Monday, July 22, 2013

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጉዞና ልምላሜ የተለየው ዛፍ አንድ ናቸው!

አዲስ አበባ የሀገሪቱ ርእሰ መዲና እንደመሆኗ መጠን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በገንዘብ፤ በባለሙያና በሠራተኛ አቅም ትልቁ ሀገረ ስብከት ነው። በዚህ ሦስት ተቋማዊ አቅም በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለሌሎች ሀገረ ስብከቶች የሚተርፍ በቂ ኃይል ያለው ሀ/ስብከት ነው። የርእሰ መዲናይቱ ሀ/ስብከት እንደመሆኑ መጠን የተሻለ ሥራ፤ ክፍያና ኑሮ ለማግኘት ከገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን የሚፈልሰው አገልጋይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የሚያሳዝነው ግን አዲስ አበባ ከተማ ከተኛችበት እየነቃች እዚህም እዚያም ጉች ጉች ብለው የሚታዩት ግንባታዎችና የተዘረጉ መንገዶች ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለውጥ ምን እንደሚመስል ለማየት የሚያስችል ዐይን እንዲኖረው የፈየደለት ነገር አለመኖሩ ነው። የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደር ወደኋላ መሄድ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬም የሚታይበት አንዳች እንቅስቃሴ የለም። ለውጥ የሂደት ክስተታዊ ግዴታ ቢሆንም ይህ አመክንዮ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ለምን እንዳልጎበኘው ግራ ያጋባናል። ምናልባት እንደ ቀንድ አውጣ የዐርባ ዓመት እንቅልፉን አልጨረሰ ይሆን? ጊዜ ደግሞ ታክሲ አይደለም። ጊዜ ሲሄድ ባለበት ከሚቆመው ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በስተቀር።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ተቋማዊ የኋሊዮሽ መንገድ ስንገመግም ቤተክርስቲያኒቱ የት እንዳለች ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል። እነማን ቤተ ክርስቲያኒቱን እየመሯት እንዳሉ ያመላክተናልም። በሌላ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያኒቱን የ40 ዓመት የቀንድ ዐውጣ እንቅልፍ ውስጥ እንደገባች የተቀመጡባት ሰዎች አመራር ይጠቁመናል። ዋልታ የሌለው ጣሪያ በአናቱ ዝናብ ማስገባቱ አይቀርምና ለጣሪያው መበስበስ የአናቱ ክፍተት ምክንያት ከመሆኑ ውጪ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መበስበስ የላይኛው ጣሪያ የመበስበሱ ምልክት ተደርጎ ቢወሰድ አያስኬደንም ትላላችሁ?
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የበሰበሰ ጣሪያ ለመጠጋገን ብዙ ተሞክሯል። መጽሐፉ እንደተናገረው በአሮጌው አቁማዳ ላይ አዲስ ለመጣፍ እየተሞከረ መበጣጠሱን የከፋ አደረገው እንጂ የተቀየረ አንዳች ነገር የለም። በእነ እገሌ ዘመን የነበረው አስተዳደር ጥሩ ነበር እንዳንል የሁሉም ዘመን ችግር በመጠን ከሚበላለጥ በስተቀር በይዘቱ አንድ ነው። በእርግጥ ይዘቱ መጠኑንና ዓይነቱን ጨምሮ ዛሬ ሀ/ስብከት ሳይሆን «ኃላፊነቱ የተወሰነ የነጣቂዎች ማኅበር» ወደመሆን በመሸጋገሩ ከድሮዎቹ አስተዳደር ዛሬ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱ እውነት ነው። አንዱን ሾሞ አምሮቱ ሲጠረቃ ሌላ ያልጠረቃ በመሾም ችግሩን በማባባስ በኩል ያ! ያልታደለው ሲኖዶስ ለሀ/ስብከቱ ውድቀት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ምክንያቱም ሲኖዶሱ ያልጠረቃውን በጠረቃው አመራር በማለዋወጥ ካልዘሩበት የሚያጭዱ ነጣቂዎችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማኅበር አደራጅቶ ባልለቀቃቸውም ነበር። 

