Thursday, November 21, 2013

የወደቀው የንጋት ልጅ ምልክቶች!!


 ከግደይ ገብረ ኪዳን የተሸሸጉ ታሪኮች ጽሁፍ ( ተሻሽሎ የተወሰደ)

አሁኑ ወቅት በሃገራችን ስለ ኢሉሚናቲ ማውራት ከአመት በፊት ከነበረው ሁኔታ እንኳ በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ አሁን ቢያንስ ስሙን እንኳ የሚያውቀው ሰው ቁጥር እጅግ በዝቷል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ስለ ኢሉሚናቲ ምንነት የጠራ ወይም በነባራዊው የዓለም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ መድረክ ዙርያ ያለውን ወይም የሌለውን ሚና በቅጡ መረዳት ላይ አልተደረሰም፡፡ በዚህ ፅሁፍ በተለይ በሃገራችን ላይ አትኩሮት በማድረግ ትክክለኛ የምርምር መርህ ተጠቅመን ስውሮቹን እጆች ለመዳበስ እንሞክራለን፡፡

 ኢሉሚናቲ ምንድን ነው?

አንዳንዶች የኢሉሚናቲ ብቸኛ ፈጣሪ አዳም ዉሻፕት ነው፣ ኢሉሚናቲም ገናናነትን ለማግኘትና ለመጥፋት የ12 ዓመታት እድሜ ብቻ ነበረው ብለው ቢናገሩም አብዛኞቹ የባእድ ሚስጥራቱን የሚያቁ አባሎች እንደሚፅፉት ግን የባቫርያ ኢሉሚናቲ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ወንድማማችነት መገለጫና መሰረቱም እስከ መካከለኛው ዘመን የነበሩት ናይትስ ቴምፕላርስ (የቤተመቅደሱ ባለሟሎች) ድረስ የሚሄድ እንደሆነ ይፅፋሉ፡፡
ማንሊ ፒ. ሃል 33ኛ መዓርግ የደረሰ ሰፊ ተቀባይነት ያለው የራሳቸው የፍሪሜሶኖች ፀሃፊ “Masonic Orders of Fraternity” በሚል ፅሁፉ ለዘመናት ሳይታይ ለለውጥ ሲሰራ የነበረ “የማይታየው ግዛት” ስለሚለው ነገር ያብራራል፡፡ በታሪክ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያየ ስም በያዙ የተለያዩ ድርጅቶች አንዳንዴ ይታያል ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው እኚህ ቡድኖች የማይታወቅ ግን ታላቅ ተፅእኖ በማህበረሰቡ ላይ ፈጥረዋል ይላል፡፡ ይህም ቀጣዩን ትውልድ ለመቅረፅ የትምህርት ስርአቱን በመቀየርም ሳይቀር ይላል፡፡ በዚህ ፅሁፉ ሃል በ17ኛው እና በ18ኛ ክ/ዘመን የባቫርያ ኢሉሚናቲ በንቃት በሚንቀሳቀስበት ወቅት የሚስጥር ማህበራትን ስራ በተመለከተ “ዝምታና” የመረጃ እጥት እንደነበር ይገልፃል፡፡ በዚህ ግዜ ነው የሚስጥር ማህበራት አብዮቶችን በማስነሳት፣ ዘውዳዊና ሃይማኖታዊ ስልጣናትን በማናጋት ስራና የባንክ ስርአቱን በመቆጣጠር እንቅስቃሴዎች ተወጥረው የነበሩት፡፡ የባቫርያ ኢሉሚናቲ ሃል የሚለው የማይታየው ግዛት አካል ነበር? ዛሬስ እየተንቀሳቀሰ ነው ወይስ ጠፍቷል? መጀመርያ አዳም ዉሻፕትንና አሳፋሪ የሚስጥር ማህበሩን እንመለከታለን፡፡
በዚህ ዙርያ የበለጠ ለመረዳት የሚከተለውን ፅሁፍ ያንብቡ፡ ኢሉሚናቲ፡ አነሳሱ የሚስጥር ማህበራቱ እና ተፅእኖው
ኢሉሚናቲ እና የዓለም አቀፋዊነት እና ፅንፈኝነት ፖለቲካ ታሪክ
የኢሉሚናቲ ብዙም ስውር ያልሆኑ እጆች (እንዲህ ግዙፍ ሴራ መቶ በመቶ መሰወር ይከብዳልና) በታሪክ አጋጣሚ ተደጋግመው ተከስተዋል፤ ለአብነት ያህል የመጀመርያውን የፈረንሳይ አብዮትን እንመልከት፡፡
በ1789 የደረሰው የፈረንሳይ ዘውድ በሃይል መገልበጥ ለብዙዎች የሚያመላክተው ከባህላዊ ተቋማቱ ይልቅ የአብዮተኞቹ ጃኮቢኒዝምና ኢሉሚኒዝም የበላይነት ማግኘትን ነው፡፡ በወቅቱም የታወጀው የሰብአዊ መብቶች እወጃ ሰነዱ ሜሶናዊና ኢሉሚናቲ ሃሳቦችን ወደ ፈረንሳይ መንግስት ስርአት ያስገባ ነበር፡፡ የሃገሪቱ አዲሱ መፈክሯ የሆነው፡ ነፃነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት አስቀድሞ ለዘመናት በፈረንሳይ ፍሪሜሶን ሊጆች ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ነው፡፡
የአብዮቱ መታሰብያ በሚለው ፅሁፍ ላይ እንዳየነው ዋናው የዶክመንቱ ቅጂ ብዙ የሚስጥር ማህበሩን ምልክቶች የያዘ እንደሆነ አይተናል፡፡ መጀመርያ ከላይ ሶስት መአዝን ውስጥ ያለው የሚያበራው የሆሩስ ዓይንን እናያለን፡፡
ከአርእስቱ ስር እራሱን የሚበላው የሂወት ኡደትን ያለማክታል የሚሉት የኦሮቦሩስ እባብ ምስል ይገኛል፡፡ ይህ ከአልኬሚ፣ ግኖስቲሳውያን እና ኸርመቲዝም ሁሉም ከሜሶን ትምህርቶች ኮር የሆኑት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከኦሮቦሮሱ ስር ቀዩ የፍሪግያ ኮፍያ ጦር ላይ ተሰክቶ ይታያል፡፡ ይህ በወቅቱ በአለም ዙርያ የአብዮቶች ምልክት የነበረ ነው፡፡ የአዋጁ ክፈፍ የታጠረው በሜሶናዊ ጥንዶቹ ቋሚ አምዶች ነው፡፡ እነዚህ ሁለት አምዶች የሜሶን ቀንደኛ ምልክት ናቸው፡፡ ሌሎችም አሉበት፡፡
ፒራሚዱ እና ዓይኑ ምልክት


