Tuesday, October 30, 2012

አቶ ኑረዲን ማናቸው?



ጌታችን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ባለች አንዲት ምኩራብ ሲያስተምር በቆየበት ወቅት  ከፈሪሳዊያን አንዳንዶች ቀርበው እንዲህ ሲሉ መናገራቸውን  አንብበናል።
«በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው። ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት» ሉቃ 1331
ጌታችንም ሲመልስላቸው «እንዲህም አላቸው፦ ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ። እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት» ሉቃ 1332 አላቸው።
እንግዲህ በሰይጣን መንፈስ የሚነዳው ሄሮድስ፤  ክርስቶስ ኢየሱስን ለመግደል ቢፈልግም በጉ ከመታረዱ በፊት የፈውስና የማዳን ጊዜ እንዳለው በማመልከት የበግ ጠላት የሆነው፤ ቀበሮው ሄሮድስ ጥቂት እንዲታገስ በቀበሮ መስሎ መናገሩን እንመለከታለን።
እንደዚሁ ሁሉ «ኢትክሉ ገቢር ተቀንዮ ለክልዔ አጋእዝት» እንዳለው መጽሐፉ ለጌታ ከመገዛት ይልቅ  መንግሥተ ንዋይ ራሳቸውን በግልጽ ያስገዙና ከሥጋ አልፈው አጥንት ዘልቀው ይግጣሉ ለሚባሉት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የአዲስ አበቤው ካህን «አቶ ኑረዲን» የሚል ስመ ተቀጽላ አውጥቶላቸዋል።
«ንቡረ እድ» የሚለውን የማእርግ ስም ወደ «ኑረዲን» ቀይሮ «ኑረዲን ኤልያስ» በማለት ይጠራቸዋል። ለምን? ቢሉ ኑረዲን ኤልያስ ከዚህ ቀደም የነበረውን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለቅጥር የሚከፈል የጉቦ ዋጋ እንደዘመኑ የኑሮ ውድነት አሳድገውት ስለሚገኙ እንደሆነ ሰለባዎች ያስረዳሉ። መምህር /ማርያም /ሥላሴ ዘግተውት የነበረውን የጅቦችን አፍ አቶ ኑረዲን በደብዳቤ ክፍት ሆኖ የዘረፋ አገልግሎቱን እንዲቀጥል በደብዳቤ ከማዘዙም በላይ በሥራ ምክንያትና በጉብኝት ሰበብ ወደ አድባራት ከወረደ ለአቶ ኑረዲን 15ሺህ ብር ያላነሰ ጉርሻ እንደሚሰጠው ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ሰው ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አውግቷል።
ከአንድ ሺህ ብር ለማይበልጥ ደመወዝ ለመቀጠር አንድ መነኩሴ አስራ ስምንት ሺህ ብር ጉቦ የከፈሉ ሲሆን መነኩሴው የተጠየቀውን ክፍያ ለማሟላት ባለመቻላቸው ይህንን የጉቦ ገንዘብ ከወዳጅና ዘመድ በማዋጣት ያስተባበረ አንድ ዲያቆን የኑረዲንን ገፈፋ በምሬት አውግቶናል።
አቶ ኑረዲን ለቢሮ የስራ መደብ ከሰላሳ ሺህ እስከ ስልሳ ሺህ ብር ጉቦ እንደሚቀበሉ የተገለጸ ሲሆን የጉቦው ዋና አቀባባዮችና ግብረ አበሮቻቸው ኪሮስና ዘካርያስ የሚባሉ ነፍሰ በላዎች እንደሚባሉም ይታወቃል። አቶ ኑረዲን ክፍት የስራ መደብ ማግኘት ካልቻሉ እንደሚያፈናቅሉና ያለፍላጎት ሰራተኛውን በማዘዋወር ክፍት ቦታ እንደሚፈጥሩ ተያይዞ ተገልጿል።
የአክሱም ጽዮን ንቡረ እድና፤ የአክሱም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል የሚታወቁት ንቡረ እድ /ማርያም /ሥላሴ የአዲስ አበባ /ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንደተመደቡ የሙዳየ ምጽዋት ገልባጮችን አፍ በመሸበብ ህግና ስርዓት እንዲያዝ በማድረግ፤ ኢፍትህና ግፍ እንዲቆም በመታገላቸው ከጅቦቹ መንደር ጩኸትና ማጓራት ተሰምቶ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ አይዘነጋም። የጅቦቹን ጩኸት በማስተባበር ፊት አውራሪ የነበረው ቀንደኛው መሪና እድሜውን በክፋት የጨረሰ፤ ንስሐ ለመግባት የማይፈልግና ከመልካም ነገር ጋር ዘወትር የተጣላው የሽማግሌው ነውረኛ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሲሆን ለንቡረ እድ /ማርያምን መነሳት በማስተባበር፤ የአድማ ፊርማ በማስፈረም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

