Tuesday, August 9, 2016

ተገቢ ትኩረት የሚያሻው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ካህናት አቤቱታ!



በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ያሉ አጠቃላይ ማኅበረ ካህናቱ በአቤቱታ ድምጻቸው  ወቅታዊ፤ ትክክለኛና አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው አቤቱታ አቅርበዋል የሚል እምነት አለን። ይህንን አቤቱታ ዝም ብሎ ማለፍ በቤተክርስቲያኒቱ አጠቃላይ ውድቀት ላይ ከኤጲስቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ስህተቶች ጋር ተባባሪ መሆን ብለን እናምናለን።
ዘረኝነት፤ ጉቦና የኃጢአት ገመና እንዲህ እንደዘንድሮው ታይቶም፤ ተሰምቶም አይታወቅም። ማኅበረ ቅዱሳን በትክክል ቤተ ክርስቲያኒቱን መቆጣጠሩን ያስመሰከረበት ጊዜ ቢኖር በዚህ የኮሚቴ ምርጫ የታየው የኩነኔና የፍርድ መዝገብ በአደባባይ መነገሩ ነው። ዘረኝነት ቦታውን ተረክቧል። ሙስናው በግልጽ ይታያል። ድሮም ቢሆን በእነጉድ ሙዳይ የሚመራ ኮሚቴ ከዚህ ዓይነቱ ቆሻሻ ተግባር የራቀ ሊሆን እንደማይችል የነበረን ግምት ትክክለኛ ነበር።
የኛም ግምት ስህተት እንዳልነበር የሚያሳየው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ካህናት ድርጊቱን በመመልከት ቀጥተኛ አቤቱታ ማቅረባቸው ሲሆን ለካህናት ጩኸት ጆሮ ሊሰጠው ይገባል እንላለን። ፓትርያርክ ማትያስም ለራሳቸው ክብርና ስም፤ ታላቂቱ ቤተክርስቲያኒም ከተደቀነባት ውርደት ማዳን ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው። የካህናቱን አቤቱታ እዚህ ያንበቡ!








Sunday, August 7, 2016

ሕይወት የሆነን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ብቻ ነው!


ቅዱሳንን ማክበር እንደሚገባ ምንም ጥያቄ የለንም። መታሰቢያን በተመለከተም የድርጊቶቻችን አፈፃፀም የሁሉ ነገር ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ስምና ክብር እስካልጋረደና  እስካልተካ ድረስ የሚደገፍ ነው። ነገር ግን  «ጥቂት አሻሮ ይዞ፤ ዱቄት ወዳለው መጠጋት» የሚለውን ብሂል ለመተግበር መሞከር ግን አደገኛ ነገር ነው። በተለይም በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወቅት ወንጌል እንደዚህ ስለሚል፤ እኔም እንደዚህ ብል ችግር የለውም የሚለውን ራስን መሸሸጊያ ምክንያት በማቅረብ ለመከለል መሞከር ፀረ ወንጌል ነው። በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ሥር ኑፋቄና ክህደትን ማስተማር በአምላክ ፊት ያስጠይቃል። እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ ስለሚችል የኛን ተረት ሁሉ ይሰራልናል ማለት አይደለም። ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱትና እነዚህ የመሳሰሉ የስህተት ችካሎች አልነቀል ያሉት በምክንያት ስር በመደበቃቸው ነው።
ቅዱሳንን በማክበርና በመውደድ ሽፋን ወደአምልኮና ተገቢ ያልሆነ ሥፍራ ወደማስቀመጥ ያደገው መንፈሳዊ በሚመስል ማሳሳት ተሸፍኖ ነው።
ለክርስቲያኖች ድኅነት ዋናው ቁልፍ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው። ከዚህ ውጪ ያለው የማንም ሰው ሞትና ትንሣኤ ለመዳናችን ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። አይጨምርልንም፣ አይቀንስልንም። ማዳን የእግዚአብሔር ነውና
ኢሳይያስ 43፣11
"እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም"
ይህ የተሠጠን የቃሉ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ የጌታ እናት የድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ ለክርስቲያኖች ዘላለማዊ ድኅነት መስጠት ይችላል? ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ አይችልም ነው። ታዲያ በድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ ላይ ጥንታዊያን የሚባሉ አብያተ ክርስቲያናት የተለየ ሃይማኖታዊ ትኩረት የሚሰጠው ለምንድነው? ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ትርጉምና ትረካ የሚገልፁበትስ ምክንያት ለምን ይሆን?

