Friday, October 24, 2014

የቅዱስ ፓትርያርኩ የሲኖዶስ ጉባዔ መክፈቻ ንግግር (እዚህ ይጫኑ)



ሐራ ተዋሕዶ የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን ቀኝ ክንፍ መካነ ጦማር ቅዱስ ፓትርያርኩ በሲኖዶሱ መክፈቻ ላይ ባቀረቡት ንግግር ተወገዙ፤ ውሳኔም ተላለፈባቸው ሲል ከብራዘር ሁድ ጳጳሳቱ ጋር ያለውን የምስጢር ትስስር በሚያሳብቅ መልኩ ዘገባውን አቅርቧል። ማኅበሩ የሲኖዶስ አባል ሆኖ በጉባዔው ላይ በመገኘት የጉባዔው ተካፋይ መሆን አይጠበቅበትም። በሱ ምትክ የጉባዔውን እስትንፋስ እየለኩ ምስጢር የሚያካፍሉ አባላት የሆኑ ጳጳሳት እንዳሉት ይታወቃል። ማኅበሩን ያናደደውና ደረጃውን ያልጠበቀ የፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ያሰኘው ነገር ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለማኅበሩ ቀጥተኛ አቋም ይዘው በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አበክረው ስላሳሰቡ ከደረሰበት ጭንቀት የተነሳ መሆኑ ይገባናል። የፓትርያርኩን ንግግር ደረጃ የሚያወጣና ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ እሱ ማነው? አባ ሉቃስ? አባ ማቴዎስ?
በዚህ ዓመት ስለማኅበረ ቅዱሳን አቅምና ጡንቻ የመጨረሻ ገደብ ካልተደረገበት የነብርን ጅራት ይዞ እንደመልቀቅ ይቆጠራል። ጳጳሳቱም ቢሆን ክብራቸውን ካልጠበቁና ለማኅበሩ በአድማ ተሰልፈው ከቆሙ በተመዘገበ ግለ ታሪካቸው ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ሊደረግ ይገባል። በአጭር ቃል ባለትዳሮቹና የልጅ አባቶቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ማዕረግ ወርደው ከምዕመናን አንድነት ሊቀላቀሉ የሚገባው ዓመትም ይህ ዓመት ነው። ሳይገባቸው ከፍታ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ባለበት አስተዳደር ምን ጊዜም ሁከት፤ ክፍፍልና እርስ በእርስ መለያየት መኖሩ እርግጥ ነው።
ይህ ዓመት ቤተ ክርስቲያንን የሚያምሱ፤ በአድማ የሚወስኑ ሰዎች ሰልፍ የሚሰበርበት እንዲሆን እንመኛለን።

Wednesday, October 22, 2014

ማኅበረ ቅዱሳንን ክርስቲያናዊ ብራዘር ሁድ የሚያሰኙ ማስረጃዎችና መመሳሰሎች!

ሙስሊም ብራዘር ሁድ ወይም የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር የተባለው ድርጅት በ1928 ዓ/ም በግብጽ ተመሠረተ። ከሰማንያ ዐመታት በኋላ በጄኔራል አልሲሲ መንግሥት በአሸባሪነት ተፈርጆ ድምጥማጡ እስኪጠፋ ድረስ በ70 ሀገሮች ውስጥ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በዘመናዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች፤ በገበያ ማዕከላት፤ በንግድ ሱቆች፤ በማከፋፈያ ድርጅቶች፤ በሚዲያ ተቋማት ወዘተ የሀብት ማግበስበሻ መንገዶች እየተሳተፈ ክንዱን በማፈርጠም ለእንቅስቃሴው የሚጠቅመውን የገንዘብ ምንጭ ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ የግብጹ ሙስሊም ብራዘር ሁድ በዐረብ ሀገራት ውስጥ ተመሳሳይ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበራትን በማደራጀትና በማሰልጠን መንግሥታቱን ሲያስጨንቅ የቆየ ሲሆን አሁንም እያስጨነቀ ይገኛል።

የሙስሊም ብራዘር ሁድ ለተባለው ሃይማኖታዊ-ፖለቲካዊ ድርጅት ዋነኛ ተቀባይነት ማግኘት ዋናው ምክንያት የሆነው በእስላሙ ሕብረተሰብ ውስጥ ቶሎ ሰርጾ እንዲገባ የሚያካሂደው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱና  ለዚህ እምነት መክፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ከአላህ ዘንድ የሚከፈለውን ምንዳ ለመቀበል ቶሎ መሽቀዳደም ተገቢ መሆኑን አበክሮ በመስበኩ የተነሳ ነው።

