Friday, November 21, 2014

ፍሪማሰንሪ /freemasonry/ ምንድነው?




ከዚህ በፊት በአንድ ጽሁፍ «ስለኤርያ 51» አጭር ምስጢራዊ ጽሁፍ ማስነበባችን ይታወሳል። አሜሪካና ዲሞክራሲ፤ ሥልጣኔና አሜሪካ መሳ ለመሳ ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ ሌላው ዓለም ይቅርና የሀገሪቱ ዜጋ የማያውቃቸው ብዙ ምሥጢሮችም ያሉባት ሀገር ናት። ላይ ላዩን በዲሞክራሲው ዕድገት ጫፍ ረግጫለሁ በማለቷና በሥልጣኔውም መጥቄአለሁ እያለች ከመለፈፏ ጀርባ ብዙ ጉድ እንዳዘለች ብዙው ሰው አያውቅም፤ ቢያውቅም ትኩረት አይሰጠውም።  በነገረ መለኮት የበሰሉና የትንቢቱ ፍጻሜ ሰዓት መድረሱን በደንብ ያጠኑ ምሁራን ግን አሜሪካንን «ታላቂቱ ባቢሎን» ይሏታል። ምክንያቱም በአደባባይ ከሚታወቅላት የዲሞክራሲውና የሥልጣኔው እርከን ባሻገር የተሸከመችው ጉድ የት የለሌ ነውና። ሁሉም ነገር ከብረት በጠነከረ ምስጢርና ከምስጢሩ አጠባበቅ ጋር ሕይወት በሚያስከፍል ዋጋ፤ የረቀቀ መዋቅር በተዘረጋበት ሥርዓት የምትመራ ሀገር በመሆኗ እያወቁ ወይም ሳያውቁ ታደነዝዛለች።  በህጋዊ ደረጃ ከ«Church of Satan” አንስቶ እስከመጨረሻው ክሂዶተ እግዚአብሔር  «Atheism” ድረስ በነጻ የሚንቀሳቀሱባትና ለዓለሙ ሁሉ ማዕከል ሆና የምታገለግለዋ አሜሪካ ጾታን በመቀየር እንዲሁም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻንም በመፍቀድ መሪ በመሆን ታገለግላለች።

      ሌላው ቀርቶ በየዓመቱ የሚከበረውን የሀለዊን /Halloween/ በዓል ጥቅምት/31 ቀን ከጫፍ ጫፍ በማክበር አሜሪካንን የሚቀድማት የለም። ለነገሩ «ሀለዊን» የሞቱ ቅዱሳንን ለማሰብ በሚል ይጀመር እንጂ ድርጊቱ የሙት መንፈስ የሆነውን ሰይጣንን ለማሰብ የተሰራ ለመሆኑ የድርጊቱ ክንዋኔ ያስረዳል። የሚያስፈራ ምስልና ቅርጽ፤ ጥርሱ ያገጠጠ፤ ዓይኑ ያፈጠጠ፤ አጽሙ  የተቆጠረ ማስጠሎ ነገር ለብሶ ወይም አጥልቆ  ሰውን በማስደንገጥና በማስፈራራት ቅዱሳንን ማክበር ነው ቢባል እንዴት ሊሆን ይችላል? ለነገሩ ቅዱሳንን ተጠግቶ ይህንን ማድረጉ ራሱን የቻለ ሌላ ምስጢር ስላለው እንጂ ቅዱሳንን ስለሚወክል አይደለም። (የዚህን ምስጢር ፍቺ በዚህ ጽሁፍ ቀጣይ ክፍሎች ለመዳሰስ ይሞከራል) አሜሪካ ለመጨረሻው ዘመን የተዘጋጀችና ለጥፋት ነጋሪት የምትጎስም ሀገር በመሆንዋ ነገሩ ሁሉ እየተበላሸ ሄዷል። ባለፈው ጥቅምት 31/ 2014 ዓ/ም በሚዙሪ፤ ሴንት ሉዊስ ከተማ ዓለም አቀፍ የ«ሀሎዊን» በዓል እንደሚደረግ የተላለፈው የጥሪ ምስል እንደሚያሳየን የጨለማውን ኃይል ካልሆነ በስተቀር ሌላ ማንን ሊሆን ይችላል? እስኪ ምስሉን አይተው ግምትዎን ይስጡ!!
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን አሜሪካ ከምታስተናግዳቸው እንግዳ ነገሮች አንዱ ክፍል ስለሆነው ስለ«ፍሪማሰንሪ»/freemasonry/ ውቅያኖስ ታሪክ ጥቂቱን በጭልፋ ልናካችላችሁ ፈልገን ነው። ምክንያቱም የአንድ ዓለም አገዛዝ /One World Order/ እንዴት እየሰራ እንዳለ በማወቅ ከሚመጣው የስህተት መንፈስ እንድንጠበቅ አበክረን ለማስገንዘብ ነው። በዚህ ዙሪያ ምሁራኑ በሀገርኛ ቋንቋ ጽፈው በሰፊው እስኪያስነብቡን ድረስ ለጥንቃቄ እንዲበጅ በጥቂቱ እንዲህ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!

