Monday, August 11, 2014

ትክክለኛው ሃይማኖት የቱ ነው?



 ቀልጣፋ ሬስቶራንቶች በቀላሉ የሚስቡን የፈለግነውን ምግብ በምንወደው መንገድ እንድናዝ መንገድ ስለሚከፍቱልን ነው። ጥቂት ካፌዎች ደግሞ ከመቶ በላይ የተለያዩ የቡና ጣዕም እንደሚያቀርቡ በጉራ ይናገራሉ። መኖሪያ ቤቶችና መኪናዎችን ስንገዛ እንኳ የምንፈልገው ምርጫ እንዲያሟላ እንሻለን። በቼኮላት፣ በቫኒላና በእንጆሪ ዓለም ታጥረን መኖር አንፈልግም። ፍላጎት ንጉሥ ነው! እንደግላዊ ፍላጎትህና ምርጫህ የምታገኝበት ሁሉ የተሟላበት ዘመን ነው።
ለአንተ ብቻ ትክክለኛ ሃይማኖት የማግኘቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል? ወቀሳ አልባ፣ ብዙ ጫና የሌለውና ይህንን አድርግ አታድርግ እያለ የማያስቸግር ሐይማኖት ብታገኝስ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ያውና እዚያ አለ ነገር ግን ሃይማኖት እንደሚወዱት አይስክሬም የሚመረጥ ነው እንዴ?
ትኩረታችንን ለመሳብ የሚሻሙ በርካታ ድምፆች ስላሉ ለምን ብሎ ነው አንድ ሰው ኢየሱስን ከሌሎች ማለትም ከመሐመድ ወይም ከኮንፊሸየስ፣ ከቡድሐ ወይም ቻርለስ ቴዝ ራስል ወይም ከጆሴፍ እስሚዝ አስበልጦ የሚመርጠው? ዞሮ ዞሮ ሁሉም መንገዶች የሚያደርሱት ወደ መንግስተ ሰማይ አይደለም እንዴ? በመሰረቱ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉም እንዴ? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መንግስተ ሰማይ አያመሩም። ሁሉም መንገዶች ወደ ኢንዲያና መቼም አያደርሱም።
ኢየሱስ ብቻውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ይናገራል።
1/  ምክንያቱም ኢየሱስ ብቻ ነው ሞትን ያሸነፈው። እስካሁን ድረስ መሐመድ፣ ኮንፊሸየስና ሌሎች በመቃብር በስብሰው ይገኛሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በራሱ ስልጣን በጨካኙ የሮማውያን መስቀል ከሞተና ከተቀበረ ከሦስት ቀን በኋለ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቶአል። በሞት ላይ ስልጣን ያለው ማንኛውም ሰው ትኩረታችን ሊስብ ግድ ይላል። ማንም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ግለሰብ ሲናገር ልናደምጠው አስፈላጊ ነው። ሞትን ማሸነፍ የቻለ ከፍጥረታት መካከል ማንም የለም። ከሰማይ የመጣው ብቻ ሞትን አሸንፎ ወደሰማይ ወጥቷል።ስለዚህ እንዲህ ያለው አሸናፊ የተናገረው የእምነት መሠረት መሆን አለበት። ሰው ሟች መሆኑን ያውቃል። ሟች ደግሞ ከሞት ለማምለጥ የሚችለው በሞት ላይ ባለሙሉ ሥልጣን በሆነ ክንድ ላይ ሲያርፍ ነውና ኢየሱስን ማመን የግድ ይለዋል። ሌላ ማንም አዳኝ የለም።
2/ የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣዔ ምስክር ያለውና እውነት ነው።  የኢየሱስን ትንሣዔ የሚደግፈው መረጃ የሚያጥለቀልቅ ነው።   ሮማውያንና ሰቃልያኑ ካህናት የኢየሱስን መቃብር ማስጠበቅ ያስፈለጋቸው «በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ» ያለውን ቃሉን ይዘው እንጂ የሞተ ሰው መቃብር ስለሚጠበቅ አልነበረም።  አዎ ትንሣዔውን ለመከላከል ወታደሮች ከመቃብሩ ማንም እንዳይወጣ፤ ወደመቃብሩም ማንም እንዳይደርስ አድርገው አስጠብቀው ነበር። ነገር ግን የመቃብሩ ቦታ ባዶ ሆኗል!  እንደተናገረው አልተነሳም እንዳይሉ የኢየሱስ ጠላቶች ያን ሁሉ ስለትንሣዔው የተነዛውን ወሬ ለማክሸፍ የበሰበሰውን አካሉን በማቅረብ በቀላሉ ያስታግሱት ነበር። ግን አልቻሉም፤ መላው ሲጠፋባቸው ደቀመዛሙርቱ ሬሳውን ሰርቀውት ይሆን? አሉ።  ከሐዋርያቱ መካከል ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ የሸሹት በጊዜ ነው። የሸሹ ሰዎች ተመልሰው ከሮማ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ሰረቁት ማለት የማይመስል ነገር ነው። ቀላሉ ሃቅ ግን የኢየሱስ ትንሳኤ እንዲሁ ተነግሮ ተገልፆ የሚያልቅ መች ሆነና! ትንሣዔውን ያለምስክር ያልተወ ኢየሱስ ግን በአንድና በሁለት ሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በአምስት መቶ ሰዎች ፊት ትንሣዔውን አስመስክሯል።

«መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ» 1ኛ ቆሮ 15፤4-8

ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማመን የሚያስችላቸው በቂ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደኢየሱስ ሞትን ያሸነፈ፤ ትንሣዔውን በምስክር ያረጋገጠ ማንም የለም። ስለዚህ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም ሰው ሊደመጥ ይገባል። ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን አረጋግጧል። ስለዚህ የሚናገረውን መስማት ይገባናል። ለድነት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን ራሱ ይናገራል።(ዮሐንስ 14፡ 6)። ካሉትም ብዙ መንገዶች አንዱ አይደለም። ኢየሱስ ብቸኛ የድነት መንገድ ነው። ሌላ መንገድ ሁሉ በትንሣዔና በሕይወት ላይ ሥልጣን የሌለው የሞት መንገድ ነው።
3/ ኢየሱስ ከሸክም ያሳርፋል። በዚህ ምድር ላይ ከሸክም አሳርፋችኋለሁ ብሎ ቃል የገባ አንድም ሥጋ ለባሽ የለም። ይህ ብቸኛ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች፤ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡ 28)። ሕይወትም አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ደምተናል፣ ቆስለናል፣ ጦርነትንም እንፈራለን። ዓለምም አስጨናቂ እየሆነች ነው። ስለዚህ የሚያሳርፈንን ብንፈልግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከኢየሱስ በቀር ሸክም የከበዳችሁ ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ማንም ሌላ የለም። በትንሣዔውና በሕይወቱ የታመነ ኢየሱስ ይህንን የማለት ብቃት ስላለው በእርሱ ላይ ማረፍ ከአስጨናቂው ዓለም ለመዳናችን ዋስትናችን ነው።
ስለዚህ ምን ትፈልጋላችሁ? ከኃጢአት፤ ከድካም፤ ከተስፋ መቁረጥ በንስሐ መታደስ ወይስ  የአንዱ ሃይማኖት አባል በመሆን ብቻ መኖር? ሕያው የሆነ አዳኝ ወይስ “ከሞቱት በርካታ ነቢያት ወይም ጻድቅ” አንዱን ተስፋ ማድረግ? ትርጉም ያለው ግንኙነት ወይስ ተራ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት መከተል?
ኢየሱስ አማራጭ ሳይሆን ምርጫ ነው! ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈሳዊ ድርጅት ወይም የአንዱ ተቋም ስያሜና የዚያ አባል ሆኖ መኖር ማለት አይደለም።  ከእግዚአብሔር  አብ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ትፈልግ እንደሆን ሃይማኖትህ ኢየሱስን ማመን ነው። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ይላል መጽሐፍ። (ዮሐንስ 3፡ 36) አንዳንዶች ይህንንማ እናምናለን ነገር ግን ትክክለኛው እምነት ያለው በኛ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ አባል ሁነን ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በማኅበር ስለመጸለይ ይነግረናል እንጂ ኢየሱስን ለማመን የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተቋም አባል ሁን የሚል ትዕዛዝ የለውም። ኢየሱስ በሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ የሃይማኖት ድርጅት ሊመሠረት አልመጣም።

«የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን» 1ኛ ዮሐ 5፤15

(www.Gotquestions.org)ተሻሽሎ የተወሰደ

Friday, August 1, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

(ዘርዓ ያዕቆብ ፈላስፋ) ክፍል ሁለት

የሰው  ፍጥረት  ታካችና  ደካማ  መሰለኝ፡፡ ሰው  ግን ፍቅርን  ቢወዳትና  በጣም  ቢያፈቅራት  የተሸሸገውንም  ፍጥረትን  ቢያውቅ ይወዳል፡፡ ይህም  ነገር  እጅግ  ጥልቅ  ነውና  በትልቅ  ድካምና  ትዕግስት  ካልሆነ  በስተቀር  አይገኝም፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን፡ “ከፀሐይ  በታች  ስለተደረገው  ሁሉ  ጥበብን  ለመፈለግና  ለመመርመር  ልቤን  ሰጠሁ፡፡  እግዚአብሔር  ለሰው  ልጆች  እንዲደክሙበት የሰጣቸውን  ክፉ  ስራ  አየሁ”ይላል፡፡

   ስለዚህ  ሰዎች  ሊመረምሩት  አይፈልጉም፡፡  ሳይመረምሩ  ከአባቶቻቸው  የሰሙትን  ማመን  ይመርጣሉ፡፡  ነገር  ግን እግዚአብሔር  ሰውን  የምግባሩ  ጌታ  ክፉ  ወይም  መልካም  የፈለገውን  እንዲሆን  ፈጠረው፡፡  ሰውም  ክፉና  ዋሾ  መሆንን  ቢመርጥ ለክፋቱ የሚገባውን  ቅጣት  እስኪያገኝ  ድረስ  ይችላል፡፡ ነገር  ግን  ሰው ሥጋዊ  ነውና  ለሥጋው  የሚመቸውን  ይወዳል፡፡ ክፉ  ይሁን  መልካም  ለስጋው  ፍላጎት የሚያገኝበትን  መንገድ  ሁሉ  ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር  ሰው  የፈለገውን  እንዲሆን  ለመምረጥ  መብት  ሰጠው  እንጂ  ለክፋት  አልፈጠረውም፡፡ ስለዚህ  መምረጥ  ክፉ  ቢሆን  ለቅጣት  መልካም  ቢሆን  ደግሞ  የመልካምነት  ዋጋ  ለመቀበል  የተዘጋጀ  እንዲሆን  እድል  ሰጠው፡፡

  በሕዝብ  ዘንድ  ክብርና  ገንዘብ  ለማግኝት  የሚፈልግ  ዋሾ  ሰው  ነው፡፡  ዋሾ  ሰው  ይህን  በሐሰተኛ  መንገድ  ሲያገኝ  እዉነት አስመስሎ ሀሰት  ይናገራል፡፡ ሊመረምሩ  የማይፈልጉ  ሰዎች  እውነት  ይመስላቸውና  በእርሱ  በጽኑ  ሃይማኖት  ያምናሉ፡፡ እስኪ  ሕዝባችን  በስንት  ውሸት  ያምናል?  በጽኑ  ሃይማኖት  ያምናል፡፡  በሃሳበ  ከዋክብትና  በሌላም  አስማት፣  አጋንንት  በመሳብና በመርጨት፣ አስማት በማድረግ፣ በጥንቆላ  ሁሉ  ያምናሉ፡፡ ይህንን  ሁሉ  መርምረው  እውነቱን  አግኝተው  አያምኑም፡፡ ነገር  ግን  ከአባቶቻቸው  ሰምተው ያምናሉ፡፡ እነዚያስ  የፊተኞቹ  ገንዘብና  ክብር ለማግኝት  ካልሆነ በቀር ስለምን  ዋሹ?  እንዲሁ  ህዝብን  ሊገዙ  የሚፈልጉ  ሁሉ  እውነት  እንነግራቸኋለን  እግዚአብሔር  ወደናንተ  ላከን  ይሏቸዋል፡፡  ሕዝቡም  ያምናሉ፡፡
ከነርሱም  በኋላ  የመጡት  እነርሱ  ሳይመረምሩ  የተቀበሏትን  የአባቶቻቸውን  እምነት  አልመረመሩም፡፡  ከዚያ  ይልቅ  ለእውነትና ለሃይማኖታቸው  ማስረጃ  ታሪክን፣ ምልክቶችን ፣ ተዓምራትን  እየጨመሩ እውነት  አስመስለው  አጸኑት፡፡  በነገሩ ሁሉ እግዚአብሔርን  ስም ጨመሩ።  እግዚአብሔርንም የሐሰኞች ተካፋይና  የሐሰት  ምስክር  አደረጉት፡፡