1/ የሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅራዊ እንቅስቃሴ 

 ሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅሩ በሀገሪቱ የመንግሥት ሲቪላዊ መዋቅር ደረጃ የተዘረጋ ነው። ይህም ከማዕከላዊ ቢሮው ተነስቶ አባል በሆኑ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ በሰንሰለት የተያያዘ ነው። ቤተሰባዊውን የአባልነት ማኅበር «ኡስራ» ይሉታል። አንድ «ኡስራ» አምስት አባላት ሲኖሩት ከአምስት በላይ ከሆነ በሁለተኛ የኡስራ ስያሜ ደረጃ ይዋቀራል። በቤተሰቡ ያሉትን ኡስራዎች የሚመራ ደግሞ የቤተሰቡ አባል የሆነ በእስልምና ሃይማኖቱ የበሰለና የብራዘር ሁድ አስተምህሮት በደንብ የገባውን ሰው የቤተሰቡ ጉባዔ ይመርጠውና «ናቂብ» ተብሎ ይሰየማል። ይህ «ናቂብ» የተባለው ሰው የቤተሰቡ አባላት በእስልምናው ደንብ ዘወትር ስለመንቀሳቀሱ ይቆጣጠረዋል፤ ያስተምረዋል፤ ይነግረዋል። ያልተመለሰውን በማኅበረሰቡ ደረጃ ለተቀመጠውና ከፍ ላለው ሃይማኖታዊ መሪ ያቀርበዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ስለእስልምናው የሚደረግ እርምጃ በመሆኑ በደስታ ከሚቀበል በስተቀር ማንም በተቃውሞ አያንገራግርም፤ ሊያንገራግርም አይችልም። ምክንያቱም ጸረ እስልምና እንደሆኑ ራሳቸውን አስገዝተዋልና። በዚህ ዓይነት አደረጃጀት የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ከላይ ወደታችና ከታች ወደላይ የተሳሰረ መዋቅር አለው።

2/   የገንዘብ ምንጮቹን ማሳደግ

ገንዘብ የዚህ ዓለም እንቅስቃሴ የደም ሥር ነው። አባላት ለመመልመል፤ እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት፤ የሽብር ተግባሩን ለመፈጸም፤ ለመደለል፤ ለመሰለል፤ ሃይማኖታዊ ዶክትሪኑን ለማስተማር  እጅግ ጠቃሚ ነገር መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳው ብራዘር ሁድ የገንዘብ አቅሙን ለሀገር ውስጥና ድንበር ዘለል ተግባሩ ያውለው ዘንድ ተግቶ ይሰራል።

የእስላም ወንድማማቾች ማኅበር ሁለት ዓይነት የገንዘብ ምንጮች አሉት። አንዱ በውጪ ሀገራት ካሉ አባላቱ በመዋጮ የሚሰበሰብ እንዲሁም ብዙ ሃብት ካላቸው የድርጅቱ ደጋፊ ሚሊየነሮች  የሚደረግለት የገንዘብ ፈሰስና በእስላማዊ መንግሥታት ስር ከተሸሸጉ ባለስልጣናት የሚዋጣለት ገንዘብ ነው።  ሁለተኛው ደግሞ በተራድዖ ስም ከውጭ የሚያሰባስበውን ገንዘብ ወደልማት ካዝና በመቀየር በአካባቢ ልማት፤ በትምህርት ቤቶችና መድራሳ ማቋቋም፤ ሥራ አጥ ህብረተሰብን በማደራጀት፤ የራስ አገዝ እንቅስቃሴን በመመሥረት የሚሳተፍ ሲሆን ለዚህም ሀገር በቀል የእርዳታ ስልት በመቀየስ መዋጮውን ቅርጹን ለውጦ ያግበሰብሳል። ይህም፤

ሀ/ ከአባልነት መዋጮ
ለ/ ከንግድ ድርጅቶቹና ከሚዲያ ተቋማቱ የሚገኝ ገቢ ነው።


ይህንን ገንዘብ በተለያየ የገንዘብ ማስቀመጫ ስልቶችና በብዙ የሂሳብ አካውንቶች ቋት ውስጥ በተለያየ ስም በማስቀመጥ ለሚፈልገው ዓላማ በፈለገበት ሰዓት ማንም ሳያውቅበት ያውለው ነበር። በተለይም የእስልምና ባንኮች ተመራጭ መንገዶቹ ነበሩ።