Saturday, October 13, 2012

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አበምኔት የመምህር ወልደ ሰማእት አጭር የሕይወት ታሪክ

(ከገ/ዮሐንስ ገ/ማርያም ፤ (M. A. T.) አጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ)    ከገጽ 56 ላይ ተሻሽሎ የተወሰደ፤

ከጥቁር ሕዝቦች መካከል በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካናት ውስጥ ብቸኛ ባለርስት ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ከዚያም ባሻገር ነጮቹንም በመቅደምና እስካሁንም ሳይኖራቸው ካሉት ምእራባውያን በላይ ከመካነ ስቅለቱና ከመካነ መስቀሉ ጣሪያ ላይ የሰፈሩ ብቸኛ ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከጥንቱ ከተማ ውጪ የነበረና አሁን አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ተብላ በምትጠራው ክፍል፤ የኢትዮጵያ ጎዳና ላይ  በ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ የታነጸችው የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በአካባቢው ብቸኛዋ የአበሾች ቤተክርስቲያን ናት።
በዚህች የ121 ዓመታት እድሜን ባስቆጠረች ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው፤ ነገር ግን ታሪካቸውን በአቧራና በተንኰል ድር የተሸፈነባቸው ታላቁ መምህር አባ ወልደ ሰማእት ናቸው። መምህር ወልደ ሰማእት ትውልዳቸው ሸዋ ቢሆንም ከሃይማኖት በስተቀር ዘርንና ጎጠኝነትን መሠረት አድርገው የማያምኑ ትልቅ አባት መሆናቸውን የሚያሳየው በወቅቱ የደረሰባቸው መከራና ያደረጉት ተጋድሎ ሕያው ምስክር ነው። መምህር ወልደ ሰማእት ምሁርና መጻሕፍት አዋቂ ነበሩ።  ወደኢየሩሳሌም በማቅናት ከኢትዮጵያ ገዳም በ1856 ዓ/ም ገደማ ሄደው ከማኅበሩ አንድነት እንደተቀላቀሉ ታሪካቸው ይነገራል።
ግብጻውያን መነኰሳት በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ኢትዮጵያውያንን ለበቅሎዎቻቸው እያሰገዱ፤ በኢየሩሳሌም ያለውን ሀብትና ንብረት ደግሞ የቻሉትን ዘርፈውና ወስደው፤ በኋላ ላይ ደግሞ የፈለጉትን ለመስኮቦች ሸጠውና መነኮሳቱን ከርስታቸው ነቅለው ጸሎት ቤታቸውን በወረሷቸው  ሰዓት መምህር ወልደ ሰማእት ወደ ኢየሩሳሌም ማቅናታቸው እንደ አንድ አጋጣሚ የሚቆጠር ነው። በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውያን መነኮሳት የጸሎት ቤታቸውን ተቀምተው እሁድ እሁድን እንኳን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ተጠግተው ከሚያስቀድሱ በስተቀር ምንም መቀደሻ ሥፍራ አልነበራቸውም ነበር። መምህር ገ/መስቀል የኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አበምኔት በሞት እንደተለዩ  የመምህር ወልደ ሰማእት እውቀትና ትእግስት ታይቶ አበምኔትነቱን እንዲረከቡ ተደርገዋል። ከዚያም ከ1836 ዓ/ም ጀምሮ ጠፍ ሆኖ የቆየውን ገዳም ወደነበረበት ለመመለስ መምህር ወልደ ሰማእት ወደ ኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ዘንድ በመሄድ አንድም ንጉሡ በምጽዋ  መጥቶ ድል ባደረጉት የቱርክ ሠራዊት ላይ የተቀዳጁትን ደስታ ለመግለጽ፤ በሌላ መልኩም የኢየሩሳሌም መነኮሳት ንጉሥ የሌላቸው ሕዝቦች ያህል ተቆጥረው ያለጸሎት ቤት በመንከራተት ላይ ስላሉ ንጉሡ መላ እንዲሰጧቸው  አቤቱታቸውን አሰምተው ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስም በወቅቱ ከቱርኮች በምርኰ ያገኙትን አራት ሳጥን ገንዘብ ይሰጧቸዋል። መምህር ወልደሰማእትም የተሰጣቸውን ገንዘብ  ይዘው በመመለስ ለጸሎት ቤት ማሰሪያና ለመነኮሳቱ ማረፊያ ቦታ እንዲሆን አሁን ደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት የተባለችው ቤተክርስቲያን ያለችበትን ርስት ገዙ። ከዚያም ከፈረንሳውያንና ቱርካውያን መሐንዲሶች ጋር በመነጋገር እራሳቸው መምህር ወልደሰማእት በነደፉት ዲዛይን መሠረት ቤተክርስቲያኒቱን በሚያዚያ ወር 1874 ዓ/ አስጀምረው ሊፈጸም ጉልላቱ ሲቀር በ1883 ዓ/ም አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ አረፉ። የቤተክርስቲያኒና የመነኮሳቱ ማረፊያ ሥራ ፤ እንዲሁም በአሮጌው ከተማ ያለውን መንበረ ጵጵስና ባመጡት ገንዘብ ገዝተው፤ አስር ዓመታትን የፈጀባቸው ቤተክርስቲያኒቱ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ገንዘቡ አለቀ። የተጀመረውን ያስፈጽሙላቸው ዘንድ ወደኢትዮጵያ ተመልሰው እንዳይጠይቁ ያስጀመሩት ንጉሥ አፄ ዮሐንስ አርፈው በምትካቸው አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥትነቱን ተረክበዋል።
ከዚያም መምህር ወልደ ሰማእት ሁለት መነኮሳትን ከኢየሩሳሌም ወደ አዲሱ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ዘንድ ቤተክርስቲያኒቱ ያለችበትን ሁኔታ አስረድተው እሳቸው ማስፈጸሚያውን እንዲልኩላቸው ደብዳቤ አስይዘው ወደ ኢትዮጵያ ላኩ። አፄ ምኒልክም በደቡብና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ዘመቻ ከፍተው ሀገሪቱን አንድ በማድረግ ሥራ ላይ ተጠምደው ስለነበረና በወቅቱም ወረርሽኝ በሽታ በሀገሪቱ ገብቶ ስለነበረ  የተፈለገውን ገንዘብ መላክ እንዳልቻሉ ምላሽ ይሰጣሉ። የተላኩት መነኮሳት ባዶ እጃቸውን መመለሳቸውን እንዳዩ መምህር ወልደሰማእት በአፄ ዮሐንስ ገንዘብ ከገዙት ሰፊ ይዞታ ውስጥ ከፊሉን መልሰው በመሸጥ፤ ቤተክርስቲያኒቱን በሽያጩ ገንዘብ በ1884 ዓ/ም አስጨርሰው ቅዳሴ ቤቱን ያከብራሉ።

