Wednesday, January 15, 2014

ትግርኛ ተናጋሪ ጎንደሬው ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ ከጎንደሬዎች ጋር እየመከሩ ነው!!


( ከብሶቴ ተሰማ አዲስ አበባ )
ዘር ለእህል ነው። የእህል ዘር ግንዱ አንድ አይደለም። ዘሩ በየመልኩ ልዩ ልዩ ነው። የሰው ልጅ ግን እንደዚያ አይደለም። መልኩ ቢለያይም ግንዱ አንድ አዳምና ሔዋን ናቸው። ከዚያም በላይ ሁላችንም በክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ  አንድ ሆነናል። ይሁን እንጂ ክርስትናን ከስምና ከሹመት በስተቀር የማያውቁ አንዳንዶች ዛሬም  የሰውን ልጅ ከእህል የዘር ዓይነት ቆጠራ ራቅ ብለው ለማየት እንዳልቻሉ እርግጥ ነው።
ከእነዚህም አንዱ አባ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የማኅበረ ቅዱሳን ሊቀጳጳስ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን አንዲት ብትሆንም በአስተዳደር ይዞታዋ የተለያየ በመሆኑ ሊቀ ጳጳሱ በጅማ ሀ/ስብከት ሳሉ ገመናቸው ተሸፍኖ፤ በሰው መሳይ ሸንጎ ተከልለው በሰላም ይኖሩ ነበር።  ኅሊናቸውን አሳርፈው መኖር የሚችሉበትን ሀ/ስብከት ይዘው አርፈው እንደመቀመጥ ከወታደሮች ማኅበር ጋር አብረው በመቆም የእድሜ ልክ መጽሐፋቸው ይነበብ ዘንድ በየቦታው አለሁ ማለታቸው ያሳዝናል።  ደርሶ መንፈሳዊ መስሎ ለመታየት የአበው አጥንት ይወቅሰናል፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይፋረደናል በሚል በአስመሳይ ተቆርቋሪነት የማኅበሩን ዓላማ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለታቸው ለእርሳቸው የትጉህ ሰራተኛ ትግል ቢመስላቸውም እውነቱን ለሚያዩ ግን ያለቦታቸው በአጉል ሰዓት የተገኙ  ሰው ናቸው። ከአባ ገብርኤል ጋር ከአስመራ ጀምሮ በድሬዳዋ ዞረው፤ አዲስ አበባን አካለው ኮተቤ 02 እስካሳነጹት የመኖሪያ ህንጻ ድረስ ብዙ ጉድ መኖሩን የምናውቅ እናውቀዋለን።
በእርግጥ ሊቀጳጳሱ( ከተባሉ) ዓይናቸውን በጨው የታጠቡ ስለሆነ ስለበደልና ጥፋት ትንሽ ስሜት አይሰጣቸውም። የኅሊና ጸጸትም ፈጽሞ አይነካካቸውም። ከድፍረቱ ጋር የደነደነ ልብ ስለታጠቁ የተባለው ቢባል፤ የተወራው ቢወራ ደንታ የላቸውም። ለዚህም ነው ከበደል ጋር ዕረፍት በሌለው ወዳጅነት እስከ ህይወታቸው ህቅታ ድረስ ቃል በመግባት ዛሬም የአንድ ተራ ማኅበር ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው የመገኘታቸው ነገር  አረጋጋጭ ነው። በመሰረቱ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ለማስተዳደር ራሱ ከሙስናና ከአስነዋሪ ስነ ምግባር የጸዳ መሆን ይገባው ነበር። አፉን ሞልቶ ለመናገር፤ ሌባና ብልሹ አስተዳደር ለማስተካከል የሚችለው ከዚህ የጸዳ ቢሆንም አባ እስጢፋኖስ ግን ለአባ ማትያስ በዋሉላቸው ውለታ የተነሳ በስራ አስኪያጅነት ዘመናቸው በጉቦ የጋጡትን ሀ/ስብከት  በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስነት ስም ተመልሰው ባልያዙም ነበር። በዚህ ዘመን ከሰጪም፤ ከተቀባይም ኅሊና የሚባል ነገር ስለጠፋ እያየነው ያለው ሊሆን ግድ ሆነ።
