Wednesday, June 15, 2016

በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው!!


የቁልቁለት መንገድ ተጀምሯል!

ይህ ጽሑፍ በመጋቢት ወር 2004 በመካነ ጦማራችን ላይ የወጣ ነው። ደግመን ማውጣት ያስፈለገን፤ ሞት የሁሉም ሰው ጽዋ ቢሆንም ማኅበረ ቅዱሳን ፓትርያርክ ጳውሎስን በደጋፊ ጳጳሳቱ በኩል እስከሞት እያዋከበ መቆሚያና መቀመጫ እንዳያሳያቸው እነሆ ፓትርያርክ ማትያስን በተራቸው እስከሞት እየተዋጋ ለመቆየት መቁረጡ በዳበረ ልምዱ ሲሰራበት መቆየቱን ለማሳየት ነው። እንዲህ ብለናቸው ነበር። አንዳች ነገር ሳያደርጉ ሞት ወሰዳቸው፤ ማኅበሩም ሰፋለት። (አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤ አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው) ዛሬም ፓትርያርክ ማትያስን ለተመሳሳይ ጽዋ  በወከባና በአድማ እያንደረደረ ይገኛል። ማኅበሩ የሚተዳደርበት አዲስ ሕግ ሳይጸድቅ፤ በዐቃቤ መንበርና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሥልጣን ነጠቃውን ጀምሯል። ወደፊትስ?

በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማኅበረ ቅዱሳን ከተራ ማኅበርነት ወደ ሀገረ ስብከትነት  አደገ። በዚህም የተነሳ ሲኖዶሱ ሙሉ በሙሉ በማኅበረ ቅዱሳን እጁን ተጠምዝዞ እንደሚሰራ አስመሰከረ። የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ  የየሀገረ ስብከቶቹ  ጠቅላይ ጽ/ቤት ሆኖ ያገለግላል። ይህ ጽ/ቤት ደግሞ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ በየ3 ዓመቱ በሚያደርገው ምርጫ በሚመድበው ሊቀጳጳስ ነው። እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና አሥኪያጅ ሆነ ማለት ራሱን የቻለ ሀ/ስብከት  ሆነ ማለት ነው። የጠቅላይ ቤተክህነቱ መምሪያዎች ሊያዙት አይችሉም። ከዚያም በላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊያዙት፤ ሊናገሩትና ሊቆጡት አይችሉም ማለት ነው። በቀጥታ በቅዱስ ሲኖዶስ በሚመደበው ሊቀጳጳስ በኩል ግንኙነቱ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር ብቻ ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ ነው እንጂ ሹመት፤ መሾም ካልቀረ!! አንድ ማኅበር ባንድ ጊዜ እመር ብሎ አናት ላይ ፊጢጥ ብሎ ከመቀመጥ ወዲያ ሹመት ከወደየት ይገኛል? ከእንግዲህ  ከተቀመጠበት ደረጃ አንጻር ማኅበር መባሉ ዝቅ የሚያደርገው ስም ስለሆነ የቅዱሳን መምሪያ ወይም የወጣቶች ሀ/ስብከት እንዲባል ሲኖዶሱ በነካካው እጁ ስሙንም ማሻሻል ይገባዋል። ከዚያም አያይዞ ለዚሁ አዲስ ሀ/ስብከት አንድ ሊቀጳጳስ እንዲመድቡለትም ጥቆማውን እናቀርባለን። አንድ ነገር ታዘብን። ቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ የሚባል አካል እንደሌላት ተረዳን። በአንድ ተራ ማኅበር እየተመሩ የእሱን ጉዳይ ብቻ ሲያነሱና ሲጥሉ ሦስትና አራት ቀናት ስብሰባ መወዘፍን ምን ይሉታል? ስንት ስራ መስራት እየቻሉ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ማውረድ እስኪያቅታቸው ድረስ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አጀንዳ ይዞ መከራከርን እውነት ሰዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚመሩት እንድንል ያደርገናል። ይህ ማኅበር ባይኖር ኖሮ ስለምን ጉዳይ ሊሰበሰቡ ነበር፤፤
ይህ ማኅበር እስካሁን እየታዘዘ እንዳልቆየ የተጻፉለት ደብዳቤዎች አረጋጋጮች ናቸው። እሱ ራሱ አልቀበልም ብሎ በደብዳቤ አረጋግጧል። አንዴ ከኢህአዴግ፤ አንዴ ደግሞ ከተቃዋሚ ነኝ እያለ፤ ሌላ ጊዜ ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገለልተኛ እየመሰለ የተጓዘበትን ሁላችንም እናውቃለን። የወንድሞች ከሳሽና አሳዳጅ ስለመሆኑም ግፉን የቀመሱ ሁሉ ይመሰክራሉ። የተጓዘባቸውን ስልቶች ሁሉ ያጠናው መንግሥት ከሽብር አቀንቃኝ  ከሰለፊያ ጋር በአንድ ረድፍ አንዳስቀመጠው ነግሮናል። ስለሆነም አቡነ ጳውሎስ ይህንን የአድማና በጥቅም የተሳሰረ ውሳኔ አልፈርምም በማለት ውድቅ ሊያደርጉት ይገባል። ማኅበሩ አስቀድሞ ከሰለፊያ ተግባር ነጻ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማምጣት ይጠበቅበታል። ደጋፊዎቹ ጳጳሳትን በማስረጃና በሰው ምስክር ተጠንተው ብቁ ሆነው ያልተገኙ ካሉ ከማዕርጋቸው መሰናበት አለባቸው።  ቄስ የነበሩ፤ ልጆች የወለዱ፤ ቅምጥ ያላቸው እንዳሉ ይወራል፤ የአንዳንዶቹም ይታወቃል።  እየተሸፋፈነ መቀመጡ ለቤተክርስቲያን ጠንቅ የሆነ ውሳኔ ለማስወሰን ያልተመለሱ ሰዎች ስብስብ መሆኑ ከታየ ውሎ አድሯል።  ነውራቸውን ለመሸፈን እንኳን ከድመት አንሰዋል።
በአንድ ወቅት አባ ገብርኤል፤ አቶ ኢያሱ ተብለው ከማዕርጋቸው ተገፈው እንደነበረው፤ ማንነታቸው እንደገና ተመርምሮ  አስቸጋሪ በሆኑት ላይ ዛሬም ተመሳሳይ ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል። ጨከን ያለ የሥርዓት ማስከበር አካሄድ መውሰድ ካልተቻለ ሲኖዶሱን በነሱ በኩል እያወከ ነገ ፓትርያርክነቱን አስቀድሞ ከዚያም ቤተመንግሥቱን እንደሚረከብ የሚጠራጠር ካለ የማኅበሩን አካሄድ የማያውቅ ብቻ ነው። አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤ አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው። ከሆነለት ፓትርያርክነቱን ለሚታዘዝ  ሰው  ሰጥቶ ወደ ቤተመንግሥት ሰተት ብሎ ለመግባት ከጽዋ ማኅበርነት ወደ መምሪያ ተገዳዳሪነት፤ አሁን ደግሞ ወደ ሀገረ ስብከትነት ማደጉ ከምንም በላይ ማሳያ ነው።  ታዲያ ከእንግዲህ የቀረው ምንድነው? ይህ ሁሉ ለጽድቅ ነው እንዳይትሉንና እንዳንስቅ ጥቂት እዘኑልን። ነጋዴና  ሸቃጭ የሆነ  ቅዱስ ማኅበር  አራት ኪሎ የለም ። እያየነው በትንሽ በትንሹ የወጣው ይህ ሐረግ ቤተ ክህነቱን አንቆ ወዳሰበበት በመጓዝ ላይ ነው። እግዚአብሔር ለዚህ ክፉ ማኅበር አሳልፎ ከሰጠ በእውነትም ቤተክርስቲያኒቱ ለፈተናና ለውድቀት ተመርጣለች ማለት ነው። ተወደደም፤ ተጠላ ሲኖዶስ በየዓመቱ ያለህውከት ማለፍ አይችልም።
ሰውዬው «ሁሉን ለማየት መቆየት»እንዳለው የሚሆነውን ለማየት ከዕድሜው አይንፈገን!

Monday, June 13, 2016

"ፓ" ይላል ምዕመኑ!!!



«በዘውድአለም ታደሰ»
ነብይ ነኝ ባዩ የቤተክርስቲያን ደላላ!