እንኳን እኛ ጠያቂዎቹ ራሳቸው በትክክል ምክንያቱን የሚያውቁ አይመስለንም። የሆኖ ሆኖ ትርክታቸውን ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ስለማርያም እረፍት፤ ትንሣኤና እርገት አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዓይነት የእምነት አቋም የላቸውም። ካቶሊኮች በጥር ሞቶ በነሐሴ መቀበር የሚለውን ታሪክ አይቀበሉም። በየዓመቱ ነሐሴ 8 ያከብራሉ። በሌላ መልኩ ንዲያውም ስለማርያም ሞትና የእርገት ዕለት በግልጽ የሚታወቅ ማስረጃ እንደሌለ በ5ኛው ክ/ዘመን  የኖረው የሳላሚሱ ኤጴፋንዮስ   ተናግሯል።  ዕረፍቷና እርገቷ በኢየሩሳሌም እንደሆነ  የሚናገሩ ቢኖሩም  ይህንን አባባል የማይቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትና የቴኦሎጂ ምሁራን ሞልተዋል። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚለውን አባባል የማይቀበሉበትን ማስረጃ ሲያቀርቡም ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ እንደተናገረው «እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት»  ዮሐ19፤27 ባለው መሠረት ማርያም እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ከዮሐንስ ጋር ስለኖረችና ወንጌላዊው ዮሐንስም ከጌታ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም  ጥቂት ዓመታትን ከቆየ በኋላ በ37 ዓ/ም ገደማ ወደ ቤዛንታይን ከተማ ኤፌሶን ሄዶ ወገኖቹን ወንጌል እያስተማረ መቆየቱንና  ማርያም በሞት እስከተለየችው ድረስ  ከ48-52 ዓ/ም እዚያው እንደነበር ብዙ ተጽፏል። ሌሎቹ ደግሞ ኤፌሶን መኖሯን ይቀበሉና ያረፈችው በኢየሩሳሌም ነው ይላሉ።
 ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን ነበረች ባዮች በቅርብ ርቀት ባለችው ደሴተ ፍጥሞም  በግዞት መኖሩ መኖሩና ከዶሚኒሽን አገዛዝ ቀደም ብሎ የራእይ መጽሐፉን  ከ55-65 ዓም ገደማ ስለፃፈ የማርያምም ቆይታ እስከዚያው ድረስ በኤፌሶን ነበር ይላሉ።
እንደዚህ ከሆነ  ማርያም በኤፌሶን ከዮሐንስ ጋር ኖራለች  ወይስ አልኖረችም ነው ጥያቄው።  በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚሉ ሰዎች አንድም ጊዜ ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን ኖራለች ሲሉ አይደመጥም። ለምን?  ዮሐንስ ማርያምን እንደእናት ሊይዛት አደራ ተሰጥቶታል የሚባል ከሆነ ከዮሐንስ ጋር ኤፌሶን ስለመቀመጧ የማይነገረው ለምንድነው?  ዮሐንስ እስከ 96 ዓመቱ ድረስ ከኤፌሶንና ከደሴተ ፍጥሞ ውጪ ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም። ማርያም ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን አልኖረችም ብሎ በመከራከርና ከኤፌሶን መጥታ ኢየሩሳሌም  ማረፏን በግልጽ በመናገር  መካከል ልዩነት አለ።  «እነኋት እናትህ» ባለው መሰረት አብረው ኤፌሶን ኖረው እዚያው ማረፏን የማይቀበሉና  የለም፣ ኢየሩሳሌም  አርፋለች የሚሉ ሰዎች የታሪክም፣ የጊዜም ልዩነት አላቸው።

 ወይ ደግሞ ኤፌሶን ላይ እድሜውን ሙሉ የኖረው ዮሐንስ ከማርያም ጋር ተለያይተው ነበር ሊሉ ይገባል።
ሮበርት ክሬው የተባለ የነገረ መለኮትና የታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዘመኑን ሁሉ በኖረበት ከኤፌሶን ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ ባለች ኰረብታ ላይ በተሰራ ቤት ውስጥ እንደኖረና ማርያምም እዚያ ማረፏን ጽፏል።  ይህንን በኤፌሶን ያለውን የማርያምን መቃብር የዓለም ክርስቲያኖች እንዲሆም ሙስሊሞች ሳይቀሩ ይጎበኙታል፤ ይሳለሙታል።  በቱርክ ግዛት ያለው ይህ ስፍራ በቱርካውያን ሙስሊሞች ዘንድ «ሜሪዬ ማና» ተብሎ ይጠራል።

ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም የተለየችው መቼ ነው? በሚለውም ጥያቄ ላይ ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የምሥራቁና የምዕራቡ ጎራዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው።
 በተወለደች በ58 ዓመቷ ዐርፋለች የሚሉ አሉ። በ72 እና 63 እድሜዋም አርፋለች የሚሉ መረጃዎች አሉ። እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ግን የሚታመነው በ64 ዓመት እድሜዋ ማረፏ ነው።  ኖረችበት ተብሎ ከሚገመተውና አርፋለች ከሚባለው ቦታ ያለው ልዩነት እንዳለሆኖ በጥር ወር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታ በ40ኛው ቀን ማረጓን የሚናገሩ አሉ። በነሐሴ ወር አርፋ ከተቀበረች በኋላ ትንሣኤዋን ሳያዩ መቃብሯ ባዶ ሆኖ ስላገኙት ሐዋርያት ሱባዔ ይዘው በሦስተኛው ቀን ተገለጸችላቸው የሚሉም አሉ። እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ በጥር ሞታ፤ በነሐሴ ተቀበረች የሚል ትምህርት አለ። በጥር ወር አርፋ፤ በነሐሴ ተቀብራለች የሚሉ ሰዎች ሥጋዋ በገነት ዛፍ ስር ለስምንት ወራት መቀመጡንና በሱባዔ ጸሎት በተደረገው ልመና የተነሳ ለመቀበር መቻሏን አስፋፍተው ይነግሩናል። ከጥር እስከ ነሐሴ ድረስ ለ8 ወራት ማርያም አልተቀበረችም።

