Saturday, December 21, 2013

(ሰበር ዜና) የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ ፀሐፊዎችና አጠቃላይ ማኅበረ ካህናቱ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቤቱታቸውን አቀረቡ!


     ስድስት ገጽ የያዘው የማኅበረ ካህናቱ አቤቱታ በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፤ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትርና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ ገቢ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል!
         (ደብዳቤውን ከታች አቅርበንላችኋል)
        ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ አይደለም በማለት ያሳሰቡ ሲሆን ይህ ተረፈ ደርግና በቤተ ክርስቲያን ታዛ የተጠለለ ነጋዴ ድርጅት የመጨረሻ እልባት ሊሰጠው የሚገባው ወቅት አሁን ነው በማለት ጠየቁ!
        ማኅበረ ቅዱሳንና ታማኝ አገልጋዮቻቸው ሊቃነ ጳጳሳት በሚፈጥሩት ሁከት ቤተ ክርስቲያናችን እየታመሰች መቀጠሏ ማቆም አለበት በማለት ድምጻቸውን ሲያሰሙ ውለዋል!
        የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ችግር ከአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ጋር በሲኖዶስ የሚታይና የአስተዳደር ለውጥ ለማድረግም ሲኖዶሱ በሚሰጠው መመሪያ በምሁራን ልጆችዋ፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሕግ አዋቂዎች፤ በአስተዳደርና በማኔጅመንት እውቀትና ልምድ ባላቸው አባላት ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶት በሚቀርብ የማሻሻያ ረቂቅ ደንብ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረቴን መቆጣጠር አትችልም ባለ ዐመጸኛ ቡድን መሆን ስለማይገባው ቅዱስ ፓትርያርኩ አስቸኳይ መፍትሄ ይስጡን በማለት ተጠይቀዋል!
        21 ዓመት የተሸከምነውን ይህን ማኅበር ከእንግዲህ ተሸክመን በዚህ ዓይነት መልኩ ለመዝለቅ ስለማንችል መንግሥት አንድ እልባት እንዲሰጠን እንጮሃለን ብለዋል! በቃ የሚባልበት ወቅት ቢኖር አሁን ነው ያሉት ተሰብሰባዎቹ ወደፊት በዚህ ማኅበር ምክንያት ለሚመጣው ጉዳት ኃላፊነቱን አንወስድም ሲሉ ያላቸውን ፍርሃትም አሳስበዋል!
        ቅዱስ ፓትርያርኩም ጉዳዩን በቀላሉ እንደማይመለከቱትና መፍትሄም እንደሚሰጡ ቃል የገቡላቸው ሲሆን ማኅበረ ካህናቱ ያላቸውን ችግር ለመፍታትና ለመነጋገር የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አዳራሽ ክፍት ሆኖ እንደሚያገለግላቸው ገልጸውላቸዋል!
     ከታች የቀረበው ጽሁፍና ማመልከቻ ለቅዱስ ፓትርያርኩ በጠቅላይ ቤተክህነቱ አዳራሽ የቀረበ የማኅበረ ካህናቱ ፊርማና አቤቱታ ነው።
                       ዐቢይ ዜና