3/ በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ሰርጎ መግባት

ብራዘር ሁድ አባላቱን ሲመለምል ነጻና ገለልተኛ የሆኑትን ብቻ አይደለም። ከሚኒስትሮች እስከፍርድ ቤቶች፤ ከመከላከያ እስከ ፖሊስ መምሪያዎች፤ ከድርጅት ሥራ አስኪያጆች እስከ አስተዳደር ኃላፊዎች ድረስ በአባልነት መልምሎ፤ አሰልጥኖና ሃይማኖታዊ ትጥቅ አስታጥቆ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር። እነዚህ የመንግሥታዊ አካላት ክፍሎች ድርጅታቸው ለሚነሳበት ተቃውሞና ኅልውናውን ፈታኝ ለሆኑ ችግሮች የግብዓት ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ። አስፈላጊ በሆነ የመረጃ፤ የፋይናንስና የአፈና ሥራው በትጋት ይሰራሉ።
ይህ ድርጅት እንደሃይማኖታዊ ተቋም አራማጅነት ተነስቶ ወደፖለቲካዊ ሥልጣን መቆናጠጥ እርምጃው ለማደግ መሠረት አድርጎ የሚነሳው የእስልምና ሃይማኖትን ነው። ይህም ብራዘር ሁድን መቃወም እስልምናን እንደመቃወም እንዲቆጠር በሕብረተሰቡ ዘንድ የኅልውናውን ስዕል በማስቀመጥ እንዳይነካ ወይም እንዳይጠፋ ረድቶታል። የእስልምናውን አስተምህሮ መነሻ በማድረጉ የማይነቃነቅ ፖለቲካዊ ግብ ለማስረጽ ያገዘው ሲሆን የዚህም መገለጫው በአልሲሲ መንግሥት ላይ በአንድ ጊዜ እስከ 33 ሚሊዮን ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በመላ ሀገሪቱ ማንቀሳቀስ የሚችል ድርጅት አድርጎታል።
 ይሁን እንጂ የጀነራል አልሲሲ መንግሥት እርምጃ ስልታዊ በመሆኑ በአንድ ቀን ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ከፍተኛና ዝቅተኛ አመራሩንና የሃይማኖታዊ ተፍሲር መምህራኖቹን ለቃቅሞ ወደማጎሪያ ካምፕ በመክተቱ ድርጅቱ በ85 ዓመት እድሜው አይቶት የማያውቀውን ውድቀት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያስተናግድ አድርጎታል። በአልሲሲ መንግሥት የተተገበረው «ወፎቹ እንዲበተኑ ቅርንጫፉን መቁረጥ» የሚለው አባባል ብቻ ሳይሆን ግንዱን መንቀል በመሆኑ የብራዘር ሁድ ዋና መሪ መሐመድ ሙርሲን ጨምሮ ከፍተኛውን የሹራ ካውንስል ሳይቀር ከስር ገርስሶታል። በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱም የሞትና የእስራት ፍርድ ተከናንበዋል። አልሲሲ በቲቪ ቀርበው "ብራዘር ሁድን ከስረ መሠረቱ ነቅለን ካላጠፋን ሰላም የለንም" በማለት ድራሹን አጥተውታል። ዛሬም ድረስ የተቃውሞ ሰልፎች ያሉ ቢሆንም በሃይማኖት ካባ ስር በተሸፈነው ድርጅት በኩል የአእምሮ አጠባ ተደርጎ የተታለለው ሕብረተሰብ እንጂ ብራዘር ሁድ እንደተቋም በግብጽ ታሪክ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል። ያ ማለት ግን ብራዘር ሁድን የሚደግፍ፤ የሚጠባበቅና እንዲያንሰራራ የሚፈልግ የለም ማለት አይደለም።

4/ማኅበረ ቅዱሳን እንደክርስቲያን ብራዘር ሁድ ስንል ምን ማለታችን ነው?