ፍሪማሰንሪ ምንድነው?

     «ማሰን» የሚለው ቃል ከላቲኑ / machio/ ከሚለው ቃል የተወረሰ ነው።  ትርጉሙም «ድንጋይ ጠራቢ ፈላጭ ወይም ግንበኛ  ማለት ነው።  ቃሉም ከ1155 እ,ኤ,አ ጀምሮ አገልግሎት ላይ ውሏል። freestone-mason ማለት «ነጻ ድንጋይ ጠራቢ፤ ግንበኛ ሰው ማለት ሲሆን ይህም ስያሜ በዚህ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች «free mason» ፍሪማሰን በሚል አኅጽሮት አገልግሎት ላይ እንደዋለ በ1908 ዓ/ም የታተመው የፍሪማሰን ዜና መዋዕል መጽሐፍ ያስረዳል።  የላቲኑን ውርስ ቃል ተከትሎ “free” እና “mason” ከሚለው የእንግሊዝኛ ጥምር ቃላት የተገኘው ይህ ስያሜ ድንጋይ የመጥረብ፤ የመቁረጥና የመገንባትን ድርጊት ሲያመለክት «ፍሪማሰንሪ» /freemasonry/ ይባላል።  ይህም በነጻ ፈቃድ፤ በራስ ውሳኔ ዓለቱን ጠርቦ የማይነቃነቅና የማይናወጥ መሠረት ያለው ግንብ የመገንባት ዓላማ ነው ማለት ነው።  

«ፍሪማሰን» የተባለው ስያሜ በግንበኝነት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች በተናጠል ሲጠሩበት የቆየ ቢሆንም ከ14ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በአውሮፓ የህንጻ ምህንድስና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በጥቂት ሰዎች ተደራጅተው ራሳቸውን የመጥራት እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ የማሰን የተናጠል እንቅስቃሴ ቀደም ሲል እንደነበረ ቢሆንም ድርጅታዊ ሕግና ፒራሚዳዊ የብቃት የእርከን ደረጃ ወጥቶለት የተመሰረተው በ1717 ዓ/ም በለንደን ከተማ ነው።። በ1731 በአሜሪካ ፤ በ1736 በስኮትላንድ መሰረቱን አስፋፋ። ከዚያም በ1725 በአየር ላንድ እንደተጀመረ ይነገራል።  አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመው በጣም ደርጅቶና ጎልብቶ ዓለም ዐቀፍ ቅርጽ ለመያዝ በቅቷል። 