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ንቡረ እድ መምህር ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እያሉ አውድማውን ሳያሄዱ የተመረተውን ዝም ብለው የሚቅሙ አጋሰሶችን አፍ በመዝጋታቸው ብቻ በእህል በሎች ክስ ባላባረሯቸውም ነበር። የሆነው እውነታ ግን ጠርጎ በሎችን መረን ለቆ፤ «ሊሰራ የማይወድ አይብላ» ብለው የታገሉትን ጠንካራ ሰው ባላባረረም ነበር። ድሮስ ጠርጎ በልን ሊታደግ የሚችለው ከጠርጎ በል በቀር ማን ሊሆን ይችላል?
የንቡረ እድ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ ወንጀል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሙዳየ ምጽዋት ዘረፋ ማስቆም መቻላቸው ነበር። ከ200 ሺህ ብር በላይ ተቆጥሮ የማያውቀው የመንበረ መንግሥት ቅ/ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ  ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የተቆጠረው በንቡረ እድ ገ/ማርያም ክትትል መሆኑ ታሪክ መዝግቦታል። የሌሎቹም አድባራት ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች እየተዘቀዘቁ ከመገልበጥ የተረፉት በኚሁ ሰው አስተዳደር ዘመን ስለመሆኑ ገልባጮቹ ሳይሆን አገልጋይ ካህናቱ የሚናገሩት እውነታ ነው። ምን ያደርጋል ታዲያ? እውነተኛና ሀቀኛ እርሟ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ንብረ እድ ገ/ማርያምን ከአዲስ አበባ ወደሽሬ  በመወርወር ሲኖዶሱ ቁጭቱን ተወጣባቸው። ገልባጮችንም አስደስቷል። አባ ገ/ማርያም ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መነሳታቸውን የሰሙ ምሽት ሙዳየ ምጽዋት ገልባጮች ሻምፓኝ ሲራጩ ማደራቸው ተሰምቷል። እንግዲህ ይህ ክፍል ነው በመበደሉ ምክንያት ሲኖዶሱ በነፍሱ የደረሰለት። አሳዛኝ ዘመን?
ዛሬ ደግሞ በፓትርያርክ ማትያስ ምርጫ ላይ የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱት አባ እስጢፋኖስ ለፈጸሙት የታማኝነት አገልግሎት ከፓትርያርኩ በገጸበረከትነት የቀረበላቸው ስጦታ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሲሆን በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስነት ሽፋን ተዝቆ የማያልቀውን ካዝና የድርሻቸውን እንዲናኙ  ተመድበው እነሆ ከመነሻው በስመ ሥልጠና ሽፋን ተረክበው እያመሱት ይገኛሉ። የሚያሳዝነው ደግሞ ገና ምኑንም ሳይጀምሩ አባ እስጢፋኖስ አድባራቱን ገንዘብ አዋጡና ወደ ሀገረ ስብከቱ ገቢ አድርጉ እያሉ ሥልጠና በተባለው አሰልቺ መድረክ ላይ ነጋ ጠባ መጮሃቸው ነው። አዋጡ ማለት ምን ማለት ነው? ፐርሰት ክፈሉ ነው? ወይስ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የሚጦራቸው ድኩማን አሉት? ጥያቄውን ለአቡኑ እንተውና ከአዋጡ ጭቅጨቃቸው የምንረዳው እውነታ ቢኖር ሀ/ስብከቱ ዛሬም ፈውስ የራቀው መሆኑን ነው። ሥልጠና በተባለው የጩኸት መድረክ ላይ ሥልጠናውን የሚካፈሉት እነዚያው የቤተ ክርስቲያንን ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ሰዎች መሆናቸውን ስናይ አቡኑ አዲስ ነገር መጀመራቸውን በማሳየት በቀደመው ጎዳና ለመሄድ ያቀዱት ስላለመሆኑ የሚያሳምን አንዳች  ሥር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ አለመኖሩ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።  ስልጠና በተለወጠ ሰውና ለለውጥ በተዘጋጀ አእምሮ ላይ የሚዘራ ዘር እንጂ የለውጥ መንገድ እንቅፋት ሆኖ በቆየና በጨቀየ አእምሮ ላይ ሲሆን ስናይ ረዳት ሊቀጳጳሱ ወይ ስራውን አያውቁትም፤ ወይም ስራው አያውቃቸውም።
