Tuesday, December 10, 2013

ራሺያ የአሸባሪዎች መመሪያ ብላ የሰየመችው «ቁርአንን» በሀገሯ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዳይገባ አገደች።


 
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ የራሺያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአሸባሪዎች የሽብር መመሪያ ነው ያለውን ቁርአን ወደሀገሩ እንዳይገባ የእግድ ውሳኔ አሳለፈ። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ እንዳመለከተው ፤ አንድ መጽሐፍ ወደራሺያ ከመግባቱ በፊት ማኅበራዊ ኑሮን፤ የራሺያን ባህልና ወግ የማይጻረር መሆኑ ሳይመረመር በፊት መግባት ስለማይችል፤ ቁርአን የተባለው መጽሐፍ በሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ በራሺያው ዜጋ ኤልሚር ኩልየቭ በኩል ተተርጉሞ በነጻ ከታተመ በኋላ  ኮፒውን መርምረናል ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ይህ መጽሐፍ እንደማንኛውም ሌሎች መጽሐፍ ውስጡ ተመርምሮ የተደረሰበት ጭብጥ እንደሚያስረዳው ትርጉሙ ወደራሺያ ምድር ቢገባ ሽብርን በማበረታታት፤ ጥላቻን በመዝራትና ባህልና ወጋችንን በማደፍረስ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ በማድረግ በኩል አሉታዊ ጎኑ የበረታ በመሆኑ እንዳይገባ የእግድ ውሳኔ አሳልፈንበታል ሲል በውሳኔው ላይ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
  በኤልሚር ኩልየቭ በኩል የተተረጎመው ይህ በስም «ቁርአን» የተባለው መጽሐፍ በፍርድ ቤቱ የታየው በየትኛውም የሃይማኖት መጽሐፍነቱ ሳይሆን እንደአንድ ተራ መጽሐፍ ሲሆን የተመረመረውም ይኸው መጽሐፍ ሊሰጥ እንደሚችለው ሀገራዊ ጠቀሜታ አንጻር መሆኑንም ፍርድ ቤቱ ሳይገልጽ አላለፈም።

 ስለሆነም መጽሐፉ ለሀገራቸው ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ውስጡ ሲመረመር ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ትርጉሙ ወደሀገር ውስጥ እንዳይገባ ያገደ ሲሆን ይህንን የፍርድ ቤት እግድ ተላልፎ የተገኘ ማንም ዜጋ ሽብርተኝነትን በማበረታታትና በማስፋፋት በሚያስጠይቀው የሀገሪቱ ሕግ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆንም ተገልጿል።
  ይህ «ቁርአን» የተባለው መጽሐፍ የዐረቢኛው ትርጉም በራሺያውያን ሙስሊሞች እጅ የሚገኝ ቢሆንም ከራሺያ ቋንቋ ውጭ ስላሉ ትርጉሞች የተባለ ነገር የለም።

የራሺያው ቋንቋ የቁርአን ትርጉም  በወደሀገሪቱ እንዳይገባ መታገዱን በመቃወም የራሺያው የሙስሊሞች ሙፍቲ ራቪል ጋይኑትዲን ለራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጻፉት ደብዳቤ እንዳመለከቱት «ይህ እውቀት የጎደለውና ጸብ አጫሪ ውሳኔ እንደገና መታየት አለበት»  በማለት በኃይለ ቃል መግለጻቸውን «ኸፍ ፖስት» ጋዜጣ ዘግቧል።
  ጠቅላይ ሙፍቲው እንዳሳሰቡት « በጥቁር ባህር ወደብ ላይ ወደራሺያ ሊገባ የተዘጋጀው ይህ የቁርአን ትርጉም በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው፤ የእስላሞች መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ውሳኔ አድርገን እንቆጥራለን» ሲሉ መናገራቸውም ተሰምቷል። አንድ ራሺያዊ ዜጋ ስለጉዳዩ በሰጠው አስተያየት እንደተናገረው « ራሺያ እስልምና ለሚፈልገው ማንኛውም ጉዳይ እንደውሻ ጭራዋን እየቆላች ለማስተናገድ የምትገደድበት ምክንያት የለም፤ እስልምና እዚያው ተፈጠርኩበት ካለው በሳዑዲ ምድር አርፎ ይቀመጥ፤ እንግድነት ከፈለገም እኛ ዜጎቹ በምንፈቅድለት መጠንና መንገድ ብቻ ሊስተናገድ ይገባዋል ሲል የገለጸ ሲሆን ምሬቱን በማከልም « ሳዑዲ ዐረቢያ ቁርአንን አሳትማ ወደራሺያ ስትልክ እንድንቀበልላት እንደምትፈልገው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በዐረብኛ ተርጉመን ወደሀገሯ እንድናስገባ በኦፊሴል ትፈቅድልናለች ወይ? ሲል ጠይቋል።

የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተመለከተ ለሙፍቲው የሰጡት መልስ ምን እንደሆነ አልተዘገበም።

Saturday, December 7, 2013

መነኩሴው በግብረሰዶም ወንጀል በእስራት ተቀጡ



በአሸናፊ ደምሴ /ሰንደቅ ጋዜጣ፤ ህዳር 25 እትም/

ዐቃቤ ሕግ ለአካለ መጠን ባልደረሰ ታዳጊ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት ፈፅመዋል ሲል ክስ የመሰረተባቸው የ33 ዓመቱ ተከሳሽ አባ ገብረፃዲቅ ወልደሩፋኤል በቀረበባቸው ማስረጃ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 19 ቀን 2006 ዓ.ም ውሎ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ ሰጠ።
የፌዴራሉ ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሽ ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ ፆታ ካለውና ዕድሜው ለአካለ መጠን ባልደረሰው ልጅ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት ለመፈፀም አስበው ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡00 ሲሆን፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/15 አካባቢ ልዩ ቦታው ዳንኤል ሆቴል ውስጥ ዕድሜው 15 ዓመት ከሆነው የግል ተበዳይ ጋር ግንኙነት ለማድረግ በመስማማት በሆቴሉ ሽንት ቤት ውስጥ ተከሳሽ አባ ገብረፃዲቅ ወልደሩፋኤል የግል ተበዳይን ካስገቡት በኋላ የግብረ ሰዶም ግንኙነት ሊፈፅሙ ሲል ሌሎች ግለሰቦች እየተከታተሏቸው መሆኑን ሲያውቁ ሱሪያቸውን አጥልቀው መሸሻቸውን ድርጊቱም በጅምር የተቋረጠ መሆኑን ያትታል። በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ለፈፀመው ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የሚፈፀም የግብረ ሰዶም ጥቃት ለሥነ-ምግባር ተቃራኒ በሆነ ሌላ ድርጊት ሙከራ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።  
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎትም የጉዳዩን ግራና ቀኝ ሲመረምር ከቆየ በኋላ ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃዎች በሚገባ ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነው ሲል ብይን ሰጥቷል። ይህም በመሆኑ ባሳለፍነው ሐሙስ ህዳር 19 ቀን 2006 ዓ.ም በዋው ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙበት ወንጀል በአራት አመት ፅኑ እስራትና ለአራት አመታት በሚዘልቅ የመምረጥ መመረጥ እና ከማንኛውም ህዝባዊ መብቱ እንደታገድ ቅጣት ተጥሎበታል።

Wednesday, December 4, 2013

አይ አበሻ! አበሻና ሆድ!

 
አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤
Posted on
by መስፍን ወልደ-ማርያም (Mesfin Wolde-Mariam)
ጥቅምት 2006