በአዲስ አባ ሀስብከት ውስጥ መልካም አስተዳደር እንዲመጣ ካስፈለገ ያለው አማራጭ የአባ እስጢፋኖስ ከቦታው ማስነሳት ብቻ ነው። የተባለውም መዋቅር ጥናት እንደአዲስ ከሚታይ በስተቀር በእሳቸው አስፈጻሚነትና በማኅበሩ ገፊነት ችግሮችን ያባብሳል እንጂ ፈቺ ሊሆን አይችልም። /ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ/ ችግሮችን ያባብሳል እንጂ ፈቺ ሊሆን አይችልም።
አባ እስጢፋኖስ የጎንደር ተወላጅ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችንና የሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቃነ መናብርትን በደጋፊነት በማሰለፍ በማቅ የተዘጋጀውን የመዋቅራዊ ለውጥ በተግባር ላይ ለማዋልና ከጀርባቸው ያለውን አሳፋሪ ታሪክ ለመደበቅ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡
አቡነ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት በእሳቸው ድጋፍ የድራፍት ቡድን በማቋቋም አዲስ አበባን ሲያውኳት እንደነበር ቀደምት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ያን ጊዜ ስያሜውን ያገኘው የድራፍት ቡድን አባ እስጢፋኖስን ቤተክርስቲያን ወንበር ላይ በስራ አስኪያጅነት አስቀምጦ በከተማዋ በሚገኙ ዝነኛ ሆቴሎች በመቀመጥ ቅጥር ዝውውርና እድገት በመስተት መላውን የቤተክርስቲያኒቱ ሰራተኞች ሲያበጣብጥ በወቅቱ በጉዳዩ መንግሥት እጁን አስገብቶ እሳቸውንም ከኃላፊነታቸው ድራፍት ቡድኑንም ከጣልቃ ገብነቱ በመግታት በወቅቱ ሰላም ተገኝቶ ቆይቷል፡፡ ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለው ዛሬም ሳይገባቸው ያገኙትን አስኬማ ለዚሁ ሰላም አደፍራሽ ለሆነ ተልእኮ በመጠቀም በመላው አዲስ አበባ በመንግሥት ላይ ካኮረፈው የማቅ ቡድን ጋር በመሆን  ዛሬም ቤተክርስቲያኒቱን እያወኩ ይገኛሉ፡፡
በቅርቡ በማቅ ቡድን ራዕይ መሠረት ቤተክርስቲያኗን ለመቆጣጠር  በተዘረጋው ወጥመድ መዋቅራዊ ለውጥ በሚል የተዘረጋው ስውር እስትራቴጂ በግልጽ የቤተክርስቲያኗ ችግር መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ በማቅ የተዘጋጀው የመዋቅራዊ ጥናት ውድቅ ሁኖ በቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት ሁሉን ያማከለ ሕግ እና መመሪያ እንዲወጣ የማቅን የሽብር ሴራ ቀድመው ለተገነዘቡ አገልጋዮች ቃል ገብተው ነበር፡፡ አቡነ እስጢፋኖስ ከቤተክርስቲያኗ ሕግ ውጪ የወለዷቸውንና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በቁጥጥር እና ሒሳብ ሹም የቀጠሯቸው ልጆቻቸው ጉዳይ እንዲጣራም ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ታድያ ይህ አካሄድ ያሰጋቸው አቡነ እስጢፋኖስ በፖለቲካ ምክንያት የተገለሉና አካላቸው ኢትዮጵያ ሆኖ ልባቸው  የሰሜን አሜሪካው ሲኖዶስ  ጋር