 አቡነ ቀውስጦስ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳሉ በተጠናወታቸው ዘረኝነት የጎጣቸውን ሰዎች እያመጡ ሲሰገስጉና ሲያሳድጉ ንቡረ እድ ገ/ማርያም በሩን ዘግተ አላሳልፍ ስላሏቸው ብቻ በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ከሳሽ ሆነው መገኘታቸውን አንዘነጋውም። ዛሬም አቡነ እስጢፋኖስ የንቡረ እድ ገ/ማርያምን ወደ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ዳግም የመመለስ የካህናት ጥያቄ አልቀበልም ያሉት ንቡረ እዱ እጅ ከወርች አስረው ረጅም እጆችን ሁሉ ስለሚያስቆሙ ከወዲሁ የተወሰደ መላ መሆኑ ይገባናል። አቡኑ ሙስናን የሚዋጉ ከሆነ ምነዋ! የሙስናውን በር ድርግም አድርገው የዘጉትን ንቡረ እድ በሥራ አስኪያጅነት ማስቀመጥ ፈሩ? በእርግጥ አቡኑ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሳሉ ጥንቱኑ በሩን የከፈቱት እሳቸው አይደሉ እንዴ? ስለሆነም ሙስናን የመዋጋት ብቃትም፤ ሞራልም የላቸውም። ስልጠና መልካም ቢሆንም ሙስና በስልጠና አይጠፋም። ሙስናን በሚጠየፍና ለመዋጋት በተዘጋጀ አመራር እንጂ በገንዘብ አዋጡ ስልጠና ሊሆን አይችልም። የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤትም ይሁን አድባራቶቹ በእነማንና በተደራጀ አዲስ አመራር ተዋቅሯል?
 ሙስናው ከዐለማውያኑ በዐይነቱ የከፋ ሆኗል። አፍኒንና ፊንሐሶች ተፈልፍለዋል። ሁሉም በዐመጻው ተካክሏል። ጠቅላላው ታማሚ በመሆኑ መድኃኒት የሚሆን ነገር ርቋል። ለዓለም ትተርፍ ዘንድ አደራ የተጣለባት ቤተ ክርስቲያን በባላንጣ ተወራለች።  አሳዛኝ ዘመን!
የሚገርመው ደግሞ ሰሞኑን ከጳጳሱ እግር ከሥር ሥራቸው ቱስ ቱስ የሚሉ የማኅበረ ቅዱሳን አሸርጋጆችን ስንመለከት  በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ እንደፈለጉ ለመፋነን እድል ማግኘታቸው ጠቋሚ ሲሆን የሚፈሩትን ማኅበር ለማገልገል ግንባራቸውን እንደማያጥፉ  የሊቀ ጳጳሱ የቆየ ልምድ ደግሞ ያረጋግጥልናል። ከወዲያ ፓትርያርክ ማትያስ በቀጥታ መስመር በውዳሴና በተጠናው ደካማ ጎን በኩል በለስላሳ ጥበብ ተይዘዋል። ከወዲህ አቡነ እስጢፋኖስ በረዳት ሊቀ ጳጳስነት ተጠፍንገዋል። በመሀከል የሲኖዶስ ጸሐፊው የማቅ ታማኝ አባል አባ ሉቃስ ተቀምጠዋል። ጥሩ የመድረክ አዳማቂ የነበሩት አቡነ ጢሞቴዎስ ለማኅበሩ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለምርቃት ሳይበቃ በጎዶሎ ቀን ከኮሌጅ ተማሪዎች ጋር ተጋጭተው ከሥፍራ ተወግደዋል።  ያገለገሉትን መለስ ብሎ የማያየው ይህ ማኅበር ከአባ ጢሞቴዎስ ጋር ራሱ ተጣልቶ ከመለያየት የገላገለው የተማሪዎቹ ግርግር ሳያስበው መከሰቱ ነበር። ከጀርባም ሆኖ የተማሪዎቹን ችግር በማራገብ ነዳጅ ያርከፈክፍ የነበረው ይህ እድል ሳያልፈው ለመጠቀም ካለው ፍላጎት የመነጨ ነበር። ያሰበው በተማሪዎቹ ችግር ጀርባ ፍጻሜ አገኘ።  ከዚህ የተነሳ ማኅበሩ በትኩስ በትኩስ ምድብተኞች ለመገልገል እድል ያረግድለታል ወይም  አካሄዱን ያውቅበታል። ይኸው እንደ ሳሙና እየተሙለጨለጨ ዛሬ ላይ ደርሷል። ከዚህ በፊት ውጥረት ሲበዛበት የዐባይን ቦንድ እገዛለሁ እስከማለት መድረሱ እንደሳሙና በመሙለጭለጭ ላለመያዝ መሄድ የሚችልበት ስልት ረቂቅ መሆኑን ያሳያል።
ከላይ እያልነው እንደመጣነው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ  ዛሬም አዲስ ለውጥ የለም። በላተኞች ስልጠና እየወሰዱ ከመሆኑ በስተቀር አዲስ የሥራ ኃይል፤ አዲስ የመዋቅር ለውጥ የለም። አሁንም የታመነባቸው፤ የሚታወቁና የተመሰከረላቸው ሰዎች በለውጥ ሂደቱ ውስጥ የሉም። በአምናውና በካቻምናው በሬ አርሶ ምርት መጠበቅ ከቶ እንዴት ይቻላል? ካልዘሩበት ማጨድ ማለት ይህ ነው።
ሁለት ወገኖች ግን ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ሀ/ስብከቱ በፓትርያርክ ማትያስ የተሰጣቸው ሽልማት ሲሆን ከዚህ በሚገኘው ሲሳይ የሚናኙት አዲሱ ሊቀ ጳጳስና ከአባ ጳውሎስ ሞት በኋላ ታማኞቹ ብቻ ቦታ ቦታቸውን የያዙለት ማኅበረ ቅዱሳን ተጠቃሚዎች ናቸው።
ከዚህ በተረፈ ሀ/ስብከቱ ከሕመሙ ይድናል ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርገን የሚታይ አዲስ መንፈስ፤ አዲስ መዋቅር፤ አዲስ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት፤ አዲስ የውጤት ምዘና ስልት፤ አዲስ የልማት እቅድ የለም። ካህናቱ ከላይ የሚፈሰውን መመሪያ እንደቧንቧ ከሚጠጣ በስተቀር በሂደቱ ላይ ወሳኝ አካል ተደርጎ አልተወሰደም። ጉዞው ከየት ወደየት? ነው ብንል ከድጡ ወደማጡ ነው መልሳችን። ገንዘብ አዋጡ፤ ገንዘብ አዋጡ! ድሮም ዛሬም ከሀ/ስብከቱ ውስጥ ያልጠፋ የበላዮች ድምጽ አልቀረም። ዛሬ ላይ ይህንን እንደዘገብን አምላክ ቢፈቅድ የዛሬ ዐመትም እንዲሁ የለውጥ ያለህ ብለን እንዘግብበት ይሆናል። የዚያ ሰው ይበለን!

