Tuesday, May 13, 2014

በውስጡ ቀና መንፈሳዊ አባላት መኖራቸው ብቻ የሃይማኖት ማህበር አያሰኘውም!


(ከወልደገብርኤል ስሁል)
 
የየትኛውም እምነት ተከታዮች መንፈሳዊ ህይወትና የሃይማኖት ቀኖና በሚመለከቱ ጉዳዮች ያሻቸው ማመንና መከተል ይችላሉ፤ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር የሚለውን መርህ አክብረው ሁለቱን ሳያደበላልቁ እስከተጓዙ ድረስ። መጋቢት 1983 “በአቡነ ደርግ” ብላቴ ላይ የተቋቋመው ማ.ቅ. ዋና ዓላማው ጠመንጃ የታጠቀ የቅዱሳን ብርጌድ ሁኖ በማርክሲዝም የተከዳውን አምባገነን መንግስት የማዳን ተልእኮ ይዞ ሲሆን፤ ይህ ካልተቻለም “የብሄራዊ እርቅ መንግስት ይመስረት” በማለት ባቋራጭ የመንግስት ስልጣን ሊጨብጡ ይቋምጡ ለነበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን (ማርክሲዝም ባዶ ሜዳ ላይ ጥሏቸው በመሄዱ የቆጫቸውና የደርግ ለሞት መቃረብ “ንስሃ” ለመግባት የተገደዱ የደርግ ቀኝ እጆች) በድህረደርግ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ይሆናቸው ዘንድ ተጠፍጥፎ የተሰራ ማህበር ነው። መስራቾቹም የደርግ ደህንነት ያሰባሰባቸው አንዳንድ “ምሁራን”ና “መንፈሳዊ አባቶች” ሲሆኑ በህቡእ እንዲመሩት የተሰየሙትም ከነሱ የተውጣጡ “ታላላቅ ወንድሞች” ናቸው(ለማንም ግልጽ በሆነ ምክኒያት ስማቸውን እዚህ ላይ መጥቀስ ሳያስፈልግ)። ስለዚህ መስራቾቹና ህቡእ መሪዎቹ ፖለቲከኞች ናቸው፤ የተመሰረተበት ዓላማ ደግሞ መንፈሳዊም ሃይማኖታዊም አልነበረም፤ አሁንም አይደለም። በውስጡ ቀና መንፈሳዊ አባላት መኖራቸው ብቻ የሃይማኖት ማህበር አያሰኘውም።

Monday, May 5, 2014

«ኢየሱስ ለእኔ እንዲህ ነው፤ ለእናንተስ?»



የኦሪቱ የኃጢአት ማስተስርያ
ኢየሱስ በኔ ኃጢአት ምትክ ሞቶ ሕይወትን ይሰጠኝ ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ህያው በግ ነው።
ዮሐንስ ወንጌላዊ እንዲህ ሲል እንደተናገረ;
 «በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ዮሐ 1፤29

እስራኤል ዘሥጋ የተባሉት የብሉይ ኪዳን ሕዝቦች እግዚአብሔር ከሰጣቸው ተስፋ መካከል አንዱ ኃጢአት ቢሰሩ ወይም ቢበድሉ ከዚህ መንጻት የሚችሉበትን መንገድ  አሳይቷቸው ነበር።  ይኼውም
 «ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል» ዘሌ 5፤15
ኃጢአተኛው ይህንን የኃጢአት ወይም የበደል መስዋዕት በታዘዘው ደንብ መሠረት ለሊቀ ካህናቱ ካቀረበ በኋላ እጁን በመስዋእቱ ላይ ጭኖ ከጸለየለት በኋላ ኃጢአተኛው ለሰራው ኃጢአት ምትክ ማስተሰርያ ሆኖ አንገቱን ይቆለምመዋል። ከደሙም የመሰዊያ ግድግዳው ላይ ይረጨዋል። ያን ጊዜም የኃጢአት መስዋዕት ሆኖ ኃጢአተኛው ከሰራው ኃጢአት ነጻ ሆኖ ይመለስ ነበር።
 ይህ ከኃጢአት ለመንጻት የሚደረግ የመስዋዕት ስርዓት ኃጢአት በሰሩ ቁጥር መቅረብ የሚገባውና ኃጢአተኞች ሁሉም ለየራሳቸው ያለማቋረጥ ለማቅረብ የሚገደዱበት የመንጻት ደንብ ነበር።  ይህን መስዋዕት ሁልጊዜ ለመፈጸም ያስገደደው ምክንያት ሊቀካህኑም ሆነ የሚሰዋው በግ  ዘላለማዊ ስላልነበሩና ብቃት ስለሚጎላቸው ነበር።   ሊቀካህኑ ለራሱ መስዋዕት እንዲያቀርብ ይገደዳል። በጉም  ነውር እንዳይኖርበት ጥንቃቄ ይደረግበታል።  እንደዚያም ሆኖ ፍጹም ማዳን አይችሉም።
  
«ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል» ዕብ 5፤1-3

ስለዚህ ይህንን ኪዳን በማስቀረት እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን ለመግባት ወዷል። በዚሁ መሠረት እነዚህን አምስት ነጥቦች የሚያሟላ ነው ፤
1/ ኃጢአትን የሚያስተሰርየው ሊቀ ካህን በሞት የሚሸነፍ መሆን የለበትም።

2/ ሊቀ ካህኑ በመሐላ የተሾመ መሆን አለበት።

3/ ለራሱ መስዋዕት ማቅረብ የማይገባው ንጹህ መሆን አለበት።

4/ ሊቀ ካህኑ እንደኦሪቱ በግ የሚያቀርብ ሳይሆን ራሱ ለኃጢአተኛው በግ ሆኖ መሰዋት አለበት።

5/ ኃጢአተኛው ወደሞተለት ሊቀካህን በመቅረብ መናዘዝ እንጂ ስለኃጢአቱ በግ ማቅረብ አይጠበቅበትም።
ስለዚህ ይህንን የሚያሟላ መስዋዕት እግዚአብሔር አብ ልጁን ወደምድር ልኳል። እሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ነው። 
«ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው» ዮሐ 3፤13 
ኢየሱስ በመሃላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀካህን ስለሆነ ዛሬ ሌላ ሊቀካህን የለንም። የኦሪቱ የኃጢአት መስዋዕት በግ ከኃጢአት ያነጻ ነበር። የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር በግ ደግሞ ላመኑበት ለዘለዓለም ያድናል። ከዚህ ውጪ የመዳን መንገድ ለሰው ልጅ አልተሰራም። ኢየሱስም «መንገዱ እኔ ነኝ» ያለውም ለዚህ ነው። ሌላ የመዳኛና የመጽናኛ መንገድ በጭራሽ በዚህ ምድር በሌላ በማንም የለም።

«እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።» ዕብ 7፤20-27
ስለዚህ ኢየሱስ በሞቱ ሞቴን ያሸነፈ፤ የሕይወቴ ቤዛና በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። በእርሱም አዳኝነት አምናለሁ። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ዮሐ 3፤36 እንዳለው የዘላለምን ሕይወት በሞቱ በኩል አግኝቻለሁ። ከሌላ ከማንም የድኅነትን ተስፋ አልጠብቅም። በኃጢአት ብወድቅ የምነጻው፤ የምነሳው በእሱ ብቻ ነው። የምለምነው፤ የምጠይቀው፤ የምማጸነው እሱን ብቻ ነው። በሩ እሱ ስለሆነም «አንኳኩ ይከፈትላችኋል» በማለት የሰጠኝ የመዳን ተስፋ የማይለወጥ ነውና። ኢየሱስ ለእኔ እንዲህ ነው። እናንተስ የመዳናችሁን ተስፋ የምትጠባበቁት ከእነማን ነው?

