Saturday, December 13, 2014

በማኅበረ ቅዱሳን ተቃውሞ ባቀረቡ ካህናት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የተደረገው ተጋድሎ ከሸፈ!

   ( 4/4/ 2007 )
 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቅት ወርን መባቻ ተከትሎ የአጠቃላይ ሰበካ ጉባዔ ዓመታዊ ስብሰባና የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚደረግ ይታወቃል። በዚህ ዓመት የተለየ የሚያደርገው ከሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የስብሰባ አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተደረገ የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ልዩ ልዩ ኃላፊዎች በተጠራ ጉባዔ ላይ የተካሄደው ውይይት ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ አልፏል። በወቅቱ ከተደረገው ውይይትና ከተሰብሳቢዎቹ ድምጽ ለማወቅ እንደተቻለው በአጭር ቃል «ማኅበረ ቅዱሳን» ስለተባለው ማኅበር እንቅስቃሴ ላይ ያጠነጠነ ውይይት መሆኑ የተለየ አድርጎታል።

  ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ድርጅት እንቅስቃሴ፤ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያለው የሥራ ድርሻ፤ የአባላት ምልመላ፤ የገንዘብ አሰባሰብና ውጪን ስለማሳወቅ፤ ሊኖረው ሲለሚገባው ገደብና ሌሎች  አሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው እንደነበር ይታወሳል። በማኅበሩ ዙሪያ በተነሱት የማኅበረ ካህናቱና የፓትርያርኩ ውይይት ደስተኛ አለመሆን ከማኅበሩ ዘንድ የሚጠበቅ ቢሆንም በአስገራሚነቱ የተመዘገበው ተቃውሞ የተነሳው ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራሉ ተብለው በከፍተኛ ስልጣን ላይ በተቀመጡት በዋና ሥራ አስኪያጁና ከዋና ፀሐፊው በኩል መሆኑ ነው። የማኅበሩ አባል የመሆን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማኅበሩን በተመለከተ ፓትርያርኩ ማኅበረ ካህናቱን የማወያየት አቅምና ሥልጣን የሌላቸው በማስመሰል መቃወም ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ማኅበሩ ምን እየሰራ ነው? እንቅስቃሴው ምን ይመስላል? ቤተ ክርስቲያን የምትቆጣጠረው እንዴት ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች የማኅበረ ካህናቱን ድምጽ የመስማትና የማወያየት አቅም ፓትርያርኩ የላቸውም ከተባለ ዋና ሥራ አስኪያጁ ስለማኅበሩ የመጮህ ሥልጣንን ከየት አገኙ? የሚል አንጻራዊ ጥያቄን ማስነሳቱ የግድ ነው ።

  ሌላው ስለማኅበሩ የጦፈ ክርክር ተደርጎ የነበረው ከአዲስ አበባው ሀ/ስብከት ጉባዔ በኋላ በተፈጸመው የሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ ላይ በድጋሜ መነሳቱ ነበር። በዚህ ጉባዔ ላይ ስለማኅበረ ቅዱሳን ያልተነገረና የቀረ አንዳች ነገር አልነበረም። የተናገሩትን ሰዎች ማንነት ለጊዜው ወደጎን ትተን በተነገረው ጉዳይ ላይ ስናተኩር ከተነገረው እውነት የቀረ ነገር ካልሆነ በስተቀር የተጨመረ አዲስ ነገር ምንም አልነበረም ማለት ይቻላል። ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ጣልቃ ይገባል? ያልተፈቀደ ጉባዔ ይጠራል? የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባልነት ይመለምላል? ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቀውን ገቢ ይሰበስባል?  የቤተ ክርስቲያኒቱን የኦዲት ምርመራ አልቀበልም ይላል?  ለሁሉም አንድ መልስ «አዎን» ነው። በነዚህ አንኳር ነጥቦች ላይ የካህናቱና የፓትርያርኩ መነጋገር የሚያንገበግበው ቢኖር ማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለማኅበሩ ጥብቅና የሚቆሙ ወገኖች ብቻ ናቸው። ካልሆነ ስለማኅበረ ቅዱሳን ተግባር መነጋገር ለምን ያናድዳቸዋል?

