Wednesday, June 4, 2014

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ችግር፤ የአንድ ጤናማ ሰው የጤንነት መስተጓጎልን ይመስላል!


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሚገጥሟት ፈተናዎች ሁሉ ከውስጧ እንደሚነሳው ፈተና የሚከፋ የለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ የኢኮኖሚ አቅሟ እያደገና ውጫዊው ተግዳሮቶቿ እየገዘፉ በመጡ ቁጥር የውስጥ ፈተናዎቿ መቀነስ ሲገባቸው በተቃራኒው እንደአዲስ ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ መከራዋ ገዝፎ መልህቅ መጣያ ወደብ እንዳጣች መርከብ በእስራ ምእቱ የአስተዳደር እክል የባህር ማእበል እየተናጠች ትገኛለች። ይህንን ውስጣዊ ፈተና በቅድሚያ አትኩሮ የሚመለከት ዓይን የሌለው ማንም ቢሆን ውጫዊ ተግዳሮቶቿን ለመመከት የሚያስችል አቅም በምንም ተአምር ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ውስጣዊ ፈተናዎቿን ለይቶ በማስቀመጥ ለመፍትሄውም መንገድ ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል። በዚሁ መሠረት ተለይተው መቀመጥ የሚገባቸውን አንኳር ችግሮች እንደታየን መጠን ለማስቀመጥ ወደድን።

ዋና ዋና ችግሮቿ፤

1/ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚችል በእውቀት፤ በልምድና በችሎታ የዳበረ ላዕላይ መዋቅር አለመኖሩ፤

2/ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ፤ ደንብና መመሪያ ጤናማ ሥራ የሚያሠራ ካለመሆኑም በላይ እንደአስፈላጊነቱ አለመሻሻሉ፤


3/ በልምድ፤ በባህልና በትውፊት እንጂ በወንጌል እውነት የታነጸና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ተከታይ ትውልድ መቅረጽ አለመቻሉ፤


በዋናነት የሚቀመጡ ናቸው ብለን እንገምታለን። ይህ ማለት አጠቃላይ ችግሮች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ችግሮቿ መነሻ የሚያደርጉት እነዚህ ሦስት ዐበይት የአንድ ሰው የሕይወት እስትንፋስን የማግኘት ያህል ህልውና ያላቸው ነጥቦች ናቸው የሚል እምነት አለን።
አንድ ሰው ሕልውና አለው የሚያሰኘው ነፍስና ሥጋው ሲዋሃድ ነው። ሥጋውም ሕይወት አለው የሚባለው አእምሮው፤ አጥንትና ጅማት ከውስጥ ሕዋሱ ጋር ተገቢ ሥራውን ማከናወን ሲችል መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ተነስተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሕይወት እንዳለው ሰው ለመቁጠር የሚያስችለን የቁመና መለኪያችን ዋና ዋና ችግሮች ከላይ በሦስት ልየታ ያስቀመጥናቸው ነጥቦች ናቸው። እንዴት? የሚለውን ቀጥለን እንመልከት።

