Friday, April 1, 2016

ያገር ያለህ ወይም የዳኛ ያለህ!!!


ከእውነቱ ( ክፍል ሁለት)

በማህበሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ላይ ያስተዋልኩት ድካም፡

 የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የጫነችብንን ኢመጽሐፍቅዱሳዊ የባእላት አከባበርን ሕዝቡ በበለጠ
መልኩ እዲቀጥልበት ለማድረግ ሰምተናቸው ለማናውቃቸው ሰዎች የቅድስና ማእረግ
በመስጠት/በማሰጠት ሕዝቡ ከሥራ ይልቅ ባእል አክባሪ እንዲሆን መደረጉ፣
 በሌለ የጉልበትና የገንዘብ አቅም ሕዝቡ ለጽድቅ እየተባለ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች በመጓጓዝ
እንዲደክም መደረጉ /ፈጣሪ በቦታ የሚወሰን ይመስል/
 በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የጽላት ቀረጻና
የታቦት ተከላ ሥራ መሥራት፣
 እግዚአብሔርን ተርቦና ተጠምቶ በአውደ ምህረቱ ዙሪያ ለተሰበሰበው የዋህ ሕዝብ ፍቅር
የሚያስተምረውን የወንጌል ቃል ከመስበክ ይልቅ በእለቱ የሚከበረውን የጻድቅ ገድልና ታሪክ
ከሃይማኖትህን ጠብቅ የማስፈራሪያ መርገም ጋር በማሰማት ለጦርነት ማዘጋጀት፣
 ሕዝቡ በራሱ መረዳት ማን ምን እንደሆነ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እየመዘነ ሃሰቱንና
እውነቱን በመለየት የሚጠቅመውን እንዳይዝ መረጃ በሌለው አሉባልታ ተሞልቶ በውስጡ
ጥላቻና ቂም አዝሎ የራሱን ወገን እንዲጠላ በልዩ ወንጌል ሰባኪዎች መሰበኩ፣
 የበጉ ሐዋርያትና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ቀደምት የእምነት አባቶች አድርገውት የማያውቁትን
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ በጸበል ተገኘ ጋጋታ ሕዝቡን ማንገላታታቸው፣
 በአጠቃላይ ሕዝቡን በቃል እውቀት ሳይሆን በቅርስና በባንዲራ ፍቅር የራሱን ወንድም
በጭፍን ወግሮ የሚያሳድድ ሃይማኖተኛ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ይህ ጸሐፊ በራሱ ቤተ
ሰብ መካከል ባደረገው አጭርጥናት ሊያረጋግጥ ችሏል።

2/ ኦርቶዶክስ ተሐድሶ ማነው?

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተወልደው በማደግ ባህሏንና ትምህርቷን ጠንቅቀው የሚያውቁ
የቤተ ክርስቲያኒቷ ልጆች ነን ይላሉ፤ የኦርቶዶክስ ተሐድሶ ማህበር በሚል መጠሪያ ስም፡ ኦርቶዶክስ
ቤተ ክርስቲያናችን ከውጭና ከውስጥ በደረሱባት ልዩ ልዩ ተጽእኖ ምክንያት ከተመሰረተችበት
የክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ርቃ ልዩ ወንጌል በመስበክ የመስቀሉን የማዳን ሥራ ቸል ብላለች፤ ስለዚህ
ወደ ቀደመ የወንንጌል ጅማሬዋ ትመለስ፤ በእግዚአብሔር ቃል /መጽሐፍ ቅዱስ/ መስተዋት ፊቷን
በማየት ክፉ ሰዎች ያለበሷት የደብተራዎች፣ ያስማተኞችና የደጋሚዎች ልብስ በንጹሁና እንከን የለሽ
በሆነው በእግዚአብሔር ቃል ልብስ /በክርስቶስ/ ይተካ በማለት ይጮሃሉ።