1/ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ከመንግሥትም፤ ከቤተ ክህነትም ቁጥጥር ነጻ መሆኑ
2/ የራሱን አባላት የሚመለምልና የሚያደራጅ መሆኑ
3/ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ ያለውና የንግድ ተቋማትን የሚያንቀሳቅስ መሆኑ
4/ ከአባላቱ ልዩ ልዩ መዋጮዎችና የስጦታ ገቢዎችን በመሰብሰብ በልማት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንዳለ የማሳየት ብልሃት ያለው መሆኑ
5/ በመንግሥት ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች፤ ፍርድ ቤቶች፤ ፖሊስ መምሪያዎች፤ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ስውር መዋቅር ያለው መሆኑ
6/ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላዕላይ መዋቅርና እስከ አጥቢያ ድረስ በተዘረጋው አስተዳደር የራሱ አደረጃጀት የዘረጋ መሆኑ
7/ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ውስጥ የራሱን ጳጳሳት በመመልመል ማስሾም የቻለ መሆኑ
9/ ከሀገር ውጭ ዓለም አቀፍ ቢሮዎችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስና አባላት ያሉት መሆኑ
10/ ከዓለም አቀፍ የገቢ ፈጠራው ውስጥ በልማት ሰበብ የሚያጋብስ መሆኑ
11/ የመረጃ፡ የስለላና የትንተና መዋቅር ያለው መሆኑ
12/ የቤተ ክርስቲያኒቱን አደረጃጀቶች ለራሱ ዓላማ የመጠቀም አቅም ያለው መሆኑ
( ሰንበት ት/ቤቶችን፤ የጥምቀት ተመላሽና የጽዋ ማኅበራትን)
14/ የግለሰቦችን ስም በማጥፋት ወይም ራሳቸውን በማጥፋት፡በማባረር፡በመደብደብ ወይም ግለታሪካቸውን ለራሱ ዓላማ ጠምዝዞ በማዋል እርምጃ መውሰድና ማስወሰድ የቻለ መሆኑ
15/ ስሙን ለማግነን፤ ክብሩን ለማስጠበቅ የሚያስችል በራሱ የሚመራ እንዲሁም በፖለቲካ የተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ደጋፊዎችና በስውር መረብ የሚንቀሳቀስ የሚዲያ ተቋም ያለው መሆኑ፤
ማኅበረ ቅዱሳንን ክርስቲያናዊ ብራዘር ሁድ እንድንለው ያስችለናል።

እስካሁንም ማንም ምላሽ ሊሰጥበት ያልቻለው ዋናው ነጥብ ማኅበረ ቅዱሳን ከመንግሥት እይታ ውጪ መሆን ባይችልም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ክርስቲያናዊ ማኅበር መሆኑ ሲሆን እንደክርስቲያናዊ ተቋምነቱ  ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ ላይ ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ችሎታ አንዳችም አቅም የሌላት በመሆኑ ያሳዝናል:: በመንግሥትም፤ በቤተ ክህነቱም ማንም ጠያቂ የሌለው ሆኖ መቆየቱን ለማመን ያለመፈልግ ዝንባሌ መኖሩም ያስገርማል::  ማኅበሩ እንደምክንያት ሁልጊዜ የሚያቀርበው ሲኖዶስ በሰጠኝ ደንብ እመራለሁ ቢልም እውነታው ግን ብራዘር ሁድ በሆኑ ጳጳሳት አባላቱ በኩል የሚመቸውን ደንብ አስጸድቆ ያለጠያቂ በነጻነት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የገቢ አቅሙን እያሳደገ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባላት እየመለመለ፤በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁመናና መልክ የራሱን አደረጃጀት፤ መዋቅርና እንቅስቃሴ እያከናወነ ያለ ማኅበር መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው። ለምሳሌ የማኅበሩ ብራዘር ሁድ አባላት ጳጳሳቱ አባ ማቴዎስ፡አባ ቀውስጦስ፡ አባ ቄርሎስ፡ አባ ያሬድ፡አባ አብርሃም፡አባ ሳሙኤል፡ በአባ ማቴዎስ አደራዳሪነት የትግሬን መንግስት በጋራ መዋጋት በሚል ፈሊጥ ከማኅበሩ እግር ላይ ወድቀው የታረቁት አባ ፋኑኤል ተጠቃሾች ናቸው:: አባ ገብርኤል ግን ከአቶ ኢያሱነታቸው ጀምሮ የተጠጋቸው የውግዘት በሽታ  መቼም አይለቃቸውም::

5/ ለመሆኑ አሁን ያለው ማኅበረ ቅዱሳን አደረጃጀት፤   

የሰንበት ት/ቤት ስብስብ ነው? እርዳታ ድርጅት ነው? የልማት ተቋም ነው? የበጎ አድራጎት ማኅበር ነው? ራሱን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ውጪ አስደርጓል። በዋና ሥራ አስኪያጅ ሥር የሚተዳደር ነገር ግን የቤተ ክህነቱ መምሪያ ያልሆነ መምሪያ ነው?
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሥፍራው ከየት ነው? በምንስ እንመድበው? ማኅበሩ በምን ሂሳብ እንደተቋቋመና በምን አደረጃጀት ኅልውና እንዳገኘ አይታወቅም::

እስከሚገባን ድረስ እንቅስቃሴውንና ያለውን አደረጃጀት ተመልክተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳናዊ ብራዘር ሁድ ብንለው ተግባሩ ያረጋግጣል።
በሌላ መልኩ መንግሥት በኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እንዲህ ዓይነት ማኅበር ከእስልምና ምክር ቤቱ ውጪ እንዲቋቋም ይፈቅዳል ወይ ብለን እንጠይቃለን? መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው።

Saturday, October 18, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን የሚፈርሰው በራሱ ተግባር ነው፤ ኢሕአዴግ ላለፉት 22 ዓመታት መቼ ነካው?

