Friday, May 14, 2021

ኦርቶዶክስን የማፍረስ ዘመቻ!

 


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ተዋሕዶን የማፍረስ ዘመቻ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። አብዛኛዎቹ ዘመቻዎች ውጫዊ ነበሩ። የዮዲት ጉዲት ዘመቻ: ከደቡብ ወደሰሜን የተካሄደው የገዳዎች ወረራ: የግራኝ: የማህዲስት: የካቶሊክ ሚሲዮናውያን: የፋሺስት ጣሊያን ዘመቻዎች ሁሉ መሰረታቸው ኢትዮጵያን የመቆጣጠርና ግዛት የማስፋፋት ቢሆንም ቤተ መንግስቱንና ቤተ ክህነቱን ትቆጣጠር የነበረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ግብ የሁሉም ወራሪዎች ተመሳሳይ አላማ ነበር። የሕዝቡን እምነትና ለመንግስት አሜን ብሎ የመገዛት ስነልቦናውን ለማፍረስ መጀመሪያ ኦርቶዶክስን ማጥፋት የሁሉም ግብ ነበር። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከውጪ የመጣባትን ጥቃት ሙሉ በመሉ በመቋቋም ከመጥፋት ተርፋ ይሄን ሁሉ ዘመን መዝለቅ የቻለችው ውስጣዊ አንድነት ስለነበራት ብቻ ነው። ነገር ግን ከ1966 ዓ/ም በኋላ የኦርቶዶክስ ሲሶ መንግስትነት ተንኮታኩቶ ፈጣሪ የለሽ መንግስት በቦታው ሲተካ ከውጫዊ ጥቃት ይልቅ ውስጣዊ አንድነቷን የሚፈታተን አደጋ ተጋርጦባታል። ለሁለተኛው ፓትርያርክ በደርግ መገደል መነሻው ምክንያት የውስጠኛው አመራር  የሆነው የሲኖዶሱ መከፋፈል ነበር። ለአራተኛው ፓትርያርክ ሹመት የነመላኩ ተፈራ ደርጋዊ እጅ ቤተ ክህነቱ ውስጥ ዘልቆ መግባቱና ለአምስተኛው ፓትርያርክ ሹመትም ተረኛው የወያኔ እጅ እንደፈለገው ማቡካት መቻሉን ስለምናውቀው እውነቱን መካድ አይቻልም። 

ደርግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት ወርሶ ለ17 ዓመት: ህወሀት ለ27 ዓመት የቤተ ክርስቲያኒቱን የውስጥ አመራር ተቆጣጥረውት የቆዩት ለፖለቲካዊ አላማቸው የማታስቸግር ቤተ እምነት እንድትሆን ቀፍድዶ ለመያዝ እንደነበር ይታወቃል። 

ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ አስተዳደር መበላሸትና ለጥቃት ተጋላጭ ያደረጋት ዋናው ምክንያት ቅዱስ የተባለው ሲኖዶስ በሚጠበቀው ደረጃ አስተዳደሩን በቅድስና መምራት አለመቻሉ እንደሆነ እርግጥ ነው። ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከ25ሚሊዮን በላይ አማኞቿ ትተዋት የኮበለሉት በቁጥርም: በዝናም ሲኖዶስ የተባለው ማኅበር በጨመረ ቁጥር ነው። ለምን? ብሎ መጠየቅ የግድ ይላል። ይሄ ሲኖዶስ የሚባለው ማኅበር ትክክለኛው የበጎች እረኛ ሳይሆን የበጎቹን መንጋ ለቀበሮ አሳልፎ የሚሰጥ ለደመወዝ የሚኖር ቅጥረኛ ስለሆነ ብቻ ነው። በነቀዘ የአስተዳደር መዋቅር: በጉቦና በዘረፋ የተሰማራ አመራር: ዘመኑን የሚዋጅ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አለመኖር:  ፍትህ በአፍጢሙ በመደፋቱና በሌሎች ውስጣዊ ገፊ ምክንያቶች የተነሳ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለቀው ሄደዋል።  ያሉትም በሚያዩት ነገር ተስፋ ቆርጠው ቤታቸው ተቀምጠዋል። በአንድ ወቅት አንድ የሙስሊም ስኮላር ያለውን አስታውሳለሁ። እስልምና የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በሙሉ ሲቆጣጠር የነቢያችንን ዘመዶች የተቀበለችው ኢትዮጵያን መቆጣጠር ያቃተን በኦርቶዶክስ የተነሳ ነበር። እኛ ያቃተንን ጳጳሳቶቿ ራሳቸው እያዳከሙልን ስለሆነ ምስጋና ይገባቸዋል ሲል ተደምጧል።  ነገሩን ቆም ብለን ስንመረምር ቤተክርስቲያኒቷ ጳጳሳት በበዙ ልክ ማደግ ሲገባት ጳጳሳቱ በበዙ መጠን እያሽቆለቆለች መገኘቷ የስጋውያን መሪነት የመንገሱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። 