እንዲያውም እነዚህ ሰዎች የቤተ ክርስቲያናችን ወይም ያገራችን ታሪክ ይፈተሽና ይመርመር፤ ይዘነው
የተነሳነውንም የተሐድሶ ጥያቄና ሃገራዊ አጀንዳ ያገራችን ሽማግሌዎች፣ ጳጳሳት፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች
በአጠቃላይ ሕዝቡ ይስማውና ማን የኦርቶዶክስ ጠላትና ወዳጅ እንደሆነ ጠቅላላ ምእመኑ እውነቱን
ይረዳ በሚል ግልጽነት በይፋ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መረዳት ችያለሁ።
እኔም እነዚህን አንዳንድ የኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያንን የተሀድሶ ሥራ አራማጆችን ጠጋ ብየ በመጠየቅ
የሚከተሉትን መረጃዎችን አግኝቻለሁ፡

1. የቤተ ክርስቲያናችን ጅማሬ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ በወንጌል ላይ ብቻ የተመሰረተች መሆኗን፣

2. በመጀመሪያው ጳጳስ በወንጌል ላይ የተጀመረው ክርስትናችን ግን እኒሁ ጳጳስ ከሞቱ በኋላ፡
 በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ስር በመውደቅ ለ1600 ዓመታት ከ110 በላይ በሚሆኑ
የውጭ ሀገር ጳጳሳት /የግብጽ የፖለቲካ ሠራተኞ/ መንፈሳዊ ቅኝ ተገዢዎች በመሆን አባይን
በመገደብ ሥራ ሠርተን እንዳንበላ እስካሁን ድረስ የ30 ቀናት ባእላት ባሪያዎች መደረጋችንና
ከእነዚህ መካከል አንዱ የካሊፋው ዋና ወኪል /አቡነ ሳዊሮስ/ እነደነበረ፣
 የዮዲት ጉዲት የ40 ዓመታት ግዛትና የቤተ ክርስቲያኗ መጽሐፍትና ካህናት መቃጠል፣
 የግራኝ ሙሐመድ የ15 ዓመታት ግዛትና የሙስሊም ክርስቲያኑ ሬሽዮ 9፡1 መድረሱና የቤተ
ክርስቲያኒቷን ውበት ማበላሸቱ፣

 ዘርዓ ያእቆብ በንግስናው ወራት በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተመዘኑ የድርሰት ጽሑፎችን በቤተ
ክርስቲያኒቷ ውስጥ ያለገደብ ማስገባቱና የተሃድሶን ጥያቄ ያነሱ መነኮሳትን መጨፍጨፉ
/የፕ/ር ጌታቸውን ደቂቀ እስጢፋኖስን መጽሐፍ መረጃ ይጠቅሳሉ/፣
 የቤተ ክርሰቲያኒቷ ሲሦ መንግሥት ውል መዋዋልና ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ መንግሥትን
ከሰሎሞንና ከዳዊት ጋር በማያያዝ የታቦትና የጽላት መጥቷል አፈታሪክ ጅማሬ /አቡነ ተክለ
ሐይማኖትን ተጠያቂ ያደርጋሉ/፣

 የደብተራ ቡድን በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ተነስቶ የመናፍስት አሠራር እስካሁን ድረስ
በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በሰፊው መለመዱ ……….. ወዘተ።
የመሳሰሉትን ነጥቦች በድፍረትና በማስረጃ በማቅረብ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከተመሰረተችበት የወንጌል
መሰረቷ ፈቀቅ ብላለችና ወደ ቀደመ የወንጌል ጅማሬዋ ትመለስ በማለት አጥብቀውና በነፍሳቸው
ተወራርደው ለዚህ ሥራ እንደተነሱ ጨክነው ይሟገታሉ። ይህም መንፈሳዊ መታደስ በአገሪቱ ውስጥ
ላለው ሁለንተናዊ ችግር /ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ችግር/ ዋና መፍትሄ ይሆናል
ብለው በማስራጃ ለማሳመን ይሞክራሉ።
ይህን ጉዳይም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ተረድቶና ማን ምን እንደሆነ ተገንዝቦ ለመንፈሱ፣ ለነፍሱና
ለሥጋው የሚበጀውን በመጽሐፍ ቅዱስ/በወንጌል ሚዛን መዝኖ የሚረባውን ይይዝ ዘንድ
ራእያቸውንና ዋና ተልእኳቸውን ለሕዝብ በይፋ ያቀርባሉ፡