ማኅበረ ቅዱሳን በአዲሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ ለውጥ ምክንያት እየደረሰበት ያለው ተቋሞ ተጋግሎ ቀጥሏል፡፡ በየሆቴሉ በድብቅ ይሰበሰባሉ ሲባሉ የቆዩት የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አለቆች በገሀድ በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ ተሰብስበው ፓትርያርኩንና አንዳድ የማኅበሩን ደጋፊ ሊቃነ ጳጳሳት አስጠነቀቁ፡፡ ጥያቄዎቻችን ምላሽ የማያገኙ ከሆነ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር በጥቁር ራስ (መነኮሳት ባልሆኑ) ሰዎች እንዲካሄድ በሕጋዊ መልኩ እንደሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሰራተኞች ቤተክርስቲያኒቱ የአሰራር ለውጥ እንደሚያስፈልጋት አምነው ለውጡ ሁለንተናዊና መላውን የቤተክህነቱ ክፍል ሊያቅፍ እንደሚገባ ሕጉም ከዋናው ከሕገ ቤተክርስቲያን መጀመር እንዳለበትና በየደረጃው ደንቦችና መመሪያዎች ሊወጡ እንደሚገባው አስረድተው ይህንን የሚሰራው አካልም ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከሊቃውንት ጉባዔ፣ በየደረጃው ከሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ሰራተኞች ፣ ከገለልተኛ ባለሙያዎች ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በተወጣጣ ኮሚቴ መሰራት እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጥያቄያችሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ትኩረት ይፈልጋል  በማለት ኮሚቴ እንዲቋቋም ፈቅደዋል በቤተክህነቱ አዳራሽ መሰብሰብ እንደሚችሉ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ስብሰባው ያበሳጫቸው አቡነ እስጢፋኖስ ግለቱ ከብዷቸው ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ ግልጽነት የጎደለውና ቤተክርስቲያኗን ለአንድ ማኅበር ድብቅ ዓላማ እና ፍላጎት አጋልጦ የሰጠ በመሆኑ፣ የካህናት ቅነሳ በሚል አገልጋዮችን የሚበትን ፣ ቤተክርስቲያኒቱ ያሏትን ሊቃውንት ያላካተተ በመሆኑ፣ የሰንበት ትምህርት ቤትን በማዳከም በአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ብዙ ማኅበር እንዲደራጅና ሕጋዊ እንዲሆን በማድረግ በወጣቱ ዘንድ መከፋፈል የሚፈጥር በመሆኑ እንደማይቀበሉት  አስታውቀዋል፡፡    ማኅበረ ቅዱሳን  በጥቅምቱ የሰበካ ጉባዔ ምልአተ ስብሰባ በተወሰነው መሠረት  የ55 ሚሊዮን የቤተክርስቲያኗ ምእመናን ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በወሰኑትባ በአቋም መግለጫ ባጸኑት ውሳኔ  መሠረት  ሀብትና ንብረቱን እንዲያሳውቅና በቤተክርስቲያኗ አሰራር መሠረት በሕጋዊ ሞዴሎች እንዲጠቀም ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለቅዱስ ፓትርያርኩ በ 5000 ሰራተኞች ፊርማ በቀረበውና ለመንግሥት አካላት ግልባጭ በተደረገው ደብዳቤ ተጠይቋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን በተዘጋጀውና ለአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ብቻ እንዲተገበር በታለመው የመዋቅራዊ ጥናት ምክንያት  በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ አድባራትና ገዳማት ሠራተኞችና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ያለው አለመግባባት ቀጥሏል፡፡ መዋቅራዊ ጥናቱን ይቃወማሉ የሚባሉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራት ሰራተኞች ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በማምራት ቅዱስ ፓትርያርኩንና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳትን አነጋግረዋል፡፡ የአቋም መግለጫቸውንም ለፓትርያርኩ ሰጥተዋል፡፡ በመድረኩ ማኅበረ ቅዱሳን አንድ የቤተክርስቲያን አካል ሆኖ እያለ ለመላዋ ቤተክርስቲያን መመሪያ አውጪ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን ወዴት ነው ያለው እንዳስባላቸው ተሰብሳቢዎቹ ለፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እራሱ ለቃለ አዋዲውና ለሕገ ቤተክርስቲያን ሳይገዛ እንዴት ሕግ አውጪ ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ መመሪያ የሚያስፈልግ በመሆኑ ከሕገ ቤተክርስቲያን ጀምሮ በየደረጃው መመሪያና ደንብ እንዲወጣና ይህንንም አንድ ማኅበር ሳይሆን የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ እና ገለልተኛ አካላት ሊያዘጋጁት ይገባል ብለዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩ መዋቅራዊ ጥናቱን ለምን በድብቅ መስራት አስፈለገው፣ ሊቃውንት ለምን እንዲሳተፉ አልተፈለገም የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ መልስ በሚሰጥበት ወቅት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የማኅበሩ የኢዲቶሪያል ኮሚቴ አባል ስለ መዋቅሩ አስፈላጊነት ለመግለጽ የሞከሩ ሲሆን አቡነ እስጢፋኖስ ግን ስለ ጥናቱ ብዙም መረጃ እንደሌላቸውና አንዳንዱንም ከተሰብሳቢው ወገን እንደሰሙ በመግለጽ እርስ በእርሱ የተምተታ መልስ ሰጥተዋል፡፡ መመሪያውና ጥናቱን ወድቆ ብናገኘውስ ምን ችግር አለው ሲሉ ምንጩን ለመደበቅ ሞክረዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄያቸውን ማይመልስ ከሆነ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር በጥቁር ራስ (መነኮሳት ባልሆኑ) ሰዎች እንዲካሄድ በሕጋዊ መልኩ እንደሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የተሰብሳቢዎቹ ጥያቄ አግባብ የሆነና በትኩረት መታየት እንዳለበት አስረድተው ከተሰብሳቢዎቹ ጉዳዩን የሚከታተል 15 ዐቢይ ኮሚቴ እና 20 ንዑሳን ኮሚቴዎች አስመርጠው በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ በመሰብሰብ ጉዳዩን በይበልጥ በትኩረት እንዲያጠኑ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጊዜው እንዲቋረጥ ብፁአን አባቶች ሀሳብ የሰጡበት የመዋቅራዊ ጥናት ስብሰባ በአቡ እስጢፋኖስ ትእዛዝ እንደቀጠለ ሲሆን የሥልጠናው መሪ ማኅበረ ቅዱሳኑ አቶ ታደሰ ፍስሐ በሥልጠናው ተሳታፊዎች እናንተ እነማን ናችሁ? ከሊቃውንትስ ማንን ይዛችሁ ነው የምትሰሩት በሚል ለተነሳላቸው ጥያቁ በደፈናው የቤተክርስቲያን ልጆች ነን ከሊቃውንትም ታላቁን ሊቅ አቡነ እስጢፋኖስን ይዘን ነው የምንሰራው በማለት ምላሽ ሲሰጡ አዳራሹ በስላቅ ሳቅ ደምቋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኛ አቶ ደስታን በሥልጠናው ሥፍራ በወሬ አቀባይነት መድቦ በሬኒ ካፊና ሬስቶራንት የምሳ እና የሻይ እየተከፈለው አንዳንድ መረጃዎችን ለማኅበሩ ሥውር ብሎጎች እንዲያቀብል መድቦታል፡፡ የአዲሱ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት አባል የነበረውና ወደ ቤተክህነት እቃ ሊያደርስ ተልኮ በድንገት ሠራተኛ የሆነው አሁንም በጠ/ቤተ ክህነቱ ገዳማት አስተዳደር ተጧሪ ሆኖ ደመወዝ የሚበላውን ይህንን ጨዋ የአድባራት እና ገዳማት አለቆችንንና ሰራተኞችን ስም በማጥፋት ተግባሩ ማኅበሩ አንቱታን ቸሮታል፡፡ በተጨማሪ እነ ጳውሎስ መልክአ ሥላሴም በዚሁ ተግባር በመሳተፍ ከቤተክህነቱ አደባባይ መዋል ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ 



































