Sunday, April 27, 2014

«ኤሪያ 51» በአሜሪካ ውስጥ ያለ ሌላ አሜሪካ!



ይህ ሀገር «Area 51»  ይባላል። ስያሜውን ያገኘው አሜሪካ በ1967 በቬትናም ላይ ወረራ በፈጸመች ጊዜ ከኦኪናዋ እየተነሳ እንዲደደበድብ ትዕዛዝ የተሰጠው የሲአይኤ የምስጢር ኮድ በወቅቱ ኤርያ 51 ይባል ነበር።  የያኔው ትዕዛዝ ተቀባይ የነበረው ሲአይ ኤ ይህንን በአሜሪካ ውስጥ ያለውን ሌላ አሜሪካ ብዙ ዓመታት ሲሰልል ከቆየ በኋላ በጥንቱ  የቬትናም ኮድ «ኤርያ 51» ሲል ጠራው። በዚሁ መሰረት «Groome Lake» ይባል የነበረው ይህ ቦታ «Area 51» ተብሎ ይጠራ ጀመረ። ኤርያ 51 የሚገኘው በግሩም ሌክ /ግሩም ሐይቅ/ ዳርቻ በኒቫዳ ስቴት ውስጥ ነው። ከላስቬጋስ ከተማ ሰሜናዊ አቅጣጫ ወደኒቫዳ ሲሄዱ በአስቤስቶስ ፋብሪካ ሠራተኞች በተቋቋመችውና በኋላም ጥቂት ጡረተኞች የከተሙባት የራሔል ከተማን ለመጎብኘት የሚሄድ ሰው ወደግራ የሚታጠፍ ቀጥ ያለ ኮረኮች መንገድ ተከትሎ ከሄደ በአሜሪካ ውስጥ ያለውን ሌላ አሜሪካ የሆነውን  «ኤርያ 51» መግቢያ ያገኛል። ነገር ግን እዚህ አሜሪካ ውስጥ ይገባ ዘንድ ማንም አይፈቀድለትም። 23 በ25 በሆነ  ስኴር ኪሎሜትር ውስጥ ያረፈው «ኤርያ 51» በረቀቁ ካሜራዎች የተተከለለት ማለትም ከየትኛው አቅጣጫ የሚመጣ ሰው የሚናገረውን መጥለፍ የሚችል፤ ቪዲዮ ቀርጾ የማስተላለፍ ብቃት ያለው፤ ምን እንደሚሰራ፤ ምን እያደረገ እንዳለ በመለየት መተንተን የሚችል ሴንሰር የተገጠመበት ክልል ነው። በአደገኛ የማስጠንቀቂያ ጽሁፍና ቁጥራቸው በማይታወቅ የጥበቃ ፖሊስ መኪና የታጠረው ይህ ሌላው አሜሪካ እስከመኖሩ የታወቀው ከ1960ዎቹ በኋላ ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ በእምቢተኛነቱ ጸንቶ ለማለፍ የፈለገውን ግለሰብ ወይም ቡድን ከጉጉት ዓይን በበለጠ የሚከታተለው ፈጣኑ ጠባቂ ኃይል በመኪና ከተፍ ብሎ ያለምንም ምርመራ የደረሰበትን ሊያጠፋው ይችላል። እጅግ አደገኛና ምስጢራዊ ክልል «ኤርያ 51» እሱ ነው።