 ይህ የሚታየው የአሜሪካን ገንዘብ አንድ ዶላር ሲሆን፣ ገንዘቡ ላይ ከቀኝ በኩል የሚታየው ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ የተጨመረው ከአሜሪካ ሃገር ማህተም በስተጀርባ የነበረ ነው፡፡ ማህተም የጀርባ ቅርፅ እንዴት ሊኖረው እንደቻለ የቀረፁት ያውቁታል፡፡ ይህ አርማ የአዲስ የአለም ስርአትና የኢሉሚናቲ የሀረም/ፒራሚድ ማህተም የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ማህተም የሴራው እቅድ የንድፋዊ መግለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከላይ "Annuit Coeptis—ጅማሪያችንን መርቆታል” ሲል ከስር ደግሞ፣ "Novus Ordo Seclorum—የዘመናቱ አዲስ ጅማሮ” ይላል፡፡ ከሀረሙ ጫፍ ያለችው ዓይን የሆሩስ--የፀሃይ አምላክ ሁሉን ተመልካች ዓይን የሚሉት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን መልአክ /ሉሲፈር የነበረውን ነው፡፡ በባእድ አምልኮ ዶክትሪን መሰረት እንደሚታመነው በመንፈስ እና ቁስ አካል ውህደት (ሀረሙ ከድንጋይ፣ አለትና አፈር የተሰራው የማያውቀውን (unconscious) አካል ሲወክል ከላይ የምታበራው ዓይን ያለባት ደግሞ ቁሳዊ ባልሆነ አካል --ብርሃን ወይም መንፈስ-- የሚወክል ሲሆን አዋቂው (conscious) አካል ነው፡፡ ከስር ጀምሮ ወደ ላይ የደረሰም አዲስ ሁኖ ይፈጠራል፡፡ ሀረሙ የሚያመላክተው ከሚስጥር ማህበራቱ ገብቶ ሚስጥር የሚነገረው ሰው የሚያልፍባቸውን የእድገት መአርጎች ነው፡፡ ሁሉንም ፈተናዎች ያለፈ ወደመጨረሻው መንፈሳዊ አካል ይወሃዳል፡፡ ዶላር ሌሎችም ብዙ ምልክቶች በስውር አሉበት፡፡
የአሜሪካን ማህተም የሰሩት ሰዎች ይህን አርማ በጀርባው ሲቀርፁ ማህተም የጀርባ ምስል ለምን አስፈለገው ሊያሥብል ይችላል ግዚያቸውን ጠብቀው ኢኮኖሚዊ ድቀት ካስገኙ በውኋላ ይፋ አደረጉት፡፡
“ሶስት-መዓዝን (ትሪያንግ) በኢሉሚናቲ የተለያዩ መገለጫዎች፡-  በሮዚክሩሽያኖችም ሆነ በሜሶኖች ወይም በመተተኞች፣ ኮከብ ቆጣሪዎች እና ጥቁር አስማት /ጠቋዮች እና ሌሎችም ኢሉሚናቲ ተከታዮች ዘንድ በበዓላት አከባበር ግዝያት ወሳኝ ስፍራ ይይዛል፡፡
ሴጣናውያንና መተተኞች፣ ጥንዱ ሶስት መዓዝን፣ የሰለሞን ማህተም (ሄክሳግራም) የሚባለው ሰፊ ቦታ አለው፡፡ ይህ ማህተም በተጨማሪም የአይሁዶች “ማገን ዴቪድ” ይባላል፣ ይህ ኮከብ ከሁለት ትሪያግሎች የተሰራ ነው፡፡ አንዱ ትሪያግል ወደ ላይ የሾጠጠው ስጋ ወይም ቁሳዊውን አካልና የወንድ የመራባት ተግባርን ይወክላል፤ ወደ ታች የሚጠቁመው ትሪያግል የሴት ወሲባዊነትንና መንፈሳዊ አለምን ይወክላል፡፡ ስለዚህም እዚህ የወንዴውና የሴት ትሪያግሎች ተጠላልፈው እናያለን፡፡ ይህ ወሲባዊ ውህደትን ይወክላል፡፡ በተጨማሪም የተቃራኒዎች መጣጣምን /መታረቅን፣ ዪን እና ያንግ (በሩቅ ምስራቆቹ)፣ እግዚአብሄርና ሴጣንን ያሳያል፡፡ ይህ መገዳደር የበዛበት የምልክቱ ትርጉም ግልፅ ሆኗል፡፡” ቴክሴ ማርስ “Codex Magica” (361)
ይበልጥ ለማንበብ የሚከተለውን ፅሁፍ ያንብቡ፡ ፒራሚዱ እና ዓይኑ ምልክት
ኢሉሚናቲ በኢትዮጵያ፡ ተረት እና እውነት
መጀመርያ ደረጃ እስካሁን ባለኝ ውሱን መረጃ መሰረት በቀጥታ የኢሉሚናቲ ተፅእኖ ወይም ሙሉ ቁጥጥር የለም፡፡ ሆኖም ግን በተዘዋዋሪ ዓለሙን ሁሉ እንደሚቆጣጠሩት ኢትዮጵያም ከዚህ ውጪ አይደለችም፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ንቅናቄዎች ጋር ይበልጡኑ ይተሳሰራል፡፡ ዘውዳዊ አገዛዙ ከዚህ ቀጥተኛ ያልሆነ የርእዮተ ዓለም የሚያመጣው እስር ነፃ ነበር፡፡
አሁን ከስር የማቀርብላቹ ምልክቶች በእርግጥም ኢሉሚናቲ ኢትዮጵያን ሲገዛ ነበር ብሎ አስረግጦ የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም፡፡ ገፋ ቢል ሊጠቁመን የሚችለው የኢሉሚናቲ ስውር እጆች ከበስተጀርባ እንደነበሩ ነው፡፡ ለዚህም ዋና ምክንያት የሚሆነው በመንግስት ደረጃ ቅድሚያ ለብሄራዊ ፖሊሲዎች የሚሰጥ በመሆኑ ነው፤ ኢሉሚናቲ ደግሞ በተቻለ ፍጥነት ዓለም አቀፋዊነትን እንዲከተሉ ይፈልጋል፡፡

የላሊበላ ስልጣኔ እና የቴምፕላሮች እጅ
ቴምፕላሮች እንተዋወቃቸው

በ1118 ዓ.ም የመስቀል ጦርነት በክርስቲያኖቹ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ወደ እየሩሳሌም የሚደረገውን መንፈሳዊ ጉዞ ለመጠበቅ በሚል ያሸነፉት በሁጎ ደ ፓይኔ እና ጎድፈሮይ ደ ሰይንት-ኦሜር መሪነት ማህበር መሰረቱ፡፡ በእስራኤል ዘውዱን የተረከበው ባልድዊን ሁለተኛ ለማህበሩ የሰለሞን ቤተ መቅደስ በነበረበት አካባቢ ቤት ሰጣቸው ስያሜአቸውንም --የቤተ-መቅደሱ ባለሟሎች - Knights Templar-- ከዛው አገኙ፡፡ በ1128 ዓ.ም በትሮይ በተደረገው ስብሰባ ማህበሩ በሰይንት በርናንድ በተቀረፁ ደንቦች መሰረት የቤተ-መቅደሱ ባለሟሎች እራሳቸውን በድህነት፣ በድንግልናና በታዛዥነት ለመያዝ ቃለ-መሀላ ፈፅመው እውቅና ተሰጣቸው፡፡
መተዳደርያቸው ምፅዋት በሚደረግላቸው ላይ እንደመሆኑ ይህ ደግሞ እጅግ እየበዛ በመሄዱ በድህነት ለመኖር የገቡትን ቃል አስረሳቸው፣ በ12ኛው ክ/ዘመን መጨረሻም በመላው አውሮፓ የተስፋፉ እጅግ ሃያል እና ሃብታም ማህበር እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ከአረቦቹ ገዳዮቹ ጋርና ከደማስቆ ጋር በስምምነት ይሰሩ ነበር፤ በዚህም የእውነት መመርያቸውንና እምነታቸውን ይከተሉ ነበር ማለት ከባድ ነው፡፡ በ13ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ በቀሳውስቱ ብቻ ሳይሆን በተራው ህዝብም ጭምር በክህደት መጠርጠር ጀመሩ፡፡ የሰው መመኘታቸው፣ ግድ የለሽነታቸው፣ ለቅንጦት ያላቸው ፍቅርና ስስታምነታቸው በግልፅ የህዝብ ትዝብት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ምግባራቸው ለተረትም ተርፎ፡- “መጠጣትስ እንደ ቴፕላሮች ነው” ይባል ነበር፡፡
የቴምፕላሮቹ ወዳጅ የነበረው የፈረንሳዩ ንጉስ ፊሊፔ ሌ ቤል ለጳጳስ ክለመንት አምስተኛ ጉዳዩን እንዲያጣራ መልእክ ይልክለት ነበር፤ ጳጳሱ ግን አስቀድሞ መሪያቸውን ጃኲ ደ ሞላይን ለጥያቄ ጠርቶትም ነበር፡፡ የፈረንሳዩ ንጉስ ጉዳዩን በራሱ እጅ በማድረግ ጥቅምት 13፣ 1307እ.አ.አ ቴምፕላሮችን በፈረንሳይ ማጣራትና መክሰስ እንዲጀመር አስደረገ፤ የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች፡
  1.    በማህበሩ የአባልነት መግቢያ ስነ ስርአት ላይ መስቀሉን መሳደብ፣ ክርስቶስን መካድ እና አፀያፊ የነውር ምግባሮች ማድረጋቸው፤
  2.  እውነተኛው አምላክ ነው የሚሉትን ምስልን ማክበር፤
  3.  በቅዳሴ ግዜ ለስርአተ ቁርባኑ የሚደረገው ፀሎት ማስቀረት፤
  4.  ተራዎቹ አለቆች ሃጥያት የማስተሰረይ ስልጣን አለን ማለት፤
   5.    ጋጠወጥ የሆኑ ጥፋቶችን መፍቀድ፡፡
ሙሉ ፅሁፉን ይመልከቱ፡ ቴምፕላሮች --THE TEMPLARS

ላሊበላስ?
ላሊበላ በ12ኛው ክ/ዘ መጨረሻ እና በ13ኛው ክ/ዘ መጀመርያ ኢትዮጵያን የገዛ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ፃድቅ የሆነ ንጉስ ነበር፡፡ ስሙ የተገኘው ከወላጅ እናቱ ሲሆን መነሻውም በጨቅላነቱ ከተኛበት ንቦች በዙርያው አርፈው ከበውት ስለተገኘ ለወደፊቱ ንጉስ እንደሚሆን ትንቢት ተደርጎ ስለተወሰደ ይህን ለመጠቆም የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
በንግስና ዘመኑ እየሩሳሌም በአረቦቹ መሪ ሳላዲን ተይዛ ስለነበረች ለመንፈሳዊ ተጓዦች የሷ ምትክ የሚሆን ለማነፅ ያስጀመራቸው ከተራራ ተፈልፍለው የሚወቀሩ አብያተ ክርስትያናቱ እስካሁን የታላቅነቱ ህያው ምስክሮች ሁነው ይታያሉ፡፡ 
አንዳንዶች ታድያ ላሊበላ ይህን ሊሰራ የቻለው እየሩሳሌምን ጎብኝቶ ስለነበረ ከቴምፕላሮቹ ጋር በፈጠረው ትውውቅ ብሎም ይዟቸውም በመምጣት በነሱ ድጋፍ የሰራው ነው ይላሉ፡፡ ይህን የሚሉትም አንዳድ ምልክቶችን ከአብያተ ክርስትያናቱ በመውሰድ ከቴምፕላሮቹ የተዋሰው ነው በማለት ነው፡፡
ሆኖም ግን ይህን ውድቅ የሚያደርጉ ማስረጃዎች አሉ፡፡ አንድ የቤተክርስትያኑ አወቃቀር ወይን ስነ ህንፃ ጥበብ በምድረ አውሮፓ በቴምፕላሮቹ ረዣዥም ህንፃዎች ከምድር ወደላይ ሲገነቡ በላሊበላ ግን ከዚህ በተቃራኒ ወደ ስር ተፈልፍለው ነበር የታነፁት፡፡ ይህ ሃሳብ ከላሊበላ ውጭ የትም ዓለም የለም፡፡
ምልክቶቹስ ታድያ? የተባለ እንደሆን ቴምፕላሮች ከመፈጠራቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በአክሱም ስልጣኔም የነበሩ መሆናቸውን ልብ ስንል፡ እንግዲህ ቴምፕላሮቹ ጥንታዊ ሚስጥራቱን ወስደው የሚያጣምሙ መሆናቸወን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡  ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን የቴምፕላሮች ዋና ምልክት የሆነው መስቀላቸው ነው፡፡
ላሊበላ ይህ ምልክት ከመከተቡ በፊት በአክሱማዊው ንጉስ ካሌብ መቃብር ላይ ማየት ይቻላል፡
ስለዚህ ሌሎቹም የቴምፕላር ብለን የምናውቃቸው ምልክቶች ሌላ ትርጉም ወይም መልእክት እና ዓላማ ይዘው ቀድሞኑ በጥንታዊ ኢትዮጵያ ስልጣኔ እንደነበሩ መገመት ይቻላል፡፡   



ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና ኢሉሚናቲ
አፄውንም ቢሆን ከሚስጥር ማህበራቱ ጋር ለማገናኘት የሚቀርበው ማስረጃ ውሃ አይቋጥርም፡፡ አንዳንድ አፄው ፈጣሪ ናቸው የሚሉ ራስታዎች እጃቸውን ቁልቁል በተደፋ ሶስት መአዝን ሲይዙ ሲያይዋቸው እንደ ሚስጥራዊ ምልክት እንደተጠቀሙ አድርገው ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህ የእጅ አያያዝ በኢትዮጵያ የተለመደ መሆኑን ስናስብ የአጋጣሚ ጉዳይ ወደ መሆኑ እንጂ የሚስጥር ምልክት ሁኖ አይታየንም፡፡
ከዚህ ይልቅ የሚያሳስበን ሃይለስላሴ አባል የሆኑባቸው ሜሶናዊ ማህበሮች ዝርዝር ነው፡-
Chief Commander of the Order of the Star of Ethiopia - 1909
Grand Cordon of the Order of Solomon - 1930
Riband of the Three Military Orders Of Christ
Knight of the Order of the Most Holy Annunciation - 1928
Order of the Elephant - 1954
Order of the Gold Lion of the House of Nassau of Luxembourg - 1924
Collar of the Order of the Seraphim - 1954
Maha Chakri - 1954
Order of Suvorov 1st class of USSR - 1959
Collar of the Order of Muhammad Ali of Egypt - 1930
Grand Cross of the Legion d'Honneur - 1924
Chief Commander of the Legion of Merit - 1945
Grand Collar of the Order of Pahlavi - 1964
Collar of the Order of the Aztec Eagle - 1954
Royal Victorian Chain (RVC) - 1930
Knight of the Order of the Garter (KG) - 1954
Knight Grand Cross of the Order of the Bath (GCB) - 1924
Knight Grand Cross of the Order of St Michael and St George (GCMG) - 1917
Knight Grand Cross of the Royal Victorian Order (GCVO) - 1924
Collar of the Order of the Chrysanthemum-1956 (Grand Cordon-1930)
Order of St James of the Sword of Portugal
Order of the Liberator San Martin of Argentina
Order of the Nile of Egypt
Order of Pius IX of the Vatican - 1970
Order of Idris I of Libya
Order of Independence of Tunisia
Order of Hussein ibn Ali of the Jordan
Order of Muhammad of Morocco
Chain of Honor of the Sudan
Grand Order of the Hashemites of Iraq
Order of the Crown of Italy - 1917
Order of Leopold (Belgium) - 1924
Order of Saints Maurice and Lazarus - 1924
Order of the Tower and Sword of Portugal - 1925
Knight Grand Cross of the Order of William - 1954
Knight Grand Cross of the Order of the Netherlands Lion - 1930
Order of the White Eagle of Poland - 1930
Collar of the Order of St Olav of Norway - 1949
Collar of the Order of Charles III of Spain
Collar of the Order of the White Rose of Finland
Grand Cross of the National Order of Vietnam- 1958
Order of Truth of Burma - 1958
Collar of the Order of the Southern Cross of Brazil - 1958
Collar of the Order of the Leopard of Zaire
Order of the Lion of Senegal
Order of the Lion of Malawi
Order of Valor of Cameroon
Order of the Sun of Peru
Collar of the Order of the Bust of the Liberator Simon Bolivar of Venezuela
Order of the Condor of the Andes of Bolivia
Special Grade of the Order of the Propitious Clouds of China

ምንጭ፡ http://www.redicecreations.com/article.php?id=9711

ከነዚህ ውስጥ ናይትስ ኦፍ ጋርተር የአውሮፓ ነገስታት ማህበርን እንየው፡፡ የአውሮፓ ነገስታት የዘር ሃረግ የሚገኘው ከፍሎረንስ ነገስታት ሲሆም የብላክ ኖቢሊቲ ወይም ጥቁር መሳፍንት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይበልጥ ለመረዳት የሚከተለው፡ “ጥቁር መሳፍነት” – "Black Nobility" ያንብቡ፡፡ እኚህ ባላባቶች ከኢሉሚናቲ በስተጃርባ እንዳሉበትና አሁንም በዘመናዊው ዓለም ፖለቲካም ንቁ ተሳታፊ ለመሆናቸው ጥያቄ የለውም፡፡
ከስር ሃይለስላሴ ለናይት ኦፍ ጋርተር አባል ሲሆኑ እንደ ማህበሩ ልማድ መሰረት የተደረገላቸውን ስነ ስርዓት ያሳያል፡፡
ከስር የአፄው የናይት ኦፍ ሴራፊም አርማ ይታያል፡
ሆኖም ግን ይህም በእርግጠኝነት የኢሉሚናቲዎች ጭፍራ ሆኑ ማለት አይደለም፡፡ አፄ ኃይለስላሌ የዚህ ማህበር አባል መሆናቸው የሚስጥር ማህበራቱን አሰራር ለማያውቁ ሊያስገርም ይችላል፡፡ በእነዚህ ሜሶናዊ ማህነራት በዝቅተኛ መአርግ አባል የሚደረጉት እጩዎች መጨረሻ መአርጎች ላይ ሲደርሱ ወይም ኢሉሚናቲ አስኪሆኑ ድረስ የማህበሩ አባል መሆኑ ትክክለኛ ሚስጥር አይገባቸውም፡፡ እናም በመልካም ስማቸው አባል እንዲሆኑ ሲጠሩ እንደክብር ከመቁጠር ውጪ ስለሴጣናዊው ሚስጥር የሚያስቡት ነገር አይኖርም፡፡


ድህረ-ነገስታት ኢትዮጵያ እና ኢሉሚናቲ
ነገስታቱ ከሃይማኖት ጋር ባላቸው ቁርኝት ከሚስጥር ማህበራቱ ጋር ቁርኝት ሊኖራቸው ይችላል የሚለውን በቀላሉ ላይሆን እንደሚችልም አይተናል፡፡ አሁን ደሞ ከነገስታቱ በኋላ ኢትዮጵያን የሚመሩቱ በሚያንፀባርቁት ርእዮተ ዓለም እና የሚጠቀሙበትን ምልክቶች ተጠቅመን የኢሉሚናቲን ስውር እጆች ማግኘት እንችላለን፡፡ እዚህ ጋርም ግን ክፍተት አለ፡፡ የምልክቶች መተሳሰር የኢሉሚናቲ ምንንነትን ከማሳየት ውጪ በሁለት ነገሮች ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡
አንድ ምልክቶቹ ከህዝባዊ ንቅናቄ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንደመሆናቸው ከሚስጥር ውጪ ሌላ ህዝባዊ ትርጉምም አላቸው፣ እናም በዚህ ህዝባዊ ትርጉማቸው ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፤ 
ሁለት ድህረ ነገስታቱ የመጡት መሪዎችም ቢሆኑ ብሄራዊ ፖሊሲዎች የሚያስቀድሙ እንደመሆናቸው የኢሉሚናቲ ምልክት ቢገኝባቸው በውስጣቸው ምልክቶቹን እንዲጠቀሙ ያደረጉ አካላት መኖራቸውን ብቻ ያሳያል እንጂ ሙሉ ለሙሉ የኢሉሚናቲ ተከታዮች መሆናቸውን አያሳይም፡፡
ፒራሚዱ እና ዓይኑ ምልክት የሚለውን ፅሁፍ ካነበብነው ከታች የምናየውን ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን አንድ ዓይና ምልክት በኢትዮጵያ ማግኘት በውነቱም ያስደንቃል፡፡ ይህኛው ለየት የሚያደርገው አንፀባራቂው የዐዓይን ምልክት ከኢትዮጵያም ሆነ ዓለም አቀፋዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ጋር የማይገናኝ መሆኑ ነው፡፡


ከስር ደሞ አሁንም አንድ ዓይናማ የኢትዮጵያ ካርታ ምስል ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህን ምስል ይዘው የወጡት ወታደሮች ከምሁራኑ ፓርቲ ይልቅ ወታደራዊው ደርጉ የበላይ ሁኖ የወጣበትና ሰራዊቱ ለደርጉ ያለውን ድጋፍ ያሳያበት ሰልፍ ግዜ የታየ ካርታ ነበር፡፡ ይህኛው ልክ የአሜሪካ ዶላር ላይ እንዳለው አይን እና ፒራሚድ ቅርፅ ነው፡