1/ «ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚችል በመንፈስ፤ በእውቀት፤ በልምድና በችሎታ የዳበረ ላዕላይ መዋቅር አለመኖሩ» የሚለው የጉድለት ነጥብ የአንድን ሰው የአእምሮ አስተሳሰብ ይወክላል። ሰውን ከሌላው እንስሳ የሚለየው ይህ አእምሮና ከአእምሮው የተያያዘው የጀርባው አጥንት በሚያስተላልፉት ኅብለ ሰረሰራዊ መዋቅር የተነሳ ነው። አእምሮ ካልሰራ ሰው ሊያሰኝ የሚችለውን የማንነት መገለጫዎችን ለመሥራት አይችልም። ስለዚህ በዚህ ደረጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአእምሮ ማዕርግ የተቀመጠው «ቅዱስ ሲኖዶስ» የሚባለው ክፍል ነው። ይህ ላዕላይ መዋቅር ህልውና እንዳለውና ምሉዕ ሰው ሊሰራ እንደሚገባው እንደባለ አእምሮ መስራት ካልቻለ ሌላው የሰውነት ክፍል በተገቢው መንገድ ሊሰራ አይችልም። ይህ የአንድ ጤናማ ሰው ዋና ማዕከል የሆነው አእምሮ በዚህ ሰዓት በተገቢው መንገድ እየሰራ አይደለም። ስለዚህ አካል የሆነችው ቤተክርስቲያን እክል ገጥሟታል ማለት ነው። እክሎቹ በምን በምን ይገለጻሉ? የሚለውን ጥያቄ በሌላ ጽሁፍ እንመለስበታለን። በጥቅሉ ግን እዚህ ላይ ማስገንዘብ የምንፈልገው ነገር አንድ ጤናማ ሰው እንዳለው አእምሮ መስራት ያለመቻል ችግሮች ነጸብራቅ የሚመሰለው «ቅዱስ ሲኖዶስ» ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አለመቻሉና የመንፈሳዊነት ብቃት፤ የእውቀት፤ የልምድና የችሎታ ጉድለት ስለሚታይበት የቤተ ክርስቲያኒቱ አእምሮ ችግር ላይ መሆኑን እንረዳለን ማለት ነው። አእምሮ ካልሰራ፤ ሰው ጤናማ ሊሆን አይችልም። ይህ አእምሮና የኅብለ ሰረሰር መዋቅሩ የሚታከመው እንዴት ነው? ጤናማ ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን ታማለች ማለት ነው።

2/  «የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ፤ ደንብና መመሪያ ጤናማ ሥራ የሚያሠራ ካለመሆኑም በላይ እንደአስፈላጊነቱ አለመሻሻሉ» የሚለው ነጥብ ምሳሌነቱን ወስደን ለአንድ እንደ ባለአእምሮ ጤናማ ሰው ግዘፈ አካል ብንወስድና ብንተረጉመው የሰውየውን ሥጋ የውስጥ አካሎቹን ያሳየናል። ሕግ፤ ደንብ፤ መመሪያና ሌሎች የማስፈጸሚያ ስልቶች ማለት «ልብ፤ ኩላሊት፤ ጉበት ወዘተ» ውስጣዊ የዝውውር ሕዋሳትን ይወክላል። ጤናማ አእምሮ የሌለው ሰው ካለበት ችግር በተጨማሪ ከእነዚህ ውስጣዊ አካላቱ ውስጥ በአንዱ ላይ ሌላ እክል ካለበት የሕመሙን መጠን የከፋ ያደርገዋል። ስለዚህ ሲኖዶሱ እንደባለ አእምሮ ፤ አእምሮውን ማሠራት አለመቻሉ እንዳለ ሆኖ በላይ የሰው ልጅ የሕልውና ክፍሎቹ እንደሆኑት የውስጥ አካላቱ ተጨማሪ እክል ዓይነት የሕግ፤ የደንብ፤ የመመሪያ ወይም የማስፈጸሚያ ስልቶች ዓይነትና መጠን ተገቢ የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያስችል ካልሆነ በሽታው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም። ከአእምሮው ላይ በተጨማሪ ከውስጥ ክፍሎቹ ባንዱ ላይ ችግር የገጠመውን አንድ ሰው እስኪ በዓይነ ልቡናዎ ይሳሉና ይመልከቱ! እጅግ አሳዛኝና አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ለመረዳት የሚከብድዎ አይመስለንም። ቤተ ክርስቲያን አእምሮውን በታመመ አመራር ስር መሆኗ ሳያንስ ስራዋን በተገቢውን መንገድ የሚያስኬድላት የውስጥ አካላቷን መጠበቂያ ማዕቀፍ አለመኖሩ የችግሯን ውስብስብነት የሚያሳይ ይሆናል።