ይሄ ሰውዬ "ጎሳ" ይባላል። በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ቸርቾች ሲሰብክ አይቼዋለሁ። (ጎፋ መድሃኒአለም ፣ ዘፀአት ፣ FBI ፣ ወዘተ... ) የሚደክም አይነት ሰው አይደለም። ውሃ ሳይጎነጭ በተከታታይ ለሶስት ሰአታት የማውራት አቅም አለው! የምእመኑን ሳይኮ በልቶታል። ህዝቤን ምን እንደሚያስጮሀት ስለሚያውቅ አዳራሹን በጩኸት መናጥ ለነብይ ጎሣ ቀላል ነው!
ብዙ ግዜ ቸርቾች ይህን ሰውዬ ሚጋብዙት ገንዘብ ክፉኛ ሲያስፈልጋቸው ነው። ወይ መሬት ሊገዙ ሲያስቡ ... አሊያም የተሻለ አዳራሽ ሊከራዩ ሲፈልጉ ... ብቻ የሆነ የፈንድ ሬይዚንግ ጉዳይ ሲኖር ጎስሻን ይጠሩትና በዚያች ጮሌ ምላሱ የራሱንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ታሪክ እያጋነነ በመስበክ የዚህን ምስኪን ምእመን ኪስ ያራቁትላቸዋል!
«ነኝ ያልኩ ኮንትራክተር ነበርኩ፣ ነፍፍ መኪኖችና ብዙ ሰራተኞች ነበሩኝ፣ ጌታ ሲገባኝ ግን ንብረቶቼን ሸጬ ለቸርች ሰጠሁ» ብሎ ይጀምራል ተረት ተረቱን።
«ፓ» ይላል ምእመኑ!
«ከዛ ክፉኛ ተቸገርኩና፣ ምልስ ምቀምሰውን አጣሁ፣» ብሎ ለፅድቅ ሲል የከፈለውን መከራ እያጋነነ ያወራል!
«በከተማዋ ስሜ የተጠራ ኮንትራክተር እንዳልነበርኩ ምልስ ምቀምሰውን አጥቼ ተቸገርኩ» ሲል ረሃብን የሚያውቀው የዚህ ህዝብ አንጀት በሀዘኔታ ይላወሳል።
የሰዉን አቴንሽን ማግኘቱን ሲያረጋግጥ ታዲያ ... እንዴት ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ እግዜር ሀብታም እንዳደረገው፣ እንዴት እንዳበለፀገው ትረካ በሚመስል ሁኔታ ያወራ ያወራና የህዝቡን አእምሮና ስሜት በሚገባ እንደተቆጣጠረ ሲረዳ እንዲህ ይላል ..
«ጌታ እንዲህ ሲል ተናግሮኛል» ብሎ ይጀምራል ነብይ ጎሳ። (ማን ነብይ እንዳረገው እንጃለቱ)
«ጌታ ዛሬ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ያላችሁትን ሁላችሁን እባርካለሁ ብሎኛል» ሲል እቺ በረከቷን ከአርያም ሳይሆን መድረክ ላይ ከቆመው አረም የምትጠብቅ ምእመን አዳራሹን በጩኸት ታቀልጠዋለች! በጭብጨባው የሚሟሟቀው ጎሲሻም «አንዳንዶቻችሁ ከዚህ አዳራሽ ስትወጡ ከበረከታችሁ ጋር ትገናኛላችሁ» ሲል አዳራሹ በአንድ ድምፅ «አሜን» ይላል።
«አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ቤታችሁ ስትገቡ በረከታችሁ ቁጭ ብሎ ይጠብቃችኋል»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ ስራ ቦታችሁ ላይ»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ የዛሬ ሳምንት»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ የዛሬ ወር»
