Tuesday, November 19, 2013

አርቲስት አቦነሽ አድነው፡- ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት ክፍል -፩-

በዲ/ን ኒቆዲሞስ ዕርቅ ይሁን  ~nikodimos.wise7@gmail.com

ከሰሞኑን ለረጅም ዓመታት በዘፋኝነት ምናውቃት ተወዳጇ አርቲስት አቦነሽ አድነው ከዘፋኝነት ዓለም ተፋትቻለሁ ስትል ‹‹ክብሬ ነህ!›› የሚል የመዝሙር አልበም ለክርስቲያኑ ዓለም በማበርከት ወደዘማርያኑ ጎራ ተቀላቅላለች፡፡ ይህን ‹‹ክብሬ ነህ!›› በሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኘውን ፍቅርን፣ ሕይወትንና ተስፋን ያወጀችበትን የአርቲስቷን መዝሙሮች ለማድመጥ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ አርቲስት አቦነሽ ከዚህ በፊት ‹‹በባላገሩ›› አልበሟ ጥልቅ የሆነ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ ታላቅ ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል በማድነቅ ማቀንቀኗን ብዙዎቻችን እናስታውሳለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ እንዲሁም አርቲስቷ በእምነቷ የሃይማኖት ትምህርት፣ መንፈሳዊ የአምልኮ ሥርዓትና ትውፊት እየተደመመች ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሄደሽ ወንጌል ተማሪ›› ይለኛል በማለት ያዜመችው ‹‹ባላገሩ›› የሚለው ተወዳጅ ዜማዋ በአርቲስቷ ልብ ውስጥ ቀድሞውኑ ለዓመታት ሲንቀለቀል የነበረ አንዳንች የመንፈሳዊ ሕይወት ናፍቆትና ቅናአት እንደነበራት ያሳየ ነው ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ይህ የአርቲስቷ የልብ ናፍቆትና መንፈሳዊ ቅናአት ዛሬ ሙሉ በሙሉ ዕውን ሆኖአል እያለች ያለ ይመስላል አርቲስት አቦነሽ አድነው፡፡ ይህ የአቦነሽ ውሳኔና ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪዎቹ ጎራ የመቀላቀል አጋጣሚ ምናልባትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን የቅርብ ታሪክ ብዙም ያልተለመደና እንግዳ ነገር ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ብዙም በአቀንቃኝነቷ የማናውቃት የቀድሞዋ ዘፋኝ ዘማሪት ዘርፌ ከበደ ልትጠቀስ ትችል ይሆናል፡፡
ከዚህ ውጪ ሙሉ በሙሉ ከዘፈን ዓለም ወደ መዝሙር ዓለም ፊታቸውን የመለሱ አቀንቃኞቻችንን እንጥቅስ ቢባል የፕሮቴስታንቱ ዓለም አንጋፋ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን በመማረክ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ይመስለኛል፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በ1970ዎቹ፣ 80ዎቹ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ከነገሡትና እስካሁንም ድረስ ትልቅ ዝና፣ ስምና ተወዳጅነት ካላቸው ድምፃውያን መካከል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ሙሉቀን መለሰና ሒሩት በቀለ የፕሮቴስታንቱን ዓለም የተቀላቀሉ የመቼም ጊዜም ተወዳጅ አርቲስቶቻችን ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ዘመን ታሪክ በእጄ ላይ ባለው መረጃ መሠረት ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ታዋቂና አንጋፋ አርቲስት ወደ ዘማሪነት ጎራ ስትቀላቀል አርቲስት አቦነሽ አድነው የመጀመሪያዋ ትመስለኛለች፡፡ ወደ አርቲስት አቦነሽ ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት ስለተቀላቀለችባቸው የመዝሙሮቿ መልዕክትና አጭር ዳሰሳ ከማለፌ በፊት ግን ዘፈንና ዘፋኝነት አስመልክቶ ያሉትን የተሳሳቱ አመላካከቶችና ትርጓሜዎች ለማጥራት ይመቸን ዘንድ ጥቂት ቁም ነገሮችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
ዘፈንና ዘፋኝነትን በመንፈሳዊው ዓለም እንዴት ይታያሉ
 ዘፈን ወይም ዘፋኝነት እስካሁንም ድረስ በበርካታ ክርስቲያኖች መካከል የመለያየትና የክርክር ርእስ ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድም ዘፈን ወይም ዘፋኝነት እንደ ትልቅ ኃጢአት ተቆጥሮ የተረገመበትንና የተወገዘበትን በርካታ አጋጣሚዎችን ታዝበናል፤ አልፎ አልፎ እንደምናስተውለውም አሁንም ድረስ ውግዘቱና እርግማኑ ያቆመ አይመስልም፡፡ እነዚሁ ዘፈንና ዘፋኝነትን አጥብቀው የሚጠሉና የሚኮንኑ ወገኖች ለዚህ አቋማቸው እንደ መነሻ አድርገው የሚወስዱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን የገላትያ ፭፣፳፩ መልዕክቱን ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹የሥጋ ፍሬም የተገለጸ ነው፣ እነርሱም መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት … አስቀድሜ እንዳልኩ እነዚህን የሚያደርጉ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡›› በዚህ ጥቅስ ላይ በመመርኰዝ ‹‹ዘፈን የተወገዘ ነገር ነው፣ ዘፋኞችም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ዕድል ፈንታ የላቸውም፡፡›› በማለት ብዙዎች ክርስቲያኖች ባሕላዊ ጨዋታና ማንኛውም ለእግዚአብሔር ክብር ከሚቀርብ መዝሙር ውጭ የሆነ ሙዚቃ ሁሉ ኃጢአት ነው የሚል አቋም ሲያራምዱ ይሰማል፡፡