  ጥልቅ   ምርመራ  ስለ  ሙሴና  መሐመድ  ሕግጋት

 ለሚመረምር  ግን  እውነት  ቶሎ  ይገለፃል፡፡  ፈጣሪ  በሰው  ልብ  ያስገባውን  ንጹህ  ልቦና  የፍጥረት  ሕግጋትና  ስርዓትን  ተመልክቶ የሚመረምር  እርሱ  እውነትን  ያገኛል፡፡ ሙሴ  ፈቃዱንና  ሕጉን  ልነግራችሁ  ከእግዚአብሔር  ዘንድ  ተልኬ  መጣሁ  ይላል፡፡ ከሆነ ታዲያ «ሴት በወር አበባ ወቅት የረከሰች ናት» ለምን ይላል? የሙሴ  መጽሐፍ  ከፍጥረት  ሕግ  ሥርዓትና  ከፈጣሪ  ጥበብ  ጋር  አይስማማም፡፡  ከውስጡ  የተሳሳተ  ጥበብ  ይገኛል፡፡ ለሚመረምር  ግን  እውነት  አይመስለውም፡፡  በፈጣሪ  ፈቃድና  በፍጥረት  ህግ  የሰው  ልጅ  እንዳይጠፋ  ልጆችን  ለመውለድ  ወንድና  ሴት  በፍትወተ  ሥጋ  እንዲገናኙ  ታዟል፡፡  ይህም  ግንኙነት  እግዚአብሔር  ለሰው  በሕገ  ተፈጥሮ  የሰጠው  ነው፡፡ እግዚአብሔርም  የእጁን  ሥራ  አያረክስም፡፡ እግዚአብሔር  ዘንድ  እርኩሰት  ሊገኝ  አይችልም፡፡  ፈጣሪ የፈጠረውን መልሶ አያረክሰውም እላለሁ። 

  እንደገናም  የክርስቲያን  ሕግ  ለማስረጃዋ  ተአምራቶች ተገኝተዋልና  ከእግዚአብሔር  ናት  ይላሉ፡፡  ነገር  ግን  የወሲብ  ሥርዓት  የተፈጥሮ  ሥርዓት  እንደሆነ  ምንኩስና  ግን  ልጆች ከመውለድ  ከልክሎ  የሰውን  ፍጥረት  አጥፍቶ  የፈጣሪን  ጥበብ  የሚያጠፋ  እነደሆነ  ልቦናችን  ይነግረናልና  ያስረዳናል፡፡ የክርስቲያን  ሕግ  ምንኩስና  ከወሲብ  ይበልጣል  ብትል  ሐሰት  ትናገራለችና  ከእግዚአብሔር  አይደለችም፡፡  የፈጣሪን  ሕግ  የሚያፈርስ  እንዴት  ከጥበብ በለጠ ?  ወይስ  የእግዚአብሔርን  ስራ  የሰው  ምስክር ሊያስተካክለው ይቻለዋልን ? ሰዎች ግን ሳይመረምሩ ምንኩስና ከጋብቻ ትበልጣለች ይላሉ። ዘርን የሰጠ ፈጣሪ ዘር አያስፈልግም አይልም። ቀጣፊዎች በእግዚአብሔር ስም  እውነት አስመሰሉት እንጂ።

እንዲሁም  መሐመድ  የማዛችሁ  ከእግዚአብሔር  የተቀበልኩትን  ነው  ይላል፡፡  መሐመድን  መቀበል  የሚያስረዱ  የተዓምራት  ፀሐፊዎች  አልጠፉምና  ከሱም  አመኑ፡፡ እኛ  ግን  የመሐመድ  ትምህርት  ከእግዚአብሔር  ሊሆን  እንደማይችል  እናውቃለን፡፡ የሚወለዱ  ሰዎች  ወንድና  ሴት  ቁጥራቸው  ትክክል  ነው፡፡ በአንድ  ሰፊ  ቦታ  የሚኖሩ  ወንድ  ሴት ብንቆጥር  ለእያንዳንዱ  ወንድ አንዲት  ሴት  ትገኛለች  እንጂ  ለአንድ  ወንድ  ስምንት  ወይም  ዐሥር  ሴቶች  አይገኙም፡፡ የተፈጥሮ  ህግም  አንዱ  ከአንዲት  ጋር እንዲጋቡ  አዟል፡፡ አንድ  ወንድ  ዐሥር  ሴት  ቢያገባ  ግን  ዘጠኝ  ወንዶች  ሴት  የሌላቸው  ይቀራሉ፡፡ ይህም  የፈጣሪን  ስርዓትና  ሕገ ተፈጥሮን  የጋብቻንም  ጥቅም  ያጠፋል፡፡ አንድ  ወንድ ብዙ ሴቶች ሊያገባ  ይገባዋል  ብሎ  በእግዚአብሔር  ስም  ያስተማረ  መሐመድ  ግን  ትክክል  ነው አልልም፡፡ ከእግዚአብሔር  ዘንድ  አልተላከም፡፡  ጥቂት  ስለጋብቻ  ሕግ  መረመርኩ  ፡፡ ከመጀመሪያም  ለአዳም አንድ ሴት ከመፍጠር ይልቅ ዐሥር ሴት ያልፈጠረለት ለምንድነው? ይህን የፈጣሪ ሕግ  ሳይመረምሩ የመሐመድን  ሕግ መቀበል ስህተት ነው። ከእግዚአብሔር እንደተገኘ  ብመረምርም  በህገ  ኦሪትና  በክርስትናና  በእስልምና  ሕግ  ፈጣሪ  በልቦናችን  ከሚገልጽልን  እውነት  እና  እምነት ጋር የማይስማማ ብዙ ነገር አለ  አልኩ።

