Monday, December 2, 2013

የአፍሪካ ኅብረት ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ምዝበራ ተጋለጠ!

ለውድ ደጀ ብርሃን  ብሎግ በቤተክርስቲያናችን ያሉ ሕገ ወጥ አሰራሮችን በመቃወም የምታደርጉትን እንቅስቃሴ የምንደግፍ ሲሆን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በእውነት የሚታመኑ መሆን እንዳለባቸው እናምናለን እኛ የአፍሪካ ኅብረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ሰንበት ተማሪዎች ከእኛው አብራክ የወጡ ቤተክርስቲናችንን ይጠብቁልናል ባልናቸው ወንድምና እህቶቻችን ቤተክርስቲያን እየተመዘበረች ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ይህንን እውነት ተረድቶ በስመ ታማኝነት ከሌቦች ጋር የተሰለፉ ሰንበተማሪዎችን እንዲጠብቅና እንዲያጋልጥ በቅርቡ የተፈጸመውን ምዝበራ በብሎጋችሁ እንድታወጡልን እንጠይቃለን፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በህዳር 12 ከተሰበሰበ ገንዘብ 200.000.00 (ሁለት መቶ ሺህ ብር ) በላይ ገንዘብ ተመዘበረ፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ የዓመት ፍቃድ በመሆናቸው በእለቱ ቆጠራ አልተገኙም ይህንንም እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠርና የሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቀ መንበር ስልክ ተደውሎላቸው ቆጠራውን አቋርጠው በመውጣታቸው የደብሩ ዋና ጸሐፊ መ/ስ አብርሃም አቧይ  የወረዳው ስራ አስኪያጅ የአባ አእምሮ የቅርብ ዘመድ ከወረዳ የተወከሉት ወ/ሮ አባይ እና የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ ወ/ሮ አዲስ ዓለም እንዲሁም በአዲስ አበባ ሙስናና ዘረፋን በማበረታታት እነ የካ ሚካኤልን እንዳያገግሙ አድርጎ በዘረፋ ባዶ ያስቀራቸው በአዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ የውጪ ሀገር ኗሪዎች 7 ፎቅ ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች  ሰርቶ የሚያከራየው ቀድሞ አለቃ የአደራው ንጉሤ ሴት ልጅ  ወ/ት እጸገነት አደራው በገንዘብ ያዥነት እንዲሁም በካቴድራሉ መልካም ሰው በመምሰል ለሁሉ ወዳጅ የሆነው አቶ ፋንታሁን ምረቴ እና ሊቀ ቀትጉሃን ኃ/ጊዮርጊስ በጋራ ዘረፋውን ማከናወናቸው ታውቋል፡፡የአፍሪካ ኅብረት ቅ/ሚካኤል በህዳር 12 ቀን ከምእመናን የተሰበሰበውን ገንዘብ ግማሹን በመቀነስ 280 ሺህ ብር ብቻ ወደ ደብሩ ባንክ እንዲገባ ሲደረግ ሌላውን ግን በቆጠራው የተገኙት ስማቸው የተዘረዘሩት ግለሰቦች ተካፍለውለታል፡፡ የደብሩ ጸሐፊ አብርሃም አቧይ ለአቡነ እስጢፋኖስ ቀራቢ ነኝ በማለት ደብሩን እየበጠበጠ ሲሆን፤ በትዳሩ ላይ በመወስለት እና ከሙስሊም ሳይቀር ዲቃላ በመውለድ ቤተክርስቲኒቱን ያሰደበ ተግባር መፈጸሙንና በአባ እስጢፋኖስ ዘንድ አለኝ በሚለው ተሰሚነት ሰራተኛውን እያስፈራራና እያሸበረ እንደሚገኝ ለማወቅ ተእሏል፡፡ በደብሩ ሰንበት ት/ቤት ተማሪ የነበሩና በኋላ በግል ጥቅም ታውረው የምዷየ ምጽዋት ገንዘብ የጣማቸውና ወደ ሰራተኛነት ያደጉት ዲ/ን ዳዊት ወርቁ ከሰበካ ጉባዔ አባልነት በተጨማሪ የደብሩ የእለት ገንዘብ ሰብሳቢ ተደርጎ የተመደበ ሲሆን ሌላዋ ሰንበት ተማሪ የመ/ር እንቁ ባሕርይ ቅምጥ የደብሩ ምክትል ሒሳብ ሹም በመሆን ስትሰራ የነበረቸው ወ/ት ምንጭቱ ከሒሳብ ሹሙ ጋር  ባለት የፍቅር ግንኙነት ቤተክርስቲኑ ውስጥ ያልተገባ ተግባር በመፈጸሟ ወደ ሌላ ቤተክርስቲያን መዛወሯን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የገንዘብ ምዝበራውን ለማን አቤት ይባላል? ባለቤት የሌላት ቤተ ክርስቲያንን ከታች እስከላይ ወሮበሎች ወረዋታልና።

Friday, November 29, 2013

ሰው መሆን ከቻልን ስደትም ያልፋል!