የተሐድሶ ራእይ፡

‘‘ጥንታዊና ሐዋርያዊት የነበረች ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን በየዘመናቱ ከደረሰባት ውስጣዊና
ውጫዊ ተጽዕኖ የተነሳ ከተተከለችበት የእውነት ወንጌል በማፈንገጥ አሁን ላለችበት ውድቀት
በመዳረጓ ይህን ሁኔታዋን በከበረው የጌታችንና የመድኃኒታችን ቅዱስ ወንጌል በመመዘንና ወደ ቀደመ
የወንጌል ክብር በመመለስ በእጇ የሚገኘውን ተከታይና የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ክርስቶስ
ኢየሱስን በማወቅና በማመን የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት በማግኘት ለጌታችን ቀን ያለነውርና
ያለነቀፋ ሆኖ እንዲገኝ በማዘጋጀት ለአፍሪቃና ለተቀረው ዓለም የሚላኩ ቅዱሳን አገልጋዮችን
በማፍራት የሚጠበቅባትን የወንጌል አደራ ስትወጣ ማየት ነው’’

የተሐድሶ ተልዕኮ፡

1. የቤተ ክርስቲያኒቷን አንድነትና የሀገራችንን ጥቅም በጠበቀ መልኩ ምዕመናን በጌታችንና
በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ትክክለኛና እውነተኛ ተሀድሶ በማድረግ ለዘላለም
ሕይወት እንዲዘጋጁ መርዳት፣

2. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደ የደረጃው በተዘጋጁ የወንጌል
ትምህርቶች በማሰልጠንና በማሳወቅ ለስብከተ ወንጌል ሥራ ማዘጋጀትና የአገልግሎት ቦታዎች
ሁሉ እውነትን በተረዱ አገልጋዮች እንዲሸፈኑ ማድረግ፣

3. በየዘመናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የገቡትን የስህተት ትምህርቶች ሥርዓቶችና ባሕሎች በቅዱሱ
ወንጌል በመዳኘት ከሕዝባችንና ከቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶቻችን እንዲወገዱ ማድረግ፣

4. ለአገራችን ኢትዮጵያ ዕድገትና ለዓለማችን ጥቅም በክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ከመልካም ዜጋ
ግንባታ ጀምሮ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ግዴታቸውን የሚወጡ ትጉህ
ሠራተኞችን ማፍራት፣

5. ጸረ ወንጌል ያልሆኑና ለክርስቶስ ወንጌል መስፋፋት ጠቀሜታ ያላቸውን ሥርዓቶች፣ ባህሎችና
ልማዶች ለክርስቶስ ወንጌል መሰበክ እንዲያገለግሉ መጠበቅና ማስጠበቅ።

Tuesday, March 29, 2016

የሕይወት ጉዞ ጠላቶች አይለወጡም!