በተጨማሪም የችቦው ጥያቄ ነው፡፡ ይህም በሕብረተሰባውያን ንቅናቄ ችቦው ለህዝቡ እንደተነገረው ከሆነ የነፃነት ብርሃን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በሚስጥር ማህበራቱ ግን ሌላ ትርጉም አለው፡
አልበርት ፓይክ ያአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ሃውልት የተሰራለት 33ኛ መዓርግ የደረሰው ፍሪሜሶን (Morals and Dogma, 321) በሚለው መፅሃፉ እንደሚከተለው ይላል፡- ሉሲፈር፣ ብርሃን [ችቦ] ያዢው! ለጭለማ መንፈስ ይህን ስም መስጠት እንግዳ ነው፡፡ ሉሲፈር፣ የንጋት ልጅ! እሱ ነው ብርሃን የሚይዘው…



እርግጥ ነው ሴጣን በትእቢቱ ምክንያት ከገነት ከመባረሩ በፊት የንጋት ልጅ፣ ብርሃን ያዥ ይባል ነበር፣ ይህ መዓርጉ መገፈፉ ግን ለሚስጥር ማህበራቱ አልተዋጠላቸውም፣ አሁንም ድረስ እውቀት ይሠጣል፣ ብርሃኑን ይዞ ነው ከገነት የወጣው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ይህ ሉሲፈራዊነት ይባላል፣ የዚህ ታሪክ የግሪክ አቻው ፕሮሚትየስ ይባላል፣ እናም ፕሮሚትየስን ሲያገኑ ከሰማችሁ ሉሲፈርንም እያሰቡ መሆናቸውን እወቁ፡፡ ፕሮሚቲየስ በግሪክ አፈታሪክ በማስዋል ብቃቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም የአማልክቱ ፈጣሪ/አለቃ ዜኡስን እሳት በመስረቅ ለሰው ልጆች በመስጠት ክዷል፡፡ በዚህም ምክንያት ለሰው ልጆች የስልጣኔ ጥበብን፡- ፅሁፍ፣ ሂሳብ፣ ግብርና፣ ህክምና እና ሌሎች ሳይንሶችን በማስተማር ይመሰገናል፡፡ ለጥፋቱም ከአለት ጋር ታስሮ ታላቅ ንስር በየቀኑ ጉበቱን እንዲበላውና መልሶ ሲያድግ ዳግም እንዲበላው በማድረግ ቀጥቶታል፡፡



“ፕሮሚቲየስ [አርቆ ማሰብ ማለት ነው] ሞኝ አልነበረም፣ ለምንድነው ዙኡስ ላይ ያመፀው? (ሁሉንም የሚያየውንና የሚያውቀውን) ዜኡስን በሃሰት መስዋእት ሊያታልለው ሞከረ፡፡ ከዚህ በላይ ሞኝ መሆን ይቻላል? በተጨማሪም ፕሮሚቲየስ እሳት ከዜኡስ ሰርቆ ምድር ላይ ላሉ ሟቾች ለኋላ ቀሮቹ ለሰዎች ሰጣቸው፡፡ ዜኡስ ፕሮሚቲየስን ለብቻው አልቀጣውም በዚህ አመፀኛ አምላክ ድፍረት ምክንያት ዜኡስ ዓለሙን በሞላ ቀጣ፡፡” ስቴዋርት
በሉሲፈር እና በፕሮሚትየስ ያለው ትስስር ግልፅ ነው፡ ፕሮሚትየስ ሲሳልም ሆነ ሃውልቱ ሲቀረፅ ችቦ ይዞ ነው፡

በዚህ ዙርያ የበለጠ ለማወቅ፡ የሮክፌለር ማእከል – Rockefeller Center ይመልከቱ፡፡
ይችቦ ምልክቶች በሃገራችን:
ሌሎችም የህብረተሰባውያን ምልክቶች እንዲሁ በቀላሉ ከሚስጥር ማህበራቱ ጋር ባላቸው ሚስጥራዊ ፍቺ ማስተሳሰር ይቻላል፡ ለምሳሌ የማጭዱ እና መዶሻው ምልክትን ብናይ መዶሻው ዜኡስ የተባለው የጥንታውያን ግሪክ አምላክ የሚይዘው ሲሆን ማጭዱ ደሞ በሌሎች ጥንታዊ አውሮፓውያን ባእድ እምነት የሞት መልአክ የሚይዘው ይሆናል፡፡
እንዲህ ሕብረተሰባውያን እና ባእድ ልማድ ምልክቶች በቀላሉ መገጣጠማቸው ምክንያቱ ቀድሞውኑ የሕብረተሰባውያ ንድፈ ሃሳብ አመንጪዎች የሚስጥር ማህበራቱ በመሆናቸው ነው፡፡ የህብረተሰባውያኑ መመርያ መፅሃፍ የሆነችው ኮሚውኒስ ማኒፌስቶ የያዘችው አስር ትእዛዛት ከፃፉት ማርክስ እና ኢንግልስ ከመወለዳቸው ከሺህ ዓመታት በፊት የነበሩ የተወገዙ የሚስጥር እምነቶች ዶግማዎች ነበሩ፡፡
እዚህ በተጨማሪ በመጨረሻ ላይ ልናያት የምንችለው የኮኮብ ምልክትን በተመለከተ ይሆናል፡፡ ባለ አምስት ጫፉ ኮከብ ወይም ፔንታግራም ከጥንት ከፓይታጎረስ የሚስጥር ማህበር ጀምሮ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ሚስጥራዊ ምልክት ነበር ሆኖም ግን ከአብዮታውያኑ ንቅናቄ በኋላ ሁለት ትርጉም ይዞ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡



በሚስጥራዊ አስተምህሮ ፊቺው እንደሚከተለው ነው፡ አምስቱም ጫፎች የየራሳቸው ፍቺ አላቸው ወደላይ ያቀናው አንዱ ጫፍ መንፈሳዊውን ይወክላል የተቀሩት አራቱ ደግሞ እሳት፣ ምድር፣ አየር እና ውሃን ይወክላሉ፡፡
በሚስጥር ዶግማ እያንዳንዱ ሰው ኮከብ ነው በሚለው የትእቢት አስተምህሮ (ይህ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ የሚለውን የእባቡን ምክር ተከትሎ የመጣ ነውና) በዚህ ደግሞ ሰውን በአምስቱ ጫፎች ሚዛን ጠብቀው ይስላሉ፡፡
ወደሃረጋችን ስንመጣ እንደማንኛውም የዓለም ህዝቦች ባለ አምስት ጫፉ ኮከብን በተለያየ መልኩ ድህረ-ነገስታት ኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተጠቅመውበታል፣ አሁንም ይጠቀሙበታል፡፡ ከስር ኮከብ ያለው ደርግ ፓርቲ ባጅ ይታያል፡
ከስር ደግሞ በደርግ ግዜ የነበረ ሃውልት ክብ ውስጥ የገባች ፕንታግራም እና ችቦ ያሳያል፡
አሁን የኢትዮጵያ አርማ የሆነውና ባንዲራው መሃል ላይ ያለው ኮከብም ልክ በወታደራዊው ደርግ ግዜ እንደታየው አንድ አይና ምልክት ወጣ ያለ ነው፡፡ ይህም ኮከቡ በተጠላለፉ ዘንጎች የተሰራ መሆኑ ነው ዘንጎቹ ሲጠላለፉ ለየት ያለ ትርጉም ስለሚሰጡ ነው፡፡ እንዲሁም የሚያንፀባርቅ መሆኑ ከንጋት ብርሀን ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡



 የሆነ ሁኖ ግን በዚህ ዘመናዊ አለም ላይ ባለው ሰፊ የመወራረስ ልማድ መሰረት ባእድ ምልክቶች እና ዘመናዊ የህዝባዊ ንቅናቄዎች ምልክቶችን ይወራረሳሉ፡፡ ስለዚህም ሁሌም ቢሆን ትርጓሜ በሁለት መስመር ሊሄድ ይችላል፡፡ ምልክቱ ልክ ህገ መንግስቱ ላይ እንደሚለው ከሆነ ግን ልዩነትንና አንድነትን የሚያመላክት ጨረሩ ደሞ ብልፅግናን ሰመያዊው ሰሃን ሰላምን ይወክላል፡፡
መደምደምያ
እስከአሁን አንዲትም ቀጥተኛ ማስረጃ አላቀረብኩም፡፡ ቀጥተኛ ሊሆን የሚችለው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሜሶናዊ ማህበራት አባል መሆን ነው ግን ይህም ቢሆን ማህበራቱን የተቀላቀለ ሁላ ሚስጥራቱን ሁሉ አውቆ ተስማምቶበት አይደለምና ምንም አለማለት ሊሆን ይችላል፡፡ በግሌ የምረዳውም በዚህ መልኩ ነው፡፡
ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው ምልክቶች ያሉበትን ስናይ ደሞ ሃገሪቱ የዓለም አቀፋውያንን ፖሊሲ የማታራምድ መሆኗ ከበስተጀርባ መጠነኛ ተፅእኖ ያለው ሰው ስራ ነው ሊያስብል ይችላል ምክንያቱም ዋና መሪዎቹ ኢሉሚናቲ ቢሆኑ ኖሮ በኢትዮጵያ ብዙ ብሔራዊነት የሚንፀባረቅበት ፖሊሲ አይራመድም ነበር፡፡ ለምሳሌ ያክል፡ የዓለም ፍርድ ቤት እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አለመሆናችን፣ በዙርያችን እና በአህጉራችን ያሉ ሜሶናዊ ፖለቲከኞች አንድ ገንዘብ፣ ነፃ ኢኮኖሚ ቀጠና ይኑረን እያሉ ሲወተውቱን አለመተግበራችን፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሞኖፖል የሚሰጡ ስትራቴጅያዊ ዘርፍች ማጠራችን ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ስለዚህም ኢሉሚናቲ ኢትዮጵያ ውስጥ በትንሹ ምልክቶቹን ቢያሳይም እንደሌሎች ሃገሮች ግን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮናል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ባለኝ ውሱን መረጃ የደረስኩበት ነው ከዚህ የተሻለ መረጃ ያለኝ አለ የሚል ካለ ለመማር ዝግጁ ነን፡

