Sunday, March 20, 2016

በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት!

መዝ 150
ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት።
በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት።
በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት።
በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።
ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።
እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን፦ ሃሌ ሉያ።



Saturday, March 19, 2016

ያገር ያለህ ወይም የዳኛ ያለህ!!!


ከእውነቱ /ለውይይት የቀረበ/

 1/ መግቢያ

በድሮ ጊዜ ሰው በሰው ሲበደልና ፍትሕ ሲጓደል ‘ያገር ያለህ’ ወይም ‘የዳኛ ያለህ’ በማለት ይጮህ ነበር፤ ይህ ዓይነቱ የተበዳይ ጮኸትም ለትውልድ መርገም እንዳይሆን ተብሎ በአካባቢው በሚኖሩ እድሜና ልምድ ጠገብ ሺማግሌዎች ገላጋይነት/ዳኝነት የበደለ እንዲክስ የተበደለ ደግሞ እንዲካስ በማድረግ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ይደረግ ነበር፤ እኔም ዛሬ በዲሞክራሲ ስም በምድራችን ውስጥ እየሆነ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ /በተለይ ባለውለታ በሆነችው በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ውስጥ/ ቀረብ ብየ ስመለከት ይህ እውነተኛ የፍትህ ፈላጊዎች ያገር ያለህ ጩኸት ትዝ ብሎኝ ለኢትዮጵያውን በሙሉ ለውይይትና ለመፍትሄው ፍለጋ ጭምር የሽማግሌ ዳኞች ያለህ በማለት ጮኸቴን ላቀርብ ተገደድኩ። መቸም ለተወሰኑ ዓመታት ከአገሩ ራቅ ብሎ ለኖረ ኢትዮጵያዊ የአዲስ አባባ ገጽታ ቀየር እንደምትልበት ይታመናል፤ በርካታ ሕንጻዎችና መንገዶች ተሠርተዋል፤ ባቡርም ተጀምሮ ሕዝቡ እየተጠቀመበት መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ለራሴ ሕሊና ታማኝ መሆን ስላለብኝ የሚታዩትን መልካም ነገሮች እሰየው በማለት፣ ደስ የማይሉትንና ደካማ የሆኑትን ደግሞ ለእርምት በግልጽነት ብጠቁም ሰውነቱን የሸጠ ካልሆነ በስተቀር ቅር የሚሰኝ እውነተኛ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። እዚህ ላይ የሕንጻዎችና የመንገዶች መገንባት መልካም ቢሆንም፤ በራሳቸው ግን ያንድ አገር እድገት ዋና መስፈርቶች ናቸው ብሎ መውሰዱ ተገቢ አይመስለኝም፤ ሕንጻ ያለሰው ከንቱ የድንጋይ ክምር ብቻ ስለሚሆን! በሌላ መልኩ ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ በኑሮ ችግር እየተጠበሰና ያገሪቱ ሃብት በጥቂቶች እጅ ውስጥ ሆኖ እያለ ኢኮኖሚስቶች በነፍስ ወከፍ የገቢ ስሌት ተመስርተው አድገናል ማለታቸው በሕዝቡ አጠቃላይ የኑሮ ምጥ ላይ የሚታየውን የህይወት ማቃሰት በግልጽ መካድ ነው የሚሆነው፤ የተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል በሌለበት አገር ውስጥ ይህ ዓይነቱ የሂሳብ ቀመር እንዴት ሆኖ እውነተኛ ሚዛን እንደሚሆን ፈጽሞ አይገባኝም። ማየት ከመስማት የበለጠ ጥሩ መረጃ እንደሆነ ይታመናል፤ በመሆኑም አገራችን ኢትዮጵያ ምን እየሆነችና ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ ከዚህ በፊት በጆሮዬ የሰማሁትን ዛሬ በዓይኔ አይቼ ለራሴ ህሊና ያገኘሁትን መረዳት በሚከተሉት ርእሶች ላይ ያለኝን ስጋት በትንሹ ላካፍል፡

 1. ፖለቲካውና ኢኮኖሚው በሕዝቡ ኑሮ ላይ ያስከተለው አውንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ፣ /በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ይሆናል/

