Thursday, August 28, 2014

«ፍትሕን ለግል ስሜት መወጫ ማድረግ የቱን ያህል ለትውልድ መተዛዘቢያ ሆኖ የተሰወረ ሊሆን አይችልም» አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ለአፄ ኃ/ሥላሴ በ1957 ዓ/ም ከጻፉት ደብዳቤ







ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

አዲስ አበባ

ግርማዊ ሆይ፣

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሕይወት የሚታየውን ምሬትና ግፍ፣ የፍትሕም መጓደል ምክንያት በማድረግ ወደ አገሬ ለመግባት ያለኝን አሳብ ማቆየት ግድ እንደሆነብኝ ለግርማዊነትዎ መግለጥ አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚታረምበትን በኅብረት ለመሥራት ባንሞክር ታላቅ ብጥብጥ እንደሚያስከትልብን ከታሪክ መማር ካልቻልን፣ ከተከታዩ መቅሰፍት የምናመልጥበትና የምንከለልበት ሰው ሠራሽ ዘዴ ይገኝለታል ብሎ ራስን መደለል በሕልም ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደ መፈተን ይቆጠራል፡፡
ከዚህም በቀር ለተተኪው ትውልድ አቋም ይሆናሉ ብለን ተከባክበን ልናሳድጋቸው አላፊነት ያለብንን ሕፃናትና ውለታ ትተው ለማለፍ የተደራጁትን ሽማግሎቻችንንም ደህና ዕረፍት እንዳያገኙ ከአገሪቱ በተፈጥሮ ያገኙትን ዕድል መንፈግ ያሰኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በፈጸምነው ስህተት ታሪክ ምሕረት ሊያደርግልን በፍጹም አይችልም፡፡
ይህን የመሳሰለው ሁኔታ በብርቱ የሚያሳስበን መሆኑን ስንገልጥ ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ‹‹አንተ ምን አገባህ?›› በማለት በጉዳዩ ባለቤትነት ክፍያ ድርሻችንን ለማሳነስ ቢሞክሩም በኢትዮጵያዊነት ትክለኛ መብት ላይ አጥብበው ያሰመሩትን የወሰን ክልል አሜን ብሎ ለመቀበል ከቶ ስለሚያስቸግር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አላፊነቱን የማስወረድ ተግባር እንዳለበት አይካድም፡፡ እኔም ይህን ምክንያት አድርጌ በአሁኑ የመንግሥት አስተዳደር የደረሰውን ሕገ ወጥ አፈጻጸም ሁሉ ለማረምና ፍትሕን ለማደላደል የሚቻልበትን አሳብ በነፃ ለመግለጥ ስል እውጭ አገር መቆየትን መረጥሁ፡፡
በአሁኑ አያያዝ እንዲቀጥል የተተወ እንደሆነ በኢትዮጵያ የወገን መለያየትና የደም መፍሰስ እንደሚያሠጋ የመላው ኢትዮጵያውያን ግምት የወደቀበት ነው፡፡ ዋናው አላማ ይህ እልቂት የሚወገድበት መድኃኒቱ ምንድነው? ለተባለው ጥያቄ ለመመለስ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ መቸም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚመስለውና በሚያምንበት ረገድ መልሱን ለመስጠት ሞክሯል፡፡ አሁን የጐደለ መስሎ የሚታየው ከዙፋኑ በኩል የሚጠበቀው ይሁንታ ብቻ ነው፡፡ ነገሩን በመጠኑ ለማብራራት ያህል በሚከተሉት መስመሮች አስተያየቴን ለመግለጥ እሰነዝራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዙፋኑ የሰጠው ልባዊ አክብሮት ዘላቂ ሆኖ በታሪካዊ ቅርስነት እንዲጠበቅ በቤተ መንግሥቱ በኩል አልታሰበበትም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ባለፈው ‹‹መለኮታዊ መብት›› የተባለው የዘውድ ቴዎሪ የተሳሳተ መሆኑን ቢረዳውም፣ ሕዝቡ፣ ዘውዱን ታሪካዊ ሲምቦል ወይም ምሳሌ አድርጐ በክብር ሊያኖረው ሲፈቅድ ወደ መለኮታዊ መብት አስተያየት እንደገና እንዲመለስና ጣኦታዊ ስግደት እንዲያደርግ ማስገደድ፣ በእልህ ዘውዱን ለማስረገጥ ካልሆነ በቀር ለሌላ አያገለግልም፡፡
ጃንሆይ፣ ባለዘውድ፣ አስተዳዳሪ፣ ሕግ አውጭ፣ ዳኛ፣ ምስለኔ፣ ፖሊስ፣ ጭቃ ሹም ሆኜ ልሥራ ሲሉ፣ በ፳ኛው [20ኛው] ክፍለ ዘመን የሚገኝ ሕዝብ ይህን መብት አጠቃሎ በፈቃዱ ለዘውዱ ብቻ ይለቃል ማለት የማይታመን ነው፡፡ መቸም እየተደጋገመ የሚሰጠው ምክንያት ‹‹ሕዝቡ ኃላፊነትን ለመቀበል አልደረሰም›› የሚል መሆኑን በየጊዜው ሰምተናል፡፡ በውነቱ ከአፍሪካና ከኤሻ ሕዝብ መካከል አልደረሰም ተብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ መፍረድ ይገባልን? ደግሞስ ያለመድረስ ትርጓሜው ምንድነው? ምናልባት የማሰብ፣ የመምረጥ፣ የማመዛዘን፣ የመፍረድ ሴንስ አልተፈጠረለትም ማለት ነው? እንደዚህማ ከሆነ በ፫ሺሕ [በ3 ሺሕ] ዘመን ውስጥ ለዚህ ሕዝብ ጭንቅላት ሆኖ ያሰበለት፣ ዓይን ሆኖ ያየለት፣ ጆሮ ሆኖ የሰማለት የዛሬው ዘውድ ነው ማለት ነዋ! የሚፈተነው ይህን የመሰለ አስተያየት ለማቅረብ እንደሆነ ምሕረት የሌለው በደል ነው፡፡
ይልቁንስ ጃንሆይ የሕግ ጠባቂነትን ልብስ ተጐናጽፈው በዚህ መንፈስ ፍትሕን ከሚያጓድሉ፣ ሥልጣኑን ለሕዝብዎ ሰጥተው እርሱ ቢጨነቅበት እንደሚሻል ጥርጥር የለውም፡፡ ያለዚያ ከዚህ ማስታወሻዬ ውስጥ ለስማቸው እንኳ ሥፍራ ለመስጠት ዋጋ የሌላቸውና ሕሊና ቢሶች የሚያቀርቡልዎትን ‹‹ደህና ታይቷል›› እያሉ ፍትሕን ለግል ስሜት መወጫ ማድረግ የቱን ያህል ለትውልድ መተዛዘቢያ ሆኖ እንደሚኖር የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡
ይህን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ለማሻሻል የሚቻለው ጃንሆይ ዘውዱን ለራስዎ አስቀርተው አስተዳደሩን ለሕዝብ በመስጠትና የዴሞክራሲን መንፈስ በማስገባት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አስተያየት ለግርማዊነትዎ ሰውነት አለርጂ ሆኖ ቢያስቸግርም እንኳ ሌላ ማማረጫ ይኖራል፡፡ ይኸውም ዘውዱን ለልዑል አልጋ ወራሽ ማስተላለፍና አብዲኬት ማድረግ ነው፡፡ እርሳቸው ሕገ መንግሥት ጠብቀው ለመኖር ፈቃደኛ እንደሆኑ አያሌ ሰዎች ሲመሰክሩላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ያለዚያ ተከታዩ ትርምስና ደም መፋሰስ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
ይህ አቤቱታ ከኔ ብቻ የቀረበ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርኃት ታፍኖ ነጋም መሸም የሚያጕተመትመው ይህንኑ ነው፡፡ ድምፁን ከፍ ለማድረግ ግን አካባቢው አልፈቀደለትም፡፡ እኔም ከርሱ የተለየሁ መስዬ ታይቼ እንደሆነ ያጋጣሚ ነገር ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ የታፈንኩትን ያህል እዚህ ከተነፈስሁ በኋላ ወደ አገሬ እንድመለስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምናልባት ይህን አቤቱታ በመጻፌ እወነጀል ይሆናል፡፡ ግድ የለም፡፡ የሆነ ሆኖ በትእዛዝ ሳይሆን በነፃ የሚፈርድና በግልጽ የሚያስችል ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ራሴን በሕጋዊ ጠበቃ አማካይነት ለመከላከል ጃንሆይ የሚፈቅዱልኝ ከሆነ በአገሬ ውስጥ ለመተንፈስ ዕድል ተሰጠኝ ማለት ነው፡፡
ከዚህም ሁሉ ጋር ላስታውሰው የምፈቅደው፣ ይህን ማስታወሻ በመጻፌ ተቀይመው የእኔን ሕይወት ለማስጠፋት በሺሕ የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም፡፡ አዝናለሁ፡፡ እኔ ለሞት የተዘጋጀሁ ስለሆነ ገንዘቡ ባይባክንና ለነፍሰ ገዳይ በመስጠት ፈንታ ለጦም አዳሪ ችግረኛ ቢውል የበለጠ እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም፡፡ በበኩሌ በአገራችን ሬሾሉሽን እንዲነሣና የማንም ደም እንዲፈስ አልፈቅድም፡፡ በዚህ ባቤቱታዬ የምወተውተውም ሰላማዊ ለውጥ እንዲሆንና የምንፈራው ደም መፋሰስ እንዳይደርስ ስለሆነ ጃንሆይ አንድ ቀን ‹‹ለካ ብርሃኑ ውነቱ ኖሯል!›› ሳይሉ አይቀርም፡፡
እንኳን ዘውድ የጫነ ሰውነትንና ማናቸውንም ሰው የማክበር ልምድ ስላለኝ፣ ይህ አቀራረቤ ክብርን ለመድፈር እንደማያስቆጥርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ውነት ሁል ጊዜ መራራ ናት፡፡ የመድኃኒት ፈውሱ እንጂ ምሬቱ አይታሰብም እንደተባለው ይህ በቅን ልቡና የቀረበው ውነተኛ አቤቱታዬ የግርማዊነትዎን ልብ አራርቶ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሕይወት አንድ ፈውስ እንዲያመጣለት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ጃንሆይ! በኢትዮጵያ ወጣቱ ሽማግሌው ሴቱ ወንዱ የአኗኗሩ ዘዴ ውሉ ተዘባርቆበታል፡፡ አምላካችን፣ ፈጣሪያችን እያለ ቢደልልዎት አይመኑት፡፡ ጨንቆት ነው፡፡ ከልብ የሚመርቅዎት ግን ራስህን አስተዳድር ብለው አርነት ሲያወጡትና ወደ ዴሞክራሲ ሲመሩት ነው፡፡ ይህንንም ስል ሕዝብ በራሱ ሲተዳደር ችግር አይገጥመውም ማለቴ አይደለም፡፡ እስከዚህ አልሳሳትም፡፡ ነገር ግን ሌላው ለፍቶ ከሚጥለውና ላንሣህ ከሚለው፣ ራሱ ወድቆ በራሱ መነሣትን ይመርጣል፡፡ ይኽም በሥሕተት መማር ይባላል፡፡ ስለዚህ ጃንሆይም ተሳሳቱ እያለ ከሚከስዎት እርሱ ለሥሕተት እንዲጸጸትና እንዲማር ቢያደርጉት ትልቅ ውለታ ይቆጠራል፡፡
የዛሬው ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስገንባት የሚረዳ ካለመሆኑም በላይ ያንኑም ቅሉ አክብሮ ለመጠበቅ በአንቀጽ ፳፩ [21] እንደተመለከተው ከንጉሠ ነገሥቱ በመሐላ የተሰጠው ቃል ፈርሷል እያሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን እንደሚያማርሩ ግርማዊነትዎ ሳይሰማው አይቀርም፡፡ መቸም ሕገ መንግሥቱን፣ ለመጣስ አንድ የጽሕፈት ሚኒስቴር ደብዳቤ ይበቃል፡፡ እንግዴህ ሕዝቡ ወይም ሹማምቱ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ ነኝ እያሉ ቢምሉም፣ ንጉሠ ነገሥቱ በበኩሉ መሐላውን የሚጠብቅ ካልሆነ በመሐላቸው ታስረው እንደማይኖሩ በልጅ ኢያሱ ጊዜ የደረሰው ሁኔታ ምሳሌ ሊሆን ይችል ይመስለኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የገጠመንን ፕሮብሌም እንደ መጠኑ ለመግለጥ ‹‹በግርማዊነታቸው መንግሥት ያገኘሁት ኤክስፔሪያንስ›› የሚለው መጽሐፌ በሙሉ ታትሞ እስከወጣ ድረስ ፲፪ኛውን [12ኛውን] ምዕራፍ ከዚህ ጋር አያይዤ ለግርማዊነትዎ በትህትና አቀርባለሁ፡፡