በዚህ ዘፈንና ዘፋኝነትን በተመለከተ በሚነሡ የክርክር ሐሳቦች ላይ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ን አባትና የሥነ መለኮት ምሁር የሆኑት ዶ/ር አባ ዳንኤል ‹‹ዘፈን ኃጢአት ነውን?›› በሚል ርእስ ባስነበቡት አጭር መጣጥፋቸው ያነሷቸውን ሐሳቦች እዚህ ላይ ደግሜ ማንሳት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዘፈንና ዘፋኝነት ሲያወግዝ ስለየትኛው ዓይነት ዘፈንና ዘፋኝነት እያወራ እንዳለ ከመናገራችን በፊት ይላሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል፡- ‹‹ዘፈን በምንልበት ጊዜ በአእምሮአችን የሚመጣው ምንድን ነው? በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚቀርቡት ድምፃውያንና የሚያጅባቸው የተወዛዋዦች ቡድን እንዲሁም የሚያጅባቸው የሙዚቃ መሳሪያ ነውን? ወይስ ወደ ሲኦል የሚወስድ አስፈሪ ኃጢአት ነው? በፊታችን የሚደቀነው … የዚህስ ምክንያቱ ምን ይሆን በማለት ይጠይቃሉ፡፡››
‹‹ሙዚቃ የነፍስ ቋንቋ፣ የፈጣሪ ልዩ ጸጋ፣ የሰው ልጅ ፍቅርን፣ ውበትን፣ ጥበብን የሚገልጽበት ረቂቅ ቋንቋ፣ ጣፋጭ ዜማ ናት …፡፡›› ተብላ የተበየነችውን ሙዚቃን ሐዋርያው ያወገዘበት ትክክለኛ ምክንያቱ ምን ይሆን? በእርግጥስ ቅዱስ ጳውሎስ የተቃወመው ከላይ የገለጽነውን ዓይነት ሙዚቃ ይሆን? እሱን ‹‹ከመግደል፣ ከስካርና ከቅናት፣ ከመናፍቅነትና ከምቀኝነት›› ጋር እንዴት ሊደምረው ይችላል?! ወደ ትክክለኛው ምላሽና ብያኔ ለመድረስ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶችም ሆኑ ሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በመጀመሪያ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ስለሆነ ‹‹ዘፋኝነት›› በሚል ቃል የተተረጐመው የትኛው የግሪክ ቃል መሆኑን በጥንቃቄና በሚገባ መርምሮ ማየት ያስፈልጋል ይላሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ ቋንቋ ‹‹ኮማይ›› ብሎ ያስቀመጠውም ቃል የአማርኛ መጽሐፈ ቅዱስ (የ፲፱፻፶፬ እና የ፲፱፻፸፪ ዓ.ም. ትርጉም) በዘፋኝነት ይተረጉመዋል፡፡ እርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ በሚያወግዘው ድርጊት ውስጥ ዘፈንና ሙዚቃ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ‹‹ኮማይ›› የሚለው ቃል ከላይ በተጠቀሰው ዘፈን የሚፈታ አይደለም፡፡ ‹‹ኮማይ›› ከልቅ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር የሚገናኝ ትርጉም አለው፡፡ ሰዎች ለጣዖት አምልኮ እየበሉና እየጠጡ የሚፈፅሙትን ሕገ ወጥ የዝሙት ኃጢአትን ያመለክታል፡፡ ይህም በሮማውያንና በግሪካውያን ዘንድ ይፈፀም እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ይህንን ከዘፈን ጋር ተያይዞ የሚፈጸመውን ልቅ ርኩሰት የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም›› ያለበትም ምክንያት አሁን መረዳት እንችላለን፡፡›
ለዚህ ተጨማሪ ማረጋገጫ ከፈለግን የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን መመልከት እንችላለን፡፡ እንግሊዝኛው “ኮማይ” የሚለውን ቃል ‹‹Orgy›› ብሎ ይፈታዋል፡፡ በአንጻሩ በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚቀርበው ዘፈን ‹‹Song›› የሚባል ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻም በአዎንታዊ ትርጉሙ በዘፈን ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ውበትን፣ ፍቅርን፣ መልካም ነገሮችን ማድነቅ እንደምንችል እናውቃለን፡፡ ያን ደግሞ እግዚአብሔር የሚቃወመው አይመስለኝም፡፡ ስለ ወንድና ሴት ፍቅር መዝፈን ኃጢአት ከሆነ ‹‹መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን›› የተባለውን መጽሐፍ ምን ልንለው ነው?! እሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ብንተረጉመው በቀጥታም ሆነ በተምሳሌነት የወንድና የሴት ፍቅርን ይገልጻል፡፡
እንግዲህ አስቀድመን ከመፍረዳችን በፊት ምን ዓይነት ዘፈን ብለን መለየት ያስፈልገናል፡፡ ወደ ኃጢአት ይመራል ወይስ ትምህርታዊ መልእክት አለው? ብለን መለየትም ያስፈልጋል፡፡ በ፻፲፰፸፱ ዓ.ም የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ ፭፣፳፩ ላይ ‹‹ዘፋኝነት›› ተብሎ የተተረጐመውን ቃል ‹‹ማሶልሶል›› በሚል ቃል ነው የሚተረጉመው፡፡ ሊፈጠር ከሚችለው የምሥጢር መዛባትና የትርጉም አሻሚነት የሚያድን ቃል ይሆን? ወይስ ‹‹መስከር›› የሚለው ቃል ከሁሉም ይሻል ይሆን፡፡ ምክንያቱም የግሪኩ ቃል ቅጥ ማጣትንና መስከርን ይገልጻልና፡፡ በመሠረቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የግዕዙ አዲስ ኪዳን ገላትያ ምዕራፍ ፭ ላይ ዘፋኝነትን ‹‹ስክረት›› እንጂ ‹‹ዘፈን›› ብሎ አይደለም የሚተረጉመው፡፡