 ከቤተክርስቲያኑ ቅጽር  መግቢያ በር ላይ እና  ከቅድስቱ ዙሪያ የውጪው ግድግዳው ላይ ቤተክርስቲያኒቱን አፄ ዮሐንስ በላኩት ገንዘብ መፈጸሙን የሚገልጽ ጽሁፍ በወርቅ ዓምድ እንዲጻፍ ያስደርጋሉ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የመምህር ወልደ ሰማእት መከራና ስደት ይጀምራል። ነገረ ሰሪና ሹመት ፈላጊ የሀገራቸው የሸዋ ሰብቀኛ ወንድሞቻቸው መነኮሳት ከአፄ ምኒልክ ዘንድ ይከሷቸዋል። እርስዎ ንጉሠ ነገሥቱ በሕይወት እያሉ በሞት የተለዩት ንጉሠ ነገሥት ስም እንዴት ይጻፋል? ብለው ስለከሰሷቸው  መምህር ወልደ ሰማእት ለጥያቄ ወደ ኢትዮጵያ ይጠራሉ። መምህር ወልደ ሰማእትም የንጉሡን ጥሪ አክብረው ከሄዱ በኋላ ለምን የዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ስም እንዳልሰፈረ ሲጠየቁ፤ መምህር ወልደ ሰማእት ምንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ ሀቁን ግልጥልጥ አድርገው ይናገራሉ።  መንበረ ጵጵስናውን፤ የደብረ ገነት ኪዳነ ምህረትን ቤተክርስቲያንን ሙሉ ይዞታና የመነኮሳቱን ማረፊያ የገዙት በአፄ ዮሐንስ የስጦታ ገንዘብ መሆኑንና ለማስፈጸሚያም መነኮሳት ልኬ ገንዘብ ባለመገኘቴ ከገዛሁት ርስት ላይ ቀንሼ በመሸጥ ያስፈጸምኩ ሲሆን ሙሉ በሙሉ በንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ገንዘብ ስለተፈጸመ፤ የጻፍኩት ያንን በመሆኑ ጥፋቴ ምንድነው? ብለው ይጠይቃሉ። መምህር ወልደ ሰማእት ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳላጠፉ ቢታወቅም ሕያው የነበረውን ንጉሥ ትተው የሙቱን ንጉሥ ስም በማስጻፋቸው ብቻ በደብረ ሊባኖስ ገዳም እንደጥፋተኛ በግዞት እንዲቀመጡ ይወሰንባቸዋል። ከከንቲባ ገብሩ ደስታ ጋር ሌሎች ሁለት ሰዎች ተልከው የመምህር ወልደሰማእት ጽሁፍ እንዲቀየር ይደረጋል።

Thursday, October 11, 2012

ቋሚ ሲኖዶስ ጀግኗል!