Sunday, December 15, 2013

የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ለውጥ ከላዕላይ መዋቅር ይመነጫል እንጂ ለአንድ ሀ/ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ቢሮ አይደለም!


  • የማኅበረ ቅዱሳን ሩጫ ሀገረ ስብከት የመቆጣጠር ስልት እንጂ ዘረፈ ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለመፍታት አያገለግልም።
  • ማኅበረ ካህናቱ ከማኅበረ ቅዱሳን አፈናና ስለላ ለመዳን መታገል ያለባቸው ዛሬ ነው!
  • ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ ተቋማዊ ለውጥ የሚያስፈልገው ድርጅት ነው!
   ከዚህ ቀደም እንዳልነው ተቋማዊ ህዳሴና አስተዳደራዊ ለውጥ የሚያስፈልገው ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን  መነሻ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት የሚለው ሃሳብ በመጀመሪያ ረድፍ የሚቀመጥ አጀንዳ ነው። ከላዕላይ መዋቅሩ ወይም ከዋልታው የለውጥ ተሐድሶ ባልተጀመረበትና ፈጽሞ ባልታሰበበት ሁኔታ በተናጠል የአንዱ ሀገረ ስብከት አጀንዳ እንደሆነ በመቁጠር በዚያ ዙሪያ መኮልኮል ውጤታማ ፍጻሜ ሊኖረው በፍጹም አይችልም።

