Wednesday, October 28, 2015

ሰበር ዜና፣ ፖሊስ አጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ ወንድሙን በቁጥጥር ስር አዋለ።


አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ መምህር ግርማ ወንድሙን በቁጥጥር ስር አዋለ።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምንጮች መምህር ግርማ ዛሬ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መምህር ግርማ በተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት በማስተማርና በማጥመቅ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው።

ይሁን እንጂ መምህሩ በማጥመቅ እና በማስተማር በሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሃገራት ቤተክርስቲያኒቱን ወክለው እንዳያገለግሉ እውቅና መነፈጋቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነገጋረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጠቅላይ ቤተክህነት አረጋግጧል።

የፋና ምንጮች መምህር ግርማ ከአገልግሎታቸው ጋር በተያያዘ በወንጀል ሳይጠረጠሩ እንዳልቀረ ነው የተናገሩት።

ጣቢያችን ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን እየተከታተለ ያቀርባል።


በጥላሁን ካሳ እና 

Tuesday, October 27, 2015

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!

ከአማን ነጸረ (ክፍል 3)
(6.6) እስኪ እነዚህ ምዕራባውያን ሚሽነሪዎች ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ባሕል የነበራቸው አመለካከት ከኢኦተቤክ ሊሻል ይቅርና ምን ያህል የዘቀጠ እንደነበረ በራሳቸው መነጽር እንፈትሽ፡፡ Eric Gilchist የተባለ አሜሪካዊ በነመኩሪያ ቡልቻ ‹‹የአቢሲኒያ ትርክት›› ተጽእኖ ስር ሆኖ እንኳ በሠራው የ2ኛ ዲግሪ (ማስትሬት) ማሙያ ጥናት <<....as a result of their fundamental beliefs, SIM [Sudan Interior Missonary] missionaries viewed all non-Chiristean religious practices as evil and they demanded that their converts compeletly change their life style, with no compromise to accommodate local customs....>> በማለት ሚሲዮናውያኑ ለነባሩ የኦሮሞ ባሕል የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት ካሳየን በኋላ Dough Priest የተባለውን በወለጋ ከ10 ዓመታት በላይ የሚሲዮናውያን መሪ የነበርን ትምክተኛ ሰው ጽሑፍ በመጥቀስ <<...the lives of the Galla people in general were one round after another of drunkness,adultery,thievery,lying,fighting,cheating,and worshiping false gods....today,many of the lives in our area have changed greatly....>> እያሉ (ሚሽኖቹ) ራሳቸውን ወለጋን የታደገ መሲኅ አድርገው ይመጻደቁ እንደነበር ጽፏል--ይቅርና ባሕሉን እንደ ባሕል ሊቀበሉ ( Eric Gilchist፡p.74)፡፡አናሲሞስ ነሲብም ቢሆን ሁሉንም የኦሮሞ አኗኗርና ባሕል ‹‹ቅዱስ›› ብሎ የተቀበለ አይመስልም፡፡በአንድ ደብዳቤው ላይ በስብከታቸው ስላመጡት ለውጥ ሲገልጽ ‹‹...በጋብቻ ላይ የሚፈጸም ጋብቻን እና በአካባቢው የሚታዩ ጎጂ ልማዶችን አጥብቀን ተፋልመናል፤እናም በዚህ በኩል ተሳክቶልናል፡፡ከዚህ ሌላ በኅብረተሰቡ መካከል ይዘወተር የነበረው የጥንቆላ፣የድግምት፣ለክፉ መናፍስት መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ፣ሐሰተኛ ምስክርነት፣ውሸትና ሌላም ጎጂ ልምዶች ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሱ መጥተዋል›› ብሎ ነበር (ደማቆቹ፡ገ.35)፡፡እዚህ ላይ አንድ ሀቅ ላስታውስ፡፡በሰሜን ኢትዮጵያም ቢሆን አናሲሞስ ያነሳቸው ከክርስትና ጋር የሚቃረኑ ባሕላዊ ጎጂ ልማዶችና አምልኮዎች ነበሩ፡፡ዛሬም ርዝራዣቸው አለ፡፡ችግሩ በኦሮሚያ ብቻ የነበረ/ያለ አይደለም፡፡ስለሆነም ማንም በማንም ላይ ሊመጻደቅ አይችልም፡፡