 በጥር ወር እንዳረፈች፤ ለመቀበር ያልተቻለውም ታውፋንያ የሚባል ሽፍታ፤ ጎራዴ ሲመዝባቸው ወደ ቀብር ሥጋዋን ተሸክመው ይሄዱ የነበሩት ሐዋርያት በመፍራት ጥለዋት በመሸሻቸውና ዮሐንስ ብቻውን ቀርቶ ወደ  መቃብር ሳትገባ ወደ ገነት ዛፍ ስር በመወሰዷ ይባላል።  ነገር ግን የገነት ዛፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነና በገነት ዛፍ ስር የሰው ሬሳ እንዴት ሊቀመጥ እንደሚችል አንድም ጽሑፍ በአስረጂነት ሲቀርብ አላየንም።

 ይህ በጥያቄነቱ ይቆየንና ታሪኩን እንቀጥል። ዮሐንስም ወደቤቱ ማምራቱንና ሸሽተው የነበሩትም ሐዋርያት ሥጋዋስ የታለ? ብለው ቢጠይቁት በገነት ዛፍ ስር መቀመጧን  ስለነገራቸው ዮሐንስ ገነት ዛፍ ሥር ሬሳዋ መቀመጡን አይቶ  እኛስ ለምን ይቀርብናል በማለት ነሐሴ 1 ቀን 49 ዓ/ም የጾም፣ የጸሎት ሱባዔ አውጀው በ15ኛው ቀን ትኩስ ሬሳ ከገነት ዛፍ ስር እንደመጣላቸውና በጌቴሴማኒ እንደቀበሯት ይናገራሉ።  ዮሐንስ በገነት ዛፍ ሥር ስትቀመጥ አያት የሚለውን ተረት እውነት አድርገን ብንቀበለው እንኳን ዮሐንስ ሀገረ ስብከቱ የሆነውንና እስከ መጨረሻው ጊዜውም የኖረበትን ኤፌሶንን ትቶ ወደኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር ወይ? እንድንል ያደርጋል።

ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳው ነገር  በጥር ወር አርፋ  ለቀብር ሲሄዱ ሽፍታ በፈጠረው ሁከት ሐዋርያቱ ስለሸሹ ወደገነት ዛፍ ስር ስለመወሰዷ ዮሐንስ ለሐዋርያቱ ከነገራቸው በኋላ ለስምንት ወራት የመቆየታቸው ምክንያትና ዮሐንስ ያየውን ማየት አለብን ያሉበት የጊዜና የሃሳብ አለመገጣጠም ጉዳይ አስገራሚ ይሆንብናል።
ዮሐንስ እንደነገራቸው ማየት አልፈለጉም ነበር? ከስምንት ወራት ቆይታ በኋላስ ማየት የፈለጉት ምንድነው?
ይህ ሁሉ ሲሆን የማርያም ሥጋ በተባለው የገነት ዛፍ ሥር ተቀምጧል። ሐዋርያቱ ሱባዔ ባይገቡ ኖሮ ሥጋዋ ምን ሊሆን ነበር? አይታወቅም። ዘግይቶም ቢሆን የሐዋርያቱ ሱባዔ ችግሩን ለማቃለል ችሏል።

የሚያስገርመውና የሚያስደንቀው ትርክት በጥር ወር አርፋ ሳይቀበር የቀረውን የማርያምን ሥጋ በስምንተኛው ወር ከገነት ወጥቶ ከተሰጣቸውና ከቀበሯትም በኋላ ማርያም ከመቃብር ተነስታ ስታርግ ሐዋርያቱ ለማየት አለመታደላቸው ነው።  ሐዋርያቱ ቀብረዋት ወደ ቤታቸው  ከገቡ በኋላ ከሐዋርያቱ አንዱ የነበረውና በቀብሯ ላይ ያልተገኘው ቶማስ የተባለው ሐዋርያው በደመና ተጭኖ ከህንድ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ማርያምን ሐዋርያት በቀበሯት በሦስተኛው ቀን ወደ ሰማይ ስታርግ የዳመናው ጎዳና ላይ ያገኛታል።  መላእክት አጅበዋት ሲሄዱ ያገኛት ቶማስ ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፣  አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ልቀር ነው? ብሎ ራሱን ከዳመናው ሠረገላ ላይ ወደመሬት ሊወረውር ሲል ቶማስ አትዘን፣ ትንሣኤዬን ያላንተ ማንም አላየም ካለችው በኋላ ለማየቱ ማስተማመኛ እንዲሆነው የተገነዘችበትን ጨርቅ እራፊ ሰበን ለምልክት ሰጥታው እንዳረገች ሰፊ ታሪክ ይነገራል።