«አሜን»
«እግዜር በተራራው ላይ ሙሴን ሲያገኘው በእጅህ ላይ ምን አለ? ብሎ ነው የጠየቀው ወገኖቼ። እግዜር እጃችን ላይ ባለ ነገር ነው ሚሰራው። ዛሬ በእጃችሁ ላይ ምን አለ?» ይላል ብልጣብልጡ ጎሳ!
ይሄ የዋህ ሁን ሲባል ሞኝ የሆነ ህዝብም እውነት መስሎት እጅና ኪሱን ያያል! ከዛማ በቃ አዋራው ይጨሳል .... ፒፕሉ በረከቱን በስጦታው ለመግዛት ይጋፋል! አዳሜ ወርቋን ከአንገቷ ላይ እየበጠሰች፣ ገንዘቧን ከቦርሳዋ እያራቆተች፣ ምንም የሌላት ደግሞ የእጅ ስልኳን ሳይቀር መባ እቃ ውስጥ እየጨመረች የማይፈፀም ትንቢት ታቅፋ እርቃኗን ከአዳራሹ ትወጣለች ... ልትባረክ ነዋ ሃሃሃሃ
ከላይ እንዳልኩት ነብይ ጎሳ ነብይነቱን ከየት እንዳገኘው ማንም አያውቅም። የሚያወራው ታሪክም እውነት ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም። ይህን ሰውዬ የሚጋብዙት ስግብግብ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም የሰውየው ምስክርነት እውነት የተፈፀመ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ጥረት አያደርጉም! እነሱ ሚፈልጉት በሱ ጅንጀና የሚዘንበውን የገንዘብ ዶፍ ነው። የስብከቱ መለኪያ በሱ ስብከት አማካኝነት የገባው የገንዘብ መጠን ነው እንጂ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም!
አሁን ቤተክርስቲያን በጎሳና ጎሳን በሚመስሉ መንፈሳዊ ደላሎች እየታመሰች የምትገኝበት ሰአት ላይ ትገኛለች። መፅሀፉ ጎሳንና መሰል አገልጋዮችን «ለመንጋው የማይራሩ» ይላቸዋል!
እንዲጠብቁት የተሰጣቸውን ምእመንና እረኛ የሆኑለትን መንጋ ስጋ እየበሉ ሰብተው ቆዳውን ገፍፈው ይለብሳሉ! በአስራትና በበኩራት፣ በመባና በፍቅር ስጦታ ስም፣ ገንዘቡ ወደካዝናቸው ይጋዝ እንጂ የገንዘቡ አመጣጥ እነሱን አያስጨንቃቸውም። በምእመኑ ፍራንክ ትልልቅ እቅዶች ያቅዳሉ፣ የህዝቡን መሶብ አራቁተው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ይገነባሉ፣ በሊትር ሶስት ኪሎሜትር የሚሄዱ ላግዥሪ መኪኖችን ይነዳሉ። ይሄ ተስፈኛ ምእመን ግን ከሰማይ መና እየጠበቀ በደረቅ ምድረ በዳ ደረቅ ትንቢታቸው ታቅፎ ከቃዴስ ቃዴስ ሲንከራተት ይኖራል።
በአብዛኞቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያኖች ዘንድ ምድር ምድር የሚሸት ስብከት በዝቷል። ሰባኪው ሁሉ የ prosperity Gospel (የብልፅግና ወንጌል) አቀንቃኝ ሆኗል፣ ምእመኑም በረከቱን የሚለካው በምድራዊና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ነው! «ሀገሬ በሰማይ ነው» አይነት ንግግሮች ከምእመኑ አንደበት መደመጥ አቁመዋል። ኢየሱስ የሞተው ለቼቭሮሌት መኪናና ለግራውንድ ፕላስ ስሪ ፎቅ ይመስል ወሬው ሁሉ ቤት ስለመስራትና ቤት ስለማፍረስ ሆኗል ... እንደ ዊነርስ ቻፕል አይነት ቸርቾችማ ወሬው ሁሉ ሱሪ ስለመቀየርና መኪና ስለመንዳት ከሆነ ቆየ። «በመንፈስ መኪና የመንዳት» ፕሮግራም ሁሉ ያካሂዳሉ አሉ! ሃሃሃ