አበሻ ድግስ ይወዳል፤ ድግስ የሚወደው መብላትና ማብላት ስለሚወድ ነው፤ ለመብላት የአበሻ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ልጅ ተወለደ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ ክርስትና ተነሣ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ አገባ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ ሞተ ብሎ መብላት ነው፤ አበሻ ሰው ቀብሮ ሲመለስ በንፍሮ ይጀምርና ቀስ በቀስ ወደሌላው ይተላለፋል።
ሃይማኖትም ቢሆን ለመብላት ካልሆነ የነፍሱ ጉዳይማ በጣም ሩቅ ነው፤ ሕያዋን ለነገሥታት፣ ሙታን ለካህናት ይገብራሉ፤ በሚለው መመሪያ መሠረት
ግብር መቀበል ያለ ነው፤ ክርስቶስ ተወለደ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ተጠመቀ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ሞተና ተቀበረ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ተነሣ መብላት ነው፤ ማርያም አረገች መብላት ነው።
ማኅበርም የሚጠጣው (የሚበላው ለማለት ነው፤) ለመብላት ነው፤ አምላክ በተለያዩ ስሞቹ፣ ቅድስት ማርያም በተለያዩ ስሞችዋ፣ መላእክት፣ ቅዱሳን፣ ሰማዕታት ሁሉ ለመብላትና ለማብላት ያገለግላሉ፤ ወደመንግሥተ ሰማያት ለመግባት አማላጅ ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉ ማኅበር ለመብላት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፤ የሌሎች አገሮች ክርስቲያኖች በመብል አይመለሱም፤ ገበያቸው በጠገራ ብር ነው፤ ስለዚህም አብሮ መብላት ብሎ ነገር የለም።
አበሻ የሚበላው የመጣውን ሲቀበል ብቻ አይደለም፤ የሚሄደውን ሲሰናበትም  መብላት ይወዳል፤ ሞትም ቢሆን ለመብላት ምክንያት ነው፤ ቀብር ብሎ እዝን እያቀረቡ መብላት ነው፤ ሠልስት ብሎ መብላት ነው፤ ለሰባት መብላት ነው፤ ለዓርባው መብላት ነው፤ የሙት-ዓመት ደግሶ መብላት ነው፤ በቀብር ላይም  ቢሆን ለቅሶውም ‹‹ሆዴ! ሆዴ!›› ነው።
ለአበሻ ጾምም ቢሆን ለመብላት ነው፤ የጾም ትልቁ ምሥጢሩ ምግብ እንዲናፍቅ ለማድረግ ነው፤ የፍስኩ የተትረፈረፈ ምግብና ጥጋብ ባይኖር ማን ይጾማል? የለየላቸው ጠጪዎች በሁዳዴ መለኪያውንና ብርጭቆውን አርግፍ አድርገው የሚተውት ሲፈሰክ በናፍቆት ዊስኪውንና ቢራውን ለመጋት ነውኮ! ይህ ባይሆን አንድ ጊዜ ሞጣ ያየሁትየበግ ሌባ ለምን ይጦም ነበር? ታሪኩ እንዲህ ነው፤ በሞጣ አውሮጵላን ማረፊያ አንድ የበግ ቆዳ የያዘ ሰውዬ በፖሊሶች ይጠበቃል፤ እንደሰማሁት በግ ሰርቆ ጫካ ይወስድና ቆዳውን ገፎ ለመሸጥ ወደገበያ ሲሄድ ተይዞ ነው፤ የሁዳዴ ጾም ስለነበረ ሥጋውን ለማይጾሙ አውሬዎች ጫካ ውስጥ ጥሎ ነው! አሁን ይህ ሰውዬ የሚጾመው ሲፈሰክ ደህና አድርጎ በናፍቆት ለመብላት ካልሆነ ለሌላ ለምንድን ነው ሊባል ነው?