ሰዎቹ ነገሩን ሁሉ ለማጣፈጥ የሚጠቀሙበት ነገር አስገራሚ ነው። የሰው ልጅ ከትንሣኤው በኋላ የዚህን ዓለም ጨርቅና ልብስ እንደተሸከመ ወደ ሰማይ ይገባል? ብለን እንድንጠይቃቸው ይጋብዙናል። እንደዚህ የሚናገር ክርስቲያናዊ አስተምህሮስ አለ ወይ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል። ወንጌል ከትንሣኤ በኋላ ክርስቶስን ይመስል ዘንድ  ይለወጣል ይላል እንጂ የመቃብሩን ልብስና ሰበን እየተሸከመ ያርጋል የሚል ትምህርትን አይነግረንም።
« 2ኛ ቆሮ 3፤18
እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን»

ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በመቃብሩ የተገነዘበትን ጨርቅ ትቶ መነሳቱን እንጂ  ያንኑ ለብሶ መነሳቱን አላነበብንም።
ዮሐ 20፤6-8. «ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ»
የሁላችን አማኞች ትንሣኤ የክርስቶስን ትንሣኤ መምሰል ካለበት በቀብር ወቅት ከዚህ ዓለም ጉድጓድ የገባ ጨርቅ ወደ ሰማይ አብሮን የሚያርግበት ምንም መንገድ የለውም። ስለዚህ ከምድራዊ ማንነት ወደተለየ ሰማያዊ ማንነት እንሻገራለን እንጂ እንደሀገር ጎብኚ ጓዝ ይዘን የምንሄድበት ታሪክ ፀረ ወንጌልና ፈጠራ ላይ የተመረኮዘ ተረት ከመሆንአአያልፍም።
ስለዚህ ተጠራጣሪ እንደሆነ ሁል ጊዜ የሚነገርበት ቶማስን በማርያም ትንሣኤ ላይ ግን የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ  ሲባል ማርያም ወደ ሰማይ ስታርግ የመቃብሯን ከፈን ተሸክማ የሄደች በማስመሰልና ለምልክት ይሆን ዘንድ ከፍላ  ሰጠችው የሚለው አባባል በአንዳችም ነገር  ከወንጌል እውነት የተጠጋ አይደለም።
ሌላው ነገር በመንፈስ ቅዱስ በመነጠቅ፤  በሌላ ስፍራ ወዲያውኑ መገኘት ስለመቻል ለሐዋርያው ፊልጶስ  ከተነገረው የወንጌል ቃል  በተለየ በዳመና ላይ ተቀምጦ ስለመሄድ ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ባይኖርም የቶማስን ጉዞ ከህንድ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ እንደፊልጶስ መነጠቅ አድርገን ብንቆጥረው እንኳን የቶማስ ሰብአዊነትና የማርያም የትንሣኤ እርገት የተለያየና ፈጽሞ የማይገናኝን ነገር ለማቀራረብ መሞከር ነው።  የቶማስን የዳመና ላይ ውይይትን ከረቂቅ  ክርስቶሳዊ አዲስ ፍጥረት ጋር ለማገናኘት መሞከር የጥንቶቹን የግሪክ ወጎች/fable story/ እንድናስታውስ ያደርገናል። በግሪኮች የተረት ታሪክ "ጁፒተርና ሳተርን ተጋብተው ቬነስን ወለዱ" የሚል ታሪክ አለ። ይህ ታሪክ የገሀዱ ዓለም ተቃራኒ መሆኑን ማንም አይስትም። ቶማስና የማርያም ነፍስ የዳመናው ሜዳ ላይ ሰፊ ውይት አደረጉ. የተሸከሟት መላእክትም ጉድ፣ ድንቅ እያሉ ውይይቱን ይከታተሉ ነበር ዓይነት አባባል ከግሪኮች ጥንታዊ የተረት የተቀዳ ይመስላል።
በሞትና በትንሣኤ እንዲሁም በእርገት መካከል እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን እግዚአብሔር በሰውኛ ትረካ ይጫወታል ማለት እግዚአብሔር ስለሞትና ትንሣኤ በተናገረው መቀለድ ይሆናል።
ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ማርያምን በጥር ሞታለች ያሉ ሰዎች፤  በመጀመሪያው ሞት ዮሐንስ ብቻ እድለኛ ሆኖ በገነት ዛፍ ስር ለማየት መቻሉ አንዱ ክስተት ሲሆነረ በኋለኛውም ቀብር ቶማስ ብቻ ተጠቃሚ የሆነበትን የእርገት እድል፤  ሌሎቹ ሐዋርያት ለማግኘት ባለመቻላቸው ሐዋርያቱ ሁለተኛ እድል ያመለጣቸው መሆኑ ነው።   ተረቱን የሚያቀናብሩት ሰዎች ለዚህም መላ አስቀምጠዋል።
ሐዋርያቱ ቶማስ በዳመና ላይ ያገኘው እድል ለምን ያምልጠን ብለው በቀጣይ ዓመት ነሐሴ1 ቀን 50 ዓ/ም ጀምረው ሱባዔ ለመያዝ መገደዳቸውንና በ16ኛው ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ማርያምን ከገነት አምጥቶ አሳያቸው።
ሁለተኛ  ትንሣኤና እርገትን ለማየት የመቻላቸው ነገር  አስደናቂ ትርክት ነው።
ቀብር ሳይኖር ትንሣኤዋንና  እርገቷን እንዴት ማየት እንደቻሉ ግልጽ አይደለም። በምሳሌ ይሁን በምትሃት እርግጠኝነቱን ያብራራ ማንም የለም።  ሁለት ጊዜ ትንሣኤና እርገትስ ማለት ምን ማለት ነው?
ዛሬም ድረስ ትንሣኤና እርገቷን የተመለከተውን ሱባዔ በማሰብ በየዓመቱ የሱባዔ ጺም ይደረጋል። የዘንድሮውም ነሐሴ 1/2008 ዓ/ም ተጀምሯል። የድሮውን ለማሰብ ነው ወይስ እንደገና ለማየት?