Sunday, May 4, 2014

አንዳንድ ቅዱሳን በጣም ያስቁኛል...፪ (ካለፈው የቀጠለ)


(by Tedy Sih)

ስለማህበረ ቅዱሳን ስውር አመራር የሙሉጌታ ማደናገርያና የዳንኤል እውነታ

ማህበሩን ከጥንስሱና ከአመሰራረቱ ጀምረን በተጨባጭ ለምናውቀው እንጂ ህቡእ ገጹ ለብዙሃኑ አባላት እስከቅርብ ጊዚያት ግልጽ አልነበረም። አሁን ግን ስለማህበሩ ቆም ተብሎ ማሰቢያና ለርኩሰቱ መላ መፈለጊያ ጊዜ መጥቶ በር እያንኳኳ ነው። በቤተክርስቲያኗ ላይ እስካሁን ያደረሳቸውና በሃገርም ደረጃ ሊያደርሳቸው የሚሰናዳባቸው ነገሮች ፈጥጠው ወጥተዋል። የማሀበሩ እኩይ ስነፍጥረት፣ እኩይ ዓላማና እኩይ አካሄድ እርቃኑ እየወጣ ነው። ይህም ሃቅ ዘግይተውም የተቀላቀሉትን ጨምሮ ለአብዝሃኞቹ ቀና አባላቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። የቤተክርስቲያኗ ምእመናን፣ የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ የሆኑት የሃገሪቱ ህዝቦች፣ እንዲሁም መንግስት ከእንቅልፋቸው በቅርቡ እየነቁ መጥተዋል። የማህበሩ ማንነት አጠያያቂ መሆን በጀመረበት በዚህ ወቅትም ከራሷ ከቤተክርስቲያና እና ከማህበሩ ከፍተኛ አመራሮችም እያፈተለኩ የሚወጡት መግለጫዎች ይበልጥ እርቃኑን እያስቀሩት አደገኛ ባህርያቱ ወደ አደባባይ እየተገለጠ መታየት ጀምሯል። ባለፉት ሳምንታት በማህበሩ አመራሮች የተሰጡ መግለጫዎች ላፍታ ብንመልከት እንቆቅልሹን በደንብ ይፈቱልናል። የመምህር ሙሉጌታ ሃይለማርያም ሃሰትና የዲያቆን ዳንኤል ክብረት እውነት ተደምረው ባለፉት ክፍሎች ስለማህበሩ የገለጽኳቸውን ነገሮች እውነትነት ይበልጥ ያረጋግጣሉ።
ማህበሩ ግልጽ ጥያቄዎች በመጡበት ወቅት የማህበሩ ዋና ጸሃፊ መምህር ሙሉጌታ ሃይለማርያም ከድንጋጤ የሚመስል ማብራርያ ሰጥቷል። መምህር ሙሉጌታ እንቁ መጽሄት ጋር ባደረገው አስገራሚ ቃለ ምልልስ ማህበሩ ከተቃውሞ ፖለቲካ ጋር ምንም ንክኪ እንደለለው በማበከር ስጋትና ምጸት በቀላቀለ ችኮላ አብዛሃኞቹ የማሀበሩ አባላት የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው ብሏል። ይህንን ለማስረዳት የተጠቀመበት አመክንዮ ደግሞ አባላቶቻችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡ ስለሆኑና በነዚህ ስፍራዎች ደግሞ ኢህአዴግ ሁሉንም አባላቱ አድርጎ ስለሚመለምል የኛም አባላት ብዙዎቹ እነሱ ናቸው የሚል ነው።