Tuesday, November 19, 2013

አርቲስት አቦነሽ አድነው፡- ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት ክፍል -፩-

በዲ/ን ኒቆዲሞስ ዕርቅ ይሁን  ~nikodimos.wise7@gmail.com

ከሰሞኑን ለረጅም ዓመታት በዘፋኝነት ምናውቃት ተወዳጇ አርቲስት አቦነሽ አድነው ከዘፋኝነት ዓለም ተፋትቻለሁ ስትል ‹‹ክብሬ ነህ!›› የሚል የመዝሙር አልበም ለክርስቲያኑ ዓለም በማበርከት ወደዘማርያኑ ጎራ ተቀላቅላለች፡፡ ይህን ‹‹ክብሬ ነህ!›› በሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኘውን ፍቅርን፣ ሕይወትንና ተስፋን ያወጀችበትን የአርቲስቷን መዝሙሮች ለማድመጥ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ አርቲስት አቦነሽ ከዚህ በፊት ‹‹በባላገሩ›› አልበሟ ጥልቅ የሆነ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ ታላቅ ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል በማድነቅ ማቀንቀኗን ብዙዎቻችን እናስታውሳለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ እንዲሁም አርቲስቷ በእምነቷ የሃይማኖት ትምህርት፣ መንፈሳዊ የአምልኮ ሥርዓትና ትውፊት እየተደመመች ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሄደሽ ወንጌል ተማሪ›› ይለኛል በማለት ያዜመችው ‹‹ባላገሩ›› የሚለው ተወዳጅ ዜማዋ በአርቲስቷ ልብ ውስጥ ቀድሞውኑ ለዓመታት ሲንቀለቀል የነበረ አንዳንች የመንፈሳዊ ሕይወት ናፍቆትና ቅናአት እንደነበራት ያሳየ ነው ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ይህ የአርቲስቷ የልብ ናፍቆትና መንፈሳዊ ቅናአት ዛሬ ሙሉ በሙሉ ዕውን ሆኖአል እያለች ያለ ይመስላል አርቲስት አቦነሽ አድነው፡፡ ይህ የአቦነሽ ውሳኔና ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪዎቹ ጎራ የመቀላቀል አጋጣሚ ምናልባትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን የቅርብ ታሪክ ብዙም ያልተለመደና እንግዳ ነገር ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ብዙም በአቀንቃኝነቷ የማናውቃት የቀድሞዋ ዘፋኝ ዘማሪት ዘርፌ ከበደ ልትጠቀስ ትችል ይሆናል፡፡
ከዚህ ውጪ ሙሉ በሙሉ ከዘፈን ዓለም ወደ መዝሙር ዓለም ፊታቸውን የመለሱ አቀንቃኞቻችንን እንጥቅስ ቢባል የፕሮቴስታንቱ ዓለም አንጋፋ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን በመማረክ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ይመስለኛል፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በ1970ዎቹ፣ 80ዎቹ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ከነገሡትና እስካሁንም ድረስ ትልቅ ዝና፣ ስምና ተወዳጅነት ካላቸው ድምፃውያን መካከል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ሙሉቀን መለሰና ሒሩት በቀለ የፕሮቴስታንቱን ዓለም የተቀላቀሉ የመቼም ጊዜም ተወዳጅ አርቲስቶቻችን ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ዘመን ታሪክ በእጄ ላይ ባለው መረጃ መሠረት ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ታዋቂና አንጋፋ አርቲስት ወደ ዘማሪነት ጎራ ስትቀላቀል አርቲስት አቦነሽ አድነው የመጀመሪያዋ ትመስለኛለች፡፡ ወደ አርቲስት አቦነሽ ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት ስለተቀላቀለችባቸው የመዝሙሮቿ መልዕክትና አጭር ዳሰሳ ከማለፌ በፊት ግን ዘፈንና ዘፋኝነት አስመልክቶ ያሉትን የተሳሳቱ አመላካከቶችና ትርጓሜዎች ለማጥራት ይመቸን ዘንድ ጥቂት ቁም ነገሮችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
ዘፈንና ዘፋኝነትን በመንፈሳዊው ዓለም እንዴት ይታያሉ
 ዘፈን ወይም ዘፋኝነት እስካሁንም ድረስ በበርካታ ክርስቲያኖች መካከል የመለያየትና የክርክር ርእስ ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድም ዘፈን ወይም ዘፋኝነት እንደ ትልቅ ኃጢአት ተቆጥሮ የተረገመበትንና የተወገዘበትን በርካታ አጋጣሚዎችን ታዝበናል፤ አልፎ አልፎ እንደምናስተውለውም አሁንም ድረስ ውግዘቱና እርግማኑ ያቆመ አይመስልም፡፡ እነዚሁ ዘፈንና ዘፋኝነትን አጥብቀው የሚጠሉና የሚኮንኑ ወገኖች ለዚህ አቋማቸው እንደ መነሻ አድርገው የሚወስዱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን የገላትያ ፭፣፳፩ መልዕክቱን ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹የሥጋ ፍሬም የተገለጸ ነው፣ እነርሱም መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት … አስቀድሜ እንዳልኩ እነዚህን የሚያደርጉ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡›› በዚህ ጥቅስ ላይ በመመርኰዝ ‹‹ዘፈን የተወገዘ ነገር ነው፣ ዘፋኞችም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ዕድል ፈንታ የላቸውም፡፡›› በማለት ብዙዎች ክርስቲያኖች ባሕላዊ ጨዋታና ማንኛውም ለእግዚአብሔር ክብር ከሚቀርብ መዝሙር ውጭ የሆነ ሙዚቃ ሁሉ ኃጢአት ነው የሚል አቋም ሲያራምዱ ይሰማል፡፡
በዚህ ዘፈንና ዘፋኝነትን በተመለከተ በሚነሡ የክርክር ሐሳቦች ላይ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ን አባትና የሥነ መለኮት ምሁር የሆኑት ዶ/ር አባ ዳንኤል ‹‹ዘፈን ኃጢአት ነውን?›› በሚል ርእስ ባስነበቡት አጭር መጣጥፋቸው ያነሷቸውን ሐሳቦች እዚህ ላይ ደግሜ ማንሳት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዘፈንና ዘፋኝነት ሲያወግዝ ስለየትኛው ዓይነት ዘፈንና ዘፋኝነት እያወራ እንዳለ ከመናገራችን በፊት ይላሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል፡- ‹‹ዘፈን በምንልበት ጊዜ በአእምሮአችን የሚመጣው ምንድን ነው? በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚቀርቡት ድምፃውያንና የሚያጅባቸው የተወዛዋዦች ቡድን እንዲሁም የሚያጅባቸው የሙዚቃ መሳሪያ ነውን? ወይስ ወደ ሲኦል የሚወስድ አስፈሪ ኃጢአት ነው? በፊታችን የሚደቀነው … የዚህስ ምክንያቱ ምን ይሆን በማለት ይጠይቃሉ፡፡››
‹‹ሙዚቃ የነፍስ ቋንቋ፣ የፈጣሪ ልዩ ጸጋ፣ የሰው ልጅ ፍቅርን፣ ውበትን፣ ጥበብን የሚገልጽበት ረቂቅ ቋንቋ፣ ጣፋጭ ዜማ ናት …፡፡›› ተብላ የተበየነችውን ሙዚቃን ሐዋርያው ያወገዘበት ትክክለኛ ምክንያቱ ምን ይሆን? በእርግጥስ ቅዱስ ጳውሎስ የተቃወመው ከላይ የገለጽነውን ዓይነት ሙዚቃ ይሆን? እሱን ‹‹ከመግደል፣ ከስካርና ከቅናት፣ ከመናፍቅነትና ከምቀኝነት›› ጋር እንዴት ሊደምረው ይችላል?! ወደ ትክክለኛው ምላሽና ብያኔ ለመድረስ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶችም ሆኑ ሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በመጀመሪያ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ስለሆነ ‹‹ዘፋኝነት›› በሚል ቃል የተተረጐመው የትኛው የግሪክ ቃል መሆኑን በጥንቃቄና በሚገባ መርምሮ ማየት ያስፈልጋል ይላሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ ቋንቋ ‹‹ኮማይ›› ብሎ ያስቀመጠውም ቃል የአማርኛ መጽሐፈ ቅዱስ (የ፲፱፻፶፬ እና የ፲፱፻፸፪ ዓ.ም. ትርጉም) በዘፋኝነት ይተረጉመዋል፡፡ እርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ በሚያወግዘው ድርጊት ውስጥ ዘፈንና ሙዚቃ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ‹‹ኮማይ›› የሚለው ቃል ከላይ በተጠቀሰው ዘፈን የሚፈታ አይደለም፡፡ ‹‹ኮማይ›› ከልቅ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር የሚገናኝ ትርጉም አለው፡፡ ሰዎች ለጣዖት አምልኮ እየበሉና እየጠጡ የሚፈፅሙትን ሕገ ወጥ የዝሙት ኃጢአትን ያመለክታል፡፡ ይህም በሮማውያንና በግሪካውያን ዘንድ ይፈፀም እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ይህንን ከዘፈን ጋር ተያይዞ የሚፈጸመውን ልቅ ርኩሰት የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም›› ያለበትም ምክንያት አሁን መረዳት እንችላለን፡፡›