                          ዋሽንግተን ግንቦት ፳፭/፶፯ [ግንቦት 25/57]
                                ከታላቅ አክብሮታዊ ፍርሐት ጋራ
                                          ብርሃኑ ድንቄ


Friday, August 22, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

 (ዘርዓ ያዕቆብ ፈላስፋ

ስለ አምላክ  ሕግና ስለ ሰው ሕግ

እግዚአብሔር  የገዛ  ሕዝቡን  እንዲያስቷቸው  ስለምን  ዋሾ  ሰዎችን  ይተዋል  ብዬ  አሰብኩ፡፡  እግዚአብሔር  ግን  ለሁሉም
ለእያንዳንዱ  እውነትንና  ሐሰትን  እንዲያውቅ  ልቦና  ሰጥቶናል፡፡  እውነት  ወይም  ሐሰት እንደፈቃዱ  የሚመርጥበት
መምረጫም ሰጠው፡፡ እውነትን ብንወድ ለፍጥረት ሁሉ አስፈላጊና ተገቢ የሆነውን እርሱም እንድናይበት እግዚአብሔር
በሰጠን ልቦናችን ውስጥ እንፈልጋት፡፡ ሰው ሁሉ ዋሾ ነውና እውነትንም በሰዎች ትምህርት አታገኟትም፡፡ ከእውነት ይልቅ
ሐሰትን ብንመርጥ ስለዚህ እኛ በስህተታችን እንጠፋለን እንጂ ለፍጥረት ሁሉ የተሰራው የፈጣሪ ሥርዓትና ሕግ አይጠፋም፡፡
እግዚአብሔር ማንንም በሠራው ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ከሰው ሥራ ግን የእግዚአብሔር ሥራ ይጸናል፡፡ የሰው ሥራ ሊያጠፋው
አይችልም።  ስለዚህም  ከጋብቻ  ይልቅ  ምንኩስናን  ይበልጣል  ብለው  የሚያምኑ  እነርሱ  በፈጣሪ  ሥራ  ጽናት  ወደ  ጋብቻ
ይሳባሉ፡፡ ፆም ነፍስን እንደሚያፀድቅ የሚያምኑ እነርሱ ደግሞ ረሃብ በበዛባቸው  ጊዜ ይበላሉ፡፡ ገንዘቡን የተወ ፍፁም
እንዲሆን  የሚያምኑ በገንዘብ  ለሚያገኙት   ጥቅም  ወደ  ገንዘብ  መፈለግ  ይሳባሉ፡፡  ብዙዎች  የሀገራችን  መነኩሴዎችም
እንደሚደርጉት ከተዉት በኋላ እንደገና ይፈልጉታል፡፡ እንደዚሁ ዋሾዎች ሁላቸው የተፈጥሮን ሥራ ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ፡፡
ነገር ግን ደካማነታቸውን ያሳያሉ እንጂ አይችሉም፡፡ ፈጣሪም ይስቅባቸዋል፡፡ የፍጥረት ጌታም በላያቸው ይሳለቅባቸዋል፡፡
እግዚአብሔር የእግዚአብሔርን ፍርድ ማድረግ ያውቃልና ኃጥአንም በእጁ ሥራ ወጥመድ  ተጠመደ፡፡ ስለዚህም የጋብቻን
ሥርዓት የሚያስነውር መነኩሴ በክፉ በሽታና ፍጥረቱ ባልሆነ በሌላ የሴት አበሳ በዝሙት ተጽዕኖ ይጠመዳል፡፡ ገንዘባቸውን
የሚንቁ  ገንዘብ  እንዲያገኙ  በሀብታሞችና  በነገሥታት  ዘንድ  ግብዞች  ይሆናሉ፡፡  ለእግዚአብሔር  ብለው  ዘመዶቻቸውንም