ሌላው  ደግሞ  ማርያምን መንበር፤ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፤ እስጢፋኖስን ገባሬ ዲያቆን አድርጎ በመቀደስ አቁርቧቸዋል የሚለው  ትረካ እርገቷን ተከትሎ የመጣው አባባል ነው። የማርያም ነፍስ እንዴት መንበር መሆን እንደሚችል? ምን የሚባለው ቅዳሴ እንደተቀደሰ? ለማወቅ አልተቻለም።   ሰራዔ ካህኑ ክርስቶስ የማንን ሥጋ  እንደቆረበ? እንዲነግሩን ግን እንጠይቃቸዋለን። ለየትኛው ድኅነት/መዳን/ እሱ ይቆርባል?  ክርስቶስ ቀደሰ እንጂ አልቆረበም ማለት አንድ ነገር ነው።  ቆርቧል የሚባል ከሆነም ምክንያትና ውጤቱን የሚተነትን ትምህርት አያይዞ ማቅረብ የግድ ይላል። እሱማ የሕይወት ምግብ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለም የሚባል ከሆነም  ሰራዔ ካህናት በዚህ ምድር መቅደስ ውስጥ ከመቀደስ ባሻገር መቁረብ አይጠበቅባቸውም በማለት አብነታዊ የክህነት አስተምህሮን አያይዞ ማቅረብ  የተገባ ይሆናል። ቀድሶ አለመቁረብን ከክርስቶስ አብነት መውሰድ ይቻላል እያሉ ነው።
እንግዲህ ማርያምን እንዴት መንበር አደረጋት፤ ክርስቶስ ሰራዔ ካህን ሆኖ  ያልታወቀ ቅዳሴ ቀደሰ ማለትስ ምንድነው?
  ስለማርያም  ትንሣኤና እርገት ማጠናከሪያ በማቅረብ ትዕይንቱን  ተአማኒ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር አንድም እውነትነት የለውም። እንደተለመደው አባባል ቅዳሴ እግዚእ ነው የተቀደሰው የሚል  ካለም ክርስቶስ ራሱን በሁለተኛ መደብ አስቀምጦ « ነአኩተከ አምላክ ቅዱስ፤ ፈጻሜ ነፍስነ፤ ወሀቤ ሕይወትነ ዘኢይማስን»  ሲል አይገኝም።  ራሱ ሕይወት ሰጪ ሆኖ ሳለ ሕይወት ይሰጠው ዘንድ አይለምንምና ነው። እንደዚህ ዓይነቱ አደገኛ ክህደት፤ ሰዎች ለማርያም ባላቸው ፍቅር ውስጥ ተደብቆ ለዘመናት ቆይቷል።

በጉ መስዋእቱን ለሕይወታችን ሰጥቷል። ከዚያ ውጪ እሱ  በመንግሥቱ የፍርድ ሰዓት ዳግመኛ ሊመጣ ካልሆነ በስተቀር ከማእዱ አይካፈልም።«ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት» ሉቃ 22፤14-17