 2. በሐይማኖታዊ ተቋማት /በተለይ አብዛኛው ሕዝብ ችግሩን ለፈጣሪው የሚያቀርብባትና ለመጽናናት የሚሞክርባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን/ ውስጥ እየሆነ ያለው መተራመስ፤ በምድራችን ውስጥ በርካታ የሃይማኖት ተቋማት ይገኛሉ፤ ሆኖም ግን ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላትና በበርካታ ጠንካራ ጎኗ ጉሉህ ስፍራውን ይዛ የምትገኘው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለመሆኗ የሚክድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፤ ካለ ግን ልሟገተውና ጣሊያንን በምስክርነት ጠርቸ ላስመሰክርበት እችላለሁ፤ ይህ የሚሆነውም በራሳቸው ሙያ የሚተማመኑ እውነተኛ ዳኞች ከተገኙ ብቻ ነው። ስለዚች ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አጀማመር፣ ላገር ስላበረከተችው መልካም አስተዋጽኦ፣ በረጅም የታሪክ ሂደቷ ውስጥ ስለገጠሟት በርካታ ተግዳሮቶችና ስለከፈለችው ከፍተኛ መስዋትነት ማወቅ ለሚፈልግ /የራሱን ታሪክ ማወቅ ለሚፈልግ/ ወደ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጎራ እንዲል እየጠቆምኩ፤ የዛሬውን መልእክቴን ግን በቤተ ክርስቲያኒቷ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በስፍራው ላይ ተገኝቼ ያየሁትን እውነት ብቻ ጥንቃቄ ባለው መልኩ በዚህ የመጀመሪያ ጽሑፌ ላይ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

   በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከላይ ከፓትሪያሪኩ ጀምሮ በተዋረድ ወደታች የሚፈስ ያስተዳደር መዋቅር አለ፤ በተጨማሪ በርካታ መንፈሳዊ የትምህርት ማሰልጠኛዎች እያስመረቁ የሚያወጧቸው ወጣቶች ዐውደ ምህረቱን ሞልተውት የሰንበት ትምህርት የማስተማሩን ሥራ በሰፊው ተያይዘውታል፤ እኔን የገረመኝና የማላውቅበትን ብእር እንዳነሳ ያደረገኝ ግን በዚህ ግራና ቀኙን በማያውቅና እግዚአብሔርን በሚፈራ የዋህ ወገናችን መካከል በተለያየ መንፈሳዊ ስያሜ ተመስርተው የሚያካሂዱት የእርስ በርስ ጦርነት ነው፤ በዘመናት መካከል እኔ ‘አውቅልሃለሁ የሚልለት ተቆርቋሪ አጥቶ የማያውቅ’ አሳዛኝ ሕዝብ፤! በዚህ መሰረት ለዛሬ ማህበረ ቅዱሳንን እና ኦርቶዶክስ ተሐድሶ የሚባሉትን መንፈሳዊ ማህበራትን ከሥራቸውና ከሚያራምዱት ዓላማ አኳያ በማየት ፍርዱን ለእውነት ፈላጊዎችና ለወገን ተቆርቋሪ ወገኖች ስተወው፤ ለበለጠ መፍትሄ ፍለጋ ግን ቤተ ሰብ ከቤተሰብ፣ ጓደኛ ከጓደኛ፣ ባል ከሚስት፣ ጎረቢት ከጎረቢት፣ አንዳችን ከሌላው ጋር በእውቀትና በቅንነት ግልጽ ውይይት በማድረግ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅመውን መደገፍ ለሁላችንም ይበጃል።

1/ ማህበረ ቅዱሳን ማነው?