      ይህ የፍሪማሰን ማኅበር የአውሮፓን የኢንዱስትሪ አብዮት ተጠግቶ የተመሰረተው የህንጻና የምህንድስና ባለሙያዎችን የያዘው እንቅስቃሴ ቅርጹንና መልኩን ለውጦ በሰው አእምሮና አስተሳሰብ ላይ እንደህንጻ የሚያድግ ግብረገብነትን፤ በጎ አድራጎትንና  መልካም ስብእና ያለው ሕብረተሰብን የመፍጠር ዓላማ ባለው መመሪያ ላይ ራሱን በማቆም ሕግና ደንብ አውጥቶ መሥራት መጀመሩን የተጻፈ ታሪኩ ያስረዳል። 

  ምንም እንኳን የፍሪማሰንሪ ማኅበር በኦፊሴል ከአምልኮና ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ ነኝ ቢልም በ1723 እና በ1738 ዓም ተሻሽሎ በወጣው የፍሪማሰንሪ ሕገ መንግሥት ላይ እንደተመለከተው የሁሉም ነገር ንድፍ / architect/ ባለቤት «እግዚአብሔር ነው ስለሚል እንቅስቃሴው ሃይማኖት ለበስ እንደሆነ ፍንጭ ከመስጠቱም በላይ ድርጅቱ የራሱ የሆነ ዶግማና መመሪያ ስላለው የእምነት ድርጅት አይደለሁም የሚለው አባባሉ ተቀባይነት እንዳይኖረው አድርጓል።  ድርጅቱ የአንድ ወጥ የሃይማኖት ተቋም ላለመሆኑ እንደመከራከሪያ የሚያቀርበው ጭብጥ የፍሪማሰንሪ አባል ለመሆን  የየትኛውንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም የሃይማኖት መጽሐፍ ተቀባይ ወይም የትኛውንም የፖለቲካ መስመር የያዘ ሰው በአባልነት መቀበል መቻሉን በማስረጃነት ያቀርባል።  ድርጅቱ ይህንን ይበል እንጂ አባል የሚሆን ሰው ቀድሞ የነበረውን እምነቱን ይሁን አመለካከቱን እንዲጥል ሳይገደድ የፍሪማሰንን አስተምህሮና ሕግ በተከታታይ ተምሮ በድርጅቱ የረቀቀ አስተሳሰብ ውስጥ እንዲሰጥም ማድረግ በራሱ ቀድሞ የነበረውን የማስቀየር ዘዴ እንደሆነ በተሞክሮ ያዩት ሰዎች በተግባር ያረጋገጡት ሀቅ ነው።

    እንደፍሪማሰንሪ አባባል የጥበቦች ሁሉ /Architect/ የንድፍ ባለቤት እግዚአብሔር ሲሆን ያገኙትን ጥበብ ወደተግባር የሚለውጡት ደግሞ የፍሪማሰንሪ እውቀት የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው ይላሉ። ለምሳሌም የኖኅ መርከብ የተሰራቸው በኖኅ የፍሪማሰን እውቀት ነው። የባቢሎን ግንብ ይሁን የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ያለፍሪማሰን እውቀት ፍጻሜ አያገኝም ነበር ባዮች ናቸው። የግብጽ ፒራሚዶች የፍሪማሰን ጥበብ ውጤት ነው። የኖስቲኮች እውቀት፤ የግሪክ ፍልስፍና፤ የፓይታጎረስ ስሌት፤ የዞሮአስተር ትምህርት፤ የቻይና ጥበብ፤ የአልኬሚስቶች ፈጠራ ሁሉ በፍሪማሰን እውቀት ጎልምሶ ወደተግባር የተለወጠ መሆኑን ያምናሉ። 

   ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የፍሪማሰንሪ ድርጅት አባል ሲመለመል የትኛውንም ሃይማኖት የሚከተል ወይም የትኛውንም የሃይማኖት መጽሐፍ የሚቀበል ሰው መሆኑ ችግር የለውም። እንዲተውም አይጠበቅም። ቁምነገሩ አንድ ጊዜ የፍሪማሰንሪ ድርጅት አባል ከሆኑ በኋላ ድርጅቱን መልቀቅ እንደማይቻል ወይም በምክንያት ከለቀቁ ደግሞ የቆዩበትን የድርጅቱን ምስጢር ማውጣት የሞት ዋጋ እንደሚያስከፍል አስቀድሞ ቃለመሃላ ይፈጽማል። ፍሪማሰንሪ በስብከትና በድለላ የአባልነት ምልመላ አያደርግም። አብዛኛው የዚህ ድርጅት አባላት ፕሬዚዳንቶች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ ዶክተሮች፤ ፕሮፌሰሮች፤ ጀነራሎች፤ ዳኞች፤ የሴኔትና የምክር ቤት አባላት፤ ቢሊየነሮች፤ ታዋቂ ሰዎችና ከፍተኛ ነጋዴዎች ናቸው። ከአሜሪካ 44 ፕሬዚዳንቶች ውስጥ 14ቱ የፍሪማሰንሪ ድርጅት አባላት እንደነበሩ በግልጽ ሲታወቅ  ከተቀሩትም ውስጥ በምስጢራዊ አባልነት የነበሩ እንዳሉ ይነገራል።

ፍሪማሰንሪ ካሉት 330 (ሠላሳ ሦስት ድግሪ) ማእርጋት አንዱ በሆነው የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ የተወሰኑ ትምህርቶችን አስቀድሞ ከወሰደ በኋላ ወደድግሪ ትምህርቱ ሲገባ ይህንን መሃላ ይፈጽማል።

« ዛሬ የፍሪማሰንሪ አባል ከሆንኩ በኋላ አባል ለሆንኩበት ድርጅት ካልታመንኩ ወይም ብከዳ ወይም ምስጢር ባወጣ በጎሮሮዬ ላይ ስለት ይረፍ፤ ምሳሴ ከስሩ ተነቅሎ ይጣል፤ አጽሜ አመድ ሆኖ ከውቅያኖስ የጥልቁ አሸዋ ውስጥ የተሰወረ ይሁን» ይላል። ለምን?

የፍሪማሰንሪ ዓርማና ሌሎች ምልክቶች ምንድናቸው? ከኢሉሚናቲ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? ይህንንና ሌሎች ምስጢሮችን በቀጣይ ክፍል ለማቅረብ እንሞክራለን።

Monday, November 17, 2014

«ጌታ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን» (ዮሐ. 12፥21)

“ንፈቅድ ንርአዮ ለእግዚእ ኢየሱስ - ጌታ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን”
 (ዮሐ. 12፥21)
( ከጮራ ድረ ገጽ የተወሰደ)
ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል መጥተው የነበሩ የግሪክ ሰዎች ለሐዋርያው ፊልጶስ ያቀረቡት ሐሳብ ነው። ፊልጶስም ለእንድርያስ ነግሮት ኹለቱም ለኢየሱስ መጥተው የሰዎቹን መሻት አወሩለት። ጌታም፥ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” አለ። በዚህ መስተጋብር ውስጥ በተለይ ኢየሱስን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችንና ለእነርሱ ኢየሱስን ማሳየት የቻሉ አገልጋዮችን መመልከት እንችላለን።
ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚፈልጉና ኢየሱስን ከፈላጊዎቹ ጋር የሚያገናኙ ምን ያኽል ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት ይኖርብናል። በዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን እየታየ ያለው አንዱ ችግር፥ ጌታ ኢየሱስን የሚፈልግ ምእመንና እርሱን የሚያሳይ አገልጋይ ቍጥር እየተመናመነ መምጣቱ ነው። ርግጥ የምእመናን የልባቸው መሻትና የነፍሳቸው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ብዙዎቹ አገልጋዮች ግን ዕረፍተ ነፍስ ወደ ኾነው ጌታ ምእመናኑን ማድረስ ሲገባቸው ወደ ራሳቸው ይስቧቸዋል። በዚህ ምክንያት ምእመናን የክርስቶስ ተከታዮች ሳይኾኑ የእነርሱ ተከታይና አድናቂ እንዲኾኑ፥ ክርስቶስን ሳይኾን እነርሱን እንዲመለከቱ፥ የሕይወታቸው ዋና ምሳሌም ክርስቶስ ሳይኾን አገልጋዮቹ እንዲኾኑ በማድረግ፥ ኢየሱስን ፈልገው የመጡትን ምእመናን ወደ ኢየሱስ ሳያደርሷቸው እነርሱ ዘንድ በማስቀረት የእነርሱ ሎሌ ያደረጓቸው አገልጋዮች ጥቂቶች አይደሉም። 