ወደዋናው ሃሳባችን ስንመለስ ለመሆኑ በማርያም ላይ ስንት ቀብር፤ ስንት ትንሣኤና ስንት እርገት ተደረገ? ብለን ብንጠይቅ እንደሚነገረው  ከሆነ ፤
1/ዮሐንስ ያየውና አፈር ያልነካው እርገት በገነት ዛፍ ስር
2/ አፈር የነካው የሐዋርያቱ ቀብር በነሐሴ 14 ቀን /ከስምንት ወር በኋላ/
3/ ቶማስ ያየው የትንሳኤ እርገት፤ ከቀብር በኋላ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16
4/ ከአንድ ዓመት በኋላ ሐዋርያት ያዩት የነሐሴ 16 ትንሣኤና እርገት ናቸው።
እንግዲህ በማርያም ሞትና እርገት መካከል አራት ትእይንት መከሰቱን ዛሬም ድረስ ከሚሰጡት የቃል አስተምህሮዎችና የተዘጋጁ ጽሁፎች ውስጥ በግልጽ እናገኛለን። ማርያምን መውደድ አንድ ነገር ነው። ማርያምን ግን እየቀበሩና እያነሱ ለማረጋገጥ መሞከር ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ክስተት ይሆናል። እንዲያውም  ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻልኩ ሰባት ጊዜም ቢሆን እሞታለሁ ብላ ለልጇ ተናግራለች የሚልም  ተረት ተያይዞ ይነገራል።  የእሷ መሞት የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻለ የክርስቶስ ከእሷ መወለድ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሃሳብን የሚያንጸባርቀው ይህ አባባል ከአሳሳች ትረካዎች ውስጥ የሚደመር ከመሆን አያልፍም።
እኛ  ማርያምን ብንወዳትና ብጽእት ብንላት «እናትህንና አባትህን አክብር»  ያለውን  የአምላክ ቃል መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለእርሷ  የተነገረ ቃል ስላለም ጭምር ነው። ነገር ግን የዘላለማዊ አምላክ የክርስቶስ ፤ እናቱ ስለሆነች  በማዳላት ወይም አምላካዊ ባህርይውን በሰውኛ ጠባይ በመለወጥ ከፍርድ ሚዛኑ በማጉደል  የእሷን ሞትና ትንሣኤ የተለየ ያደርጋል ብሎ ማሰብ የዋሕነት ይሆናል። የእሷ ሞትም የመድኃኒትነትን ውክልና ለሰው ልጆች የያዘ እንደሆነ ማሰብ ክህደት ነው። ብቸኛው መድኃኒት አንዱ በግ ኢየሱስ ብቻ ነው። ማርያምም ይህንን ስለምታውቅ « ነፍሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ተስፋ ታደርጋለች» ብላ ነግራናለች።የትንሣኤ በኩር የሆነው ሁላችንም በሞቱ እንድንመስለው እንጂ የተለየ አድሎአዊ ጥቅምን/ faver/ ለተለዩ ሰዎች በመስጠት አይደለም።ወንጌል የሚናገረው ይህንን ነውና።
ሮሜ 6፥5
«ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን»
 ስለዚህ ደጋግሞ መሞት፤ መነሳትና ደጋግሞ ማረግ አለ ከተባለ ያ ነገር ከክርስቶስ ትንሣዔ ጋር ያልተባበረ ስለሆነ አንቀበለውም። እንዲያውን ይህ ኑፋቄና ወንጌልን መካድ ነው።  ሐዋርያው ጳውሎስም የተናገረው ስለክርስቶስ ወንጌል በሞቱም ክርስቶስን እንዲመስል ነበር።
ፊልጵ 3፥10-11  «እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ»
ማርያምን እንወዳለን እያሉ በጥር ሞተች፤ ገነት ዛፍ ስር ስምንት ወር በሬሳ ቆየች፤ በስንት ሱባዔ ስጋዋ መጥቶ ነሐሴ ተቀበረች፤ እስከነ ምድራዊ ልብሷ አረገች፤ በዳመናው ጎዳና  ላይ ከቶማስ ጋር ጨርቅ ተለዋወጠች፤ እድል ላመለጣቸው ሐዋርያት ዳግመኛ በስንት ሱባዔ በሌላ ትንሳኤና እርገት ተረጋገጠች፤ መንበር ሆና ተነጠፈች ወዘተ  በማለት እየገደሉና እያነሱ በማርያም ላይ መጫወት ተገቢ ነው ብለን አናምንም። የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤንም ማፋለስና መካድ ይሆናል።

የማርያም ሞትና ትንሣኤ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካዘጋጀው የትንሣኤው በኩር አንድያ ልጁ የተለየ አያደርገውም።  ሞትም አንድ ነው ትንሣኤ ዘሙታንም አንድ ነው።  በትንሣኤ ዘሙታንና በእርገት መካከል ልዩነት አለ። ባልሆነ ጭንቁር ሃሳብ ተረቱን እያጋነንን ሕይወት የሆነንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መጋረድ ተገቢ አይደለም።

Monday, July 25, 2016

የሚፈውስና የሚያሳምም ስም - ኢየሱስ!!


(ከዙፋን ዮሐንስ)
የሆነ ጊዜ ፷፬ ሰው በሚይዝ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ተሣፍረን ወደክልል የሁለት ቀን መንገድ ተጓዝን። ቁርስ፣ ምሳ፣ አብሮ ከመብላት፣ አብሮ ከመቀመጥ፣ የተነሳ ሁሉ ዘመድ ቤተሰብ ሆነ። የሆድ የሆዱን ተጫወተ። ስልክ ተቀያየረ፣ እጮኛም ያገኘ አይጠፋም። ያልተነሳ ርእስ አልነበረም። ፖለቲካ፣ የኑሮ ውድነት፣ ስለሳይንስ፣ ሃይማኖት፣ ስለታዋቂ ደራሲያን፣ ዘፋኝ፣ ፈላስፋ፣ ስለሃይማኖት አባት፣ ብዙ ብዙ….ብቻ ያልተወራ አልነበረም። አንዳንዶቹም ወሲብ ቀስቃሽ ቀልዶችን ግጥሞችን አውርተው መኪናው ውስጥ ከጫፍ እስከጫፍ አነቃቅተዋል። የወሲብ ነገር ሲወራ ጆሮውን ቀስሮ ያዳምጣል። የሚያስቅ ከሆነ ይስቃል፣ የሚያሳፍር ከሆነም መስማት ያልፈለገ ይመስል የኮረኮሩት ያህል ግንባሩ ጥርስ በጥርስ ይሆናል። የአለቃ ገ/ሐና ነገር ሲነሳማ የአለቃን ወሲብ ወዳጅነትና ይጠቀሙ የነበረበትን የማማለል ዘዴ እያደነቀ ከልምዳቸው ብዙ የቀሰመው ነገር ያለ ይመስል ተሳፋሪው ይስቃል፣ ያውካካል።