ቃለምልልሱም ብዙዎቹን የማህበሩ አባላት ከማስቆጣቱም በላይ ከእውነት የራቀ ነበር። ቁጣ የቀሰቀሰውም ይበልጥ ጥያቄዎቸ አስነስቶ ከማህበሩ አባላት ጋር ብቻ የሚነገር ግን ለማህበረሰቡ በግላጭ ለገበያ የማይቀርብ መረጃ እንዲወጣ በር ይከፍታል በሚል ነው። በዚህ መልኩም ህቡእ ገጽታው እንዳይጋለጥ በሚሹት ሁሉ የናሩ ነቀፌታዎች ተሰንዝረዋል። የነቃፊዎቹም ስጋት የማህበሩ አባላት የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው በመባሉ አይደለም። አባባሉ ትክክል ስላለመሆኑ ዋና ጸሃፊውና ነቃፊዎቹም ሆኑ ከነሱ ውጭ ያለ ማንኛውም ወገን እንደማያጣው ያውቃሉና። የስጋቱና የቁጣው ምንጭ የማህበሩ አባላት ካላቸው የብሄር ወይም የፖለቲካ ወገንተኝት ተነስቶ ሲዘረዘር ዋና ጸሃፊው በሃሰት የለጠፈው ኢህአዴግነት ሳይሆን ማህበሩ በተልእኮና በገቢር የጨበጠው እውነተኛ ማንነት(ተቃዋሚነት) ስለመሆኑ ከራሱ ከአመራሩ ግልጽ ጥቆማና እማኝነት ተመስርቶ እንዳይታወቅ በመፍራት ነበር። የፈሩት ግን አልቀረም። መምህር ሙሉጌታ በቃለምልልሱ የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ስም ጠቅሶ ስላንቋሸሸ ዳንኤል በሰጠው ምላሽ ስውር አመራር እንዳለ ምናልባትም ለመጀመርያ ጊዜ ከውስጥ ሰው ይፋ ተደረጓል። ዳንኤልም የምናውቀውን ያክል የማህበሩን ህቡእ ገጽታ ደፍሮ ባያፍረጠርጥም ስለ ስውር አመራሩና ስለ እኩይ ድርጊቶቹ ከውስጥ አዋቂ በሚሰጥ እማኝነት ሰጥቷል።
ዳንኤል አደባባይ ካዋላቸው የማህበረ ቅዱሳን አካሄዶችም የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እነሱንም አጠር አድርጌ በማስቀመጥ ከማህበሩ ፖለቲካዊ ተልእኮ አንጻር ትርጉማቸውን እገልጻለሁ።
ማህበሩ ስለ ቤተክርስቲያኒቱ ግልጽ መረጃ ሳይጨብጥና የት እንደሚያደርሳት ግልጽ ግብ ሳይኖረው ስለ መጓዙ ተናግሯል።
(መጀመሪያውንም በመንፈሳዊ ቤተክርስቲያኗን የሚደግፍ ሃይማኖታዊ ተልእኮ ያልነበረው ስለመሆኑ ይነግረናል። አመራሩም ቤተክርስቲያን ተኮር ስትራቴጂ የሌለውና የፖለቲካ አባቶቹ ጭፍን ፈረስ ስለመሆኑ በማያሻማ ቋንቋ ይመሰክራል።)
አመራሩ ማህበሩ ለቤተክርስቲያኗ አገልግሎት የተመሰረተ ሳይሆን ቤተክርስቲያኗ ለማህበሩ አገልግሎት ወደሚል አመለካከት መዞሩ፣
(አመራሩ ቤተክርስቲያኗን ለህቡእ ተልእኮው መሳካት ሊቆጣጠራት ይፈልጋል እንጂ እሷ የምትፈልገውን አገልግሎት ሊሰጥ አይሻም ። ሲጀምር የሚያገለግላት መስሎ ቢገባም ቀስ በቀስ ለተልእኮው ሊገለገልባት ወደሚያደርግ አቅጣጫ ማምራቱን ያሳየናል።)
ተሃድሶን ለማጋለጥ እንጂ ተሃድሶን እንዲፈጠር ያደረገውን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት ስትራቴጂ የሌለው መሆኑ፣