እንጠብቀዋልን ብለው ከጌታ በዐደራ የተቀበሉትን መንጋ የራሳቸው የግል ንብረት በማድረግ በተሳሳተ መንገድ ስለ መሩት፥ ብዙው ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያንም ኾነ ወደ መንፈሳውያን ጉባኤዎች የሚኼደው ክርስቶስን ለማየት ሳይኾን ተከታዮቻቸው ያደረጓቸውን አገልጋዮች ለማየትና ለእነርሱ ለመገበር ይመስላል። ይህ ለምእመናን ትልቅ ኪሳራ ለአገልጋዮቹም ከባድ ቅጣትን የሚያስከትል ዐደራ በልነት ነው።
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ብቻ ሙሽራ ናት። ዘወትር ልትፈልግና ልትሻ የሚገባት ውዷን ኢየሱስን ብቻ መኾን አለበት። ጌታ ለሙሽራው ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን የሰጠው ለቤተ ክርስቲያኑ እንጂ ለአገልጋዮቹ ጥቅም እንዳልኾነም ሊታወቅ ይገባል። አገልጋዮቹ በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲሠለጥኑባት፥ ትልቅ ስምና ዝናን እንዲያገኙ፥ እንዲበለጽጉና የመሳሰለውን ምድራዊ ትርፍ እንዲያተርፉ አይደለም። ቃሉ እንደሚመሰክረው፥ ጌታ አገልጋዮችን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መኾን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚኾን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይኾኑ ዘንድ” ነው (ኤፌ. 4፥12-13)። ስለዚህ አገልጋዮች ይህን ተረድተው ለተሰጣቸው ተልእኮ መፋጠንና ኀላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው።
ምእመናንም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የእነርሱ መጋቢዎች እንጂ አምላኮቻቸው እንዳልሆኑ ዐውቀው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆነውን ትምህርታቸውን ሊቀበሉ፥ የሕይወታቸውን መልካም ምሳሌነት ሊከተሉ፥ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከቱ በእምነታቸው ሊመስሏቸው ይገባል። ከዚህ ዐልፈው እነርሱን በማክበር ስም ከማምለክ ያልተናነሰ ተግባር በመፈጸም የመጥፎ ሥራቸው ተባባሪ መኾን የለባቸውም። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚሹ ምእመናን ኢየሱስን የሚያሳዩ አገልጋዮች በእጅጉ ያስፈልጋሉ።

ዐዲሱ ዓመት ጌታን የምንፈልግበት ጌታን የምናሳይበት ዓመት ይሁንልን
(በጮራ ቍጥር 46 ላይ የቀረበ)

Wednesday, November 12, 2014

ግብረ ሰዶማዊነትና የእኛ ዘመን አገልጋዮች

( ከአቤኔዘር ተክሉ )

    ስለግብረ ሰዶማዊነት በሁለት የተለያዩ ክፍሎች መጻፌና በሁለቱ ክፍሎችም ለጊዜው የነበረኝን ሃሳብ ማጠቃለሌን አልዘነጋውም፡፡ ነገር ግን አሁንም ግብረ ሰዶማዊነት የቤተ ክርስቲያንን ቅድስና ከማርከስ፤ ምድራችንን ለከፋ ጉስቁልናና ርኩሰት አሳልፎ ከመስጠት ያላቆመ ፍጹም ወደመስፋፋት የሄደ ክፉ ርኩሰት ነውና ዳግም ይህንን ርዕስ ማንሳት አስፈልጎኛል፡፡ ለዚህ እውነታ ብዙ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ብቻ ማንሳቱ በቂ ይመስለኛል፡፡