/ኤፍሬም ባለጊዜ/
ሁለት ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ክርክር ገጥመዋል። አንዱ አማኝ ሲሆን ሌላኛው ከሀዲ ነው፣ ያውም የፈጠረውን አምላክ የካደ። ክርክራቸው ወዲህ ነው። አማኙ እግዚአብሔር አለ ይላል። ከሀዲው ሰው ደሞ በፍጹም የለም ይላል። አማኙ ሰው የእግዚአብሔርን መኖር ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱሱንም፣ ሳይንሱንም እያጣቀሰ ብዙ ተናገረ። ነገር ግን ሰሚ አልነበረውም። ከብዙ ክርክር በኋላ ይህ አማኝ ሰው አንድ ጥበብ መጣለትና ከሀዲውን ሰው እንዲህ ሲል ጠየቀው። እግዚአብሔር ቢኖር ይሻላል ባይኖር? ይህን ጊዜ ከሀዲው ሰው ፈጠን ብሎ ባይኖር ይሻላል አለ።        ልብ በሉ!  እንግዲህ ከሀዲው ሰው እግዚአብሔር የለም ብሎ ሲከራከር የነበረው የመረጃ ችግር ስለነበረበት አልነበረም። እግዚአብሔር የለም የሚለው እግዚአብሔር እንዳይኖር ስለሚፈልግ ብቻ ነው። ጠላቶችሁ ያላችሁን የከበረ ነገር በፍጹም ማመን አይፈልጉም።  ያ ማለት ግን የከበረ ነገር እንዳላችሁ አያውቁም ማለት አይደለም። አንዳንዶች ግልጡን እውነት በጭራሽ መስማት አይፈልጉም ወይም ቢያውቁም ለማመን አይፈልጉም።

  በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተፃፈው ዳዊት ለወንድሞቹ ምግብ ለማድረስ ወደ ጦሩ ሰፈር በመጣ ጊዜ የኤልያብ ቁጣ በዳዊት ላይ ነዶ " ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሀቸው? እኔ ጠማማነትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁ፣ ሰልፉን ለማየት መጥተሀልና" ነበር ያለው።  አሁን ኤልያብ ለዳዊት መንገር የፈለገው ዋና ሀሳብ ግልጽ ነው። አንተ እረኛ ነህ፣ አርፈህ በጎች ጠብቅ የሚል ነው። ነገር ግን እረኝነት ለዳዊት የስልጠና ስፍራ እንጂ የህይወቱ ጥሪ ላለመሆኑ ከኤልያብ የተሻለ ምስክር የለም። ምክንያቱም ዳዊት ለንጉሥነት በተቀባ ጊዜ ኤልያብ እዚያው ቦታ ላይ ነበር። (ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። 1ኛ ሳሙ 16፥13)

  ነገር ግን ኤልያብም እንደዚያ ከሀዲ ሰው ችግሩ የመረጃ ሳይሆን የፍላጎት ነበር። ፍላጎቱ ደግሞ ዳዊት በእረኝነት ዘመኑን እንዲጨርስ ነው።  በሥራችሁ፣ በሙያችሁና በንግግራችሁ ሁሉ እውነተኞች ብትሆኑም የሚቃወሟችሁ ሰዎች ቁልቁል ሊደፍቋችሁ ይሞክራሉ። መንገዳችሁን በወጥመድ ያጥራሉ። የምትወድቁበትን ጉድጓድ ይቆፍራሉ። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወማችሁ ይችላል?

በመጨረሻም ለማለት የምፈልገው በከንቱ በሚጠሏችሁና ሁልጊዜ ውድቀታችሁን በሚመኙ ሰዎች ልባችሁና መንገዳችሁ አይያዝ። ከዛሬ ነገ በእኔ ላይ ያላቸውን አቋም ይቀይራሉ ብላችሁም አታስቡ።  እንዲህ አይነት ሰዎች የሕይወት ዘመን ቋሚ ጠላቶች ናቸው። ነገር ግን እንደ ክርስቲያን በብዙ ፍቅርና ጸሎት አስቧቸው። እኔም እናንተም እዚህ የደረስነው በሰው ፍቅር አይደለም፣ በእግዚአብሔር ምህረት እንጂ!

Saturday, March 26, 2016

ቀሲስ የ“ክብረት ልጅ”፥ ምነው በስድብ ቃል በጣም ጮኸ?!