    ፈጣሪ  ለሰው  ልጅ  ክፉና  መልካም  የሚለይበት  ልቦና  ሰጥቶታል፡፡  «በብርሃንህ  ብርሃንን  እናያለን»  እንደተባለውም  የሚገባውን  የማይገባውን  ሊያውቅ፣  እውነትን  ከሐሰት እንዲለይ ነው፡፡ ስለዚህ የልቦናችን  ብርሃን  እንደሚገባ  በእርሱ  ብናይበት  ሊታይልን አይችልም፡፡ ፈጣሪያችን ይሄን ብርሃን  የሰጠን  በርሱ  እንድንድን  ነው እንጂ  እንድንጠፋ  አይደለም። የልቦናችን  ብርሃን  የሚያሳየን  ሁሉም  ከእውነት  ምንጭ  ነው፡፡ ሰዎች  ከሐሰት  ምንጭ  ነው  ቢሉን ግን  ሁሉን  የሰራ  ፈጣሪ  ቅን እንደሆነ  ልቦናችን  ያስረዳናል፡፡ ፈጣሪ  በመልካም ጥበቡ  ከሴት  ልጅ  ማህጸን  በየወሩ  ደም  እንዲፈስ አዟል፡፡  ሙሴና  ክርስቲያኖች  ግን  ይህን የፈጣሪ  ጥበብ  እርኩስ  አደረጉት፡፡
እንደገና  ሙሴ  እንዲህ  ያለችው  ሴት ከተቀመጠችበት የተቀመጠውንም፤ የተገናኛትንም  ያረክሳል፡፡  ይህም  የሙሴ  ህግ  የሴትን  ኑሮ  በሙሉና  ጋብቻዋን  ከባድ አድርጎታል፡፡ የመራባትንም  ህግ  አጥፍቷል፡፡ ልጆችንም  ከማሳደግ  ከልክሎ  ፍቅርንም  ያፈርሳል፡፡ ስለዚህ ይህ  የሙሴ  ሕግ  ሴትን  ከፈጠረ  ሊሆን  አይችልም  እላለሁ፡፡ «ሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል » የምትለው የሙሴ ሕግ ሞትን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር አይደለችም። እንደገናም  የሞቱትን  ወንድሞቻችንን  ልንቀብራቸው  ተገቢ መሆኑን ልቦናችን  ይነግረናል፡፡ በድኖቻቸውም  በሙሴ  ጥበብ  ካልሆነ  በስተቀር  ከመሬት  የተፈጠርንበት  ወደ መሬትም  ልንገባበት  በፈጣሪያችን  ጥበብ  እርኩሳን  አይደሉም፡፡ ነገር  ግን  ለፍጥረት  ሁሉ  እንደሚገባ  በትልቅ  ጥበብ  የሰራ  እግዚአብሔር ሥርዓቱን  አያረክሳውም፡፡ ሰው  ግን  የሐሰትን  ቃል  እንዲያከብር  ብሎ  ሊያረክሰው ይፈልጋል፡፡

  እንደዚሁም  እግዚአብሔር  የከንቱ  ነገር  አያዝም፡፡  «ጥረህ ግረህ በላብህ ወዝ ብላ» ያለው አምላክ ይህን  ብላ፣ ይህን  አትብላ፣ ዛሬ ብላ፣ ነገ  አትብላ  አይልም፡፡ ለክርስቲያኖች  እንደሚመስላቸውና  የጾም  ሕግጋት  እንደሚጠብቁ  ሥጋን  ዛሬ  ብላ፤  ነገ  አትብላ  አይልም፡፡  ለክርስቲያኖች እንደሚመስላቸውና  የጾም  ሕግጋት  እንደሚጠብቁ  ሥጋን  ዛሬ ብላ ነገ ግን  አትብላ  አይልም፡፡  እስላሞችንም  እግዚአብሔር  ለሊት  ብሉ  ቀን  አትብሉ  ብሎ  ይሄንና  የመሳሰሉትን  አይላቸውም፡፡ የፍጥረታችንን  ጤና  የማያውክ ነገር ሁሉ  ልንበላ  እንደሰለጠንን  ልቦናችን  ያስተምረናል።  አንድ  የመብል ቀን፤ አንድ  የጾም  ቀን ግን  ጤናን  ያውካል፡፡ የጾም ህግ መብላትን  ለሰው  ሕይወት  ከፈጠረና  ልንበላቸው  ከፈቀደ  ፈጣሪ የወጣ  አይደለም፡፡ በልተን ልናመሰግነው  እንጂ  በረከቱን  ልናርም አይገባንም፡፡ ሕገ  ፆም  የሥጋን  ፍትወት ለመግደል  የተሰራ  ነው  የሚሉም  ቢኖሩ  ፍትወተ  ሥጋ  ወንድ  ወደ ሴት  ሊሳብ  ሴትም ወደ  ወንድ  ልትሳብ  የፈጣሪ ጥበብ  ነውና  እርሱ  ፈጣሪ  በሰራው  በታወቀ  ማጥፋት  አይገባም  እላለሁ፡፡  ፈጣሪያችን  ይህን ፍትወት ለሰው፤  ለእንስሳት  ሁሉ  በከንቱ  አልሰጠም፡፡ ነገር ግን  ለዚህ  ዓለም  ሕይወትና  ለፍጥረት  የተሰራለት  መንገድ  ሁሉ  መሠረቱ  ሆኖ እንዲቆይ  ይህ  ፍትወት  ለሰው  ልጅ  ተሰጠ፡፡ አስፈላጊያችንን ልንበላ  ይገባናል፡፡ በእሁድ  ቀንና  በበዓል  ቀናት  በአስፈላጊው  ልክ  የበላ  እንዳልበደለ  እንዲሁ  በአርብ  ቀንና  ከፋሲካ  በፊት  ባሉት  ቀናት  ለክቶ  የሚበላ  አልበደለም፡፡  እግዚአብሔር  ሰውን  በሁሉ  ቀንና  በሁሉ  ወራት  ካስፈላጊ  ምግብ  ጋር  አስተካክሎ  ፈጥሮታል፡፡  አይሁድ፣  ክርስቲያንና  እስላም  ግን  የፆምን  ሕግ  ባወጡ  ጊዜ ይህን  የእግዚአብሔር  ሥራ  ልብ  አላሉም፡፡ እግዚአብሔር  ፆምን  ሰራልን፤  እንዳንበላም  ከለከለን  እያሉ ይዋሻሉ፡፡ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን  ነው፡፡ ግን  የምንበላውን  ምግባችንን   እንድንመገበው ሰጠን  እንጂ  እርሱን  ልናርም  አይደለም፡፡  በሚያስተውል ልቡናችን  ለክተን  መኖር የኛ ፈንታ ነው።

