Wednesday, December 3, 2014

ሰበር ዜና፤ አባ እንባቆም ኢየሩሳሌም ገቡ፤ አባ ዳንኤል ደግሞ ሚኒያፖሊስ ከተሙ!

(ደጀ ብርሃን፤ሕዳር 24/2007 )

 አባ እንባቆም እስራኤል በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀጳጳስ ሆነው በጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባዔ መመደባቸው ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ በነበሩትና ባለመግባባት ከቦታው እንዲነሱ በተደረጉት በአባ ዳንኤል ምትክ የተመደቡት አዲሱ ሊቀ ጳጳስ አባ እንባቆም ትናንት በ23/3/ 2007 ዓ/ም ኢየሩሳሌም መግባታቸውና ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

    አባ እንባቆም ቀደም ሲል በድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ይሰሩ እንደነበር ሲታወቅ በቆይታቸውም ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ጋር ከፍተኛ አለመግባባት ላይ ደርሰውና ከቦታው እንዲነሱ የሕዝብ ግፊት አይሎ በነበረበት አጋጣሚ ወደኢየሩሳሌም መመደባቸው ለጊዜውም ቢሆን ትንፋሽ የመግዢያ ጊዜ ሊሆናቸው እንደሚችል ተገምቷል።

 በተመሳሳይ መልኩ ሊቀጳጳሱ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ሲደርስባቸው የቆየ ሲሆን የጉዳዩን ዝርዝር ምክንያት ለመግለጽ የተቆጠቡት ምንጮቻችን ሊቀጳጳሱ ከኢየሩሳሌም መነኮሳት ጋር ተግባብተው መስራት ይችላሉ ወይ? የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና በሂደት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል ሲሉ አክለው ገለጸውልናል።
በሌላ በኩል ከገዳሙ አባቶች ጋር ባለመግባባት የተነሱት አባ ዳንኤል የተመደቡበትን ሀገረ ስብከት ሳይረከቡ እስካሁን አሜሪካ በሚኒሶታ ስቴት ሚኒያፖሊስ ውስጥ በምትገኘው የግላቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከትመው የሚገኙ ሲሆን  ታቦተ ኪዳነ ምህረትን ከአዲስ አበባ ተሸክመው እንዲሄዱና ከመድኃኔዓለም ታቦት ጋር በደባልነት እንዳስገቡ ለመረዳት ችለናል። ሀገረ ስብከቱ በአቡነ ዘካርያስ የሚመራ ቢሆንም የሲኖዶሱን ህግ በመጻረር አንዱ በሌላው ሊቀ ጳጳስ ሀ/ስብከት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የፈለገውን መሥራት የለመደ አሰራር ሆኗል። በተለይም በአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ሊቀ ጳጳስ ጡረታውንና ድጎማውን እየተቀበለ በስሙ ያቋቋማትን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በግሉ ያለከልካይ ያስተዳድራል።



Sunday, November 30, 2014

በምድር ላይ በክፉው መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ አሰተኛ ክርስቶሶች (ክፍል 4 )

ላዝሎ ቶት(1938-2012) 

በትውልዱ ሀንጋሪ፤ በዜግነት አውስትራሊያዊ የሆነ ሰው ነው። በትውልድ ሀገሩ በጂኦሎጂ ትምህርት ዲፕሎማ የነበረው ቢሆንም የእንግሊዝኛ ቋንቋው ደካማ ስለነበርና የሙያ ክህሎቱም ተቀባይነት ባለማግኘቱ አውስትራሊያ እንደገባ ሀንጋሪ በተማረው ሙያ መስራት አልቻለም። በኋላም በአንድ ሳሙና ፋብሪካ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሮ ጥቂት ከቆየ በኋላ በ1971 ዓ/ም ወደኢጣሊያ አቅንቷል።  ጣልያን እንደደረሰም እኔ «ኢየሱስ» ነኝ እያለ ለመስበክ ቢሞክርም ጣሊያንኛ ባለመቻሉ ስብከቱን ያዳመጠው አልነበረም። ከሮማው ካቶሊክ ፖፕ ጳውሎስ 6ኛ ለመገናኘትና የራሱን ማንነት ሊገልጽላቸው እንደሚፈልግ ደብዳቤ ጽፎላቸው ደብዳቤው ከፖፑ ሳይደርስ መንገድ ላይ ቢቀርበትም በሌላ መንገድ ለመገናኘት ያልተሳካ ሙከራም አድርጓል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ተስፋ ያልቆረጠው «ቶት» የመጨረሻ ሙከራውን ለማድረግ በ33ኛው ዓመት ዕድሜው ግንቦት 21 ቀን 1972 ዓ/ም ጂኦሎጂስቶች በተለይ የሚጠቀሙበትን ትንሽ መዶሻ ከፍ አድርጎ በመያዝና በአደባባይ እየጮኸ «እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ ሞቼም ነበር፤ ሕያው ነኝ» እያለ ይረብሽ ጀመር። ከዚያም ወደ ቫቲካን ሲቲ በመግባት በሚካኤል አንጄሎ የተሰራውን ቅርጽ ማለትም ኢየሱስ ከመስቀል ላይ ወርዶ በእናቱ በማርያም እቅፍ ላይ ሆኖ ከአንገቱ ዘንበል ብሎ የሚታየውን ምስል በያዘው መዶሻ መደብደብ ጀመረ። በድብደባውም የማርያምን ምስል ቀኝ ክንድ፤ የአንድ ዓይን ክፍሏንና አፍንጫዋን ሰብሮ ጥሏል።


