Friday, July 20, 2012

ለሁሉም ነገር መልካም ጤንነት ይሁንልዎ!


መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ሰሞኑም መታመማቸውን ከሰማን ጊዜ ጀምሮ ሞታቸው እንዲቃረብ ከሚጸልዩት ጀምሮ ፤ በሀገሪቱ ውስጥ እየታየ ባለው የልማት እንቅስቃሴ ላይ አንድ ምዕራፍ ላይ ሳያደርሱ በሞት እንዳይሉ እስከሚማጸኑት ድረስ አይተናል። ከዚህ በተለየም  በሦስተኛው ረድፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት የማይመኙ ነገር ግን በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ በደል ስላደረሱ፤ ከህመም ኃያልነት የተነሳ ጠላቶቼ ከሚሏቸው ወይም ከሚጠሏቸው ጋር እርቅን የሚፈጽሙበት ጊዜ  እንዲሆንላቸው የሚመኙትንም  ተመልክተናል።
እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በታሪክ አጋጣሚ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው። መሪነትና የፖለቲካ ስልት እንደማይነጣጠሉ ሁሉ ከፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመነጭ አመራር ሀገሪቱን እየመሩ 21 ዓመታትን አሳልፈዋል። በዚህ የአመራር ዘመን ያልተደሰቱ እንዳሉ ሁሉ በእሳቸው አመራር የሚመኩ መኖራቸው አይካድም። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የተደሰቱባቸውና ያዘኑባቸውን ሰዎች ማንነትና የፖለቲካ ልዩነት፤ ምንነቱንና አፈታቱን ለማብራራት ስላልሆነ ያንን ለሚተነትኑ ሰዎች ትተን በጤናቸው ዙሪያ ማለት በሚገባን ላይ ለማተኰር ነው።
እንደእኛ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህመም  ወይም በሌላ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ አብሯቸው ይወገዳል ብለን አናስብም። የጠቅላይ ሚኒስትሩም በህይወት ረጅም ዘመን መኖርም እንደዚሁ የሀገሪቱ የተጠራቀመ የዘመናት ችግርና ውስብስብ የፖለቲካ ባህል ባንድ ጊዜ ያበቃለታል ብለን አንጠብቅም።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን ሁኔታ ከእሳቸው መኖርና መሞት ጋር በሚያዛምዱ ሰዎች ዘንድ ያለን ልዩነት ከነባራዊ ሁኔታ የሚነሳ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም እንደ መልካም አጋጣሚ በመመልከት ሞታቸውን በሚጠባበቁ ሰዎች በጣም እናዝናለን።  ስለሞቱ ማንም ምስጥ ሆኖ አይበላቸውም። በሕይወት ቢኖሩም ማንም  ቤተመንግሥት ገብቶ በምኞት ወንበሩን አይረከብም።
ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ሰሎሞን!