Friday, July 19, 2013

«መጽሐፈ አበው» ስለመነኮሳት ምን አለ?

ምንኩስና ምንድነው? ለመጽደቅስ ጠቃሚ ነው?  የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ስልት ነው? የክብር ወይስ የመከራ፤ የተጋድሎ ወይስ የፍልሰት ጎዳና ነው? ብዙ ሊባልለት የሚችልና ሊባልበት የሚገባ ይህ ሰዋዊ ሥርዓት ቆሜለታለሁ ከሚለው ዓላማ ጋር እየተጣረሰ ዘልቆ በዚህ ዘመን ያለበትን ደረጃ እንድንመለከት «መጽሐፈ አበው» የተባለው ትልቁ መጽሐፍ  በምንኩስና ላይ ካሰፈራቸው ሕግጋት ውስጥ በጥቂቱ ለማቅረብ ወደድን። የግእዙን ትርጉም አንብበው ይህ ሰዋዊ ሥርዓት ዛሬ በሕይወት አለ ወይ? ብለው ራስዎ ይጠይቃሉ።  የሕይወት መንገድ የመሆን፤ አለመሆኑ ጉዳይ ተከድኖ ይቆየንና ምንኩስና ራሱ ተነስቼበታለሁ ከሚለው አቋሙ ጋር ዛሬ ላይ የለም። መነኩሴስ ማነው? «መጽሐፈ አበው» እንዲህ ይናገራል።
መነኮስ ከሀገሩ ወደሌላ ሀገር ይሂድ። በዚያም በዋሻ፤ በኮረብታው፤ በተራራው ይንቀሳቀስ። በረሃብ፤ በብርድ፤ በጥም፤ በመራቆት፤ በድካም፤ በትጋት ይኑር። ልብሱ የከብት ቁርበት፤ የፍየል ቆዳና ለምድ ይሁን። ሥጋ በሕይወት ዘመኑ አይብላ። የዘወትር ምግቡ የበረሃ ጎመን፤ ቅጠልና የዛፎች ፍሬ ብቻ ይሁን። ካገር አገር አይዙር። ወደሠርግ፤ ወደ ድግስ አይግባ። በሕዝብ መካከል የሚኖር መነኮስ ቢኖር እርሱ ውሸታም ነው። የአጋንንት ረድእ፤ አገልጋይ ነው። ወንድ መነኩሴና ሴት መነኩሲት በአንድ ላይ አይኑር፤ ይራቁ። በአንድ ላይ እየኖሩ፤ በአንድ አጸድ እያደሩ ንጽህ እንጠብቃለን ቢሉ ውሸት ነው። ነብርና ፍየል አንድነት ይኖሩ ዘንድ እንዴት ይቻላል? መነኩሴ ማንንም አይማ። ሃሜተኛ ጸሎተኛ አይደለም። አብዝቶ የሚበላ መነኩሴ የትም እንደሚፈነጭ ፈረስ ነው። መነኩሴ በፀሀይ ግባት አንድ ጊዜ ብቻ ይብላ። ወፎች መብል አይተው በወጥመድ ይያዛሉ። ትልቁ አንበሳ በመብል ምክንያት ወጥመድ ውስጥ ይወድቃል። አዳም በመብል ወደቀ። ይሁዳ ከወጡ አጥልቆ በበላ ጊዜ ሰይጣን ገባበት። ሠይጣን መነኮሳትን በመብል ፤በመጠጥ፤ በሃሜት፤ በሳቅና በስካር ያድናቸዋል። ልቅ፤ ልቅ እየጎረሱ፤ የላመ የጣመ እያግበሰበሱ መነኮስ መባል አይገባቸውም። በእንቅልፍ ተውጠው፤ ከጸሎት ተለይተው እንደአዞ ተገልብጠው እንዲተኙ ያደርጋቸዋል። ዘማውያንም ይሆናሉ። ያኔም አጋንንቱ በመነኮሳቱ ላይ ይዘፍናሉ። በእጃቸውም ይጨበጭባሉ። እንደፈረሶች ሰኮና ሆነው ይረግጡአቸዋል። የዓለምን ጣዕም የቀመሱ፤ የወደዱ መነኮሳት የነፍሳቸውን ደዌ ያያሉ። የነፍሳቸውንም መድኃኒት ይተዋሉ። በሕዝባውያን መካከል የሚመላስ መነኮስ  ከቅዱሳን ክብር መድረሻ የለውም። መነኮስ ወደዓለማዊ ችሎት፤ ሸንጎና ፍር አይሂድ።  ምሥክር አይሁን። መነኩሴ ማለት ምዉት ማለት ነውና አይቻለሁ፤ ሰምቻለሁ፤ ዳኝነት አውጡልኝ አይበል። ለሕዝባውያን አበ ነፍስ አይሁን። መነኮስ የሞተ ነውና የሚሰማ ጆሮ፤ የሚናገር አፍ የለውም። ዓለም ውስጥ እየኖረ ዓለምን አሸንፋለሁ ቢል ውሸታም ነው። አትመነው። አፉን፤ ጆሮውንና ዓይኑን የማይጠብቅ መነኩሴ ነፍሱን አያድናትም። መነኮስ እነዚህን ሦስት ሰይፎች ካልታጠቀ መነኮስ አይባልም። የዋህነት፤ ትህትናና ድህነት ናቸው። የዋህነት ከቂም፤ ከበቀል ከጥላቻና ከስጋዊ ነገር ሁሉ መራቅ ነው። ትህትና ራስን ዝቅ ማድረግ ሲሆን ድህነት የኔ የሚለው ሀብትና ገንዘብን ሁሉ መናቅ ናቸው። መነኮስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል። በሕይወት ዘመኑ በእንደዚህ ያልተጠበቀ መነኮስ፤ መነኮስ አይደለም።