 በቦታው ከነበሩ ጎብኚዎች አንዱ የሆነው ቦብ ካሲሊ የተባለ ሰው ቶት ላይ ተጠምጥሞ በመያዝ ሊያስጥለው ችሏል። ቶት በቁጥጥር ስር ውሎ ህክምና ሲደረግለት የአእምሮ በሽተኛ መሆኑ በመረጋገጡ ከጣሊያን ወደአውስትራሊያ በአስቸኳይ እንዲባረር ተደርጓል። አውስትራሊያም እንደደረሰ በተመሳሳይ ድርጊት ላይ በመገኘቱ ከህሙማን ክብካቤ ማዕከል እንዲገባ ተደርጎ ህይወቱ እስካለፈችበት 2012 ዓ/ም ድረስ በዚያው ሲረዳ ቆይቷል።

===============================================================================

ዌይን ቤንት ወይም ማይክል ትራቬሰር (ከ1941- እስካሁን በሕይወት ያለ)

 በ1941 ዓ/ም የተወለደ ሲሆን  በአይዳሆ ሴንትፖይንት ከተማ በምትገኝ «ጌታ የኛ ቅድስና ቤተ ክርስቲያን» መሪ የነበረ ሰው ነው። ቤንት የዚህች ቤተክርስቲያን መሪ ከመሆኑ በፊት «በሰባተኛ ቀን ቤተ ክርስቲያን» ፓስተር ሆኖ ያገለግል ነበር። በ1987 ዓ/ም ቤተ ክርስቲያኒቱን በይፋ ለቆ ሲወጣ «ሰባተኛ ቀን ቤተ ክርስቲያን የታላቂቱ ጋለሞታ ሴት ልጅ ናት» ብሎ በአደባባይ ተናግሮ ነበር። ይህንን ለማለት ያበቃውን ምክንያት ግን በወቅቱ አልተናገረም።  ከዚያም ወደ አይዳሆ በማምራት ጥቂት ጊዜ በአባልነት ከቆየ በኋላ በ2000 ዓ/ም «ጌታ የኛ ቅድስና» በተባለችውና አነስተኛ ቁጥር በያዘችው ቤተ ክርስቲያን መሪ  ለመሆን ቻለ። በዚያው ዓመት «እግዚአብሔር፤ አንተ ኢየሱስ ነህ ብሎ ተገልጾ ነገረኝ» በማለት ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አወጀ። ጥቂት ቆይቶም ከሰባት ደናግላን ጋራ ለወሲብ እንድትተኛ የሚል ትዕዛዝ ስለመጣልኝ ደናግል ልጆቻችሁን እንድትሰጡኝ በማለት ጥያቄውን አቀረበ። ገሚሶቹ የቡድኑ አባላት ሃሳቡን ውድቅ ያደረጉበት ቢሆንም በግላጭ ሴት ልጁን አሳልፎ የሰጠው ማን እንደሆነ ሳይታወቅ በምስጢር ከደናግላን ጋር ወሲብ መፈጸሙ በኋላ ላይ በፖሊስ በተደረገበት ምርመራ ሊረጋገጥ ችሏል። ቻናል 4 የተባለው የዩኬ ቴሌቪዥን ጣቢያ በ2007 ዓ/ም ከዌይን ቤንት ጋር ባደረገው ቃል ምልልስ ስለደናግላኑ ወሲብና ከእግዚአብሔር ስለሚመጣለት ትዕዛዛት ተከታታይ ፕሮግራም አስተላልፎ ነበር።(ከቪዲዮዎቹ አንዱን ለማየት እዚህ ይጫኑ)
  የዓለምም መጨረሻ ጥቅምት 31/2007 ዓ/ም እንደሚሆንና ተከታዮቹም ለመነጠቅ እንዲዘጋጁ የተናገረ ቢሆንም ቀኑ ሲደርስ እንዳለው የሆነ ነገር ምንም አልነበረም።  ይልቁንም ቤንት ከልጁ ሚስት፤ ከደናግላን ጋር እንዲሁም ለአቅመ ሄዋን ካልደረሱ ታዳጊዎች ጋር ወሲብ በመፈጸም ወንጀል ተከሶ በ2008 ዓ/ም የ18 ዓመታትን እስራት ተከናንቦ ከርቸሌ ወርዷል። ዌይን ቤንት ከርቸሌ ከወረደ በ2014 ዓ/ም ገና 6ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን ቢያንስ በአመክሮ ለመፈታት ከእንግዲህ 3 ዓመት ገደማ በዚያው መቆየት ይጠበቅበታል። 