የቃላቱን ትርጉም ለማመዛዘን ይረዳን ዘንድ እስቲ የተለያዩ መዝገበ ቃላት ስለ ዘፈን የሰጡትን ትርጓሜዎች ወይም ፍቺዎች እንመልከት፡፡ ስለ ዘፈን የደስታ ተ/ወልድ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፡- ዘፈነ፡- ‹‹አቀነቀነ፣ አወረደ፣ ግጥም ገጠመ፣ አዜመ፣ አንጐራጐረ፣ ዘለለ፣ ተረገረገ›› በማለት ሲፈታው የአማርኛ የመጽሐፍ ቅድስ መዝገበ ቃላት ደግሞ ዘፈንን እንዲህ ይተረጉመዋል፡-
‹‹በቅኔና በግጥም ከልዩ ልዩ መሣሪያ ጋር እየተቀነባበረ የሚቀርብ የደስታ ምልክት በልደት ቀን (ኢዮብ ፳፩፣፲፩-፲፪፣ ማቴ. ፲፬፣፮) በሠርግ ቀን (ኤር. ፴፩፣፬ ማቴ.፲፩፣፲፯) በድል በዓል ቀን (ዘጸ. ፳፣፳፩፣ ምሳ. ፲፩፣፴፬፣ ፩ሳሙ. ፲፰፣፮) በመንፈሳዊ በዓል ቀን (፪ሳሙ. ፮፣፲፬)፡፡ ከዚህም ሌላ በልዩ ልዩ የደስታ ቀን ይዘፈናል (ሉቃ. ፲፭፣፳፭)፡፡ በእስራኤል የአምልኮት ሥርዓት ዘፈን (ማኅሌት) ትልቅ ቦታ ይይዝ ነበር፡፡ (መዝ. ፻፵፱፣፫/፻፶፣፬)፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባዕድ አምልኮትንና ዝሙትን የሚያስከትል ዘፈን አልተፈቀደም (ዘዳ. ፴፪፣፮-፲፱፣ ማር. ፮፣፳፩-፳፪)፡፡ እዚሁ ላይ ሐዋርያት ዘፈን የማይገባ መሆኑን ተናግረዋል ይላል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ምን ዓይነት ዘፈን እንደተቃወሙ አልገለጹም፡፡ አብዛኛዎቹ ጥቅሶች ተቀባይነት ስላለው ዘፈን እንደገለጹ ግን እናስተውል፡፡
ይህ በዘፈንና በዘፋኝነት ዙሪያ ያለው የትርጉም መዛባት የፈጠረውን መደናገርና የትርጓሜ ስህተት ላይ ይህን ያህል ለማየት ከሞከርን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለን አንድ ታሪክ ብቻ በማንሳት ሐሳቤን ለማጠናከር ልሞክር፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ታሪክ እንደሚነግረን ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ፣ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና ሐዋርያቱ ዘፍንና ባህላዊ ጨዋታዎች ወደሚስተናገድበት የአይሁድ ሠርግ ላይ ለመታደም እንደሄዱ ወንጌላውያኑ ጽፈውልናል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው በአይሁድ ባሕል ውስጥ ተወልዶና አድጎ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚያ ባሕል የተቃወማቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የተቀበላቸውም ነበሩ፡፡ በአይሁድ ሠርግ ላይ ባሕላዊ ውዝዋዜ እንደነበረ ይታወቃል፤ ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን ከሠርግ ጋር ስለሚገናኝ ሙዚቃና ጨዋታ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሠርግ ላይ የተገኘው ኢየሱስ በሠርጉ ላይ የነበረውን ዘፈንና ባህላዊ ጨዋታ ተቃውሟል የሚል ንባብ ግን የለም፡፡
በመሠረቱ ይላሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል ‹‹ዘፈን ኃጢአትን ነውን›› በሚለው ጽሑፋቸው በመሠረቱ፡- ‹‹ባሕል የሰው ልጅን ከእንስሳት የሚለይ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ ማንኛውም ባሕል በክርስቶስ ወንጌል ትምህርት የሚገመገምና የሚፈተን ሲሆን አስፈላጊነቱን ማመን ግን የግድ ይሆናል፡፡ ጌታችንም በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ሲታደም የሠርግ ዘፈን አልነበረም ለማለት አዳጋች ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልን ስናነብ ስለአይሁድ ባሕል ብዙ ነገር እናገኛለን፡፡ ብሉይና አዲስ ኪዳንን ለመረዳትም ይህንኑ የአይሁድ ባሕል ማጥናት ሊጠቅመን ይችላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር እራሱ በአንድ ዘመን በነበረ ባሕል፣ ቋንቋና ሥልጣኔ አማካኝነት መናገሩን አንዘንጋ፡፡›› በማለት ይደመድማሉ ዶ/ር አባ ዳንኤል፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ እንደ የጉራጌኛ፣ የኦሮምኛ፣ የትግርኛ፣ የአማርኛ፣ የወላይትኛ ወዘተ… ባሕላዊ ጨዋታዎችን መመልከትና መሳተፍ ክፋቱ ምንድን ነው፣ የተፈጥሮን ውበትን፣ ታሪክን፣ ፍቅርን፣ ጥበብን፣ ውበትን፣ እውነትን፣ ፍትሕን፣ ነጻነትን፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያወድሱ ዜማዎችን ማቀንቀንም ሆነ ማድመጥ ችግሩ ምኑ ላይ ነው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ በዚያ ዘፈን፣ ባህላዊ ጨዋታዎችና ውዝዋዜ ከአሥርቱ ትእዛዛት የትኛውን እናፈርሳለን? ከየትኛውስ በደል ሊመደብ ይችላል? ከመግደል ወይስ ከመስረቅ በሐሰት ከመመስከር ወይም ከማመንዘር?