ለዚህ ተጨማሪ ማረጋገጫ ከፈለግን የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን መመልከት እንችላለን፡፡ እንግሊዝኛው “ኮማይ” የሚለውን ቃል ‹‹Orgy›› ብሎ ይፈታዋል፡፡ በአንጻሩ በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚቀርበው ዘፈን ‹‹Song›› የሚባል ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻም በአዎንታዊ ትርጉሙ በዘፈን ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ውበትን፣ ፍቅርን፣ መልካም ነገሮችን ማድነቅ እንደምንችል እናውቃለን፡፡ ያን ደግሞ እግዚአብሔር የሚቃወመው አይመስለኝም፡፡ ስለ ወንድና ሴት ፍቅር መዝፈን ኃጢአት ከሆነ ‹‹መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን›› የተባለውን መጽሐፍ ምን ልንለው ነው?! እሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ብንተረጉመው በቀጥታም ሆነ በተምሳሌነት የወንድና የሴት ፍቅርን ይገልጻል፡፡
እንግዲህ አስቀድመን ከመፍረዳችን በፊት ምን ዓይነት ዘፈን ብለን መለየት ያስፈልገናል፡፡ ወደ ኃጢአት ይመራል ወይስ ትምህርታዊ መልእክት አለው? ብለን መለየትም ያስፈልጋል፡፡ በ፻፲፰፸፱ ዓ.ም የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ ፭፣፳፩ ላይ ‹‹ዘፋኝነት›› ተብሎ የተተረጐመውን ቃል ‹‹ማሶልሶል›› በሚል ቃል ነው የሚተረጉመው፡፡ ሊፈጠር ከሚችለው የምሥጢር መዛባትና የትርጉም አሻሚነት የሚያድን ቃል ይሆን? ወይስ ‹‹መስከር›› የሚለው ቃል ከሁሉም ይሻል ይሆን፡፡ ምክንያቱም የግሪኩ ቃል ቅጥ ማጣትንና መስከርን ይገልጻልና፡፡ በመሠረቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የግዕዙ አዲስ ኪዳን ገላትያ ምዕራፍ ፭ ላይ ዘፋኝነትን ‹‹ስክረት›› እንጂ ‹‹ዘፈን›› ብሎ አይደለም የሚተረጉመው፡፡
የቃላቱን ትርጉም ለማመዛዘን ይረዳን ዘንድ እስቲ የተለያዩ መዝገበ ቃላት ስለ ዘፈን የሰጡትን ትርጓሜዎች ወይም ፍቺዎች እንመልከት፡፡ ስለ ዘፈን የደስታ ተ/ወልድ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፡- ዘፈነ፡- ‹‹አቀነቀነ፣ አወረደ፣ ግጥም ገጠመ፣ አዜመ፣ አንጐራጐረ፣ ዘለለ፣ ተረገረገ›› በማለት ሲፈታው የአማርኛ የመጽሐፍ ቅድስ መዝገበ ቃላት ደግሞ ዘፈንን እንዲህ ይተረጉመዋል፡-
‹‹በቅኔና በግጥም ከልዩ ልዩ መሣሪያ ጋር እየተቀነባበረ የሚቀርብ የደስታ ምልክት በልደት ቀን (ኢዮብ ፳፩፣፲፩-፲፪፣ ማቴ. ፲፬፣፮) በሠርግ ቀን (ኤር. ፴፩፣፬ ማቴ.፲፩፣፲፯) በድል በዓል ቀን (ዘጸ. ፳፣፳፩፣ ምሳ. ፲፩፣፴፬፣ ፩ሳሙ. ፲፰፣፮) በመንፈሳዊ በዓል ቀን (፪ሳሙ. ፮፣፲፬)፡፡ ከዚህም ሌላ በልዩ ልዩ የደስታ ቀን ይዘፈናል (ሉቃ. ፲፭፣፳፭)፡፡ በእስራኤል የአምልኮት ሥርዓት ዘፈን (ማኅሌት) ትልቅ ቦታ ይይዝ ነበር፡፡ (መዝ. ፻፵፱፣፫/፻፶፣፬)፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባዕድ አምልኮትንና ዝሙትን የሚያስከትል ዘፈን አልተፈቀደም (ዘዳ. ፴፪፣፮-፲፱፣ ማር. ፮፣፳፩-፳፪)፡፡ እዚሁ ላይ ሐዋርያት ዘፈን የማይገባ መሆኑን ተናግረዋል ይላል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ምን ዓይነት ዘፈን እንደተቃወሙ አልገለጹም፡፡ አብዛኛዎቹ ጥቅሶች ተቀባይነት ስላለው ዘፈን እንደገለጹ ግን እናስተውል፡፡
ይህ በዘፈንና በዘፋኝነት ዙሪያ ያለው የትርጉም መዛባት የፈጠረውን መደናገርና የትርጓሜ ስህተት ላይ ይህን ያህል ለማየት ከሞከርን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለን አንድ ታሪክ ብቻ በማንሳት ሐሳቤን ለማጠናከር ልሞክር፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ታሪክ እንደሚነግረን ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ፣ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና ሐዋርያቱ ዘፍንና ባህላዊ ጨዋታዎች ወደሚስተናገድበት የአይሁድ ሠርግ ላይ ለመታደም እንደሄዱ ወንጌላውያኑ ጽፈውልናል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው በአይሁድ ባሕል ውስጥ ተወልዶና አድጎ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚያ ባሕል የተቃወማቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የተቀበላቸውም ነበሩ፡፡ በአይሁድ ሠርግ ላይ ባሕላዊ ውዝዋዜ እንደነበረ ይታወቃል፤ ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን ከሠርግ ጋር ስለሚገናኝ ሙዚቃና ጨዋታ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሠርግ ላይ የተገኘው ኢየሱስ በሠርጉ ላይ የነበረውን ዘፈንና ባህላዊ ጨዋታ ተቃውሟል የሚል ንባብ ግን የለም፡፡
በመሠረቱ ይላሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል ‹‹ዘፈን ኃጢአትን ነውን›› በሚለው ጽሑፋቸው በመሠረቱ፡- ‹‹ባሕል የሰው ልጅን ከእንስሳት የሚለይ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ ማንኛውም ባሕል በክርስቶስ ወንጌል ትምህርት የሚገመገምና የሚፈተን ሲሆን አስፈላጊነቱን ማመን ግን የግድ ይሆናል፡፡ ጌታችንም በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ሲታደም የሠርግ ዘፈን አልነበረም ለማለት አዳጋች ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልን ስናነብ ስለአይሁድ ባሕል ብዙ ነገር እናገኛለን፡፡ ብሉይና አዲስ ኪዳንን ለመረዳትም ይህንኑ የአይሁድ ባሕል ማጥናት ሊጠቅመን ይችላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር እራሱ በአንድ ዘመን በነበረ ባሕል፣ ቋንቋና ሥልጣኔ አማካኝነት መናገሩን አንዘንጋ፡፡›› በማለት ይደመድማሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ እንደ የጉራጌኛ፣ የኦሮምኛ፣ የትግርኛ፣ የአማርኛ፣ የወላይትኛ ወዘተ… ባሕላዊ ጨዋታዎችን መመልከትና መሳተፍ ክፋቱ ምንድን ነው፣ የተፈጥሮን ውበትን፣ ታሪክን፣ ፍቅርን፣ ጥበብን፣ ውበትን፣ እውነትን፣ ፍትሕን፣ ነጻነትን፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያወድሱ ዜማዎችን ማቀንቀንም ሆነ ማድመጥ ችግሩ ምኑ ላይ ነው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ በዚያ ዘፈን፣ ባህላዊ ጨዋታዎችና ውዝዋዜ ከአሥርቱ ትእዛዛት የትኛውን እናፈርሳለን? ከየትኛውስ በደል ሊመደብ ይችላል? ከመግደል ወይስ ከመስረቅ በሐሰት ከመመስከር ወይም ከማመንዘር?