 ከ1970ዎቹና 80ዎቹ ወዲህም «ኤርያ 51» የሚባል ቦታ ስለመኖሩ እንጂ «በኤርያ 51» ምን እንደሚደረግና ምን እንደሚሰራ ምናልባት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ያውቁ እንደሆነ እንጂ ይህ ስፍራ እንኳን ለዓለም ሕዝብ በቅርቡ ላሉት ለራሔል ከተማ ሕዝቦች እንግዳ ሀገር ነው።
«ኤርያ 51» ተብሎ ከመሰየሙ በፊት ግሩም ሐይቅ ዳርቻ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በ1942 ዓ/ም አሜሪካ የአውሮፕላን ማረፊያ ነገር ነበራት። ዙሪያውን በተራራ የተከበበውን ይህንን የሀይቅ ዳርቻ ካምፕ በማድረግ በ1955 ዓ/ም ወደምስጢራዊ ተግባር አዛወሩት። ይህ ካምፕ የአሜሪካ አቪየሽን መስሪያ ቤት የማያውቁት የራሱ አውሮፕላኖች አሉት።  ከፔንታጎን ወይም ከመከላከያ ቁጥጥር ነጻ የሆነ ልዩ ሀገር ነው። ብዙ አሜሪካኖች የዚህን ቦታ ምንነት ለማወቅ ያደረጉት ሙከራ ከተወሰኑ ግምቶችና መላምቶች በስተቀር የተጨበጠ መረጃ ሊያገኙበት አልቻሉም። ሆሊውዶች ደግሞ ይህንን ምስጢራዊ ስፍራ በፈጠራ ታሪክ ሞልተውት «AREA 51» የተባለ ፊልም ሰርተውበታል።
በኤርያ 51 የአየር ክልል አውሮፕላን መብረር አይችልም። በአካባቢው ለመብረር ለአየር ማማ ተቆጣጣሪ ማሳወቅ አለበት። «ኤርያ 51» ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች የሚኖሩበት ራሱን የቻለ ከተማ ነው። ምናልባትም የሳይንስ ጠበብቶች ስብስብ ከተማ ይሆናል። የከተማው ዋናው ክፍል በምድር ውስጥና በተራራዎቹ የታችኛው ክፍል ሊሆን እንደሚችል የካርታ ጥናት ባለሙያዎች «ጉግል ማፕ» ን አይተው ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በአንድ ወቅት አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቡድን አካባቢውን ለመሰለል ከረጅም ርቀት ምስል ማስቀረት በሚችሉ ዘመናዊ ካሜራዎች እየታገዘ ቦታውን በቪዲዮ ለመቅረጽ ሞክሮ ነበር። በተወሰነ መልኩ የኤርያ 51 የመብራትና ድምቀትና የቦታ ስፋት መረጃ ለማስቀረት ችሏል። ወደኤርያ 51 የሚገቡ የአውሮፕላን ማመላለሻዎችንም ተመልክቷል። ነገር እነማንን? ከየት? ለምን? የታወቀ ነገር የለም።
ታዲያ «ኤርያ 51» የምን ከተማ ነው?
ከመነሻው በ1942 ዓ/ም የአውሮፕላን ማረፊያ የነበረው ይህ የግሩም ሀይቅ ስፍራ ወደተሻሻለና ምስጢራዊነቱ ወደተጠበቀ ወታደራዊ የምርምር፤ የሙከራና የምርት ጣቢያ ተቀይሯል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ለዚህም የሚጠቀሰው አሜሪካ የታጠቀቻቸውና ማንም ያላገኛቸውን ዘመናዊ ሄሊኮፕተሮች፤ ቦምበር ጄቶች፤ የስለላ መሳሪያዎች፤ ሰው አልባ ድሮን ጭምር የሚመረቱት በዚህ ከተማ ነው የሚል እምነት አላቸው። ምክንያቱም እነዚህ ዘመናዊ የጦር ምርቶች በተለያየ ጊዜ ከዚህ ከኤርያ 51 ውስጥ እየተነሱ በአካባቢውን ትናንሽ ከተሞች ላይ ሲበሩ ታይተዋልና ነው። ይህንንም የሚከታተል የረጅም ርቀት ካሜራዎችን ተክለው የዕለት ዕለቱን የሰማይ እንቅስቃሴ የሚከታተሉ የምርመራ ጋዜጠኞች ለማረጋገጥ መቻላቸው ነው።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነውና ስለኤርያ 51 ምስጢራዊነት ትኩረት የሰጠው ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነው። ከኤርያ 51 የሚወጡና ወደኤርያ 51 የሚገቡ በዚህ ምድር ላይ ያልታዩ አካሎች የመኖራቸው ጉዳይ ነው። እነዚህ በረጅም ርቀት ካሜራዎች የኤርያ 51ን ሰማይ በሌሊት ምን ክስተት እንዳለው ለማየት ባደረጉት ሙከራ የበራሪ አካሎቹን ምስል ለማስቀረት ችለዋል።  በጣም ፈጣንና ልዩ መልክ ያላቸው በራሪ አካሎች በኤርያ 51 ምን ያደርጋሉ? ከማንስ ጋር ይገናኛሉ? ያስነሳው ልዩ ጥያቄ ነው።
በኤርያ 51 ቅርብ ርቀት በኒቫዳ በረሃ ባለችው ራሔል ከተማና አልፎ ተርፎም  130 ኪሎሜትር በምትርቀው በቀለጠው መንደር በቬጋስ ጎዳናዎችና ቤቶች ላይ የእነዚህ የበራሪ አካሎች ምስል ይገኛል። ከዚህ በፊት ታዋቂው ደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ ስለነዚህ ያልታወቁ አካሎች ታሪክ አስነብበውን እንደነበር አይዘነጋም። እነዚህ በራሪ አካላት በኤርያ 51 ምን ይሰራሉ? አሜሪካ ለደረሰችበት እጅግ የረቀቀ ምድራዊ ጥበብ እነዚህ በራሪ አካላት ድርሻ ይኖራቸው ይሆን? በራሪ አካላሎቹ ወይም UFO የሚባሉት ከየት የሚመጡ አካላት ናቸው?
በራሄል ከተማ የምትገኝ አነስተኛ ምግብ ቤት (የምስሉን ዓይን ይመልከቱ)
የነገረ መለኮት ምሁራን UFO ወይም ያልታወቁ በራሪ አካላት የተባሉት የወደቀው መልአክ ሰራዊት ናቸው ይላሉ። እነዚህ ሰራዊት የሰይጣንን ፈቃድ ለመፈጸም ቃል በገቡ ሀገራት ውስጥ ስራቸውን ይሰራሉ፤ አንዳንዴም በሰው አእምሮ ውስጥ ጥበባቸውን በማሳደር ልዩ ልዩ ነገር እንዲፈጥር ያደርጋሉ። በተለይም የሰውን ልጅ ከምድረ ገጽ ጠርጎ ማጥፋት የሚችል የምርምርና የመሳሪያ ፈጠራ ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ «ኤርያ 51» አካባቢ ሲበሩ የሚታዩት እነሱ ናቸው በማለት ያስረዳሉ። ለዚህም ግብረ መልስ የሚሆን ስራ ግብረ ሰዶምን በመፍቀድ፤ ጾታን በመለወጥ፤ ክሂዶተ እግዚአብሔር እንዲስፋፋ የሚያደርግ ህግ እንዲተገበር ያስደርጋሉ። በዚህም አሜሪካ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ትወስዳለች ይላሉ። ምክንያቱን ሲያስረዱ፤
«ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ» ራእ12፤9
ወደምድር ከነሰራዊቱ ወደቀው ሰይጣን ስራው ምንድነው? የሰው ልጅ የሱን የጥፋት መንገድ እንዲከተል ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለዚህ ባለው ግንኙነትና ከሰው ጋር በሚፈጥረው ውኅደት ሌላው ዩፎ የሚለው አካል የሱ ሰራዊት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ። ለዚህም ያልታወቁ በራሪ አካሎች የተባሉት ፍጡሮች ምስል እንደተዘገበው የኢሉሚናቲ ምስሎችን የተከተለ መሆኑ ነው። ለዚህም አለምን ለመቆጣጠር ሰይጣናዊና አስፈራሪ ፊልሞች ማምረት፤ በዘፋኞቻቸው የዓለሙን ህዝብ ቀልብ በመሳብ የዘፈን መንፈሱን የማስረጽ ተግባር እየሰራ መገኘቱን ይገልጻሉ። የሁለት ጣት ምልክት፤ በዓይን ቅርጽ ምስል፤  ወዘተ ስምምነት ይፈጽማል፤ያስፈጽማል።
ላስቬጋስ
 ስለዚህ ኤርያ 51 ምስጢራዊ የግንኙነት ማዕከል ሆኖ ሊያገልግል ቢችል አያስገርምም። ሌላውን ጉዳይ መንግስት የሰይጣንን ፈቃድ በህግ ይፈጽሙለታል።
  አንፈጽምም የሚሉትን ደግሞ ያስፈራራሉ ወይም ያስገድዳሉ። ከዚያ በፊት ግን በፊልሞቻቸው አስፈራሪ /horror/ እና በአስጸያፊ የወሲብ ተግባራቸው የሌላውን ቀልብ በመማረክ ወደተግባር እንዲቀየር ያበረታታሉ። ከዚያም በህግ እንዲጸድቅ ያስደርጋሉ። እንግዲህ ያልታወቁ የሚባሉት እነዚህ አካላት ለኋላው ዘመን የጥፋት መሳሪያ ያስታጥቃሉ፤ አሁን ደግሞ በመንፈስ ሰውን ይቆጣጠራሉ ማለት ነው።
አይ ኤርያ 51? አሜሪካ ውስጥ ያለሽ ሌላዋ አሜሪካ!!