ከማሕበረ ቅዱሳን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሁላችንም ልንማረው የሚገባ ቁምነገር እንዳለ አምናለሁ፤ ዋና ዓላማው ግልጽ ባይሆንልኝም የአባላቱ ስብጥር፣ አባላት ለማህበራቸው የሚከፍሉት ዋጋና የርስ በርስ መደጋገፍ ይበል የሚያሰኝ ነው። እንዲሁም በየደብሩና በየገዳማቱ ለወደቁ ምስኪን ወገኖቻችን ከሚያደርገው መልካም ሥራ ባሻገር /እውተኛው ክርስትና የመስቀሉ ሥራ ውጤት እንጂ የመልካም ሥራ ውጤት አይደለም ወይም በሌላ አባባል የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በመጀመሪያ በጸጋው አምኖ መጽደቅ አለበት ይላሉ ተሐድሶዎች/ ለባህልና ለቅርስ ጥበቃው ሥራ የሚከፍለው ዋጋም በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። የዚህ ማህበር ሌላ መገለጫ ባህሪው የተለያየ የጉዞ ፕሮግራም በማዘጋጀት ሕዝቡ ገንዘቡን ከፍሎ በነጭ ልብስና በኢትዮጵያ ባንዲራ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሕዝቡ ማህበራዊ ትስስር እንዲበረታታ ያደርጋል፤ ሌላው አብዛኛው ሕዝብ አዲስና ልዩ ፈዋሽ ጸበል ተገኘ በተባለበት ስፍራና በየገዳማቱ ሁሉ አብዝቶ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል።
ማህበሩ በተጨማሪ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ፡- ሕንጻ መገንባትን፣ ንግድ መነገድን፣ የራሳቸውን አባላት ማሰልጠንን፣ አዳዲስ ታቦታት መትከልንና ስነጽሁፎችን በሰፊው አውጥቶ ማሰራጨት ሲሆኑ በእነዚህ ጽሁፎቻቸውም ላይ በዋናነት ተሐድሶን የሚያጥላላና የሚያወግዝ መልእክት በትኩረት ያወጣል። የማህበሩን እንቅስቃሴ ለማጠቃለልም፡  የውስጣቸውን/የልባቸውን ባላውቅም አለባበሳቸው በባንዲራ የታጀበ ነጭ ልብስ በመሆኑ የየዋሁን ሕዝባችንን ልብ ለዓላማቸው በቀላሉ ማማለል ይችላሉ፤ ችለዋልም፣  ለቅርስና ባህላዊ እሴቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸውም ለአገር ብቸኛ ተቆርቋሪ ከነሱ ሌላ ፈጽሞ የሌለ አስመስሏቸዋል፣  ባህላዊ የቆሎ ትምህርት ቤቶች የበለጠ እንዲጠናከሩ ድጋፍ ያደርጋል፣ የገዳምና የምንኩስናን ኑሮ በማበረታት ምሁራን ሳይቀሩ ወደገዳም እንዲገቡ ያበረታታል፤ እንዲያውም ከውጭ አገር ኑሯቸው ተመልሰው ገዳም እንዲገቡ የተደረጉ እንዳሉ ይነገራል፣  ዘርዓ ያዕቆብን የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለወለታ በማድረግ ያወድሱታል፤ታሪኩንም ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ የተደጋገመ ወርክሾፕ በስሙ አድርገውለታል/እያደረጉለትም ነው፣  መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቃቸውን አዳዲስ ቅዱሳንን ሳይቀር ሕዝቡ እንዲያውቃቸውና ጽላት/ታቦት እንዲቀረጽላቸው ያደርጋል፤ አድርጓልም /ምሳሌ አርሴማ የምትባልን ነጭ ሴት/፣  ለአባላቱ ሁለንታዊ ድጋፍና ስልጠና በትጋት ከማድረጉም ባሻገር በምረቃና በሰርግ ላይ ከበሮና ጸናጽን ይዞ በመገኘት በሚያደርገው ሞቅ ያለ የሽብሸባ አምልኮ ከጴንጤዎች ጋር ውድድር የገባ አስመስሎታል፣  ሕንጻ ይገነባል፣ ንግድ ይነግዳል፣ ገንዘብ ይሰበስባል፣ አባላትን ያደራጃል /ከቀን ሰራተኛ እስከ ምሁር ባለስልጣናት ድረስ/፣  በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ የሚማሩትን ተማሪዎች በማሰልጠንና በእረፍታቸው ወቅት ወደየቤተ ሰቦቻቸው በመላክ ዓላማቸውን በሰፊው እንዲያስተዋውቁላቸው ያደርጋል //ይህን በተመለከተ አንድ በመንፈሳዊም ሆነ በታሪክ በቂ እውቀት የሌለው /ከስሜታዊነት በስተቀር/ የወንድሜ ልጅ መሳተፉን አጫውቶኛል//፣  ማህበሩ በሚያደርገው አጠቃላይ እንቅስቃሴ አባላቶቹንና የዋሁን ሕዝብ ፍጹም የጉልበት ሃይማኖተኛ እያደረገው እንደሆነ በአንዳንድ ደብር በስሜታዊ አባላቱ በኩል የሚታዩት የደም መፋሰስ ግጭቶች ይመሰክራሉ፣  አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ላይ በሙያተኞቹ በኩል በሰፊው ይሳተፋል፣  ጎልቶ የሚታየው ሌላው ሥራው በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ከሚገኙ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶችን በመክሰስና ከሥራ በማሳገድ እስከ ቤተሰባቸው ችግር ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል /ይህ በደል የደረሰባቸውን አንድ ሊቅ ይህ ጸሐፊ አናግሯል/፣  ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ያስፈልጋታል የሚሉትን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች፣ መነኮሳት፣ ዲያቆናትና አባላትን በሙሉ የፕሮቴስታንት ቅጥረኞችና ጸረ ኦርቶዶክስ ናቸው በማለት በመጽሄታቸው፣ በጋዜጣቸውና በአውደ ምህረት ላይ በማውጣት ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጋል።
ይቀጥላል