ዜማና መዝሙር በኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም ገና ስለ ሙዚቃና የዜማ ምሥጢር ማወቅና መነጋገር ከመጀመሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊትና ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ዜማ ድርሰት፣ ቀመርና ምልክቶች ምን መሆኑን ሳይደርስበት በፊት በታላቁ ሊቅና ማሕሌታይ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት የሰማያዊ ዜማ ባለቤት ለመሆን የበቃች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህን እውነታ በኖርዌይ ትሮንድሄም እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው በ፲፮ኛው ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረንስ ላይ ‹‹The Significance of St. Yared’s Music in the Age of Globalization›› በሚል ርእስ ጥናታዊ ወረቀት ያቀረበው በአሜሪካ ኮሎምቢያ የኦሃዮ ዩኒቨርስቲ ምሁሩ ሊቀ ዲያቆን ክፍሌ አሰፋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዜማ ያለውን ረቂቅነትንና ልዩ ውበቱን ሲገልጽ፡-
‹‹የቅዱስ ያሬድ/የኢትዮጵያ ቤ/ን ዜማ እጅግ ጥንታዊ፣ ጥልቅ፣ ከመንፈስና ከነፍስ በሚመነጭ ፍሰትና ልዩ ጥበብ የተፈጥሮን የለሆሳስ ድምፅና የፍቅርን ልዩና ረቂቅ ዜማ የሚያስቃኝ ሰማያዊና ሕያው መንፈሳዊ ዜማ ነው፡፡›› በተጨማሪም ክፍሌ አሰፋ በዚሁ የጥናት ሥራው ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ጥንታዊ ዜማ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት (ከተፈጥሮ) ጋር በእጅጉ የጠበቀ ምሥጢርና ትስስር እንዳለው የሚከተለውን ሐሳብ ያክላል፡-
‹‹Ethiopian liturgical music is quite unique; those who listen carefully will recognize the haunting sounds of mother nature.›› ይህ ለሺሕ ዓመታት የዘለቀው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ዜማና የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥርዓት ዛሬ ዛሬ እየተበረዘ ነው የሚሉ ታዛቢዎችን በብዛት እያስተናገደ ነው፡፡
በተለይ በዘመናችን ወጣት ዘማሪያን እያወጧቸው ያሉ መዝሙሮች በአብዛኛው ምድራዊ ምኞቶችና ፍላጎቶች ላይ የሙጥኝ ያሉ፣ የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመስቀሉን ውለታና ፍቅር ኃላፊና ጠፊ በኾነ ምድራዊ ሀብትና ክብር የሚያነጻጽርና የሚለካ፣ በአብዛኛው ገበያ ተኮር የሆኑ፣ በእጅጉ ዓለማዊነት ያየለባቸው፣ ለጸሎትና ለተመስጦ እንዲሁም ልዩ ምሥጢር ላለው ሰማያዊና ዘላለማዊ ሕይወት መንፈስንና ነፍስን ወደወዲያኛው ዓለም ለማሻገር አቅም የሚያነሳቸው፣ ደካማና ልፍስፍስ ናቸው … የሚሉ ብርቱ ትችቶችን እያሰተናገዱ ይገኛል፡፡
ለዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ምሁራን ዘንድ ዘማሪዎቻችን ከቅዱስ ያሬድ ዜማ እየወጡ ነው፣ የመዝሙሮቻቸው ግጥሞችም መንፈሳዊ ምሥጢር የማይንጸባረቅባቸው፣ ግልብና የይድረስ የይድረስ እየሆኑ ናቸው የሚለው ትችት የተጋነነና እውነታውን የሳተ ነው የሚሉ አንዳንዶች የራሳቸውን የመከራከሪያ ሐሳብ እንዲህ ሲሉ ያቀርባሉ፡፡ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ዜማ፡- ልዩ፣ ሰማያዊና ረቂቅ ቢሆንም ከእርሱ ወዲያ በተለያዩ ጊዜያት የተነሡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የእርሱን ዜማ አመስጥረውና አራቀው እንደተጠበቡበትና በአዲስ የምስጋና ዜማና ሰማያዊ ቅኔ አምላካቸውን በመላእክት ሥርዓት እንዳመሰገኑት፣ እንዳወደሱትና እንዳመለኩት አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡
ለአብነትም ያህል ይላሉ እነዚሁ ተከራካሪዎች በቤተ ክርስቲያናችን የቅዳሴ ዜማ ታሪክ የደብረ ዓባይ፣ የሰደል ኩላ፣ የአዲስ አበባ ዜማ … ተብለው የሚጠሩ የቅዳሴ ዜማዎች መኖራቸውን እንደ መረጃ በመጥቀስ ከቅዱስ ያሬድ ዜማ ወጥታችኋል የሚለው መከራከሪያ ውኃ የሚያነሳ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት የኾነው የቅዱስ ያሬድ ዜማ በተለያዩ ዘመናት በተነሡ አባቶቻችን መሠረታዊ ይዘቱን ሣይለቅ መሻሻል ተደርጎበታል፡፡ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን የማሕሌት ስርዓት እንኳን እውቁ የ፲፱ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያዊው ምሁር አለቃ ገብረ ሃና ለልጃቸው ለተክሌ በመኖሪያ አካባቢያቸው ያሉ ሸንበቆና ደንገል በንፋስ አማካኝነት የሚያደርጉትን ውዝዋዜ በማየት ያስተማሩት የአቋቋም ሥርዓት ‹‹የተክሌ አቋቋም›› በሚል የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ይላሉ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የጎንደር አቋቋም፣ አስደማሚው የጎጃሙ አጫብርና ቆሜም የማሕሌት ሥርዓት ሌላው የምንኮራበት መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብታት ናቸው፡፡ ስለሆነም ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት ሳናፈነግጥ በቅዱስ ያሬድ ጥልቅና መንፈሳዊ ዜማ እየተመሰጥንና እየተደነቅን ዛሬም ወደፊትም ደግሞም ለዘላለም በአባታችን ቅዱስ ያሬድ መንፈስ አዲስ ዜማ፣ ልዩ የምስጋና ቅኔን ለአምላካችን እናመጣለን፣ እንሠዋለን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
እንደውም ይህ ዘመን ይላሉ እነዚሁ ተከራካሪዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርብ ታሪክ ዘመናት ውስጥ ‹‹የመዝሙር አብዮት›› የተከሰተበት ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነው ሲሉ የእውቁን የቅኔ መምህርና ሰባኪ ወንጌል መጋቢ ሐዲስ መምህር እሸቱ አለማየሁን አገላለጽ በመዋስ ይህ አዲስ ‹‹የዝማሬ አብዮት›› ብዙዎችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናኖች፣ ወጣቶችን እየማረከና አርቲስቶቻችንም ከዘፈን ዓለም ወደ ዘማሪነት ክብር እያፈለሰ ያለ የለውጥ ሂደት ነው ሲሉ በኩራት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ስለሆነም ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተከሰተው ‹‹አዲስ፣ ልዩ የምስጋና፣ የዝማሬ ቅኔ ማዕበል›› እንደ ዘርፌ ከበደ ያሉትንና አሁንም ደግሞ ታዋቂዋን አርቲስት አቦነሽ አድነውን ወደ ዘማርያኑ ጎራ እንዲቀላቀሉ ያስቻለ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሰማያዊ ቅኔ፣ ይህ ልዩ መንፈሳዊ ምስጋና ገና ብዙዎችን ወደ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይጠራል፣ ያፈልሳል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ምናልባት በዚህ የመዝሙሮቻችን ዜማና ግጥሞችና እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየተካሄዱ ላሉ ክርክሮችና ሙግቶች፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉ የዜማ ሊቃውንትና ምሁራን የጠራ አቋምና ግንዛቤ ይኖረን ዘንድ የሚያስችል ሙያዊ የሆነ ትንታኔ ሊሰጡበት ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ ግን የተነሣሁበትን ‹‹አርቲስት አቦነሽ አድነው ከዘፋኝነት ወደ ዘማሪነት›› በሚል ርእስ የጀመርኩትን አዲሱን የአቦነሽ አድነውን መዝሙሮች አጭር ዳሰሳ በዛሬው ጽሑፌ ላካትተው አልቻልኩም፡፡ በቀጣይ ጽሑፌ አርቲስቷ በዝማሬዎቿ ያነሳቻቸውን መንፈሳዊ መልእክቶችና የግጥሞቹን ይዘት በተመለከተ የሚያትተውን መጣጥፌን በቀጣይ ሳምንት እንደምመለስበት ቃል በመግባት ልሰናበት፡፡