   ማኅበሩ የተሳሳተውን መንገድ አውቆ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብና የማኅበሩ ቅን አባላት ለተሻለ መንፈሳዊ ተግባር ትኩረት እንዲሰጡ የሚያስችል ውይይት ማድረግ ተገቢና ተቀባይነት ያለው መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስለንም። ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። በጠራ ቃል «ማኅበሩን ይፈረስ ያለ ማንም የለም» ብለዋል። ከዚህ ውጪ እነዚህ ቡድኖች ምን እንዲሆን  ይፈልጋሉ? በዚህ ዙሪያ የሚታመም ሊቀ ጳጳስ ወይም ተመሳሳይ ሰው ቢኖር ራሱን መመርመር ያለበት ራሱን ነው። ህመሙ የጤንነት ምልክት አይደለም። ዘረኝነት፤ ጥቅምና ጭፍን ደጋፊነት ብቻውን ማንነትን ከሚያጋልጥ በስተቀር የትም አያደርስም። ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አባ ማቴዎስ ለቅዱስ ፓትርያርኩ የተናገሩት « ማኅበረ ቅዱሳንን ከነኩ እርስዎም እንደአባ ጳውሎስ ይሞታሉ» ማለታቸውን ሰምተን ጤንነታቸውን ተጠራጥረን ነበር። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር እንዴት አብረው ሊሰሩ እንደሚችሉ ስናስብ እጅግ ያስገርመናል። ዓይን ያወጣ ጥላቻና አንድን ቡድን መደገፍ አሳዛኝም አስገራሚም ነው። በዚህ ዓይነት ጉዞ ቤተ ክርስቲያን ወዴት እየሄደች እንዳለ ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለራስ ክብርና ለማኅበር መቆም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ውድቀት እየገፏት መሆኑን ለማወቅ ምርምር አይጠይቅም። ባለፉት 23 ዓመታትም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት መካከል ከ16 ሚሊየን በላይ ልጆቿ ወጥተው የቀሩትም በዚህ ዓይነት ቡድናዊ አስተዳደርና ደካማ አስተምህሮ የተነሳ ነው።

 የሰበካ አጠቃላይ ጉባዔ እንደተፈጸመ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ቀጥሎ ነበር። በዚህ የሲኖዶስ ጉባዔ ላይም በግንባር ቀደምትነት የተነሳው ጉዳይ ቢኖር ማኅበሩ ለምን ተነክቶ? የሚሉ የጳጳሳት ቡድን በአንድ በኩል፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ብቻቸውን በሌላ በኩል ሆነው የጦፈና የከረረ ውይይት ማድረጋቸውን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ሰምተን ነበር።  ማኅበሩን የሚያወግዙና የሚወቅሱ የማኅበረ ካህናት አባላት እኛንም ከማኅበሩ ጋር ቀላቅለው ስለዘለፉን ቀኖና እንዲሰጣቸውና እንዲቀጡ ይደረግ የሚሉ አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ጳጳሳት የጉባዔውን አቅጣጫ ለማሳት ሙከራ አድርገው ነበር። ፓትርያርኩ ምንም እንኳን ለጉዳዩ መልስ በመስጠት ዝም ለማሰኘት ሞክረው የነበረ ቢሆንም «ወደ ገዳማችን እንሄድልዎታለን፤ ሲኖዶሱን ሊያከብሩ ይገባል፣ እርስዎ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው፤ ሲሉ የነበር  ዛሬ እርስዎ ለምን ይሽሩታል?» ወዘተ መከራከሪያ ነጥብ ለማንሳት ተሞክሮም ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው የሲኖዶስ ውሳኔ ስለተሻረ ሳይሆን በሲኖዶሱ ሉዓላዊ ስልጣን ከለላ በማኅበረ ካህናቱ ዘለፋና ውግዘት የደረሰበትን ማኅበር ለመካስ ሲባል በማኅበሩ ላይ የተናገሩት ካህናት ሁሉ እንዲቀጡና ቀኖና እንዲሰጣቸው ለማስቻል ነበር።