የሆኑ የጎንደር ተወላጅ አለቆችን በመሰብሰብ ይኸው የልጆቻቸው ጉዳይ ተዳፍኖ እንዲቆይና መዋቅራዊ ጥናቱ በተገባር ላይ እንዲውል የእሳቸው ሥላጣን ቆይታን የሚያረጋግጥ ውሳኔ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያስወስኑ አደራ በማለት አሰማርተዋቸዋል፡፡ በየትኛውም ወገን አዲሱ መተዳደሪያ ሕግ ተግባራዊ ቢሆን  በሚፈጠረው አለመግባባት ሐገር ሲታመስ ከዚሁ ብጥብጥ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘትና የሰሜን አሜሪካው ሲኖዶስ ከብጥብጡ መልካም አጋጣሚ እንዲያገኝ ጥረታቸውን በመቀጠል ፓትርያርኩ ድረስ ዘልቀው የአደራ መልእክታቸውን አሰምተዋል፡፡
የአቡነ እስጢፋኖስ የሀገር ልጅና የጥቅም ተሳታፊ የሆነው የአፍሪካ ኅብረቱ ዋና ጸሐፊ አቶ አብርሃም አቧሀይ የእነዚህ የጎንደር ኃይሎች ዋና አደራጅና መሪ ሲሆን እራሳቸውንም የአርበኞች ግንባር ብለው ሰይመው ፓትርያርኩ ዘንድ በመቅረብ የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመፈጸም ሞክረዋል፡፡ የጳሳሳት ልብስ ሰፊው ወርቁ አየለ ፤ የየረር ዑራኤል አለቃ ዘማርያም ሙጬ፤ የጃቲ ኪዳነምሕረት አስተዳዳሪ፤ የደብረሲና እግዚአብሔር አብ ምክትል ሊቀ መንበር፤   እና የሰሚት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ገብረ ስላሴ ከጎንደር ተወላጅ ሊቃነ መናብርቶቻቸው ጋር በመሆን ብዙ ባሉበት ስብሰባ  የአቡነ እስጢፋኖስ ሥልጣን እንዲራዘም ልመናቸውን ለፓትርያርኩ አቅርበዋል፡፡
ከአቡነ እስጢፋኖስ ተቃዋሚዎች ይቅርታ ጠይቀዋል በማለት  አዲስ ፕሮፓጋንዳ በማናፈስ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ለማስበርገግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እንደ ሌሊት ወፍ ከዚህኛውም ከዚያኛውም ቡድን አለሁ በማለት በመሀል ሰፋሪነት አንዴ ተቃዋሚ ሌላ ጊዜ ደጋፊ አሁን ደግሞ አስታራቂ የሆነውና የቦሌ መድኃኔዓለምን ጸሐፊነት ላለመነጠቅ በሚባዝነው በቀሲስ ሰሎሞን በቀለ አስታራቂነት ይቅርታ የጠየቁት የሲኤምሲ ሚካኤል አለቃ መ/ር ዘካርያስ ሲሆኑ እሳቸውም ይቅርታ የጠየቁት አዲስ በሚሰራው  ካቴድራል ስም የሚገባ ሲሚንቶ  ከንብረት ክፍል ኃላፊዋ ወ/ሮ ሰርክ አዲስ እና ከምክትል ጸሐፊው ፋንታሁን ከሙጨ ወንድም ጋር በመሆን መሸጣቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ በአቡነ እስጢፋኖስ ሰዎች በመያዙ ይህንን እንደመደራደሪያ በመጠቀም አንተም ተው እኔም እተዋለሁ በሚል በአቡነ እስጢፋኖስ የተደረሰ ድራማ መሆኑን ታውቋል፡፡
ለቤተክርስቲያን ለውጥ የሚያስፈልጋት ቢሆንም ለውጡ ሁሉን አቀፍ የሆነና ከቤተክርስቲያኒቱ ሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣረስ አዘገጃጀቱም ሁሉን ያሳተፈ እንዲሆን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ሰራተኞች በግልጽ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
ጥያቄው መቼም አይቆምም!!