በሽምግልናቸውና በችግራቸውም ረዳት ባጡ ጊዜ የተዉ በነሱ ሽምግልና ጊዜ ሰውና እግዚአብሔርን ወደ ማማት፤ መሳደብ
ይደርሳሉ፡፡  እንደዚሁም  የፈጣሪን  ሥርዓት   የሚያፈርሱ  ሁሉ  በእጃቸው  በሰሩት  ወጥመድ  ይወድቃሉ፡፡  እንደገናም
እግዚአብሔር  ክፋትን፤ ስህተትን  በሰው  መካከል  ይተዋል፡፡  ነፍሶቻችን  በዚህ  ዓለም  የእግዚአብሔር ጥበብ  የፈጠረውን
የፈተና ቀን ይኖራሉ፡፡

ጠቢቡ ሰለሞን

"እግዚአብሔር  ፃድቃንን  ፈተናቸው፡፡  ወርቅ  በእሳት  እንደሚፈተን  ይፈትናቸዋል፡፡  ለእርሱ  የተዘጋጁ  ሆነውም
አግኝቷቸዋልና፡፡ እንደተወደደ ዕጣን መዐዛም ይቀበላቸዋል" ይላል፡፡
ከሞታችን በኋላም ቢሆን ወደፈጣሪያችን በገባን ጊዜ እግዚአብሔር በእውነትና በትልቅ በጥበብ ከሠራው ሁሉ እውነትና ቅን
የሆነውን መንገድ ሁሉ እንለያለን፡፡ ነፍሳችንም ከሥጋዊ ሞታችን በኋላ እንደምትድን ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓለም ውዴታችን
አይፈፀምምና የሌላቸው ይፈልጋሉ፤ ያላቸው ባላቸው ላይ እንደገና ሊጨምሩ ይፈልጋሉ፡፡ሰው በዚህ ዓለም ያለው ሁሉ
እንኳን  ቢኖረው  እንደገና  ይወዳል  እንጅ  አይጠግብም፡፡  ይህም  የፍጥረታችን  ጠባይ  ለሚመጣው  ንብረት  እንጂ  ለዚህ
ዓለም ንብረት ብቻ እንዳልተፈጠርን ያመለክታል፡፡ በዚያውም የፈጣሪያቸውን ፈቃድ የፈፀሙ ነፍሳት ፍፁም ይጠግባሉ
እንጂ ከእንግዲህ ሌላ አይወዱም፡፡ አለዚያ ግን የሰው ፍጥረት አስፈላጊውን ሁሉ አላገኝምና ጎዶሎ በሆነ ነበር፡፡ እንደገናም
ነፍሳችን  እግዚአብሔርን  ማሠብ  ትችላለችና  በሃሳቧም  ታየዋለች፡፡  እንደገናም  ለዘላለም  መኖር  ማሰብ  ትችላለች፡፡
እግዚአብሔርም ይህን ማሰብ በከንቱ አልሰጣትም፡፡ ነገር ግን እንደሰጣት ልታስብና  እንድታገኝም ሰጣት፡፡ ደግሞ በዚህ
ዓለም ፅድቅ ሁሉ አይፈፀምም፡፡ ክፉ ሰዎች ከዚህ ዓለም መልካም ይጠግባሉ፡፡ ደጋጎች ይራባሉ፡፡ የሚደሰት ክፉ አለ፣
የሚያዝን ደግ አለ፣ የሚደሰት ዐመፀኛ አለ፣ የሚያለቅስ ፃድቅም አለ፣ ስለዚህም  ከሞታችን በኋላ ለሁሉ እንደየምግባሩ
የሚከፍለው  ሌላ  ኑሮና  ፍፁም  ፅድቅ  ያስፈልጋል፡፡  በብርሃን  ልቦናችን  ተገለፀላቸው፡፡  የፈጣሪን  ፈቃድ  የፈፀሙና
በተፈጥሯቸውም ፀባያዊ ህጉን የጠበቁ ዋጋቸው ይከፈላቸዋል፡፡ የተፈጥሮን ሕግ ከመረመርን የተረጋገጠ መሆኑን ልቦናችን
በግልፅ  ይነግረናል፡፡  ነገር  ግን ሰዎች  ሊመረምሩ  አልፈለጉምና  የፈጣሪያቸውን  ፈቃድ በእውነት  ከመፈለግ  የሰዎችን  ቃል
ማመን መረጡ፡፡