Saturday, April 19, 2014

«አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና»



ዕብራውያን     פֶּסַח «ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው።  በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት  ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል። 
ደሙን ደግሞ  የበሩን ሁለት ረድፍ «መቃንና ጉበኑን» ይቀቡታል።  ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።


ይህ ቅርጽ የዕብራውያን ስምንተኛውን ፊደል «ኼ» የተባለውን ይወክላል። (እንደአማርኛው በጉሮሮ ሳይሆን በላንቃ የሚነበብ ነው) «ኼ» ማለት በዕብራውያን ትርጉም «ሕይወት» ማለት ነው። ዕብራውያንም በፊደላቸው በ«ኼ» ቅርጽ በሚቀቡት ደም የተነሳ ወደፈርዖናውያን ሠፈር የሚያልፈው ሞት አይነካቸውም። ምክንያቱም ሕይወት የሚል ማኅተም በራቸው ጉበንና መቃን ላይ ታትሟልና። ፋሲካ ማለት ይህ ነው። በደሙ ምልክት የተከለሉ በሕይወት ለመቆየት ዋስትና የያዙ ሲሆን ይህንን ማኅተም ያላገኙና ምን እየሆነ እንዳለ የማያውቁ ደግሞ  በሞት የሚወሰዱበት  የፍርድ ምልክት ነው። ደሙ የሞትና የሕይወት መለያ ምልክት ሆኖ አገልግሏል።
ይህ ሥርዓት እስራኤላውያንን ከባርነት፤ ከጠላት አገዛዝና ከመገደል የታደገ የዋስትና መንገድ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካ ሕዝብና አሕዛብን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለም ሞት የታደገ በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና» 1ኛ ቆሮ 5፤7 በማለት የሚነግረን።  አሮጌውን እርሾ ካላስወገድን ፋሲካችን የሆነውን ክርስቶስ መቀበል አይቻልም። የክርስቶስን ፋሲካ እካፈላለሁ በማለት የበዓሉን አከባበር ማድመቅ፤ እንኳን አደረሰህ/አደረሰሽ መባባል ልምድ እንጂ የመለወጥ ምልክት አይደለም። የክፋት እርሾ የተባሉትን ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ ሲነግረን እንዲህ ይለናል። «ሴሰኛ፤ ገንዘብን የሚመኝ፤ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ፤ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ» ከመሆን መታቀብ ብቻ ሳይሆን ከሆኑትም ጋር አብሮ ባለመብላት ጭምር በመከልከል ከአሮጌው እርሾ ሆምጣጣነት መራቅ እንዲገባን ያስፈልጋል። (1ኛ ቆሮ 5፤11) የእስራኤል ዘሥጋ ፋሲካ መጻጻና የቦካ ይከለክል እንደነበረው ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካም እንዲሁ ይከለክላል። በኃጢአትና በዐመጻ የቦካ የውስጣችንን ሆምጣጣ እርሾ ካላስወገድን በስተቀር በፋሲካው የሚገኘውን ሕይወት በፍጹም  አናገኝም።  የቀደመው ፋሲካ እርሾ ያለውን ነገር ከቤቱ ያላጠፋ «ከእስራኤል ጉባዔ ተለይቶ ይጥፋ» የሚል ሕግ ነበረው።  ምድራዊው ፋሲካ ይህንን ያህል ከከበረ ሰማያዊውማ እንደምን የበለጠ አይከብር? ፋሲካን መናገርና ፋሲካን አውቆ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለፋሲካ ብዙ ማስተማርና መናገር ይቻል ይሆናል። ስለፋሲካ የመልካም ጊዜ መግለጫና ስጦታም መለዋወጥ ይቻል ይሆናል። ፋሲካን ማክበር ማለት 2 ወራት በጾም አሳልፎ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ/ፈታልሽ» ተብሎ ልጓም አልቦ የመሆኛ ሰዓት ደረሰ በማለት የሰላምታ መሰጣጣት ፕሮግራም አይደለም። ጾሙ ሲፈታ እንደፈለገን ልንበላ፤ ልንጠጣ፤ ልንናገር የልጓም አጥራችን ተከፈተ ማለት ከሆነ በአሮጌው እርሾ ብቻ ሳይሆን ከሰው የልማድ ስርዓት ጋር እንኖራለን ማለት ነው። የክርስቶስ ፋሲካ ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አይገኝም። ፋሲካ በስግደትና በወይራ ቅጠል በመጠብጠብ የሚገኝም ጸጋ አይደለም።  ፋሲካ የአንድ ወቅት ራስን ማስገዛትና በጽኑ እሳቤና ጭንቅ ማለፍ ውስጥ የሚመጣም አይደለም።
ፋሲካ በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የደሙን ምልክት በመያዝ ዕብራውያን ከሞት እንዳመለጡበት የ «ኼ» ምልክት ማኅተም በመያዝ ብቻ ነው የምንድነው። ያን ጊዜ ብቻ ነው ሞት በራችን ላይ ያለውን የአዲስ ኪዳኑን «ፔሳኽ» አይቶ የሚያልፈው። ይህንን የደም ማኅተም ለመያዝም ከክፋት፤ ከሀሰት፤ ከግፍና ከዐመጻ እርሾ መለየት የግድ ነው። ከዝሙት፤ ከስርቆት፤ ከጉቦ፤ ከምኞትና ከኃጢአት ሁሉ እርሾ ሳንለይ ውስጣችን የሞላውን መጻጻ ተሸክመን የፋሲካ ሕይወት የለም። እስራኤላውያን መዳን የቻሉት የፋሲካቸውን የበግ ደም ምልክት በመያዛቸው ብቻ ነው።  እኛም የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር በግ የክርስቶስን ደም ምልክት ካልያዝን በማንም በሌላ ምልክት ወይም ጻድቅ ዋስትና ልንድን አንችልም። ሁሉም ይህንን የደም ምልክት የመያዝ ግዴታ ስላለበት ማንም ለማንም ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ጳውሎስም «ልዩነት የለም፤ ሁሉም የመዳን ጸጋ ያስፈልገዋል» አለን። 

«እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ» ሮሜ 3፤22-24
እንግዲህ  ከፋሲካው ተስፋ የምናደርግ ሁላችን እስኪ ራሳችንን እንመርምር። እንደመጽሐፍ ሊያነበን በሚቻለው ከፋሲካችን ክርስቶስ ፊት እስኪ ራሳችንን እናንብበው። በእውነት እነዚህ እርሾዎች በውስጣችን ከሌሉ ከ2000 ዓመት በፊት ለሕይወት የፈሰሰውን ደም ይዘናል ማለት ነው። ያኔም ሞት በኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደሌለው አረጋግጠናል። እስራኤላውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን በቀቡ ጊዜ ሞት እንደማይነካቸው እርግጠኞች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የበለጠውንና የተሻለውን የሕይወት ደም በእምነት ስለያዝን ለዘላለማዊ ሕይወት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚያ ባሻገር በየዓመቱ በሚመጣ በዓል የሚገኝ የደም ምልክት የለም። በጥብጠባና በስግደትም የሚገኝ የሕይወት ዋስትና እንዳለ ካሰብን የፋሲካውን ምስጢር በልምድ ሽፋን ስተነዋል ማለት ነው። የተደረገልንን ማሰብ አንድ ነገር ሆኖ ሰው ግን ዓይኑን በዚያ በዓል ላይ ተክሎ የዓመቱ ኃጢአት ወይም ሸክም እንደሚወድቅ ማሰብ ስህተት ነው። ዓመቱን ሙሉ ከክፋትና ከግፍ እርሾ በመላቀቅ፤ ለአንድም ሰከንድ የማይለይ ምልክት ልባችን ጉበንና መቃን ላይ ደሙን በእምነት ይዘን መገኘት የግድ ይሆንብናል። ያኔ ነው ፋሲካችን ታርዷል የምንለው። ያኔም ነው ሁልጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ እንዳለን የምናውቀው። መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሰምርልን ዕለት፤ ዕለት መታደስ መታደስ ይገባዋል።
«ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል» 2ኛ ቆሮ 4፤16 ንስሐ እንግባና እንታደስ።
ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን ውስጣችንን መፈተሽ የግድ ነው። በአምናው እኛነታችንና በዘንድሮው እኛነታችን መካከል የሕይወት ለውጥ ከሌለን ሞት በመጣ ጊዜ ምንም የመዳን ምልክት እንደሌላቸው ፈርዖናውያንን ወደዘላለማዊ ሞት መሄዳችን እውነት ነው። በወይራ በመጠብጠብ 30 እና 40 ለመስገድ ከመሽቀዳደም ይልቅ፤ ከሞት የማምለጫ የፋሲካው ዓርማ ክርስቶስን ከኃጢአት በጸዳ ማንነታችን ውስጥ ዘወትር ይዘነው እንኑር። ዝሙት፤ ውሸት፤ስርቆት፤ ሃሜት፤ ነቀፋ፤ ምኞትና ገንዘብን መውደድ ሁሉ ሳንተው ፋሲካን ማክበር አይቻልም። ከቦታ ቦታ በመዞርም ፋሲካ አይገኝም። ፋሲካ በልባችን ላይ አንዴ የተሰራው የክርስቶስ የእምነታችን ከተማ ነው። በዚያ ላይ የማይጠፋ ብርሃን አለ። ክርስቶስ ባለበት በዚያ የልባችን ከተማ ውስጥ ማስተዋል፤ ደግነት፤ በጎነትና ቅንነት አለ። ከዚያ መልካም ከተማ የሚወጣው ሃሳባችን የተራቡትን ያበላል፤ የታረዙትን ያለብሳል፤ የታመሙትን ይጠይቃል። ኑሮአችን፤ አነጋገራችንና አካሄዳችን በልክ ነው። ዕለት ዕለት በምንኖረው ሕይወት እንጂ በዓመት አንድ ቀን በሚከበር ፋሲካ ክርስቶስን መምሰል አይቻልም። ሞት የደሙ ምልክት የሌለባቸውን እስራኤላውያንን ሁሉ ይገድል ነበርና። እኛም በሰማይ የተሰጠንን ተስፋ እስክናገኝ ድረስ ሞት ከተጠበቀልን ተስፋችን እንዳያስቀረን ፋሲካችን ክርስቶስን ዕለት ዕለት በልባችን ይዘን እንኖራለን። ያኔም በክርስቶስ ያለ ተስፋችን ምሉዕ ስለሆነ ስለመዳናችን አንጠራጠርም። አብርሃም ልጅ ሳይኖረው «ዘርህ ዓለሙን ይሞላል» ሲባል በእምነቱ ተስፋውን ተቀበለ። በክርስቶስ ትንሣዔ ያመንን እኛ ደግሞ እንደምንድን ካመን የተሰጠን የመዳን ተስፋ በሰማይ እውነት ሆኖ ይጠብቀናል።  ምክንያቱም የመዳናችን የእምነት ተስፋ ክርስቶስን በልባችን ዕለት ዕለት ይዘን እንዞራለንና!!

Monday, April 14, 2014

«ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ከሆነ እኔም አክራሪ ነኝ» የሚሉ ድምጾች ምነው በዙሳ?



የሚያከሩ እስኪበጠስ ያክርሩ፤ የማያከርና ተግባብቶ የሚኖር የት ይድረስ?
 