ሥራም ቢሆን ለመብል ነው፤ ከመኝታው ሲነሣ ጀምሮ እስኪተኛ ቢበላ ደስታውን አይችለውም፤ለገና፣ ለፋሲካ፣ ለእንቁጣጣሽና ለመስቀል ለገናና ለፋሲካ፣ ለእንቁጣጣሽና ለመስቀልም ከሌሊት ጀምሮ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት እየተዘዋወሩ በመብላት ቀኑ ያልፍ የለም እንዴ! በእውነት አበሻ መብላት የሚወደውን ያህል ማብላትም ይወዳል፤ ስሞት! ስቀበር! አፈር ስገባ! … ወዘተ. እየተባባለ የጠገበውን ሰው በቁንጣን እንዲሰቃይ ማድረግ የአበሻ ልዩ የፍቅር መግለጫ ነው! መጎራረስም አለ፤ ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው እየተባለ ፍቅርና ሆድን ያያይዛል፤ አነጋገሩ አበሻ ለመብላት ያለውን እንጂ ፍቅርን አይገልጽም፤ ማሰጨነቅንና ፍቅርን ምን አገናኛቸው! አበሻ ሌላም ተረት አለው፤ የወለዱትን ካልሳሙለትና የሠሩትን ካልበሉለት ደስ አይለውም ይባላል፤ የልጅ ፍቅር ከምግብ ፍቅር ጋር ተስተካክሎ የቀረበ ይመስላል፤ ደሞም ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል፤ ይላል፤ ጉድ ነው! ሲሞትም ተከተሉኝ የሚል ይመስላል!! ለነገሩማ ፍቅርምኮ አበሻ ዘንድ ምግብ ነው፤ ሆዴ! አንጀቴ! ጎንደሬዎች ሲያሳምሩት ደግሞ ራቴዋ! ይሉታል።
ዛሬ ዛሬ አበሻ ከማብላት ይልቅ ማጠጣት ይወዳል፤ እስቲ ሰዎች ሰብሰብ ብለው በሚጠጡበት ቦታ ብቅ በሉ፤ ያቺን የፈረደባትን ጉበት ለማቃጠል በአቦ፣ በሥላሴ የማይል የለም፤ ቸገረኝ ብሎ ገንዘብ የሚጠይቅ አይምጣ እንጂ ለማብላትና ለማጠጣት፣ ለአንድ ጥሪኝ ፈሳሽ አበሻ ቸር ነው፤ በላኤ ሰብስ በማርያም ስም አንድ ጥሪኝ ውሀ ሰጥቶ አይደለም እንዴ የበላው ሰው ሁሉ የተሰረዘለት? አበሻ በሆድ አይጨክንም።
ለአበሻ ምግብ ክቡር ነው፤ ስለዚህም ምንም ነገር ሲበላ ተቀምጦ ነው፤ ፈረንጅ ቂሉ በየመንገዱ እንደመጋዣ ያመነዥካል፤ በየመንገዱ ማመንዠክ ምግቡን ማዋረድ ነው፤ ከዚያም በላይ ቆመው ሲበሉ ወደጉልበት ይወርዳል ይላል፤ ለአበሻ ጨጉዋራና ጉልበት በቀጥታ የተገናኙ ናቸው፤ ሳይንሱ የሚለው ሌላ ቢሆንም አበሻ አበሻ ምን ቸገረው?
ለመሆኑ ከሆድ ጋር ያልተያያዘ ነገር አበሻ ምን አለው?  ነገርን በሆድህ ያዘው ምን ማለት ነው? ነገርን ማብላላት የማሰብ ምትክ መሆኑ ነው፤ ልጆች ሆነን አይጥ አበላሁት እንል ነበር፤ አሸነፍሁት ለማለት ነው፤ ዛሬም ቢሆን ቁማርተኞች በላሁ-ተበላሁ ይባላሉ፤ አይጥ ከማብላት ገንዘብ ወደማብላት ተለወጠ እንጂ ከሆድ አልወጣም፤
አበሻ በሆዱ የማይዘው ምን ነገር አለ? ፍቅርም፣ ጥላቻም በሆድ ነው፤ ቂምም በሆድ ነው፤ ምኞትም ፍላጎትም በሆድ ነው፤ ተስፋም በሆድ ነው፤ መጥኔ ይስጠው የአበሻ ሆድ! ሁሉን ከተናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፤ አይ የአበሻ ሆድ! የነገር ስልቻ ከመሆኑ በላይ ነገር አልቆበት ‹‹ነገር እንዳይርበው(!)›› ጥንቃቄ ማድረግ አለበት! የአበሻ ሆድ እህል ቢያጣና ከእህል ባዶ ቢሆንም ከነገር ባዶ መሆን የለበትም፤ እህል ቢጠፋም ነገር አይጥፋ!
የአበሻና የሆድ ነገር በዚህ አያበቃም፤ አበሻ ሲያመው ቡዳ በልቶት ነው፤ ቆንጆውን ሁሉ ቡዳ ይበላዋል፤ ልብ በሉ ለአበሻ በዓይንም ይበላል ማለት ነው! አንዳንዴም ሲያመው መድኃኒቱ ምግብ ነው፤ ለሆድ ቁርጠት ብላበት፤ አበሻ ሲሞትም ለቅሶው ሁሉ ስለሆድ ነው፤ ‹‹የኔ ሆድ፣ ሆዴ እንዴት ይቻለው! ፋሲካን የት ልፈስክ?››
እስከናካቴው ‹‹ሆድ›› የሚባል ቃል ከአበሻ ቋንቋ ፈጽሞ ቢሰረዝ ቋንቋው ብቻ ሳይሆን አበሻም ጉድ ይፈላበታል፤ አእምሮ፣ ኅሊና የሚባሉትን ቃላት አበሻ አያውቃቸውም፤ ተግባራቸውንም ሁሉ ለሆድ ሰጥቶታል።