በአጠቃላይ ከ1966 ዓ/ ም በፊት የነበሩ ውጫዊ አደጋዎቿን በውስጣዊ አንድነቷ መቋቋም የቻለችው ቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ አንድነቷን የሚያናጋ ውስጣዊ ችግሮችን እያመረተች በመገኘቷ በምእመናኖቿ ቁጥር የቁልቁለት ጉዞዋን ተያይዛዋለች። በመንፈሳዊ ወሥጋዊ ዘመናዊ አስተዳደር አለመኖርና የፋይናንስ ስርአቱ ብልሹነት የተነሳ ዘረፋ: ጉቦ: ዘረኝነትና ዐመፃ በመንሰራፋቱ ራሷን ከውጪ ጥቃት እንዳትከላከልና ውስጣዊ ተጋላጭነቷ ከፍ እንዲል አድርጓታል።

ይህ ሁሉ ዐመፃና ስርአተ አልበኝነት ነግሶ እያለ አንዳንዶች እግዚአብሔር ስለሚጠብቃት ኦርቶዶክስ አትፈርስም ሲሉ ይደመጣሉ። ይሄ ግን በስመ እግዚአብሔር የሚፈፀም ራስን የማታተል ግብዝነት ነው። በራእየ ዮሐንስ ላይ የተመለከቱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ዐመጽና በደልን እንዲተዉና ወደእግዚአብሔር የቀደመ መንገዳቸው እንዲመለሱ ቢነገራቸው መስማትና ንስሐ መግባት ባለመፈለጋቸው የተነሳ አብያተ ክርስቲያናቱ በሙሉ ፈራርሰው ዛሬ በሙዚየምነት የሚጎበኙ የእስላማዊ ቱርክ የገቢ ምንጭ ፍርስራሽ ሆነው ቀርተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም መጨረሻ በዚህ መልኩ እንዳይደመደም የሚያስችል ሁኔታ እየታየ አይደለም። ሲኖዶስ የተባለው በስመ ቅድስና የተሰየመው የበላይ አካል በቅድስና እየመራት ከሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ዐመጽ: ዘረፋ: ጎጠኝነት: የአመራር ክፍፍልና ልዩነት ለምን መለያዋ ሊሆን ቻለ? 

አሁን በቅርቡ በታየው የቤተ ክርስቲያኒቱ መግለጫ በተባለው ጉዳይ ላይ (አባ) ወ/ ኢየሱስ ወይም ህፃን የተባለው ጎረምሳ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክሎ ያደረገው ንግግር የሚያሳየው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓትና ሕግጋት እየፈረሰ መሆኑን ያመላክታል። ይህ ሰው በመኪና ስርቆት ወንጀል ተፈርዶበት 4 ዓመት ከርቸሌ የከረመ መሆኑ እየታወቀ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ በዓላት በልደት: በጥምቀት: በዘመን መለወጫ: በከፍተኛ ስብሰባዎች እየተገኘ በውክልና መግለጫ የሚሰጠው በምን አግባብ ነው?



 አባ ሕጻን (በአማን ዘውእቱ ሕጻን) ከዘመናዊ ትምህርት ይሁን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ሩቅ ነው። ግን መግለጫ በመስጠት ቀዳሚ ነው። እውነት ነው: ሲኖዶሱ በዝምታ ድባብ ሲዋጥ አላዋቂዎች ቢሰለጥኑባት አይገርምም። "ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ" እንዲሉ!

የዓሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ ነው እንደተባለው በመላው ሀገሪቱ እየታየው ባለው የቤተ ክርስቲያን መቃጠልና የምእመናን እልቂት ፊት ለፊት መናገር ሲገባቸው እንደቀንድ አውጣ አንገታቸውን ቀብረው የቆዩ ሁሉ ቅዱስ ፓትርያርኩ በትግራይ እየተከሰተ ያለውን እልቂት ማውገዛቸውን ተከትሎ ፓትርያርኩ ላይ አፋቸውን ሲከፍቱ ስናይ ቅጥረኞች ቤተክርስቲያኒቱን እንደወረሯት ማሳያ ነው። በልብስ ሰፊነት ባደለቡት ገንዘብ ያገኙትን ሹመት በመንፈሳዊ ብቃት ያገኙት ያህል እንድንቆጥርላቸው ይፈልጋሉ። የብርሃኑ ጁላ ታናሽ ወንድም 



ሆነው ፓትርያርኩ የተናገሩትን የግላቸው አቋም ነው ብለው የማን ቅጥረኛ እንደሆኑ ሲያሳብቁ እነርሱ በማን ፈቃድ? የማንን አቋም? እንዳንፀባረቁ ድንቁርናቸው ራሱ ያጋልጣቸዋል። ጊዜ ወለድ የሆኑ ጳጳሳት ባሉባት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገርመው ውድቀቷ ቶሎ አለመፈፀሙ ብቻ ነው። 

የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መስራቹ አቶ በላይ መኮንን ባቋቋመው ቲቪ ላይ ከጀነራል ጳጳሳቱ ጋር ተሰይሞ እንደሕዝብ አማራን: እንደተቋም አሁን ያለው ሲኖዶስ ሲያዋርዱና ሲዘለፉ ተመልክተናል።  


ፓትርያርኩ የትግራይ ህዝብ እየተጨፈጨፈ ነው ብለው መናገራቸው ስህተት ተደርጎ የተቆጠረው የኦሮሚያ ኦርቶዶክስን ለማቋቋም እንደእጅ መንሻ ለመንግስት ለማቅረብ መሆኑ ያልገባው ካለ እሱ ጅል መሆን አለበት። ፓትርያርኩ የአስተዳደር ብቃት ችግር እንዳለባቸው ይታወቃል። ነገር ግን ለቤተክርስቲያን ባለመቆርቆር ወይም በዘረኝነት እሳቸውን ለመክሰስ ብቃት ያለው አንድም ጳጳስ እንደሌለ እርግጠኞች ነን።

የአቶ አሻግሬ መንግሥት ተለያይቶ የነበረውን ሲኖዶስ ያሰባሰበው በተለያየ ጎራ በፖለቲካ ውጊያ እንዳያስቸግሩትና ሰብሰብ ባለ ጠላት ላይ ኃይሉን በሙሉ ለማሳረፍ እንዲያስችለው እንጂ መንፈሳዊ መልእክት ከሰማይ ወርዶለት አይደለም። በአጠቃላይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማፈራረስ እቅድ በመንገድ ላይ ይገኛል። ውስጣዊ አንድነቷ የለም። ሲኖዶሱ እንደእከ " እኔን ነው?" ከማለት  የእንቅልፍ አዚም መውጣት አልቻለም።

ምእመኑ የተመሪነት ፍላጎቱ ቢኖረውም መሪ እንደሌለው የበግ መንጋ በሃዘንና በስቃይ እየተቅበዘበዘ ነው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ኦሮሙማ ቤተ መንግሥቱንና ቤተ ክህነቱን ከመዋጥ ከመሰልቀጥ አይመለስም። መጨረሻውስ ምን ይሆን?

እድሜ ይስጠን ገና ብዙ እናያለን: እንሰማለን!

Saturday, February 22, 2020

ጉባዔ ከለባት እና የዘመኑ ሆድ አደር ሲኖዶስ!