ይህን ጽሑፍ በመጋቢት ወር 2006 ዓ/ም በመካነ ጦማራችን ላይ አውጥተነው ነበር።። ዳግመኛ ማውጣት ያስፈለገን ጉዳይ ሰሞኑን በፓትርያርክ አቡነ ማትያስና በማኅበረ ካህናቱ በኩል ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን በቅኝ ገዢነት የመቆጣጠር ስልቱና ይህንን ስለማስቆም በአንድ ድምጽ የተናገሩትን አቋም በመጻረር የማኅበረ ቅዱሳን ቀኝ ክንፍ የሆኑት አባ ማቴዎስ የሰጡትን  ማስጠንቀቂያ መነሻ በማድረግ ለማስታወስ የምንፈልገው ቁም ነገር ስላለ ነው።
 ዛሬ አባ ማቴዎስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን « እንደአቡነ ጳውሎስ በሞት ይወገዳሉ» በማለት የተናገሩትን ቃል ከስምንት ወራት በፊት ማኅበሩ ራሱ በአሉላ ጥላሁን መካነ ጦማር በኩል ተናግሮት ነበር። ያንኑ የእናስወግዳለን ዛቻ አባ ማቴዎስ ሲደግሙት በቤተ ክህነቱ ውስጥ በተቃርኖ የቆሙ አካሎች ስውር መጠፋፋት እንደሚፈጽሙ ማሳያ ምስክር ነው።  በሌላ መልኩም ማኅበሩ ሊታረም የሚችል አካል ስላይደለ እየታየ ባለው የምድራዊ ሥልጣን ግብግብ ውስጥ ማኅበሩ በያዘው መንገድ ከቀጠለ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መጥፋቱ የማይቀር መሆኑንም አስረግጠን ገልጸን ነበር። መቅኖ አጥቶና ባክኖ እንዲቀር ባንፈልግም አንዴ «ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ነው፤አንዴ አቡነ ማትያስ ሊበሉኝ ነው» የሚለው ጩኸት የራሱን ሥፍራ ቆም ብሎ እንዳያይ እያደረገው ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ቢጠፋ፤ መጥፋቱ በሌላ በማንም ሳይሆን በራሱ ተግባር መሆኑን ጠቁመን ነበር።
 መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!!

ይህ ሕንጻ የማነው? የቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን? የመንበረ ፓትርያርክ? የአስመጪና ላኪ? የበጎ አድራጊ ድርጅት?

 የሀገሬ ሰው «ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል» ይላል። ይህ አባባል ለሰሞነኛው የማኅበረ ቅዱሳን የጅቡ በላኝ ጩኸት ይስማማል። ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ነው ሲል በየግል ጋዜጣው ማስወራቱ 22 ዓመታት ኢህአዴግ በሚመራት ሀገር ውስጥ ያልነበረ ይመስላል። ሲነግድ፤ ሲያስነግድ፤ ሲሸጥ ሲለውጥ፤ከግብርና ታክስ ተከልሎ በሚሊዮኖች ብር ህንጻ ሲገነባ በሀገሪቱ ኢህአዴግ ያላየው ወይም የማያውቀው ይመስላል። ኢህአዴግ ማኅበረ ቅዱሳንን በአስማት ይሁን በምትሃት እስከዛሬ ሳያየው ቆይቶ አሁን ለማየት ዓይኑን ሲከፍት ማኅበረ ቅዱሳንን አገኘውና ሊበላው ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ለምን ፈለገ ሲል ለመጠየቅ የተገደደ ይመስላል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለው ተግባሬ ከማኅበረ ካህናቱ ጋር አጋጨኝ፤ በማያገባኝ አስተዳደር ውስጥ እጄን ሳስገባ ተገኘሁ እንዳይል ከመሬት ተነስቶ ኢህአዴግ ሊውጠኝ ነው ወደሚል ቅስቀሳ መግባቱን  ከመምረጡ በስተቀር በምድር ላይ ያለው እውነታ ግን የምርጫ ዘጠና ሰባት ውጤትና ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ስንቱን ፓርቲና የተቃዋሚ መሪዎች እየደፈጠጠ ሲያልፍ ማኅበረ ቅዱሳን ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታዛ ተጠልሎ አልፏል።ኢህአዴግ ቢያጠፋው ኖሮ ያኔ ባጠፋው ነበር። 