ይህ ሁሉ ሲሆን አንድ ሰው ከዚህ ሁሉ ሳቅና ፍንደቃ ራሱን አግልሎ ከመስኮት ጥግ ተቀምጦ ያነብ ነበር። ድንገት ብድግ ብሎ “ኢየሱስ“ የሚለውን ስም አንስቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ አዳኝነቱን፣ ተስፋነቱን፣ አጽናኝነቱን መናገር ሲጀምር ብዙ ፊቶች ተቀያየሩ። አንዳንድ ፊቶች ቲማቲም መስለው ቀሉ። የባሰባቸው አንዳንዶች ደግሞ እንደበርበሬ ቀልተው የቁጣ ብናኛቸው በሰውየው ላይ በተኑ። ስለዝሙት ቀልድ ቦታ ሳይመርጡ ሲያውካኩ የነበረውን ረስተው ስለኢየሱስ ለመስማት ቦታ አጡና “ሰብከት ቦታ አለው“ አሉና ደነፉ። ጫወታችንን አታበላሽ አሉና አጉረመረሙ። ስለፌዝ፣ እርባና ስለሌለው ቀልድና ስለዝሙት ማውራት እንደጥሩ ጫወታ ተቆጥሮ ስለኢየሱስ መስማት ግን ጫወታን እንደማበላሸት ሆኖ ተቆጠረ።
እርግጥ ነው። የሥጋን ነገር መከተል ከእግዚአብሔር የመለየት ጉዳይ ስለሆነ ማበሳጨቱ የሚጠበቅ ነበር።

ሮሜ 8፣7
 “ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል” እንዳለው ሐዋርያው።

በየትኛውም መመዘኛ “ኢየሱስ” የሚለው ሃይለኛ ስም ሲጠራ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል የሰዎች አስተሳሰብ ከሁለት ነገር ውጭ አይሆንም።
አንድም የኢየሱስን ጌትነትና አዳኝነት የሕይወቷ ቤዛ ላደረገችው ነፍስ ሃሴትን ያመጣልና በስሙ መጠራት ይኽች ነፍስ አታፍርም፣ አትቆጣም።
 ሁለትም የኢየሱስ አዳኝነት፣ ጌትነትና አምላክነት ብቸኛ ቤዛዋ ያላደረገችውን ነፍስ ያበሰጫታል፣ ያናድዳታል።

ምክንያቱም ፪ቆሮ ፪፣፲፮ “ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፣ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን“ እንደሚል ይኽ ስም ለዘላለማዊ ሕይወት ለተመረጡት የፕሮቴስታንት ይሁኑ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ አማኞች ሕይወት፣ ሕይወት የሚሸት ሰላምና እረፍት የሚያመጣ ሲሆን ለጥፋት ለተመረጡት ግን የሚያስቆጣ፣ የሚያነጫንጭ ጥርስ የሚያፋጭ ይሆናል። ዘፈንና ቀልዱ፣ ቧልትና ፌዙ ሲነገር ሁሉ ያለምንም ልዩነት አንድ ሆነው ሲስቁና ሲፈነድቁ እንዳልነበር “ኢየሱስ” የሚለው ስም ሲጠራ የሚያበሳጭበት ምክንያት ለምንድነው? እነዚህ ጴንጤዎች ቦታ የላቸውም እንዴ ማሰኘቱስ ለምን ይሆን? የራሱ የሆነውን ኢየሱስ ያዘጋጀ ሃይማኖት የለም።

ቢያንስ አዳምጦ ከወንጌል ቃል ውጪ የሆነውንና ያልሆነውን መለየት ሲቻል መቃወም ተገቢ አይደለም። ደደግሞም ፌዝና ሥጋዊ ነገርን ከማውራት ስለኢየሱስ መስማት በብዙ መልኩ ይሻላል። ለሁሉ ስለሞተው ስለኢየሱስ መናገር የተወሰኑ ሰዎች ስጦታ ሆኖ ሲያስወቅስ፣ ስለዝሙት መናገር ግን ለሁሉ የተፈቀደ መልካም ተግባር ሆኖ የሚቆጠርበት ምክንያት መኖር አልነበረበትም። ነገር ግን ይኽ ስም ሲጠራ ያስፈራቸውና ሐዋርያቱን፣ “ጀመሩ ደግሞ እነዚህ የተረገሙ!” ያስብል እንደነበር ወንጌል ያስታውሰናል።