(6.7) እስልምና የኦሮሞን ባሕል በምልዓት ይቀበላል የሚል ካለም እስኪ እንፈትሽ!! ‹‹Islamic Front for Liberation of Oromia›› የሚል ሃይማኖት ጠቀስ የኦሪሚያ ነጻ አውጪ ሽምቅ ተዋጊ በሼክ አብዱል ከሪም (ሼክ ጃራ አባ ገዳ) መፈጠሩን፣በባሌ አካባቤ ‹‹የሶማሌ አቦ...›› የሚባል አፍቃሬ-ሶማሊያ የኦሮሞ ሙስሊሞች የፖለቲካ ቡድን በታሪክ መታየቱን፣ይኸው ቡድን በ1969 ዓ.ም ከዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ በእስልምና ስም ተቃቅፎ ኢትዮጵያን ያውም ሐረርጌን መውጋቱን፣ከሽግግር መንግስቱ ምስረታ ጀምሮ በተደጋጋሚ በምድረ-ኦሮሚያ እየተንቀሳቀሱ በወሐቢያና በሃዋርጃ ስም ብሔር ሳይለዩ ኦርቶዶክሳውያንና ለዘብተኛ ሙስሊሞችን እንዲሁም ፕሮቴስታንቶችን በተለይ ደግሞ የመካነ-ኢየሱስ ሉተራውያንን ያጠቁ የሙስሊም አክራሪዎችን ድርጊት እንደቀላል የእኩልነት ጥያቄ ብቻ እንድናየው እነ አባስ ሀጂ ስለመከሩን እንዳላየ እንለፈው፡፡ነገር ግን ከአክስት ልጅ ጀምሮ መጋባትን የሚፈቅደው የእስልምና ስብከት እንኳንስ ከአክስት ልጅ ጋር ከጎሳ አባል ጋርም ጋብቻን ከሚከለክለው የኦሮሞ ብሉይ ልማዳዊ ሕግ ያለው ተቃርኖ፣ኦሮሙማን በምድረ-ኦሮሚያ ለመገንባት ከሚታገለው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ጋር ‹ድንበር-ለምኔ› የሚለው ዘመናዊው እስልምና ያለው አለመጣጣም፣እንዲሁም ወደ ድሬ ሼክ ሁሴን መሄድን ወደ አባ ሙዳ እንደሚደረግ ምትክ መንፈሳዊ ጉዞ (ጂላ) የማይመለከተው የዘመኑ እስልምና (ወሀቢዝም) በነአባስ ሐጂ (Abas Haji:p.110-113) ቀደም ሲል ለስላሳ ትችት ሲደርስበት የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን እስልምና በኦሮሚያ ኤሊቶች ዙሪያ ኃይል እየተሰማው ስለመጣ ነው መሰለኝ ትንፍሽ የሚል የለም፡፡በነገራችን ላይ የልሂቁን ኦሮሞ ድምጽ የሚቃኙት በዋናነት ሙስሊም የመደብ ጀርባ ያላቸው ኦሮሞ ልሂቃን ሲሆኑ በተከታይነት የምዕራብ ኦሮሚያ ፕሮቴስታንቶች ያጅቧቸዋል፡፡ለሃይማኖት ልዩነት ልበ-ሰፊ ከነበረው ሜጫ እና ቱለማ መፍረስ በኋላ ባሉ ኦሮሞ-ተኮር አደረጃጀቶች ኦርቶዶክሳውያን ኦሮሞዎች በኅቡዕና በገሀድ ክፉኛ እንዲሸማቀቁና ከኦሮሞነት እንደወረዱ እንዲሰማቸው ሰፊ አግላይ ፕሮፖጋንዳ ተሰርቷል፤እየተሰራ ነው፡፡
(6.8) ካቶሊክስ ለምን ይቅርባት?!ትፈተሸ::የካቶሊክ ሚሽነሪዎች ገና ወደ ክርስትና ያልገባችውን ምድረ-ኦረሚያ (ፊንፊኔ) እንዴት ይመለከቷት እንደነበር አባ አንጦንዮስ ሲጽፍ ‹‹...የፊንፊኔና የአካባቢው ሕዝብ በጨለማ ውስጥ በሞት ጥላ ስር ይኖር ስለነበር የወንጌል ስርጭት በእርግጥ አስፈላጊ እንደነበር አባ ቶረን ሻኽኝ አስረድተው በአካባቢው የወንጌል ትምህርት ለማድረስ ቢያንስ አራት ወይም አምስት ተጨማሪ ሚሲዮናውያን እንደሚያስፈልጉዋቸው ኣሳስበው ነበር››ይሉናል (አባ አንጦንዮስ፡ገ.126) የአባ ቶረን ሻኽኝን የጥቅምት 14 ቀን 1868 ዓ.ም ደብዳቤ ጠቅሰው፡፡የባሪያ ንግድ፣ሴት ልጆችን ያለፈቃዳቸው መዳር፣በጋብቻ ላይ ጋብቻ የመሳሰሉ በኦሮሞና ሲዳማ ግዛቶች የሰፈኑ ልማዶች ለካቶሊካውያን ሚሽነሪዎች ፈተና ሆነው እንደነበርም አባ አንጦንዮስ በዚሁ መጽሐፍ ከገጽ 120 ጀምሮ ለስለስ ባለ የሚሲዮናውያን ቋንቋ በጊዜው የነበረውን ጎጂ ባሕል ተችተው ተርከውታል፡፡
(6.9) ከላይ የቀረቡት በኦሮሞ ባሕልና እምነት ላይ ያሉ አመለካከቶች ከራስ አስተሳሰብ/ሃይማኖት ውጭ ያለውን ባሕላዊ/ሃይማኖታዊ አመለካከት በራሱ በባሕሉ ዐይን ሳይሆን ‹‹በግል›› መለኪያ መለካት የሚያመጣውን የተዛነፈ ችግር ያንጸባርቃሉ፤ችግሩ ይብዛም ይነስም በሁሉም ወገን አለ--በሁሉም--የኢኦተቤክ ምዕመናንና የዋቄፈና አማንያንን ጨምሮ፡፡የዚህ አመለካከት አንጸባራቂ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ የሆነው Krapf የጻፈውን የኛው መሐመድ ሐሰን እንዳለ ገልብጦ በኦሮሞ ጥናት መጽሔት ቁጥር-7 ላይ በገጽ-118 ያሰፈረውን እንይ! <<...the Amhara Clergy were not sensitive to Oromo food habits in which milk, butter and meat were central>> ሲል አስቀምጦታል፡፡በKrapf ፕሮቴስታንታዊ እይታና በመሐመድ የከረረ ብሔርተኛ ምልከታ መሰረት የኢኦተቤክ የዐማራ ብቻ ናት፤የኢኦተቤክ ዶግማና ቆኖና አፈጻጸሙም ከብሔር-ብሔር እየተለያየ መተግበር አለበት!