ፓትርያርኩ እድል ይሁን የችሎታ ማነስ ቤተ ክርስቲያን በዘመናቸው እየፈረሰች ነው።
ጳጳሳቱስ ችግር ፈቺ ናቸው ወይስ ችግር ፈጣሪ? ሁሉም ቤተ ክርስቲያንን በማፈራረስ የየድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው።
አቡነ ጃዋር: አቡነ ጃዊሮስ ቀውስ በላይንና ሌሎች ሃይማኖት የለሽ ኦነጋውያንን ማስቆም ያልቻለ ሲኖዶስ ጥጉን ይዞ ይስቃል።


Friday, December 20, 2019

የዛሬ 7 ዓመት ይህን ተናግረን ነበር!

አዲሱ ፓትርያርክ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል!


በዚህም ተባለ፤ በዚያ አቡነ ማትያስ ፮ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል። ባለፈው ግድፈትና እውነት ላይ  እያነሳንና እየጣልን ጊዜ አናጠፋም። ይልቅስ ብዙዎች የታገሉለት የምርጫው ስኬት እንዳሰቡት ጥሩ የሥራ ጊዜ ይዞ ይመጣላቸው  እንደሆነ የምናይበት፤  ገሚሶቻችንም የምናያቸው የቤተ ክህነት ተግዳሮቶች የሚቀረፉበት፤ ሰናይ የአስተዳደርና መንፈሳዊ ዘመን ናፍቆታችንን ተስፋ በማድረግ እንደዚህ በፊቱ አስቀድመን አንዳንድ ነገሮችን ለማመልከት ወደድን።
የአዲሱ ፓትርያርክ አዲስ የሥራ ዘመን ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። የተጠራቀሙ የቤተ ክህነቱ ችግሮችና ብዙ እንከኖች  ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል። የችግሮቹ ዓይነቶች፤ ደረጃና ጥልቀት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የተለያየ ውሳኔና እርምጃንም የሚጠይቁ ናቸው። ለዚህ የተዘጋጀ የአእምሮ ዝግጁነት፤ የእውቀት በሊህነት፤ ድፍረትና ማስተዋል እንደሚጠይቁም አይጠረጠርም።  ያንን ዓይነት ሰው ከየት እናገኛለን ብለን አናሳብም። ምክንያቱም ምርጫው /ከተባለ/ ትልቅ አባት ሰጥቶናልና። ስለዚህ ወደችግሮቹ እንንደርደር።

1/ የቤተ ክህነቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር ማሻሻል

የቤተ ክህነቱ ቀዳሚው ችግር ሥራና ሠራተኛ የተገናኘበት ተቋም አለመሆኑ ነው። ሥራና ሠራተኛ ካልተገናኘ ደግሞ  በየትኛውም መልኩ የቤተ ክህነቱ የሥራ አፈጻጸም «ከርሞ ጥጃ» መሆኑ አይቀርም። ሥራና ሠራተኛ ማለት ለተገቢው ሥራ ተገቢ ባለሙያ ወይም ተቀራራቢ ችሎታ ያለው ሰው ማለት ነው። እንደዚህ ባለው ሰው ላይ የተቋሙን ዓላማና ግብ በደንብ ካስጨበጡት ከችግሮቹ ብዛት አንጻር ባንድ ጊዜ ፈጽሞ ባይወገድም፤ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። በዘመድ አዝማድ የተለጣጠፉና የተደረቱ ክፍሎችን ይዞ መቀጠል ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናልና አሁን ያለን የሥራና ሠራተኛ አቋም የችግሩ ዋና ምንጭ ነው ባይባልም የችግሩ አካል ነውና ከጥገናዊ ለውጥ ወይም ከማስመሰል /pseudo/ የራቀ ለውጥ ያስፈልገዋል። ከአቅም በታች ለመሥራት የእድሜ ጣሪያ የገደባቸውም  በየመልኩ ቦታቸውን መያዝ  ካልቻሉ ቤተ ክህነት የዘመዳ ዘመዶች የጡረታ ተቋም ሆኖ ይቀጥላል እንጂ የሥራ ብቃት መለኪያ ስፍራ ሊሆን አይችልም።