ማንንም መውቀስ አንሻም። እየሆነ ያለውን ግን ከመናገር አንቆጠብም። ኢትዮጵያውን ዓለሙን ሁሉ እንደጨው ዘር ተበትነው መሙላታቸው እውነት ነው። ከደርግ ዘመን ልደት ጀምሮ የፖለቲካና ከረሀብ የመሸሽ ስደት እንደአማራጭ የተወሰደ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ብሶበታል። ሰው «ብሞትም ልሙት» በሚል መንገፍገፍ ሀገር ለቆ መሰደድን እንደአማራጭ ሳይሆን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። የሞቱ፤ መከራ የደረሰባቸውና የተጎዱ እንዳሉ እያየ፤ እየሰማ ይሰደዳል። በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሰው ለማለፍ መሰደድን የሚመርጠው ለምንድነው? ብሎ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ዓይናችንን ጨፍነን ከእውነታው ለማፈግፈግ ካልፈለግን በስተቀር ኢትዮጵያ የኔ ናት፤ ሠርቼ ልኖርባትና ልለወጥባት እችላለሁ የሚል ስሜት ከውስጡ ያለቀ ይመስላል። ሁሉም ስደተኛ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለሚገኝ ይሰደዳል ባይባልም አብዛኛው ግን የኢኮኖሚ አቅሙ እንደሰው ለማኖር ስላልስቻለው ማንኛውንም ሥራ ሰርቶ የተሻለ ክፍያ በማግኘት ራሱን መለወጥ ወደሚችልበት ሀገር መሰደድን እንደሚመርጥ ለማወቅ ምርምር አይጠይቅም። የሕይወታችን አንዱ ገጽታ ስለሆነ እናውቀዋለን።
  ሀገር ውስጥ ባለው ልማትና እድገት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ብዙዎች መሆናቸውም አይካድም። የሚጨበጥ፤ የሚዳሰስና የሚታይ እድገት መኖሩም እውነት ነው። የእድገቱ መነሻና ሂደት፤ መጠንና ስፋት፤ የተጠቃሚነት አንጻራዊ ሚዛንን እንዴትነት በተመለከተ ለባለሙያዎቹ ትንተና ትተን ለስደት የሚዳርገውን አንዱን ነጥብ በመምዘዝ የስደት እንግልቱን ልክ ለመመልከት እንሞክር።