(ማህበሩ የቤተክርስቲያኗን መሰረታዊ ቀኖናዎች እና አስተምህሮዎች ለመጠበቅም ሆነ ለማስፋፋት የቆመ ስላለመሆኑ ያስረዳናል። ይልቁንም የተሃድሶን አደጋ በተጋነነ ምስል እያቀረበ ብጥብጥ ህውከትና መመሰቃቀል ቤተክርስቲያኗን እንዳይለያት በትጋት እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ያስረዳል።)
የማህበሩ አመራር የእለት ተለት ነገሮችን ለማየት የሚሰበሰብ፣ ማህበሩ ስራውን ትቶ አባላቱን እንደሚሰልል፣ አባላቱ የሚወገዙትና የሚታገዱትም ማህበሩን ከነኩ ወይም የተለየ አቋም ከያዙ እንጂ ለቤተክርስቲያኗ እምነትና አስተምህሮ ወይም ለመንፈሳዊው ምግባር አደጋ ናቸው ተብሎ አለመሆኑ ገልጿል፣
(ማህበሩ በየእለቱ በሚከናወኑ ዓለማዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ፣ አባላቱንም ማንነታቸውንና አመለካከታቸው የተለየ እንዳይሆን ሲል በየጊዜው እንደሚከታተል ብሎም ህቡእ ተልእኮውና እንቅስቃሴዎቹ እንዳይታወቁበት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሚስጢራዊ ጉዞ እያካሄደ ስለመሆኑ አስረጅ ነው።)
ማህበሩ ስውር አመራር ያለው መሆኑ፣ ስውሩም አመራር ጥላቻውን የሚገልጽበት ሶስት መንገዶች ያሉት ስትራቴጂ እንዳለው፣ እነሱም ስለሚጠላው ሰው ክፉ በመናገር ስለሚጠላው ሰው የሚያውቀውን ጥሩ ነገር ባለመናገር እና ስለሚጠላው ሰው ተራ ነገር በመናገር የሚገለጹ ስለመሆናቸው፣ ከነዚህ በተጨማሪም ስውር አመራሩ የማስከፋትና የጭር ሲል አልወድም ስትራቴጂ ስለመያዙ አስረድቷል።
(ይህ ደግሞ በነ አቡነ ሺፈራው ተነድፎ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የአሁኑን መንግስት ጥላሸት እየቀቡ ተቀባይነት የመንሳትና ድሮ የነበሩትን ሁሉ ቅዱስ አድርጎ የመሳል ስትራቴጂ በማህበሩ ስውር አመራር እንዴት እንደሚተገብረው ይጠቁመናል።ማህበሩ በግልጽ በሚታወቀው አመራሩ ሳይሆን በህቡእ አመራሩ ቁጥጥር ስር መሆኑ ይህም አመራር የጥላቻ ስትራቴጂ እንዳለው፣ ስለሚጠላቸውም ወገኖች( መንግስትንና የቤተክህነትን አመራር) ክፉውን ብቻ በመናገር በጎ ስራቸውን ባለመናገር እና ተራ አሉባልታ ፈጥሮ በማጥላላት የማስጠላት ስልት እንደሚተገብር ይመሰክራል። እውነትና ሃሰት አዛብቶ ጥላቻ ማራመጃ ከማድረጉ በተጨማሪም ጭር ሲል አልወድምን ሆን ብሎ በመከተል በማህበሩ በቤተክርስቲያኗ እና በሃገሪቱ ላይም አጠቃላይ ብጥብጥ በሚፈጥር የዓመፃ መንገድ ላይ መቆሙን ያሳያል።)