የሚወዳቸውም ቢኖር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጥላቻ ላላቸው ሰዎች ማማካሻ መስጠት ስለማይችል፤ ለጥላቻችንም ሆነ ለፍቅራችን እንደሰብአዊ ፍጡር ዳርቻ ቢኖረው  ጥሩ ነው። ሚዛናዊ ሰዎች ብንሆን እግዚአብሔር በዚህ አመለካከት ይደሰታል እንጂ ቅር አይሰኝም።
 አንዳንድ ጊዜ በአጭሩ የምንመኘው ነገር ረጅም ጠባሳ ሊያደርስ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴን ግንድ ላይ በስቅላት በመቀጣቱ ተበድናል ያሉቱ ተደስተው ነበር። የሚወዱት ደግሞ በሞቱ እጅጉን አዝነው እንደነበር አይዘነጋም። ሳዳም ያልፈጠራቸውን ሰዎች እየገደለ ነፍስና ሥጋቸውን በመለየቱና ለዚህ ድርጊቱ እሱም የእጁን ማግኘት አለበት በማለት  በተመሳሳይ መንገድ ያልፈጠሩት ሰዎች የሳዳምን ነፍስና ሥጋ   ግንድ ላይ በሞት ለይተዋል።  ሳዳም  ያልፈጠራቸውን ሰዎች ገደለ፤ ሳዳምንም ያልፈጠሩት ሰዎች ገደሉት። ሁለቱም  ያልፈጠሩትን ሰው በመግደል አንድ ናቸው።
እንደዚሁ ሁሉ ለአቶ መለስ ስህተቶች፤  ሞታቸው  ለእኛ ማካካሻ ይሆናል ማለት የደካማ አስተሳሰብ ውጤት  ነው። ምክንያቱም  በሳዳም ሞት ምክንያት ያልፍልናል የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው ኢራቃውያን  እንኳን ሳይቀሩ  117,000  ሞተዋል። 4 ሚሊዮን ኢራቅን ጥለው ተሰደዋል። ሳዳም ከበደላቸው ይልቅ የሳዳም ድንገተኛ ስቅላት የፈጠረው የኢራቅ ቀውስ ከባድ ነው። ዛሬም አላባራም። በሀገራችንም አፄውን ሌባ ሌባ ያሉና በሞታቸው እልል ያለ ሁሉ በቀይ ሽብር ወዮ! ወዮ! ለማለት ዓመት አልፈጀባቸውም። ስለዚህ አሁን ይሆን ዘንድ የምንመኘውን ነገር ቆይቶ ምን ይከተለዋል ማለቱ ጠቃሚ ነው።
 እንደዚሁ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደህልም አላሚዎቹ በድንገት ቢሞቱ፤ በሚፈጠረው ክፍተት ሀገሪቱ ችግር ላይ አትወድቅም ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል። ሥልጣናቸውን የሚመኝ ማንም ስለተመኘ አያገኝም። በድንገተኛ ሞት ምክንያት በሚፈጠር ቀውስ ሥልጣን ወደ ደም ማፋሰስ ሊያመራ፤ ሕዝቡንም ሊያቃውስ ይችላል። ቢያንስ ቢያንስ፤ የመተካካት ሁኔታ እስኪኖር የሃሳብና የአመለካከት ሽኩቻ መኖሩን የማይጠረጥር ቢኖር እሱ የዋህ ነው። ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስብ ሰው በአቶ መለስ ሞት ሳይሆን ሥልጣን በሕጋዊ መንገድ በሕይወት ሳሉ እንዲሸጋገር መመኘት የተሻለ መሆኑን ማሰብ እንጂ ህመማቸው አጣድፎ ሞታቸውን እንዲያቃርብ ማለም ከጤነኛ አእምሮ የሚመነጭ አይደለም።
ሥልጣን ምን ጊዜም  በሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ሽግግር እስካልተደረገበት ድረስ ቀውስና ብጥብጥ  ሊከተለው ይችላል። ስለዚህ እንደ ደጀ ብርሃን ብሎግ እምነት፤
1/ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ከደረሱበት ህመም ድነው ፈውስና ጤንነት እንዲጎበኛቸው እንጸልያለን። ለታሰሩ፤ ለተሰደዱና በሀገሪቱ ውስጥ በሰላም መኖር ለሚፈልጉ ሁሉ መንግሥት አባት ነውና ይቅር እንዲሉም እንመኛለን።
2/  አንዳንዴ ከዚህ ዓለም ገዢ የፖለቲካ መንፈስ ወጣ ብለው፤ ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ህይወት በማሰብ  ቢያሳልፉ ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም እንላቸዋለን። በጤንነት ዘመን መሪነት እንዳለ ሁሉ በጤንነት መጣት አልጋ ላይ መዋል፤ ሞትና ከሞት በኋላ  ስላለው ነገር ማሰቡን ባይረሱ ምክራችን ነው።
3/  ለመሥራትም፤ ለመስማማትም፤ ይቅርም ለማለትና ከፖለቲካው መንፈስ ለመውጣትም ቢሆን የእርስዎ ጤና መሆን አስፈላጊ ነውና እግዚአብሔር ጤናውን እንዲያድልዎ ጸሎታችን ነው።
 ለሁሉም ነገር መልካም ጤንነትና የቀና ሃሳብ መጻዒ ጊዜ ይሁንልዎ!