ነብያቶች በዝተዋል። ነብይነት ግን ከሞተ ቆየ! ሰባኪዎችም አሸን ናቸው። ስብከት ግን ስልሳዎቹ ላይ ቆሟል! በየመድረኩ ተኳኩለው እንጣጥ እንጣጥ የሚሉ (ባለብዙ ሚስት ዘማሪዎች እልፍ ናቸው) መንፈሳዊ ማንነትን የሚያንፅ መዝሙር ግን ከመድረኩ ነጥፏል!
በፅድቅና በቅድስና የሚያገለግሉ አንዳንድ አገልጋዮች እንዳሉ አይጠፋኝም። ግን እነዚህ አገልጋዮች ከጎሳውያኑ ጋር ሲተያዩ በገምቦ ውስጥ እንዳሉ ጥቂት ጠብታዎች ናቸው! ስለዚህ ባህር ውስጥ እንዳሉ አይቆጠሩም። እኔ ማወራው ባህሩን ስለሞሉት የተበከሉ አሳዎች ነው!
 ቸርቾች በየመቶ ሜትሩ ከተማ ውስጥ ፈልተዋል። ደቀመዝሙር ማፍራት የማይችሉ ውሀ አልባ ምንጮች ናቸው እንጂ! ክርስቲያን ያልሆኑ የክርስቶስ ሰባኪዎችና ክርስቶስን የማያውቁ አገልጋዮች ይሄን ምስኪን ምእመን እንደአሻንጉሊት እየተጫወቱበት ነው! አገልግሎታቸው ያከበራቸውን ህዝብ በመናቅና በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ነው! «ለምን?» ብሎ ጥያቄ የሚያነሳ ሲመጣ «ጌታ በቀባው ላይ እጅህን አታንሳ» በማለት በጥቅስ ያስፈራሩታል። በፅድቅ ለማገልገል ከላይ እታች እያሉ የጅብ ድግሳቸው ላይ የማይሳተፉትን ንፁሀን ደግሞ የተለያየ ስም ጀርባቸው ላይ በመለጠፍ ከአገልግሎት ያግዷቸውና የሚከተላቸውን ምእመን ኑሮ እየቀሙ ይኖራሉ! ሳቁን መንትፈው ይስቃሉ! ደስታውን አራቁተው ይደሰታሉ! እውነትም ለመንጋው የማይራሩ ሆዳሞች!
ዘመኑ የባቢሎናውያኑን ዘመን ይመስላል። ትርምስ እንጂ መረጋጋት የለም! ጩኸት እንጂ መግባባት ጠፍቷል። ግራ የተጋቡ ባለራእዮችና ያልተማሩ አስተማሪዎች መሬት ባልረገጠ የትምህርት ወጀብ ህዝቡን እየናጡት ነው። በተቀየጠ ዶክትሪንና በስህተት አስተምህሮ ምእመኑን ከወንጌል አርቀው አይኑን በማሰር ወደቁልቁለት እየነዱት ነው! ነብያት ነን ባዮቹ ወንዝ በማያሻግር ትንቢት ሲወራጩ መድረኮቻችን ላይ ውለው ያድራሉ። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች በተራ ፉከራና ሽለላ የተሞሉ ፍሬ አልባ ደረቅ መሬቶች ናቸው!
በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች እየተጋበዘ ህዝቡን የሚያራቁተው ደላላው ነብይ .... «ነብይ ጎሳም» ከላይ ለጠቀስኳቸው ሆዳም አገልጋዮች እውነተኛ ምልክት ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ!