 በተለይም ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን በተባለ አንጃ ተጠንስሶና የዲስኩር ውሃ ተሞልቶ ካህናቱ እንዲጠጡ በተዘጋጀው የስልጠና ወሬ የተነሳ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለውጥ ይመጣል ማለት ዘበት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ ተቋማዊ ለውጥ የሚያስፈልገው አፈንጋጭ ድርጅት ሆኖ ሳለ የሀገረ ስብከቱ እቅድ ነዳፊ፤ አሰልጣኝና «የያብባል ገና» ዜማ ደርዳሪ ሆኖ መሰየሙ አስገራሚ ነው። እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ላይከዱት በልጆቻቸው ስም ቃለ መሃላ የገቡለት ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ «ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ» ብለው ለማኅበሩ ያስረከቡትን ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናቱ አሜን ይሁን፤ ይደረግልን ብለው መቀበላቸው ያሳዝናል። በጣፈጠና በለሰለሰ አማርኛ ነገ ብርሃን ሊወጣልህ ነው እያሉ በማደንዘዝ ላይ የተጠመዱት የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች የአዲስ አበባን ችግር ከአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር በተለየ የመፍታት ምትሃታዊ ኃይል ስላላቸው ሳይሆን ማኅበረ ካህናቱ ማቅ የተባለውን ድርጅት ውስጣችን አናስገባም ብለው ለ21 ዓመት የታገሉትን ለመቋቋም ይቻለው ዘንድ ገሚሱን የስልጠናው ደጋፊና ገሚሱን የስልጠናው ተቃዋሚ አድርጎ ከፋፍሎ በመምታት እግሩን በመሃከል አደላድሎ ለመትከል ያለመ መሆኑን ሊጤን ይገባል።
  ማኅበረ ካህናቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲመጣ ካስፈለገ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና ምሁራን እንጂ ይህ ገንዘቡን በጓሮ እያደለበ፤ ስንት እንደነገደና ስንት እንዳተረፈ ካዝናው የማይታወቅ የመሰሪዎች ስብስብ ማኅበር በሚያረቀውና በሚያቀርበው የስልጠና መርሃ ግብር መሆን እንደሌለበት ማኅበረ ካህናቱ ሊገነዘብ ይገባል። የራሱን በጉያ ደብቆ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ካዝና ለመቆጣጠር እቅድና ትልም ማውጣቱ ድፍረት ብቻ ሳይሆን ጳጳሳቱ እስከደገፉት የሚከለክለው እንደሌለ ያሳየበት አጋጣሚ ነው።
  መዋቅራዊውን ለውጥ ከግቡ ለማድረስ አቅሙና እውቀቱ ካላቸው ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከቅዱስ ሲኖዶስ መመንጨት አለበት። ከዚያም በተረፈ ቤተ ክርስቲያን ብትጠራቸው ይህንን ለመስራት ማገዝ የሚችሉ ቅን፤ የቤተ ክርስቲያናቸው ጉዳይ ግድ የሚላቸው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት የአስተዳደር ጉድለት ዘወትር የሚያንገበግባቸው ኦርቶዶክሳውያን ምሁራን ሞልተዋል። ስለዚህ ነጋዴ የወጣቶች መንጋ ስኬት ያገኘ ስለመሰለው ብቻ ሀገረ ስብከቱን ልዘዘው፤ ልናዘው ብሎ ስለጠየቀ ሊፈቀድለት አይገባም። ደረጃውም፤ አቅሙም ስላይደለ ሀይ ሊባል የሚገባው ሰዓት ቢኖር አሁን ነው።

 ስለሆነም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናት የሆናችሁ ሁላችሁም ይህ ካዝናውን በጓሮ የደበቀ ማኅበር የናንተን የአገልግሎት ካዝና እንዲቆጣጠር ልትፈቅዱለት አይገባም። እርግጥ ነው፤ የብዙ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳደሮች ጉድለት፤ ብክነትና ምዝበራ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በእኛ እምነት ይህ ችግር የሚቀረፈው የቤተ ክርስቲያኒቱ ላዕላይ መዋቅር የችግሩን አንገብጋቢነትና ስፋት በጥልቀት ተመልክቶ በቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራንና ሊቃውንት አስጠንቶ አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ እንደሆነ እናምናለን። ከዚህ ውጪ አንዱን ጫፍ ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ በመስጠት ለውጥ ሊመጣ ስለማይችል ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ማሻሻል ጉዳይ እንዲወጣ መታገል ወቅቱ ዛሬ ነው።
በውስጥ ጉዳያችን ማኅበረ ቅዱሳን መግባት የለበትም ለማለት የማኅበረ ካህናቱ ድምጽ መሰማት ያለበት ዛሬ ነው።

Thursday, December 12, 2013

የማኅበረ ቅዱሳን መግነንና ብቀላ መሳ ለመሳ ናቸው፤ እንደጠዋት ጤዛም ቀትር ላይ ይጠፋሉ!