  ማኅበሩን አጋልጠው ለአጋላጭ ሰጥተዋል የተባሉት በዋናነት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፤ ሊቀትጉኃን ዘካርያስ ሐዲስ፤ መልዓከ መንክራት ኃይሌ አብርሃ፤ ዲያቆን አበበ፤ ዲያቆን ዘመንፈስ አብርሃ፤ አባ ነዓኩቶ ለአብ የመሳሰሉት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና ቀኖና እንዲሰጣቸው እንዲሁም ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በተለይ ከፓትርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት እንዲባረሩ ይደረግ የሚል ውሳኔ ለማሳለፍ ተሞክሮ ነበር። በተካፈሉበት ጉባዔ ላይ ሁሉም አሳብ ሰጪዎች የተናገሩት በማኅበሩ ዙሪያ ብቻ ሆኖ ሳለ ከእስከዛሬው በተለየ ሁኔታ በእነዚህ ካህናት ላይ የበቀል እርምጃ እንዲተላለፍ የተፈለገው ለምንድነው? ዋና የስም ማጥፊያ ማጠንጠንጠኛው ሙሰኞችና አማሳኞች ናቸው የሚል ቢሆንም ማን ምን ሰረቀ? ስንት ሰረቀ? መቼ ሰረቀ? የት ሰረቀ? ለሚለው የጥያቄ ጭብጥ መልስ የሚሰጥ አካል የለም። በወሬ ደረጃ የምናየውንና የምንሰማውን ይዞ ካልሆነ በስተቀር ማስረጃውን በነጥብ የሚያስረዳ አካል የለም። የተጠቀሱት ግለሰቦች በሥራቸው ያልተመሰረከላቸው መሆኑ ወይም የሙስና ተሳታፊ ስለመሆናቸው መጠርጠራቸው ብቻውን ስለማኅበረ ቅዱሳን መናገራቸውን ስህተት ሊያደርገው አይችልም። ታዲያ ቅዱስ ሲኖዶስ በነዚህ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወሰድ! የሚለው በምን መነሻ ነው? ሲኖዶስ ሊያደርግ የተገባው ሀቅ ቢኖር ማኅበሩንም ይሁን በማኅበሩ ዙሪያ ተቃውሞ ያነሱ ሰዎች ያጠፉት ነገር ካለ መርምሮ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም የእርምት እርምጃ መውሰድ ነበር። ነገር ግን አንዱን አጥፊ ደግፎ ሌላው አጥፊ ላይ ጣትን መቀሰር ቅንም፤ መንፈሳዊም አካሄድ አይደለም።