Monday, January 13, 2014

ጦርነቱ በማጣጣር ላይ ባለው የማኅበረ ቅዱሳን አልሞት ባይነትና እጁን ለመስጠት በተዘጋጀው የቤተ ክህነት ባለሥልጣናት መካከል ነው!!!



እንደወትሮው ስለማኅበረ ቅዱሳን የምናትተው ሰፊ ጽሁፍ የለንም። ማኅበሩ እያጣጣረ ነው። ለጊዜው ትንሽ መቆየቱ የእድገት መጨረሻውን አያስቀጥለውም።  ይሁን እንጂ ይህ የብላቴ ትራፊ «አንዲት ጥይት ወይም ሞት» በማለት የጥንት ቃል ኪዳኑን ለማደስ እየተንፈራገጠ ነው።
ለዚህም በመሞትና በመዳን መካከል እየተንፈራገጠ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን ለማዳን እየታገለ ይገኛል። ለመዳን የሚያደርጋቸውን ትግሎች በአጭር በአጭሩ በነጥብ ሲቀመጡ ይህንን ይመስላሉ።


1/ በሙስናና በአስተዳደር ብልሹነት ሊጠየቁ የሚገባቸው አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች አዲሱን ስልቴን እየተቃወሙት ነው በማለት ራሱን ደብቆ ለቤተ ክህነት የለውጥ ማሻሻያ ህግ አያስፈልጋትም የተባለ አስመስሎ ማሳየት ይፈልጋል።

2/ ህጉ ከየትምና ከማንም ይመንጭ ለቤተ ክህነት ስለማስፈለጉ ብቻ እንተማመን በማለት የሕጉን ምንጭ ማንነት እንዳይገለጥ በአስፈላጊነቱ ስር ሸሽጎ ለማስቀጠል ይፈልጋል።

3/ ከአባ አማቴዎስ፤ ከአባ ሉቃስ፤ ከአባ እስጢፋኖስ እና ለጊዜው ስማቸው መጥቀስ ከማንፈልጋቸው ሌሎች ጳጳሳት ጀርባ ተጭኖ የህጉን አስፈላጊነትን በማጦዝ ሲኖዶሳዊ ለማስመሰል በትጋት ይሰራል።

4/ ስለህጉ እጹብ ድንቅነትና ትንግርታዊነት በመረጃ መረብና በስመ ነጻ ሚዲያ ጋዜጦች ላይ በመለፈፍ የምርጫ ዓይነት ቅስቀሳውን በህዝብ ውስጥ በማስረጽና በጳጳሳቱ መካከል የወደፊት በል  ዘመቻውን ለማስቀጠል  ድፍረት የሚሆናቸውን ኃይል በማስታጠቅ ላይ ተጠምዷል።

5/  በካህናት ሽፋን፤  የጥምቀት ተመላሾችንና የተወሰኑ አባላት ምእመናኑን በማሰለፍ በፓትርያርኩ ላይ ጫና በማሳደር የሰማይ ተሰበረ ሽብሩን በመንዛት ላይ ላይ ይገኛል።
እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የተዘረዘሩት እስትንፋሱን የማስቀጠል ዘመቻው ጊዜ ከሚገዛለት በስተቀር በፍጹም ሊታደጉት አይችሉም። ምክንያቶቹ፤
ሀ/ በቤተ ክህነት አጠቃላይ መዋቅራዊ ማሻሻያና የለውጥ እስትራቴጂ ጥናት አስፈላጊነትን የተቃወመና የሚቃወም ማንም የለም። ሊቃወምም አይችልም።

ለ/ የለውጥ ጥናቱ መምጣት ያለበት  ከሲኖዶስ ውስጥ የሚመነጭ ሆኖ በሊቃውንቱ፤ በምሁራኑ፤ በካህናቱ፤ በአዋቂዎቹና በህግ ባለሙያዎች የሚዘጋጅ እንጂ ከማኅበረ ቅዱሳን ጡንቻ ነጻ የመሆን አቅምና ጠባይ በሌላቸው አባ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ የማዘዝ ስልጣንን ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም  ዓላማን የማስፈጸም ግብ ሊሆን አይችልም።

ሐ/ በመሰረቱ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቷ ምኗም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ነጋዴ አይደለችም። እሱ ግን የሚታይ የሚጨበጥ የንግድ ተቋም ያለው ግልጽ ነጋዴና አትራፊ ድርጅት ነው። በዐውደ ምሕረቷ ላይ የሚነግድ ይህ ድርጅት የንግድ ጠረጴዛው መገልበጥ አለበት። በጅራፍም ሊባረር የተገባው ነው። ስለዚህ በምንም ዓይነት መልኩ ወርቅና አልማዝ አቅርቤአለሁ ቢል ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