ነፍሳቸውን በአጸደ ቅዱሳን ያሳርፍልንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለውልና ፊርማ ተረክቧት እያስተዳደረ ይገኛል። አቡነ ጳውሎስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህንን መሠሪ ማኅበር ከመነሻው የደገፉት ሲሆን ውሎ አድሮ አካሄዱን አይተው የእድሜ ዘመኑን ለማሳጠር ብዙ ቢጥሩም ማኅበሩ ስር ሰዶ፤ የራሱን ጳጳሳት በመመልመል የሲኖዶሱን እኩሌታ መቆጣጠር የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ጥቂት ከማንገዳገድ ውጪ ሊጥሉት ሳይችሉ ቀርተው ወደማይቀረው ሞት ሄደዋል።
  አበው «የጠሉት ይወርሳል፤ የፈሩት ይደርሳል» እንዲሉ ይህንን ማኅበር የጠላነውን ያህል ሳይዳከም፤ የፈራነው ቤተ ክርስቲያኒቱን የመረከብ የረጅም ጊዜ ህልሙ እውን እያደረገ መገኘቱን ስንመለከት መጨረሻውስ? ብለን እስክንጠይቅ ድረስ መደመማችን አልቀረም። ምናልባት ቤተ ክህነቱን እንደወረሰ ቤተ መንግሥቱንም ይረከብ ይሆን? ይህንንም እንጠይቃለን። ማኅበሩን ስለመጥላት ስንናገር ሰውኛ ጥላቻ ሳይሆን  እንዴት አንድ ተራ ማኅበር፤ ለዚያውም በጦር ካምፕና በዝሙት መስዋእት ተመስርቶ ሁለት ሺህ ዘመን የዘለቀችውን ቤተ ክርስቲያን ተረክቦ በእጁ ያደርጋታል ከሚል መንፈሳዊ ቁጭትና መሸሻውም ይሁን መገኛው ከንስሐ ሥፍራ መሆን ሲገባው ዐመጽ ወልዶት፤ ዐመጽ ያሳደገው ማኅበር እዚህ መድረሱ አስገራሚም አስደማሚም ከመሆኑ የተነሳ ነው። አንዳንዶች ይህ ማኅበር እንደቴዎዳስ ዘግብጽ ቶሎ ያልጠፋው እግዚአብሔር ስለተከለው ነው በማለት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር በማስተሳሰር ሊያሳምኑን ይከጅላሉ። ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አጥፍቶ፤ ሕዝቡን 70 ዘመን በባርነት የገዛው ናቡከደነጾር እግዚአብሔርን ያመልክ ስለነበር ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለው እስራኤል ከእግዚአብሔር አምልኮ ስላፈነገጠ መሆኑም እንዳይዘነጋ ማስረጃ እናቀርብላቸዋለን። ማኅበረ ቅዱሳን 21 ዓመት የመቆየቱ ምስጢርና ቤተ ክርስቲያኒቱን እስከማዘዝ የመድረሱ ነገር በቅድስናው ልክ እግዚአብሔር በመደሰቱ ነው ብለን አናስብም። በዚህ ርዕስ የማኅበረ ቅዱሳንን አነሳስ ትተን አሁን ያለበትን መንፈሳዊ መሰል ሕይወቱን ብንዘረዝር ውሎ ያሳድረናል። ሌላው ቀርቶ የማይታዘዙለትን ጳጳሳት እንዴት እንደሚያበሻቅጥና ሰጥ ለጥ ብለው የሚታዘዙለትን ደግሞ የቱንም ያህል አስነዋሪ ገመና ቢኖራቸው ምን ያህል እንደሚያንቆለጳጵሳቸው በመመልከት ስለማኅበሩ መናገር ይቻላል። «ከእነማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ» ይባል የለ!