3/ በልምድ፤ በባህልና በትውፊት እንጂ በወንጌል እውነት የታነጸና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ተከታይ ትውልድ መቅረጽ አለመቻሉ፤ የሚለውን ደግሞ የአንድ ምሉዕ ሰው ወሳኝ የክፍል እንቅስቃሴ ምሳሌያዊ መገለጫ አድርገን ብንወስደው  ደም፤ አጥንት፤ ጅማትና ቆዳን ይወክልልናል። ሰውየው ግዘፍ እንዲነሳ የሚያደርጉት፤ እንቅስቃሴውን የሚወስኑትና የዑደት ዝውውሩን የሚያገናኙት እነዚህ ዋና የሰውነት ክፍሎቹ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ስንል የክርስቶስ ጉባዔ ምዕመናን ማለታችን እንደመሆኑ መጠን ለቤተ ክርስቲያን ኅልውና ደም፤ አጥንት፤ ጅማትና ቆዳ ሆኖ ያስተሳሰረው ይህ የመዘወሪያ አካል ንጹህ፤ ያልተበከለ፤ ያልተጣመመና ጤናማ የህንጻ ክፍል ካልሆነ ጉባዔ ቤተ ክርስቲያን ጤናማ ልትሆን በጭራሽ አትችልም። በነዚህ መሠረቶች ላይ የቆመው አካላዊ ህልውና የዝውውር ዑደቱ ከፈጣሪው በተቸረውና እፍ በተባለበት የሕይወት እስትንፋሱ በኩል አምላኩን በተገቢው ሊያመሰግን አለመቻሉ ጉባዔው የሚታወክ፤ የሚታመስ፤ በወሬ በሽታ የተጠመደ ይሆናል። በእድሜው መኖር በመቻሉና ነፍስያው አለመለየቷ ብቻውን አንድን ሰው ሕያው ሰው አያሰኘውም። በመንፈሱ የሞተ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ የለውም።
«በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና» ሮሜ 8፤14
በዚህም የተነሳ ጉባዔ አክሌሲያ እንደሆነ የሚታሰበው ትውልድ በልምድ፤ በባህል፤ በትውፊት ገመድ ተጠፍንጎ ከወንጌል እውነት ሳይታረቅና ፈሪሃ እግዚአብሔርን በልቡናው ሰሌዳ ላይ ሳይጽፍ ነገር ግን አንገቱ ላይ የመስቀልና ምስል አንጠልጥሎ የሚሳደብ፤ የሚዋሽ፤ የሚሰክር፤ የሚያጨስ፤የሚያመነዝር፤ የሚሰርቅ፤ እምነት የማይጣልበት የባህል እምነት ተከታይ ሆኖ የሚታየው የእውነትን ወንጌል በመጋት አሳድጎ የቃሉን አጥንት መጋጥ ወደሚያስችል ሰውነት ማድረስ ስላልተቻለ ነው። በእምነት ሳይሆን በሃይማኖት የኖረውም በልምድ እንጂ እውነት ስለገባው አይደለም።  «እውነት ባለበት በዚያ አርነት አለ» የተባለው አንገት ላይ መስቀል አንጠልጥሎ ነገር ግን ነጻ እንዳልወጣ ሰው የሥጋ ሥራ የሚሰራ ሰው ማለት አይደለም። ስለዚህ ትውልዱ በወንጌል ነጻ የመሆን የእውነት ቃል ተኮትኩቶና በቀደምት አባቶቹ አስተምህሮ ታንጾ ባለመኖሩ አርነት ያልወጣ ሰው የሚያደርገውን የሥጋ ሥራ እየፈጸመ  በስም ክርስቲያን እየተሰኘ የባህልና የልምድ ተከታይ ሆኖ እንዲኖር ተፈርዶበታል።  ከልምድና ከባህል መንፈስ ነጻ መውጣት አለበት።
2ኛ ቆሮንቶስ 3፥17  «ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ»

