ሊሠሩ እንደሚችሉ መንፈሳዊ ልጆቻቸው ተስፋ እናደርጋለን፡፡
     በቀጣይ ጽሑፌ በዴር ሱልጣን ገዳም ዙሪያ ያለውን ታሪክና የግብፃውያኑን ሴራ ከወቅታዊው የዴር ሱልጣን ገዳም ጉዳይ ጋር አያይዤ ለመጻፍ ከወዲሁ ቃል በመግባት ልሰናበት፡፡

ሰላም! ሻሎም!