መ/ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚደግፉ ሊቃነ ጳጳሳት በግልጽ ቋንቋ ስንናገር፤

ሀ/ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ደንብ መሰረት ለጵጵስና የሚያበቃ ሥነ ምግባር በጭራሽ የሌላቸው ናቸው።

ለ/ በዘር ፖለቲካ የተለከፉና ኢህአዴግ እንደጉም ተኖ፤ እንደጢስ በኖ  ይጠፋ ዘንድና  የራሳቸውን ሥርወ ቤተ ክህነት ለመትከል የሚናፍቁ ናቸው።  ከዚህ የወጣ  ደጋፊ የለውም።
በተለይ አባ እስጢፋኖስ ለማኅበሩ ጥብቅና የመቆማቸው ነገር በፍቅሩ ስለተቃጠሉ አይደለም።  ጵጵስና ስሙና ታሪኩ ክብር ያጣው ጸሊማን አርጋብ በምግባር /ጥቋቁር እርግቦች/ የሆኑ ቦታውን ከወረሩት በኋላ ነው። አባ እስጢፋኖስ ኮተቤ ያሰሩት የሚሊዮን ብሮች ግምት ቤታቸው የተሰራው በደመወዛቸው ነው?  መነኩሴ እናቱም አባቱም ቤተ ክርስቲያን ናት ስለሚባል እስኪ ለቤተ ክርስቲያን የውርስ ኑዛዜ ይስጡ!!
ስለዚህ እስትራቴጂ፤ ጥናት፤ ስብሰባ፤ ተቃውሞ፤ ስነ ምግባር፤ ሙሰኛ ወዘተ በሚሉ የቃላት ማደናገሪያ ቤተ ክህነቱ እጁ ሲጠመዘዝ አሜን ማለት የለበትም። አካፋን አካፋ ማለት የሚገባው ወቅት ቢኖር አሁን ነው። ቤተ ክህነት ችግሮቿን ታውቃለች። ለችግሮቿም መፍትሄ ማመንጨት አይሳናትም። የወላድ መካንም አይደለችም። ስለዚህ በፓትርያርኩ አመራር ከራሷ ልጆች በወጣ ህግ ለችግሮቿ መፍትሄ መስጠት አለባት እንጂ በማመልከቻና በደጋፊ ብዛት መጠምዘዝ አይቻልም። 
የማኅበረ ቅዱሳን ስፍራው መናገር ካስፈለገ ሼር ካምፓኒ/ የአክሲዮን ማኅበር መሆን ብቻ ነው። አዲዮስ ማኅበረ ቅዱሳን ከማለት ውጪ በዚህ ማኅበር ስንታመስ መቆየት ያብቃ!!  በዚህ ማኅበር ዙሪያ ከቤተ መንግሥቱ የተሰማውን መረጃ በሌላ ጽሁፍ ይዘን እንመለሳለን።

Saturday, January 11, 2014

የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲያድርባችሁ ሳር ጋጡ የተባሉ ደቡብ አፍሪካውያን ሳር ሲግጡ ዋሉ!!

የፍጻሜው ዘመን የተቃረበ ይመስላል። ጤናማ አእምሮና በማኅበራዊ ኑሮው ሰላማዊ የነበረ ሕዝብ እንደጋማ ከብት ሳር እንዲግጥ ሲታዘዝ  ሲበላ ዋለ ማለት እጅግ ያስገርማል። ነገሩ በእርግጥ ሆኗል። በደቡብ አፍሪካ ፤ ጋራኑካ በተባለች ከተማ ውስጥ  የተቋቋመችውና ከ1000 በላይ ተከታዮች ያሏት ማኅበር መሪ የሆነው ፓስተር ሌሴጎ ዳንኤል የስብከት መርሐ ግብሩን እንደፈጸመ መገለጥ መጥቶልኛልና ከአዳራሽ ወጥታችሁ የሜዳውን ሳር ጋጡና በመንፈሰ እግዚአብሔር ትሞላላችሁ ባላቸው መሰረት ትእዛዙን ተቀብለው ሳር ለመጋጥ መሰማራታቸውን «ክርስቲያን ፖስት» ጋዜጣና «ቺካጎ ዲፌንደር» ዘግበዋል።