 ይህንን ዘገባ እስካወጣንበት ጊዜ ድረስ ከላይ በጠቅስናቸውና በሌሎች ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማኅበሩ ከኋላ እየገፋ ብዙ ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል። በአባ ማቴዎስና በአባ ሉቃስ አሳሳቢነት ቋሚ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ጉዳዩን እያነሱ የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደአንዱ ተቆጥሮ በተጠቀሱት ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ላለፈው አንድ ወር ሙሉ ጽኑ ክርክር ሲያደርጉ መቆየታቸው ተሰምቷል። ከተወሰኑ ጉባዔዎች በስተቀር ያልተነሳበት ስብሰባ አልነበረም። በተለይም አባ ሉቃስ «ሊቃነ ጳጳሳት ተዘልፈዋል፤ የቤተ ክርስቲያን ክብር ሲነካ ዝም ማለት አይቻልም፤ ማኅበሩም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ እየሰራ ነው» በሚል መከራከሪያ በተቃዋሚ ካህናት ላይ እርምጃ ለማስወሰድ ብዙ ተጉዘው ነበር። ነገር ግን በፓትርያርኩ በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውድቅ ተደርጓል።
    የፓትርያርኩ አቋም ማኅበረ ካህናቱን ሰብስቦ ለማናገር የማንንም ፈቃድ አልጠይቅም። ቅዱስ ፓትርያርክ የሚመራቸውን ካህናት የማናገር መብቱን የሚያገኘው ሥልጣኑን  ከተቀበለት ሰዓት ጀምሮ ነው። ካህናቱንም የተሰማቸውንና የታያቸውን ጉዳይ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማቅረባቸው ትክክልና ተገቢ ነው። አያስወቅሳቸውም። ከዚያ በተረፈ የሊቃነ ጳጳሳቱን ስም አንስቶ ጸያፍ ቃል የተናገረ ካለ በቦታና በስም ተለይቶ ይነገረንና ምክርና ተግሳጽ እንሰጠዋለን እንጂ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ የመሰለውን ሃሳብ ያንጸባረቀ ሁሉ ጥፋተኛ አይባልም» በማለት የማኅበሩን ደጋፊ ጳጳሳት ኩም አድርገዋቸዋል። በተለይም ባለፈው አንድ ሳምንት በማኅበሩ በኩል ከኋላ ይገፉ የነበሩትና አሳባቸው ውድቅ የሆነባቸው አባ ማቴዎስንና አባ ሉቃስን ያየ መጨረሻቸውን ለማየት ናፍቆ ነበር።
ሁልጊዜም የሚሸሸጉበት ስነ ሞገት «የሲኖዶሱ ውሳኔ ይከበር» የሚል ሲሆን ሲኖዶስ የማንን የመናገር መብት እንደከለከለ የሚገልጽ ማስረጃ ግን ማቅረብ አልቻሉም። ወደፊትም አይችሉም።

 ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደረሰን መረጃ እንደሚያስረዳው ማኅበሩን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ካህናት መብታቸው በመሆኑ የትኛውም አካል ይህንን መብታችሁን ለምን ገለጻችሁ?ብሎ እርምጃ የሚወስድ አካል ቢኖር የሕግ ጥበቃ እንዲደደረግላቸው ለመንግሥት አካላት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ቃል የተገባላቸው መሆኑ ታውቋል።

Wednesday, December 3, 2014

ሰበር ዜና፤ አባ እንባቆም ኢየሩሳሌም ገቡ፤ አባ ዳንኤል ደግሞ ሚኒያፖሊስ ከተሙ!

(ደጀ ብርሃን፤ሕዳር 24/2007 )

 አባ እንባቆም እስራኤል በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀጳጳስ ሆነው በጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባዔ መመደባቸው ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ በነበሩትና ባለመግባባት ከቦታው እንዲነሱ በተደረጉት በአባ ዳንኤል ምትክ የተመደቡት አዲሱ ሊቀ ጳጳስ አባ እንባቆም ትናንት በ23/3/ 2007 ዓ/ም ኢየሩሳሌም መግባታቸውና ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

    አባ እንባቆም ቀደም ሲል በድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ይሰሩ እንደነበር ሲታወቅ በቆይታቸውም ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ጋር ከፍተኛ አለመግባባት ላይ ደርሰውና ከቦታው እንዲነሱ የሕዝብ ግፊት አይሎ በነበረበት አጋጣሚ ወደኢየሩሳሌም መመደባቸው ለጊዜውም ቢሆን ትንፋሽ የመግዢያ ጊዜ ሊሆናቸው እንደሚችል ተገምቷል።