በነመሐመድ እምነት ለምሳሌ፡- የደብረብርሃን ዐማራ ኦሮቶዶክሳውያን በፍልሰታ ከሥጋና ቅቤ ሲታቀቡ የእነሱ ጎረቤት የሆኑት የልቼ እና የሸኖ ኦሮሞዎች ግን በፍልሰታ ስጋና ቅቤ የተከለከሉት በሃይማኖቱ ዶግማና ቀኖና ሳይሆን በዐማራ ቸልተኝነት ነው!!የደጀን (ጎጃም) አባይ ዳር ያሉ የቅ/ሩፋኤል ቤ/ክ አካባቢ ዐማራ ጸዋሚዎች በጾም ከስጋ ታቅበው፤በሌላ በኩል በሰ/ሸዋ ገርበ-ጉራቻ የፍልቅልቅ እና አካባቢዋ የቅ/ሩፋኤል የአባይ ዳር (የደራ?) ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ጾማቸውን ከስጋና ወተት ጋር ማከናወን ነበረባቸው!!ይሄ ያልሆነው የኢኦተቤክ ኋላቀር ስለሆነች ነው--በመሐመድና በKrapf አረዳድ!!እሺ!የኢኦተቤክ የጾም ስርዓትስ በነመሐመድ ጥልቅ የነገረ-ኦርቶዶክስ ጥናት የዐማራ ቀሳውስት ፈጠራ ነው ተብሏል!ሰው እንዴት ከግብጽ እስከ ሕንድ፣ከሶርያ እስከ አርመንያ፣ከአቴንስ እስከ ሞስኮ፣ከአስመራ እስከ አልባኒያ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በጾማቸው ወራት ጥሉላት ምግቦችን (የእንስሳት ተዋጽኦዎችን) እንደማይመገቡ ጎግልን ጎልጉሎ መረዳት ያዳግተዋል??መሐመድ ሐሰንን የሚያክል የታሪክ ባለሙያ ለጾም ያን ያህል የተደነገገ ዝርዝር ቀኖና ከሌለው የክርስትና ዘውግ (ፕሮቴስታንት) ሃይማኖታዊ ግንዱ የሚመዘዘውን (ፓስተር?) Krapf ምንጩ አድርጎ እንዴት ስለ ኢኦተቤክ የጾም ቀኖና ብይን ይሰጣል? ከሰጠስ ለምን የረመዳን አጽዋማት በኦሮሚያ ያላቸውን አቀባበል ጨምሮ መርምሮ በንጽጽር አይተነትንልንም?‹‹ሌሊት እየተመገቡ ቀን-ቀን መጾምን የሚደነግገው ረመዳን ከኦሮሞ ባሕል ጋር ያለው ተዛምዶ እንዴት ይታያል?በሙስሊምና በኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን መካከል ያለው የሃይማኖት ሕገጋት አቀባበል ከኦሮሞ ባሕል ጋር ያለው አንጻራዊ ውሕደትስ?›› ብለን ብንጠይቅስ?
7-- ክስ-ሰባት፡- የኢኦተቤክ እንደመሬት ከበርቴ (ባለ‹‹ሲሶ›› ግዛት)!!
በሁሉም የሀገራችን ጸሐፍያን የኢኦተቤክ ባለሲሶ ይዞታ የነበረች መሆኗ በስፋት ተጽፏል--በራሷ መጻሕፍት ሳይቀር፡፡እነ መኩሪያ ቡልቻም ይህንኑ ደጋግመው ጽፈውታል፡፡አባስ ሐጂም የቡልቻን ጽሑፍ ጠቅሶ <<...the clergy were given land that was confiscated from the Oromo peasants and become landlords, they owned Oromo peasants as Gabbars (serfs) and thrived upto their labour...>> በማለት ብሶቱን ያቀርባል (Mekuria cited in Abas Haji:p.104)፡፡ጥሩ፡፡እዚህ ላይ አንድ እውነት አለ::በኦሮሞም ሆነ በተቀሩት ብሔር-ብሔረሰቦች (ዐማሮችንና ትግራውያንን ጨምሮ) ‹የሰሞን መሬት› የሚባል የቤ/ክ ይዞታ አይነት ነበር፡፡ነገር ግን የዚህ መሬት ይዞታ ለስሙ የኢኦተቤክ ይባል እንጂ ባለቤቶቹ ተመልሰው መኳንንቱና መሳፍንቱ ነበሩ፤ያዙበታል፤ምርቱን ይቆጣጠራሉ፤እንዲሁም ሲሞቱ ለልጆቻቸው ያወርሱታል--መሳፍንቱ፡፡የካሕናቱ እጣ-ፈንታ በመሳፍንቱ ስር ቅጥረኛ ሆኖ በድርጎ (የእለት ምግብ) ብቻ ማገልገል ነው፡፡በሌላ አነጋገር ካሕናቱ የበላይነታቸው በመንፈሳዊ ጉዳዮች እንጂ በቤ/ክ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የማዘዝ መብት አልነበራቸውም፡፡ስለሆነም መሳፍንቱ በካሕናት ስም በተቆጣጠሩት ይዞታ መልሰው ካሕናቱን በእለት ምግብ ብቻ እየደለሉ በማስገልገል የተረፈውን ምርት ለግላቸው ይጠቀሙበታል፡፡ይሕ የባላባትና የደሃ ካሕናት ሥርዓታዊ የብዝበዛ ግንኙነት በተለምዶ ‹‹የቶፋ ሥርዓት›› ይባላል፡፡እንዲሕ ስር ሰድዶ የኖረው ሥርዓት ብዙም አይተረክም፡፡በቤተክሕነት ወገኖች የቀደሙ ነገሥታትንና ባላባቶችን አንዳንድ የማይካዱ ውለታዎች እንደማሳነስ ስለሚቆጠር ይመስለኛል የማይተረከው፡፡በዓለማዊ ጸሐፍት ደግሞ አንድም አሰራሩን በቅርብ ካለማወቅና ከቸልተኝነት፣ሁለትም ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ተራማጆቻችን (ተራ-ማጆች!) የኢኦተቤክ’ንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጅምላ ፈርጆ ማሳቀል ቀላል ስራ ስለሆነላቸው ይመስለኛል፡፡እንጂማ የኛ ወላጆች (ወላጅ አባቴ ካሕን ነበር!) በልመና እንጀራ ተማሩ፤ከእጅ ወደ አፍ እንኳ ሊባል በማይችል የሰቆቃ ኑሮ እድሜያቸውን ገፉ፤የረባ ጥሪት ለልጆቻቸው ሳያኖሩ ድኅነትን አውርሰውን ያለእድሜያቸው ተንከራተው አለፉ፡፡ሞቱ፡፡‹‹ሕያዋን ለነገሥታት፤ሙታን ለካሕናት ይገብራሉ›› በሚለው ብሂል በሙታን ተዝካርና የሙት አልባሳት ሲደጎሙ ኖረው ሞቱ፡፡በዋናነት 5ቱ ቀዳስያንና በዙፋኑ ዙሪያ ያሉ ‹‹ካሕናተ-ደብተራ›› ብቻ ነበሩ የንጉሡና የምዕመኑ እርጥባን ተቋዳሾች፡፡የተቀረው ለማኝ ነው፡፡በካሕናቷ ‹ምንዳቤ ወረኀብ› የኢኦተቤክ ‹የልመና ሃይማኖት› ተብላ ትጠራ ነበር፤አሁንም ይሕ ስያሜ በከፊል አለ፡፡ይሄ ይታወቃል፡፡ታሪክ ሲጻፍ ግን ‹‹ባለሲሶ ግዛት›› ይባልልናል!!ግና እንዲያ እንዳልሆነ ይታወቅ ነበር፡፡ስለመታወቁ ማስረጃ እንቁጠር...

Saturday, October 10, 2015

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!


 ከበአማን ነጸረ (ክፍል ሁለት)


5-- ክስ-አምስት፡- በኦርቶዶክስ እልህ ወለጋ ጰነጠጠ፤ወሎ-አርሲ-ጅማ-ሐረር ሰለሙ!!
መኩሪያ ቡልቻ ‹‹...In Wollo in the North, in Arsi in Bale and Hararghe in the South and Sout-East, and in Jimma in the South-West Islam was adopted to avoid the often forced mass conversion by the clergy of the Abyssinian Orthodox Church.In Wallaga, in the West many Oromos including most of the traditional elites became protestants>>ይለናል (Being and Becoming Oromo:p.55)፡፡እስኪ ይቺን የመኩሪያ ጽሑፍ ገላልጠን እንያት--አንድ በአንድ!!
(5.1) ወሎ እነ መኩሪያ ቡልቻ ‹‹አቢሲኒያ›› ብለው ከሚጠሩት ግዛት ራሱን ገንጥሎ የኖረ ሳይሆን በግዛቱ ውስጥ ተዋናይ ነበር፡፡‹‹ወሎ በእልህ እስልምናን ተቀበለ›› የሚል ታሪክ ምናልባት ከካቶሊካዊው አቶ አጽሜ አግኝተው እነ መኩሪያ ቡልቻ ‹የአዋቂ አጥፊ› እንሁን ካላሉ በቀር ታሪኩ በራሳቸው በሙስሊም አማንያንና በውጭ ሀገር ጸሐፊዎች ተተርኳል--ወደ ወሎ እስልምና የገባበት ጊዜ፡፡ለማሳያ ያሕል ታቦር ዋሚ ሙስሊም ጸሐፍትንና ፖርቱጋላዊው አልፋሬዝ በ1520ዎቹ ስለሙስሊምና ክርስቲያን ወለየዎች ተፋቅሮ የከተበውን ማስታወሻ ዋቢ አድርጎ የግራኝ አህመድ ጦር በአካባቢው ከመድረሱ በፊት ወሎዬ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንደነበሩና ሕዝቡ [የወሎ] በሃይማኖት ሳይለያይ በሰላም አብሮ ይኖር እንደነበር አትቷል (ታቦር ዋሚ፡ገ.306)፡፡ከዚህ አንጻር ‹ወሎ በኦርቶዶክስ እልህ ሰለመ› ብሎ መጻፍ የኦርቶዶክስን ብቻ ሳይሆን የእስልምናንም ሆነ የወሎን ሕዝብ ታሪክ ያገናዘበ አይመስለም፡፡
(5.2) የአርሲን እስልምና በሚመለከት በአካባቢው ታሪክ ላይ ወረቀቶች የሠራው አባስ ሐጂ ሲገልጽ <<....among the Arsi and the Oromos of Harar where there was an old Islamic presence, Christianity failed to get foot hold>>በማለት (Abas Haji: p.107) አካባቢው የሰለመው ቀደም ብሎ ማለትም ከክርስቲያኑ ኃይል ማንሰራራት በፊት መሆኑን ያመለክታል፡፡አቶ አጽሜ ‹‹ኦሮሞ ዐማራን ስለጠላ ሰለመ›› እያሉ በካቶሊካዊ ሚሽነሪ ወገንተኛነት የጻፉትን አባስ ሐጂ ሲተችም <<This [Atsme’s] explanation is however, not adequate because Islam entered the region long before Imperial conquest...>> እያለ በአርሲ ነዋሪ ነባሪ የእስልምና እርሾ መኖሩን ይነግረናል፡፡የአባስ ትችት ለሀቅ ሳይሆን ለእስልምና ከመቆርቆር ነው ብዬ ለመጠርጠር እገደዳለሁ፤ቢሆንም ለእውነታው ከመኩሪያ እና ከአቶ አጽሜ ጽሑፍ የእሱ ይቀርባልና ተጠቀምኩት!