 ስለ ባህሪያዊ ዕውቀት

የፈጣሪ ፈቃድ ግን ለእግዚአብሔር ለፈጣሪህ ስገድ ፣ ሰውንም ሁሉ እንደነፍስህ አፍቅር ይላል፡፡ ይህ በልቦናችን እውነት
መሆኑ  ይታወቃል፡፡  እንደገናም  በልቦናችን  እውነትነቱ  የሚታወቅ  ሌላ  እውነት  "ሊያደርጉብህ  የማትፈልገውን  በሰው
አታድርግ፡፡  ላንተ  ሊያደርጉልህ  የምትፈልገውን  አድርግላቸው"  ይላል፡፡  የሰንበትን  ማክበር  የሚለው  ካልሆነ  በቀር  ዐሥሩ
የኦሪት  ትዕዛዛት  የፈጣሪ  ናቸው፡፡  ሰንበትን  ለማክበር  ግን  ልቦናችን  ዝም  ይላል፡፡ ልንገድልና  ልንሰርቅ፣  ልንዋሽና  የሰው
ሚስት  ልንሰርቅ  ይህን  የሚመስለውን  ልናደርግ  እንደማይገባን  ልቦናችን  ይነግረናል፡፡ እንዲሁ  ስድስቱ  የወንጌል  ቃላት
የፈጣሪ  ፈቃዶች  ናቸው፡፡  እኛ  ይህን  የምህረት  ሥራ  ሊያደርጉልን  እንፈልጋለን፡፡  በሚቻለን  ለሌሎች  ልናደርግላቸው
ይገባናል፡፡ ደግሞም በዚህ ዓለም ሕይወታችን፣ ንብረታችን እንድንጠብቅ የፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ ከፈጣሪ ፈቃድ ወጥተን
በዚህ ሕይወት እንኖራለን፡፡ በተቀደሰ ፈቃዱ ካልሆነ በቀር ልንተወው አይገባንም፡፡እርሱ ፈጣሪያችን ለሁሉ ልቦናና ችሎታ
ስለሰጠ ኑሯችንን በዕውቀትና በሥራ እንድናሳምረው ይፈቅድልናል፡፡ ይህ ካልሆነ በቀር የሕይወታችን ፍላጎት አይገኝም፡፡
እንዲሁ  አንዱ  ካንዷ  ጋር  መጋባትና  ልጆች  ማሳደግን  ፈቅዷል፡፡  ደግሞም  ከልቦናችን  ጋር  የሚስማማ  ለህይወታችንም
ለሁሉም  የሰው  ልጆች  ኑሮ  የሚያስፈልጉ  ሌሎች  ብዙ  ሥራዎች  አሉና  የፈጣሪ  ፈቃድም  እንዲሁ  ስለሆነ  ልንጠብቀው
ይገባናል፡፡ እግዚያብሔር ፍፁማን አድርጎ እንዳልፈጠረን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ለመፈፀማችን የተዘጋጀን አዋቂዎችና በዚህም
ዓለም  እስካለን  ድረስ  እንድንፈፅምና  ፈጣሪያችን  በጥበቡ  ላዘጋጀልን  ዋጋ  የተዘጋጀን እንድንሆን  አድርጎ  ፈጠረን፡፡  በዚህ
ምድር ፍፁማንና ብፁዓን አድርጎ ሊፈጥረን ለእግዚአብሔር ይቻለው ነበር፡፡ ነገር ግን ለመፈፀማችን የምንዘጋጅ አድርጎ
ፈጠረን እንጅ እንዲሁ ሊፈጥረን አልፈቀደም፡፡ ከሞታችን በኋላ ፈጣሪያችን ለሚሰጠን ዋጋ የተዘጋጀን ፍፁማን እንድንሆን
በዚህ የፈተና ዓለም መካከል አኖረን፡፡ በዚህ ዓለም እስካለንም ወደ እርሱ እስኪወስደን ድረስ እየታገስን ፈቃዱን እየፈፀምን
ፈጣሪያችን  ልናመሰግነው  ይገባል፡፡  የፈተናችንንም  ጊዜያቶች  እንዲያቀልልን  ባለማወቃችን  ሠራነውን  የእብደት  አበሳ
እንዲተውልን የተፈጥሮ ሕግጋትን አውቀን እንድንጠብቃቸው ልቦና እንዲሰጠን ወደቸርነቱ እንለምን፡፡ ፀሎት ደግሞ ላዋቂ
ነፍስ  አስፈላጊ  ነውና  ዘወትር  ልንፀልይ  ይገባናል፡፡  አዋቂ  ነፍስ  ሁሉን  የሚያውቅና ሁሉን  የሚጠብቅ  ሁሉን  የሚገዛ
እግዚአብሔር እንዳለ ታውቃለች፡፡ ወደ እርሱ እንድትፀልይም ከእርሱ መልካም እንድትለምን፣ ከክፉ እንድትድንና ሁሉን
ወደሚችል እጅ እንድትማፀን ወደ እርሱ ትሳባለች፡፡ እግዚአብሔር ምሁርና ትልቅ ነው፡፡ የሚሳነውም የለም፡፡ ከበታቹ
ያለውን ያያል፣ ሁሉንም ይይዛል፣ ሁሉን ያውቃል ፣ ሁሉን ይመራል፣ ሁሉን ያስተምራል አባታችን ፈጣሪያችን ጠባቂያችን
ነው፡፡  የነፍሳችን  ዋጋ  ቸርና  ይቅር  ባይ  ችግራችንን  ሁሉ  የሚያውቅ  ነው፡፡  ለሕይወት  እንጂ  ለጥፋት  አልፈጠረንም፡፡
በትዕግስታችን ይደሰታል፡