 በተመሳሳይ መልኩ ሊቀጳጳሱ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ሲደርስባቸው የቆየ ሲሆን የጉዳዩን ዝርዝር ምክንያት ለመግለጽ የተቆጠቡት ምንጮቻችን ሊቀጳጳሱ ከኢየሩሳሌም መነኮሳት ጋር ተግባብተው መስራት ይችላሉ ወይ? የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና በሂደት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል ሲሉ አክለው ገለጸውልናል።
በሌላ በኩል ከገዳሙ አባቶች ጋር ባለመግባባት የተነሱት አባ ዳንኤል የተመደቡበትን ሀገረ ስብከት ሳይረከቡ እስካሁን አሜሪካ በሚኒሶታ ስቴት ሚኒያፖሊስ ውስጥ በምትገኘው የግላቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከትመው የሚገኙ ሲሆን  ታቦተ ኪዳነ ምህረትን ከአዲስ አበባ ተሸክመው እንዲሄዱና ከመድኃኔዓለም ታቦት ጋር በደባልነት እንዳስገቡ ለመረዳት ችለናል። ሀገረ ስብከቱ በአቡነ ዘካርያስ የሚመራ ቢሆንም የሲኖዶሱን ህግ በመጻረር አንዱ በሌላው ሊቀ ጳጳስ ሀ/ስብከት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የፈለገውን መሥራት የለመደ አሰራር ሆኗል። በተለይም በአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ሊቀ ጳጳስ ጡረታውንና ድጎማውን እየተቀበለ በስሙ ያቋቋማትን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በግሉ ያለከልካይ ያስተዳድራል።



Sunday, November 30, 2014

በምድር ላይ በክፉው መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ አሰተኛ ክርስቶሶች (ክፍል 4 )

ላዝሎ ቶት(1938-2012) 

በትውልዱ ሀንጋሪ፤ በዜግነት አውስትራሊያዊ የሆነ ሰው ነው። በትውልድ ሀገሩ በጂኦሎጂ ትምህርት ዲፕሎማ የነበረው ቢሆንም የእንግሊዝኛ ቋንቋው ደካማ ስለነበርና የሙያ ክህሎቱም ተቀባይነት ባለማግኘቱ አውስትራሊያ እንደገባ ሀንጋሪ በተማረው ሙያ መስራት አልቻለም። በኋላም በአንድ ሳሙና ፋብሪካ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሮ ጥቂት ከቆየ በኋላ በ1971 ዓ/ም ወደኢጣሊያ አቅንቷል።  ጣልያን እንደደረሰም እኔ «ኢየሱስ» ነኝ እያለ ለመስበክ ቢሞክርም ጣሊያንኛ ባለመቻሉ ስብከቱን ያዳመጠው አልነበረም። ከሮማው ካቶሊክ ፖፕ ጳውሎስ 6ኛ ለመገናኘትና የራሱን ማንነት ሊገልጽላቸው እንደሚፈልግ ደብዳቤ ጽፎላቸው ደብዳቤው ከፖፑ ሳይደርስ መንገድ ላይ ቢቀርበትም በሌላ መንገድ ለመገናኘት ያልተሳካ ሙከራም አድርጓል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ተስፋ ያልቆረጠው «ቶት» የመጨረሻ ሙከራውን ለማድረግ በ33ኛው ዓመት ዕድሜው ግንቦት 21 ቀን 1972 ዓ/ም ጂኦሎጂስቶች በተለይ የሚጠቀሙበትን ትንሽ መዶሻ ከፍ አድርጎ በመያዝና በአደባባይ እየጮኸ «እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ ሞቼም ነበር፤ ሕያው ነኝ» እያለ ይረብሽ ጀመር። ከዚያም ወደ ቫቲካን ሲቲ በመግባት በሚካኤል አንጄሎ የተሰራውን ቅርጽ ማለትም ኢየሱስ ከመስቀል ላይ ወርዶ በእናቱ በማርያም እቅፍ ላይ ሆኖ ከአንገቱ ዘንበል ብሎ የሚታየውን ምስል በያዘው መዶሻ መደብደብ ጀመረ። በድብደባውም የማርያምን ምስል ቀኝ ክንድ፤ የአንድ ዓይን ክፍሏንና አፍንጫዋን ሰብሮ ጥሏል።