(5.3) የሐረር እና ጅማ ኦሮሞዎችን ቀደም ብሎ መስለምና የሸዋን ኦሮሞ ኦርቶዶክሳዊነት በሚመለከት ዶናልድ ሌቪን ሲገልጹ ‹‹ሐረር የፖለቲካ ማዕከል መሆኗ ቀርቶ የእስልምና ባህል ማስፋፊያና መስበኪያ ስለሆነች ፣ኦሮሞዎች ለሐረር ቅርብ በመሆናቸው እንዲሁም ደግሞ ምናልባት የሱማሌዎችንና የአፋሮችን ምሳሌ በመከተል ተነሳስተው አብዛኞቹ ኦሮሞዎች የእስልምና ተከታይ ሆነዋል፡፡......በላይኛው ጊቤ የሠፈሩት የኦሮሞ ጎሣዎች....በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የራሳቸውን ነገሥታት አቋቁሙ፡፡የአቋቋሙት የዘውድ ሥርዓት የእስልምና ሃይማኖትን ተቀብሏል፡፡በአጭሩ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ከምኒልክ ድሎች በፊት፡፡...በሣሕለሥላሴ ዘመን (1813-1847 ዓ.ም)...አብዛኛው የሸዋ ኦሮሞ ክርስቲያን ሆነና በዐማራና ኦሮሞ መካከል የሚፈጸመው ጋብቻ የዘወትር ክስተት ሆነ፡፡››(ሌቪን፡ገ.73-75)፡፡የኢናርያውን ንጉሥ የአባ ባጊቦን አስቀድሞ መስለም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ጸሐፊው አባ አንጦንዮስም ገልጧል (አባ አንጦንዮስ፡ገ.83)፡፡
(5.4) ዶ/ር ላጵሶ ጌ.ድሌቦ በ‹‹የኢትዮጵያ ረጅም ሕዝብና ታሪክ፣አንደኛ መጽሐፍ›› ሁኔታውን ሲገልጹ ‹‹...በ1840 እና 1870 መካከል ከሸዋና ከሰሜን ኢትዮጵያ እስላማዊ የወርጅ-ጀበርቲ ነጋዴዎች በአምስቱ የጊቤ ማለትም የጉንጋ ኦሮሞ መንግሥታት ከንግድ ጋር እስልምና አስፋፉ፡፡›› በማለት የጊቤ መንግሥታትን ወደ እስልምና መግባት ከሙስሊም ሲራራ ነጋዴዎች ስብከት ጋር አያይዘውታል፡፡ትረካቸውን ሲቀጥሉም ‹‹....በተጨማሪም በደቡብ ምስራቅ ጥንት የባሊ የአዳልና የሀዲያ እስላም አገሮች የሰፈሩ የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ከገዳ ሥርዓት ወጥተው በአጭር ጊዜ ውስጥ እስላሞች ሆኑ፡፡›› በማለት የእስልምናን መስፋፋት እንደ መኩሪያ እና አቶ አጽሜ አበባል ‹‹ከዐማራ ቄሶች እልህ ጋር›› ሳይሆን ከንግድ መነቃቃት ጋር አያይዘው ተአማኒ በሆነ መንገድ አቅርበውታል (ዶ/ር ላጵሶ ጌ.ድሌቦ፡ገ.252)፡፡የዶ/ር ላጵሶን አተራረክ ተአማኒ የሚያደርገው በአጠቃላይ በ19ኛው ክፍለዘመን እስልምና በንግድና በግብጻውያን መሪዎች የተጠናከረ ኢስላማዊ ስብከት በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኤርትራ ቆላማ አካባቢ የነበሩ የትግረ፣የቢለን፣የማሪያ (የሀባብ፣የመነሳ፣የሳሆ) ጥንተ-ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ወደ እስልምና መግባታቸው ነው (ዝኒ ከማሁ፡ገ፣258)፡፡የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (M.A) ከዚህ የዶ/ር ላጵሶ ትረካ ጋር በሚመሳል መልኩ የኤርትራ ቆላማ አካባቢ ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ‹‹መሐመድ አሚን እልሚርጋኒ›› በተባለ ከግብጹ ገዥ ‹‹አህመድ ኢብን ኢድሪስ›› የተላከ ሙስሊም ሰባኪ ተሰብከው ስለመስለማቸው ጆን ስፔንሰርን ዋቢ አድርገው ጽፈዋል (አቡነ ጎርጎርዮስ፡ገ.69-71)፡፡ስለሆነም ይሕን በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በውጫዊ ኃይል ተልእኮና በውስጣዊ የሲራራ ነጋዴ ሙስሊም ሰባክያን የተገኘ የእስልምና መነቃቃት በኢኢተቤክ እልህ ብቻ ያውም በኦሮሚያ ብቻ እንደታየ እንግድ እንቅስቃሴ አድርጎ መተረክ አድማስን ማጥበብ ይመስለኛል፡፡