ማጠቃለያ፤

አንድ ሰው ጤናማ የሚባለው አእምሮው፤ ኅብለ ሰረሰሩ፤ የውስጥ አካላቶቹ፤ ደም፤ ስጋ፤ አጥንትና ጅማቱ ተዋሕደው በጤንነት ሲገኙ ነው። ምሉዕ ሰው ሆኖ ሕይወት ያለው መንፈሳዊ ጤንነቱ የሚጠበቀው ደግሞ የነፍስያው ራስ የሆነው ፈጣሪውን ሲያውቅና በተገቢው መንገድ ሲያመልክ ብቻ ነው። ከእነዚህ ባንዱ ጉድለት ቢገኝ አደጋ ውስጥ መሆኑ እርግጥ ነው። ከዚህ ተነስተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን የሕይወት ኅልውና ስንመለከት ጤናማ ሁኔታ ውስጥ እንዳይደለች ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች ያስረዱናል። የተከታዮቿ ቁጥር ወደታች የማሽቆልቆሉ ምክንያት የበሽታውን ደረጃ ያሳየናል። የአስተዳደር ሰላም አለመኖር፤ የነበራት ክብርና ተደማጭነት ማነሱም የገጠማት የህመም ደረጃ አደገኛ መሆኑን ያስረዳናል። የመከፈፋሏ መነሻ፤ የመከባበር ድቀት፤ የነውር ገመና ማደግ፤ ዋልጌነት፤ የብክነትና የዝርፊያው የትየሌለነት የበሽታዋ ደረጃ ምን ያህል እንደገዘፈ ለማወቅ ምርምር አይጠይቀንም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ያልጠፋችውም ከእግዚአብሔር ታጋሽነትና ለንስሐ የሚሆን እድሜ ከመስጠት አምላካዊ ባሕርይው የተነሳ ይመስለናል። እንደሚገባን ሆነን መልካም ፍሬ ካላፈራን ግን መቆረጣችን አይቀርም።
የፈለገውን ያህል ተኩራርተን የቀደመችቱ መንገድ እያልን ብንደሰኩር ከእግዚአብሔር አስቀድሞ የተቀበልነውንና የሰማውን ዛሬ ይዘን በተግባር ካልተገኘን ከያዝነው የቁልቁለት መንገድ አያድነንም።  በአንድ ወቅት በትንሹ እስያ ለነበረችውና በተመሳሳይ የቁልቁሊት መንገድ ላይ ለነበረችው ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን በዮሐንስ በኩል መልእክት ደርሷት ነበር።  ነገር ግን መስማት ስላልቻለች እየወረደች ካለበት የቁልቁሊት መንገድ ወጥታ፤ ስህተቶቿን አርማ፤ በእውነት የጌታዋ መንገድ ላይ ለመጓዝ የሚያስችላትን የንስሐ እድሜ ባለመጠቀሟ ከ500 ዓመት በኋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጥፋት በቅታለች። በፍርስራሾቿ ላይም የእስልምና አዛን የሚያስተጋባባት የታሪክ ቤተ ክርስቲያን ሆናለች። ከመሆኗ በፊት የተነገራት ቃል ይህ ነበር።
«እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም» ዮሐ 3፤3
( በቀጣይ ጽሁፋችን  ዝርዝር ነገሮችን ለማየት እንሞክራለን)

Thursday, May 29, 2014

በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲፈጸም የቆየው የሊቃነ ጳጳሳቱ አድማና የማኅበረ ቅዱሳን ጣልቃ ገብነት በአቡነ ማትያስ ላይም ቀጥሏል!