 በቦታው ከነበሩ ጎብኚዎች አንዱ የሆነው ቦብ ካሲሊ የተባለ ሰው ቶት ላይ ተጠምጥሞ በመያዝ ሊያስጥለው ችሏል። ቶት በቁጥጥር ስር ውሎ ህክምና ሲደረግለት የአእምሮ በሽተኛ መሆኑ በመረጋገጡ ከጣሊያን ወደአውስትራሊያ በአስቸኳይ እንዲባረር ተደርጓል። አውስትራሊያም እንደደረሰ በተመሳሳይ ድርጊት ላይ በመገኘቱ ከህሙማን ክብካቤ ማዕከል እንዲገባ ተደርጎ ህይወቱ እስካለፈችበት 2012 ዓ/ም ድረስ በዚያው ሲረዳ ቆይቷል።

===============================================================================

ዌይን ቤንት ወይም ማይክል ትራቬሰር (ከ1941- እስካሁን በሕይወት ያለ)

 በ1941 ዓ/ም የተወለደ ሲሆን  በአይዳሆ ሴንትፖይንት ከተማ በምትገኝ «ጌታ የኛ ቅድስና ቤተ ክርስቲያን» መሪ የነበረ ሰው ነው። ቤንት የዚህች ቤተክርስቲያን መሪ ከመሆኑ በፊት «በሰባተኛ ቀን ቤተ ክርስቲያን» ፓስተር ሆኖ ያገለግል ነበር። በ1987 ዓ/ም ቤተ ክርስቲያኒቱን በይፋ ለቆ ሲወጣ «ሰባተኛ ቀን ቤተ ክርስቲያን የታላቂቱ ጋለሞታ ሴት ልጅ ናት» ብሎ በአደባባይ ተናግሮ ነበር። ይህንን ለማለት ያበቃውን ምክንያት ግን በወቅቱ አልተናገረም።  ከዚያም ወደ አይዳሆ በማምራት ጥቂት ጊዜ በአባልነት ከቆየ በኋላ በ2000 ዓ/ም «ጌታ የኛ ቅድስና» በተባለችውና አነስተኛ ቁጥር በያዘችው ቤተ ክርስቲያን መሪ  ለመሆን ቻለ። በዚያው ዓመት «እግዚአብሔር፤ አንተ ኢየሱስ ነህ ብሎ ተገልጾ ነገረኝ» በማለት ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አወጀ። ጥቂት ቆይቶም ከሰባት ደናግላን ጋራ ለወሲብ እንድትተኛ የሚል ትዕዛዝ ስለመጣልኝ ደናግል ልጆቻችሁን እንድትሰጡኝ በማለት ጥያቄውን አቀረበ። ገሚሶቹ የቡድኑ አባላት ሃሳቡን ውድቅ ያደረጉበት ቢሆንም በግላጭ ሴት ልጁን አሳልፎ የሰጠው ማን እንደሆነ ሳይታወቅ በምስጢር ከደናግላን ጋር ወሲብ መፈጸሙ በኋላ ላይ በፖሊስ በተደረገበት ምርመራ ሊረጋገጥ ችሏል። ቻናል 4 የተባለው የዩኬ ቴሌቪዥን ጣቢያ በ2007 ዓ/ም ከዌይን ቤንት ጋር ባደረገው ቃል ምልልስ ስለደናግላኑ ወሲብና ከእግዚአብሔር ስለሚመጣለት ትዕዛዛት ተከታታይ ፕሮግራም አስተላልፎ ነበር።(ከቪዲዮዎቹ አንዱን ለማየት እዚህ ይጫኑ)
  የዓለምም መጨረሻ ጥቅምት 31/2007 ዓ/ም እንደሚሆንና ተከታዮቹም ለመነጠቅ እንዲዘጋጁ የተናገረ ቢሆንም ቀኑ ሲደርስ እንዳለው የሆነ ነገር ምንም አልነበረም።  ይልቁንም ቤንት ከልጁ ሚስት፤ ከደናግላን ጋር እንዲሁም ለአቅመ ሄዋን ካልደረሱ ታዳጊዎች ጋር ወሲብ በመፈጸም ወንጀል ተከሶ በ2008 ዓ/ም የ18 ዓመታትን እስራት ተከናንቦ ከርቸሌ ወርዷል። ዌይን ቤንት ከርቸሌ ከወረደ በ2014 ዓ/ም ገና 6ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን ቢያንስ በአመክሮ ለመፈታት ከእንግዲህ 3 ዓመት ገደማ በዚያው መቆየት ይጠበቅበታል። 