Thursday, July 18, 2013

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምን ተሐድሶ ያስፈልጋታል? ክፍል ሁለት፡-

      
              (www.tehadeso.com)
ላደግንባት፣ ቃሉን ላወቅንባት እና አሁንም እያገለገልንባት ላለችው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ሁሉ ዐዲስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል በመደገፍ እንደ ቃሉ የሆነ እና የሰላም አለቃ የሚሰለጥንበት ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት፣ በሙሉ ልባችን እናምናለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተዘፍቃበት ካለው ሁሉን አቀፍ ችግር ለመውጣት የሚያግዛት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚከናወን ተሐድሶ አስፈላጊ ነው፡፡
“…እንደ ምሕረቱ መጠን ለዐዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን..”  የሚለው ዐረፍተ ነገር፣ ተሐድሶ በእግዚአብሔር መንግሥት አስፈላጊው እና ፍሬያማው እውነት እንደሆነ ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረት ከፍተኛነት በመንግሥቱ ውስጥ ለሚኖረን ቦታ የሚያበቃን፣ በመንፈስ ቅዱስ በኩል የሆነው መታደስ ነው፡፡ ይህ እውነት ለግለሰብም ለቤተ ክርስቲያንም በእኩልነት ይሠራል፡፡ አንድ ሰው ከጠፋው ማንነቱ ተመልሶ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ እንዲሆን ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው ተሐድሶ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ቤተክርስቲያንም የቀበረችውን እውነት ቆፍራ እንድታወጣ እና ለእግዚአብሔር ሐሳብ እሺ በጄ ብላ እንድትታዘዝ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡

ባለፈው በክፍል አንድ ጽሑፋችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምን ተሐድሶ አንደሚያስፈልጋት ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶችን አንሥተን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡  ዛሬ ደግሞ ቀጣይ ሐሳቦችን እናቀርባለን፡፡