 ስለ  ሃይማኖቶች    መለያየት

 ሌላ ትልቅ  ምርመራ  አለ፡፡ ሰዎች  ሁሉ  በእግዚአብሔር  ዘንድ  ትክክል  ናቸው፡፡ እርሱም  አንድ  ሕዝብ ለሕይወት፤  አንድ  ሕዝብ ለሞት፤  አንድም  ለምህረት፤  አንድም  ለኩነኔ  አልፈጠረም፡፡  ይህም  አድሎ  በስራው  ሁሉ  ጻድቅ  በሆነ  በእግዚአብሔር  ዘንድ እንደማይገኝ  ልቦናችን  ያስተምረናል፡፡ ሙሴ  ግን  አይሁድን  ለብቻቸው  እንዲያስተምራቸው  ተላከ፡፡ ለሌሎች  ሕዝቦች  ፍርዱ አልተነገረም፡፡  እግዚአብሔር  ስለምን  ለአንድ  ሕዝብ  ፍርድ  ሲነግር  ለሌላው  አልነገረም፡፡  በዚህም  ጊዜ  ክርስቲያኖች  የእግዚአብሔር  ትምህርት  ከኛ  ጋር  ካልሆነ  በስተቀር  አይገኝም  ይላሉ፡፡ አይሁድና  እስላም  የህንድ  ሰዎችም  ሌሎችም  ሁሉ እንደነሱ  ይላሉ፡፡ እንዲሁ  ደግሞ  ክርስቲያኖች  እርስ  በርሳቸው  አይስማሙም፡፡ ካቶሊኮች  እግዚአብሔር  ከኛ  ጋር  ነው  ያለው እንጂ ከናንተ  ጋር አይደለም  ይሉናል፡፡ እኛም  እንዲሁ  እንላቸዋለን፡፡ ሰዎች  እንደምንሰማቸው  ግን  የእግዚአብሔር  ትምህርት  እጅግ  ጥቂቶች  ወደ ሆኑት  እንጂ  ለብዙዎቹ  አልደረሰም፡፡  ከእነዚህ  ሁሉ  ደግሞ  ወደ  ማን  እንደደረሰ  አናውቅም፡፡ እግዚአብሔር  ከፈቀደ ቃሉን  በሰው  ዘንድ  ማጽናት ተስኖት  ነውን?  ሆኖም  ግን  የእግዚአብሔር  ጥበብ  በመልካም  ምክር  ይህ  ነገር  እውነት እንዳይመስላቸው  ሰዎች  በሐሰት  ሊስማሙ  አልተወም፡፡ ሰዎች  ሁሉ  በአንድ  ነገር  በተስማሙ  ጊዜ  ይህ  ነገር እውነት ይመስላል፡፡ ሰዎች  ሁሉ  በሃይማኖታቸው  ምንም  እንደማይስማሙ  በሃሳብም  ሊስማሙ  አይችሉም፡፡
    እስኪ  እናስብ  ሰዎች  ሁሉ  ሁሉን  የፈጠረ  እግዚአብሔር  አለ  በማለታቸው  ስለምን  ይስማማሉ?  ፍጡር  ያለ  ፈጣሪ  ሊገኝ  እንደማይችል፤ ስለዚህም  ፈጣሪ  እንዳለ እውነት  ነውና  ነው፡፡ ይህ  የምናየው  ሁሉ  ፍጡር  እንደሆነ  የሰው  ሁሉ   ልቦና  ያውቃል ፡፡ ሰዎች ሁሉ በዚህ  ይስማማሉ፡፡  ነገር  ግን  ሰዎች  ያስተማሩትን  ሃይማኖት  በመረመርን  ጊዜ  በውስጡ  ሐሰት  ከእውነት  ጋር  ተቀላቅሎበታል፡፡  ስለዚህ  እርስ  በርሱ አይስማማም፡፡ ሰዎች  እርስ በርሳቸው  አንዱ  ይህ  እውነት  ነው ሲል፤ ሁለተኛው  አይደለም፤  ሐሰት  ነው  ሲል  ይጣላሉ፡፡ ሁሉም  የእግዚአብሔርን  ቃል  የሰው  ቃል  እያደረጉ  ይዋሻሉ፡፡  እንደገናም  የሰው  ሃይማኖት  ከእግዚአብሔር  ብትሆን  ክፉዎችን   ክፉ  እንዲያደርጉ  እያስፈራራች  መልካም  እንዳያደርጉ ትፈቅድላቸው  ነበር፡፡ ደጎችንም በትዕግስታቸው ታጸናቸው ነበር፡፡

  ለኔም እንዲህ ያለው  ሃይማኖት  ባሏ  ሳያውቅ  በምንዝርና  የወለደች ሴትን ትመስለኛለች፡፡ ባሏ ግን  ስለመሰለው  በሕፃኑ  ይደሰታል፡፡ እናቲቱንም ይወዳታል፡፡ በዝሙት  እንደወለደችው  ባወቀ  ጊዜ  ግን  ያዝናል፡፡ ሚስቱንም  ልጅዋንም  ያባርራል፡፡ እንዲሁም  እኔም  ሀይማኖቴን አመንዝራና  ዋሾ  መሆኑዋን  ካወኩ  በኋላ  ስለርሷ  በዝሙት  ስለተወለዱ   ልጆቿ አዘንኩ ፡፡ እነሱ  በጠብ፣ በማሳደድ፣ በመማታት፣ በማሰር፣ በመግደል  ወደዚህ  ዋሻ  ያባረሩኝ  ናቸው፡፡  ከውሸታቸው ጋር ስላልተባበርኩ ጠሉኝ። ነገር  ግን  የክርስቲያን  ሃይማኖት  ሀሰት  ናት እንዳልል  በዘመነ  ወንጌል  እንደተሰራ  ክፉ  አልሆነችም፡፡  የምህረትን  ሥራ  በሙሉ  እርስ   በርስ መፋቀርን ታዛለች፡፡  እነሱ ግን ፍቅርን ፈጽሞ አያውቋትም። በዚህ ዘመን  ግን  የሀገራችን  ሰዎች  የወንጌልን  ፍቅር  ወደ ጠብና  ኃይል  ወደ  ምድራዊ  መርዝ  ለወጡት፡፡  ሃይማኖታቸውን  ከመሰረቱ  ዐመጻ  እየሰሩ  ከንቱ  ያስተምራሉ፡፡  በሐሰትም  ክርስቲያኖች ይባላሉ፡፡

Wednesday, July 30, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

 ዘርዓ ያዕቆብ ፈላስፋ (ክፍል አንድ)

እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ ለነፍስ ያደረጋችሁትን መናገር እጀምራለሁና ኑ ስሙኝ፡ ሁሉን በፈጠረ መጀመሪያና መጨረሻ በሆነ ሁሉን በያዘና የሕይወትና የጥበብ ሁሉ ምንጭ በሆነ እግዚአብሔር በሰጠኝ ረዥም እድሜየ ትንሽ እጽፋለሁ፡፡ ነፍሴ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረች ትሁን ጆሮዎችም ሰምተው ይደሰቱ፡፡ እኔ እግዚአብሔርን ፈለኩት መለሰልኝ፡፡ አሁንም እናንተ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፤ ፊታችሁንም አያሳፍርም፡፡ እግዚአብሔርን ከኔ ጋር ከፍ ከፍ አድርጉት አብረን ስሙን እናንሳ፡፡

  እኔ የተወለድኩት በአክሱም በካህናት ሀገር ነው፡፡ ነገር ግን እኔ በአክሱም አውራጃ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት በ1592 ዓ/ም ከ አንድ ገበሬ ቤተሰብ ተወለድሁ፡፡ በክርስትና ጥምቀት ዘርዓ ያዕቆብ ተብየ ተሰየምኩ፡፡ ሰዎች ግን ወርቄ ይሉኛል፡፡ ካደኩ በኋላ ትምህርት እንድማር አባቴ ወደ ትምህርት ቤት ላከኝ፡፡ ዳዊትም ከደገምኩ በኋላ መምህሬ አባቴን ይህ ህፃን ልጅህ ልቦናው የበራ በትምህርት ታጋሽ ነውና ወደ ትምህርት ቤት ብትልከው ሊቅና መምህር ይሆናል አለው፡፡ አባቴም ይህን ሰምቶ ዜማ እንድማር ላከኝ፡፡ ሆኖም ድምጼ ሸካራ ሆኖ አላምር አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ጓደኞቼ መሳቂያና መዘባበቻ አደረጉኝ፡፡ እዚያም ሦስት ወር ያህል ቆየሁ፡፡ ስላልተሳካልኝ ከልቤ አዘንኩ፡፡ ተነስቼ ሰዋስውና ቅኔ ለመማር ወደ ሌላ አስተማሪ ሄድኩ፡፡ ከጓደኞቼ ፈጥኜ እንድማርም እግዚአብሔር ጥበቡን ሰጠኝ፡፡ ይህም የመጀመሪያ ሃዘኔን አስረሳኝ ፡፡ በጣም ተደሰትኩ፡፡ እዛም አራት አመት ቆየሁ፡፡ በነዚያ ቀኖች እግዚአብሔር ከሞት አዳነኝ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ስጫወት ወደገደል ወደቅሁ፡፡ እግዚአብሔር በታምራቱ አዳነኝ እንጅ ፈጽሞ ልድን አልችልም ነበር፡፡ ከዳንኩ በኋላ ገደሉን በረዥም ገመድ ለካሁት፡፡ ዐሥራ ሦስት ሜትር ሆኖ ተገኝ፡፡ እኔም ድኜ ያዳነኝን እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ወደ መምህሬ ቤት ሄድኩ፡፡ ከዚያም ተነስቼ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ ለመማር ሄድኩ፡፡

 በዚያም ዐሥር ዓመት ቆየሁ፡፡ መጻሕፍትን ፈረንጆች እንዴት እንደሚተረጉሟቸው፤ የኛም ምሁራን እንዴት እንደሚተረጉሟቸው ተማረኩ፡፡ ትርጓሜያቸው ግን ከኔ ልቡና ጋር የሚስማማ አልነበረም፡፡ ሆኖም ይህን ስሜቴን፤ ሃሳቤን ለማንም ሳልገልጽ በልቤ ይዠው ቆየሁ፡፡ ከዚያም ወደሃገሬ ወደ አክሱም ተመለስኩ፡፡ በአክሱም ለአራት አመት መጽሐፍ አስተማረኩ፡፡
ይህ ዘመን ክፉ ዘመን ሆነ፡፡ አፄ ሱስንዮስ በነገሠ በ 19ኛው ዓመት የፈረንጆች ተወላጅ አቡነ አልፎንዝ መጣ፡፡ ከ2 ዓመት በኋላም ንጉሡ የፈረንጆቹን ሃይማኖት ስለተቀበለ በኢትዮጵያ ትልቅ ስደት ሆነ፡፡ ይህን ሃይማኖት ያልተቀበለ በሙሉ ግን እጣው ስደት ሆነ፡፡

 አፄ ሱስንዮስ፣ አልፎንዝና ጠላቴ ወልደ ዮሐንስ

እኔ በሃገሬ መጻሕፍት ሳስተምር ብዙዎቹ ጓደኞቼ ጠሉኝ፡፡ በዚህ ዘመን የባልንጀራ ፍቅር ጠፍቶ ነበርና ቅናት ያዛቸው፡፡ በትምህርትና ጓደኛን በመውደድ ከነርሱ እበልጣለሁ፡፡ ከሁሉ ሰው፤ ከፈረንጆቹና ከግብጻውያን ጋር እስማማለሁ፡፡
መጻሕፍትን ሳስተምርና ስተረጉም እንዲህ እንዲህ ይላሉ፤ ግብጻዊያኖች ደግሞ (ኦርቶዶክሶች) እንዲህ እንዲህ ይላሉ እላለሁ፡፡ እኛም ብንመረምር ይህን ሁሉ እናውቃለን እላለሁ እንጅ ይህ መልካም ነው፤ ይህ ደግሞ ክፉ ነው አልልም፡፡ ግብጾቹ የፈረንጅ፣ ፈረንጆቹ ደግሞ የግብጻውያኖቹ እመስላቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ጠሉኝ፡፡ ብዙ ጊዜም ወደንጉሡ ከሰሱኝ፡፡ እግዚአብሔር ግን አዳነኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ከአክሱም ካህናት አንድ ወልደ ዮሐንስ የተባለ ጠላቴ፤ የንጉሥ ወዳጅ ስለነበረ፣ የነገሥታት ፍቅር በሽንገላ ምላስ ስለሚያገኝ ወደ ንጉሡ ሄደ፡፡ ወደ ንጉሡም ገብቶ እንደዚህ አለው ፡፡
“ይህ ሰው ህዝብን ያሳስታል፡፡ ስለሃይማኖታችን እንነሳና ንጉሡን እንግደለው፣ ፈረንጆቹንም እናባራቸው ይላል” እያለ ይሄንና ይሄን በመሰለ ውሸት ከሰሰኝ፡፡ እኔም ይህን አውቄ ገና ለገና ይገድለኛል ብዬ ፈርቼ የነበረኝን ሶስት ወቄት ወርቅና የምጸልይበትን መዝሙረ ዳዊት ይዠ በሌሊት ሸሸሁ፡፡ ወዴት እንደምሄድ ለማንም አልተናገርኩም፡፡ ወደተከዜ በረሀ ገባሁ፡፡ በነጋታውም ራበኝ፡፡