ማህበሩ በእውቀትና በተጨባጭ መረጃ ተመስርቶ ስራ ከመስራት ይልቅ በአሉባልታና በስሚ ስሚ እንደሚንቀሳቀስ እቅዶቹን 50 በመቶ ያህሉን እንኳን መስራት ያልቻለና እስካሁንም የባለጉዳይ መስመር እንጂ የሃሳብ መስመር የሌለው መሆኑ፣ የማህበሩ አመራር ተሰብስቦ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እንደገና ለብቻቸው ተሰብስበው ባሻቸው የሚቀይሩ ታላላቅ ወንድሞች እንዳሉ፣ ከነዚህ አመራሮቹም ውስጥ የማኅበሩ አባላት መንግሥትን እንዲፈሩ እና እንዲጠሉ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው፣ እነሱም ምንጊዜም አንዳች ከባድ ነገር ሲነሣ መንግሥት እንዲህ ብሎናል፣ በዚህ ስብሰባው እንዲህ ብሏል፣ ሊዘጋን ነው፣ ሊያስረን ነው፣ ሊጨርሰን ነው ከማለት ያለፈ አንድም ቀን በጎ ነገር ስለ መንግሥት እንደማያነሡ፣
(ማህበሩ በግልጽ እቅድና በአመክንዮ የተመሰረተ መርህ ከመመራት ይልቅ በአሉባልታና በበሬ ወለደ እንደሚነዳ፣ በግልጽ የሚታወቀው የማህበሩ አመራር የስውር አመራሩ አሻንጉሊት ስለመሆኑና ወሳኝ ወይም አድራጊ ፈጣ የሆነው ስውር አመራሩም በታላላቅ ወንድሞች እጅ እንደተያዘ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። ከታላላቅ ወንደሞችም መካከል በተለይም የነ ካህን ሽፈራው የድሮ ቀረ ማንዋል እንዴት ባለ ዘዴ ቤተክህነትን እያመሰ እንዳለ በቂ ምስክርነት ይሰጣል። ይህም ዘዴ ማህበሩና አባላቱ የአሁኑን መንግስት እንዲፈሩት፣ ያለተጨባጭ ምክኒያትም እንዲጠሉት እና በመከበብ ስሜት እንዲታጠሩ በማድረግ ለአመጽ እንዲነሳሱ ስለሚቀሰቀሱበት አጠቃላይ ሁኔታ በቂ ጥቆማ ይሰጣል።)
ዲያቆን ዳንኤል የገለጻቸው እነዚህንና ሌሎች በማህበሩ ውስጥ የታመቁ ሚስጥሮች በክፍል አንድና በክፍል ሁለት ባቀረብኳቸው ተከታታይ ጽሁፎቼ የተገለጹትን እውነታዎች ተጨማሪ ማስረጃ ይሰጣሉ። በተለይ የሱ ምስክርነት ክብደት የሚያሰጠውም ከጅምሩ አንስቶ ማህበሩን በይፋ እየመራ የነበረ በመሆኑ ከሱና ከመሰል ወንድሞቹ በላይ ሁነው ታላላቅ ወንድሞች በስውር ለቅዱሳኑ ማህበር ልዩ አመራር እንደሚሰጡ ከሱ በላይ እማኝ መጥራት ስለማይቻል ነው። እርግጥ ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ ገላልጦ ባይጽፍም በመምህር ሙሉጌታ አስተያየት ተቆጥቶም ቢሆን ዳንኤል ይህንን ሲጽፍ አጽንኦት የሰጠው ስለስውሩ አመራርና ከቤተክርስቲያን አገልጋይነቱ የሚጻረሩ ፖለቲካዊ ገጾቹ ላይ ነው። ተወደደም ተጠላም ዳንኤል እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ “አውላላ ሜዳ ላይ የተኛውን በሬ፣ ነካክተው ነካክተው አደረጉት አውሬ።” እያለ ተማርሮ ስለማህበረ ቅዱሳን በልቡ ብቻ ይዟቸው የነበሩትን እውነቶች አጋልጧል። ማህበረ ቅዱሳንና የታላላቅ ውነድሞቹ ስውር አመራርም እርቃኑን ወጥቷል። የዳግመ ደርጊዝምና የዳግመ ሞናርኪዝም ፈረስ እንደሆነ ለምናውቀው ብዙ ባያስገርምም ቢያንስ እስካሁን ስለማህበሩ ሃቁን ለማያውቁት ግን የእውነት ብርሃን ፈንጥቆ ጨለማውን ያጋለጠ ምስክርነት ስለመሆኑ አንዳች ጥያቄ የለውም።