1. ስሙን ሲጠራ ለተቀበሉ የሕይወት ሽታ የሆነላቸው። ሐዋ ፰
 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፊልጶስ ስለኢየሱስ ሲሰብክለት ልቡ ደስ ተሰኘ። አጥምቀኝ አለው እንጂ “የእናትና አባት ሃይማኖቴን ተከትዬ ከኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ድረስ ያስመጣኝና ተራራ የወጣሁበትን ታላቅ የበረከት ጉዞ አድርጌ ከመመለስ ባለፈ ያንተን ኢየሱስ ለመስማት አልመጣሁም“…ብሎ አልተቆጣም።
በሉቃ ፳፯-፳ ላይም የኤማሁስ መንገደኞች ስለኢየሱስ በመጽሐፍ የተጻፈውን ሲሰሙ ልባቸው ይቃጠልባቸው ነበር። በዚያ በነበርንበት አውቶቡስ ላይ ግን ለብዙዎች ልባቸው የተቃጠለው ለምን ይኄንን ስም ትጠራላችሁ? ብለው በመናደድ ነበር።
ሐዋ ፲-፳፬ ላይ መቶአለቃ ቆርኔሌዎስም ጭራሽ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን ጠርቶ ስለኢየሱስ ስበኩኝ ብሎአል። ስለኢየሱስ መስማት ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ ጆሮ የሚያሳክክበት ምክንያት አይኖርም። ቢያንስ ስለአለቃ ገ/ሐና የዝሙት ጥበብና ሴቶችን እንዴት እንደሚያጠምዱ ከመስማት ይልቅ አምነው ባይቀበሉት እንኳን ስለኢየሱስ የሚነገረውን የወንጌል ቃል ማዳመጥ ለዝሙት ልብን ከማነሳሳት ከንቱ ወሬ ሳይሻል አይቀርም።
  በበዓለ ሃምሳ የተሰበሰቡት አይሁድ ስለኢየሱስ ሲወራ ልባቸው ተነክቶ ሐዋርያትን “ምን እናድርግ ?? “ብለው እርዳታ ጠየቁ እንጂ “በየመንገዱ በየአደባባዩ በየባሱ እየሰበካችሁ፣ አታስቸገሩ “ብለው በተቆርቋሪነት ሰበብ የአጋንንትን ቁጣ አልተቆጡም። እነዚህ ስሙን የሰሙና ያልተቃወሙ ሁሉ መጨረሻቸው ያመረ ክርስቲያኖች ሆነው በሰማይ የዘላለም ሕይወትን በምድርም በረከትን አግኝተው ወደጌታ ሄደዋል።

2. የሞት ሽታ የሆነባቸውና ስሙ ሲጠራ የሚያበሳጫቸው የሚያስቆጣቸው ሰዎች እንዲህ የሚሆኑት እነሱ ሳይሆኑ በውስጣቸው የተቀመጠው ክፉ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው። ይኽ ስም ሰዎችን ከሥጋዊና መንፈሳዊ ደዌ ስለሚፈታ ሰይጣን ይጠላዋል። መድኃኒትን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ ሰውነት መድኃኒት ለሞት እንደሚሆንበት ሁሉ ኢየሱስ የሚለውም ስም ለሞት ይኾንባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብን አምላክ እንደሚያመልክ ስለሚያምን “ኢየሱስ” የሚባለው ስም ያበሳጨው ነበር። ይኽንን ስም የሚጠሩትን ያስርና ያስገድል ነበር። ሐዋ ፬:፲፰ “በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው” “ በማለት ፈሪሳዊያን ስሙ የሞት ሽታ እንደሆነባቸው ያሳያል። “ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።“ በማለት ስሙ እንዳስገረፈ አንብበናል።

ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬም ይህንን ስም መጥራት ያስደነግጣል/ያስፈራል/ኤሌክትሪክ ያስጨብጣል። በስካር መንፈስ ናውዞ ውሃ መውረጃ ቱቦ ስር የሚያድረው ብረቱ፣ አንበሳው ሲባል ዘማዊውና አለሌው ቀምጫዩ እየተባለ ሲሞካሽ፣ ሌባው ቢዝነሳሙ፣ እሳቱ ሲሉት የኢየሱስ ስብከት ሲነሳ ግን ሃይማኖተኛ ሆኖ ሲያፈጥ ማየት በጣም ያሳዝናል። ጫትና ሲጋራ፣ ሀሺሽና ሺሻ የሚያናውዘው ሱሰኛው ሰው ለጥምቀትና ትንሣኤ በአጭር ታጥቆ መንገድ ከሚጠርግ፣ ቄጠማ ከሚጎዘጉዝ፣ ምንጣፍ ከሚያነጥፍ ውስጡ ተጎዝጎዞ ከተቀመጠው ክፉ መንፈስ ኢየሱስን ንጉሡ አድርጎ ቢያኖር ኖሮ ከዐመጻ ተግባራቱ ነጻ በወጣ ነበር። የሕይወቴ መሪ ነው ያለ ሰው ንሰሃ ገብቶ ኢየሱስ ሰው አደረገኝ ይላል እንጂ “ኢየሱስ” ብሎ የሚሰብክን ሰው “መግደል ነበር“ አይልም። እህቴና ወንድሜ ዛሬ ኢየሱስ አንተና አንች ጋር የሞት ሽታ ወይስ የሕይወት ሽታ ነው? ሁላችን ራሳችንን እንመርምር።
 ክብርና ምስጋና ነፍስ ሥጋና መንፈስን ነጻ ለሚያወጣው ሰው ለሚያደርገው ትልቅ ስም፣ ለኢየሱስ ክብር ይሁን! አሜን