==============================================================================

አሪፊን ሙሐመድ ( 1943- እስካሁን ያለ)

 አሪፊን ሙሐመድ በ1943 ዓ/ም ከሙስሊም ቤተሰብ በማሌዢያ ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ህውከት እንደደረሰ በ1980ቹ አጋማሽ  በማላያን ቋንቋ «ካራጃአን ላንጊት» ወይም በእንግሊዝኛው «የሰማይ መንግሥት» የተሰኘ ድርጅት አቋቋመ። በአክራሪ ሙስሊሞች በምትታወቀው ማሌዢያ ውስጥ አሪፊን ሙሐመድ «እኔ አልመሲህ ዒሳ፤ ቡድሃ፤ ሙሐመድ ሺቫ ነኝ» እያለ በመስበክ ተከታዮችን ለማፍራት ጊዜ አልፈጀበትም። በዚህ አድራጎቱ ብርቱ ተቃውሞ ገጠመው። በተደጋጋሚ ሲታሰር፤ ሲፈታ ቆይቶ መንግሥታዊ ስርዓቱን በዓመጽ ለመገልበጥ በመሞከርና ሃይማኖታዊ ብጥብጥን በመፍጠር ወንጀል ተከሶ ድርጅቱ እንዲዘጋ፤ በአባልነት የተሳተፉትም እንዲታሰሩ ሲወሰን አሪፊን ሙሐመድ ሾልኮ አመለጠ። ከአራቱ ሚስቶቹ ሦስቱና ከተከታዮቹም 58 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

 እያንዳንዳቸውም 3000 የማሌዢያን ገንዘብ እንዲከፍሉና ሁለት ዓመት እንዲታሰሩ ፍርድ ቤት ወሰነባቸው።  የድርጅታቸውም ህንጻና ማንኛውም ንብረት እንዲፈርስ ተደረገ። አሪፊን ሙሐመድ አንዴ ኢየሱስ ነኝ፤ አንዴ ማህዲ ነኝ እያለ ተከታዮቹን ቢያጭበረብርም በማሌዢያ መንግሥት በወንጀል ከሚፈለጉ ሰዎች ቀንደኛው ሲሆን ማሌዢያን ለቆ ከጠፋ በኋላ በታይላንድ ውስጥ ተሸሽጎ እንደሚገኝ ይገመታል።
==================================================================================

ማታዮሺ ሚትሱኣ (1944- እስካሁን በሕይወት ያለ) 