ከሊቃነ ጳጳሳቱ ግማሾቹ የራሳቸውን የጉባዔ ላይ የድምጽ ጡንቻ በማፈርጠም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከሚመስሏቸው ጋር የመቀናጀት ጠባያቸው ከምንኩስና ጀምሮ የተዋረሳቸው እንጂ ድንገት የተከሰተባቸው ዐመል አይደለም። ገሚሶቹ ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ከዚህ ፈርጣማና  ጠንካራ የቡድን  አቅም መፍጠር ከቻሉት ጋር መለጠፍ የሚፈልጉት አንድም ብቻቸውን መዝለቅ እንደማይችሉ ስለሚያውቁ፤ በሌላ መልኩም ሊመጣ ይችላል ከሚሉት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ከመፈለግ ራስን የማዳን ዘዴ የተነሳ ነው። ጥቂቶች ቢሆኑም አንዳንዶቹ ደግሞ ያልሆነ ንትርክና ጭቅጭቅ እንዲነሳ የማይፈልጉ፤ ዝም ብለው በመመልከት ታዛቢ የሚመስሉ በእድሜ የገፉ ሲሆኑ በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ ስለቤተክርስቲያን የሚገዳቸው ነገር ግን ድምጻቸው ብዙም የማይሰማላቸው ናቸው።
 የቡድን ኃይል መፍጠር የቻሉት አብዛኛዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት የወጣትነት ዐመል ብዙም ያልራቃቸው፤ በቂ ኃብት ማከማቸት የቻሉ፤ ለተሸከሙት ማዕርግ ሳይሆን ለስምና ለዝና የሚጨነቁ በተለይም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ንክኪ ያላቸው ናቸው። እነዚህኞቹ ለቤተ ክርስቲያን የሚታይ፤ የሚጨበጥ፤ ለትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ ቅርስና ሀብት መፍጠር ያልቻሉ ነገር ግን በምላስ የሰለጠኑ፤ እምቢተኝነትና ቡድንተኝነት እውቀት የሚመስላቸው ናቸው። ቤተክርስቲያን መታመስ የጀመረችው እነዚህኞቹ ቅዱስ ወደተባለው ሲኖዶስ የመቀላቀል እድል ካጋጠማቸው በኋላ ነው። ማኅበረ ቅዱሳንም ከሀገር ቤት እስከ ውጪ ሀገር ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ መልክና ቁመና ስሩን የሰደደው በእነዚህኞቹ ጀርባ ታዝሎና ተንጠላጥሎ ነው።
የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እግር ተወርች አስረው አላሰራ ሲሉ የነበሩት እነዚህ ቡድንተኞች ዛሬም አንድ ግንባር ፈጥረው እድሜ ካላስተማራቸው አረጋውኑ መካከል ጥቂቶቹን አሰልፈው ማኅበረ ቅዱሳንን ከጀርባቸው አቁመው ፓትርያርክ ማትያስንም በተመሳሳይ መልኩ አላሰራ፤ አላንቀሳቅስ፤ አላላውስ እያሏቸው ይገኛል። በዚህ መልኩ የት ድረስ መጓዝ እንደሚቻል ለመገመት አይከብድም። ነገር ግን «ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም» እንዲሉ አበው መላ መፈለግ ፓትርያርክ ማለት «ርእሰ አበው» ማለት እንደመሆኑ መጠን የተሰጠውን ሥልጣን ለቡድንተኞች አስረክቦ የተነገረውን የሚቀበል ተላላኪ ማለት ባለመሆኑ ሥልጣኑ ሙሉዕ መሆኑን ማመን የግድ ይሆናል። ስለዚህ በአድመኝነት፤ ለማኅበሩ ወግነው አላሰራ ለሚሉ ምን መደረግ አለበት?  ነገሮች እየጠሩ፤ የችግሩም ገፈት ከላይ ካልተወገደ በስተቀር ተለባብሶ የትም አይደረስም። ቤተ ክርስቲያንም አትድንም፤ ባለማዕርጎቹም በዘመናቸው ንስሐ አይገቡም። ስለዚህ የማያወላዳ እርምጃና ውሳኔ ያለምንም ማቅማማት መውሰድ የግድ ይላል። ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ።