Sunday, March 13, 2016

እነሆ ሁለቱ ኪዳናት!

መቅድም
 ‹‹እነሆ ሁለቱ ኪዳናት›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ በ2002 ዓ.ም ‹‹ሁለቱ ኪዳናት›› በሚል ርዕስ በመሪጌታ ሃየሎም ተዘጋጅቶ በማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነትና አከፋፋይነት በተሠራጨው መጽሐፍ ውስጥ ለተላለፉት ኢ-ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎች መልስ ለመስጠት ቢሆንም በችግሮቹ ላይ ብቻ ከማትኮር ይልቅ አንባቢያን ሃሳቤን በቀላሉ እንዲረዳልኝ ያስችላሉ ያልኳቸውን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስና የታሪክ እውነታዎች በማሰባጠር በማስረጃ አስደግፌ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ የዚህን ጽሑፍ ረቂቅ ያሳየኋቸው አንዳንድ ወንድሞች የሁለቱ ኪዳናትን ጸሐፊ፣ አርታኢና አሳታሚ ማኅበር የእምነት አቋም ተወራራሽነት ለመግለጽ የተጠቀምኩባቸውን የወል ዐረፍተ ነገሮች ባስተካክላቸውና በጸሐፊው ላይ ብቻ አትኩሬ መልእክቴን ባስተላልፍ እንደሚሻል አስተያየት ሰጥተውኛል፡፡ ሃሳባቸውን በሃሳብነቱ ብቀበለውም እንዳሉት ሶስቱን አካላት ነጣጥዬ ማየት ግን አልሆነልኝም፡፡ ለዚህም ምክንያቴ አርታኢው ከአርትዖት ተግባሩ ባሻገር የመጽሐፉን መግቢያ በማዘጋጀትና በመጽሐፉ የተካተተውን አስተምህሮ ‹‹ትክክለኛነት›› አጽንኦት ሰጥቶ በማስተጋባት እንዲሁም ማኅበሩ በሐመረ ተዋሕዶ 2001 ዓ.ም ልዩ እትሙ‹‹እቅበተ እምነት (አፖሎጂ) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን›› በተሰኘ አምድ ሥር ‹‹ሁለቱ ኪዳናት ማኅበረ ቅዱሳን በተለያየ ጊዜ በመጻሕፍትና በመጽሔት በቃል ትምህርትም መናፍቃን ለዘሩት የጥርጥር ትምህርት መልስ የሰጠበት መጽሐፍ›› ነው ብሎ መገለጹ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው የእምነት አቋም የጸሐፊው ብቻ ሳይሆን የአርታኢውና የማኅበሩ ጭምር መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ በተገለጠው የትምህርት አቋማቸው ብርሃኑ፣ ሐየሎምና ማኅበረ ቅዱሳን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውና ብርሃኑንም ሆነ ሐየሎምን ሳመሰግን ሶስቱንም ማመስገኔ፣ እንዲሁም የብርሃኑንም ሆነ የሐየሎምን ሃሳብ ስቃወም ሁሉንም መቃወሜ መሆኑን ማስገንዘብ ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በእኔ እምነት ብርሃኑ ስለማያምንበት ነገር መንደርደሪያ አልጻፈም፤ ማኅበረ ቅዱሳንም የእምነት አቋሙ ያልሆነን ትምህርት አሳትሞ አላሰራጨም፤ ለመናፍቃኑ የተሰጠ መልስ ነው እያለም አልፎከረምና ከምስጋናውም ሆነ ከወቀሳው ሊጎድሉ አይገባም ብዬ ሁሉንም ያለ ልዩነት እንዲጋሩት አድርጌያለሁ፡፡