==============================================================================

አሪፊን ሙሐመድ ( 1943- እስካሁን ያለ)

 አሪፊን ሙሐመድ በ1943 ዓ/ም ከሙስሊም ቤተሰብ በማሌዢያ ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ህውከት እንደደረሰ በ1980ቹ አጋማሽ  በማላያን ቋንቋ «ካራጃአን ላንጊት» ወይም በእንግሊዝኛው «የሰማይ መንግሥት» የተሰኘ ድርጅት አቋቋመ። በአክራሪ ሙስሊሞች በምትታወቀው ማሌዢያ ውስጥ አሪፊን ሙሐመድ «እኔ አልመሲህ ዒሳ፤ ቡድሃ፤ ሙሐመድ ሺቫ ነኝ» እያለ በመስበክ ተከታዮችን ለማፍራት ጊዜ አልፈጀበትም። በዚህ አድራጎቱ ብርቱ ተቃውሞ ገጠመው። በተደጋጋሚ ሲታሰር፤ ሲፈታ ቆይቶ መንግሥታዊ ስርዓቱን በዓመጽ ለመገልበጥ በመሞከርና ሃይማኖታዊ ብጥብጥን በመፍጠር ወንጀል ተከሶ ድርጅቱ እንዲዘጋ፤ በአባልነት የተሳተፉትም እንዲታሰሩ ሲወሰን አሪፊን ሙሐመድ ሾልኮ አመለጠ። ከአራቱ ሚስቶቹ ሦስቱና ከተከታዮቹም 58 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

 እያንዳንዳቸውም 3000 የማሌዢያን ገንዘብ እንዲከፍሉና ሁለት ዓመት እንዲታሰሩ ፍርድ ቤት ወሰነባቸው።  የድርጅታቸውም ህንጻና ማንኛውም ንብረት እንዲፈርስ ተደረገ። አሪፊን ሙሐመድ አንዴ ኢየሱስ ነኝ፤ አንዴ ማህዲ ነኝ እያለ ተከታዮቹን ቢያጭበረብርም በማሌዢያ መንግሥት በወንጀል ከሚፈለጉ ሰዎች ቀንደኛው ሲሆን ማሌዢያን ለቆ ከጠፋ በኋላ በታይላንድ ውስጥ ተሸሽጎ እንደሚገኝ ይገመታል።
==================================================================================

ማታዮሺ ሚትሱኣ (1944- እስካሁን በሕይወት ያለ) 

በጃፓን፤ ኦኪናዋ ከተማ በጥር 5/ 1944 ዓ/ም ተወለደ። ከዚያም ለአቅመ ትምህርት እንደደረሰ በመጀመሪያ በተወለደት ቦታ በኋላም በቶኪዮ ቹዋ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል። በ1997 ዓ/ም «ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ ኅብረት ፓርቲ» የተባለውን ሃይማኖትንና ፖለቲካን በጥምር የሚያንቀሳቅስ ፓርቲ መሰረተ። እንደሃይማኖት ሥርዓት ዓለም በኔ እንዲገዛ «እኔ ኢየሱስ ነኝ» አለ። እንደፖለቲካ አስተዳደር ደግሞ ዓለም በኔ እንዲመራ «የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ አለ»። የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ባለው ከፍተኛ ጉጉት የርሱ ፓርቲ በተደጋጋሚ በምርጫ ቢወዳደርም  እንኳን ከትልቅ ስልጣን ሊደርስ ቀርቶ የመንደር ምርጫም ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። በምርጫ የተፎካከሩትን ሰዎች ለዚህ ድርጊታችሁ የምሰጣችሁ ምክር «ራሳችሁን አጥፉ»  ያላቸው ሲሆን ስልጣን ብይዝ ደግሞ ሁሉንም ሰብስቤ እሳት ውስጥ እጨምራቸው ነበር እያለ ሲለፍፍ ተሰምቷል።