•    የሥጋዊ  አሠራር ሥር መስደድ፡-


በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሰውና መንፈሳዊ አሠራር ከጠፋ ሰነባብቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገሮች ሁሉ በጸሎት የእግዚአብሔርን ምሪት በመፈለግ ሳይሆን የሚሠራባት፣ የሰውን ፊት በማየት የሚከናወኑባት የዓለማውያን ሸንጎ ሆናለች፡፡ ከሞላ ጎደል በማንኛውም ጉዳይ ለማለት ይቻላል ቤተ ክርስቲያኗ የእግዚአብሔርን ምሪት ጠይቃ አገልጋዮችዋንና ምእመናኗን አስተባብራ በአንድነት በጸሎት በፊቱ ወድቃ የምትከውናቸው ነገሮች የሏትም፡፡ ይልቁንም በአሠራርዋ ከእሷ የተሻለ እንቅስቃሴ ካለው ከመንግሥት ፖሊሲዎች እና ወቅታዊ አጀንዳዎች በመነሣት እነዚያን አጀንዳዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማስፈጸም ከመሯሯጥ ያለፈ ሥራ ተሠርቶ አይታወቅም፡፡ መንግሥት “አቅም ግንባታ” ሲል ቤተ ክህነትም አቅም ግንባታ፣ መንግሥት “ደን ልማት” ሲል ቤተ ክርስቲያንም ደን ልማት፣ መንግሥት የፀረ ሙስና ርምጃ ሲወስድ ቤተ ክርስቲያንም ያውም ላትተገብረው ስለ ሙስና ማውራትን እንደ ትልቅ ቁም ነገር ወስዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የአሠራርም ሆነ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ምንም  ዝግጅትና ርምጃ ሳታደርግ የሰሞኑ ነጠላ ዜማዋ አድርገዋለች፡፡
እውነተኛው ባለ ራእይና የምሪት አለቃ እግዚአብሔር ተረስቶ፣ ትልቁ ሕገ መንግሥት መጽሐፍ ቅዱስ ተዘንግቶ “ምን ተባለ” እያሉ ሥራ ለመሥራት መሞከር በእስካሁን እንቀስቃሴዋ እንደታየው የተሻለ ለውጥ አላመጣላትም፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎችና አፈጻጸሞች የተሳሳቱ ናቸው ባንልም፣ ቤተ ክርስቲያን ግን በእግዚአብሔር መንግሥት አሠራር ውስጥ የዓለማዊውን መንግሥት አሠራር ሙሉ በሙሉ ያውም ምን እንደሆነ እንኳ ሐሳቡ ሳይገባት ለመፈጸም ከሞከረች የሥጋዊነት መገለጫዋ ነው፡፡
በሌሎችም በቤተ ክርስቲያን በሚሠሩ ሥራዎች፣ የእግዚአብሔርን ቤት እንደ መንደር እድር በዘፈቀደ የመምራት እንቅስቃሴዎች ስለምታደርግ፣ ይበልጥ ከእግዘአብሔር ሐሳብ ሲያርቃት እንጂ ወደ ዘላለማዊ አምላኳ ሲያስጠጋት አላየንም፡፡ የሚደረጉት ማንኛቸውም ነገሮች ሥጋ ሥጋ ከመሽተት ያለፈ አንዳች መንፈሳዊነት አይታዩባቸውም፡፡ ከነጭራሹም መጽሐፍ ቅዱስ ተነብቦ የማይታወቅ እስኪመስል ድረስ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ አሠራር ጠፍቷል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሲኖዶስ ጉባኤ እንደሚገኝ ለማሳየት  በጉባኤው አንድ ባዶ ወንበር ቢቀመጥም፣ መንፈስ ቅዱስ ከሲኖዶስና ከቤተ ክርስቲያን ሥፍራ ካጣ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የማናውቃቸውን ብዙ “ቅዱሳትና ቅዱሳን” እንድንቀበል አድርጋ በስማቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ስታስገነባላቸው ለመንፈስ ቅዱስ ግን ሥፍራ አልተገኘለትም፤ በርግጥ በሚያምኑበት ልብ ውስጥ ያድራል እንጂ የሰው እጅ በሚሠራው ሕንፃ አይኖርም፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ሥጋዊነትም፣ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ቤት ገፍቶ ሲያስወጣው እንጂ ወደ ንጉሥ ክርስቶስ ቤት ሲመልሰው አልታየም፡፡ ያደጉባትን ቤተክርስቲያንንም፣ በዚህ ሥጋዊነትዋ ምክንያት “አይንሽን ለአፈር” እያሉ ጥለዋት የሚሄዱ ምእመናን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊነትዋን ጥላ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራች ለብዙዎች ፈውስ ትሆን ዘንድ ተሐድሶ ያስፈልጋታልና “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” እንላለን ፡፡