በዳንኤል ጽሁፍ የተደሰቱ አባላት ያሉትን ያህል ማህበሩን ለበለጠ አደጋ አሳልፈህ ሰጠህ ብለው የተከፉበትም ብዙ ናቸው። ጽሁፉን ተከትለው በየብሎጎች የወጡት አስተያየቶችም ይህንን ያሳያሉ። አንዳንዶቹ ድረ ገጾችም ጽሁፉን ላፍታ አትመው ካወጡ በኋላ ከገጾቻቸው አንስተውታል። ይህም በማህበሩ የተጠለለው ህቡእ ክንፍ እውነተኛ ማንነት ይፋ እንዳይወጣ የተደረገ ስልት ነው። በተለይ የማህበሩ ታላላቅ ወንድሞች በጣም ተደናግጠው ጉዳዩን ለማዳፈን የቻሉትን ያህል እየተሯሯጡ ነው። ከማዳፈኛ ስልታቸውም መካከል ዳንኤልን በማስፈራራት ወይም በማባበል ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ ሁሉም ነገር አማን የሚል ምስል ለምስጠትና ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ይጥራሉ። ለማባበል ከሚመስለው ጥረታቸውም አንዱ ጽሁፉ በዳንኤልና በሙሉጌታ አለመጣጣም የመጣ ችግር እንደሆነ ወይም ማህበሩ እንዴት ተሃድሶዎችን እንደሚዋጋ በሁለቱ አመራሮች የታየ የሃሳብ መለያየት ብቻ እንደሆነ ለመተንተን ሲጥሩ ይስተዋላሉ። ጎን ለጎን ደግሞ ዳንኤል ብዙ ጽሁፎች እንደጻፈ አንዳንዶቹም በብእር ስም እንዳሳተማቸው በመጠቆም ይቅርታ ካልጠየቀ ሚስጥሩን እንደሚዘከዝኩበት ፍንጭ እየሰጡም በአንዳንድ መጽሄቶች ባወጧቸው ጽሁፎች በግልጽ አስፈራርተውታል። በዛቻው ይሁን በማባበሉ ወይም በሁለቱ ተንበርክኮ ዳንኤል ይቅርታ ጠይቆ ከማህበሩ አመራር ጋር እንደታረቀ እየተነገረ ነው።
ይህ ሁሉ ሽር ጉድ ሰሚን ለማደናገር አልያም እርቃኑ የወጣውን የማህበሩ የውስጥ ጉድ ለማዳፈን ካልሆነ በስተቀር ስለማህበሩ እውነተኛ ማንንትም ሆነ በሱ ላይ ዳንኤል የሰጠውን እማኝነት በቅንጣትም የሚለውጥ ነገር አይደለም። እንዲያውም እውነቱን ለማዳፈን ተብሎ የሚደረገው ርብርብ ይበልጥ ጥያቄዎችን እንድናነሳና የማህበሩ የጥፋት ርኩሰት ከተቀደሰው ስፍራ እንዲወጣ አጥብቀን እንድንሻ ያስገድዳል። አዎ! የእግዚአብሄር ቤት የወንበዴዎች ዋሻ አይደለምና ማህበሩን ፈረሳቸው ያደረጉት እርኩሳን መናብርት ባስቸኳይ ይውጡ እንላለን። ይህ እንዲሆንም ከማህበሩ ታላላቅ ወንድሞች መካከል ፖለቲካዊ አመራር በመስጠት ቀንደኞች የሆኑትን በመጥቀስ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ ተቋሞቻቸውን የመንቀሳቀሻ ማእከላት በማድረግ እየፈጸሟቸው ስላሉ ርኩሰቶች ጥቂት በመዘርዘር ወደ ጽሁፌ ማጠቃለያ ልሂድ።...”

( ከመልከፀዴቅ ጽሁፍ/ “የጥፋ ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ሲቆም” ክፍል‐፫/ ተቀንጭቦ የተወሰደ)