እቀጥላለሁ!‎

Saturday, June 4, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን አሁን የቤተ ክርስቲያን፤ ቆይቶ የመንግሥት መጥበሻ ምድጃ ነው!


በታሪክ አጋጣሚ የደርግን መውደቅና ግርግርን ተተግኖ የተፈጠረው ማኅበረ ቅዱሳን የመጥበሻ ምድጃ ከሆነ እነሆ 23 ዓመታት አለፉት። ብዙዎችን በትኗን፤ አሳዷል። ዳግም እንዳይመለሱ በማድረግ እንደተዋጊ በሬ እየበጠበጠ ከበረት አስወጥቷል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አፋፍተው ያሳደጉትን አቡነ ጳውሎስን ሳይቀር በአድማ የመጥበሻ እሳት እየለበለበ እስከመቃብር ሸኝቷል። የአሁኑን ፓትርያርክ የአቡነ ማትያስን ወንበር በተሾሙ ሰሞን ለመረከብ ተፍ ተፍ ብሎ ሳይሳካለት ቢቀር በተለመደ የመጥበሻ ምድጃው ላይ አስቀምጦ ላለፉት 3 ዓመታት  በአድማው ግሪል / GRILL/ እየጠበሰ ይገኛል።

ፓትርያርክ ማትያስ ብቻቸውን ሆነው ይህንን መጥበሻ ምድጃ ሊያስወግዱ ብዙ ታግለዋል። ነውራም ጳጳሳቱ እዳ በደላቸው በዚህ ማኅበር የኃጢአት መዝገብ ላይ ስለሰፈረ ከፓትርያርኩ በተጻራሪ ቆመው ውግንናቸው ለማኅበሩ ሆኖ ታይቷል። የማኅበሩ ሥፍራ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የት ነው? በሚለው ነጥብ ላይ ጥያቄ ያላቸው ፓትርያርክ ማትያስ ድርሻውን፤ አቅሙንና ተጠሪነቱን የሚወስን አዲስ መተዳደሪያ ደንብ እንዲወጣለት ያደረጉት ተጋድሎ ላይ ውሃ በመቸለስ የሲኖዶስ ጉባዔ በመጣ ቁጥር የሚያጨቃጭቅ አጀንዳ እያስገባ ሲሾልክ ቆይቷል። ዘንድሮም ይህን የቤት ሥራ ሰጥቶ በአንድ አጀንዳ ላይ ለ4 ቀናት ካጨቃጨቀ በኋላ የሲኖዶስ አባል የሆነው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር መፍትሄ አስምጦ ሊገላግላቸው ችሏል። ይህ ሁሉ የሆነው በማኅበሩና በጉዳይ ፈጻሚ ጳጳሳቱ የተነሳ ነው።

የእንደራሴ መኖር አለመኖር ለማኅበረ ቅዱሳን አሳሳቢው አይደለም። ነገር ግን በዘንድሮው ጉባዔ ላይ ማንሳት ያስፈለገው የራሱ ስሌት ስላለው እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድክመት ከሱ መኖር በላይ አስቸጋሪ ፍጡር ስለመጣ አይደለም። በዚህም የተነሳ በአቅም ማነስ ሰበብ ፓትርያርኩን አሸመድምዶ በማስቀመጥ ለ3 ዓመታት ያህል እሳት ካነደዱበት ሥጋት ነጻ ለመውጣት የተያዘ መላ ከመሆን አይዘልም። ከዚህም በፊት እንዳልነው ጳጳሳቱ በሀገረ ስብከታቸው መሥራት ያልቻሉትን የመንፈሳዊና ሥጋዊ የልማት ሥራዎች  እንደራሴው እየዞረ የሚሰራላቸው አለመሆኑንም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ማኅበረ ቅዱሳን እስካለ ድረስ ታዛዥ ያልሆነ የትኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሥልጣን  ማኅበሩ ባዘጋጀው መጥበሻ ላይ ይጣዳል። ምርጫቸው ከማኅበሩ ጋር መቆም አለያም በተጻራሪ ሆነው ለመጥበሻው ራሳቸውን ከማዘጋጀት የግድ ነው። አባ ሳዊሮስ ከአዲስ አበባ ማኅበረ ካህናት ጋር ቆመው ማኅበሩን ሲያጋልጡ ምድጃውን አዘጋጅቶ መጥበስ ሲጀምር እጃቸውን አንስተው ለማኅበሩ ለማስረከብ መገደዳቸውን አይተናል። አባ ፋኑኤል ማኅበሩ የሌለበት ቦታ የት ሄጄ ልሥራ? እንዳላሉ ሁሉ ምርኮኝነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ግን ከማኅበሩ መጥበሻ ግሪል ላይ ወርደው እረፍት ሊያገኙ ችለዋል። ሌሎቹ ግን የሚደርስባቸውን እሳት አስቀድመው ስለሚያውቁ ቃላቸውን አክብረው የጫናቸውን በማራገፍ ግንቦትና ጥቅምት በመጣ ቁጥር በማኅበሩ አጀንዳ አስፈጻሚነታቸው ቀጥለዋል።

 ማኅበረ ቅዱሳን በስመ ተሐድሶና ሙሰኛ ነጠላ ዜማው የፈጃቸውና ያቃጠላቸው ካህናት ቁጥራቸው ብዙ ነው። ስለቅድስናና መንፈሳዊ ንጽህና በዋለበት ያልዋለ የዋልጌዎች ስብስብ ይህ ማኅበር ስም እያጠፋ ያሳደዳቸው፤ ስለኃጢአታቸው ንስሐ የሚገቡበትን በር እየዘጋ ተስፋ በማስቆረጥ ያስወጣቸው የትየለሌ ናቸው። የሚገርመው ግን ነውራም ጳጳሳቱን በቅድስና ካባ ሸፍኖ ለአገልግሎቱ የሚጠቀምባቸው የከባቴ አበሳ ተፈጥሮ ስላለው ሳይሆን እስካለገለገሉት ድረስ ብቻ ነው። እያንዳንዱ የማኅበሩ አባል በተለይም አመራሩ እነአቡነ እገሌ እስከምን ድረስ የጉስቁልና ባሕር ውስጥ እንደሰጠሙ እያወቀ በስምምነት አብሮ ይሰራል። ነገር ግን ከማኅበሩ አቋም ካፈነገጡ ከዚህ በፊት እንዳደረገው የእዳ ደብዳቤአቸውን ከማንበብ አይመለስም። ይህ በተግባር የተረጋገጠ እውነት ነው።

