(To read in PDF please Click here )
አንድ ጥያቄ እናስቀድም፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ ይልቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካዊ ዜጋ ስለመሆንና አለመሆን ጉዳይ ይመለከተው ይሆን? ለማንኛውም «ሐራ ዘተዋሕዶ» መሳጩን የሲኖዶስ ውይይት በቦታው
የነበረ ያህል በአስደማሚ ዘገባ አቅርቧልና እንዲያነቡት እነሆ!
‹‹ቤተ ክርስቲያን ስትጠራኝ እምቢ እላለኹ ወይ ! ! !›› /ብፁዕ አቡነ ማትያስ/
‹‹አጃቢ ነን!›› /ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል/
‹‹እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ እኔ እጠፋለኹ›› /ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ/
‹‹እኛ መናጆ ተብለን ነው የገባነው፤ የሚመረጠው አባ ማትያስ ነው›› /ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ/
‹‹ነገ በታሪክ የሚጠየቅና የሚወገዝ ሲኖዶስና አባት መኖር የለበትም›› /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/
ከላይ በዋናው ርእስ የተመለከተው÷ ቁጭት እንጂ አቅም ያነሳቸው ንግግሮች የተሰሙት ትላንት፣ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም
በፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ለመወያየት የተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውል ያለው ግልጽ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ከቀትር በኋላ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡
በስብሰባው ሂደት÷ ለፕትርክናው የተሠየሙትን ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ተሳትፎ በነበራቸው ብፁዓን አባቶች መካከል የነበረው የከረረ የቃላት ልውውጥ፣ ተሳትፎ ባልነበራቸው ብፁዓን አባቶች ላይ የታየው ስጋትና ድብታ፣ በኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ምትክ የኮሚቴውን ሪፖርት ያቀረበው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ለቅ/ሲኖዶሱ ጠረጴዛና ለአጀንዳው ታላቅነት የማይመጥን፣ ውክልናውና ያጸደቀለትን ማኅበር የሚያስንቅና የሚያስወቅስ ደርዝ የሌለው ንግግር፣ በዋናነትም ስብሰባው የተጠናቀቀበት ውል አልባ ኹኔታ ነው ይህን የሐዘን ንግግር ያናገረው፡፡ በዚህ ቃል ሲናገሩ ከተሰሙት አረጋውያኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥቂቱን ለመጥቀስ÷ አቡነ አትናቴዎስ፣ አቡነ ኤርሚያስ፣ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ኤፍሬም እና ከዕጩዎች አንዱ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡
ስብሰባው ጠዋት 3፡00
ላይ በውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ እና መልክአ ማርያም ጸሎት ከተከፈተ በኋላ ዐቃቤ መንበሩ የዕለቱን የስብሰባ አጀንዳ ሲያስተዋውቁ፣ ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴውን ሪፖርት ሰምተን ለማጽደቅ ነው፤›› በሚል ነበር ያስጀመሩት፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ተጠርተው ገብተው በሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በኩል የዕጩዎች አመራረጥ፣ ዝርዝርና ማንነት በንባብ ከተሰማ በኋላ የነበረው የስብሰባው ድባብ ግን፣ ሰምቶ ማጽደቁ ቀርቶ የተጋጋሉ ውይይቶችንና ትችቶችን ያስተናገደ፣ ከሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በቀር ብዙኀኑ የኮሚቴው አባላት አንዳች የውስጥ ክፍፍልን በሚያሳብቅ አኳኋን (በተለይም ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ) በእጅጉ አዝነውና ተክዘው የታዩበት፣ ኮሚቴው ከብፁዓን አባቶች ለቀረቡለት ጥያቄዎች የተረጋገጠ መልስ ሊሰጥ ያልቻለበት አሳዛኝ ኹኔታ ነበር፡፡
ኮሚቴው የተረጋገጠ ወይም በቂ ያልኾነ ምላሽ ሊሰጥባቸው ያልቻለባቸውና ለተካረረ መንሥኤ የኾኑ ዋነኛ ነጥቦች፣ የመጀመሪያው÷ ዕጩ ፓትርያሪኮች የቀረበቡበት መንገድ የምርጫ ሕገ ደንቡ ተሟልቶ ያልተፈጸመበት መኾኑ ነው፤ ሁለተኛው÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይሎች ተጽዕኖ እና ለውስጥ ቡድኖች ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ እኒህን አከራካሪ ነጥቦች በየጊዜው ባወጣናቸው ዘገባዎች እያጋለጠናቸው ቆይተናል፤ እስኵ አሁን ደግሞ በስብሰባው ሂደት ከተንሸራሸሩት ሐሳቦች አንጻር በመጠኑ እንመልከታቸው፡፡
በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ከዋነኛ አነጋጋሪ ነጥቦች አንዱ÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይል ተጽዕኖ እና ለውስጥ ኀይሎች ጥቅማዊ ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ የውጭ ኀይል ሲባል ሌላ ማንም ሳይኾን የመንግሥት ተጽዕኖ ማለታችን ነው፡፡