እንደማምነው ካራ፣ ቅባት እና ጸጋ ሁሉም የተዋሕዶ አማኞች ናቸው፡፡ እንግዳ አመለካከት ሊመስል ቢችልም እንኳ ንስጥሮስ፣ አቡሊናርየስ፣ አውጣኬና ፓፓ ሊዮም ሳይቀሩ የዚሁ የተዋሕዶ ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች ናቸው፡፡ ልዩነቱ የተፈጠረው ተዋሕዶን ለመግለጽ በተጠቀሙበት ቃል ትንታኔ ላይ ነው፡፡ አውጣኬ ተዋሕዶውን ያስረዳበት መንገድ መለኮት የሥጋን ባሕርይ መጥጦታል የሚል በመሆኑ መጠፋፋትን እንጂ የሁለቱን ባሕርያት መገናዘብ አያስረዳም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትም የለውም ተብሎ ተወገዘ፡፡ አቡሊናርየስ ክርስቶስ የሰው ነፍስ የለውም፤ በነፍሱ ምትክ ነፍስ የሆነለት መለኮት ነው አለ፡፡ በዚህም የክርስቶስን ፍጹም ሰውነት አጎደለ ተብሎ ተተቸ፤ ተለየ፡፡ ንስጥሮስም በበኩሉ የቃልና የሥጋ ተዋሕዶ ሁለቱ አካላት የየግል አቋማቸውን ጠብቀው የየራሳቸውን ሥራ እየሠሩ የሚኖሩበት ስምምነት (moral union) ነው አለ፡፡ እንደ እርሱ አባባል መለኮት በሥጋ ውስጥ አደረ እንጂ ባሕርያዊም ሆነ አካላዊ ተዋሕዶን አላስከተለም፡፡ ታዲያ ይህም ቢሆን የክርስቶስን አሐዱነት በተገቢው መንገድ አይገልጥም ተብሎ ተነቀፈ፡፡ በግልጥ እንደሚታወቀው የፓፓ ሊዮ አቋም ሁለት ባሕርያት በአንድ አካል የሚል ነው፡፡ ይህም ቢሆን ተዋሕዶን ምሉዕ በሆነ መንገድ አይገልጥም፡፡ አካል ያለ ባሕርይ ባሕርይም ያለ አካል ሊኖሩ አይችሉምና አንዱ የክርስቶስ አካል የማን ነው? የሚል ውዝግብ አስነሳ፡፡ ይህም አስተምህሮው በኦርየንታሎቹ ዘንድ ጥያቄ ላይ ወደቀ፡፡ በዚህም እንደሚታየው ፓፓ ሊዮም በሁለቱ ባሕርያት መኖር ላይ ከማትኮሩና የክርስቶስ አካል የመለኮት ነው ከማለቱ በቀር ተዋሕዶን አልተቃወመም፡፡ በመጀመሪያው የኤፌሶን ጉባኤ ተቀባይነት ያገኘው የቅዱስ ቄርሎስ የ‹‹ተዋሕዶ›› አስተምህሮ (ምንም እንኳ ምዕራባውያኑ በትክክል ባይረዱትና ከፓፓ ሊዮ የአንድ አካል ሁለት ባሕርይ፣ አልፎ ተርፎም ከአውጣኬ የመጠፋፋት ትምህርት ጋር ሊያመሳስሉት ቢሞክሩም) ሁለቱ አካላትና ሁለቱ ባሕርያት ሳይጠፋፉ፣ ሳይነጣጠሉ፣ ሳይቀላቀሉ አንዱ የሌላውን አካልና ባሕርይ ገንዘብ የተደራረጉበትን ከሁለት አንድ የመሆን ምስጢር (አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ፈቃድ፣ አንድ ግብር) የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህም በተዋሕዶ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ያከናወናቸው ተግባራት ሁሉ ይህ የሥጋ ነው ያኛው ደግሞ የመለኮት ነው ተብለው ሳይከፈሉ በአንዱ በክርስቶስ (ሥግው ቃል) የተከናወኑ ናቸው የሚል ነው፡፡ በዚህ አስተምህሮ መሠረት እንደ ንስጥሮሳውያንና እንደ ኬልቄዶናውያን (ፓፓ ሊዎ) ድካሙን ለሥጋ ብርታቱንና ማዳኑን ለመለኮት የመስጠት ሙከራ በብርቱ የተነቀፈ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ከአውጣኬያውያንና ከነፓፓ ሊዮ የተዋሕዶ ሃሳብ በእጅጉ ይለያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በአቋም ደረጃ ይህንን ትቀበላለች፡፡