አንዳንዶች ማኅበሩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ብቻ አድርገው ያያሉ። ነገር ግን ማኅበሩ  እንደግብጹ የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር በፖለቲካው መድረክም የረቀቀ ተልእኮ ያለው ማኅበር ነው። በአባልነት ያቀፋቸው ሚኒስትሮች፤ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፤ ሥራ አስኪያጆች፤ ፖሊሶች፤ ዳኞች፤ የሕዝብ አገልግሎት ሠራተኞች፤ መምህራንና ተማሪዎች፤ የሙያ ማኅበራት፤ በ44 አኅጉረ ስብከት ውስጥ ያሉ ሚሊዮኖች የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ የጥምቀት ተመላሽ ተጠባባቂ ጦር የመሳሰሉትን በአባልነት እየመለመለ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የራሱን ዶክትሪን በመጋት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ካሰኛቸው ውሎ አድሯል። ዛሬ ከሲኖዶስ ወይም ከፓትርያርኩ በላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪና ጠባቂ ከማኅበሩ በላይ የለም የሚለው አስተሳሰብ በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ በሰፊው ተሰርቷል። ዘመናዊ የክርስቲያን ብራዘር ሁድ ማለት ማኅበረ ቅዱሳን ነው።

ሌላው የማኅበሩ ተንኮል አሁን ካሉት ታማኝና ታዛዥ ጳጳሳት በተጨማሪ ከእንግዲህ የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት በራሱ መስፈርት የተመለመሉና ወደፊት ችግር እንደማይፈጥሩ የተረጋገጠላቸው ብቻ እንዲሆኑ ይፈልጋል። እነዚህ የማኅበሩ እጩ ኤጲስቆጶሳት ያለፈ ታሪካቸው የቱንም ቢመስል አሳሳቢ አይደለም። ተቀባይነታቸው አርአያነት ባለው ሁኔታ ቢሆንም፤ ባይሆንም ለማኅበሩ አስጊ እስካልሆኑ ድረስ እንዲመረጡ አጥብቆ ይሰራል። ነገር ግን በተቃራኒ ማኅበሩን የሚፋለሙ ከሆነ እንደአባ ሠረቀብርሃን ወ/ሳሙኤልን የመሳሰሉት በልዩ ልዩ ስምና ወንጀል በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ እጃቸውን ካልሰጡ በስተቀር ለእጩነት ሊቀርቡ አይችሉም።

በአጠቃላይ ማኅበሩ በታሪክ አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተገኘ መጥበሻ ምድጃ ነው። በዚህ ምድጃ ዲያቆናት፤ ቀሳውስት፤ መነኮሳት ተጠብሰዋል። ሰባኪያነ ወንጌልና አስተዳዳሪዎች ተጠብሰዋል። ጳጳሳትና ፓትርያርኮች ተጠብሰዋል። እውነቱን እያወቁ ከመናገር ብዙዎች የተቆጠቡት ማኅበሩ መጥበሻው ላይ ከጣዳቸው የሚያወርዳቸው ስለሌለ ነው። ልክ እንደ መንግሥታዊ የስለላ መዋቅር የማኅበሩን ስም በተቃውሞ በአውቶቡስ፤ በታክሲ፤ በሬስቶራንት፤ በየካፌውና በሕዝብ መሰብሰበቢያ ቦታዎች መጥራት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። መንግሥት ላይ ምን ዓይነት የአንኮበር መድኃኒት እንደተረጨበት ባናውቅም እሱም በፍርሃት ይሁን በድንዛዜ ፈዞ ቀርቷል።  እውነታው ግን ማኅበሩ ለየትኛውም ወገን መጥበሻ ምድጃ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ነው።