በቅርብ የማውቀው ወዳጄ በባህር አቋርጦ የመን፤ ከዚያም ሳዑዲ ዐረቢያ፤ በለስ ቀንቶት ወደአንዱ አውሮፓ ሀገር ከመሻገሩ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ይሰራ ነበር። ደመወዙ ተቆራርጦ አንድ ሺህ ከምናምን ብር እንደነበር አውቃለሁ። ለአካለ መጠን ከደረሰ በኋላም ቢሆን ከወላጆቹ ጋር ተዳብሎ እንዳይኖር ቤተሰቦቹ ያሉት ክፍለ ሀገር ነው። ስለዚህ ቤት ተከራይቶ ከመኖር ውጪ በረንዳ እያደረ አስተማሪነቱን ሊቀጥል አይችልም። በወር 700 ብር እየከፈለ አራት በአራት በሆነች ጠባብ ክፍል እየኖረ ጊዜ ለማይሰጠው ለሆዱና ካላስተማረ ስለማይከፈለው ለትራንስፖርት የምትተርፈውን ገንዘብ እናንተው ገምቱት። የልብስ ጉዳይ በዓመት አንዴ ለዚያውም የሆነ መና ነገር ከወረደለት በቂ ነው። ቤት ሰርቶ፤ ሚስት አግብቶ የሚባለውን ነገር ሌሎች ሲያደርጉት በማየት ከሚጎመዥ በስተቀር አስቦትም፤ አልሞትም አያውቅም። የሀገሬ ሰው «እዬዬም ሲደላ ነው» ይል የለ!
  የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባ ቤት ለሌላቸው የሚል ይመስለኛል። ይህ አስተማሪ ወዳጄ ቤት ከሌላቸው ሰዎች ግንባር ቀደሙ ነው። ነገር ግን የኮንዶሚኒየም ቤት ለሌላቸው የሚለው መስፈርት ይህንን ወዳጄን አይመለከተውም። ወዳጄን ቤት ከማግኘት የከለከለው ቤት ስለነበረው ሳይሆን ገንዘብ መክፈል ስላልቻለ ብቻ ነው። እናም ኮንዶሚኒየም ቤት ለሌላቸው ሳይሆን መክፈል ለሚችሉ የሚሰጥ በመሆኑ ወዳጄ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ቢሆን  ቤት ለመሥራት ወይም ለመግዛት እንደማይችል ስለተረዳ ቀለም የሚዘራበትን፤ አዲስ ትውልድ የሚፈጥርበትን የመምህርነቱን ሥራ ትቶ እየቆሙ ከመሞት፤ እየሄዱ መሞትን ምርጫው አድርጓል። በአንድ ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምህራን የሚሆን የጋራ ቤት የመሥራት ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል ሰምቼ ነበር። ምን እንደደረሰ አላውቅም። የሆኖ ሆኖ ከኑሮው ውድነት ማለትም የቤት ኪራዩ፤ የቀለብ ዋጋ፤ የትራንስፖርቱ እጥረት፤ የሥራ ቦታ ጫና ተዳምሮ በሚፈጥረው ኅሊናን ሞጋች የዘወትር የሃሳብ ተጽዕኖ ሥር የወደቀው ወዳጄ ለስደት ቢዳረግ ብዙም ሊያስገርመን አይገባም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካውን ወሬ ትተን እንደሰው ለመኖር ሦስት ዋና ዋና ነገሮችና ዐራተኛው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነጥብን ማግኘት አስፈላጊ ይመስሉኛል።
  1/ የምግብ እህሎች ዋጋና አቅርቦት አለመመጣጠን ያስከተለው ንረት በአስቸኳይ ማስተካከል ካልተቻለ እድገታችን ካላመጣው ገቢ ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል አይገባኝም። የጠገበ የተራበ ያለ ስለማይስለው ካልሆነ በስተቀር ውድነቱ መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው።

 2/ የቤት ኪራይ ዋጋን ማርገብ፤ የቤት መሥራት አቅምን ማመቻቸት፤ ለሽግሩ ደራሽ አማራጭን መፈለግ የግድ ይላል።  ሰው በልቶ ለማደር ቤት ያስፈልገዋል። የሰው ቁጥርና የመኖሪያ ቤት አይመጣጠንም። ኪራይ ተወደደ፤ ቤት ለመሥራት አቅም የለም። መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየጣረ ቢሆንም የችግሩ ግዝፈት እየተሄደ ካለበት መንገድ ጋር አይመጣጠንም።  በአንድ ዓይነት መንገድ ማለትም የኮንዶ ቤቶች ግንባታ ላይ ችክ በማለት የተለያዩ አማራጮችን  የማመንጨት  ችግር አለ።  
  3/ እያደገ ለመጣው የስራ አጥ ቁጥር አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ወቅታዊና አንገብጋቢ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ገቢና ኑሮ ካልተመጣጠኑ ስደት መቼም አይቀርም። 30 ሺህ ቢመጣ፤ 60 ሺህ መውጣቱን አያቆምም። «የማይሰራ አእምሮ የተንኮል ጎተራ ነው» ያለው ማነው? ግድያ፤ ቅሚያ፤ ዘረፋና ስርዓተ አልበኝነት እንዳይመጣ በሥራ መጥመድ ከሚመጣው ተንኮል ሊታደግ ይችላል። ሥራ ፍጠሩ ይባላል። ከሜዳ ተነስቶ ሯጭ መሆን አይቻልም። ዋጋ ያለው ሩጫ ምን እንደሚመስልና ጥቅሙን ማስረዳት ተገቢ ነው። ያለበለዚያ ዝም ብሎ ሩጫ እብደት ነው። ቁጭ ማለትን ለተለማመደ ሥራ አጥ፤ ሥራ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል መንገድ ማሳየት ተገቢ ይመስለኛል።