    ድርጊቱ የተፈጸመው በምስራቁ የሃገራችን ክፍል ነው፡፡ የሠላሳ ሁለት አመት አጐት የአራት አመት የወንድም ልጁን በእረኝነት ሥፍራ በመሄድ ጫት እንዲቅም ያግባባዋል፡፡ ህጻኑ እንቢ ቢልም ያስገድደዋል፡፡ ጫት እንዲቅም ካስገደደው በኋላ ልጁ ራሱን መቆጣጠር ሲያቅተው ልጁን የግብረ ሰዶም ጥቃት ይፈጽምበታል፡፡ የልጁ የሰገራ ማውጫ ሙሉ ለሙሉ ይቀዳዳል፡፡ ከሆዱ የወጣው የውስጠኛው የሰገራው ክፍል ሙሉ ለሙሉ የልጁን ጠረን ይለውጠዋል፡፡ ልጁ ፍጹም ራሱን ስቶ ሲወድቅ ከወደቀበት ቦታ ተሸክሞት ከወላጆቹ ጓሮ አምጥቶ ጥሎት ይሰወራል፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የልጁ ህይወት ያልፋል፡፡

    ሌላም ብንጨምር፦ አንድ “ስመ ገናና” አገልጋይ እንዲህ ያለ ነውር እንደሚፈጽም በምስክር ይረጋገጥና ብዙዎች ተረባርበው ሊመክሩት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ከማስመሰልና የሽንገላ እሺታ ከማሳየት በቀር ከነገሩ ሳይታቀብ ይቀራል፡፡ በኋላ ይባስ ብሎ በአቋም፤ የሠራው ትክክል እንደሆነና ይቅርታ መጠየቅ እንደማያስፈልግ ከብዙ ደጋፊዎቹ ጋር በግልጥ በአቋሙ ይጸናል፡፡ ወንድሞቹን ይቅርታ ሳይጠይቅ በግልጥ ለሠራውና ሌሎችን ላሰናከለበት ኃጢአቱ ንስሐ ሳይገባ እንደዋዛ ዛሬም አለ፡፡ በድርጊቱ የተጠቁት ወንድሞች ግን “እንዲህ ያለ ነገር እያደረገ በአንድ የኃይማኖት ጥላ ሥር አንቀመጥም” በማለት ወደሌላ የእምነት ተቋም ራሳቸውን አገለሉ፡፡ (ርቀው ወደሌላ የኃይማኖት ተቋም እንዳይሄዱ ብዙ ርብርብ ቢደረግም አልተሳካም፡፡)

    በመንግስትም ደረጃ በዘንድሮው የይቅርታ መመሪያ ውስጥ ይቅርታ ከሚያሰጡ ወንጀሎች መካከል ግብረ ሰዶማዊነትም እንዲካተት ጥረቶች “መደረጋቸውና መሳካቱንም” ጭምጭምታዎች ይሰማሉ፡፡ ጉዟችን ወዴት ይሆን? እንዲህስ እስከምን ድረስ ነው የምንጓዘው?