  አብዛኛዎቹ ጳጳሳትም ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ይህንን ማኅበር ቆመው ማውረድ እስኪያቅታቸው ድረስ በተዘዋዋሪ መንገድ ለዚህ ማኅበር የምርኮኝነት እጃቸውን ሰጥተዋል። በየሄዱበት ሀገረ ስብከት ወንበራቸውን ከኋላ የሚሾፍረው ይህ ማኅበር ሲሆን በተለይም ከአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ በተጠናና በታወቀ ስልት እያደባ፤ ካህናቱንም ሳያስደነግጥ፤ በረቀቀ መንገድ አስተዳደሩን ተረክቦ የሁለት ተቋም አስተዳዳሪ ሆኖ ይገኛል። አንዱ  ቅዱስ የተባለው የሲኖዶስ መንበር ሲሆን ሁለተኛው በግልጽ የሚጠራበት የራሱ ማኅበር ተቋማዊ የንግድ አስተዳደር ነው። ለረጅም ጊዜ ባካበተው የስለላ ልምዱ መረጃዎችን ወደአንድ ቋት በመሰብሰብ እቅድና ትግበራውን በግልጽም በስውርም ያካሂዳል። ለዚህም ተጠቃሹ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዱ ነው።
  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሙስና፤ በአስተዳደር ብልሹነትና በንቅዘት ግንባር ቀደም ሀገረ ስብከት የመሆኑን ያህል ከፍተኛ የለውጥ እርምጃ የሚያስፈልገው ስለመሆኑ አያጠያይቅም።  እጃቸው በተጠመዘዘና በማኅበረ ቅዱሳን ሳንባ በሚተነፍሱት በአባ እስጢፋኖስ በኩል ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ግን «ላሞች ባልዋልሉበት ኩበት ለቀማ» ከመሆን የዘለለ ውጤት አይኖረውም ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን አናት ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ የመስጠት ሂደት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
  «የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በለውጥና ህዳሴ ጎዳና፤ ያብባል ገና» በሚለው የማኅበረ ቅዱሳን መፈክር ስር የተጠለለው የአስተዳደር ማሻሻል ትግበራ ሂደት ጥናቱ፤ እቅዱና አፈጻጸሙ ሙሉ በሙሉ እየተከናወነ ያለው በማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በኩል ስለመሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ዞሮ ዞሮ ሀገረ ስብከቱን ለማኅበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴ አመቺ በሆነ መልኩ ማዋቀርና ሊመጣ የሚችልበትን ግልጽና ስውር ተቃውሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት «ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ድምጸትን የሚያስተጋባ አስተዳደርን መመስረት ዋነኛ ግቡ ስለመሆኑ የምንሰማቸው አቤቱታዎችና እንቅስቃሴዎች አመላካች ናቸው። በቅርቡ እንዳየነው ለማኅበረ ቅዱሳን በጎ አመለካከት የላቸውም የተባሉ ካህናትና ሰራተኞች በስመ ዝውውርና ሽግሽግ ሰበብ ዱላ እያረፈባቸው መገኘቱ አንዱ አስረጂ ነው። ለወደፊቱም በፍጥነት ሳያስደነግጡና ሳያስደነብሩ በማለሳለስ ተመሳሳዩን የበቀል ዱላ እያሳረፉ ለአዲሱ ለውጥና ህዳሴ ስለሆነ ሁላችሁም «ያብባል ገና»  በሚለው ዝማሬ ስር ተሰባሰቡ ማለቱን ይቀጥላል። አባ እስጢፋኖስ ከማኅበረ ቅዱሳን ጉያ ለመውጣት አቅሙም፤ ብቃቱም፤ ሞራሉም የላቸውም፤ ስለዚህ በቦታው እስካሉ ድረስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጓሮ አስተዳዳሪ ማኅበረ ቅዱሳን ሆኖ መቀጠሉም አይቀሬ ነው። በባላ የተደገፈ ቤት ለጊዜው እንጂ በቀጣይነት ሊቆም አይችልም። የአባ እስጢፋኖስ የማኅበረ ቅዱሳን መዋቅራዊ ማሻሻያም የዚያው ተመሳሳይ ውጤት ከመሆን አይዘልም።  ምናልባትም የማኅበረ ቅዱሳን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የማቡካት የመጋገር ጅማሮ የማኅበሩን ዕድሜ ቀጣይነት ወሳኝ ምዕራፍ ከፋች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በሂደት የምናየውም ይሆናል።

ሌላው በተመሳሳይ መልኩ ማኅበረ ቅዱሳንን ካሰማሯቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል የሐዋሳው አቡነ ገብርኤል ተጠቃሽ ናቸው። እንዲያውም ማኅበሩ ራሱ በተደጋጋሚ እንደሚለፍፈው «ማኅበረ ቅዱሳን» ብለው የዳቦ ስሜን ያወጡልኝ አቡነ ገብርኤል ናቸው እያለ በሚጠራቸው የነፍስ አባቱ ቤትም ማዘዝ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በተዘዋዋሪም ተጠያቂነት ካለብኝም ይህንን ስም የሸለሙኝ ሊሆን ይገባል በሚል ድምጸት ማኅበሩ ስሙንና አቡነ ገብርኤል ለአፍታም ከአፉ አይነጥልም።