በአንድ ወቅት ዳንኤል ክብረት የተባለው ሰውዬ በእንቁ መጽሔት ላይ እንደተናገረው «ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ሆኖ የገደለው ሰው የለም!» ብሎ ነበር። በዳንኤል አስተሳሰብ «አክራሪ» ማለት በሃይማኖተኝነት ሰበብ ሰው የመግደል ደረጃ ላይ ሲደረስ መሆኑ ነው። ከመግደል በመለስ ያለው ኃይልና ዛቻ፤ማሳደድ ተፈቅዷል ማለት ነው? ሌላው የማኅበረ ቅዱሳን የሜሪላንድ አፈቀላጤ ኤፍሬም እሸቴ ደግሞ «አክራሪ ሃይማኖተኛ መሆን ጥሩ ነው» ሲል ተመራጭነቱን በማሳየት የማኅበረ ቅዱሳንን የማክረር እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲታትር ታይቷል።  አክራሪ በባህሪው እኔ ትክክል ነኝ ከሚል ጽንፍ ተነስቶ፤ የምለውን ተቀበሉኝ፤ እምቢ ካላችሁ ወግዱልኝ፤ አለበለዚያ እኔው በኃይል አስወግዳችኋለሁ በሚል ድምዳሜ የሚያበቃ አስተሳሰብ ነው።  አንዳንዶች አክራሪነት በዚህ ዘመን የተከሰተ አድርገው ሲመለከቱ ይታያል። ትርጉሙና የተግባራዊ እንቅስቃሴው ስፋትና ጥልቀት ተለይቶ ታወቀ እንጂ አክራሪነት ጥንትም ነበረ።  በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9 ላይ እንደተመለከተው ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንደነገራቸው «አስቀድማችሁ ወደሰማርያ ከተማ ሂዱና፤ ጌታ ይመጣል ብላችሁ አስናድታችሁ ጠብቁኝ» ብሎ ባዘዛቸው ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች መልዕክቱን እንዳልተቀበሉ ሐዋርያት ስለተመለከቱ «ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን?» ብለውታል።  ጌታ ግን፤ «የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም» ብሏቸዋል።  አክራሪዎች ራሳቸውን የእግዚአብሔር ብቸኛ ወታደሮች አድርገው ራሳቸውን ያስቀምጣሉ። ስለዚህ እኛን ያልመሰለ ይጥፋ ባዮች ናቸው። አስተምሮ፤ ተከራክሮ መመለስ ስለማይችሉ አጭሩ መፍትሄ ማስወገድ ነው።
እንደዚሁ ሁሉ በፖለቲካው ከተሰማሩት ድረ ገጾች አንስቶ እስከጥቃቅኖቹ ብሎጎች ድረስ አንዱ ከአንዱ እየተቀባበሉ የማያውቁትን ማኅበር ለማሳወቅና ለሃይማኖት ማክረር እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጹ ጽሁፎችን እስከማራገብ ድረስ ዘልቀዋል።  በፌስቡክና በትዊተር ገጾች «ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ከተባለ እኔም አክራሪ ልባል» ከሚለው ድምጽ አንስቶ የማኅበረ ቅዱሳንን ዓርማ የሚያሳይ ግለ ስእል በመለጠፍ አጋርነታቸውን ለማሳየት የሞከሩ ብዙዎች ናቸው።  ሁሉንም ስንመለከት «አክራሪ ሃይማኖተኛ» መሆን አስፈላጊ እንደሆነና «እኛም የዚሁ ሰልፍ አባሪ ሆነን ለሃይማኖታችን አክራሪ ነን» የሚል ይዘት ያለው አቋም እየተንጸባረቀ መገኘቱን መገንዘብ ይቻላል። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉቱ ወገኖች ያሉበትን ምክንያት ከማየታችን በፊት ፖለቲከኞቹ ነገሩን ለማስጮህ የፈለጉበትን ምክንያት እንመልከት።

1/ ፖለቲከኞች ማኅበረ ቅዱሳንን የመደገፍ ምክንያት፤

ፖለቲከኛ ሃይማኖት የለውም ማለት ባይቻልም ሃይማኖተኛ ግን ፖለቲከኛ መሆን አይችልም። ፖለቲከኛ ሃይማኖት ሊኖረው የሚችለው ስለሃይማኖቱ አውቆና አምኖበት በመከተሉና እምነቱ የሚያዘውን ለመፈጸም እንደእግዚአብሔር ቃል ለመኖር ለራሱ ኪዳን የገባ ሳይሆን በውርስ ከቤተሰቦቹ የተረከበው ወይም በልምድ ሲከተለው ስለኖረ ራሱን ሃይማኖት እንዳለው አሳምኖ ሲያበቃ ከፖለቲካ የሚገኘውን የምድራዊ ሳይንስ ጫወታ የሚጫወት ሰው ነው።
 ምክንያቱም ፖለቲካ ባላጋራህ የሆነውን የሌላኛውን ሰው አመለካከትም ሆነ ተግባር በምትችለው መንገድ በልጠህ ወይም ጠልፈህ በመገኘት ምድራዊ ሥልጣንን መቆጣጠር ማለት ሲሆን ሃይማኖት ደግሞ የሰውን ልጅ ጠላትነት የማይቀበል፤ ባላጋራውም ሰይጣን ብቻ መሆኑ አምኖ ለእግዚአብሔር መንግሥት ሲል ሃይማኖታዊ መመሪያውን በመከተል ለማይታየው ሰማያዊ ሕይወት ሲል ከሚታየው ጠልፎ የመጣልና የመዋሸት ዓለም የጸዳ ማለት ነው። የዲሞክራሲ ጣሪያ ነክተናል ከሚሉት አንስቶ የነሱኑ መንገድ ተከትለናል እስከሚሉቱ ድረስ ሁሉም ፖለቲከኞች በፖለቲካል ቲዎሪ ከሚነገረው ታሪክ ባሻገር ማስመሰል፤ መዋሸት፤ ማታለል፤ ጠልፎ መጣል ወይም እውነተኛ መስሎ መታየት፤ ሀቀኛ፤ የህዝብ ወገንተኛ መሆንን መደስኮር በሁሉ ዘንድ መኖሩ በማስረጃ አስደግፎ መናገር ይቻላል።  በግርድፉ የተቀመጠውን የፖለቲካ ትርጉም ብንመለከት ለምድራዊ ስልጣን መታገል የመጨረሻ ግብ መሆኑ እውነት ነው።
« Politics is the activities associated with the governance of a country or other area, esp. the debate or conflict among individuals or parties having or hoping to achieve power»
« ፖለቲካ ከሀገራዊ ወይም ከክልላዊ የሕዝብ አስተዳደር ክንዋኔዎች ጋር በተዛመደና በተለይም በተቃርኖአዊ የእርስ በእርስ የሃሳብ ፍጭት የተነሳ ተስፋ በሚሰጥ የፓርቲዎች ስነ ሞገት ብልጫ አግኝቶ የስልጣን ኃይልን የመጨበጥ ግብ ያለው ነው»
ፖለቲካዊ ስልጣን ማለት ግን ለሃይማኖተኛ ጥቅም አይሰጥም፤ ወይም አይጎዳም ማለት አይደለም። እንደሚመራበት የፖለቲካ ርእዮት /አመለካከት/ ይወሰናል። ሃይማኖታዊ መንግሥት ባለበት ሀገር መንግሥቱ ለተመሰረተበት ሃይማኖት አብላጫውን ወይም ዋናውን አገልግሎት ይሰጣል። ሌሎች ሃይማኖቶች እንደመንግስታዊው ሃይማኖት እኩል መብት ሊኖራቸው አይችልም።  ሃይማኖት የለሽ መንግሥት ከሆነ ደግሞ ሁሉም ሃይማኖቶች የመንግስቱ ጠላቶች ነው። ሴኩላር/ ገለልተኛ/ የመንግስት አወቃቀር ባለበት ሀገር ደግሞ መንግስት በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ይደነግጋል። ጣልቃ የማይገባው ለሴኩላር መንግሥታዊ አወቃቀሩ ስጋት እስካልሆኑ ድረስ ብቻ ነው። እንደመንግሥታዊው የፖለቲካ አወቃቀር ሥርዓቱ ሃይማኖትን ሊጠቅም ወይም ሊጎዳው መቻሉ እርግጥ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ በአፄዎቹ፤ በደርግና በኢህአዴግ መካከል ባለው የፖለቲካ ርእዮት የተነሳ ፖለቲከኞቹ ሃይማኖትን የሚመለከቱበት መነጽር የተለያየ ነው። ሃይማኖትን በተለያየ መነጽር የሚያዩ ፖለቲከኞች፤ ሃይማኖተኞች ሊሆኑ አይችሉም።  ፖለቲከኞች የቆሙለትን የተለያየ የፖለቲካ ስርዓት ያገለግላሉ።  ፖለቲከኛ ሆኖ ሃይማኖተኛ ለመሆን ከባድ የሚሆነው ለዚህ ነው። ሃይማኖተኛ ሆኖ መዋሸት አይቻልም። ፖለቲከኛ  ስርአቱን እስከጠቀመ ድረስ ይዋሻል፤ የሌለ ተስፋ ይሰጣል።  አላስፈላጊ ወይም ጠቃሚ ካልሆነ ደግሞ ማስተባበያ ወይም ይቅርታ ሊጠየቅ ይችላል። ለሃይማኖተኛ ንስሀ እንጂ ማስተባበያ ወይም ይቅርታ የሚል የአደባባይ ዲስኩር የለም። ፖለቲከኛ ሃይማኖት ሊኖረው ቢችልም ሃይማኖተኛ ግን በጭራሽ ፖለቲከኛ መሆን አለመቻሉ እርግጥ ነው። ታዲያ የልምድ ሃይማኖት ያላቸው ነገር ግን ሃይማኖተኛ መሆን የማይችሉ ፖለቲከኞች ማኅበረ ቅዱሳን ሲነካ የሚጮሁት ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። ዋናው ነጥብ «የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው» ከሚል የፖለቲካ ፍልስፍና የተነሳ ነው። 