•    አስተዳደራዊ ብልሽቷ አገልጋዮቿንና ሕዝቧን ስላስጨነቀ


ስለ ኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ሲነሣ፣ አብሮ ሳይነሣ የማይታለፍ ነገር አስተዳደራዊ ብልሽቷ ነው፡፡ ይህ ርእስ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስና በእግዚአብሔር ቃል የተመሠረተ ሁለንተናዊ ተሐድሶ አግኝታ ወደ ጥንተ ቅድስናዋና ክብሯ መመለስ ይገባታል የምንለውን እኛን እና ቤተ ክርስቲያን ከቶውንም ለውጥ አያስፈልጋትም “ስንዱ እመቤት ናት” የሚሉትን ወገኖች ያስማማናል፡፡ አስተዳደራዊ ብልሽቱን ሰዎች የሚያነሡበት መንገድ ይለያይ እንጂ  “የቤተ ክርስቲያኗ ህልውና ያሳስበኛል” የሚል ወገን ሁሉ ያለ ልዩነት የሚያነሣው ርእስ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያንዋ ከተቋማዊ እንቅስቃሴ ይልቅ የግለሰቦች ጠንካራ እና ደካማ ጎን ተገዢ መሆኗ በርግጥ ያሳስባል፡፡ ባለፈው ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አካባቢ የነበረው የአሠራር ዝርክርክነት ከእሳቸው ጋር ጠቅላይ ቤተክህነቱም የሞተ አስመስሎት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በሰው ላይ የተደገፈ አስተዳደራዊ ሥርዓት ፍጻሜው ይሄ ነው ለማለት፣ የብፁዕነታቸውን እንደ ምሣሌ አነሣን እንጂ፣ ከእሳቸው በፊት የነበሩትም አሁንም ያሉት ፓትርያርኮች አሠራር ተመሳሳይ ነው፡፡ በዙርያቸው የሚሰበሰቡ ሰዎችም እነርሱ የሚፈልጉት እስከተሳካ ድረስ ለሌላ ነገር ግድ የሚላቸው አይደሉም፡፡
የደብር አስተደደር ሹመት እንኳ በጥንት ዘመን ከነበረው አውቀት ተኮር ሹመት፣ አሁን ወደ ዝምድና እና ጉቦ ተኮር ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ እንዲህ ያለው ሹመት፣ አንድን የደብር አስተዳዳሪ፣ በደብሩ ውስጥ ከሚገኙት በእውቀት ሻል ካሉ አገልጋዮች ይቅርና ከአንድ ዲያቆን ጋር እንኳ የሚስተካከል  ክብር ስለማያሰጠው መናናቁና ጥላቸው፣ ቡድናዊነቱና ወገንተኝነቱ ሥር የሰደደ ነው፡፡ በእውነትና በእውቀት ማስተዳደር ስላልተቻለ፣ ሊቃውንቱ ተገፍተው ጨዋና ወሬ አመላላሹ ተከብሮ እና ተፈርቶ ይገኛል፡፡  የሥራ ድርሻውን የሚያውቅና ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ ሰውም ስለጠፋ ምእመኑ የክርስትና ካርድ እንኳ ለማውጣት ጉቦ እየተጠየቀ ይገኛል፡፡ የአገልጋዮች ቅጥር፣ ዝውውር እና የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ወጥ የሆነ ሕግ ስለሌለ በአስተዳዳሪው እና በሀገረ ስብከት ሹመኞች ይሁንታና ተጠቃሚነት፣ ነገሮች እንደፈለጉ የሚደረጉበት ደብር እጅግ ብዙ ነው፡፡ በብዙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ መሪጌቶች ከዲያቆን ያነሰ ደመወዝ ስለሚከፈላቸው፣ ተስፋ የሚቆርጡበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ከተማ አቀፍ የደመወዝ አከፋፈል እስኬል ስለሌለ የተሻለ ደመወዝ የሚከፍል ደብር ለመቀጠር እና ለመዘዋወር ያለው ሹክቻና የሚጠየቀው መደለያ ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ የአስተዳደር ችግር ውጤት ነው፡፡
በአስተዳደር ችግር ውስጥ እንደገና ሊታይ የሚገባው ቤተ ክርስቲያንዋ የፋይናንስ አያያዝ ነው፡፡ ከገንዘብ አሰባሰቡ ጀምሮ በዐፄ ምኒልክ ጊዜ ከነበረው የገንዘብ አስተዳደር የተሻለ ነገር ምንም  የላትም፡፡ በገንዘብ አቆጣጠር ላይ ያለውን አካሄድ ስንመለከተው፣ ለአታላይ በጣም የተመቸ ነው፡፡ ምንም ዐይነት ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ መንገድ የማይታይበት፣ ዘመናዊውን የሂሳብ አያያዝ ዘዴ የተማረ ሰው የማይቀጠርበት፣ የደመ ነፍስ መድረክ ሆናለች፡፡ ሌላው የሂሳብ አያያዙ ከፍተኛው ድክመቷ፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተረስቶ  “ወነአምን በአሀቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” የሚለው የአባቶች ትምህርት ተዘንገቶ፣ ደብሮች  እንደ ፌደራል መንግሥት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚፈለግባቸውን ብር ከሰጡ በኋላ፣  ገንዘቡን በገዛ ፈቃዳቸው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉበት መሆኑ ነው፡፡ ገጠር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በደመወዝና በንዋየ ቅዱሳት እጦት እየተዘጉ በአዲስ አበባ ግን ሰባ እና ሰማንያ ሚሊየን ብር በዝግ አካውንት የሚያስቀምጡ ደብሮች መኖራቸው የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡
ቤተ ክርስቲያን አንድ እንደሆነች ከንግግር ባለፈ በቃሉ የሚታመን ከሆነ፣ የኑሮ ድካም ትከሻቸውን አጉቡጧቸው ወደ ከተማ የሚሰደዱትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን ለመታደግና ባሉበት ቦታ በቂ ገንዘብ ከፍሎ ለማኖር ይቻል ነበር፡፡ ምእመኑ ከቤተ ክርስቲያን የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ ቀድሞ የሚታየው ኪሱ እንጂ ልቡ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ መሆንዋ ከቀረ ሰንብቷል፡፡ እንደ መንግሥት ቢሮ  ገንዘብ ያለው ከፍሎ የሚስተናገድባት የሌለው ተገፍቶ የሚወጣባት ቤት መሆንዋ ለብዙዎች የልብ ስብራት ምንጭ አድርጓታል፡፡
እንደዚህም በእጅጉ የሚያሳዝነው የአስተዳደር ብልሹነት መገለጫ በገጠር ያሉ እና ሊዘጉ የተቃረቡ አብያተ ክርስቲያናትን ለሀገረ ስብከት የተመደበባችሁን ብር አልላካችሁም በመባል የሚደርስባቸው ማስፈራራት እና “ቤተክርስቲያኑን እንዘጋዋለን” ቁጣ ነው፡፡ ለእነዚህ የገጠር ካህናት፣ በነጻ የሚያገለግሏት ቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊዎች የአባትነት ፍቅርና ምስጋና ማቅረብ ቢያቅታቸው እንኳ የኑሯቸውን ሁኔታ እያወቁ ማስጨነቅ ባልተገባቸው ነበር፡፡ ዲታዎቹን የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የእስፖንሰር ገንዘብ እየጠየቁ ለቅንጦት ነገሮች ከማዋል፣ በጭንቅ በሬ ሸጠው ዓመታዊ መዋጯቸውን እንዲከፍሉ የሚገደዱትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አባቶች መታደግ ይገባ ነበር፡፡
ይህንን የአስተዳደር ብልሹነት በቤተክህነት ሥር የሰደደውን ሙስና ባለፈው ሰኔ 29/2005 ዓ. ም.  ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ምረቃ ላይ መምህር ልዑል የተባሉ ሰው በዘይእሴ ቅኔ እንዲህ ሲሉ ገልጠውታል፡፡
ቤታችን ሆኗል ቤተ ወንበዴ፣ እጅግ ያሣዝናል በእውነት የሚፈጸመው ግፍ ተግባሩ፡፡
ሊቃነ ጳጳሳት ፍቀዱና፣  ቢ. ፒ. አር. ወፀረ- ሙስና ገብተው ይመርምሩ፡፡
ብዙዎች ስላሉ በግል መዝብረው የከበሩ፡፡
ዘረፉኝ እያለች በቀን ምንም ሳይፈሩ፡፡
ሙዳየ ምፅዋት ምስኪን ትጮኻለችና በበሩ
ዘረፉኝ እያለች በቀን ምንም ሳይፈሩ፡፡