እንግዲህ በቤተክርስቲያናችን የሚታወቁት ሶስት ቡድኖች ምንም እንኳ ‹‹ተዋሕዶ›› ነን ቢሉም የተዋሕዶ አስተምህሯቸው ከላይ ከተገለጹት ተዋሕዶ ነን ባዮች ከየትኛው ምንጭ እንደተቀዳ በጥንቃቄ መፈተሽ ቀዳሚውንና ትክክለኛውን የተዋሕዶ እምነት ተገንዝቦ ለመከተልና ያለ እውቀት ከሚሰነዘር ትችት ለመታቀብ ያስችላል፡፡ ከዚህ የተነሳ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው የኤፌሶን ጉባኤ ያጸደቀችውን የተዋሕዶ ጽንሰ ሃሳብ ከነአውጣኬና ከነንስጥሮስ የተዋሕዶ ትርጓሜ ለመለየትና አንባቢያንን ከድንጋሬ ለመጠበቅ ‹‹ትክክለኛው›› የሚል ገላጭ ቃል ተጠቅሜያለሁ፡፡ በኢትዮጵያውያኑ የእምነት ጎራዎች (ካራ፣ ቅባት፣ ጸጋ) አስተምህሮዎች ላይ የመጻፉ ጉዳይ ብዙም አልታየኝ ነበር፡፡ ሆኖም የአንዳንድ ጊዜ የገጠማቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አስተምህሮ ምንጭ በብዙሃኑ ስለማይታወቅ ከነሰባልዮስና ከነአውጣኬ ወገን ተሰልፈው የነቄርሎስን እምነት እንከተላለን እያሉ እውቀቱ የሌለውን ምእመን ከማደናገር አልፈው በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ቃል በመቃወም ላይ ስላሉና የእነርሱን ፈለግ ያልተከተሉትን ሁሉ እያሳደዱ እውነተኛ መስለው ለመታየት ሌት ከቀን እየተጣጣሩ ስለሚገኙ የአሳዳጆቹም ሆነ ተሐድሶ ናቸው በሚል ሽፋን እየተሳደዱ ያሉት ወገኖች ማንነት በግልጽ ይታወቅ ዘንድ እንዳልኩት ብዙም ትኩረት ላደርግባቸው የማልፈልጋቸውን ሶስት ቡድኖች አስተምህሮ ከመረጃ መጻሕፍት አሰባስቤ ለማቅረብ ተገድጃለሁ፡፡ በተለይ ማኅበረ ቅዱሳን የነቄርሎስን የተዋሕዶ ለምድ ለብሶ የሚያቀነቅነው ‹‹ሰባልዮሳዊ›› እና ‹‹አውጣኬያዊ›› ተዋሕዶ ፍንትው ብሎ ይታይና ትክክለኛው ማንነቱ ይገለጥ ዘንድ ይህንን ማድረጌ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በተረፈ ወደ መሠረታዊው ሃሳቤ ለመሸጋገር አንድ ጸሐፊ በተናገሩት ቁም ነገር ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህ ትውልድ የሚፈልገውን እውነት በውስጧ ይዛለች፡፡ ነገር ግን እውነቷን ባልተዛባና ትውልዱ በሚፈልገው መንገድ ገልጣ ልታቀርብ አልቻለችም አብዛኛዎቹ የስብከት መድረኮቿ የተሞሉት ሌላውን በመንቀፍ ወግና ሥርዓትን ታሪክን በመተረክ ላይ በተመሠረቱ ስብከቶች ነው፡፡ በማኅበርና በግል ደረጃ በጽሑፍ የሚተላለፉ መልእክቶችም ይኸው ገጽታ ነው ያላቸው፡፡ ያለባትን ችግር በመረዳት በሚፈለገው ሁኔታ ወንጌልን የሚሰብክ አንድ ሰው ቢነሳ እንኳ በጥርጣሬ መንፈስ እየታየ በተለያዩ ውንጀላዎች ከመድረክ የሚወገድበት መንገድ ይፈለጋል (አግዛቸው ቀ.አ፡5)፡፡