 ሃይማኖት የሌላቸው /እምነት የለሾች/ ይሁኑ ማኅበረ ቅዱሳንን በልምድ የሚመሳሰሉ ባለሃይማኖቶች እና «ማኅበሩ ተነካ ማለት የእግዚአብሔር መንግሥት ተነካ» ባይ የዋሆች ሁሉም በአንድነት ውጥንቅጡ በወጣ አቋም ውስጥ ሆነው ለማኅበሩ ለመጮህ ሞክረዋል። የሚገርመው ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳንን መጥፋት የሚመኙ እስላሞች ሳይቀሩ «የሃይማኖት ነጻነት ይከበር» በማለት ለማኅበሩ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት መሞከራቸው ነው። ዋነኛ ዓላማቸው የሃይማኖት መከበር ስላሳሰባቸው ሳይሆን በእስልምና ጎራ ያሉ ታሳሪዎችን ድምጽ ከማኅበረ ቅዱሳን ጎራ ካሉት ጋር በማስተሳሰር ጉዳዩን ለማጦዝ ከመፈለግ የተነሳ ነው።  በዘመነ ኢህአዴግ እስልምና ተጨቁኗል ቢሉ ለሰሚው ግራ ነው።  በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ የእስላም መስጊድ ከቤተ ክርስቲያን ቁጥር የበለጠው በዘመነ ኢህአዴግ መሆኑ በጭራሽ ሊስተባበል የሚችል አይደለም።  ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ 16% ለሆነው የእስልምና ተከታይ 180 በላይ መስጊዶች ሲኖሩት 74% ከመቶው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር 150 ገደማ ብቻ ነው። በኦርቶዶክስ ተጨቁነን ነበር የሚሉትን አቤቱታ እንደኢህአዴግ ያካካሰላቸው መንግስት ለእስላሞች የለም ማለት ይቻላል። በዘመነ ኢህአዴግ የተሰራው መስጊድ በሺህ ዘመናት ውስጥ ከተሰራው ይበልጣል።
 እንዳላት ተከታይ ብዛትና ሊኖራት እንደሚችለው የድርሻ ስፋት ድምጿ ያልተደመጠው ኦርቶዶክስ ናት ማለት ይቻላል። ከመንግሥታዊ ክፍል ያሉ፤ ፕሮቴስታንቱም፤ እስልምናውም፤ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ የሚለው አሮጌ ፖለቲከኛው ሁሉንም ስንመለከት በግልጽም ይሁን በስውር ይህች ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ ባበረከተችው ከመጠቀምና በስሟ ከመነገድ በስተቀር ያደረጉላት አንዳችም ድጋፍ የለም። ላበረከተችው በጎ አስተዋጽኦ ዋጋ መስጠት በራሱ ትልቅ ነበር።

ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን «ልጠፋ ነው» እያለ ለሚያሰማው ጩኸት ፖለቲከኞቹን ያስተባበራቸው ኢህአዴግን እንደጋራ ጠላት ለመፈረጅ እንጂ በሃይማኖት ስለተሰሳሰሩ አይደለም። ኦርቶዶክስ እንድትጠፋ ሲሰሩ የቆዩ የቀድሞ መንግስት ፖለቲከኞች፤ የተለያዩ የሌኒናዊ ፓርቲ አባላትና ርዝራዦች ሳይቀሩ ለማኅበረ ቅዱሳን ሲጮሁ እያየን ነው። እውን ለኦርቶዶክስ አዝነው ነው? የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ መሪዎች ከመግደል አንስቶ፤ ጣልቃ ገብቶ በመሾም፤ ሲኖዶሱን በመከፋፈልና በማዳከም ትልቅ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ጮኸው የማይሰለቹ ፖለቲከኞች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመደገፍ መሞከራቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም ቀጣይ ተግባራቸው ማሳያ ተደርጎ ከሚወሰድ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማኅበሩም ሆነ ከፖለቲከኞቹ ያተረፈችውም ምንም ነገር የለም።