ዜማና መዝሙር በኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም ገና ስለ ሙዚቃና የዜማ ምሥጢር ማወቅና መነጋገር ከመጀመሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊትና ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ዜማ ድርሰት፣ ቀመርና ምልክቶች ምን መሆኑን ሳይደርስበት በፊት በታላቁ ሊቅና ማሕሌታይ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት የሰማያዊ ዜማ ባለቤት ለመሆን የበቃች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህን እውነታ በኖርዌይ ትሮንድሄም እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው በ፲፮ኛው ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረንስ ላይ ‹‹The Significance of St. Yared’s Music in the Age of Globalization›› በሚል ርእስ ጥናታዊ ወረቀት ያቀረበው በአሜሪካ ኮሎምቢያ የኦሃዮ ዩኒቨርስቲ ምሁሩ ሊቀ ዲያቆን ክፍሌ አሰፋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዜማ ያለውን ረቂቅነትንና ልዩ ውበቱን ሲገልጽ፡-
‹‹የቅዱስ ያሬድ/የኢትዮጵያ ቤ/ን ዜማ እጅግ ጥንታዊ፣ ጥልቅ፣ ከመንፈስና ከነፍስ በሚመነጭ ፍሰትና ልዩ ጥበብ የተፈጥሮን የለሆሳስ ድምፅና የፍቅርን ልዩና ረቂቅ ዜማ የሚያስቃኝ ሰማያዊና ሕያው መንፈሳዊ ዜማ ነው፡፡›› በተጨማሪም ክፍሌ አሰፋ በዚሁ የጥናት ሥራው ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ጥንታዊ ዜማ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት (ከተፈጥሮ) ጋር በእጅጉ የጠበቀ ምሥጢርና ትስስር እንዳለው የሚከተለውን ሐሳብ ያክላል፡-
‹‹Ethiopian liturgical music is quite unique; those who listen carefully will recognize the haunting sounds of mother nature.›› ይህ ለሺሕ ዓመታት የዘለቀው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ዜማና የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥርዓት ዛሬ ዛሬ እየተበረዘ ነው የሚሉ ታዛቢዎችን በብዛት እያስተናገደ ነው፡፡
በተለይ በዘመናችን ወጣት ዘማሪያን እያወጧቸው ያሉ መዝሙሮች በአብዛኛው ምድራዊ ምኞቶችና ፍላጎቶች ላይ የሙጥኝ ያሉ፣ የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመስቀሉን ውለታና ፍቅር ኃላፊና ጠፊ በኾነ ምድራዊ ሀብትና ክብር የሚያነጻጽርና የሚለካ፣ በአብዛኛው ገበያ ተኮር የሆኑ፣ በእጅጉ ዓለማዊነት ያየለባቸው፣ ለጸሎትና ለተመስጦ እንዲሁም ልዩ ምሥጢር ላለው ሰማያዊና ዘላለማዊ ሕይወት መንፈስንና ነፍስን ወደወዲያኛው ዓለም ለማሻገር አቅም የሚያነሳቸው፣ ደካማና ልፍስፍስ ናቸው … የሚሉ ብርቱ ትችቶችን እያሰተናገዱ ይገኛል፡፡
ለዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ምሁራን ዘንድ ዘማሪዎቻችን ከቅዱስ ያሬድ ዜማ እየወጡ ነው፣ የመዝሙሮቻቸው ግጥሞችም መንፈሳዊ ምሥጢር የማይንጸባረቅባቸው፣ ግልብና የይድረስ የይድረስ እየሆኑ ናቸው የሚለው ትችት የተጋነነና እውነታውን የሳተ ነው የሚሉ አንዳንዶች የራሳቸውን የመከራከሪያ ሐሳብ እንዲህ ሲሉ ያቀርባሉ፡፡ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ዜማ፡- ልዩ፣ ሰማያዊና ረቂቅ ቢሆንም ከእርሱ ወዲያ በተለያዩ ጊዜያት የተነሡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የእርሱን ዜማ አመስጥረውና አራቀው እንደተጠበቡበትና በአዲስ የምስጋና ዜማና ሰማያዊ ቅኔ አምላካቸውን በመላእክት ሥርዓት እንዳመሰገኑት፣ እንዳወደሱትና እንዳመለኩት አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡
ለአብነትም ያህል ይላሉ እነዚሁ ተከራካሪዎች በቤተ ክርስቲያናችን የቅዳሴ ዜማ ታሪክ የደብረ ዓባይ፣ የሰደል ኩላ፣ የአዲስ አበባ ዜማ … ተብለው የሚጠሩ የቅዳሴ ዜማዎች መኖራቸውን እንደ መረጃ በመጥቀስ ከቅዱስ ያሬድ ዜማ ወጥታችኋል የሚለው መከራከሪያ ውኃ የሚያነሳ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት የኾነው የቅዱስ ያሬድ ዜማ በተለያዩ ዘመናት በተነሡ አባቶቻችን መሠረታዊ ይዘቱን ሣይለቅ መሻሻል ተደርጎበታል፡፡ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን የማሕሌት ስርዓት እንኳን እውቁ የ፲፱ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያዊው ምሁር አለቃ ገብረ ሃና ለልጃቸው ለተክሌ በመኖሪያ አካባቢያቸው ያሉ ሸንበቆና ደንገል በንፋስ አማካኝነት የሚያደርጉትን ውዝዋዜ በማየት ያስተማሩት የአቋቋም ሥርዓት ‹‹የተክሌ አቋቋም›› በሚል የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ይላሉ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የጎንደር አቋቋም፣ አስደማሚው የጎጃሙ አጫብርና ቆሜም የማሕሌት ሥርዓት ሌላው የምንኮራበት መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብታት ናቸው፡፡ ስለሆነም ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት ሳናፈነግጥ በቅዱስ ያሬድ ጥልቅና መንፈሳዊ ዜማ እየተመሰጥንና እየተደነቅን ዛሬም ወደፊትም ደግሞም ለዘላለም በአባታችን ቅዱስ ያሬድ መንፈስ አዲስ ዜማ፣ ልዩ የምስጋና ቅኔን ለአምላካችን እናመጣለን፣ እንሠዋለን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
እንደውም ይህ ዘመን ይላሉ እነዚሁ ተከራካሪዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርብ ታሪክ ዘመናት ውስጥ ‹‹የመዝሙር አብዮት›› የተከሰተበት ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነው ሲሉ የእውቁን የቅኔ መምህርና ሰባኪ ወንጌል መጋቢ ሐዲስ መምህር እሸቱ አለማየሁን አገላለጽ በመዋስ ይህ አዲስ ‹‹የዝማሬ አብዮት›› ብዙዎችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናኖች፣ ወጣቶችን እየማረከና አርቲስቶቻችንም ከዘፈን ዓለም ወደ ዘማሪነት ክብር እያፈለሰ ያለ የለውጥ ሂደት ነው ሲሉ በኩራት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ስለሆነም ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተከሰተው ‹‹አዲስ፣ ልዩ የምስጋና፣ የዝማሬ ቅኔ ማዕበል›› እንደ ዘርፌ ከበደ ያሉትንና አሁንም ደግሞ ታዋቂዋን አርቲስት አቦነሽ አድነውን ወደ ዘማርያኑ ጎራ እንዲቀላቀሉ ያስቻለ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሰማያዊ ቅኔ፣ ይህ ልዩ መንፈሳዊ ምስጋና ገና ብዙዎችን ወደ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይጠራል፣ ያፈልሳል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ምናልባት በዚህ የመዝሙሮቻችን ዜማና ግጥሞችና እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየተካሄዱ ላሉ ክርክሮችና ሙግቶች፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉ የዜማ ሊቃውንትና ምሁራን የጠራ አቋምና ግንዛቤ ይኖረን ዘንድ የሚያስችል ሙያዊ የሆነ ትንታኔ ሊሰጡበት ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ ግን የተነሣሁበትን ‹‹አርቲስት አቦነሽ አድነው ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት›› በሚል ርእስ የጀመርኩትን አዲሱን የአቦነሽ አድነውን መዝሙሮች አጭር ዳሰሳ በዛሬው ጽሑፌ ላካትተው አልቻልኩም፡፡ በቀጣይ ጽሑፌ አርቲስቷ በዝማሬዎቿ ያነሳቻቸውን መንፈሳዊ መልእክቶችና የግጥሞቹን ይዘት በተመለከተ የሚያትተውን መጣጥፌን በቀጣይ ሳምንት እንደምመለስበት ቃል በመግባት ልሰናበት፡፡