1/ ከአድመኞቹ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ብዙዎቹ ቃል የገቡበትን መሃላ አፍርሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተጠሪ ነን ካሉ በኋላ ደመወዝተኛ፤ አበልተኛና የጥቅሟ ተከፋይ ሲያበቁ መንፈሳዊነቱን ክደው፤ ሀብት ንብረት አፍርተው ፤ እንደዓለማውያኑ የሚሊዮን ብር ቤቶችን የገነቡ፤ በባንክ ያከማቹ ስለመሆናቸው መረጃና ማስረጃ የሚቀርብባቸው ስለሆነ በሊቀ ጳጳስነት ማዕርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት ብቻ ለማገልገል  ብቃት የሚጎድላቸውና «ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም» ያለውን የወንጌል ቃል ያፈረሱ ስለሆነ ከያዙት ማዕርግ ተሰናብተው ወደዓለማዊ ሀብታቸው እንዲሄዱ ሊሸኙ ይገባል።
2/ ገሚሶቹ ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ መሃላ ከፈጸሙበት «ኩሎ ኀደግነ» ሁሉን ትተን ተከተልንህ ካሉ በኋላ በቀጥታ ያለሰማንያ ጋብቻ በትዳር ወልደው ከብደው የሚኖሩ፤ ገሚሱም በአዲሱ የቤተሰብ ህግ እንደተመለከተው « ትዳር በሚመስል ሁኔታ አብሮ መኖር ራሱ ጋብቻ እንደተፈጸመ ይገመታል» በሚል የህግ መንፈስ መሰረት አግብተው ዓለሙም፤ ሊቀጵጵስናውም ሁሉም ሳይቀርባቸው አጣምረው የያዙ ስለሆነ በእነዚህኞቹ «ጸሊማን አርጋብ»  ላይ በቂ ማስረጃ መቅረብ ስለሚችል በማያወላዳ ውሳኔ ለሌሎች ትምህርት ሊሆን በሚችል መልኩ ለትዳራቸው ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ በክብር መሸኘት አለባቸው።
3/ ለዚህ ጥሩ አብነትና ምሳሌ ሊሆን የሚችለው በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዚህዓለም በሞት የተለዩት የአቡነ ሺኖዳ አስተዳደር ተጠቃሽ ነው። ሊቃነ ጳጳሳት የራሳቸውን ሀብት ማፍራት አይችሉም። መነኮሳት ከመነኮሱበት ገዳም ውጪ ሌላ ገዳም በፍጹም አይቀበላቸውም። ከገዳሙ ከወጣ ምንኩስናውን እንደተወ ይቆጠራል። በሴት የተጠረጠረ መነኩሴ በቀጥታ ተጠርቶ ይጠየቃል እንጂ እንደኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተሸፋፍኖ ያሻውን እንዲፈጽም እድል አይሰጠውም። መረጃና ማስረጃ ከቀረበበት ቀሚሱን ከታች አንስቶ፤ እስከ አንገቱ ድረስ መሃል ለመሃል በመቀስ ቀደው መቋቋሚያ ገንዘብ ሰጥተው ሕዝባዊ እንዲሆን ያሰናብቱታል። ይህ ለሌላው ትምህርት፤ ለቤተ ክርስቲያንም ክብር ይሆናል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ነገር በዚህ ዘመን አሳፋሪ ሆኗል። ከሊቃነ ጳጳሳቱ ትዳር የመሰረቱ ሞልተዋል። የመነኮሳት ነጋዴ መሆናቸው ሳይታወቅ ሚሊየነር ሆነዋል። ዝሙትና ስርቆት ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደነቀዝ እየበላት ነው። በዚህ መልኩ ከቀጠለች የቤተ ክርስቲያኒቱ ኅልውና አስጊ ነው። እዚህ ላይ ከነጋ ድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ መጽሐፍ ጥቂት ቃል እንዋስ። «እግዚአብሔር መንግሥታችንን፤ ቤተክርስቲያናችንን ለባዕድ አሳልፎ አይሰጣትም እያለ ሕዝባችን በስንፍና ያለሥራ ይኖራል» እውነትም ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ከጥፋት ተከላከለን፤ ነገር ግን እኛ ለቸርነቱ የተገባውን ሥራ ሠርተን በተግባር አላሳየንም» ብለዋል ነጋድራስ በጽሁፋቸው ከዛሬ ሰማንያ ዓመት በፊት።  ይሁን እንጂ ዛሬም ከስንፍናችን ፈቀቅ አላልንም። እግዚአብሔር ራሱ ይጠብቅ ብለን እኛው ያጠፋናትን ቤተ ክርስቲያን እንደባለእዳ ትተንለታል።