== ==============================================================



ጆሴ ሉዊስ ደ ጂሰስ ሚራንዳ ( 1946- 2013) 

 ፖርቶሪኮ ውስጥ ፖንሴ በተባለች ከተማ በ1946 ዓ/ም ተወለደ። ወላጆቹ በጣም ድሃ ስለነበሩ የሴቶችን ቦርሳ መመንተፍ የተለማመደው በልጅነት ዕድሜው ነበር። ገና የ14 ዓመት ዕድሜ ሳለም የሔሮይን አደገኛ ተጠቃሚ እስከመሆን ደርሷል።  ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በፖንሴ ከተማ በነበረችው መጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን ተቀላቀለ። እግዚአብሔር ባደረገልኝ ጥሪና እገዛ ከነበረብኝ ደባል ሱስ ሁሉ ተላቅቄአለሁ አለ።  ጆሴ ሚራንዳ በ1973 ዓ/ም  ሁለት መላዕክት መጥተው በነገሩኝ መሠረት «እኔ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ ሆኜ በምድር ላይ መገለጤን ነግረውኛል» ብሎ መለፈፉን «ሀ»ብሎ ጀመረ። በማያሚ፤ ፍሎሪዳ የስደት ኑሮውን የቀጠለው ሚራንዳ የ15 ደቂቃ የሬዲዮ ፕሮግራም በማሰራጨት የሱን ኢየሱስነት ይሰብክ ገባ። በስብከት መርሐ ግብሩ «ሚኒስትሮ ግሬሴንዴ  ኤን ግራሲያ» ወይም « በጸጋው የማደግ አገልግሎት» የተሰኘ ድርጅት ከመሰረተ በኋላ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ማስፋፋቱን ቀጠለ። በ35 ስቴቶች በከፈተው ተቋም 287 የሬዲዮ ጣቢያዎችና በእንግሊዝኛና ስፓኒሽ ቋንቋ የሚተላለፍ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ስርጭትም እስከማስተላለፍም ደርሷል።
ጆሴ ሚራንዳ አንድ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ ነኝ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ነኝ እያለ ከቆየ በኋላ በ2006 ዓ/ም ክህደቱን በማጠናከር ከዛሬ ጀምሮ «እኔ የኢየሱስ ተቃዋሚ ነኝ» ሲል አወጀ።  «Anti Christ» ወይም ተቃዋሚው ስለሆንኩኝ መለያ ምልክቴ በራእይ 13 ላይ የተጠቀሰው«666» ቁጥር ነው በማለቱ  ተከታዮቹ ሁሉ በሰውነታቸው ላይ እንዲነቀሱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ተከታዮቹም «666» ቁጥርን በሰውነታቸው ላይ በሰልፍ ተነቀሱት።
የሚራንዳ ወርሃዊ ደመወዝም ልዩ ልዩ ክፍያና አበልን ሳይጨምር 228,000 ዶላር ገደማ ነበር። ሚራንዳ ባደረበት የጉበት ህመም በተወለደ በ67 ዓመቱ በ2013 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከ2 ሚሊዮን በላይ በሚገመቱ ተከታዮቹም ዘንድ «እንደመልከ ጼዴቅ ለዘለዓለም የሚኖር» ተብሎለታል።
በአንድ ወቅት CNN ካቀረበው የጆሴ 666 ታሪክ የተወሰደ ቪዲዮ ይመልከቱ።