   ግማሹ ሳሩን አጎንብሶ እንደከብት እየጋጠ፤ ገሚሱ ደግሞ እንደጭላዳ ዝንጀሮ እየነጨ ሳሩን ሲበላ የዋለ ሲሆን የሰው ጭላዳ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው የ21 ዓመቷ የህግ ተማሪ ሮዝመሪ ፔታ ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው «ሳሩን በመጋጤ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያሰቃየኝ ከነበረው ከጉሮሮ ቁስለት በሽታ ተፈውሻለሁ» በማለት ያገኘችውን አስደናቂ ተአምርና የሳር መጋጡን ጠቃሚነት የገለጸች ሲሆን የ27 ዓመቷ ዶሪን ጋትል የተባለችው ደግሞ እንዲህ ስትል ስለተደረገላት ተአምር ያገኘችውን ጥቅም ገልጻለች። «በነበረኝ የስትሮክ በሽታ እግሮቼን ላለፉት ሁለት ዓመታት ማንቀሳቀስ ተስኖኝ ነበር። ሳር ብትበሉ በመንፈስ ትሞላላችሁ፤ በማለት ስለሳር መብላት አስፈላጊነት ፓስተሬ ባዘዘኝ ጊዜ በመብላቴ ከበሽታዬ በፍጹም ድኜ እነሆ በሁለት እግሬ ለመሄድ በቅቻለሁ» በማለት ስለተደረገላት ተአምር ለሚዲያ ተናግራለች።

  ይሁን እንጂ የሁለቱንም ሴቶች አባባል የሰሙ ታዛቢዎች በአባባላቸው ስቀዋል። ጤንነታቸውንም ተጠራጥረዋል።  ይህ የማይታመን ቀልድና በእግዚአብሔር ስም ማላገጥ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርብን ሳር አጎንብሳችሁ ጋጡ ተብለናል የሚሉት ጉዳይ የግድ መቆም ያለበትና ለህብረተሰቡ በመጥፎ አርአያነቱ ካልሆነ በመልካምነቱ የሚታይ አይደለም በማለት የተመለከቱ ታዛቢዎች ተቃውሟቸውን ገልጸዋል ። የሰው ልጅ ሲፈጠር እንደእንስሳ ሳር ለመጋጥና ለመፍጨት የተዘጋጀ የሰውነት አወቃቀር ስለሌለው የተደረገው ነገር ሁሉ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የማይገኛኝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ ድርጊቱን እንቃወማለን ሲሉ ስለሳር ጋጮቹ ተናግረዋል።

 ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስለሳር መጋጡ ውሎ እንደተዘገበው፤ በመስኩ ላይ ተሰማርተው ሳር ሲግጡ ከዋሉት የሰው ጭላዳዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሲያስመልሳቸውና ሲሰቃዩ የዋሉ ሲሆን ገሚሶቹ መብላት አቅቷቸው ሲያለቅሱ ታይተዋል። አንዳንዶቹም ሆዳቸውን ታመው ህክምና እስኪደርስላቸው ድረስ መታመማቸውም ታውቋል። ከዚህ በፊትም ፓስተር ሌሴጎ ዳንኤል በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ተከታዮቹን በጥፊ እንዲጠፋጠፉ ባዘዛቸው ጊዜ ትእዛዙን ተቀብለው፤  ጉንጫቸው ድልህ እስኪመስል በጥፊ መጠዛጠዛቸውም ተዘግቧል።

እንደሚታወቀው ሳር በመጋጥ እንደእንስሳ ይሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ የወጣበትና ልቡ የተሰወረበት ናቡከደነጾር እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።  ናቡከደነፆርም ለዚህ የበቃው በትምክህቱና በትዕቢቱ እንጂ ለበጎ ተግባሩ የተሰጠው ልዩ ጸጋ አልነበረም። እና ታዲያ የዘመኑ ሰዎች እንደናቡከደነፆር ወደእንስሳነት ወርደው ሳር በመጋጣቸው የናቡከደነፆር ቤተሰቦች የማይሆኑበት ምክንያት ይኖር ይሆን?
«ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው» ዳን 4፤32