(5.5) የወለጋን በፕሮቴስታንት ተጽእኖ ስር መውደቅ በሚመለከት ድርጊቱ የተከናወነው በኦርቶዶክስ ጥላቻ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡የቀ.ኃ.ሥ መንግሥት ከጣሊያን መውጣት በኋላ በነበረበት የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ ሚሲዮናውያን ወደ ሀገሪቱ ገብተው ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ፈቀዱ፡፡በዚህ አጋጣሚ የኦርቶዶክስና የእስልምና ተጽእኖ ወዳልበረታበት ወለጋ ሄዶ በመስበክ የአውሮፓ ሚሽነሪዎች (ኋላ ግንባር ፈጥረው መካነ ኢየሱስን የመሰረቱት) እና የአሜሪካ ሚሽነሪዎች (ኋላ ቃለሕይወትን ያቋቋሙት) እድሉን ተጠቀሙበት፡፡ሚሽኖቹ ተደብቀው ሳይሆን በሕግ ማስታወቂያ ቁጥር 3/1937(?) (decree No.3/1944) በአካባቢው በይፋ እንዲሰብኩ ንጉሡ ፈቅደው ነው የተሰማሩት፡፡ወለጋ ፕሮቴስታንት እንዳይሆን ኃይለሥላሴ አልተከላከሉም፤ይልቅስ ፈቅደዋል ቢባል ይሻላል፡፡ይሕን ደግሞ <<...CMF [Chiristean Missionary Fellowship] ....choose Ethiopia because of Haile Selassie’s friendly policy towards Missionary groups.>> በማለት (Eric Gilchist:p.63) ያብራራልናል፡፡በአጠቃላይ የወለጋ በፕሮቴስታንት ተጽእኖ ስር መውደቅ መኩሪያ ቡልቻ እንደሚለው በኦርቶዶክስ የግዳጅ ክርስትና ሽሽት ሳይሆን ለወትሮውም በአካባቢው ስር የሰደደ የእስልምና እና የክርስትና ዘውጎች ተጽእኖ ስላልነበረ፣ስለ ኦርቶዶክስ ስላልተሰበከ፣በአንጻሩ የሃይማኖት ስብከታቸውን ከማኅበራዊ አገልግሎት (ትምህርትና ጤና) ጋር አቀናጅተው የሚሰሩ ፕሮቴስታንት ሚሽነሪዎች በመንግሥት እውቅና እና ፈቃድ በአካባቢው እንዲንቀሳቀሱ ከ1930ዎቹ ጀምሮ በሕግ ስለተፈቀደ ነዋሪው በብዛት ፕሮቴስታንት ሆነ ቢባል የተሻለ ይሆናል፡፡እንደሚታወቀው ከጣሊያን መውጣት በኋላ ለሚሽኖች በወጣው ሕግ ወለጋ እና ደቡብ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት አካባቢዎች open area ተብለው ለሚሽኖች ሲፈቀዱላቸው ማዕከላዊና ሰሜን ኢትዮጵያ ግን closed area ተብሎ ሚሽኖች ወደዚያ ሄደው ለመስበክ ፈቃድ አልነበራቸውም፡፡የሚያሳዝነው mis-ነሪዎቹ ስላላዩትና ስላልሰበኩበት የሰሜን ሕዝብ (በእነሱ አጠራር ‹‹አቢሲኒያ››) እና ስለሚከተለው እምነት በነሲብ (በጨበጣ) እየጻፉ በእንግሊዝኛ የተጻፈን ሁሉ እንደወረደ ለመቀበል የሚያሰፈስፈውን ሐገራዊ ምሑር ስተው ያሳስቱታል፡፡‹እግዜር ይይላቸው› ከማለት በቀር ምን ይባላል!!
6-- ክስ-ስድስት፡- ኦርቶዶክስ የኦሮሞ ባሕል ጸር!!
‹‹ኦሮሙማ›› የሚለውን ቃል ከእምነት (belief)፣ከዘውግ (ethinicity) እና ከማንነት (identity) ጋራ አስተሳስሮ የሚሰብከው ባህል-ተኮሩ ገመቹ መገርሳ <<An Oromo person does not become a member of a beiliving community through a formal rite of incorporation such as baptism.An Oromo is born with Orommuma>> ካለ በኋላ የተለመደውን ‹‹አቢሲኒያ››ን እና ኦርቶዶክስን ሆን ብሎ አመሳስሎ የመጥራት ዘዴ ተጠቅሞ ሲተርክ <<…Borrowing their faith from the Judo-Chiristian tradition, Abyssinians came to revere a white God and reduced the Oromo belifs in Waqqa Guraacha to a form of Devil Worship>>ይለናል (Bieng and Becoming Oromo:p.97)፡፡ንባቡ አጭር ቢሆንም ስንሰነጣጥቀው ትርጉሙ ይበዛል፡፡እናብዛው!!