Thursday, July 19, 2012

«ደጀሰላም» ብሎግ እንዴት እንደሚያጭበረብር ተመልከቱ!


 የማቅ አፈቀላጤ ስለሆነውና ከዳላሱ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ራሱን ስለገነጠለው ቄስ መሥፍን ማሞ አዲስ የሥራ ፈጠራ ጉዳይ በ10/11/2004 ወይም በ(17/7/2012) ዓ/ም  ዝርዝር ሀተታ ደጀብርሃን ብሎግ ማስነበቧ ይታወሳል። ከዚያም  ስለ ላስቬጋስ ኪዳነ ምሕረት ጢም አልባው መነኩሴ ጥቂት ዳሰሳ አድርገን ወደምእራቡ ክፍለ አሜሪካ ተጉዘን፤ በመምህር ወ/ሰማዕት ስለሚመራው ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን የማቅ ሰርጎ ገቦች እያደረሱ ስላለው የህውከት አገልግሎትና የረጋውን ወተት የመበጥበጥ ተልእኰ ከጠቃቀስን በኋላ የካሊፎርኒያና የዲሲ አካባቢ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ አባታዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሲያትል ደ/ም  ቅ/ አማኑኤል ቤተክርስቲያን  እንደሚያመሩ ዘግበን እንደነበር ይታወሳል።
አስቀድመን እንደዘገብነው የማቅ ሰርጎ ገብ በጥባጮች፤ በሀገር ቤቱ እንቅስቃሴ እየተዳከሙ ሲመጡ የውጪውን ሀገረ ስብከት የመጠብጠጥ እቅድ ነድፈው፤ የቆየ  ዐመላቸውን እየተገበሩ ይገኛሉ። በቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ጉብኝት ያደርጋሉን የሰማው መምህረ ህውከት ማቅ አንድም ቀን ተኝቶላቸው እንደማያውቀው ሁሉ አስቀድሞ ጆሮውን አቅንቶ የብጥብጥ አጁን በመዘርጋት እንቅፋት መፍጠሩን ቅንጣት ሳያፍር «ደጀ ሰላም» የተባለው የማቅ ማእከላዊ ኰሚቴ ቃል አቀባይ ብሎግ  ዘግቦ አስነብቦናል።  ወደ ህውከትና ዐመጻ እንዲገቡ የሚቀሰቅሳቸውና የስህተት መንገድን አሰማምሮ ስለቅድስና እንደመታገል አድርጎ በኅሊናቸው በመሳል የሚያነሳሳቸው ከሌለ በስተቀር ምእመናን የዋሃን ናቸው። ገንዘባቸውን፤ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ለአገልግሎት የሚያበረክቱትን እነዚህን የዋሃን የእግዚአብሔር ቤተሰቦችን ማቅ እንዴት መጠምዘዝና ለተፈለገው ዓላማ ማዋል እንደሚቻል ብዙ የሥራ ልምድ ስላለው ይህንኑ ጥበበ ዐመፃውን በሲያትል አማኑኤል ቤተክርስቲያን  ተግባራዊ አድርጎ ብጹእ አቡነ ፋኑኤልን የመቃወም ህውከት ለመፍጠር ሞክሯል። እንኳን እምነት፤ ኅሊና ያለው ማንም ሰው የሚፈርደውና ጥያቄ ሊያነሳበት የሚገባው ነገር፤  ብጹእ  አቡነ ፋኑኤል በሀገረ ስብከታቸው ባሉ አድባራት ተዘዋውረው እንዳያስተምሩ የሚከለክላቸው ምንድነው? ቅዳሴ ቀድሰው፤ ቡራኬ ሰጥተው ከመመለስ በስተቀር በደብሩ የውስጥ ሥራ ምን አድርገው ያውቃሉ? እያንዳንዱ ደብር የየራሱ አስተዳደር ያለውና በምእመናን የተቋቋመ እንጂ በብጹእ አቡነ ፋኑኤል  አይፈርስ፤ አይቋቋም!!  