በቤተ ክርስቲያን ትልቁ ችግር ከአናቱ እስከ እግሩ ጥፍሩ ያለው መዋቅር በበሰበሰ አስተዳደር መተብተቡ ነው። 2 ሺህ ዘመናትን በመከራና በወጀብ ስትናጥ፤ የደም አበላ ግብሯን ጠያይም ልጆችዋን እየሰጠች፤ ከጉዲት እስከ ግራኝ፤ ከድርቡሽ እስከጣሊያን ድረስ ከልጆቿ እስከ ንብረቷ ስትገብር የቆየችና እዚህ 21ኛው ክ/ዘመን ላይ የደረሰች ቤተክርስቲያን ሉላዊ እውቀትና አስተዳደር በዘመነበት ዘመን ላይ ምን እንደነካት ሳይታወቅ የገዛ ልጆቿ የስልጣንና የሀብት ክምሯ ላይ ሰፍረው እንደ ዳልጋ ዝንጀሮ እየፈነጩ ሲንዷት ማየቱ ውሎ ያደረ ከመሆኑም በላይ ሁሉም እየተባበሩ በአንድ ድምጽ ውድቀቷን እናፋጥን የሚሉ እስኪመስል ድረስ በጥፋት እድምተኞች መሞላትዋ ግልጽ ነው።
ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ይሁዳዎች፤ አፍኒንና ፊንሐስ አመንዝራዎች፤ በነጻ የተሰጣቸውን የሚሸጡና በእናጸድቃለን ካባ የመበለት ቤቶችን የሚመዘብሩ ግብረ በላዎች፤ ስመ ብጽእናን ለምግባረ ብልሹ ስራቸው የደረቱ አባዎች ሞልተው የጋራ ክንዳቸውን በዐመጽና በጥፋት «አንስእ ኃይለከ» ተባብለው የተማማሉ የግብረ እከይ ሰዎችን ማንነትና አድራጎት መመልከቱም እንግዳ ነገር አይደለም። ሆዳቸው ከሞላ የበሻሻ አቦ ምእመናን ሰይፍ በአንገታቸው ቢያልፍ አፋቸው በስብ የተዘጋ ይመስል የማይናገሩ አፈ ዲዳዎች መሪ በሞላባት ዘመን ላይ ቤተክርስቲያን መድረሷ አጥፊዎቿ የውጪ ጉዲት ሳይሆን የራሷ እሬቶዎች መሆኑንም ብዙ ታዝበናል። በአዲስ አበባ ከተማችን የ2000 ብር ደመወዝ እየበላ የሁለት መቶ ሺህ ብር መኪና የሚነዳ የመሪነት ስምን የተሸከመ ሙዳየ ምጽዋት ገልባጭ ማየት የተለመደ ሆኗል። የዘረፋ መዋቅር ዘርግተው የቤተክርስቲያኒቱን ጡት ያለርኅራኄ የሚመጠምጡ አይጠ መጎጦች ተንሰራፍተው ይገኛሉ። ገንዘብ የሚገኝበትን ቤተክርስቲያን ለመምራት ከላይ እስከታች በሚደረገው መቆላለፍ ጅቦቹ አፋቸውን ከፍተው ሲያሰፈስፉ መስማትም ዛሬ ዛሬ እንደተገቢ እየተቆጠረ ይገኛል። በአንድ ወቅት የወይብላ ማርያም ቤተክርስቲያን ከነበራት የ400,000 ብር ካዝና ውስጥ በወራት ልዩነት ወደ 20 ሺህ ደርሶ ለካህናት ደመወዝ መክፈል እስኪያቅት መደረሱን አይተን እነሆ እስከዛሬ በአስገራሚነቱ መዝግበነዋል። ከማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እስከ ዑራኤል ቤተክርስቲያን፤ ከመርካቶ ሚካኤል እስከ ግቢ ገብርኤል የጅብ መንጋ ሲግጥ ማየት እንግዳ መሆኑ ቀርቷል።  በየደረጃው የእያንዳንዱን አብያተ ክርስቲያን ካዝና ገልብጠው ባዶ ካደረጉ በኋላ ወደተረኛው ቤተክርስቲያን የሚዛወሩ ወሮ በሎች በዚህ አጭር ጽሁፍ ዘርዝሮ የሚዘለቅ አይደለም።
 የሚያስደንቀው ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ ምን ዓይነት ቁጣ ወረደባት እስኪያሰኝ ድረስ ከሀገር ቤት አንስቶ እስከባህር ማዶ ድረስ የአበሻ ጅቦች የሰፈሩባት መሆኑ ያስገርማል። ከቦርድ እስከ ሰበካ ጉባዔ ከተገንጣይ እስከ ገለልተኛ፤ ከግለሰብ ቤተክርስቲያን እስከ ሁለ ገብ ድረስ እየተቧደኑ መዝረፍና ማስዘረፍ፤ የየሀገራቱን ፍርድ ቤቶች ፋይል እስከማጨናነቅ ያደረሰ የዘረፋ ስልጣኔ መንገሱም ፀሐይ የሞቀው፤ አገር ያወቀው ጉዳይ ነው።
የክህነቱና የመሪነቱ መስፈርት የማንነት ሚዛንስ ምኑ ተነግሮ? እንዲያው ተከድኖ ይብሰል! ይህ ሁሉ ሲሆን ቤተክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ እመራለሁ የሚል ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ሲኖዶስ ነበራት። ለመብላትና ለመናገር ካልሆነ ለመሥራት አቅሙና ፍላጎቱ የሌለው፤ ቤተክርስቲያን ብትሞት እንጂ ለእሷ ሞት ራሳቸውን ለማስቀደም የሚደፍሩ የመሪ ቁርጠኞች በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መገኘቷ ችግሯ እንዲባባስና ከልካይ የሌለበት እንድትመስል አድርጓታል። ወጉ ደርሶ ማስቆም ባይችሉ ራሳቸውም አብረው ወራሪና አስወራሪ መሆናቸውን ቢያቆሙ እንኳን እሰየው ባልን ነበር! ነገሩ ግን የተገላቦጦሽ ነው። ሕዝቡ በG ማይነስ ቤት ውስጥ እየኖረ እነሱ በG ፕላስ ውስጥ መኖራቸው ነገሩን ሁሉ አስከፊ ያደርገዋል።