      ግብረ ሰዶማዊነት እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ሙሉ ለሙሉ በመቃረን የሚፈጸም ርኩሰት ነው፡፡ ቃሉም “ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው”(ሮሜ.1፥24) እንዲል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ፍጥረት በመቃረናችን ምክንያት የገዛ ኃጢአታችን “ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ እንደሰጠን” ትልቅ ምስክር ነው፡፡(ሮሜ.1፥26)

   ጥቂት የማይባሉ አገልጋዮች “ለአገልግሎት” ወደክፍለ አገር ወይም ወደውጪ አገር ሲወጡና ጨርሰው ሲመለሱ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ሹልክ ብለው ለሴሰኝነትና ለዝሙት እንደሚገባበዙ ፀሐይ የሞቀው እውነት ሆኗል፡፡   በአቶ አስማማው ኃይሉ በተጻፈውና “ኢህአሠ” በተባለው ቅጽ አንድ መጽሐፍ ላይ ከትግል መልስ ደራሲው አንድ ታጋይ ነገረኝ ብሎ ሲጽፍ ፤ ታጋዩ ማደሪያ አገኘሁ ብሎ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ሊጠለል ጎራ ባለበት ወቅት ሌሊቱን ሙሉ  የገጠመው ሌላ ትግል ይኸው ከግብረ ሰዶማውያን ጋር ያደረገው ያለመደፈር ትግል እንደነበር በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ በእርግጥ ዛሬ በገዳም ካሉት ጥቂት የማይባሉ መነኰሳትና መነኰሳይያት፤ እንዲሁም  በወንዶችም ሆነ በሴቶችም ዘማሪዎቻችን መንደርም የምንሰማው ነገር ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡ (እንደአገር ስናስብ ደግሞ በካርዲናሎቹና በፓስተሮቹም መካከል አጸያፊ የርኩሰት ነገር ጆሯችን ከመስማት አልታከተም!!)   

     ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ኃጢአተኞችን በግልጥ ከመቃወም እየደከመች የመጣች ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የግብረ ሰዶማውያን “አገልጋዮችን” የጨለማ ሥራን ከመግለጥ (ኤፌ.5፥11)፤ ሌሎች ሰዎችም ከክፋታቸው እንዳይተባበሩ ከማስጠንቀቅና መክራ እንዲመለሱ ከማድረግ ድምጿን አሰልላለች፡፡ ስለዚህም ሌሎች ብዙዎች ግብረ ሰዶማውያኑን  “በርቱ፤ እኛም ከጎናችሁ ነን” ከማለት አልፈው ለግብረ ሰዶማውያኑ ድጋፍ ሲሰጡና ሲሟገቱላቸው በአይናችን እያየን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ኩልልና ጥርት ያለ የተቃውሞ ድምጿን ልታሰማ ግድ የሚላት ጊዜ አሁንና አሁን ነው፡፡ ከረፈደ በኋላ መሯሯጥ ድካም እንጂ ሚዛን የሚደፋ ትውልድ የማዳን ሥራ አይሠራም፡፡

    የሰዶም ሰዎች ያደርጉት የነበረው የክፋት ድርጊታቸውን እንደመልካም ከመቁጠር አልፈው እነርሱ የሚያደርጉትን ነውር የማያደርጉትን ሰዎች ይቃወሙ፤ የእነርሱን ነውር እንዲቀበሉ ያደርጉም ነበር፡፡ በአገሪቱ ካሉት ሰዎች ሁሉ ጋር ነውራቸውን ከፈጸሙ በኋላ  እንግዳ ሰዎች በመካከላቸው በተገኙ ጊዜ ከእንግዶቹ ጋር ሊፈጽሙ (በሎጥ ቤት የመጡትን መላዕክት ሲያዩ ወደአዲስ መጎምጀት መጥተዋልና!) የኃይልን መንገድ እንደተጠቀሙ፤ ጻድቁንም ሎጥ እንደተጋፉትና በሩን ሊሰብሩ እንደተገዳደሩ ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡(ዘፍ.19፥5-9) ሰው ለእግዚአብሔር ባህርይና ለተፈጥሮ እውነት መገዛት ሲሳነው የኃጢአት መሻቱ ድንበር አልባ ይሆናል፡፡ ሁሉንም ርኩሰት ከመፈጸም የሚያግደውም የለም፡፡