ለእኔም እውነታው ይኸው ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ የአውጣኬያዊውና የሰባልዮሳዊው ተዋሕዶ ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሠርጎ መግባቱ ነው፡፡ እንደ ተባለው የከበረ እውነት አለን፤ ነገር ግን በዘመናት ሂደት ውስጥ ተቀብሯል፡፡ ስለዚህ የተቀበረው እውነት ተፈልፍሎ ሊወጣና ምእመኑ በግልጥ እንዲያውቀው ሌሎችም ቢሆኑ መሠረታዊውን የተዋሕዶ አስተምህሮ ተገንዝበው አጓጉል ነቀፋዎችን ከመሰንዘር እንዲቆጠቡ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ብርቱ ትግል፣ ለመታገልም እውነቱን ከሃሰቱ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጥላቻ በጸዳ መንፈስ ከማንበብና ከመወያየት የተሻለ መንገድ የለም፡፡ አለመደማመጥና ምን ያመጣሉ ለሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም እንዳልበጃት ከታሪክ መማር ይገባል፡፡ ስለዚህ ንባብዎ እውነቱን ለመፈለግና በመመካከር መልካሙን መንገድ ለመከተል ይሆን ዘንድ ከልቤ እመኛለሁ፤ እጸልያለሁም፡፡ ሌላው ምናልባት ላሳውቀው የሚገባኝ መልሱ የዘገየበትን ምክንያት ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ጊዜ እስኪደርስ ነው ብዬ ባስብም ይህ ጽሑፍ ከታሕሣስ 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በእጄ ላይ እየተንከባለለ ድፍን አምስት ዓመታት ማስቆጠሩን ሳስበው በጥቂቱ አዝናለሁ፡፡ በሌላ መልኩ ምንም እንኳ እንዲታተም ብዙ ጊዜ ተመኝቼ ባይሳካልኝም እንደ ቀልድ ባለፉት በእነዚያ ዓመታት ውስጥ እኔ ባደግሁበት ዕድገት ልክ የማደግና የመብሰል ዕድል አግኝቷልና ደስ ይለኛል፡፡ ምናልባትም ቀድመውና ዘግይተው ከተጻፉ ጓደኞቹ ይልቅ የመታተሙን ቅድሚያ እንዲያገኝ የረዳው ይኸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንዲህም ሲሆን ፍጹም ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ይልቁንም ገና ‹‹ሁ›› ስለሆነ ከስህተትና ከችግር የጸዳ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አንብባችሁ በምትሰጡኝ ምክርና ተግሳጽ ታግዤ ስህተቴን በማረም የተሻሉ ሥራዎቼን ይዤ እንደምቀርብ ተሥፋ አደርጋለሁ፡፡ እስከዚያው መልካም ንባብ!!!
                         ጸሐፊው