ከዚህ በፊት ማኅበሩ እንደጥራጊ አውጥቶ የጣለው ዳንኤል ክብረት ይህን ኢህአዴግ ሊበላኝ ነው የሚለውን የማኅበረ ቅዱሳንን ዘፈን እንዲህ ሲል በደጀሰላም ብሎግ ላይ አውጥቶ ነበር።
«እኔ እንደምገምተው የማኅበሩ አባላት መንግሥትን እንዲፈሩ እና እንዲጠሉ የሚፈልጉ አካላት በአመራሩ ውስጥ ሳይኖሩ አይ ቀርም፡፡ ምንጊዜም አንዳች ከባድ ነገር ሲነሣ መንግሥት እንዲህ ብሎናል፣ በዚህ ስብሰባው እንዲህ ብሏል፣ ሊዘጋን ነው፣ ሊያስረን ነው፣ ሊጨርሰን ነው ከማለት ያለፈ አንድም ቀን በጎ ነገር ስለ መንግሥት የማያነሡ አካላት አሉ»
 ስለዚህ ከዚህ አባባል ተነስተን ልንል የምንችለው ነገር ይህ መንግሥት ሊበላን ነው የሚለው ዜማ እንደስልት የተያዘና መንግሥት በአባላቱ ዘንድ እንዲጠላ የተዘየደ መሆኑ ነው። ከዚያም ባሻገር መሰሪ ስራውን ለመደበቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ለመሳል የታቀደ ጥበብ ሲሆን ጻድቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ኢህአዴግ ሊያጠፋው ስለሆነ ኦርቶዶክሳውያን የሆናችሁ ሁሉ የዚህን መንግሥት መሠሪነት ተመልከቱ ብሎ ክፉ ስዕል ለመስጠት የተፈለገ ብልጠት ነው።
እውነቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ነጋዴ ድርጅት መሆኑ ማንም ያውቃል። የግል ይሁን የአክሲዮን ማኅበር መሆኑ ያልታወቀና የራሱን ሀብት የፈጠረ ተቋም ስለመሆኑም ስራው ምስክር ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከንግድ ተቋማቱና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮቹ ባሻገር የራሱ የሆኑ አባላት ያሉትና የአባልነት መዋጮ የሚሰበስብ ድርጅት ነው። ከዋናው ማዕከል ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁመት የራሱ የሆነ መዋቅርና  ራሱን የቻለ አደረጃጀት ያለው ነገር ግን አደረጃጀቱ በየትኛው የሀገሪቱ  የአደረጃጀት ፈቃድ ላይ እንደቆመ ያልታወቀ መሆኑም እርግጥ ነው። ይህንን የራሱ ተቋማዊ ኅልውና ያለውን ማኅበር በሀብቱ፤ በንግድ ተቋማቱ፤ በመዋቅራዊ አካላቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቆጣጠርና የማዘዝ ምንም ሥልጣን የላትም።  በአንጻሩም ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስር ተሸፋፍኖ እንደመጠለሉ መጠን ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ ላይ የመቆጣጠርና የማዘዝ ሥልጣን እንዳላት ግምት ያለው በመሆኑ መንግሥት ይህን ድርጅት ነክቶት አያውቅም። ስለዚህ ይህንን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኒቱም፤ መንግሥትም ሳይመለከቱት ከሁለት ወገን ቁጥጥር ነጻ ሆኖ 22 ዓመት ዘልቋል። 
 «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንዲሉ ሆኖ ማኅበሩን ማነህ? ምንድነህ? የት ነህ? ምን አለህ? ምን አገባህ? የሚሉ ካህናትና የአመራር አካላት ተባብረው በመነሳት መጠየቅ ሲጀምሩ ጥቂት ሟሳኞችና አሟሳኞች ወደሚል ሃሳብ ለመውረድ ተገዷል።  በምንም ደረጃ ያሉ ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳንን መክሰስ መቻላቸው የማኅበሩን ማንነት ማሳያው ተግባሩ እንጂ ክሱ አይደለም።  እየተከሰሰ ያለው ማኅበር በተግባሩ ያልታወቀ ማኅበር ባለመሆኑ በሟሳኞችና አሟሳኞች የቃላት ጫወታ እየፈጸመ የቆየውን ሸፍጥ ሸፍኖ ማስቀረት አይቻልም።