ሲኖዶስ የሰጣቸውን ተልእኰ ከመወጣት ውጪ አድባራቱን ምን በድለዋል? ምእመናንስ ቤተክርስቲያናቸው የምትሰጣቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት ከማግኘት ውጪ ከዐመጻና ከብጥብጥ ምን ያተርፋሉ? እነዚህንና እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ብናቀርብ መልሱ ምንም ይሆናል! ከብጥብጥና ከዐመጻ ምእመናን ምንም አያተርፉም። ይልቁንም ከኋላ ሆኖ ድብቅ አጀንዳውን እንደ ወፍ ጉንፋን/bird flu/ የሚረጨውና የሚበክለው ማቅ፤
1/  የአድባራቱ ተቆርቋሪ ሆኖ ራሱን በመሰየም መድረክ ከተቆጣጠረ በኋላ ገንዘብ መዝረፍ፤ አላስቀርብ ካሉት ደግሞ በጥቅም የሚደልላቸውን መሥፍኖች በመፍጠር መገንጠል፤
2/ አባ ፋኑኤልን በሄዱበት ሁሉ እየተከታተለ ማሳደድ የመጨረሻው ዓላማና ግቡ ስለሆነ ይህንኑ አሽክላ ሥራውን እስከእለተ ሞቱ መተግበር፤
3/ የፖለቲካ ሥራው ከሀገር ቤት ብዙም እያወላዳው ባለመሆኑ ወደውጪው ዓለም ፊቱን በማዞር በየቦታው ማመስ፤ መበጥበጥና ጉንፋኑን ማራባት ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። የሲያትሉ ቅ/ አማኑኤል ቤተክርስቲያንም ህውከት የዚያ ተግባሩ አንዱ ማሳያ ነው። 

Tuesday, July 17, 2012

የዳላሱ አቡነ አረጋዊ የማቅ ወኪል ቄስ፤ ከግንድ ላይ ተገንጥሎ በኪራይ ቤት ውስጥ ተተከለ!

የዳላስ ደ/ፀሐይ አቡነ አረጋዊ ወተ/ሃይማኖት ቤተክርስቲያን የፊት ገጽታ

በመሠረቱ ቤተክርስቲያንን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ማቋቋም ቀና ሃሳብ መሆኑ አይካድም። ጥፋት የሚሆነው አንዲቱን ቤተክርስቲያን ለማዳከምና ምእመናን በቡድን ለመከፋፈል ሲባል ከሆነ የመንፈሳዊ ተግባርን እሳቤ በማደብዘዝ ስውር ዓላማን ለመፈጸም መንፈሳዊ ካባን የደረቡ ወረበሎች የሚጠቀሙበት ስልት መሆኑ እየታየ ነው። እናም ቄስ መሥፍን ማሞ የተባለው የዳላስ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል የነበረው ግለሰብእ የተሰጠውን የማቅን ተልእኰ አንግቦ በኅቡእ የቆየ ቢሆንም ሰዓቱ ሲደርስ ከዛሬ ጀምሮ ተገንጥያለሁ ማለቱ ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ ሀገር ውስጥ  ያለ ዋና ሲኖዶስ ፤ በስደት ያለ ዋና ሲኖዶስ እና  አሁን ደግሞ በፓትርያርክ ማኅበረ ቅዱሳን የሚመራ አዲስ ሲኖዶስ በምድረ አሜሪካ እየተገነጠለና ራሱን እያራባ ወደ ሦስትነት እያደገ ይገኛል።
በዳላስ አቡነ አረጋዊ ወተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል የሆነው የማኅበረ ቅዱሳኑ ታማኝ ሎሌ ለመገንጠልና በይፋ አውጆ በ5000 ዶላር ቤት ተከራይቶ የወጣ ሲሆን  መነሻ ምክንያት  የሆነው ነገር ሲቃኝ እንዲህ መሆኑን ምንጮቻን አረጋግጠዋል።