(6.1) ይቺ ትረካ በራሷ ‹‹አቢሲኒያ›› በሚል በሚገለጸው አካባቢ በውስጡ ከኦርቶዶክ የተለዩ ባሕላዊ እምነቶችና እስልምና መኖራቸውን ትዘነጋለች፡፡አዎ!ይቺ ተደጋግማ የምትነገር ‹‹የአቢሲኒያ ቤ/ክ›› የምትል ቃል ተግሳጽ ያሻታል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ራሷን ‹‹የአቢሲኒያ ቤ/ክ›› ብላ ጠርታ አታውቅም፡፡አማንያኗም እንዲያ አይሏትም፡፡እንኳንስ እሷ የሺህ ዘመናት ታሪክ የምትቆጥረው የቅርቦቹ መካነ ኢየሱስ እና ወንጌላውያንም ራሳቸውን ሲጠሩ ‹‹የኢትዮጵያ›› የሚል ቅጽል አስቀድመው ነው፡፡ስለዚህ የኢኦተቤክ ራሷን በማትጠራበት ‹‹አቢሲኒያዊት›› የሚል ስያሜ መጥራት ‹‹ነገር ፍለጋ›› እንጂ ሌላ ስም የለውም፡፡ቤተክርስቲያኒቱን ራሷን በምትጠራበት ሳይሆን ፈረንጅ አኮላትፎ እና አጣሞ በሚጠራት ስያሜ ነው የምንጠራት ማለት የቅንነት አይመስልም፡፡ያስተዛዝባል፡፡
(6.2) በዚህ በነገመቹ መገርሳ እና የሚሽነሪ ማጠቀሻዎቻቸው ለዐማራ-ትግራይ ብቻ በመጠሪያነት በተሰጠው ስመ - ‹‹አቢሲኒያ›› ከሄድን እንደ አገው፣ቅማንት፣ነገደ-ወይጦ፣ኢሮብ፣የወሎና የትግራይ (ራያ-አዘቦ-አሸንጌ) ክርስቲያን ጥንተ-ኦሮሞዎች በትረካው ምክንያት ታሪካቸው ይጨፈለቃል፡፡ከኦሮሚያ ሕዝብ 30.5% የሚሆነው ነዋሪ የሚከተለውን ሃይማኖት እንደዋዛ በባሕላዊ ማንነት ሽፋን ምሑራዊ ቅሰጣ ተጠቅሞ ጥምቀተ-ክርስትናውን ሕሳዌ (የውሸት) ማስመሰልም ደስ አይልም፡፡ምሑራዊ አምባገነንት ይመስላል፡፡ከማንነትም አንጻር ዐማራ እና ትግራይ ራሳቸውን በዜግነታቸው (በብሔር አላልኩም) የሚገልጹት ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ብለው እንጅ ‹‹አቢሲኒያ›› ብለው አይደለም፡፡‹‹ኦሮሞ ራሱን በሚጠራበት ስም ነው ሌሎችም ሊጠሩት የሚገባ›› ተብሎ ሁላችንም ከልባችን አምነን ተቀብለን ከተስማማን በኋላ ዐማራና ትግራይ ዐረቦችና ሚሺነሪዎች ባወጡላቸው ስም ‹‹አቢሲኒያ›› ተብለው መጠራት አለባቸው ብሎ የሌላውን ማንነት በይኖ መከራከርና የሃይማኖት ተቋሙንም በዚያ መንገድ ሰይሞ ለማክፋፋት መሞከር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ቅር ያሰኛል፡፡አንድ ሰው/ተቋም ራሱን በይፋ የሚጠራበትን የመዝገብ ስም ለውጦ በዚህ እነ እከሌ ባወጡልህ ነው የምጠራህ ማለት ለመደማመጥና ስንጠራራ ለመሰማማትም ያውካል፡፡ራሴን በማልጠራበት ቢጠሩኝ ‹‹አቤት›› አልልም፡፡በአምልኮ ደረጃም ‹‹እ/ሔር ሰውን በአምሳሉና በአርአያው ፈጠረ›› እንላለን እንጅ ‹‹ነጩን በአምሳሉ አንጽቶ፤ጥቁሩን በጥላው አጥቁሮ ፈጠረው›› አንልም፡፡‹‹ሁሉም ሰው በአምሳለ-ፈጣሪ ተፈጥሯል›› ተብሎ ነው በይሁዲውም ሆነ በክርስትናው የሚሰበከው፡፡ከዚህ ውጭ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ‹‹እ/ሔር ጥቁር ነው፤ነጭ ነው›› ብላ ለፈጣሪዋ ቅርጽና ቀለም የማውጣት ትውፊት የላትም፡፡እንዲያውም አብዛኞቹ በየአብያተ-ክርስቲያናቱ ያሉ ጥንታውያን ቅዱሳት ስእላት በቆዳቸው ነጭ ናቸው ተብለው የሚታመኑትን እመቤታችንን፣ጌታን፣ሐዋርያትንና ሰማእታትን ጠይም አድርገው በማቅረብ ትውፊታቸው የሚታወቁት፡፡የሐዲስ ኪዳን መርህኣችን ይኽ ነው፡- ‹‹አይሁዳዊ፡ወይም፡የግሪክ፡ሰው፡የለም፥ባሪያ፡ወይም፡ጨዋ፡ሰው፡የለም፥ወንድም፡ሴትም፡የለም፤ዅላችኹ፡በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡አንድ፡ሰው፡ናችኹና››(ገላትያ ምዕራፍ 3 ቁጥር 28)፡፡