 አራተኛውና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ ማንኛውም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ ተንቀሳቅሶ በመስራት ሀብት ማፍራት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥቱ ይህንን ይፈቅዳል ቢልም መሬት ላይ ያለው እውነታ ለየቅል ናቸው። ተንቀሳቅሶ በሕጋዊ ሥራ፤ ሕጋዊ ሀብትን ማፍራት መቻል በራሱ የስራ አጥ ቁጥርን ይቀንሳል። አዲስ አበባ ላይ መሬት በሊዝ ገዝቶ ቤት ለመሥራት በቂ ገንዘብ የሌለው ሰው፤ ዲላ ሄዶ በአቅሙ መስራት ከቻለ ወይም ለመነገድ የሚከለከልበት ምክንያት አይገባኝም። የክልሉ ነዋሪ የሚለው ዜማ እንደሀገር ለማስቀጠል አቅም የሌለው ርካሽ ቃል ነው።
  ፖለቲካው የራሱ መንገድ ቢኖረውም ያለፖለቲካ ለመኖርም እንኳን ምግብና መጠለያ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። ዝንጀሮ «አስቀድሞ መቀመጫዬን አለች» አሉ ይባላል። ኢትዮጵያዊያን ወደሳዑዲ ዐረቢያ የተሰደዱት ዲሞክራሲን ፍለጋ ሳይሆን ዳቦ መግዢያ ለማግኘትና ሳዑዲዎችም ኢትዮጵያውያንን እየገደሉና እየደበደቡ ያባረሩት በፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ስለተንበሸበሹ ሳይሆን በፔትሮ ዶላር ስካር ስለጠገቡ ብቻ ነው።
  የኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብ ከሌላው በተለየ እርግማን የለበትም። እግዚአብሔርም ስለጠላን የደረሰብን ቁጣ አይደለም። መንግሥታችን እየሰራ ቢሆንም ችግሩ እየጨመረ የመሄዱ ዋና ምክንያት ብዙ መስራት ስላልቻለ ነው። ብዙውን ጊዜ ለወሬና ለስብሰባ፤ ትንሹን ጊዜ ለሥራ ስለሰጠ ነው። ችሎታ የሌላቸው ሰዎች አመራሩን ሲይዙ ሥራ ፈቀቅ አይልም። ውሸት እውነትን ከተካው መንግሥቴ ታማኝ ነው የሚል አይገኝም። ሌብነት ሥራ ከሆነና ፍትህን ቁልቁል ከደፈቁት እንኳን መገንባት፤ የተገነባው ራሱ ይፈርሳል።  «የትም ሥሪው ወንበሩን አምጪው» ሀገርና ሕዝብ ይጎዳል።  ቀናነትና ሀገራዊ ቀናዒነት ከሌለን ኢትዮጵያዊ ለመሰኘት የሚያችለን ምናችን ይሆን? ቀናነት ጠፍቷል። ቀናዒነትም ደብዛው የለም። እንደእሪያ ለራስ በልቶ፤ ለራስ ኖሮ፤ በኅሊና ቆሻሻ ውስጥ መጨቅየት ጥሩም አይደል።  ኢትዮጵያዊ መሆን ባንችል ሰው እንሁን። ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያዊ ውስጥ ገብተው በጉልበታቸውና በሙያቸው እያገለገሉ ያሉት ሰው መሆን በመቻላቸው ይመስለኛል። ብር፤ስንዴና ዘይትስ የሚረዱንም ሰዎች በመሆናቸው እንጂ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ አይደለም። ሰው መሆን መቻል በራሱ ለሰው ደራሽነት ትልቅ ድርሻ አለው።  እግዚአብሔር ሰው እንድንሆን ይፈልጋል። በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረን እንደሰው ተፈጥረን እንደእንስሳ እንድንኖር አይደለም። እኛ ወደን ባመጣነው ስግብግብነት የተነሳ የመጣብንን ስደት ከእግዚአብሔር የተሰጠንን እድል አድርገን ልንቆጥር አይገባም። ስስት፤ ስግብግብነትና የቀናነት እጦት እንስሳዊ ጠባይ ነው። የቤት እንስሳት ሳይጣሉ የተሰጣቸውን ተስማምተው መብላት አይችሉም። በእኛም ዘንድ ይህ ይስተዋላል። ለሥልጣን ስስት፤ ለገንዘብ ስስት፤ ለሹመት ስስት አለ። ስግብግብነትና ቀና አለመሆን ሲከተሉት ጠኔና ችጋር ሊጠፋ አይችልም። እስኪ ሰው እንሁን። ይህም ዘመን ያልፍና እንዲህም አሳልፈን ነበር የምንልበት ቀን ይመጣል። ሰው መሆን ከቻልን አዎ መምጣቱ አይቀርም።

Wednesday, November 27, 2013

አንጎላ በሀገሯ የእስልምናን እንቅስቃሴ አገደች ተባለ!