Thursday, August 14, 2014

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሷል!

  • የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲፈራርስ ዝምታው እስከመቼ?
  •  
  •  ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ጉዳይ ምላሻቸው ምን ይሆን?

ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚለው ቃል ከወረቀት ባለፈ በመሬት ላይ ተፈሚነቱ የሚታየው በጣም በጥቂቱ ነው። በተለይም ቤተ ክርስቲያኒቱ አለኝ በምትለው ማእርገ ክህነት በኩል ዲቁና፤ ቅስና ( ምንኩስና) ቁምስና በሙሉ የሚሰጠው ለማንና መስፈርቱ ምን እንደሆነ በማይታወቅ መልኩ ሥርዓተ የለሽ ሆኖ ይታይበታል። እነ መቶ አለቃ ግርማ ወንድሙ ሳይቀሩ በር የሚዘጋ መስቀል ተሸክመው እያሳለሙ በአጥማቂነት ተሰማርተው ገንዘብ ይሰበስባሉ። ከዚህ በፊት ወደእስራኤል አቅንቶ የነበረው ግርማ ወንድሙ ገና ገንዘብ መሰብሰብ ሲጀምር አንዷን ሴት ሲያጠምቅ ጎረቤቷ ቡዳ ሆና በላቻት በማሰኘቱ፤ ቡዳ ናት የተባለችው ሴት ፍርድ ቤት በስም አጥፊነት ከሳው መጥሪያ ብታመጣበት ሌሊቱኑ ፈርጥጦ ወደኢትዮጵያ ማምለጡን ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ሰምተን ተገርመን ነበር። ባለቤት የሌላትን ቤተ ክርስቲያን እየተዘዋወረ በክፉ መንፈስ የሚበጠብጠው ግርማ አሁን ደግሞ ወደአውሮፓ ዘልቆ በጣሊያን የዘረፋውንና የቡዳ በላሽ ዜማውን እያስነካው ይገኛል። እነባህታዊ ገብረ መስቀል ማርያምን ተገለጸችልኝ እያሉ ህዝቡን ሲያጭበረብሩ እንዳልነበር ብህትውናውን እርግፍ አድርገው ቆንጆ መርጠው ሚስት አግብተው ልጆች ወልደው ማርያም ተገለጸችልኝ፤ ገብርኤልን አየሁት ከሚል ማደናገሪያ ነጻ ወጥተዋል። ከማጭበር በር ይህኛው የተሻለ አማራጭ ይመስለናል።
ይህ ማእርገ ክህነት የሚባለው ሹመት በአንዳንዶች ዘንድ የክብር ዶክትሬት ይመስል ከስም ባለፈና የሕዝቡን ግንባር ከሚገጩበት በስተቀር እንደማኅበረ ቅዱሳን ባሉ ማኅበራት ዘንድም የአገልግሎት ዋጋ የሌለው መሳሪያ ሆኖ ይገኛል። በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉበት አይታይም። የማዕረጉን ስም የሚፈልጉት ክህነት የላቸውም እንዳይባሉና በክህነት ሽፋን በሚገኘው ክብር የመበለቶችን ቤት ለመዝረፍ ስለሚረዳ እንጂ ከመጀመሪያው በድንግልና ጸንተው ለማዕርገ ዲቁና በቅተው «ተንሥኡ፤ ጸልዩ» እያሉ ሲያገለግሉበት ቆይተው፤ በኋላም በስርዓተ ቤተ ክርስቲያን በተክሊል በድንግልና የጸናች አግብተው አይደለም። ሲጀመር ጀምሮ ዲቁናም ይሁን ቅስና የተቀበሉት ሰዎች ድንግላቸው የፈረሰበትን ጊዜ ራሳቸው በትክክል አያውቁትም። ራሳቸው በድንግልና ሳይቆዩ፤ ድንግልና እንደፈንጣጣ በጠፋበት ዘመን ድንግል አግብተው አይቀስሱም።  በተለይ ወንዶቹ አጭበርባሪዎች፤ ቀሳጮችና መልቴዎች ናቸው። በዚህ ዙሪያ ሀገር ሰፈሩን ሲያዳርሱ የኖሩ የዘመኑ ቀሳውስትና መነኮሳት ነን ባዮች ቅስናን እንደማጭበርበሪያ ይጠቀሙበታል። ቅዱስ በተባለው መቅደስ ገብተው በርኩስናቸው ሕዝቡን ያታልሉበታል። ይህ ዐመፃና ማታለል በሀገር ላይ ጥፋትን፤ በሕዝብ ላይ ቁጣን ማምጣቱ አይቀርም። ማንም እመራበታለሁ ብሎ ላወጣው ለራሱ ሕግ የማይታዘዝ ከሆነ የሚጠፋው በዚያው በራሱ ሕግ ነው።
«ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል» ሮሜ 2፤12
ዛሬ ሁሉም ከዚህ ከራሳቸው የሕግ ክብር ስለወረዱ ማንም ምንንም አይቆጣጠርም። ሥርዓት ፈረሰ፤ ሕግ ተጣሰ የሚል አንድም ስንኳ የለም። «ኩሉ ዐረየ፤ ወኅቡረ ዐለወ» እንዳለው ዳዊት በመዝሙሩ ሁላቸውም ተሳስተዋል፤ ሁላቸውም በዐመጻ ስለተስተካከሉ ዲቁና ሰጪውም ተቀባዩም ከሥርዓት ውጪ ሆነዋል።  ከዚህ በታች የቀረበውም ጽሁፍ ይህንን መሠረት ያደረገ ነው።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን «እንበለ አሐዱ ኄር፤ ኢይኀድጋ ለሀገር» ለሀገር እንዲሉ አንድ ተቆርቋሪ ኤርትራዊ ቄስ ከሀገረ እስራኤል-ቴል አቪቭ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ለልዩ ልዩ ድረ ገጾች በግልባጭ ሲልክ ለእኛ የደረሰውን ጽሁፍ እንዳለ አቅርበነዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምን ሆነች?

በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከመለያየታቸው በስተቀር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ዛሬም ድረስ አንድ ነን። ሥርዓቱና ሕግጋቱ የተለያየ አይደለም። በማዕረገ ክህነት አሰጣጥ ልዩነት ያለን አይመስለንም።  ነገር ግን እጅግ አሳዝኝና አስገራሚ ነገር ስናይ የምንጠይቀው አጥተናል። በተደረገው ሁኔታ እኛ በእስራኤል የምንገኝ ኤርትራውያን በተደረገው አድራጎት ተጎድተናል። ይኸውም ለሰሚ የሚከብድና ከምናውቃት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህግጋት ውጪ ማዕረገ ክህነት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ሲሰጥ በማየታችን በጣም አዝነናል። ነገሩን በአጭሩ አስረዳለሁ።
ሰውየው በትግራይ ክፍለሀገር ሰንቃጣ እንደተወለደ አውቀነዋል። ስሙም ሓጎስ አስገዶም ይባላል። በትግራይ ክፍለ ሀገር ይህ ሓጎስ አስገዶም የተባለ ሰውዬ አባ ሰላማ የሚባል ማኅበር አቁሞ ህዝብ ለህዝብ ሲያጋጭ ተይዞ ሶስት አመት ወኅኒ ታስሮ ነበር። በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ማኅበሩ በትእዛዝ ፈረሰ። በሲኖዶስም ተወሰነበት። ተስፋ ያልቆረጠው ይህ ሓጎስ አሰገዶም የተባለ ሰውዬው ወደ ሽመልባ የኤትራውያን ስደተኛ ካምፖ በመግባት ባሕታዊ ወልደ ሥላሴ እባለሎህ በማለት ማደናገር ጀመረ።
ባህታዊ ነኝ የሚለው ሓጎስ አስገዶም

በዚያም በእሱ የተጀመረ ረብሻ በሽመልባ ባሉ የኤርትራ ቤተክርስቲያን በመበራከቱ ጥቂት ተከታዮች አስከትሎ በሱዳን አድርጎ ሊቢያ ገባ። ሊቢያ ሲገባም አባ ሰላማ መልዕክት ነግረውኛል ከዛሬ ጀምሮ አንተ ሞኖክሴ ነህ ብለውኛል ብሎ አባ ሳሙኤል ነኝ አለ። ከዚያም ይህ ሓጎስ አስገዶም ከሊቢያ ወደእስራኤል ሀገር ከኤርትራውያን ጋር ገብቶ ኤርትራዊ ነኝ ብሎ የስደተኛ ወረቀት ከወሰደ በኋላ ሳይሞኖክስ አባ ሳሙኤል ተብሎ እየተጠራ ቆየ። አጠምቃለሁ እያለ ሲያታልል፤ ህዝብ ሲያሳብድ፤ ገንዘብ ሲሰበስብ ቆይቶ ብዙ ኤትራውያን ደግሞ አንተ ሞኖክሴ አይደለህም፤ ለምን አባ ትባላለህ። ክህነት የለህም ለምን ታሳልማለህ።  ንስሀ ለምን ትሰጣለህ ስንለው የእኔ ክህነት በአባ ሰላማ ፍሬምናጦስ አማላጅነት ከሰማይ ነው የተሰጠኝ፤ የእናንተ ክህነት ግን ከኃጢአተኛ ጳጳስ እጅ የተሰጠ ነው እያለ ሲሳደብ በማየታችን ህዝቡ በዚህ አታላይ ሰው እንዳይታለል ስናስተምር ተናዶ ወደኢየሩሳሌም በመሄድ ከኢትዮጵያ ሊቀጳጳስና አንዳንድ መነኮሳት ጋር በስውር መገናኘቱን ቀጠለ።
ባህታዊ ወልደ ሥላሴ ነኝ እያለ በሽመልባ ሲያታልል