ሰናይ ሳምንት!!

Friday, November 15, 2013

እናቶቻችን ጥንታውያን ሃኪሞች ናቸው!!


 
    ወላድ ሴቶች በአብዛኛው ያውቁታል። ያውቁታል ብቻ ሳይሆን አበክረው ይጠቀሙታል። የሚጠቀሙት በቤተ ሙከራ ተመራምረውና ያለውን የንጥረ ነገር ይዘት ስለደረሱበት አይደለም። በልምድና ባገኙት የጥቅም አገልግሎት ነው። አልፎ አልፎ ከሚወጣው የሚተነፍግ ጠረንና መጠነኛ ምረት በስተቀር እህልነቱ እንከን አይወጣለትም። በሁሉም የሀገሪቱ ክልል ይገኛል። ወይና ደጋማ አየር ክልል በደንብ ይስማማዋል። ስሙ በሁሉም ዘንድ እንግዳ አይደለም። እንግዳነቱ የሚጠቀሙት በአብዛኛው እናቶች ብቻ መሆናቸው ነው። ለዚያው ከእንስትም ወላዶች ብቻ!! ይህ የእህል ዘር ማነው? አወቃችሁት? ወይስ ጠረጠራችሁት?

  እንግዲያውስ እኛው እንንገራችሁ። በሀገርኛው ስሙ «አብሽ» ይባላል። በፈረንጆቹ (Fenugreek) ነው። መነሻው ኢራቅ እንደሆነ ታሪክ ይነገራል። ከዚያም ወደዓለሙ ሁሉ ተስፋፋ። ሕንድ ደግሞ ከዓለም ሀገራት የአምራች መሪነቱን ይዛ ትገኛለች። ኢትዮጵያም ለዚህ ዘር ባእድ አይደለችም። ታዲያ ስለአብሽ ምን እንግዳ ነገር ተገኘና ነው ዛሬ ስሙ የተነሳው እንዳትሉ። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለአብሽ ጠቀሜታ በሰፊ ከሚያትት መጽሐፍ ላይ ያገኘነው መረጃ ስለእናቶቻችን ቀዳሚ የምርምር ባለሙያነት እንድናደንቅ አስገደደን። እናቶቻችንን ብቻ አድንቀን ዝም ከምንል አብሽን እናቶቻችን እንዲመርጡ ያደረጋቸውን የንጥረ ነገር ይዞታና ጥቅም ልናካፍላችሁና እናንተም አብሽን እንድትካፈሉ ጥቂት ለመጻፍ ወደድን። «አብሽ» እንዲህ ነው።

አብሽ /Fenugreek/የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው? ከብዙ በጥቂቱ ከታች የተዘረዘሩትን  ይሰጣል።

1/ የጡንቻ፤ የጣት፤ የቅልጥምና የመገጣጠሚያ አካባቢን ህመም ለመቀነስና ለማስታገስ ያገለግላል።
2/ ሊንፍኖድስ/በጉሮሮ፤ በብብትና በሆድ አካባቢ የሚገኝ የመከላከያ አቅምን የሚጠብቅ እጢ ሲሆን አብሽ ይህ ስራውን በተገቢው እንዲወጣ ያደርገዋል።

3/ ቁስልና ጥዝዛዜ ያለው ህመም በመቀነስ ብሎም ቶሎ እንዲድን በማድረግ ያግዛል።
4/  በስኳር ህመም ለሚሰቃዩ ሰዎች የኢንሱሊንን አቅም በማጎልበት፤ የጉሉኮስን ክምችት በመቀነስ ከፍተኛ ጥቅም አለው።

5/ በሆድ አካባቢ የስብ ክምችት እንዳይኖር ይከላከላል። ከመጠነኛ እንቅስቃሴ ጋር ስብ በማቅለጥም እገዛ ያደርጋል።
6/ የምግብ ፍላጎት ለቀነሰባቸው ሰዎች ፍላጎትን በመጨመር ካልተፈለገ ክሳትና የምግብ አለመስማማት ተመሳሳይ ችግሮች ይከላከላል።
7/ለሆድ ሕመም፤ ለጨጓራ አልሰርና ለቃር ከፍተኛ ማስታገሻ ነው።

8/ የልብ አርተሪ ስራውን በአግባቡ እንዲያካሂድ ያግዛል።ለደም ቅዳና ደም መልስ ዝውውር፤ ለኮሌስትሮል መጠን መስተካከል፤ለኩላሊትና በቫይታሚን እጥረት ለሚከሰት የቤሪቤሪ በሽታ ከፍተኛ የፈውስ ድጋፍ አለው።

9/ ለአፍ ቁስለት፤ ለንፋስ ተገንጣይ ቧንቧ ህመም፤ ለሳምባ፤ ለደረቅ ሳልና ትክትክ ፍቱን መድኃኒት ነው።
10/ ለቆዳ፤ ለራሰ በራነትና ለጸጉር መመናመን፤ ለካንሰር፤ ለጉበት ህመም መከላከል ጠቃሚ ንጥረ ነገር ይዟል።

11/ ለስንፈተ ወሲብና አቅም ማጣት፤ ለሴቶች የጡት ግት መጨመርና የወተት አወራረድ መጨመር ከፍተኛ ድርሻ አለው,።
12/ የአፍ፤ የጉሮሮና የውስጥ እርጥበትን በመቆጣጠር ያልተፈለገ ቆሻሻን በማስወገድ፤ እንደየመኪና ሞተር ግራሶ ለሰውነታችን የሚያገለግለውን ዝልግልግ ፈሳሽ /mucus/ በመቆጣጠርና በማስተካከል መጥፎ የአፍ ጠረን፤ ከሆድ የሚወጣ ትኩሳትና ሽታ፤ በመከላከል ከመጠን በላይ የተበላሸና የለገገ አክታ እንዳይኖረን በማድረግ በኩል አብሽን የሚወዳደረው የለም።