 

 
 በትላንትናው ዕለት የግብጹ የሃይማኖት ሙፍቲ ሻውቂ ዓለም አንጎላ እስልምናን ከሀገሯ እንደሃይማኖት ተቋም ማገዷ በ 1ነጥብ 5 ቢሊዮን ሙስሊም ላይ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ልታውቅ ይገባታል ሲሉ አስጠነቀቁ። ይህም ትልቅ ዋጋ ያስከፍላታል ሲሉ ማስፈራሪያቸውንም አክለዋል።
 ይሁን እንጂ 83% የክርስትና እምነት ተከታይ ያለባት አንጎላ በሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬቷ በኩል በሰጠችው መግለጫ በቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በታች የሆነው የሙስሊም ቁጥር በነጻነት እየኖረ መገኘቱን በመግለጽ የሚታዩት አንዳንድ የእስልምና እንቅስቃሴዎችን ግን በትኩረት እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በየቦታው እየሄዱ መስጊድ መገንባት፤ የሃይማኖት ትምህርት ቤት መስራትና እስልምናን ለማስፋፋት የሚደረጉ የእጅ አዙር እንቅስቃሴዎችን ግን መንግሥታቸው በፍጹም እንደማይቀበልና እንደማይታገስ ሳይገልጹ አላለፉም። አንጎላ ከየትኛውም የእስላም ሀገራት ጋር የትብብር ስምምነት ስለሌላት በውስጥ ጉዳያቸው የትኛውም የእስላም ሀገር እጁን እንዳያስገባ አሳስበዋል።
 እስልምና በተስፋፋባቸው የአፍሪካ ሀገራት ሁከት፤ ብጥብጥና ግድያ እየተስፋፋ እያየን ቁጥሩ ምንም ትንሽ ቢሆን በሌላው ያየነው ሁኔታ በሀገራችን እንዲታይ በምንም መልኩ እድል አንሰጥም ያሉት የአንጎላው  የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክተር ያለንን ሰላም ለማስጠበቅ የምንወስዳቸው እርምጃዎች ከሃይማኖት ዲሞክራሲ ጋር በፍጹም አይያያዝም ሲሉ የሃይማኖት ነጻነትን ትጋፋለች በማለት ለሚጮሁ ክፍሎች አስረድተዋል።

ንግግራቸውን በማያያዝም እንደተናገሩት፤ ማንም አንጎላዊ በእምነቱ ሳቢያ በግሉ አይጠየቅም፤ አድልዎም አይደረግበትም።  ነገር ግን ገንዘብና ነጻነት አለኝ ብሎ የትም እየዞረ መስጊድ ለመትከልና ከራሱ አልፎ በሌላው አካባቢ ላይ የማስፋፋት መብት የለውም። በቂ የአምልኮ ስፍራና የእምነቱ መግለጫ ስፍራ እያለው ተጨማሪ የመስፋፋት እንቅስቃሴ ሲደረግ በማግኘታችን አንድ ያልተፈቀደ መስጊድ ዘግተናል፤ አፍረሰናል፤ ይህንንም ቁጥጥር አጥብቀን እንገፋበታለን ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

  በአንጎላውያኑ ዘንድ እስልምና እንደሁከትና የብጥብጥ መሳሪያ የሚታይ በመሆኑ 90% የሆነው ሕዝብ የመንግሥትን አቋም ይደግፋል። አንጎላ በነዳጅ ሀብት የበለጸገችና በእድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች የምትገኝ ሰላማዊ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ በ21ኛው ክ/ዘመን የመስፋፋትና ሁሉን እስላማዊ ግዛት የማድረግ ዐረባዊ ዘመቻ በፍጹም እንደማትቀበል እየተናገረች የምትገኘው አንጎላ በእውነት እድለኛ ሀገር ናት።
ያለምንም ማጋነንና ጥላቻ እስልምና ባለበት በየትኛውም ሀገር ሁከት አለ። የመቻቻል  ዜማ ጊዜ እስኪወጣልህ በሚል ብልጠት ስር የሚዘመር ሲሆን አጋጣሚ ሲገኝ የሃይማኖቱ መሠረት ሁከትንና ብጥብጥን ስለሚያበረታታ፤ ከእኔ በቀር ሌላውን «አላህ» አይፈልገውም በሚል ጭፍንነት ስለሚራገብ፤  ያንን ለማስፈጸም እስልምና የሚጓዝበት መንገድ ሁሉ ዐመጽና ኃይል የተቀላቀለበት  እንቅስቃሴ መሆኑ ግልጽ ነው። አንጎላ በሀገሯ የጀመረችው የእስልምናን  መስፋፋት የመገደብ ጉዳይ ከእምነት ነጻነት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን በነጻነትና በዲሞክራሲ ሽፋን በገንዘብና በዘመቻ  የሚደረግ የሃይማኖት ወረራን መከላከል በመሆኑ አንጎላ በርቺ እንላለን።