  ከሀብታሞች ገበሬዎች እንጀራ ለመለመን እየፈራሁ ወጣሁ፡፡ ሰጡኝና በልቼ እየሮጥኩ ሄድኩ፡፡ እንዲህ እያልኩ ብዙ ቀን ቆየሁ፣ በኋላ ወደ ሽዋ ግድም ስሄድ ሰው የሌለበት በርሃ አገኘሁ፡፡ ከገደሉ በታች መልካም ዋሻ ነበርና ሰው ሳያየኝ በዚህ ዋሻ እኖራለሁ ብየ ወሰንኩ፡፡ ሱስንዮስ እስኪሞትም ድረስ በዚያ 2 ዓመት ቆየሁ፡፡ አንዳንዴ ወደገበያ እየወጣሁ ወይም ወደ አምሐራ ሀገር እሄድ ነበር፡፡ ለአምሐራ ሰዎች የምበላው እንዲሰጡኝ የምለምን ባህታዊ መነኩሴ እመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች ከየት እንደምወጣና ወዴት እንደምገባ አያውቁም፡፡ ከዋሻየ ለብቻየ በሆንኩ ጊዜም በመንግሥተ ሰማያት የምኖር መሰለኝ፡፡ ቁጥር የሌለው ክፋታቸውን አውቄ ከሰዎች ጋር መኖር ጠላሁ፡፡ ሌሊት መጥተው የበርሃ አራዊት እንዳይበሉኝም በድንጋይና በአሽዋ አጥር ዋሻየን አጠርኩ፡፡
እሚፈልጉኝ ሰዎች ወደኔ ቢመጡ የማመልጥበት መውጫም አዘጋጀሁ፡፡ እዚያ በሰላም ኖርኩ፡፡ በሚሰማኝ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርጌ በሙሉ ልቤ በመዝሙረ ዳዊት ጸለይኩ፡፡

ስለአምላክ መኖርና የሐይማኖት መለያየት

ከጸሎት በኋላም ስራ ስለሌለኝ ሁልጊዜ ስለሰዎች ክፋትና ሰዎች በእርሱ ስም ሲበድሉ፣ ወንድሞቻቸውን ጓደኞቻቸውን ሲያባርሩ እና ሲገድሉ ዝም በማለቱ ስለፈጣሪ ጥበብ አስብ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ፈረንጆቹ አየሉ፡፡ ነገር ግን ያገሩ ሰዎችም ከነሱ የባሰ ክፋት ሰሩ እንጅ ፈረንጆቹ ብቻቸውን አልነበረም የከፉት፡፡ የካቶሊክ ሃይማኖት የተቀበሉት፤ ኦርቶዶክሶች የመንበረ ጴጥሮስን እውነተኛዋን ሃይማኖት ክደዋልና የእግዚአብሔር ጠላቶች ናቸው አሉ፡፡ ስለዚህም አሳደዱአቸው፡፡
ኦርቶዶክሶችም ለሃይማኖታቸው እንዲሁ አደረጉ፡፡ እግዚአብሔር የሰዎች ጠባቂ ከሆነ ለምን ፍጥረታቸው እንዲህ ከፋ ብየ አሰብኩ፡፡ በአርያም የሚያውቅ አለን ? ኧረ እግዚአብሔርስ ያውቃልን ? በቅዱስ ስሙ ሲበድሉና ሲረክሱ የሚያውቅ ከሆነ እንዴት የሰዎችን ክፋት ዝም ይላል? አልኩ፡፡
ምንም ልብ አላደረኩም ብዙ አሰብኩ፡፡ የፈጠርከኝ ፈጣሪየ ሆይ አዋቂ አድርገኝ፤ የተደበቀውን ጥበብህን ንገረኝ ብየ ጸለይኩ፡፡ ለሞት እንዳይተኙ አይኖችህን አብራቸው፤ እጆችህ አደረጉኝና ሰሩኝ፡፡ ትዕዛዝህን እንድማር ልብ ስጠኝ፡፡ ለኔ ግን እግሮቼ በተፍገመገሙ፤ ተረከዞቼም በተንሸራተቱ ነበር ፡፡ ይህም በፊቴ ስላለው ድካም ነው፡፡ ይህንን እና ይህን የመሰለ ፀሎት አደርግ ነበር፡፡
 አንድ ቀን እኔ ወደ ማን ነው የምፀልየው? አልኩ፡፡ በእውነት የሚሰማኝ እግዚአብሔር አለን? በዚህም አሳብ በጣም አዝኜ እንዲህ አልኩ፡፡ዳዊት እንዳለ እንዴት ምንኛ ልቤን አጸደኳት፡፡ ኋላም አሰብኩ።ይህ ዳዊት እንዲህ የሚለው «ጆሮን የተከለ አይሰማምን ?»  በእውነት እንድሰማበት ጆሮ የሰጠኝ ማነው? አዋቂስ አድርጎ የፈጠረኝ ማነው? በዚህስ ዓለም እኔ እንደምን መጣሁ? ከዓለም በፊት ብኖር የሕይወቴ መጀመሪያና የእውቀቴ መጀመሪያን ባወቅሁ፡፡ እኔ በገዛ እጄ ተፈጠርኩን ? ነገር ግን እኔ በተፈጠርኩ ጊዜ አልኖርኩም፡፡ አባት እናቴ ፈጠሩኝ ብልም እንደገና ወላጆችና የወላጆችን ወላጅ፣ወላጅ የሌላቸው በሌላ መንገድ ወደዚህ ዓለም የመጡትን እንደኛ ያልተወለዱትን የፊተኞቹ ድረስ ፈጣሪያቸውን እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱም ቢወለዱ የፈጠራቸው አንድ ህላዌ አለ ከማለት በቀር የጥንት መወለጃቸውን አላውቅም፡፡ ያለና በሁሉም የሚኖር የሁሉ ጌታ ሁሉን የያዘ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዓመቱ እማይቆጠር እማይለወጥ ያልተፈጠረ ፈጣሪ አለ አልኩ፡፡ ፈጣሪስ አለ፡፡ ፈጣሪ ባይኖር ፍጥረት ባልተገኘ አልኩ፡፡ እኛ ብንኖር ፍጡራን እንጅ ፈጣሪዎች አይደለንም፡፡ የፈጠረ ፈጣሪ አለ እንል ዘንድ ይገባናል፡፡ ይህም የፈጠረን ፈጣሪ አዋቂና ተናጋሪ ካልሆነ በቀር ከዕውቀቱ በተረፈ አዋቆዎችና ተናጋሪዎች አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ሁሉን ፈጥሯል ሁሉን ይይዛልና እርሱ ሁሉን ያውቃል፡፡ ፈጣሪየ ወደ እርሱ ስጸልይ ይሰማኛል ብየ ሳስብ ትልቅ ደስታ ተደሰትኩ፡፡ በትልቅ ተስፋም እየጸለይኩ ፈጣሪየን በሙሉ ልቤ ወደድኩት፡፡ ጌታየ ሆይ፤ አንተ ሃሳቤን ሁሉ ከሩቅ ታውቃለህ አልኩት፡፡ አንተ የመጀመሪያየ ነህ፡፡ የመጨረሻየን ሁሉን አወቅህ፡፡ መንገዴንም ሁሉ አንተ አስቀድመህ አወቅህ፡፡ ስለዚህም ከሩቅ ታውቃለህ ይሉሃል፡፡ እኔ ሳልፈጠር ሀሳቤን ያውቃልና ፈጣሪየ ሆይ እውቀትን ስጠኝ አልኩ፡፡