በታህሳስ ወር ገደማ በአዝማሪ መዘምራን ሴቶች የታጀበና በገበሬ አስደንግጥ ስብከቱ ስሙዓ ዜና  በሆነው ዳንኤል ክብረት የተመራው ከፍተኛ የማኅበረ ቅዱሳን የልዑካን ቡድን ጥቂት መርዝ ነስንሶ፤ ብዙ ምርት ማፈስ በሚል መርህ በሄዱበት የ3 ቀናት ዘመቻ ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ወቅት ከዳህጸ ልሳን በዘለለ የተነገረው ዲስኩር ለችግሩ መነሻ ምክንያት ሆኗል። ይኼው ቄስ መሥፍን የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን አባል የደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ እንደመሆኑ መጠን አዝማሪ መዘምራኖቹና ገበሬ አስደንግጥ ሰባኪያኑ ከደብሩ እንዲገኙ ሁኔታዎቹን በማመቻቸት ግንባር ቀደሙ ሰው ነበር።
በስብከቱ መድረክ ራሱን የሰየመው ዳንኤል ክብረት ወንጌልን እንዳያስተምር ያልዋለበት በመሆኑ በወግ ጥረቃና በምሳሌያዊ ተረት ዘመኑን የጨረሰ በመሆኑ የሚናገረው  ቢጠፋበት የተቆጣጠረውን መድረክ በመጠቀም  ሀገር ቤት አፍኖ የቆየውን የፖለቲካ  ትኩሳት አሜሪካ ሲደርስ እስኪበቃው ድረስ ሲተነፍስበት መታየቱ በምእመናኑና በደብሩ ካህናት በኩል ተቀባይነት ሳያስገኝለት  ከመቅረቱም በላይ የስብከት መድረክ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚነገርበት እንጂ የግል ስውር ዓላማንና የፖለቲካን ትኩሳት ማስተላለፊያ መንገድ እንዳልሆነ በደብሩ አስተዳዳሪ ቀሲስ ታደሰ አርአያ በሀዘኔታ መገለጹን ተሰምቷል። 
ዳንኤል ክብረት በወቅቱ ወዴት እንሂድ? ኢትዮጵያ ውስጥ ታፍነን ተሰቃየን እኰ? ዝምታው እስከመቼ ነው? ወዘተ የሚሉ ቅስቀሳዎችን ሲያስተላልፍ የደብሩ አስተዳዳሪም የዳንኤልን  «ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር» ዓይነት ስብከቱን በመቃወም አሁን ይሄ ስብከት ነው? በባእድ ሀገር ለሚገኝ ምእመንና ምእመናት ከአንድ ሰባኪ የሚሰጥ የሕይወት   ቃል ይሄ ነው? ዓላማን ለይቶ ወደ ፖለቲካው መግባት አለበለዚያም ምእመናንን የሚያጽናና ትምህርት መስጠት ሲገባ ይህን ሁሉ ሀገር አቋርጣችሁ ከመጣችሁ በኋላ ህዝብን መቀስቀስ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሀዘኔታቸውን ገልጸዋል።  ቤተክርስቲያን የሚመጣ ደጋፊም፤ ተቃዋሚም እንደመሆኑ መጠን ቤተክርስቲያን ማስተማር የሚገባት ሁሉንም የሚያንጽ እንጂ የአንድ አቅጣጫን ዓላማ ማስተጋቢያ መሆን የለበትም የተባለ ሲሆን የገበሬ አስደንግጡ ስብከት ውድቅ ተደርጓል። ማቅና ገበሬ አስደንግጥ ሰባኪያኑ ዳግመኛ እንዳይመጡ በመነገሩ ይህ ለማቅ ትልቅ ኪሳራ ሆኖ  ነበር።