ምንጭ፦ የአቤኔዘር ተክሉ ገጽ http://abenezerteklu.blogspot.com/
የክብረት ልጅ እይታዎቹን በሚያቀርብበት ብሎጉ፥ “ፓትርያርኩ፦ ለኢትዮጲያ የደኅንነት ፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት” በሚል አንድ ጽሁፍ፥ ዛሬ አስነብቦ ድንገት ያየ ሰው ጠቆመኝና ወደጡመራው መድረኩ ገብቼ አነበብኩት፡፡ ዳንኤል በዚህ ጽሁፉ “100% ማኅበረ ቅዱሳን ሊያዘጋጀው ከጫፍ የደረሰውን ዐውደ ርእይ የከለከሉት ፤ ያስከለከሉት ፓትርያርኩ ናቸው”፥ ብሎ ደምድሞ አስቀምጦታል፡፡ የዐውደ ርእዩ ባለቤት ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ፥ በዋናው ጸሐፊው አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ በኩል ትላንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ “መግለጫ”፥ “ለመታገዱ ፓትርያርኩ እንደሌሉበትና በመንግሥት አካላት መመሪያ መታገዱን”ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ዳንኤል ፓትርያርኩን ከሰይጣን እኩል ነበር የሳላቸው ፤ “... ፓትርያርክ ማለት በግሪክ “ታላቅ አባት” ማለት ነው፡፡ የታላቅ አባት ተግባር የልጆቹን ሥራ ማፍረስ አይደለም ፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፤ ...” በማለት፡፡ እንደከዚህ ቀደም ልማዱ ዳንኤል ሌሎች ማስጮኺያዎችንም በዚህ ጽሁፍ ለማካተት ጥሯል፡፡ አዳዲስ ስድቦችንም ለፓትርያርኩ እንደእጅ መንሻ አቅርቦላቸዋል፡፡

ቅዱስ ቃሉ ግን እንዲህ ይላል፥ “ፈራጆችን አትስደብ፥ የሕዝብህንም አለቃ አትርገመው።” (ዘጸ.22፥28) የሕዝብ አለቃ ወይም መሪ የሆነ ገዥ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ተወካይ ፤ እንደራሴም ነው፡፡ ስለዚህ ልናከብረው ፤ በመውደድም ከሁሉ በፊት ልንጸልይለት ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሳያስበው ይህን ቃል በመተላለፉ ምክንያት ወዲያው ተጸጽቶ ተመለሰ ፤ አለማስተዋሉንም ተናገረ፡፡ (ሐዋ.23፥4-5) ፍትሐ ነገሥቱም “በእነርሱ ላይ የተሾመውን ጳጳስ ... እንደትልቅ ወንድም ያክብሩት መሪና አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ሊታዘዙለት ይገባል” ይላል፡፡ (አን.4 ቁ.53) ዳኒ! ይህ የሕግ ቃል አንተን አይመለከትም ይሆን?!

የቤተ ክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በአንቀጽ.6 ስለቀሳውስት ድርሻ ባሰፈረበትና ቀሳውስት ከማዕረገ ክህነታቸው ስለሚሻሩበት ሁኔታ ሲዘረዝር “... ሕግን አውቆ የማይሠራባት ... ቄስ ይሻር፡፡” በማለት በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ ዳኒ! እንኳን መንፈሳዊውን ሥጋዊውን የዚህን አለም ምድራዊ ሕግ መጣስህን አውቀኸዋል? ማኅበሩ ፓትርያርኩ አልከለከሉኝም እያለ፥ አንተ ግን ለፓትርያርኩ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተሃል፡፡ እንደቤተ ክርስቲያን ቀኖና ከቅስናህ ትሻር ይሆን? እውነታው ግን አይመስልም፡፡

ፓትርያርኩ ቢያጠፉ እንኳ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ምን ነበር የሚለው? ጅል ፣ ሰይጣን ፣ የክፋት አነሳሽ ... እያሉ በአደባባይ ፓትርያርክን መዘርጠጥ አለበት የሚል “ቀኖና” አለን?! ለመሆኑ ስድብ ከማን ነው? የሕዝብን አለቃ አለማክበርስ? ያንን ሁሉ መጽሐፍ የጻፈው “ደራሲና ተመራማሪ” ምነው ምራቅ እንዳልዋጠ “ፍንዳታ”(የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ቃል ናት) ደርሶ ቱግ አለ?! እንዴ ይህ ነበር እንዴ በውስጡ የነበረው?!