በጃፓን፤ ኦኪናዋ ከተማ በጥር 5/ 1944 ዓ/ም ተወለደ። ከዚያም ለአቅመ ትምህርት እንደደረሰ በመጀመሪያ በተወለደት ቦታ በኋላም በቶኪዮ ቹዋ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል። በ1997 ዓ/ም «ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ ኅብረት ፓርቲ» የተባለውን ሃይማኖትንና ፖለቲካን በጥምር የሚያንቀሳቅስ ፓርቲ መሰረተ። እንደሃይማኖት ሥርዓት ዓለም በኔ እንዲገዛ «እኔ ኢየሱስ ነኝ» አለ። እንደፖለቲካ አስተዳደር ደግሞ ዓለም በኔ እንዲመራ «የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ አለ»። የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ባለው ከፍተኛ ጉጉት የርሱ ፓርቲ በተደጋጋሚ በምርጫ ቢወዳደርም  እንኳን ከትልቅ ስልጣን ሊደርስ ቀርቶ የመንደር ምርጫም ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። በምርጫ የተፎካከሩትን ሰዎች ለዚህ ድርጊታችሁ የምሰጣችሁ ምክር «ራሳችሁን አጥፉ»  ያላቸው ሲሆን ስልጣን ብይዝ ደግሞ ሁሉንም ሰብስቤ እሳት ውስጥ እጨምራቸው ነበር እያለ ሲለፍፍ ተሰምቷል።

== ==============================================================



ጆሴ ሉዊስ ደ ጂሰስ ሚራንዳ ( 1946- 2013) 

 ፖርቶሪኮ ውስጥ ፖንሴ በተባለች ከተማ በ1946 ዓ/ም ተወለደ። ወላጆቹ በጣም ድሃ ስለነበሩ የሴቶችን ቦርሳ መመንተፍ የተለማመደው በልጅነት ዕድሜው ነበር። ገና የ14 ዓመት ዕድሜ ሳለም የሔሮይን አደገኛ ተጠቃሚ እስከመሆን ደርሷል።  ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በፖንሴ ከተማ በነበረችው መጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን ተቀላቀለ። እግዚአብሔር ባደረገልኝ ጥሪና እገዛ ከነበረብኝ ደባል ሱስ ሁሉ ተላቅቄአለሁ አለ።  ጆሴ ሚራንዳ በ1973 ዓ/ም  ሁለት መላዕክት መጥተው በነገሩኝ መሠረት «እኔ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ ሆኜ በምድር ላይ መገለጤን ነግረውኛል» ብሎ መለፈፉን «ሀ»ብሎ ጀመረ። በማያሚ፤ ፍሎሪዳ የስደት ኑሮውን የቀጠለው ሚራንዳ የ15 ደቂቃ የሬዲዮ ፕሮግራም በማሰራጨት የሱን ኢየሱስነት ይሰብክ ገባ። በስብከት መርሐ ግብሩ «ሚኒስትሮ ግሬሴንዴ  ኤን ግራሲያ» ወይም « በጸጋው የማደግ አገልግሎት» የተሰኘ ድርጅት ከመሰረተ በኋላ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ማስፋፋቱን ቀጠለ። በ35 ስቴቶች በከፈተው ተቋም 287 የሬዲዮ ጣቢያዎችና በእንግሊዝኛና ስፓኒሽ ቋንቋ የሚተላለፍ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ስርጭትም እስከማስተላለፍም ደርሷል።
ጆሴ ሚራንዳ አንድ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ ነኝ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ነኝ እያለ ከቆየ በኋላ በ2006 ዓ/ም ክህደቱን በማጠናከር ከዛሬ ጀምሮ «እኔ የኢየሱስ ተቃዋሚ ነኝ» ሲል አወጀ።  «Anti Christ» ወይም ተቃዋሚው ስለሆንኩኝ መለያ ምልክቴ በራእይ 13 ላይ የተጠቀሰው«666» ቁጥር ነው በማለቱ  ተከታዮቹ ሁሉ በሰውነታቸው ላይ እንዲነቀሱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ተከታዮቹም «666» ቁጥርን በሰውነታቸው ላይ በሰልፍ ተነቀሱት።
የሚራንዳ ወርሃዊ ደመወዝም ልዩ ልዩ ክፍያና አበልን ሳይጨምር 228,000 ዶላር ገደማ ነበር። ሚራንዳ ባደረበት የጉበት ህመም በተወለደ በ67 ዓመቱ በ2013 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከ2 ሚሊዮን በላይ በሚገመቱ ተከታዮቹም ዘንድ «እንደመልከ ጼዴቅ ለዘለዓለም የሚኖር» ተብሎለታል።
በአንድ ወቅት CNN ካቀረበው የጆሴ 666 ታሪክ የተወሰደ ቪዲዮ ይመልከቱ።





Monday, November 24, 2014

ኡጋንዳዊቷ የቤት ሠራተኛ ሕይወት ለማጥፋት በመሞከር ወንጀል ተከሠሠች!

( ዕድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ እንዲመለከቱ አይመከርም ) The film is not suitable for viewing by anyone under 18 years of age

ባለፉት ቅርብ ቀናት በኢትዮጵያ ውስጥ ሐና በተባለች ታዳጊ ወጣት ላይ አስነዋሪና እጅግ አሳሳቢ ድርጊት ተፈጽሞ የብዙዎችን ልብ እንደሰበረ ይታወቃል። ማኅበራዊ አኗኗራችን ከመተሳሰብ እያፈነገጠ፤ ሥነ ምግባራዊ አስተሳሰባችን እያደፈ የመሄዱ ምልክት ነው። ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ነው ሲባል በመሰልጠኑ ብቻ ሳይሆን በመሰይጠኑም ጭምር በመሆኑ ስግብግብነት፤ ራስ ወዳድነት፤ ብልግናና ዐመፃንም ዓለማዊ መንደርተኝነት እያካፈለው ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት ትኩሳቱ ሳይበርድ አንድ መንደር የሆነችው ዓለም ከወደዑጋንዳ ሌላ ዜና ብቅ አለች። በአንዱ ጫፍ የተፈጸመው ወሬ ወደሌላ ጫፍ ለመድረስ ደቂቃ የማይፈጅባት ዓለማችን ካስተናገደቻቸው ብዙ ዜናዎች መካከል አንዱን አሳዛኝ ድርጊት አሰማችን። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

  ድርጊቱ የተፈጸመው በዑጋንዳ፤ ኪዋቱሌ በተሰኘች አነሰተኛ ከተማ ነው። ድርጊቱን የፈጸመችው የ22 ዓመቷ ጆሊ ቱሙሂርዌ የተባለች የቤት ሠራተኛ ስትሆን በተቀጠረችበት ቤት ውስጥ እንድትንከባከብ ከአሰሪዎቿ አደራ የተሰጣትን ሕጻን በዘግናኝ ሁኔታ ስትደበድብ በቤት ውስጥ ስውር ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ ያሳያል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራጨው ይህ ቪዲዮ ብዙዎቹን አሳዝኗል። በጣም የሚረብሸው ይህ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደዋለ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት ስቧል።  የሕጻኗ ወላጅ አባት የሆነው ኤሪክ ካማንዚ ቪዲዮውን እንደተመለከተ ለኪዋቱሌ  ፖሊስ ጣቢያ በማመልከቱ ፖሊስ ደብዳቢዋን የቤት ሠራተኛ በቁጥጥር ስር አውሎ «በማሰቃየትና ለመግደል ሙከራ በማድረግ» ወንጀል የክስ ፋይል ከፍቶ ለፍርድ ቤት እንዳቀረባት የተገኘው ዜና ያስረዳል።  የቤት ሰራተኛዋ ከተቀጠረች 26 ቀናት ብቻ ያስቆጠረች ቢሆንም የፈጸመችው ድርጊት በተመሳሳይ ሁኔታ የቆየች እንደሚመስል ፖሊስ ግምቱን የሰጠ ሲሆን  ስለሰራተኛዋ ማንነትና የቀደመ ተግባር ምርመራ ለማድረግ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ለፍርድ ቤቱ በማመልከቱ ለታህሳስ 8/2014 እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል። ሕጻኗ በደረሰባት ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም እስካሁን ህክምና እየተደረገላት በሕይወት እንደምትገኝ ታውቋል።
ሕጻናት የተለየ ክብካቤና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ዓለም በምታስተናግደው የሥነ ልቡና ማኅበራዊ ቀውስ የተነሳ ለጥቃት እየተጋለጡ ይገኛሉ። ፍሪሃ እግዚአብሔር የሌለው ትውልድ ከሥነ ምግባር ውጪ በመሆን ለማኅበራዊ ኑሮ የአስተሳሰብ ቀውስ መጋለጡ አይቀሬ ነው። አሳዛኝና አስነዋሪ ድርጊት የመፈጸሙ ምክንያትም ይህ ነው።  በየቤታችን ለሕጻናት፤ በየአካባቢው ለሴቶችና ለታዳጊ ወጣቶች፤ ለአረጋውያንና ረዳት ለሌላቸው የምናደርገውን ክትትልና ቀና ድጋፍ በማጎልበት «የአባቴ ብሩካን» ተብሎ የተነገረውን የሕይወት ዋጋ ለማግኘት ዛሬውኑ እንነሳ!!

«ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ» 1ኛ ጴጥ 2፤2