አብሽ ለምን ይህንን ሁሉ አቅም ለመያዝ ቻለ? የዘመኑ ሳይንስ እንዲህ ይላል።

አብሽ ስኳር የለሽ /Polysacchirides/ ንጥረ ነገር አለው። ይህ በራሱ  ክር መሳይ /Fiber/ ሟሚ ንጥረ ነገር ከፍተኛ ተሸካሚ አድርጎታል። saponons, hemicelluloses,macilege, tannin, pectin የተባሉ ለደም ዑደትና ለዘይት መጠን ልኬታ ጠቃሚ ንጥረ ነገርን በመያዙ ከአዝርዕት መካከል እጅግ ተመራጭ ያደርገዋል። ኢንሱሊንን በማምረት ረገድ አሚኖ አሲድ 4 ሀይድሮክሲአይዞሉሲን ይዟል። የፋይቶኬሚካል ክፍል የሆኑትን ንጥረ ነገሮች ማለትም  ኮሊን፤ ትራይጎኔሊን ዳዮስጄኒን፤  ያሞጄኒን፤ ጂቶጄኒን፤ ቲጎጄኒን የተባሉትን ንጥረ ነገሮችን/substance/አጣምሮ የያዘ ነው።
በሚኒራሎችም ረገድ አብሽ የያዛቸው ነገሮች  መዳብ፤ ፖታሺየም፤ ካልሲየም፤ ብረት፤ ሴሌኒየም፤ ዚንክ፤ ማንጋኒዝ፤ ማግኒዢየም፤ በመሳሰሉት በጣም ያዳበረ ነው።
በቫይታሚን ረገድም የተዋጣለት ነው። ታያሚን፤ ቫይታሚን ቢ 6፤ ፍሎሪክ አሲድ፤ ሪቦፍላቪን፤ ናያሲን፤ ቫይታሚን ኤ፤ ቫይታሚን ሲ፤ ቤታ ካሮቲን፤ ፎሌት/DFE/ የመሳሰሉት ይገኙበታል። በአሚኖ አሲድ ንጥረ ክፍሎች በጣም የዳበረ ሲሆን  ከካርቦ ሃይድሬት ምንጮች ውስጥም ሟሚ ከሆነው ጭረት/ ፋይበር /በስተቀር ከስታርች፤ ስኳር፤ ሱክሮስ፤ ግሉኮስ፤ ፍሩክቶስ፤ ላክቶስ፤ ማልቶስና ጋላክቶስ ፍጹም ነጻ መሆኑ ከሁሉም ተመራጭ ያደርገዋል። ፋቲ አሲድና ስብነት ካላቸው ውሁዶችና ንጥረ ነገሮች ነጻ ነው።
 
ከምዕራባውያኑ ጸሐፊያን  ጊዮርጊስ ፔትሮፓውሎስ ስለአብሽ ጥቅም በሰፊው አትቷል። ሕንዳዊው ዶ/ር ኩማር ፓቲ በ328 ገጽ  ባሰፈረውና ስለእጽዋት መድኃኒትነት በዘረዘረበት መጽሐፉ ላይ ስለአብሽ ጥቅምና ቅመማው  በደንብ ዘርዝሯል።
አብሽ በዱቄት መልክ፤ አንጥሮ ዘይት በማውጣት፤ በበቆልት፤ በፈሳሽ መልክ አዘጋጅቶ ለሻይ፤ ከሌላ ምግብ ጋር ቀላቅሎ በማዘጋጀት፤ መጠቀም ይቻላል። አወሳሰዱን በተመለከተ የቅርብ ሐኪምን ማማከር ይገባል።
በአሉታዊ ጎኑ ሲታይ ደግሞ በእርግዝና ላይ ያለች ሴት አብሽን አብዝታ እንድትጠቀም አይመከርም።
የአብሽን ጥቅም አውቀው በአገልግሎቱ የቆዩት እናቶቻችን ሳይማሩ የተማሩ አይደሉምን?
ለተጨማሪ መረጃ ቢመለከቱ ይጠቀማሉ።
1. Adamska M, Lutomski J. C-flavonoid glycosides in the seeds of Trigonella foenum graecum [in German]. Planta Med . 1971;20:224-229.
2. Gupta RK, Jain DC, Thakur RS. Minor steroidal sapogenins from fenugreek seeds, Trigonella foenum-graecum . J Nat Prod . 1986;49:1153.
3. Karawya MS, Wassel GM, Baghdadi HH, Ammar NM. Mucilagenous contents of certain Egyptian plants. Planta Med . 1980;38:73-78.
4. Valette G, Sauvaire Y, Baccou JC, Ribes G. Hypocholesterolaemic effect of fenugreek seeds in dogs. Atherosclerosis . 1984;50:105-111.
5. Singhal PC, Gupta RK, Joshi LD. Hypocholesterolemic effect of Trigonella foenum-graecum (METHI). Curr Sci . 1982:51:136.
6. Stark A, Madar Z. The effect of an ethanol extract derived from fenugreek ( Trigonella foenum traecum ) on bile acid absorption and cholesterol levels in rats. Br J Nutr . 1993:69:277-287.
7. Sauvaire Y, Ribes G, Baccou JC, Loubatieeres-Mariani MM. Implication of steroid saponins and sapogenins in the hypocholesterolemic effect of fenugreek. Lipids . 1991;26:191-197.
8. Yadav UC, Moorthy K, Baquer NZ. Effects of sodium-orthovanadate and Trigonella foenum-graecum seeds on hepatic and renal lipogenic enzymes and lipid profile during alloxan diabetes. J Biosci . 2004;29:81-91.
9. Hannan JM, Rokeya B, Faruque O, et al. Effect of soluble dietary fiber fraction of Trigonella foenum graecum on glycemic, insulinemic, lipidemic and platelet aggregation status of Type 2 diabetic model rats. J Ethnopharmacol . 2003;88:73-77.
10. Gupta A, Gupta R, Lal B. Effect of Trigonella foenum graecum (fenugreek) seeds on glycaemic control and insulin resistance in type 2 diabetes mellitus: a double-blind placebo controlled study. J Assoc Physicians India . 2001;49:1057-1061.
11. Thompson Coon JS, Ernst E. Herbs for serum cholesterol reduction: a systematic view. J Fam Prac . 2003;52:468-478.
12. Sowmya P, Rajyalkshmi P. Hypocholeserolemic effects of germinated fenugreek seeds in human subjects. Plant Foods Hum Nutr . 1999;53:359-365.

 

Saturday, November 9, 2013

«እነ ጀማነሽ ድብደባ እየተፈፀመብን ነው አሉ!»