4/ ማኅበረ ቅዱሳን ማነው? የማነው? ምንድነው? ብዙ የሚያጠያይቅ ጉዳይ ነው። የጠራና የማያሻማ መልስ ያስፈልገዋል። ተለባብሶ በበግ ለምድ ተሸሽጎ አይዘለቅም። ስለማኅበረ ቅዱሳን ጥብቅና የሚቆም ማንም ቢኖር የማኅበሩ አባል የመሆን መብቱ የተከበረ ነው። ነገር ግን ሊቀጳጳስ ከሆነ በኋላ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን የሲኖዶስ አባልነት ሥልጣን ይዞ የማኅበረ ቅዱሳን አባል መሆን አይችልም። መሆን ከፈለገ ጵጵስናውን ማስረከብ አለበት።  አንድ ሚኒስትር የኢህአዴግ ምክርቤት አባልና የሰማያዊ ፓርቲ አባል በአንድ ጊዜ መሆን አይችልም። አንዱን ይተዋል፤ ወደአንዱ ይጠጋል እንጂ። ይህንን ለማስተካከል የፓትርያርኩ ሥልጣን ምሉዕ ነው። እነዚህ በሁለት ልብ ሲኖዶሱን የሚያውኩ ጳጳሳት በህግ አግባብ ካልተወገዱ የሲኖዶስ ሕውከት ማብቂያ አይኖረውም። ስለማኅበረ ቅዱሳን የሚከራከር ሊቀጳጳስ ከሲኖዶስ አባልነቱ ወደታች ወርዶ የተራ ማኅበር ደጋፊ ከሆነ ማዕርጉን ተገፎ  በማኅበር አባልነቱ እንዲቀጥል ከሲኖዶስ ሊባረር ይገባዋል።
5/ ፓትርያርክ ማትያስ ቆምጨጭ ያለና እርምት የሚሰጥ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ በእንደዚህ ዓይነት የአድማና የቡድን ጭቅጭቅ እየተሰላቹ የትም አይደርሱም። ሊቀጳጳስ የሚባለው ማዕርግ ሊከበር የሚችለው ራሱ ማዕርጉን የተሸከው ሰው አክብሮ፤ የሚያስከብር ሥራ ሲሰራበት ብቻ ነው። ሹመትማ ይሁዳም ከሐዋርያት አንዱ ነበር። ነገር ግን ጥፋት እንጂ ልማት አልሰራበትምና ሐዋርያ መባሉ ቀርቶ «ሰያጤ እግዚኡ» ከመባል አልዳነም። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያንን ከመሸጥ የማይመለሱ እነዚህ አድመኞች ሊቃነ ጳጳሳት ሻጮች ቢባሉ ምንም አያስነውርም። ስም መጥቀስ አያስፈልግም እንጂ እነማን ማናቸው? ምን አደረጉ? ምንሰሩ? በደንብ ይታወቃል።
6/ ቤተ ክርስቲያንን ከውድቀት ለማዳን፤ ማዕርጋት ዋጋና ክብር እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲባል ያልተፈለገ ነገር ግን አስገዳጅ እርምጃ እስከመውሰድ የሚዘልቅ ክስተት መፈጠሩ አይቀርም።  ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ ከሚቆጠቁጠው የመንፈሳዊ ኅሊና ቁጭትና ከታሪክ ወቀሳ ለመዳን መስራት የሚገባውን ሁሉ ካልሰሩበት ማዕርጉን ተሸክሞ መቀመጥ በቤተክርስቲያን ውድቀት ላይ መተባበር በመሆኑ ሹመቱን አስረክቦ የራስን ነጻነት ማወጅ የተሻለ ነው።
በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲፈጸም የቆየው የሊቃነጳጳሳቱ አድማና የማኅበሩ ሴራ በአቡነ ማትያስም ላይ የሚቀጥለው  እስከመቼ ነው?
 አቡነ ማትያስ አርፈው የማኅበሩ አባል ሊቀ ጳጳስ ሌላ ፓትርያርክ እስኪሆን ድረስ ይህ ውጊያ አያቆምም።