እንዲህ ያለውን የውስጥ ብሶት በአደባባይ ሲቀርብ ሰምቶ ከማጨብጨብ እና ይበል ብለናል ከማለት ያለፈ የተደረገ ነገር የለም፡፡
ባለፉት ብዙ ወራት ሊፈታ ያልቻለውና ይልቁንም እየተባባሰ ያለው፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ጉዳይ ሌላው በቤተክርስቲያን የተንሰራፋውን አስተዳደራዊ ችግር አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ተማሪዎች ችግር አለብን ሲሉ ሰምቶ የሚያስተናግድ እና ችግሩን የሚፈታ አባት አልተገኘም፡፡ በየአቅጣጫው ከእውነታ ይልቅ ለሁኔታ እና ለቀረቤታ የሚያደሉ አሠራሮች ቤተክርስቲያኗን ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፡፡ ደቀመዛሙርቱን በግፍ ለማባረርና አስተዳደራዊ ጥያቄያቸውን ላለመመለስ፣ ፖለቲካዊ መልክ እንዳለው በማስመሰል ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት በመሪዎች እየተወሰደ ያለው ርምጃ አስተዳደራዊ ብልሽቱን ከማጋለጡም በላይ ጉዳዩን በንቀት እየተመለከቱት መሆኑን ማሳያ ነው፡፡  
ሌላው የአስተዳደር ብልሹነቱ ገጽታ የሆነው በሐዋሳ፣ በክብረ መንግሥት፣ በዲላ፣ በሐረርና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩት ችግሮች እና የምእመናን መንገላታት ነው፡፡  ለችግሮቹ “ይህ ነው” የሚባል መፍትሔ ሳይሰጠው አሁንም እንደ ቀጠለ መሆኑን ስናስብ በተለይ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ፣ ሲኖዶሱን እየተማጠነ ላለው ሕዝብ በእጅጉ እናዝናለን፡፡ የዚህ ችግር ፈጣሪዎች ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹም መንፈስ ቅዱስ ይመራዋል የሚባለው ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳት መሆናቸውን ማሰብ ልብን ያደማል፡፡ የመፍትሔ አመንጪ መሆን የሚገባቸው አባቶች የችግሩ ፈጣሪዎችና አባባሾች መሆናቸው የሚያስገርም እውነት ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን ያለው የአስተዳደር በደል እና የሥራ ዝርክርክርነት ከመነገር በላይ ነው፡፡ አገልጋዩም ሆነ ሕዝቡ በቤተ ክርስቲያን ባለው አስተዳደራዊ በደል ተስፋ ቆርጦ እና አዝኖ ይገኛል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር በቶሎ መስተካከል ካልቻለ እንደደነበረ በግ እየበረረ የሌሎችን በረት በመሙላት ላይ ያለውን የምእመናን ፍልሰት በእጅጉ ያባብሰዋል፡፡ ከዚህ እና ከሌች አስተዳደራዊ ችግሮች ለወውጣት ተሐድሶ አማራጭ የሌለው መንገድ ነውና ደግመን መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ ልንል እንወዳለን፡፡
ይቀጥላል! …