(6.3) ገመቹ መገርሳ ግን እንኳንስ ይሕን ሀቅ ወደመሬት ወርዶ ሊጽፍልን የሁሉም ክርስቲያኖች ሆነ ይሑዲዎች ወይም የሙስሊሞች የሃይማኖት መርህ ሐጋጊዎች (ደንጋጊዎች) የመካከለኛው ምስራቅ የፈካ ገጽታ ያላቸው (ነጮች?) ነቢያት/ሐዋርያት መሆናቸውን ሳያስተውል ክርስትናን እና ይሁዲን ከእስልምና ነጥሎ ስለ ‹ዋቃ ጉራቻ› ክብር ሲል ይሰዋቸዋል፡፡አናሲሞስ ወደ ኦሮሚፋ የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ከይሑዲ-ክርስቲያን ባሕል ውጭ ይመስል ጃሌ ገመቹ አቃቂር ይነቃቅሳል፡፡ምስጢሩ ዞሮ-ዞሮ የፈረደባትን ኦርቶዶክስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነጥሎ ማነወር ነው!የዋቃ ጉራቻን የጠየመ ምስል ለማጉላት ክርስቶስን (ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና) እና አምላኪዎቹን ማሳነስ ነው!!ለነገሩማ ጥቁሩ አምላክ(Waqqa Guraacha) በጥቁረቱ ከተወደሰ፣ነጩ አምላከ-ሙሴ (እ/ሔር ወይም ኢየሱስ) በንጣቱ ከተወቀሰ ዘረኝነቱ አልሸሹም ዞር አሉ ነው፡፡ማን ነው የጥቁርን ዘረኝነት ቅድስና የሰጠው?!Is it not counter-racism? Is racism of black people against white brothers justifiable?
(6.4) የኦርቶዶክሳዊነት-እና-ኦሮሞነት ውኅደት በተግባር ይታይ ከተባለ የኢኦተቤክ በኦሮሞ ባሕላዊ ጭፈራዎች ታጅባ የታቦት ንግሦችንና ጥምቀትን ማክበሯን ጃንሜዳ፣ፉሪ ሃና፣የካ ሚካኤል እንዲሁም በአጠቃላይ ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ባሉባቸው አድባራት ሄዶ መታዘብ ይቻላል፡፡በተለይ በሸዋ ኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን በማበረታታት፣በኦሮሚፋ መዝሙራት ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ብቻ በመጠቀም፣ጨፌ በየገዳማትና አድባራቱ በመጎዝጎዝ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእሬቻን ጤናማ ትርጉም በማጤንና በማጉላት ኦርቶዶክሳውያን የኦሮሞ ካሕናትም በአከባበሩ ተገኝተው በማክበር፣በኦሮሚያ በሚገኙ አብያተ-ክርስቲያናት (ደ/ሊባኖስ፣ቁልቢ፣ዝቋላ፣ወንጪ ቂርቆስ፣ደብረ-ፅጌ፣ዝዋይ ገዳማት፣ወዘተ…) መንፈሳዊ ጉዞዎችን በማካሄድ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ሲደረግ ኖሯል፤አሁንም የበለጠ ለማዳበር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡እነዚህ ድርጊቶች እንዴትም ቢተረጎሙ በኦሮሙማ ላይ አሉታዊ ጎን አላቸው ማለት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ኦሮሙማ እና ኦርቶዶክስ እንዳይጋጩ አድርጎ ማስቀጠል እንደሚቻል ኦርቶዶክሳውያን የቱለማ ኦሮሞዎች በበረከቱበት የሸዋ ምድር በድምቀት የሚከበሩት 2ቱ የፀደይና የበልግ እሬቻዎች ምስክሮች ናቸው፡፡
(6.5) ኦሮሙማን በማስተናገድ አቅሙ ኦርቶዶክስ በጥንታዊው የኦሮሞ እምነት ዋቄፋና እና በእምነቱ መሪ በአባ ሙዳ ዐይን ይገምገም ከተባለም ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ስለ እሬቻ፣ቃሉ፣ቃሊቻ፣ጂላ፣ጨሌ፣ቦረንትቻ፣ዋቃ ጉራቻ፣ሀማቺሳ፣ወዘተ ያላቸው አተያይ፣እንዲሁም ለኦሮሞ አለባበስ፣ባሕል፣ሙዚቃ፣ሥነ-ልቦና ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች በዝርዝር ተገምግመው ደረጃ ቢሰጠን ሸጋ ነው፡፡አሁን እየተደረገ ያለው በሕግ ተፈቅዶላቸው በኦሮሚያና በደቡባዊ ሀገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሚሽነሪዎች ሀገሪቱን በፈለግነው መጠን ፕሮቴስታንትና ካቶሊክ እንዳናደርጋት ተከላክላናለች የሚሏትን የኢኦተቤክ እያነወሩ የጻፉትን እንደወረደ እየገለበጡ በዋቄፋና ከለላነት ተጠልሎ ምሑራዊ ጥላቻ መዝራት ነው፡፡በውጤቱም ኦርቶዶክሳውያን ኦሮሞዎችን ሆድ እያስባሱ ወደ ፕሮቴስታንቲዝም ከማስኮብለል በቀር በኦሮሚያ የዋቄፋና ተከታዮች ቁጥር 4% እንኳ ሲደርስ አላየንም!

To be continued.......