የማቅ ታማኝ አገልጋያቸው የደብሩ ስብከተ ወንጌል ቄስ መስፍን ገበሬ አስደንግጦችን በማሰባሰብና በማስጮህ ብዙ የለፋበት የማቅ አገልግሎት ዋጋ በማጣቱና ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውስጥ ውስጡን ሲቆስል ቆይቶ ከነፍስ አባቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ከመከረ በኋላ የደብሩን አስተዳዳሪ፤ ካህናትንና ማኅበረ ምእመናንን ቆይ ሳንሰራላችሁ ብንቀር በሚል ብቀላ አዲስ ቤት በአምስት ሺህ ዶላር ገደማ ተከራይተው እዚያው በቅርብ ርቀት የተተከለ ሲሆን ይህም በፓትርያርክ ማኅበረ ቅዱሳን የሚመራው ሦስተኛው ሲኖዶስ መሆኑ ነው።
ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ ሀገረ ስብከቱ በአቡነ ፋኑኤል የሚመራ መሆኑ እየታወቀ የሀገር ቤቱን ሲኖዶስ ከድተው ማኅበረ ቅዱሳን ቤት ተከራይቶ ሲያትል በሚያኖራቸው የሶስተኛው ሲኖዶስ ቋሚ አባል በሆኑት በአቡነ ኤዎስጣቴዎስ በኩል የቄስ መሥፍን ቤት ተመርቆ መከፈቱ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል። በእርግጥ ሦስተኛውን ሲኖዶስ በምድረ አሜሪካ ቤቶችን በመክፈት ላይ የተጠመደው ማቅ ምንም ሀገረ ስብከት የሌላቸውን አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ቤት ተከራይቶ ማስቀመጡ ምናልባት የአሜሪካ ፓትርያርክ አደርግዎታለሁ የሚል ተስፋ ሰጥቷቸው ይሆናል። በዚያ ላይም ለማቅ  አልገዛም፤ አልታዘዝም ያሉትን አቡነ ፋኑኤልን ለማናደድ ጭምር የተጠቀመበት የግንጠላ ስልት ሲሆን  ካከራየበት ቤት ጎትቶ በማምጣት ጳጳሱ ታዛዥነታቸውን ማሳየታቸው  ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል። አቡነ ኤዎስጣቴዎስም የጵጵስና ማእረግ ወንድማቸውን ለማቅ ደስታ ሲሉ መጥላታቸውና ሕገ ቤተክርስቲያንን ማፍረሳቸውን ስንመለከት እንዲህ ብለንለመጠየቅ እንገደዳለን።  እሳቸው ከጣሱት የትኛውን ህገ ቤተክርስቲያን  ተግባራዊ ለማድረግ ነው የጰጰሱት እንላቸዋለን?
አንዳንድ የማቅ ደጋፊዎች አቡነ ፋኑኤልም  በአቡነ አብርሃም ላይ እንደዚሁ ሰርተዋል በማለት ሊሞግቱ ይፈልጉ ይሆናል።
ያለፈ ጥፋት  ካለ፣ ላሁኑ ጥፋት እንደትክክለኛ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም።
 ጎረምሳው ቡድን የራሱ ዓላማ ያለው ሲሆን ጳጳሱ ደግሞ  የራሳቸውን የሲኖዶስ ዓላማ ጥለው ለማቅ ዓላማ ስኬት መዞራቸው ያሳዝናል። ዘወትር የአቡነ ፋኑኤልን ስም በየድረ ገጾቹ  እያነሳ የሚያጨልማቸው አልበቃ ብሎት፤ አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ወስዶ በአቡነ ፋኑኤል ሀገረ ስብከት ላይ ቤት እንዲመርቁ ያደረገው እርር ድብን ላድርጋቸው ብሎ እንጂ  ሕገ ቤተክርስቲያን ያንን እንዲያደርግ የሚፈቅድ ሆኖ አልበረም። ነገሩ ባልበላውም ልድፋው ነው!