ሰናይ ሳምንት!!

Friday, November 15, 2013

እናቶቻችን ጥንታውያን ሃኪሞች ናቸው!!


 
    ወላድ ሴቶች በአብዛኛው ያውቁታል። ያውቁታል ብቻ ሳይሆን አበክረው ይጠቀሙታል። የሚጠቀሙት በቤተ ሙከራ ተመራምረውና ያለውን የንጥረ ነገር ይዘት ስለደረሱበት አይደለም። በልምድና ባገኙት የጥቅም አገልግሎት ነው። አልፎ አልፎ ከሚወጣው የሚተነፍግ ጠረንና መጠነኛ ምረት በስተቀር እህልነቱ እንከን አይወጣለትም። በሁሉም የሀገሪቱ ክልል ይገኛል። ወይና ደጋማ አየር ክልል በደንብ ይስማማዋል። ስሙ በሁሉም ዘንድ እንግዳ አይደለም። እንግዳነቱ የሚጠቀሙት በአብዛኛው እናቶች ብቻ መሆናቸው ነው። ለዚያው ከእንስትም ወላዶች ብቻ!! ይህ የእህል ዘር ማነው? አወቃችሁት? ወይስ ጠረጠራችሁት?

  እንግዲያውስ እኛው እንንገራችሁ። በሀገርኛው ስሙ «አብሽ» ይባላል። በፈረንጆቹ (Fenugreek) ነው። መነሻው ኢራቅ እንደሆነ ታሪክ ይነገራል። ከዚያም ወደዓለሙ ሁሉ ተስፋፋ። ሕንድ ደግሞ ከዓለም ሀገራት የአምራች መሪነቱን ይዛ ትገኛለች። ኢትዮጵያም ለዚህ ዘር ባእድ አይደለችም። ታዲያ ስለአብሽ ምን እንግዳ ነገር ተገኘና ነው ዛሬ ስሙ የተነሳው እንዳትሉ። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለአብሽ ጠቀሜታ በሰፊ ከሚያትት መጽሐፍ ላይ ያገኘነው መረጃ ስለእናቶቻችን ቀዳሚ የምርምር ባለሙያነት እንድናደንቅ አስገደደን። እናቶቻችንን ብቻ አድንቀን ዝም ከምንል አብሽን እናቶቻችን እንዲመርጡ ያደረጋቸውን የንጥረ ነገር ይዞታና ጥቅም ልናካፍላችሁና እናንተም አብሽን እንድትካፈሉ ጥቂት ለመጻፍ ወደድን። «አብሽ» እንዲህ ነው።

አብሽ /Fenugreek/የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው? ከብዙ በጥቂቱ ከታች የተዘረዘሩትን  ይሰጣል።

1/ የጡንቻ፤ የጣት፤ የቅልጥምና የመገጣጠሚያ አካባቢን ህመም ለመቀነስና ለማስታገስ ያገለግላል።
2/ ሊንፍኖድስ/በጉሮሮ፤ በብብትና በሆድ አካባቢ የሚገኝ የመከላከያ አቅምን የሚጠብቅ እጢ ሲሆን አብሽ ይህ ስራውን በተገቢው እንዲወጣ ያደርገዋል።

3/ ቁስልና ጥዝዛዜ ያለው ህመም በመቀነስ ብሎም ቶሎ እንዲድን በማድረግ ያግዛል።
4/  በስኳር ህመም ለሚሰቃዩ ሰዎች የኢንሱሊንን አቅም በማጎልበት፤ የጉሉኮስን ክምችት በመቀነስ ከፍተኛ ጥቅም አለው።

5/ በሆድ አካባቢ የስብ ክምችት እንዳይኖር ይከላከላል። ከመጠነኛ እንቅስቃሴ ጋር ስብ በማቅለጥም እገዛ ያደርጋል።
6/ የምግብ ፍላጎት ለቀነሰባቸው ሰዎች ፍላጎትን በመጨመር ካልተፈለገ ክሳትና የምግብ አለመስማማት ተመሳሳይ ችግሮች ይከላከላል።
7/ለሆድ ሕመም፤ ለጨጓራ አልሰርና ለቃር ከፍተኛ ማስታገሻ ነው።

8/ የልብ አርተሪ ስራውን በአግባቡ እንዲያካሂድ ያግዛል።ለደም ቅዳና ደም መልስ ዝውውር፤ ለኮሌስትሮል መጠን መስተካከል፤ለኩላሊትና በቫይታሚን እጥረት ለሚከሰት የቤሪቤሪ በሽታ ከፍተኛ የፈውስ ድጋፍ አለው።

9/ ለአፍ ቁስለት፤ ለንፋስ ተገንጣይ ቧንቧ ህመም፤ ለሳምባ፤ ለደረቅ ሳልና ትክትክ ፍቱን መድኃኒት ነው።
10/ ለቆዳ፤ ለራሰ በራነትና ለጸጉር መመናመን፤ ለካንሰር፤ ለጉበት ህመም መከላከል ጠቃሚ ንጥረ ነገር ይዟል።

11/ ለስንፈተ ወሲብና አቅም ማጣት፤ ለሴቶች የጡት ግት መጨመርና የወተት አወራረድ መጨመር ከፍተኛ ድርሻ አለው,።
12/ የአፍ፤ የጉሮሮና የውስጥ እርጥበትን በመቆጣጠር ያልተፈለገ ቆሻሻን በማስወገድ፤ እንደየመኪና ሞተር ግራሶ ለሰውነታችን የሚያገለግለውን ዝልግልግ ፈሳሽ /mucus/ በመቆጣጠርና በማስተካከል መጥፎ የአፍ ጠረን፤ ከሆድ የሚወጣ ትኩሳትና ሽታ፤ በመከላከል ከመጠን በላይ የተበላሸና የለገገ አክታ እንዳይኖረን በማድረግ በኩል አብሽን የሚወዳደረው የለም።

አብሽ ለምን ይህንን ሁሉ አቅም ለመያዝ ቻለ? የዘመኑ ሳይንስ እንዲህ ይላል።

አብሽ ስኳር የለሽ /Polysacchirides/ ንጥረ ነገር አለው። ይህ በራሱ  ክር መሳይ /Fiber/ ሟሚ ንጥረ ነገር ከፍተኛ ተሸካሚ አድርጎታል። saponons, hemicelluloses,macilege, tannin, pectin የተባሉ ለደም ዑደትና ለዘይት መጠን ልኬታ ጠቃሚ ንጥረ ነገርን በመያዙ ከአዝርዕት መካከል እጅግ ተመራጭ ያደርገዋል። ኢንሱሊንን በማምረት ረገድ አሚኖ አሲድ 4 ሀይድሮክሲአይዞሉሲን ይዟል። የፋይቶኬሚካል ክፍል የሆኑትን ንጥረ ነገሮች ማለትም  ኮሊን፤ ትራይጎኔሊን ዳዮስጄኒን፤  ያሞጄኒን፤ ጂቶጄኒን፤ ቲጎጄኒን የተባሉትን ንጥረ ነገሮችን/substance/አጣምሮ የያዘ ነው።
በሚኒራሎችም ረገድ አብሽ የያዛቸው ነገሮች  መዳብ፤ ፖታሺየም፤ ካልሲየም፤ ብረት፤ ሴሌኒየም፤ ዚንክ፤ ማንጋኒዝ፤ ማግኒዢየም፤ በመሳሰሉት በጣም ያዳበረ ነው።
በቫይታሚን ረገድም የተዋጣለት ነው። ታያሚን፤ ቫይታሚን ቢ 6፤ ፍሎሪክ አሲድ፤ ሪቦፍላቪን፤ ናያሲን፤ ቫይታሚን ኤ፤ ቫይታሚን ሲ፤ ቤታ ካሮቲን፤ ፎሌት/DFE/ የመሳሰሉት ይገኙበታል። በአሚኖ አሲድ ንጥረ ክፍሎች በጣም የዳበረ ሲሆን  ከካርቦ ሃይድሬት ምንጮች ውስጥም ሟሚ ከሆነው ጭረት/ ፋይበር /በስተቀር ከስታርች፤ ስኳር፤ ሱክሮስ፤ ግሉኮስ፤ ፍሩክቶስ፤ ላክቶስ፤ ማልቶስና ጋላክቶስ ፍጹም ነጻ መሆኑ ከሁሉም ተመራጭ ያደርገዋል። ፋቲ አሲድና ስብነት ካላቸው ውሁዶችና ንጥረ ነገሮች ነጻ ነው።
 
ከምዕራባውያኑ ጸሐፊያን  ጊዮርጊስ ፔትሮፓውሎስ ስለአብሽ ጥቅም በሰፊው አትቷል። ሕንዳዊው ዶ/ር ኩማር ፓቲ በ328 ገጽ  ባሰፈረውና ስለእጽዋት መድኃኒትነት በዘረዘረበት መጽሐፉ ላይ ስለአብሽ ጥቅምና ቅመማው  በደንብ ዘርዝሯል።
አብሽ በዱቄት መልክ፤ አንጥሮ ዘይት በማውጣት፤ በበቆልት፤ በፈሳሽ መልክ አዘጋጅቶ ለሻይ፤ ከሌላ ምግብ ጋር ቀላቅሎ በማዘጋጀት፤ መጠቀም ይቻላል። አወሳሰዱን በተመለከተ የቅርብ ሐኪምን ማማከር ይገባል።
በአሉታዊ ጎኑ ሲታይ ደግሞ በእርግዝና ላይ ያለች ሴት አብሽን አብዝታ እንድትጠቀም አይመከርም።
የአብሽን ጥቅም አውቀው በአገልግሎቱ የቆዩት እናቶቻችን ሳይማሩ የተማሩ አይደሉምን?
ለተጨማሪ መረጃ ቢመለከቱ ይጠቀማሉ።
1. Adamska M, Lutomski J. C-flavonoid glycosides in the seeds of Trigonella foenum graecum [in German]. Planta Med . 1971;20:224-229.
2. Gupta RK, Jain DC, Thakur RS. Minor steroidal sapogenins from fenugreek seeds, Trigonella foenum-graecum . J Nat Prod . 1986;49:1153.
3. Karawya MS, Wassel GM, Baghdadi HH, Ammar NM. Mucilagenous contents of certain Egyptian plants. Planta Med . 1980;38:73-78.
4. Valette G, Sauvaire Y, Baccou JC, Ribes G. Hypocholesterolaemic effect of fenugreek seeds in dogs. Atherosclerosis . 1984;50:105-111.
5. Singhal PC, Gupta RK, Joshi LD. Hypocholesterolemic effect of Trigonella foenum-graecum (METHI). Curr Sci . 1982:51:136.
6. Stark A, Madar Z. The effect of an ethanol extract derived from fenugreek ( Trigonella foenum traecum ) on bile acid absorption and cholesterol levels in rats. Br J Nutr . 1993:69:277-287.
7. Sauvaire Y, Ribes G, Baccou JC, Loubatieeres-Mariani MM. Implication of steroid saponins and sapogenins in the hypocholesterolemic effect of fenugreek. Lipids . 1991;26:191-197.
8. Yadav UC, Moorthy K, Baquer NZ. Effects of sodium-orthovanadate and Trigonella foenum-graecum seeds on hepatic and renal lipogenic enzymes and lipid profile during alloxan diabetes. J Biosci . 2004;29:81-91.
9. Hannan JM, Rokeya B, Faruque O, et al. Effect of soluble dietary fiber fraction of Trigonella foenum graecum on glycemic, insulinemic, lipidemic and platelet aggregation status of Type 2 diabetic model rats. J Ethnopharmacol . 2003;88:73-77.
10. Gupta A, Gupta R, Lal B. Effect of Trigonella foenum graecum (fenugreek) seeds on glycaemic control and insulin resistance in type 2 diabetes mellitus: a double-blind placebo controlled study. J Assoc Physicians India . 2001;49:1057-1061.
11. Thompson Coon JS, Ernst E. Herbs for serum cholesterol reduction: a systematic view. J Fam Prac . 2003;52:468-478.
12. Sowmya P, Rajyalkshmi P. Hypocholeserolemic effects of germinated fenugreek seeds in human subjects. Plant Foods Hum Nutr . 1999;53:359-365.