2/ ሃይማኖተኞች የማኅበሩ ደጋፊዎች፤

ማኅበሩ ራሱ እንደሚለው ከሆነ 35,000 መደበኛ አባላትና 500,000 ተከታይ አባላት እንዳሉት ይነገራል። ያለውን የፋይናንስ አቅም በትክክል ባይናገርና ባናውቅም ቅሉ ከልዩ ልዩ የንግድ ተቋማት ገቢ ምንጮቹ የሚያገኘውን ካፒታል ሳንጨምር ከ35,000 አባላቱ ላይ ብቻ በግርድፉ ብንገምት በወርሃዊ መዋጮ መልክ 10 ብር ቢሰበስብ 350,000 ብር ወርሃዊና ከ500,000 ተከታይ አባላቱ ላይ ደግሞ ለልዩ ልዩ የማኅበሩ ልማታዊ ስራዎች ሰበብ በዓመታዊ ድጋፍ 10 ብር በነፍስ ወከፍ እንዲሰጡት ቢጠይቅና ካሉት ተከታይ አባላቱ መካከል 400,000 ያህሉ ለ10 ብር የድጋፍ ጥያቄው ምላሽ ቢሰጡ 4,000,000 ብር ያገኛል ማለት ነው። ከወርሃዊ  የአባልነት መዋጮ ገቢው ጋር በዓመት ሲሰላ ከ8 እስከ 9 ሚሊዮን ያላነሰ በዓመት ይሰበስባል ማለት ነው። ይህ ስሌት በመንፈሳዊ ጉዞ ሰበብ፤ በመጽሔት፤ በሆቴልና በሱቅ ሽያጭ፤ በካሴት፤ በሲዲ፤ በእርዳታ ጥሪ፤ ከበጎ አድራጎት፤ ከለጋሽ፤ ከቤት ኪራይ ወዘተ የሚገኘውን ግዙፍ ገቢ ሳይጨምር መሆኑ ታሳቢ ይደረግ።  ጆርጅ በርንስ እንዲህ ይላል። « Don't stay in bed, unless you can make money in bed»  «አልጋህ ላይ ሆነህ ገንዘብ ካላገኘህ በቀር አልጋህ ላይ አትቆይ» እንደማለት ነው። ይህ ብሂል የገባው ቅዱስ ማኅበር «መኒ» ይሰራል። «መኒ» የማይገዛው ስልጣን፤ ጉልበትና እውቀት በሌለበት ዘመን የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አይባልም።

ይህ ማኅበር ከአንታርክቲካ በስተቀር በሁሉም ዓለማት ላይ ቢሮዎች አሉት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ ሁሉ አለ። በሳንባዋ ይተነፍሳል፤ በደም ስሯም ይዘዋወራል። ነገር ግን መዋቅሩና የመዋቅሩ መረብ ማኅበረ ቅዱሳዊ ነው። አብዛኛው አባላቱና ደጋፊዎቹ አብረው የተሰለፉት ቤተ ክርስቲያኒቱን የደገፉና የረዱ እየመሰላቸው መሆኑ እርግጥ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ከዘመኑ ጋር መዘመን ባይችልና ባንቀላፋበት ቦታ ሁሉ ማኅበሩ እየተገኘ ከበሮ እየመታ፤ እየዘመረ አለሁልሽ እያለ ማኅበሩንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለይቶ የሚያይ ተከታይ ባይኖር አያስገርምም።  የሚገርመው እንመራሃለን የሚሉቱ የማኅበሩ ተመሪ ሆነው መገኘታቸው ነው።

ሀ/ ሊቃነ ጳጳሳቱ፤

ሊቃነ ጳጳሳቱን ማኅበሩ እንዴት አባል አድርጎ እንደሚይዝ ዝርዝር ውስጥ አንገባም። ነገር ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ የሲኖዶስ አባልና በቤተ ክርስቲያኒቱ የአንዱ ሀገረ ስብከት ወይም ክፍል ተጠሪ ሆነው ሲያበቁ የማኅበሩን ዓላማ ተቀባይ፤ የማኅበሩ ጠበቃና ተከራካሪ ሲሆኑ ግርምት ይፈጥርብናል። ዋናው ጥያቄ የሚነሳውም ማኅበሩ የሲኖዶሱ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ነው ወይ? ሊቃነ ጳጳሳቱ በሀገረ ስብከታቸው መሥራት ያልቻሉትን የሚሰራላቸው ወኪላቸው ነው ወይ?  ምን መስራት ያልቻሉትን፤ ምን መስራት እንዲችልላቸው፤ የትኛውንስ ጉዳይ እንዲያስፈጽም ውክልና ተሰጥቶታል?
 በማኅበሩ ስያሜና ቁመና እንዲሁም በሲኖዶስና በሊቃነ ጳጳሳት መካከል ያለው የሥልጣን፤ የደረጃ ክፍተት የሚለካው በምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ግራ የሚያጋቡና ምላሻቸውንም በውል የሚያውቅ አለመኖሩ ጉዳዩን አስደማሚ ያደርገዋል።  ስለዚህ ጥርት ያለ መልስ የሌለው የአንድ ማኅበር ዓላማ በአእምሮአቸው የሰረጸ ነገር ግን የሲኖዶስ አባል ነን የሚሉ ሊቃነ ጳጳሳት በአንድም፤ በሌላ መንገድም የማኅበሩ ጉዳይ ፈጻሚ ሆነው መገኘታቸው እርግጥ ነው።

ለ/ ወጣት የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ የጥምቀት ተመላሽ ማኅበር፤ የጉዞና መንፈሳዊ ማኅበራት፤

እነዚህ ወጣት ክፍሎች ከማኅበሩ ሰፊና ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ አንጻር በቁጥጥር ስር መዋላቸው የግድ ነው። ደግሞም አስፈላጊ መሳሪዎች ናቸው። በአንድ በኩል በችግር ወቅት ለማንቀሳቀስ፤ በሌላ መልኩም በችግር ቀን ለመደበቅ ሊያገለግሉ ይችላሉ። መሰረታዊ የትጥቅ መሳሪያቸው ደግሞ «ቤተክርስቲያንን ከልዩ ልዩ ኃይሎች መጠበቅ» የሚል መንፈሳዊ መሰል ትጥቅ ሲሆን ወጣቶቹ ዓይናቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በእምነት እንዲጥሉ በማድረግ ማኅበሩ ለሚፈልገው ዓላማ ማገልገል እንዲችሉ ተደርገው ይቀረጻሉ። ወጣቶቹ በእርግጥም ከልባዊ እምነት ተነስተው የሚከተሉ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንን እንደማገልገል እንጂ ማኅበሩን እንደመታዘዝ አይቆጥሩም ወይም ማኅበሩን ማገልገል የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ እንደመፈጸም አድርገው እንዲያስቡ ተደርገዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሰንበት ተማሪዎች፤ የጥምቀት ተመላሽ ቡድኖችና የጉዞ ማኅበራት የማኅበሩ ታዛዥና ተጠባባቂ ኃይሎች ናቸው። የእነዚህ ማኅበራት አባል ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳንን ማውገዝ ወይም መቃወም በጭራሽ አይታሰብም።