(አዲስ አድማስ ጋዜጣ)ፕ/ር ይስማውና ሌሎች አባላት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

“የማኅበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ማኅበር አባላት፤ በተናጠል እና በጋራ በምናራምደው እምነት ምክንያት ሕገመንግስቱ የሰጠን መብት ተጥሶ ድብደባ፣ ወከባና እንግልት እየተፈፀመብን ነው፤በአባላቶቻችን ላይም ክስ እየተመሠረተ ነው ሲሉ አማረሩ፡፡ አርቲስት ጀማነሽ ሠለሞን አባል የሆነችበት ማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ “ኤልያስ መጥቷል፣ ሰንበት ቅዳሜ ነው፣ አርማችን ቀስተደመና ነው” የሚሉና መሠል ሃይማኖታዊ ሃሳቦችን የሚያራምድ ሲሆን አባላቱ ሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሰዎች ለማስተማር ሲሞክሩ ለሕይወታቸው አስጊ የሆኑ ጥቃቶች እየተፈፀሙባቸው እንደሆነና በአቃቤ ህግ ክስ እንደቀረበባቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ 65 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አሌልቱ ከተማ አቡነ ተክለሃይማኖት ፅላልሽ ገዳም አጥቢያ ነዋሪና የገዳሙ አገልጋይ እንደሆኑ የገለፁት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጀማነህ፤ የማኅበረ ሥላሴ አባልና አገልጋይ በመሆናቸው ብቻ በቤተሰቦቻቸው ላይ ውክቢያ፣ እንግልትና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተናግረዋል፡፡
ግለሰቧ እንደሚሉት መስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም የገዳሙ የሃይማኖት አባቶች፤ ቤተሰቦቻቸውን ሰብስበው “ልጃችሁ ሃይማኖታችንን እያጠፋች ነው” በሚል እንዳነጋገሯቸውና ከዚህ ድርጊት እንድትታቀብ አድርጉ የሚል ማሳሰቢያ እንደተሰጠ ገልፀዋል፡፡ የማህበረ ስላሴ አባላትን ወደ ገዳሙ ለበረከት ሐምሌ 30ቀን 2005 መጋበዛቸውን የሚገልፁት ወ/ሮ ቀለመወርቅ፤ ይህን በመፈፀማቸው “ሃይማኖታችንን የሚያጠፋ ተግባር ፈጽመሻል” ማለት፣ እንደበድብሻለን የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው አስታውሰው፤ ጥቅምት 17 ቀን 2006 ዓ.ም ዛቻው በቤተሰባቸው አባላት ላይ እንደተፈፀመ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በወላጅ እናታቸው ቤት በተዘጋጀ የመታሰቢያ ዝክር ላይ ተከፍለው ወደመጡበት ሲመለሱ መንገድ ላይ ድብደባ የተፈፀመባቸው የቤተሰባቸው አባላት፤ በአካባቢው ማኅበረሰብ እርዳታ እና በፖሊስ ትብብር ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ክስ ማቅረባቸውንና ጉዳዩም በህግ እየታየ መሆኑን ወ/ሮ ቀለመወርቅ ገልፀዋል፡፡ ከድብደባው ጋር በተያያዘም በድርጊቱ ተሣትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ የሃይማኖት አባቶችም ታስረው መለቀቃቸውን እኚሁ ቅሬታ አቅራቢ አክለው ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የገዳሙን የስራ ሃላፊዎች በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም ጉዳዩን የያዙት የወረዳው ፖሊስ ባልደረባ አቶ ገዙ ወርቁ፤ የተፈፀመው ድርጊት ገና በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ የማህበሩ አመራር አባላት ለዝግጅት ክፍላችን ባቀረቡዋቸው የክስ ዝርዝር ሰነዶች እንደተመለከተው፤ ከማህበሩ አመራሮች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ይስማቸው አለሙን ጨምሮ በባህርዳር እና በደብረ ብርሃን የሚገኙ አባላቶች አስተምህሮውን በመስበካቸው የወንጀል አንቀጽ ተጠቅሶባቸው ክስ እንደተመሠረተባቸው ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት ፕ/ር ይስማው ላይ የተመሠረተባቸው ክስ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሹ በ28/07/2005 ዓ.ም ከሌሊቱ 10.00 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ክልል፤ ልዩ ቦታው ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የቅዳሴ ስነ ሥርዓት እየተካሄደ እያለ ወደ ቤተመቅደስ በመግባት “ኤልያስ መጥቷል የተዋህዶን ነገር በደንብ መናገር አለብኝ፤ እናንተ በከንቱ ነው የምትደክሙት፤ ኦርቶዶክስ ትክክለኛ ሃይማኖት አይደለም፤ በውስጡ ቅባትና ዘጠኝ መለኮት የሚገለጽበት ነው፡፡
እውነተኛ እና ትክክለኛ ሃይማኖት ተዋሕዶ ብቻ ነው፤ ይሄንን እውነታ ለሕብረተሰቡ አስተምራለሁ እሰብካለሁ” በማለት ሃይማኖታዊ ስነሥርዓቱ እንዲታወክ እና ረብሻ እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ፤ በፈፀመው ሃይማኖታዊ ሠላምና ስሜት መንካት ወንጀል ተከሷል ይላል፡፡ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጽ/ቤት በአቃቤ ህግ ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ጌጤ ሣህሉ ንጋት የተባሉ የማኅበሩ አባል በቤተክርስቲያን ላይ የንግግር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በደብረ ብርሃን ለባሶና ወራና ወረዳ ፍ/ቤትም አቶ አበበ ነጋሽ የተባሉ ግለሰብ፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን በማሽሟጠጥና በማራከስ እንዲሁም የተለያዩ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ፈፀሙ በተባሉት ሃይማኖታዊ ሠላምና ስሜት መንካት ወንጀል መከሰሳቸው ታውቋል፡፡