ማኅበረ ቅዱሳን በተግባር በሌለው ሥልጣንና መብት መናፍቃን ናቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን በራሱ ጥቁር መዝገብ አስፍሮ አስደብድቧል፤ ሰልሏል፤ ስም አጥፍቷል፤ አስፈራርቷል፤ እንዲሰደዱ አድርጓል። ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያኒቱ ስም መጽሔትና መጻሕፍትን፤ ካሴትና ቪዲዮ፤ አልባሳትና ንዋየ ቅድሳትን ከታክስና ከቀረጥ ነጻ ሆኖ ነግዷል። የማኅበረ ቅዱሳን አቋም የሚቃወሙ ሁሉ ጠላቶቹ ናቸው። የሚደግፉት ደግሞ ጳጳሳቱ ሳይቀሩ ወንጀል ቢኖርባቸው እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ታማኝ አገልጋይ ተደርገው ዜና ይሰራላቸዋል፤ ሙገሳ ይሰጣቸዋል። አባ እስጢፋኖስን ማንሳት ይቻላል። ጠላቶቼ ከሚላቸውና ስማቸውን ሌሊትና ቀን ሲያጠፋቸው ከቆዩት ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ደግሞ የጥላቻ የአፍ መፍቻው ናቸው። ሌሎቹም ፈርተው አንገታቸውን ደፍተውለታል። የተገዳደረውን አንገት ያስደፋል፤ አለያም ቀና ካለ አንገቱን ይሰብራል።  ሌላው ቀርቶ ሲያመሰግናቸው የነበሩትን አዲሱን ፓትርያርክ ጠላቶቼ የሚላቸውን ሰዎች ሲቀጣ በቆየበት መልኩ በስም ማጥፋት ቅጣት ናዳውን እያወረደባቸው ይገኛል። ለራሱ ኅልውና ብቻ የሚጨነቅ፤ ካልመሰለው ደግሞ ሲያወድሳቸው ለነበሩት ሳይቀር ግድ የሌለው ማኅበር ስለመሆኑ ከድርጊቱ ተነስቶ መናገር ይቻላል።  ወትሮውንም ሸፋጭ ነጋዴ ገንዘቡን እንጂ ወዳጅና እውነት በእሱ ዘንድ ዋጋ የሌላቸው ስለሆኑ የሚያስበው ጊዜያዊ ትርፉን ብቻ ነው። በዚህ ዙሪያ ማኅበሩ አሸንቅጥሮ የጣለውና ለተቀበለው የእጅ መንሻ በውጪ እንዳለ የሚለፈልፈው ዳንኤል ክብረት ማኅበሩ ስለግለሰቦችና ስለቤተ ክርስቲያኒቱ ደንታ ቢስ እንደሆነ ያጋለጠው እንዲህ ሲል ነበር።
«ዲያቆን በጋሻው ማስተማር የጀመረው መቼ ነው? ማኅበሩ በነዲያቆን በጋሻው ላይ ሃሳብ ዛሬ መሠንዘር ለምን ጀመረ? በጋሻው ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው ብሎ ስላሰበ አይደለም፡፡ በጋሻው ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ስለ ተናገረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም ያልተናገረው ማኅበር ስሙ ሲነሣ ቤተ ክርስቲያን ተነካች ብሎ ተነሣ፡፡ ማኅበሩ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝ የጀመረው መቼ ነው? «እርሳቸው ማኅበሩን ሊያፈርሱ ነው» ብሎ መሥጋት ከጀመረ በኋላ፡፡ አባ ሠረቀንም ቢሆንኮ ዛሬ ዛሬ በእምነት ችግር ይከሳቸዋል እንጂ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው ዋናው ችግሩ ማኅበሩ መነካቱ ነው፡፡ አባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳንን ሳይነኩ የፈለጉትን ቢሆኑ ኖሮ አይናገራቸውም ነበር፡፡ ባለፈው ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ችግር ሲፈጠር፣ ዝምታን መርጦ የነበረው አመራር የመንግሥት አካላት ከቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ስለ ማኅበሩ ሲያወያዩት ግን አገር ይያዝልኝ አለ፡፡ የአዋሳ ምእመናንን ችግር በዝምታ ያለፈው አመራር አባ ሠረቀ አንዳች ነገር ተናገሩ ብሎ ድምፁን አሰምቶ ተናገረ፡፡ እነዚህ እና መሰል ሁኔታዎች አመራሩ የሚቆረቁረው ማኅበሩ ሲነካ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትነካ አለመሆኑን ያመለክታሉ» ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ከራሱ በላይ ማንንም እንደማይወድ እርግጥ ነው። የራሱን ድክመት ቆም ብሎ በመገምገም ለመስተካከል ከመሞከር ይልቅ አንገቱን በማደንደን ወደ ስድብ፤ ዛቻ፤ ማስፈራራትና ስም ማጥፋት ይሮጣል። ይህም በመሆኑ ማኅበሩ የሚጠፋው በራሱ ተግባር እንጂ በቅንነቱ ወይም በቀናዒነቱ አይደለም። ይህም ማለት ግን ቀናዒና ቅን አባላት የሉትም ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ቅን አባላቱ ጠማማውን አመራር ማስተካከል የሚችል አቅም የላቸውም። ማኅበሩ ራሱ የሚመራው በቡድናዊ ስልት ስለሆነ በቡድን ይመታሉ፤ በቡድን ይወገዳሉ። 