ሐ/ የመንግሥት ተቋማት አባሎቹ፤

ማኅበሩ ከሚያገኘው ሰፊ የፋይናንስ አቅም አኳያ አባላትን ለመመልመል መጠቀሙ እንዲሁም ከሚጓዝበት አደገኛ የስብከት ዘዴው አንጻር አእምሮአቸውን የመጠምዘዝ ስልት ረገድ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ብዙ አባላትን ማደራጀት ችሏል። የማኅበሩን አቅም ማደራጀት ብቻ ሳይሆን አንድ አቅጣጫ ማየት እንዲችሉ ተደርገው የተቀረጹ የመንግሥታዊ ተቋማት አባላቱ በጣም ጠቃሚ ክፍሎቹ ናቸው።  በመንግሥት ጉዳይ እንደማይገቡ ማሳያዎቹ ናቸው። በሌላ መልኩም የመረጃ ምንጭ ሆነውም ያገለግላሉ። የየትኛውም የመንግሥት ተቋማት ሰራተኛ በየትኛውም ማኅበርና የእምነት ተቋም ውስጥ አባል የመሆን መብት ያለው መሆኑ ባይካድም የያዘውን የመንግስት ስራ ለማኅበሩ አገልግሎት ማዋል ግን ወንጀል ነው። ፖሊሳዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም ለማኅበሩ አገልግሎት ተሰማርተው ያላግባብ ያሰሩ፤ የደበደቡ አሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትጠይቃቸው ከመተባበር ይልቅ ማኅበሩ ሲጠራቸው አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ የመንግሥታዊ ስልጣን አካላት መኖራቸው ማኅበሩ የቱን ያህል ስር እንደሰደደ ያሳያል። እነዚህ አካላት ከማኅበሩ ጎን በግልጽም፤ በስውርም መቆማቸው ነገሩን ከባድ ያደርገዋል።

3/ ማኅበሩ ራሱን ለማዳን የሚቀያይራቸው ስልቶች፤

ማኅበሩ የልዩ ልዩ ሰዎች ተዋጽኦ መሆኑ እንዳለ ሆኖ አመራሩ ራሱን ከወቅቱ የፖለቲካ ሙቀት ጋር በማስማማት የሚያደርጉት የጉዞ ስልት እጅግ የሚደነቅ ነው። ማኅበሩ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዳይደለ ይታወቃል። የድርጅት/ Organization/ ቅርጽ ያለው ነገር ግን በተቋምነት/ Institution/ ደረጃ የተደራጀ ይመስላል። ደግሞም በቤተ ክርስቲያን ስር ያለ የሰንበት ተማሪዎችም ማኅበር ለመምሰልም ይሞክራል። ምሁራን አመራሩ በሳል ስለሆኑ ከሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ስር ያወጡት አለምክንያት አይደለም። የሰንበት ት/ቤት በመባልና የሚንቀሳቀስበት ቅርጽ ተመሳሳይ ስላይደለ እንዳይበላሽበት ከመፈለግ የተነሳ የተዘየደ መላ መሆኑ ነው። ዛሬም ያ የማኅበሩ አመራር ኢህአዴግ ከገባበት የሙስሊሞች እንቅስቃሴ፤ ከምርጫ 2007 ዝግጅት እና የጥላቻ ፖለቲካ ካሰባሰባቸው ኃይሎች ጋር ያለበትን ክፍተት በመጠቀም ከመንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት ለመጠቀም እየሰራ ይገኛል። በአንድ ወገን ስለማኅበሩ ጉዳይ እያስጮኸ ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ከጩኸቱ በሚገኘው የስውር ድምጽ ብዛት መንግሥት ወደያዘው ፤ልቀቀው እሰጥ አገባ እንዳይሄድ ባለበት በማስቆም ለመንግስት ፈቃዳት ሁሉ ታማኝ መሆኑን ለማሳየት በመሞከር ራሱን በማዳን ስልት ላይ ተጠምዷል። የቅዱሳን ማኅበር ሳይሆን ጠንካራ የፖለቲካ ቅዱሳን ያሉት ማኅበር ስለሆነ ሊደነቅ ይገባዋል።

4/ ማኅበሩና የመጨረሻ ውጤቱ፤

በትግርኛ የሚተረት አንድ ተረት አለ። «ወጮስ እንተገምጠልካዮ ወጮ» ይላሉ። «ብርድ ልብስን ብትገለብጠው ያው ብርድ ልብስ ነው» እንደማለት ነው። ያውም የደብረ ብርሃን ብርድልብስን ብትገለብጠው ያው ዥንጉርጉሩ  የደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ ነው። የሰንበት ት/ቤት?/Sunday school/  ድርጅት? /organization/ ተቋም? /Institution/ የቱ እንደሆነ ማኅበረ ቅዱሳን እስካሁን የለየለት አይደለም። ነገር ግን ቅርጹንና መልኩን እንደእስስት እየቀያየረ 22 ዓመት ቆይቷል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለማኅበሩ ምኑ እንደሆነች ሲኖዶሱ በእርግጥ አያውቅም። ማኅበሩ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዴት እንደሚጠቀምባት አሳምሮ ያውቃል። በጣም አደገኛና ስልታዊ ጉዞ የማድረግ ብቃት ያለው አመራር እንዳለው በጉዞው ላይ የሚያጋጥመውን ሳንካ ካለፈበት ተነስቶ መናገር ይቻላል። እውነተኛና ቅን የቤተ ክርስቲያን አባላት የሱም አባል መሆናቸው ሳይዘነጋ ማለት ነው። ነገር ግን ማኅበሩ  ቢደግፉት፤ ቢከተሉት፤ ቢጮኹለት፤ ቢታገሱት እንደ«የደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ ቢገለብጡት ያው ብርድ ልብስ» ከመሆን የሚያልፍ አይደለም!!