Thursday, May 22, 2014

ግዝት(ውግዘት)…ኑፋቄ….መናፍቅነት…ግዝት-ዘበከንቱ… እና ወፈ-ገዝት መሆን!


 ( በአማን ነጸረ )
1. ግዝት(ውግዘት)፡ ማለት አንድ ምዕመን(አማኝ) በአፉ ክርስቲያን ነኝ ቢልም በተግባር ከሃይማኖት ወጥቶ ከበጎ ምግባር አድጦ(ተዛንፎ) ሲገኝ ከማኅበረ ምዕመናን እንዲለይ በስልጣነ-ክህነት የሚፈጸም መንፈሳዊ ቅጣት ነው፡፡
2. የውግዘት ዓላማ፡(ሀ)ቤ/ክ እንዳትረክስ፣(ለ)ኑፋቄው ወደ ሌሎች እንዳይዛመት፣(ሐ)ተወጋዡ በንስሐ እንዲመለስ እድል ለመስጠት ነው፡፡
3. የውግዘት ቅድመ-ሁኔታዎች፡(ሀ)ተጠርጣሪው ከሃይማኖት እና/ወይም ከበጎ ምግባር መውጣቱን ማረጋገጥ፣(ለ)ከጥፋቱ/ከክህደቱ እንዲመለስ ደጋግሞ መገሰጽና መምከር፣(ሐ)ተመክሮ ካልተመለሰ በስልጣነ-ክህነት አውግዞ መለየት፣(4)ውግዘቱ እንደጥሰቱ ዓይነት ከማዕረግ ዝቅ ማድረግ ወይም ስመ-ክርስትናን ነጥቆ መለየት ሊሆን ይችላል፡፡ከዚህ በኋላ ድርጊቱ-ኑፋቄ ተወጋዡም-መናፍቅ ይባላሉ፡፡በነገራችን ላይ ምንፍቅና የሚል ቃል በየመጻህፍቱ አላየንም፡፡በግእዙ ኑፋቄ ነው የሚባለው፡፡በአማርኛ መናፍቅነት፡፡
4. ግዝት-ዘበከንቱ እና ወፈ-ገዝት መሆን፡ ከላይ ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ያላሟላ ግዝት ግዝት-ዘበከንቱ ሲባል ገዛቹም ወፈ-ገዝት ይባላል፡፡ነገር ግን ተጠርጣሪው በግልጽ የተወገዘ ሃይማኖትንና ምግባርን ሲያራምድ ያገኘነው እንደሆነ መናፍቅ ብንለው ፍርድ የለብንም፡፡
5. ከንቱ እና ከንቱ አንድ ወገን ብለን ስለመርገም ዘበከንቱም እንናገር፡ ሀቅ ላይ ያልተመሰረተና የሚረገመውን ሰው ህሊና የመውቀስ አቅም የሌለው ከንቱ እርግማን በመጽሐፈ ምሳሌ 26 ቁ 2 እንደተገለጸው….እንደሚተላለፍ ድንቢጥ፣ወዲያና ወዲህም እንደሚበር ጨረባ እንዲሁም ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም፡፡ፍትሐ ነገስቱም በአንቀጽ 11 እንዲህ አይነቱን ረጋሚ “ወኩሎ ዘይረግም ይረግም ነፍሶ” ይለዋል::
ምንጭ፡ (1) መርሐጽድቅ ባህለ ሃይማኖት በ1988 ዓ.ም በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የታተመ ገጽ 157 እስከ 161 ፣ (2)የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ-237፣ (3) ጥቅሶች፡ ማቴ 18 ቁ 15-18፣2ተሰ 3ቁ14፣ቲቶ 3 ቁ 11፣1ጢሞ 1ቁ 19፣2ጢሞ 2 ቁ 17፣1ቆሮ 5 ቁ 5፣2ቆሮ 2 ቁ 6
መነሻ፡ በ40 ቀን ያገኘነውን ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ባልተሰጠ ስልጣነ-ክህነት ሊነጥቁ የሚሞክሩ ወፈ-ገዝት ወንድሞቻችን!!