አቡነ ገብርኤል እድሜ ለንስሐ የሰጣቸውን አምላክ ከማመስገን ይልቅ ይህንን ማኅበር በጌታ ምትክ ዘወትር ሲያወድሱት ይታያሉ። በአሜሪካ አደባባይ «የፍየል ወጠጤ፤ ልቡ ያበጠበት…………» ከሚለው የጸረ ኢህአዴግ  ሰላማዊ ሰልፍ አንስቶ በይቅርታ ይሁን በንስሐ ከኢህአዴግ ጋር የታረቁበት መንገድ ለጊዜው ባይታወቅም ሐዋሳ እስከደረሱበት ጊዜ ድረስ በየሄዱበት ሰላም አስፍነው እንደማያውቁ ግለ ታሪካቸው  ይናገራል። ሐዋሳ እንደገቡም የመጀመሪያ ስራቸው ምእመናኑን በመከፋፈል ገሚሱን በማስደንበር የማባረር ስራ አሐዱ ብለው የጀመሩ ሲሆን ከዚህ ጀርባም ያ ቁጭ ብለው የሰቀሉትና ቆመው ማውረድ ያቃታቸው የነፍስ ልጃቸው ማኅበሩ አብሯቸው ነበር።
  እነመጋቤ ሐዲስ በጋሻውን፤ ቀሲስ ትዝታውንና ሌሎቹንም ዘማርያን ነክሶ የያዘውን ማኅበር ደስ ለማሰኘት አባ ገብርኤል እስከመጨረሻው ድረስ ለማሳደድ አላቅማሙም። ደም እስኪፈስና አካል እስኪጎድል ድረስ ሐዋሳን የጦርነት አውድማ ለማድረግም ወደኋላ አላሉም። ማኅበሩ ካዘዘ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥም ከመግባት እንደማይመለሱ ይታወቃል። እንዲያው ተሸፋፍኖ ይቅር ብለን እንጂ አባ ገብርኤል ምን የማያደርጉት ነገር አለ? ከዚህ በደል ለመገላገል ደግሞ ያላቸው ብቸኛው አማራጭ ንስሐ መግባት ሳይሆን ያንን ከነከሰ የማይለቅ ማኅበር እስከመጨረሻው ማገልገል ብቻ ነው። ሰሞኑን በእርቅ ሰበብ ከተጣሏቸው ምእመናን ጋር በመታረቅ አቡነ ገብርኤል ተስማምተውና አካባቢውን መስለው ለማደር ቢፈልጉም ያ ማኅበር ከኋላቸው ሆኖ «አይሆንም፤ አይደረግም» እያለ ሰቅዞ ይዟቸዋል። በተለይም የጥሉ አስኳል ተደርገው በማኅበሩ የብቀላ መዝገብ ላይ የሰፈሩት እነ በጋሻው ይቅርታ ይደረግልን የሚል ማመልከቻ ያቅርቡ እያለ መገኘቱ የሁከቱ ባለቤት ማን እንደነበረ በግልጽ እያሳየ ይገኛል። በዳይና ተበዳይ ማን እንደሆነ የመመርመር ሳይሆን ጉዳዩን በእርቅ የመፍታት ጥረት ላይ ነገሩን ለማደፍረስ የሚደረገው የማኅበሩ ሩጫ አስገራሚም አሳዛኝም ያደርገዋል።  በጋሻው «የበደላችሁኝን ሁሉ ይቅር ብያለው» ማለቱ ሲሰማ ማኅበሩ በተገላቢጦሽ «በድያችኋለሁና ይቅር በሉኝ» ሊል ይገባል በማለት ላይ መጠመዱ ሳያንስ ማኅበሩ በዚህ መካከል የሚጨምረው የተንኮል ቅርቃር ደግሞ «በጋሻው ሃይማኖታዊ ሕጸጽ ስላለበት ጉዳዩ በይቅርታ አያልቅም» የሚል መሆኑ ነው።

«የበደሉንን ይቅር እንደምንል» ጌታ ያስተማረን ጸሎት ነው። በጋሻው ይህንን በማለቱ ተቀባይነት የለውም ማለት ምን ማለት ነው? በግልባጩ በጋሻው በድሎናል የሚል ካለም ይህንን ቃል መልሶ በመጠቀም «የበደሉንን ይቅር እንደምንል» ማለት በጋሻው በድሎናል፤ ግን ይቅር ብለነዋል ማለት የክርስትና መገለጫ እንጂ የትንሽነት ወይም የተጠቂነት ስሜት ማንጸባረቂያ አይደለም። ይሁን እንጂ ማኅበሩ « የበደልኩ እኔ ነኝ፤ ይቅር በሉኝ» የሚል ልመና ሊቀርብልን ይገባል ሲል ይደመጣል። እንዲያማ ቢሆን ኖሮ እኛ የሰው ልጆች  ወደ እግዚአብሔር የማቅረብ የበደለኛነት ጥያቄ እያለብን  የተበደለው አምላክ በደላችንን ይቅር ሊለን ሥጋ ለብሶ ባልመጣ ነበር እንደማለት ነው።  «ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን» ሮሜ 5፤10
ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት» ማር 11፤25
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ» ቆላስ 3፤13