ውድ ወንድሜ ቀሲስ ዳንኤል፦ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና አላት ፤ በየትኛውም የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ሽቅብ ፓትርያርክን እንዲህ መዘርጠጥ አይደለም ምእመንን መናገር አጸያፊ ነው፡፡ ተግሳጽ ነው ብትለኝ፥ ለመሆኑ ተግሳጽ መቼ ነው የሚመጣው? ደርሰህ ከመገሰጽህ በፊት ስንቴ ይሆን የመከርካቸው? ስንቴ ይሆን የወቀስካቸው? ስንቴ ይሆን ካሉበት ነቀፌታ እንዲርቁ በሚራራ ልብ አዝነህላቸው እንደእግዚአብሔር ቃል በጸሎት ቃል ወደጌታ የማለድክላቸው? ... ደጋፊ ስላገኙ ብቻ ብዙ ማለት፥ ከማያዳላ ኅሊና ጋር ያፋጥጣል፡፡ ወንድምን ሰባት ጊዜ ሰባ ይቅር ማለትና መቀበል እኮ ከአባት ባሻገር ወንድም ለሚሆነን ፓትርያርክንም ያካትታል ፤ ለመሆኑ ይህን ታውቀዋለህን?!

ፓትርያርኩ ቢያጠፉ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና አላት፡፡ “...የአገሩ ሁሉ ኤጲስ ቆጶሳት ስለእርሱ የሚገባውን ይመረምሩ ዘንድ እርሱንም ለማየት በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ከጳጳሳቸው (ፓትርያርካቸው) ዘንድ ይሰብሰቡ፡፡ ስለተሰጣቸው ሥልጣን በምታስፈራዪቱ ቀን መልሳቸው የጸናች ትሆን ዘንድ፡፡” (አን.4 ቁ.55) የሚል፡፡ የሚያዩት ፊቱን ብቻ አይደለም ፤ ሥራውን በማየት ያመሰግኑታል ፤ ነቀፌታም ካለ ይነቅፉታል፡፡ ዳኒ! ይህችን አላነበብካት ይሆን?! ፓትርያርኩን መውቀስና መምከር ፤ መገሰጽም ካለብህ መንገዱን አልሳትከው ይሆን? ይህን ያህል ግን ለምን ይሆን የጠላሃቸው? ዳኒ! ወንድምን ስለመጥላት ቃሉ በትክክል ይወቅስሃል፡፡

በእርግጥ ዳንኤልና ማኅበሩ መንገድ ሲተላለፉ ይህ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ግን እውነት ለመናገር ባልተጣራ ወሬ ፤ በተራ አሉባልታ ያውም ስንት ሽልማት ያግበሰበሰው ሰው ይቺን ትንሿን ነገር ከማጣራት ቸኩሎ “በሚቆረቆርላት” ቤተ ክርስቲያን መሪ ላይ የስድብ ናዳ ያወርዳል ብሎ ማን ይጠብቃል?! ከዚህ ስህተቱ ይማር ይሆን ዳንኤል? ወይስ ወደፊትም ሌላ የስድብና የመዘርጠጥ ጽሁፍ ያስነብበን ይሆን? ወይስ እንደጳውሎስ በግልጥ የይቅርታ ልብ ይዞ “የሕዝብን አለቃ” ስለተሳደበበት ስድቡ ንስሐ ይገባ ይሆን? የምናየው ይሆናል፡፡ ፈጥነህ ንስሐ ብትገባ ግን ማሰናከያን ታስወግዳለህና እስኪ ቀድመህ ወደራስህ እይ!!!

ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