 ከዚያም ከሊቀ ጳጳሱ አባ ዳንኤል ዘንድ ዲቁና ተቀበልኩ አለና በአስማቱ ለሚያታልላቸው ደጋፊዎቹ  ማዕረጉ ሲሰጠው የሚያሳይ ፎቶና ፊልም አሳየ። ትንሽ ቆይቶ ሞኖኮስኩኝ ብሎ እንደቦብ ማርሊ ያሳደገውን ጸጉሩን ቆርጦ ጥቁር ቆብና ቀሚስ አድርጎ መጣ። አንተን አመነኮሰች ቤተ ክርስቲያን? ብለን አዘንን። አለቀስን።
በአባ ሳሙኤል ስም ቄስና መነኩሴ ነኝ አለን ደግሞ

ከሱ ጋር የነበሩና ስናስተምራቸው የተመለሱ ሁለት ዲያቆናት ለመመንኮስ 50 ሺህ ሼቄል ከፍሏል አሉን። ለሊቀ ጳጳሱና ከመነኮሳቱ መካከል አባ ፍስሐና አባ ብርሃና መስቀል የተባሉም ገንዘብ መቀበላቸውን አሁንም ይመሰክራሉ። የሰው ማስረጃ አለን። ሌሎችም መነኮሳት የተቀበሉ አሉ። ይህ አታላይ አባ ሳሙኤል የተባለው ትንሽ ቆይቶ የቅስና ማዕረግ ከአባ ዳንኤል ተሰጠኝ ብሎ በደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሥርዓት በቢዲዮና በፎቶ  ቴልአቪቭ አምጥቶ ለተከታዮቹ አሳየ። ይህ ሁሉ ማስረጃ በእጃችን ይገኛል።
ምንም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሙያ ለሌለው፤ ዲቁና ሳይኖረው  ለሓገስ አስገዶም ቅስና ሲሰጡት አቡነ ዳንኤል ናቸው

 የዚህ ሁሉ አስተባባሪ አባ ፍስሐ ይባላሉ። አባ ብርሃነ መስቀል የተባሉት፤ አባ ተወልደ የተባሉትም አብረውት አሉ። ገንዘብ የተቀበሉ መኖክሴዎች ዝርዝር በእጃችን አለ። በቁጥር ትንሾች ቢሆኑም የቤተ ክርስቲያን ስርዓት ጠፋ ብለው የተናገሩ ቢኖሩም የሰማቸው የለም።  ገንዘብ የሁሉንም አፍ ዝም አሰኝቷል።



 እኛ የምናዝነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ሹማምንት በገንዘብ ስልጣነ ክህነት እየሰጡ ለምን ቤተ ክርስቲያንን ያሰድባሉ? የኢየሩሳሌም ገዳም ሞኖክሴዎችስ ለምን በገንዘብ ይደለላሉ? ክህነት እንደዚህ ነው? ሙንኩስናስ እንደዚህ ነው? በበኩላችን ይህን ሰውዬ ያለአግባብ እያታለለ ከኤርትራውያን እጅ የወሰደውን በብዙ መቶ ሺህ ሼቄል ለማስመለስና በህግ ፊት ለማቆም ማስረጃዎቻችንን ይዘናል። እናንተ በሰጣችሁት ክህነት አንታለልም። አንታወክም። ለነገሩ ቤተ ክርስቲያንን አዋርዳችሁታል። ሓጎስ አስገዶም ቄስ ሆነ? ሚስቱንም አምጥቶ አመነኮሰ። አንድ ቤት አንድ ላይ ይኖራሉ። አይ ኦርቶዶክስ፤ እንደዚህ መሆና ያሳዝናል። ሕግ ካለ፤ ዳኛ ካለ ኢየሩሳሌም ያሉ ሞነኮሳትን ከገዳሙ ማባረር ነበር። ለሓጎስ አስገዶም ቅስና የሰጡ ሊቀጳጳሱም መቀጣት ነበረባቸው።
ያሳዝናል። ያሳዝናል። በትክክልም ዘመኑ ተጨርሷል። ክህነትና ሙንኩስና  በገንዘብ ሆነ። ኤሎሄ ኤሎሄ ይባላል።

ለምእመን በገንዘብ ክህነት እንዲያገኝ ያደረጉ አባ ብርሃነ መስቀል የሚባሉት በቀኙ፤ አባ ፍስሐ የሚባሉት አባ ፍስሐ የሚባሉት በግራ በመሀል አቡነ ዳንኤልና ሲሆኑ በደብረ ገነት ቤተመቅደስ ውስጥ ሓጎስ አስገዶም ፤ ወልደሥላሴና አባ ሳሙኤል የተባለው ቅስና ሲቀበል የሚያሳይ ፎቶ። የዚህ ሥርዓት ሙሉ ቪዲዮ በእጃችን አለን።
             
                     ፍትዊ አንገሶም ቴልአቪቭ