ዳሩ ግን ይህ ተበቃይ ማኅበር የጠላቸው ሰዎች መንበርከካቸውንና እጃቸውን በመሸነፍ ስለማስረከባቸው የማረጋገጫ ቃል ካላገኘ በቀር «የበደሉንን ይቅር ብለናል« የሚለው ቃል አያረካኝም እያለ ይገኛል። የወንጌልን ቃል የማይቀበል ይህን መናፍቅ ማኅበር ደርሶ የወንጌል ቃል ተቆርቋሪ ሆኖ በመታየት ሌሎችን የሃይማኖት ሕጸጽ አለባቸው በማለት አለማፈሩ ያስገርማል። የእነ ደብተራ ገለፈትን መጽሐፍ እንጂ ማኅበረ ቅዱሳንና ወንጌል የትም እንደማይተዋወቁ እርግጥ ነው። መናፍቁና ጸረ ወንጌሉ ማኅበር ተግባር የሚመሰክርበትን የወንጌል ቃል ተቃርኖ እየተናገረ ስለወንጌል የመናገር ብቃቱም፤ እውቀቱም የለውም። ዳሩ ግን «ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል» እንዲሉ ባሰረጋቸው መነኮሳቱ በኩል ጳጳሳት ሆነው ስለተገኙ ብቻ  ቤተ ክርስቲያኒቱን በእነሱ እጅ በመጥፎ አጋጣሚ እያሾራት መገኘቱ ያሳዝናል። እነ አባ ሉቃስን በመሳሰሉ አድር ብዬዎች በኩል መለመላዋን የተገኘችውን ቤተ ክርስቲያን ለጊዜው ተረክቧት ማኅበሩ እያስተዳደረ ነው። «የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን» ማለት የክርስትና ጸሎት ነበር። ይህንን ማለት ግን የአላዋቂዎች ጸሎት ተደርጎ ተቆጥሯል። ዳሩ ግን ሥልጣን እውቀትን በተካበት ዘመን ወንጌል ሥፍራ እንደሌለው እውነት ነው። ይሁን እንጂ የወንጌል እውነት በሥልጣንና በገንዘብ ተቀብሮ ሊቀር አይችልም። ከማኅበረ ቅዱሳን አገልጋይ ጳጳሳትና ከማኅበሩም በላይ ሥልጣንና ኃይል የነበራቸውም እንኳን በታሪክ ውስጥ የወንጌልን እውነት ቀብረው ሊያስቀሩ አልተቻላቸውም። ወንጌል በኃይልና በሥልጣን ሊነሳ ሲፈልግ ቦታውን ግሳንግስ ይወረዋል። በውሸት መካከል የወጣ እውነት ሕይወትን የመስጠት ኃይል የሚኖረው ያኔ ነውና።
  የማኅበሩ እንዲህ መገስገስና በየስፍራው  እያየነው የመንገስ ጉዳይ የጥዋት ጤዛን ያሳየናል። ፀሐይ ሲወጣ ጤዛ ባለበት አይገኝም። ዛሬ ለእግዚአብሔር ያለመመቸታችንና ስለኃጢአታችን በፊቱ ያለመውደቃችን ምክንያት እንጂ ንስሐ ገብተን፤ መልካሙን ዘመን እንዲያመጣልን ከልብ ከጸለይን ብላቴን ላይ የተፈለፈለው ማኅበር እንደጥዋት ጤዛ ቢያለጨልጭም ቀትር ላይ ተመልሰን እንደማናገኘው እርግጠኞች ነን። ለዚህ ጸሎት አንድ ኤልያስ በመካከላችን እንደማይጠፋም እናውቃለን። በሰው ላይ እየፈረደ፤ ራሱን ለንግድ አሳልፎ የሚሰጥ ለጊዜው እንጂ ከቆመበት መውደቁ አይቀርም። ይልቅ ራሱን ለንስሐ ቢያዘጋጅ ይበጀዋል።

«እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ። ኃጥአን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም። ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል» መዝ 37፤34-38