ማኅበረ ቅዱሳን በፖለቲካው ዙሪያ ከምርጫ 97 በፊትም ሆነ በኋላ ስላለው ሁኔታ መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው ይሰማል። በዚህ ዙሪያ መንግሥት ያለውን መረጃ እስኪያወጣ ድረስ የምንለው ነገር የለም። ነገር ግን ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያምሳት መቆየቱን፤ እጁን እያስገባ ሲኖዶሱን ሳይቀር እንደሚጠመዝዝ እናውቃለን። ማኅበሩ ደፋርና የልብ ልብ የተሰማው አንዳንድ የሲኖዶስ አባላት ተጠግቶ የጉባዔ ሃሳብ በራሱ መንገድ እስከመጠምዘዝ የመድረሱን አቅም እየለካ በመሄዱ ነው። ዛሬ ላይ ያ ነገር የለም። ፓትርያርክ ማትያስ ለዚህ የማኅበሩ ሃሳብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ከኢህአዴግ ጋር ተመሳጥረው ሊያጠፉኝ ነው እያለ ስም ወደማጥፋት ወርዷል። በተቃራኒው ደግሞ ማንም እንደማያጠፋው በሚገልጽ ጀብደኝነቱ ፓትርያርክ ጳውሎስም እንደዚሁ ሊያጠፉኝ ሞክረው እንደማያዋጣቸው አውቀው አጃቸውን ከእኔ ላይ ለማንሳት ተገደዋል በማለት ለፓትርያርክ ማትያስ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ እየሰራ ይገኛል። እጅዎን ከእኔ ላይ የማንሳትን ጉዳይ ችላ ሳይሉ ከቀድሞው ፓትርያርክ ትምህርት ውሰዱ በማለት ማሳሰቢያ እየሰጠ መሆኑ ነው። 
የሚፈራው ከተገኘ ጥሩ ጀብደኝነት ነው፤ ነገር ግን ባለቀ ጊዜ ማላዘን ዋጋ የለውም። ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያኒቱ ስንት ችግር ባለባት ሰዓት ራሱ ችግር ፈጣሪ ሆኖ ካለቦታው የተገኘ ማኅበር ስለሆነ ተገቢ ቦታውን መያዝ ካለበት ሰዓቱ አሁን ነው። ማኅበረ ካህናቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር አባላት ጠንክሮ መታገል የሚገባችሁ ወቅት ቢኖር ዛሬ ነው። ማኅበሩ ቁጭ ብሎ አዋጭ የሆነውን መንገድ መቅረጽ ካለበት ቶሎ ብሎ ይህንኑ እንዲፈጽም ምክር እንለግሰዋለን። የአክሲዮን ማኅበር፤ የሃይማኖት ተቋም፤ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም የተሻለ ነው ብሎ የደረሰበትን ውሳኔ ወደተግባር መቀየር ካለበት ቀኑ ሳይመሽ በብርሃኑ ይሆን ዘንድ ልናሳስበው እንወዳለን። ሲሆን ዘንድሮ፤ ካልሆነም በቀጣዩ ዓመት፤ ቢረዝም፤ ቢረዝም አንድ ቀን ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጉያ እንደመዥገር የተጣበቀበት ቀን እንደሚያበቃ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ማኅበሩና ተግባሩ፤ ካህናቱና አስተዳደሩ መቼም ቢሆን አሁን ባለው መንገድ አብረው መጓዝ አይችሉምና ነው።  ከዚህ ሁሉ ፓትርያርኩም፤ ካህናቱም፤ አመራሮችም፤ መንግሥትም ይህንን ማኅበር ቦታ የማስያዙን ጉዳይ ችላ ሊሉት አይገባም። ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖር ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖርም ትኖራለች!!!  «ማኅበረ ቅዱሳን ከሌለ ቤተ ክርስቲያን ትጠፋለች» የሚለው ራሱ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ነው።