ስለ ሃይማኖት ምርመራና ፀሎት

በኋላም ይህ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈ ሁሉ እውነት ይሆን? ብየ አሰብኩ፡፡ በጣም አላወቅሁምና የተማሩና ተመራማሪ ሰዎች እውነቱን እንዲነግሩኝ ሄጄ ልጠይቃቸው ብዬ ብዙ አሰብኩ፣ እንደገናም ሰዎች በየልባቸው ያለውን ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ይመልሱልኛል ብየ አሰብኩ፡፡ ሰው ሁሉ የኔ ሃይማኖት እውነተኛ ናት ይላል፡፡ በሌላ ሃይማኖት የሚያምኑ ሐሰተኞች
የእግዚአብሔር ጠላቶች ናቸው፡፡ ዛሬም ቢሆን ፈረንጆች ሃይማኖታችን መልካም ናት፣ ሃይማኖታችሁ ግን መጥፎ ናት ይሉናል፡፡ እኛም መልሰን እንዲዚህ አይደለም፤ የናንተ ሃይማኖት መጥፎ፤ የኛ ሃይማኖት ግን መልካም ናት እንላቸዋለን፡፡
እንደገናም የእስልምና፣ የአይሁድ አማኞችን ብንጠይቃቸው እንዲሁ ይሉናል፡፡ በዚህም ክርክር ፈራጅ ማን ይሆናል? ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው ወቃሾችና ተወቃሾች ሆነዋል፡፡ አንድ እንኳን ከሰው ልጅ የሚፈርድ አይገኝም፡፡ እኔ መጀመሪያ ስለብዙ ሃይማኖቶች ጉዳይ አንድ የፈረንጅ መምህር ጠየኩ፡፡ እሱ ግን ሁሉን እንደራሱ ሃይማኖት አድርጎ ፈታው፡፡ ኋላም አንድ ትልቅ የኢትዮጵያ መምህር ጠየቅሁ ፡፡ እርሱም ሁሉን እንደ ሃይማኖቱ አድርጎ ተረጎመው፡፡ እስልምና እና አይሁድንም ብንጠይቅ እንዲሁ እንደ ሃይማኖታቸው ይተረጉማሉ፡፡ ታዲያ እውነት የሚፈርድ የት አገኛለሁ? የኔ ሃይማኖት ለኔ ትክክል እንደሚመስለኝ እንዲሁ ለሌላውም ሃይማኖቱ እውነት ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን ጽድቅ አንዲት ብቻ ናት፡፡

 እንደዚህ እያልኩ አሰብኩ፡፡ ጠቢብና የእውነተኞችም እውነተኛ እኔን የፈጠርክ ሆይ አዋቂ አድርገህ የፈጠርከኝ ሆይ፤ ዳዊት ሰው ሁሉ ዋሾ ነው ካለው በስተቀር በሰው ዘንድ ጥበብና እውነት አይገኝምና አንተ አዋቂ አድርገኝ ብዬ ጸለይኩ፡፡ ሰዎች በዚህ ትልቅ ነገር ነፍሳቸውን ለማጥፋት ስለምን ይዋሻሉ? ብየ አሰብኩ፡፡ የሚዋሹም መሰለኝ፡፡ የሚያወቁ እየመሰላቸው ምንም አያውቁምና የሚያውቁ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ እውነትን ለማግኝት ብለው አይመረምሩም፡፡ ዳዊት እንዳለው ልባችን እንደወተት ረካ፡፡ ከአባቶቻቸው በሰሙት ልባቸው ረክቷል፡፡ እውነት ወይም ሀሰት ሊሆን ይችላል ብለው አልመረመሩም፡፡ እኔም ጌታ ሆይ ፍርድህን እንዳውቅ ያሳመንከኝ ይገባኛል አልኩ፡፡
አንተ በእውነት ቅጣኝ፣ በምህረትህም ገስጸኝ፡፡ አንተ አዋቂ አድርገህ የፈጠርከኝ ጥበበኛ አድርገኝ እንጅ የዋሾ መምህራንና የኃጢአት ቅባት እራሴን አልቀባም፡፡
እኔ አዋቂ ብሆን ምን አውቃለሁ ብየ አሰብኩ፡፡ ከፍጥረት ሁሉ የሚልቅ ፈጣሪ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ከታላቅነቱ የተረፈ ታላላቅን ፈጥሯልና፡፡ ሁሉንም የሚያውቅ ነውና፡፡ ከአዋቂነቱ በተረፈ አዋቂዎች አድርጎ ፈጥሮናልና፡፡ ለርሱ ልንሰግድለት ይገባል፡፡ እርሱ የሁሉ ጌታና ሁሉንም የያዘ ነውና ወደርሱ በጸለይን ጊዜ ይሰማናል፡፡ እግዚአብሔር አዋቂ አድርጎ የፈጠረኝ በከንቱ አይደለም፡፡ እንዲህ አድርጎ የፈጠረኝ እንድፈልገውና እርሱ በጥበቡ በፈጠረኝ መንገድ እንዳውቀው እስካለሁም ድረስ እንዳመሰግነው ነው ብየ አሰብኩ፡፡ ሰዎች ሁሉ ሀሰት ካልሆነ በስተቀር ስለምን እውነት አይናገሩም ብየ አሰብኩ፡፡