   ዛሬ ላይ ድሆች ሃገራትን ለመርዳት የሚዘረጉ ብዙ የእርዳታ እጆች ስውር አጀንዳቸው ግብረ ሰዶምና ሰዶማዊነት ለመሆኑ ብዙ ማስተንተኛ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ግብረ ሰዶምን በግልጥ የተቃወመች ብቸኛይቱ አፍሪካዊት ሃገር ይህንን በግልጥ አይታዋለችና፡፡ እኛ “ከቃል ባልዘለለ” ክርስትናችን በከንቱ ስንመካ ከአገራችን ቀድማ ግብረ ሰዶማዊነትን በግልጥ አለም አቀፍ በሆነ ዕይታ ህግን አስደግፋ ተቃውሞ ያሰማችው አፍሪካዊት አገር ኡጋንዳ ናት፡፡ በእርግጥ የእኛ ወንጀል ህግ “ግብረ ሰዶማዊነት ወንጀል ነው” ይላል፤ ግን የአገሪቱን ትልልቅ ከተሞች ጎዳና እያጥለቀለቁ ያሉትና ቁጥራቸው የማይናቅ አገልጋዮችን እንደወረርሽኝ በሽታ እየወረሱት ያሉት “ሴት እንተኛ አዳሪዎች” ብቻ ሳይሆኑ ግብረ ሰዶማውያኑም ጭምር ናቸው፡፡ ህጉ ቢኖርም ለነዚህ ምድርን ለሚያረክሱ “ወገኖች” ግን ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

   የኡጋንዳ መሪዎች ያንን የመሰለ ቁርጥ ያለ አቋማቸውን በግብረ ሰዶማዊነት ላይ ሲያሰሙ፤ ሰለጠን ያሉቱ ምዕራባውያን የኡጋንዳን ድርጊት “የሰይጣን ድርጊት” አድርገው ለማቅረብ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ (እግዚአብሔርስ ይቅር ሰይጣን እንኳ እንዴት ታዝቦን ይሆን?!)  የእኛ አገልጋዮች ግን ዛሬም ግብረ ሰዶማዊነትን በመካከላችን ያሽሞነሙኑታል፡፡ ከዓመታት በፊት ግብረ ሰዶማውያኑም አለም አቀፍ ስብሰባ አፍንጫችን ስር ባለችው አዲስ አበባ አድርገው አባላታቸውን መልምለው ሲሄዱ እንኳ ዝም ጭጭ ሆኗል ክርስትናችን፡፡ እንኪያስ ወርቁ ለምን ይሆን የደበሰው?
   ግብረ ሰዶማውያንን ለመቃወም የአገልጋዮች “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት ከበለጠብን እንኪያ እኛስ ከእነርሱ በምን እንሻላለን? መንፈሳዊነት መለኪያው የአገልግሎት ስኬት ሳይሆን የህይወት ጥራት ነው፡፡ ጌታ ጥራት ከሌለው ሸንጋይ መንጋ ጋር ህብረት እንደሌለውና ጥራት ካለው ጥቂት አማኝ ጋር ብቻ ህብረት እንዳለው በጌዴዎንና በሐዋርያት ህይወት አይተናል፡፡ ምክራችን፣ ጩኸታችን፣ ተግሳጻችን፣  ቁጣችን … “ምክር ለምኔ” ያሉ ግብረ ሰዶማውያን አገልጋዮች በንስሐ ተመልሰው የበደሏቸውንና ያሰናከሏቸውን ወንድሞች ይቅርታ በመጠየቅ እንዲመለሱ ነው እንጂ በመካከላችን ተቀምጠው ሌሎችን ለማጥቃት እንዲያደቡ አይደለም፡፡

    የእግዚአብሔርን ምህረት የሚያሸንፍ ወይም የሚበልጥ ኃጢአት የለም፡፡  እንዲህ የምንለው ግን በንስሐ ለሚመለሱ እንጂ ልብን ለሚያደነድኑ አመጸኞች አይደለም፡፡ ጌታ ለምድሪቱ ምህረትና የንስሐን ልብ ያውርድላት፡፡ አሜን፡፡